ከግሪክ፣ የኤሶጵ
ተረቶች አንዱ እንዲህ ይተረካል፡፡ አንድ ሰውዬ እና ልጁ፣ አህያቸውን አስከትለው ወደገበያ ሲሄዱ የተመለከታቸው የአገሩ ሰው፣
‹‹እናንት ሞኞች፣ አህያው እኮ የተፈጠረው ሊጋለብ ነው›› ይላቸዋል፡፡ አባት ልጁን አህያው ላይ ጭኖ ትንሽ እንደተጓዙ የሆኑ ሰዎች
ይመለከቱ እና ‹‹ምን ዓይነት የተረገመ ልጅ ቢሆን ነው አባቱን በእግሩ እያስኬደ እሱ የሚጋልበው?›› አሉ፡፡ አባት ልጁን አስወርዶ
ራሱ መጋለብ ቀጠለ፤ ጥቂትም ሳይጓዙ ግን ‹‹ምን ዓይነት ክፉ አባት ነው ልጁን በእግሩ እያስኳተነ እሱ አህያ የሚጋልብ?›› ብለው
የሚተቹ ሰዎች አለፉ፡፡ ግራ የተጋባው አባት ልጁን ከኋላው ጭኖ አህያውን ለሁለት ይጋልቡት ጀመር፡፡ ይህንን የተመለከቱ ሰዎች
‹‹ምን ዓይነት ጭካኔ ነው፣ አንድ አህያ ለሁለት የሚያስጋልባችሁ?›› አሏቸው፡፡ ግራ የተጋቡት አባትና ልጅ በመጨረሻ አህያውን
ለሁለት ተሸክመውት ገበያ በመግባት የገበያተኛው መሳለቂያ ለመሆን በቅተዋል፡፡
የተረቱ ሞራል፣
ሁሉንም ማስደሰት እንደማይቻል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም የሚያስማማ መፍትሄ ባይገኝም ቅሉ ለትችቱ መፍትሄ ለመስጠት ባደረጉት
መፍጨርጨር አባት እና ልጅም በፈረቃ ጋልበዋል፣ አህያውም አርፏል፡፡ የሚቀበሉትን ትችት ማወቅ እና አለማወቅ፣ ብሎም ለትችቱ ሁነኛውን
መፍትሄ መፍጠር የተተቺው ድርሻ ቢሆንም ‹ትችት› ግን የማይቀር እና ሊቀር የማይገባው ነው፡፡
አሁን የራሳችንን
ትችት ባሕል ወደመተቸት እናልፋለን፤ የትችት ባሕላችንን ከመተቸታችን በፊት ግን ለቃሉ ትርጉም በማበጀት ብንጀምር መልካም ነው፡፡
‹ትችት› የሚለው ቃል ከመነሻው አሉታዊነት እንዳለበት የሚከራከሩ አሉ፡፡ እነዚህ ተከራካሪዎች ‹ሂስ› የሚለው ቃል የተሻለ አስማሚ
እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሁለቱ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ማስታረቅ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ - ሳይስማሙ እንዲኖሩ እንተዋቸውና
‹ትችት› በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንዲኖረው ስለሚፈለገው ትርጉም እንነጋገር፡፡
‹ትችት› በዚህ
ጽሑፍ ውስጥ ‹‹በሆነ ርዕሰ ጉዳይ፣ ሐሳብ፣ ፍልስፍና፣ ድርጊት ወይም
የሥራ ውጤት ላይ የሚሰነዘር፣ በምክንያት ላይ የተመሰረተ የተቃርኖ ወይም የነቀፌታ አስተያየት ነው፡፡››
በአገራችን
ለትችት የተነወሩ (አይነኬ) በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህ ጉዳዮች መካከል ለጠቅላላ የትችት ባሕላችን ጉብጠት ምሳሌ ይሆናሉ በሚል
በጥንቃቄ የመረጥኳቸውን ጉዳዮች እያነሳሁ ለማቅናት እደረድራለሁ፡፡ ትችቴ ያልተስማማው የመልስ ምት ቢጽፍ በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ
ለማስፈር ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡