Friday, October 16, 2015

ከዞን ዘጠኝ የተሰጠ መግለጫ

በዛሬው ዕለት የልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ፩ኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ፪ተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ሃይሉ ፫ተኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ ፭ተኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃኔ እና ፯ተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ ተጠርጥረው ከነበረበት የሽብርተኝነትና የኅብረተሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ የመጣል ክስ ነጻ መውጣታቸውን በበጎ መልኩ የምንቀበለው ቢሆንም 
  1. ፪ተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ሃይሉ በሃይል ተገዶ ማዕከላዊ ምርመራ ውስጥ በማሰቃየት ስር የሰጠው ቃል ተቆጥሮ አመጽን በማነሳሳት ወንጀል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 257 መሰረት አንዲከላከል መባሉን አጥብቀን እንቃወማለን ፡፡ 
  2. ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ከአንድ አመት ከአምስት ወር በላይ በእስር የቆዬት የዞን9 ጦማርያን የመፈቻ ወረቀት ከችሎቱ መጠናቀቅ በኋላ በአስቸኳይ በፍርድ ቤቱ አማካኝነት ተጽፎ ለማረሚያ ቤቱ ተወካይ ቢሰጥም ማረሚያ ቤቱ እስከ አርብ የስራ ሰዓት መጠናቀቂያ ድረስ መፈቻው አልደረሰኝም በሚል ሰበብ ሶስቱን ጦማርያን በእስር ማቆየቱን አስጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ 
ይህ ተግባር ከዚህ በፊት እንደታየው ሁሉ አቃቤ ህግ ለይግባኝ ጊዜ አንዲገዛ ከማረሚያ ቤቱ የሚደረግለት የጓሮ ትብብር አንዳይሆን እጅግ ከፍተኛ ስጋት አለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለመደው የፍርድ ቤቶችን ስልጣን ዝቅ አድጎ የማየት እና የማረሚያ ቤቶች የእጅ አዙር ፍርድ ሰጪነት ማሳያም ነው ፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት አንደታየው በአደባባይ በሕግ አግባብ የተሰጠን ነጻነት በጓሮ ከሕግ ውጪ ሊነጠቅ የሚችልበት ከፍተኛ ስጋት አሁንም የዞን9 ጦማርያን ፊት ተጋርጧል ፡፡
539 ቀናት ያለአግባብ እስር መቆየታችን ሳያንስ በራሱ መቆም የማይችል እና ምንም ማስረጃ ያልቀረበበትን ክስ አቃቤ ሕግ በጓሮ ከማረሚያ ቤት ጋር በመመሳጠር የመንፈግ ሌላ ተጨማሪ ግፍ አንዳይሰራብን አጥብቀን እንጠይቃለን ፡፡

ስለሚያገባን አንጦምራን!
ዞን9

No comments:

Post a Comment