Friday, May 16, 2014

አንቀጽ 19 በተግባር ተጥሷል - ሕገ መንግስቱን ሳያከብሩ ማስከበር አይቻልም የታሳሪዎች የምርመራ ሂደትን አስመልክቶ ከዞን 9 የተሰጠ መግለጫ



ከታሰሩ 22 ቀናትን ስቆጠሩት የዞን ዘጠኝ አባላትና ጋዜጠኞች በቤተሰብም ሆነ በሕግ ባለሞያ የመገናኘት መብታቸውን ለማግኘት 19 ቀናት ፈጅቶባቸዋል፡፡ ከታሰሩ እስከ 17 ቀን ድረስ ማንም የቤተሰብ አባል ሳይጎበኛቸውና በወዳጅ ዘመዶች ሳይጠየቁ የከረሙ ሲሆን ከጠበቆች ጋር ለመገናኘት ደግሞ 19 ቀናት ፈጅቷል፡፡ አሁንም ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት ያልቻሉ ቀሪ እስረኞች አሉ፡። 
በተለምዶው እነደሚደረገው የፓሊስ ማእከላዊ ምርመራ የቤተሰብ ጉብኝትን አይቻልም በሚል ቀላል ቃል የከለከለ ሲሆን ለጠበቆች ስብሰባ ላይ ነን የሚል ምክንያት ሲሰጥ ከርሟል፡፡ ይህ በመሆኑም የተነሳ የተያዙ ሰዎች መብት የሆነው የህገ መንግስቱ አንቀጽ 19 ሁለት ላይ ያለው የተያዙ ሰዎች ያለመናገር መብት ( the right to remain silent) በይፋ ተጥሶ ያለማንም የህግ ባለሞያ ምክር ለብዙ ቀናት ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቷል፡፡
ምርመራቸውን ጨርሰዋል ተብለው የታሰቡ ታሳሪዎቸን ካልሆነም በስተቀር በምርመራ ወቅት የህግ ባለሞያ ለማግኘት አልተፈቀደላቸውም፡፡
መሰረቱ መሰረታዊ የሆነው ያለመናገር መብትና የሕግ ባለሞያ የማግኘት መብት መከልከሉ የተለመደውን ማእከላዊ ምርመራ የሚታማበትን የማስገደድ ምርመራ እውነተኛነት የሚያጋልጥ ነው፡፡ በተጨማሪም የአካልና የስነልቦና ጉዳት የማድረስ ምርመራ ሲፈጸምባቸው እነደነበረ የተያዙ የዞን ዘጠኝ አባላት በተናገሩበት ወቅት ፍርድ ቤቱ የነዚህን ጉዳቶች መከልከል ላይ አስተያየት ከመስጠት ውጪ ይሄ ነው የሚባል እርምጃ እና ማጣራት ለመውሰድ አልሞከረም፡፡
ማዕከላዊ ምርመራ ከዚህ በፊት የሚታወቅበት ድብደባ፣ ምግብና እንቅልፍ መከልከል፣ የስነልቦና ጫና እና ማስፈራሪያ የተለያዩ ዛቻዎች ሁሉም በተያዙ የዞን ዘጠኝ አባላትና ጋዜጠኞች ላይ በተለያየ መልኩ እነደደረሰ ተረድተናል፡፡ ይህም ምርመራውን ተከትሎ የሚመጣውን ማንኛውንም ማስረጃ በሕግም በሞራልም ተቀባይነት እነዳይኖረው እነደሚያደርግ እናውቃለን፡፡
ከታሳሪዎች የሚገኙ ማንኛውም መረጃዎች በከፍተኛ ተጽእኖ ስር እንደተሰጡ አንዲሁም ዝም የማለትና የሕግ ባለሞያ ምክር የማግኘት ሕገ-መንግስታዊ መብቶቻቸው ተጥሰው የተገኙ እንደሆኑ ዞን ዘጠኝ ያምናል፡፡ በወንጀል ህግ ስነስርአት መሰረት እነዚህ ያለህግ ባለሞያ ጉብኝት ያለመናገር መብታቸው (የህገ መንግስቱ አንቀጽ 19) ተጥሶ የተገኙ መረጃዎች በዚህ ምክንያት ብቻ ተቀባይነት እነደማይኖራቸውም የአገሪትዋ ሕግ ይደነግጋል፡፡
በመሆኑም መንግስት ታሳሪዎቹን አንደፈታ እና ጉዳያቸው ሕገ መንግሰታዊ እና የወንጀል ህግ ሥነ-ስርአት ሕጉን ተከትሎ አንዲሆን እንዲያደርግና ሌሎች እንዲያከብሩ የሚጠይቀውን ሕግ መንግስት ራሱን በማክበር አንዲጀምር አሁንም በድጋሚ ጥሪ እናቀርባለን ፡፡
ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተጥሶ ማእከላዊ ምርመራ የሚገኙ የዞን ዘጠኝ አባላት እና ጋዜጠኛ ወዳጆቻችን ያለንን ክብር እና ፍቅር እየገለጽን ጽናታቸው አስተማሪ ሲሆን በሚከተሉት ቀናት በሚኖሩት ማንኛውም የህግ ሂደቶች ውስጥ የሚኖሩትን አዳዲስ መረጃዎች ለዞን ዘጠኝ ነዋሪያን እንገልጻለን፡፡ነገ ቅዳሜ ግንቦት 9 እና እሁድ ግንቦት 10 የሚደረጉ የፍርድ ቤት ሄደቶችን አራዳ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ጠዋት በመገኘት መከታተልና አጋርነታችሁን ማሳየት ትችላላችሁ፡፡
የዞን ዘጠኝ ስብስብ አባላቶቹ ምንም አይነት ህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደማያውቁ በድጋሚ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

No comments:

Post a Comment