Tuesday, September 10, 2013

የ2005 የጊዜ መሥመር


በማሕሌት ፋንታሁን

ክቡራት የዞን 9 ነዋሪዎች ዓመቱ ከማለቁ በፊት እንዴት እንዳለፈ ለማስታወስ እንዲረዳን በማሰብ በ2005 የተከናወኑ አበይት ተግባራትን በዓመቱ የጊዜ መሥመር ላይ እንደሚከተለው ለማሳየት ሞክረናል፡፡ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ፡፡

መስከረም
  • §  መስከረም 11/2005 የተከበሩ ኃ/ማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ሆነው፣ የተከበሩ ደመቀ መኮንን ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ ፈፀሙ፣
  • §  መስከረም 17 ቀን 2005 ድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በሒልተን ሆቴል አንድ ሺሕ ያህል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ጋብቻውን ፈፀመ፣

ጥቅምት
  • §  ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ አሜሪካን ሃገር ከሚገኘው የዓለም አቀፉ የሴቶች ሚዲያ ፋውንዴሽን የ2012 ‹ፅናት በጋዜጠኝነት ሥራ› የተሰኘ ሽልማት አገኘች፣
  • §  የ2005 የእስልምና ምክር ቤት /መጅሊስ/ ምርጫ በየቀበሌው ተካሄደ፣  
ሕዳር
  • §  የጋዜጠኝነት እና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ዶ/ር መሠረት ቸኮል ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
  • §  ጠ/ሚኒስቴር ኃ/ማርያም ደሳለኝ አቶ ቴድሮስ አድሃኖምን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤አቶ ሙክታር ከድር እና ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በጠ/ሚኒስቴርነት ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ፣ የትራንስፖርት እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር፤ አቶ ከበደ ጫኔን የንግድ ሚኒስቴር እንዲሁም ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አድርገው ሾሙ፣

ታኅሳስ
  • §  በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የወንጀል ችሎት በቀረበባት የሽብርተኝነት ወንጀል 14 ዓመታት እስርና 33 ሺሕ ብር ቅጣት የተጣለባት ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮተ ዓለሙ፣ በይግባኝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የእስር ጊዜዋን ወደ አምስት ዓመታት በመቀነሱ ምክንያት ለሰበር ችሎት “በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል” ስትል አቤቱታ አሰምታ፤ ሠበር ሰሚ ችሎቱ  በሰጠው የመጨረሻ የቅጣት ውሳኔ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፉትን የቅጣት ውሳኔ አፀና፣
  • §  የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ለጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፤ ከሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶበት የ18 ዓመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በአፋጣኝ ከወህኒ ቤት እንዲለቀቅ ጥያቄ አቀረቡ፣
  • §  አራት በፍ/ቤት እስር የተፈረደባቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የ2012 የሄልማን/ሃሜት ሽልማት መሸለማቸውን፤ ተሸላሚዎቹ በእስር ላይ የሚገኙት እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ እንዲሁም በሌለበት የተፈረደበት የቀድሞዋ የ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ አዘጋጅ መስፍን ነጋሽ ሲሆኑ ጋዜጠኞቹ ሽልማቱን ያገኙት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማስጠበቅ ላደረጉት ጥረት መሆኑም ተጠቅሷል፣

ጥር
  • §  የ33ቱ ፓርቲዎች ኅብረት በሚያዚያ ወር የተካሄደውን የአዲስ አበባ መስተዳደር እና በመላው ሃገሪቱ በሚካሄደው የወረዳና የክልል ምክርቤቶች ምርጫዎች ላይ ላለመሳተፍ ውሳኔ አሳለፉ፣
  • §  በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በቃ፤ በዚሁ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አዳነ ግርማ ከ37ዓመት በኋላ የመጀመሪያ የሆነችውን ብቸኛ ጎል ለኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ አስቆጠረ፣
  • §  ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ለማምጠቅና የሰው ኃይሏን ከቴክኖሎጂው ጋር ለማስተዋወቅ የሚያስችል የሙከራ ሥራ መጀመሯን፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ / ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል አስታወቁ፣
  • §  በ2004 ከሃያ ዓመት እስር በኋላ የተፈቱት ከፍተኛ የደርግ አመራር የነበሩት ኮሎኔል ደበላ ዴንሳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣

የካቲት
  • §  ድምፃዊ ታምራት ሞላ ለረጅም ዓመታት ሕክምና ሲከታተል በነበረበት የደም ካንሰር ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፣
  • §  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክርስቲያን 6ኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን አድርጋ መረጠች፣
  • §  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር  የነበሩት ዶክተር ዮናስ አድማሱ 69 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፣
  • §  በአዲስ አበባ በባሕል ሕክምና ታዋቂ የነበሩት ሐኪም ማሞ ኃይሌ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
  • §  ከሁለት ዓመት በፊት በአምባሳደርነትና በምክትል አምባሳደርነት ማዕረጐች ተሹመው በተለያዩ አገሮች ከተመደቡ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከልሥራ ስምንት የሚሆኑት ወደ አገር እንዲመለሱ ተደረገ፤ ሁለቱ በድጋሚ ሹመት ወደሌሎች አገሮች ሲመደቡ የተቀሩት ግን በአገር እንዲቀሩ ውሳኔ ተላለፈ፣

መጋቢት
  • §  በኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ኮሚቴ፣ በሰማያዊ ፓርቲ እና በባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር አስተባባሪነት፤ በጣሊያን አፊሌ በተባለ ቦታ የተገነባውን የግራዚያኒ ኀውልት እና መታሰቢያ ቦታ በመቃወም፤ ከሰማእታት ኀውልት (6 ኪሎ) አንስቶ እስከ ጣሊያን ኤምባሲ የሚዘልቅ የእግር ጉዞ መጋቢት 8/2005 ጥሪ ተላለፈ፤ ሰልፉን ለማካሄድ የተገኙ አባላት እና የሰልፉ ዓላማ ደጋፊዎች ሰማእታት ኀውልት መሰባሰብ እንደ ጀመሩ  ፖሊስ ሰልፉን ሕጋዊ አይደለም ብሎ በኃይል በመበተን እና 40 የሚሆኑ በሰልፉ የተገኙ ሰዎች ለአንድ ቀን ታስረው ተፈቱ፣
  • §  የኢሕአዴግ ዘጠነኛ ጉባዔባሕር ዳር ከተማ ለአራት ቀናት ተካሄደ፣
  • §  ‹ኢትዮትዩብ› በአሜሪካ አምስተኛ ዓመቱን አከበረ፣ በዕለቱም ‹ለፕሬስ ነፃነት የተጋ› በሚል ዓመታዊ  ሽልማት ለጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተሸላሚ በወኪል ተበረከተለት፣
  • §  የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታሰቢያመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽንመሥራች ጉባኤ በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ፣

ሚያዚያ
  • §  ላለፉት አምስት ዓመታት በተደረገ ኮንትራት አማካኝነት በአሜሪካ ስትጎበኝ የነበረችው ሉሲ (ድንቅነሽ) ጉዞዋን ጨርሳ ወደ ሃገሯ ተመልሳ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆነች፣
  • §  ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ጀርባ የሚገኘው የአቡነ ጴጥሮስ ኀውልት፤ በአዲስ አበባ በመሠራት ላይ በሚገኘው የቀላል ባቡር ግንባታ ምክንያት ከነበረበት ቦታ ተነስቶ ብሔራዊ ሙዚየም እንዲገባ ተደረገ፣
  • §  በጋምቤላ ክልል አኙዋክ ዞን አቦቦ ወረዳ ልዩ ቦታው ቁርጫ በሚባል አካባቢ 17 ተማሪዎችንና በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሠማራው ሳዑዲ ስታር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሠራተኞች የሆኑ ስድስት ሰዎችን፣ በድምሩ 23 ሰዎችን በጥይት ደብድበው በመግደልና በሽብር ወንጀል ተከሰው ከነበሩት 14 ግለሰቦች መካከል፣ ዘጠኙ በሞት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው፣
  • §  ጋምቤላን ለሰባት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ኡሞድ ኡቦንግ የጋምቤላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) እና የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርነትና ከክልሉ ፕሬዚዳንትነት እንዲነሱ በመወሰኑ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ጋትሉዋክ ቱት በምትካቸው የክልሉ ፕሬዚዳንትነት ሆነው ተሾሙ፣
  • §  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰጠውን የጥፋተኝነት ብይንና ብይኑን ተከትሎ የተጣለባቸውን የቅጣት ውሳኔ በመቃወም፣ ከነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበው በነበሩት፣ እነ እስክንድር ነጋ ላይ ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶ ይግባኝ ካሉት ፍርደኞች ውስጥ ከክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) በስተቀር የሁሉም የሥር ፍርድ ቤት ቅጣት ውሳኔ እንዲፀና ተደረገ፤ በመሆኑም ክንፈሚካኤል በሥር ፍርድ ቤት ተጥሎበት የነበረው 25 ዓመት ፅኑ የእስራት ቅጣት ማቅለያው ሲያዝለት ወደ 16 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀነሰ፣
  • §  የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር በ124 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2004 ዓ.ም. ሒሳብን ኦዲት በማድረግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፣ መንግሥት ሊያገኘው የሚገባ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አለመታወቁንና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ደግሞ መንግሥት ማጣቱን አሳወቀ፤ ከዚህ ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር 401.757 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 173.756 ሚሊዮን ብር፣ የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ሥልጠና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ 155.597 ሚሊዮን ብር የታየባቸው መሥሪያ ቤቶች መሆናቸው ተገለፀ፣

ግንቦት
  • §  የፌደራል ፀረ ሙስና እና የሥነ ምግባር ኮሚሽን የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መላኩ ፋንታን ጨምሮ ሌሎች የባለሥልጣኑ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በመዋላቸው የክስ የፍርድ ሒደቱ ተጀመረ፣
  • §  በባሕርዳር ከተማ የፌደራል ፖሊስ አባል የሆነ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ 10 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ወንጀለኛው ፖሊስም ራሱን አባይ ወንዝ ውስጥ ወርውሮ ሕይወቱን አጠፋ፣
  • §  በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ዣቪየር ማርሻል በ61 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
  • §  በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉት በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ምትክ፣ የአዳማ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ በከር ሻሌ ተሾሙ፣
  • §  በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በመምህርነት፣ በተመራማሪነት እና በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት እና “ቤተ ክሕነትና መንግሥት በኢትዮጵያ ከ1262-1527” (Church and state in Ethiopia 1262-1527) በተሰኘው መጽሐፋቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፣
  • §  አዲስ አበባ የሚከበረውን የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በዓል ላይ ሰማያዊ ፓርቲ ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ቢያደርግም የአ.አ መስተዳድር ሰልፉን ጥበያ የሚያደርግ የፖሊስ ኃይል እጥረት አለብን በማለት ለሌላ ጊዜ እንዲያዘዋውሩት ጠየቀ፣
  • §  የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/የአፍሪካ ኅብረት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ዋናው ጽ/ቤት በሚገኝበት በኢትዮጵያ አከበረ፣
  • §  የሕዳሴው ግድብ ቀጣይ የግንባታ ምዕራፍ የሆነው ወንዙን አቅጣጫ የማስቀየስ ሽራ ተከናወነ፣ ይህን ተከትሎም ከሃገሪቷ ፖለቲከኞች ጋር በቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት ሙርሲ የተመራ ውይይት ሲካሄድ የግድቡ ሥራ እውን እንዳይሆን የሚያደርጉ ሐሳቦች መሰንዘራቸው፤ ይህ ውይይትም በስህተት በሃገሪቱ የብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ በቀጥታ ተላለፈ፣   
  • §  ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ መነሻውን የፓርቲው ፅ/ቤት፤ መድረሻ ቦታውን ኢትዮ-ኩባ አደባባይ ያደረገ፣ በርካቶችን ያሳተፈ እና ከ97 ምርጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ  የተቃውሞ ሰልፍ አካሄደ፣

ሰኔ
  • §  አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ‹‹ሚሊዮን ድምፆች ለነፃነት›› የተሰኘ፣ ለሦስት ወራት የሚቆይ ሕዝባዊ ንቅናቄ ጀመረ፤ በንቅናቄው ሕዝባዊ ስብሰባዎች፣ ሠላማዊ ሰልፎችና በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ የተቃውሞ ፊርማ እንደሚሰበሰብ ተነግሯል፣
  • §  ለቀደሙት 20 ወራት በሽብር ወንጀል ተፈርዶበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ፣ ጦማሪ እና አራማጅ እስክንድር ነጋ፤ ከባለቤቱ እና ልጁ ውጪ በሆኑ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ እንዲጎበኝ ሲፈቀድለት የሚጎበኝበት ሰዓትም እንደማንኛውም በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ታራሚዎች እንደሆን ተደረገ፣
  • §  በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የ2013ቱ የቢግ ብራዘር አፍሪካ ውድድር ከኢትዮጵያ የሄደችው ቤቲ የወሲብ ትእይንና አነጋጋሪ መሆን፣
  • §  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሦስተኛውን ጨዋታ በሃገሩ አድርጎ ተጋጣሚውን ደ/አፍሪካን 2-1 በመርታት የቀሪውን ጨዋታ ነጥብ ሳያሳስበው ምድቡን በአንደኝነት መምራቱን ቢያረጋግጥም በማግስቱ በፌዴሬሽኑ ስህተት ብሔራዊ ቡድናችን ሦስት ነጥቦችንና ሦስት ጎሎች የሚያስቀጣውን ጥፋት ማጥፋቱን ተነገረ፣
  • §  ፓርላማው 2005. የሥራ ዘመን ማጠናቀቂያ ላይ የሥልጣን ሹም ሽር በማድረግ አስር አዳዲስ ሚኒስተሮች ሾመ፣
  • §  የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ማጣሪያ ያለፈ የመጀመርያ ክለብ መሆኑ፣

ሐምሌ
  • §  ወጣት የፖለቲካ ተንታኙ ጃዋር መሐመድ አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሚያዘጋጀው   ‹ዘ ስትሪም› በተሰኘ ፕሮግራም ላይ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ እና ተያያዥ ጉዳዮች የብዙዎችን (በተለይም ማኅበራዊ አውታር ተጠቃሚዎችን) ትኩረት የሳበ እና ያነጋገረ ንግግር አደረገ፤
  • §  አንድነት ፓርቲ በጎንደርና ደሴ ከተሞች በተመሳሳይ ቀን (ሐምሌ 7/2005) ‹‹ሚሊዮን ድምፆች ለነፃነት›› በተሰኘው ሕዝባዊ ንቅናቄው ሠላማዊ ሰልፎችን አካሄደ፣
  • §  አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው በ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ አዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በመወዳደር ወደ ፓርላማ ለመግባት ማቀዱን በቃለ ምልልሶች አረጋገጠ፣

ነሐሴ
  • §  የአምስት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ፣

  • §  1434ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች በተለይ በአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ሲከበር፣ ፌደራል ፖሊስ በዓሉን ለማክበር የተገኙትን በርካታ ሰዎች ላይ እስር እና አካላዊ ጥቃት ፈፀመ፣

  • §  ሞስኮ በተዘጋጀው 14ኛው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 3 የወርቅ፣ 3 የብር እና 4 የነሃስ ሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም 6 ከአፍሪካ 2 ሆና አጠናቀቀች፤ ወርቁን ያስገኙት ዝነኞቹ የረጅም ርቀት ተወዳዳሪዎች ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር እንዲሁም በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነውን 800 ርቀት አሸናፊ መሐመድ አማን ናቸው፣

  • §  የአቡነ ጳውሎስ እና  የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበሩ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሙት ዓመት ለማክበር መንግሥት አረንጓዴ ዘመቻ አደረገ፣ በርካታ ፓርኮችንም በስማቸው ተሰየመላቸው፣
  • §  ወጣቱ ድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ባደረበት ድንገተኛ ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፣
  • §  የ33ቱ ፓርቲዎች ዐቢይ ኮሚቴ ባደረገው የጋራ ስብሰባ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በየጋዜጣው ላይ የሚሰጡት መግለጫ የፓርቲው አቋም መሆኑ በመረጋገጡና በጋራ ለመሥራት ከተስማሙበት የጋራ ሰነድ ውጪ ሆነው መርሖችን በመጣላቸው ምክንያት ፓርቲው ከኅብረቱ መታገዱን አሳወቁ፣
  • §  ሰማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 26/2005ዓ.ም በአዲስ አበባ  ሊያካሂድ ያቀደውን እና ከሦስት ወር በፊት ሲያስተዋቅ እንዲሁም ዝግጅት ሲያካሂድ የከረመበትን ሠላማዊ ሰልፍ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሰልፉ እንዳይካሄድ ከለከለ፣ 
  • §  በተለያዩ የእምነት ተቋማት ኅብረት ጠሪነት፤ በመንግሥት ወኪሎችና የኢሕአዴግ አባላት ቀስቃሽነት የሃይማኖት አክራሪነትና ፅንፈኝነትን ለመቃወም በሚል ነሐሴ 26/2005ዓ.ም በአዲስ አበባ  ሰላማዊ ሠልፍ  ተካሄደ፣

ጳጉሜ
  • የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ኮንጎ ብራዛቪል ላይ ገጥሞ ተጋጣሚውን 2 ለ 1 በመርታት፤ ምድቡን በመሪነት በማጠናቀቅ አፍሪካን የሚወክሉ 5 ቡድኖች ተለይተው ለሚወጡበት 10 ብሔራዊ ቡድኖች ለሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጥሎ ማለፍ ከገቡት ውስጥ መካተት ቻለ፡፡

No comments:

Post a Comment