Friday, May 2, 2014

We are alive we will survive this and we will keep being alive. ‪#‎FreeZone9blogger‬ ‪#‎FreeEdom‬ ‪#‎FreeTesfalem‬ ‪#‎FreeAsemamw‬ ‪#‎StopKillingOrmoStudents‬ ‪#‎OromoProtest‬ ‪#‎Ethiopia‬

እነደሁልጊዜው ሁሉ ህገ መንግስታዊ መብቶቻችን መጠየቅ እንቀጥላለን በማሰርና በመደብደብና በመግደል የአገር ችግር አይፈታም
ክቡራን የዞን ዘጠኝ ነዋሪያን
ሳምንቱ በአራማጅነት ቆይታችን ከነበሩን ጊዜያት መካከል በጣም ከባድ ሆኖ አለፈ። የዞን ዘጠኝ አባላትና ወዳጅ ጋዜጠኛ ጓደኞቻችን ከታሰሩ 7 ቀናትን አሳለፋ፡፡ በሳምንቱ ውስጥ ቤተሰብና የህግ ባለሞያ ሳያገኛቸው እሁድ ቀን ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ከመስማት ውጪ አያያዛቸውንም ሆነ ያሉበትን የጤንነት ሁኔታ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ እስካሁንም ቤተሰብም ሆነ የህግ ባለሞያ እነዲያያቸው አልተፈቀደም፡፡ ይህ በግልጽ ህገ መንግስቱን የሚጥስ የምርመራ ሂደት በማእከላዊ ሲካሄድ አዲስ አይደለም፡፡ ከዚህ በፌት የነበሩ የፓለቲካ እስረኞችም በተመሳሳይ ሁኔታ የመታየት መብታቸው ከማእከላዊ ጀምሮ ተነፍጎ አሁንም ቤተብሰብም ሆነ ወዳጅ እነዳይጎበኛቸው የተደረጉ እንዳሉ ይታወቃል ፡። ዞን 9 ከመጀመሪያ ዘመቻዎች አንስቶም ህገመንገስቱ አንዲከበረ ስንጠይቅ መቆየታችን ይታወቃል፡። ይህ መሆኑ ሳያንስ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብታቸውን ሲጠቀሙ የነበሩ (ሶስተኛው የዞን ዘጠኝ ዘመቻ) የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች እስር የአካል ጉዳትና ሞት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡ይህ በመላው አገሪትዋ እየታየ ያለውን ተቃውሞ መንግስት ምላሽ እየሰጠ ያለበት መንገድ አሳሳቢ አስፈሪና አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ ሳምንቱንም በሰብአዊ መብቶች ረገድ በጣም የከፋ ያደርገዋል፡፡
መንግስት የዞንዘጠኝ አባላትንና ጋዜጠኞቸን ሰርተዋል ብሎ ያቀረበው ወንጀል በማህበረሰብ ሚዲያ በመጠቀም ህዝብን ለብጥብጥ ማነሳሳት ነው ሲል የመንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው በጻፉት ሳይሆን በወንጀል በመሰማራታቸው ነው የታሰሩት ብለዋል፡፡ ወንጀሉ ፓሊስ እንዳቀረበው ደግሞ በማህበረሰብ ሚዲያ ብጥብጥን የማንሳት ተግባር ከአገር ውጨ ከሚገኝ ራሱን ከሰብአዊ መብት ብሎ ከሚጠራ ተቋም ጋር ተባብረው ብጥብጥ ማስነሳት ነው ብሎታል ፡፡ ክሱ በአጭሩ ሁለት ነገሮችን ይይዛል፡፡ አንደኛው በማህበረሰብ ሚዲያ ብጥብጥ ማስነሳት ሲሆን ሁለተኛው በሃሳብና በገንዘብ ከውጪ ድርጅቶች ጋር መተባበር ነው ፡፡
ማህበረሰብ ሚዲያ ብጥብጥ?
በማህበረሰብ ሚዲያ ብጥብጥ ማንሳት የሚል ክስ ለማቅረብ በማህበረሰብ ሚዲያ ብጥብጥ የሚያስበሱ መልእክቶቸን ማስተላለፍ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ማንኛውም የዞን 9 ነዋሪያን እነደሚመሰክሩት ህገ መንግስታዊ መብቶች እነዲከበሩ ከመጠየቅና መንግስትን የሚተቹ ጽሁፎችን ከማቅረብ ባለፈ አንድም የዞኑ ስራ ለብጥብጥ እና ለሁከት ምክንያት ለመሆን የሚበቃም አይደለም፡፡ ይህንነ ለመረዳት የዞኑን ዘመቻዋች እና ጽሁፎች ማየት ብቻውን የክሱን አስቂኝነት ለማስረዳት ይበቃል፡፡ እስከዛሬ በጻፍናቸው የመንገስት ትችቶች ካልሆነ በስተቀር ባነሳሳናቸው ብጥብጦች አንታወቅም ፡፡ ለዚያም ነው በጽሁፋቸው አይደለም የታሰሩት የሚለውን የመንግሰት ማስተባበያ አስቂኝ የሚያደርገው ፡። በጽሁፍ ካልሆነ በምንድነው የዞን 9 አባላትን እንድ ላይ እንደቡድነ ሰብስቦ መክሰስ የሚቻለው??
ከውጨ ድርጅት ጋር መተባበር 
ዞን 9 ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሁለት አመታት በነበረው ቆይታ የተለያዩ አጋርነቶችነ ከተለያዩ አካላት ጋር ፈጥሮአል፡። በዚህም በተለያየ ጊዜ እነደግለሰብም አንደቡድን ተወካይ በመሆን አባላቱ አገሪትዋ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብጥ ጥሰት አያያዝ አስመልክቶ ለተለያዩ ቦታዎች ንግግር አድርገዋል፡፡ ኢንተርኔት ለነጻነትና ለዴሞክራሲ የሚያደርጋቸውን አስተዋእጾም አስመልክቶ በቡድንም በነጠላም በተለያዩ ቦታቸዎች ላይ በመገኘት ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ይህ መንግስት ሲፈልግ የሚፈቅድላቸው ሲፈልግ ወንጀል የሚያስመስለው ተግባር ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጲያዊ ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ ዜጎች በመጓዛቸው ስራቸውን እና ልምዳቸውን በማካፈላቸው እነዲሁም ራሳቸውን ብቁ በማድረግ የሚሰሩትን የሰብአዊ መብት እነቅስቃሴ ለሌሎች መናገራቸውን ወንጀል ለማስመሰል የሚደረገውን ጥረት አሁንም ቢሆን እንደዞን 9 አጥብቀን እናወግዛለን፡፡ ከዚህ በፌትም እነደተናገርነው በህግ እስካልተከለከለ ድረስ ህጋዊ እንቅስቃሴዎቸን መንግስት ስላልወደዳቸውና ህገ ወጥ ስላስመሰላቸው የምናቆምበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሁሉም የዞን ዘጠኝ አባላትና ወዳጆች በፓርላማ በህገ ወጥነት ከተፈረጁ ተቋማት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበራቸውም የላቸውምም፡። ለዞን ዘጠኝ ስራም ምንም አይነት የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተን አናውቅም፡፡ (በመሰረቱ የፋይናንስ ድጋፍ የማያስፈልገው የበጎ ፍቃደኝነት ስራ ነው የምንሰራው ) ከዚያ ውጪ ግን በፓርላማ ህገ ወጥ እስካልተባሉ ወይም ከልካይ ህግ እስካልመጣ ድረስ ከተለያዩ በተባበሩት መንግስታት እውቅና ካላቸው የመብት ተሟጋች ተቋማት ጋር ያለንን ግንኙነት ወንጀል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት አንቀበለውም፡።
አንዳንድ አስቂኝ የመንግስት ወዳጆች በህቡህ ተደራጅተው የሚል ክስም ሲለጥፉብን ሰምተናል፡፡ ህቡህ ማለት ምን ማለት እነደሆነ ትርጉሙን እንዲያጣሩ ከመጠየቅ ባለፈ ምንም የምንጨምረው ነገር የለንም ፡፡ ባለፉት ሁላት አመታት ቆይታችን ፎቶአችን የሚታይ ሙሉ ህጋዊ ስማችን የሚታወቅ አገር ውስጥ የምንኖር ኢንተርኔት ላይ የተናገርነውን በግንባር የምንደግም ህጋዊ ዜጎች ነን፡። ከዞን ዘጠኝ እሴቶች መካከልም አንዱ ለተናገሩትም ሆነ ለሚያስተላልፉት መልእክት ሙሉ ሃላፌነትን መውሰድም ጭምር ነው ፡፡ በመሰረቱ ኢንተርኔት ላይ ቡድን መመስረት በየትኛውም ህግ የማይከለከል ህጋዊ ተግባር መሆኑን ለመንግስትና የመንግሰት እርምጃ ለደገፉ ለማስታወስ አንወዳለን፡፡
ባለፉት ቀናት ስንናገር እንደነበረው መንግሰት የዞን ዘጠኝ አባላትና ወዳጆችን እነዲፈቱ መጠየቁን አሁን ደግሞ በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በመቃወም በጋራ ድምጻችንን ማሰማታችንን እንቀጥላለን፡፡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እየተደበደቡና እየሞቱ የዞን9 አባላትን እስር ብቻ ለይተን ዘመቻ ማድረጉን ሃላፌነት የሚሰማው ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በመሆኑም ሁለቱ ጉዳዪች ላይ አተኩረን የሚመለከተው አካል ሃላፌነቱን እነዲወጣ ግፌት ለማድረግ እንሞክራለን፡። ዞን ዘጠኝ እንቅስቃሴን በማሰር ለመገደብ ቢሞክርም ብዙ የዞኑ ነዋሪያን ጋር በመተባበር ከምርጫ ጋር የተያያዙ ስራዎችን የመስራት እቅዳችነን አጠናክረን እንቀጥልበታለን፡።
ከነገ ሚያዝያ 25 ጀምሮ የዞን 9 ጦማርያንን እና ወዳጅ ጋዜጠኞችን መፈታት እነዲሁም በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የምን ቃወምበት መጠነ ሰፌ ዘመቻ እንጀምራለን፡፡ እስካሁን በተናጠል ላሳያችሁን ህብረት በከፍተኛ ሁኔታ እያመሰገንን በጋራ የአገራችንን “ዞን ዘጠኝተነት” በመቃወም ህብረታቸንን እናሳይ ፡።
የዘመቻውን ዝርዝር በሚቀጥሉት ፓስቶች የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment