Tuesday, October 6, 2015

ናት

‘The First 100 Days’ለተፈቺም ይሆናል እንዴ ናት? ‹የመጀመሪያዎቹ መቶ የፍቺ ቀናት› ብዬ ብፅፍስ? ብዬ ራሴን እጠይቅና፤ 400 ቀናት ብቻ ታስሮ ሰለ100ቀናት መፃፍ ጉራ መስሎ ሲታየኝ ጊዜ እተወዋለሁ፡፡ ዛሬ ግን ያንተ ልደት ነውና እስኪ የአጭር አጭር ማስታወሻ ልፃፍ ብየ መጣሁ፡፡
ናት! ዛሬ ከታሰርክ 529ኛ ቀንህ ነው፡፡ ይሄን የምነግርህ እዛ እስር ቤት ቀኑን እንደማትቆጥር ስለማውቅ ነው፡፡ የታሰሩበትን ቀን መቁጠር ለእስረኛ ‹እስሩን ያከብድበታልና› ቀን አይቆጠርም አይደል? እኔ ግን ይሄው ‹የሆደ ሰፊነቱ› ተጠቃሚ በመሆን የታሰሩበትን ቀን ከማይቆጥሩት እስረኞች ተርታ ወጥቼ‹ከነፃዎቹ› ቀን ቆጣሪዎች ተርታ ተሰልፌያለሁ፡፡ ለኔ ‹ሆደ ሰፊ› (magnanimous) የሆነ አሳሪ-ፈቺ አንተና ሌሎች ጓደኞች ላይ ይሄ ‹ሆደ ሰፊነት› አልታይ ማለቱ እንዲሁ ሁሌ ያስገርመኛል፡፡
ናት! ‹ሆደ ሰፊው› እየተጫወተ ያለው ጨዋታ ‹አይጥ ነሽ? እዩት ክንፌን፤ ወፍ ነሽ? እዩት ጥርሴን› አይነት ሁኖ ሲያስቀኝ ይውላል፡፡ ‹‹ያለወንጀላቸው ነው ያሰርካቸው ፍታቸው? እሱ በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ነው፤ ግማሾቹን ፈተህ ግማሾቹስ? እሱ የመንግስት ልዕልናና ሆደ ሰፊነት ነው›› እያለ የማይበርበትን የዶሮ ክንፉን ያራግባል፣ የማያኝክበትን denture ጥርሱን ያገጣል፡፡ የዚህ ጨዋታና ሕመም ዋነኛ ተጠቂ መሆንህ ሁሌም ያንገበግበኛል፡፡ ግን ምን ይደረግ?
ናት! እነዚህን ሁሉ ቀናት ለምን በእስር እንዳሳለፍክና እያሳለፍክ እንደሆነ ለመግለፅ እንኳን እኔ አሳሪህ እንኳን የሚችል አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ከሰውየው ወስደን፤‹ወጣትነት ጥሩ ነው፡ ቢገሉህም አትሞትላቸውም፣ ቢያስሩህም ሕሊናህን ነፃ ታወጣዋለህ› እንላቸዋለን እንጅ አንሞትም! አንታሰርም!
ናት! ቅንነት ዋጋ እንደሚያስከፍል ካንተ በላይ ምን ምሳሌ ይኖራል? እጆችህ መንቀሳቀስ እስኪያቅታቸው ድረስ ከፍ አድርገህ በቅጣት ውስጥ ‹ምርመራ› ላይ የቆየህባቸው የማዕከላዊ ሌሊቶች ስለቅንነት ምንም የማያውቁ ግዑዛን ነበሩ ለካ?! እነዛ ‹Made in England› የተፃፈባቸውን እጀ ሙቆች ቅንነትህ እንዴት እንዳልበጠሳቸው ይገርመኛል፡፡ እነዛን ማጎሪያዎች ከብበው የቆሙት የእስር ቤቱ አጥሮች ስለቅንነትህ ሲባል አለመፍረሳቸው፤‹ለካ ቅንነት አቅመ ቢስ ነው› ያስብሉኛል፡፡ ቅንነትህ ‹የሆደ ሰፊውን› ልብ አለማራራቱ ‹ይሄ ሆደ ሰፊነት እንዴት ነው?› ያስብለኛል፡፡ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር ቅንነትህ ከተቀመጥክበት ዛሬም እያስነሳ በዝምታ ያስቆምሃል፤ ቅንነትህን የሚያይ የሚሰማ የለም አንጅ፡፡
ናት! ሁሌም ተይዘህ በታሰርክበትቢሮ በር ሳልፍ ‹እዚህ በጣም ቅንና ደግ ወንድም ነበር› እላለሁ፡፡ እንዳንተ ያለ ሰራተኛን ከስራው፣ ነጋዴን ከንግዱ፣ አሳ አስጋሪን ከባህሩ… አንስቶ እስር ቤት የሚጥል ጊዜ ነውና ለጊዜው ከሀዘን በላይ ምን እንላለን? ተስፋ ግን ሁሌም የኛው ነች፡፡
ናት! ያንተን ግጥም ጠቅሼ ልሰናበትህ፡፡አዎ! ያችን በ17 ዓመትህ ፅፈሃት ቤትህ ሲፈተሸ የልጅነት ደብተርህ ውስጥ የተገኝችውን አሁን አንተ ላይ በዋነኛ የሰነድ ማስረጃነትየቀረበችውን በከሳሽ አገላለፅ ‹አንድ ገፅ የሽብር ሰነድ› እኮ ነው የምልህ፡፡ እንዲያውም ይሄው ልጥቀስልህ፡

‹ኢትዮጵያ እንድታድግ፣ ረሃብ እንዲጠፋ፤
መንግስት ያስፈልጋል፤ ላገሩ ‘ሚለፋ፡፡›
መቼም ዛሬ 28ኛ ዓመትህን ስታከብርከአስራ አንድ ዓመት በፊት የፃፍካትን ግጥም መጥቀሴ ነውር የለውም አይደል፡፡ እንዲያው ዘንድሮ ‹7.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ተርበዋል›ብሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መግለጫ ማውጣቱን ለመግለፅ ያክል ነው፡፡ ‹…ብንናገር እናልቃለን› ሁኖብኝ ነው ዳር ዳሩን መዞሬ፡፡
ናት! ሁሌም በተስፋ መልካም ዜናንእናፍቃለሁ፡፡

መልካም ልደት ወንድሜ!

በኋላ በባቡር መጥቼ የምጠይቅህወንድምህ - ዘላለም
Natnael Feleke

2 comments: