Tuesday, October 27, 2015

‹ዞን ፱› ከትላንት እስከ ዛሬ

ይህ ጽሁፍ የዞን፱ ጦማርን አስልክቶ በቀለም ቀንድ ጋዜጣ ላይ የወጣ ነው ፡፡ አርታኢው በጠየቁን መሰረት ለዞን9 ነዋርያን ይነበብ ዘንድ እዚህ አትመነዋል፡፡

በሙሉቀን ተስፋው

ብዙዎቻችን ስለ ዞን ፱ ጦማርያን እንጅ ስለ ‹ዞን ፱› ብሎግ ያለን ግንዛቤ ውስን ሊሆን ይችላል፡፡ እንዴት ተመሰረተ? ለምን ዞን ፱ ተባለ? ጦማርያኑ ተጠራርገው ወደ እስር እስኪወርዱ ድረስ ምን አከናወኑ? ለምን ሁሉም ሊታሰሩ ቻሉ? እንዴት ተፈቱ በሚለው ላይ ዘርዘር አድርገን ለማዬት ወደድን፡፡
በ2004ዓ.ም. ከወደ ቤሩት አንድ መጥፎ ነገር ተከሰተ፡፡ ‹ዓለም ደቻሳ› የተባለች ኢትዮጵያዊት በአሰሪዎቿ ተገደለች፡፡ የሚያሰሯት ሰዎች ታማ ነው የሞተች ቢሉም የሊባኖስ ቴሌቪዥን በአሰሪዎቿ በገመድ ስትጎተት የሚያሳይ ምስል ለቀቀ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስቆጣ፡፡የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ ‹ዓለም› የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ወደ ቤሩት የሄደችውም ገንዘብ ተበድራ ነበር፡፡ ‹ልጆቼንና ቤተሰቦችን ከችግር አድናለሁ› የሚል ተስፋን ይዛ የተጓዘችው ዓለም የተበደረችውን ገንዘብ እንኳ ሳትከፍል ሕይወቷ ማለፉ ሀዘኑን የከበደ አደረገው፡፡‹ዓለምን› ዓለም ከዳቻት፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው በሰፊው ተራገበ፡፡
ከአስር በላይ የሆኑ ሰዎች በፌስ ቡክ ‹‹የዓለምን ቤተሰቦች ለምን አንረዳም›› የሚል እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹ በርግጥም ቀደም ሲል ጀምሮ የራሳቸው ብሎግ ነበራቸው፡፡ ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ሰው ሐሳቡን ደገፈው፡፡ ምናልባትም ማህበራዊ ሚዲያ መሬት የነካ ስራ በኢትዮጵያ የተሰራበት የመጀመሪያ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዘመቻው ፍሬ አፈራና በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ለዓለም ደቻሳ ቤተሰቦች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰብ መርሐ ግብር በሚያዚያ 2004 ዓ.ም ተዘጋጀ፡፡ አዘጋጆቹ ደግሞ እኚሁ ከደርዘን በላይ የሆኑ ልጆች፡፡ ገቢማሰባሰቡ ውጤታማ ሆነና የተፈለገው ድጋፍ ለዓለም ቤተሰቦች ተሰጠ፡፡
ከአዘጋጆቹ ጥቂት የሚሆኑ ልጆች ለምን ይህ ሆነ? የሚል ጥያቄ አንስተው በሰፊው ተወያዩ፡፡ የሥርዓቱ ብልሹነት ዜጎችን ለዚህ እንደሚዳርጋቸው ለማወቅ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ አማካሪም ቀጥረውም ማስጠናት የሚጠይቅ አልነበረም፡፡ ከብላቴናዎቹ የእሳቤ አድማስ በላይም አልሆነም፡፡ለሁሉም ግልጽ የሆነ ነገር ነው፡፡ ሥርዓቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የሆነች፣ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው የሚያድጉበት መንገድ ዝግ የሆነባት፤ ዜጎቿ በሰው ሀገር እንደ ዓለም ደቻሳ ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ ሲገደሉ እንኳ መጠየቅ የማይችል እንደሆነ ለማወቅ የመጠቀ አእምሮ ባለቤት መሆን አይጠይቅም፡፡ ግልጽና ግልጽ ፍንትው ብሎ የሚታይ እውነታ ነው፡፡
ብላቴናዎቹ የችግሩን ምንጭስ አወቅን፤ ከዚህ በኋላ ምንድን ነው ማድረግ የምንችለው? የሚል ወሳኝ ጥያቄ አነሱ፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ ማገኘት ቀላል ነው፤ ግን መስዋትነት ይጠይቃል፡፡ ለዚያውም የወጣትነት የጌጥ ዘመንን የሚበላ መስዋትነት፡፡ መስዋትነቱ ወንጀል ስለሆነ አይደለም-ግን በአፋኝ ሥርዓት ውስጥ ለመብት ቦታ የለም፡፡ ሀገራችን የጋራ እናድርጋት፤ ስለሚያገባን ስለሀገራችን እንነጋገር፤ አማራጭ ሐሳብ እናቅርብ ማለት ያስወነጅላል፡፡ በሞት ፍርድ አሊያም በእድሜ ልክ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ የማን ደፋሮች ናቸው ፈርዖንን የሚናገሩ? በፈርዖን ላይ ማነው ከቶ ምላሱን የሚያነሳ? እንደሙሴ ኮልታፋ ለመሆን ካልሆነ በስተቀር? ያስብላል፡፡ ለፈርዖን የሰው ልጆች ደምናስቃይ የሰርግና የምላሽ ያክል ይጥሙታል፡፡ የጨቋኝነት ባህሪው ይኸው ነውና፡፡
ብላቴናዎቹግን ይህን አስበው ፈርተው ወደ ኋላ አላፈገፈጉም፡፡ የዓለምን ቤተሰቦች ለመርዳት ዝግጅቱን ካስተባበሩት 5 ልጆች፣ ፌስ ቡክ ላይ በንቃት ይከታተሉ ከነበሩት ደግሞ 4 ልጆች ሲደመሩ 9 ያክል ልጆች ሆነው የ‹አክቲቪዝም› ሥራ ለመስራት ዝግጅታቸውን አጠናቀቁ፡፡የፖለቲካ እስረኞችን በፕሮግራም ለመጠየቅ የእቅዳቸው አካል አደረጉት፡፡ በፌስ ቡክ፣ ቲዊተርና በየነ መረብ ዘመቻ ጀመሩ፡፡ በ2005ዓ.ም. ከእለታት በአንደኛው ቀን ‹ርዕዮት አለሙን› ለመጠየቅ 9 ሆነው ቃሊቲ ወረዱ፡፡ ርዕዮት አለሙ ጋር እያወሩ አንዲት ‹አሸባሪ› ሴት ‹‹እንዴት ናችሁ ዞን ፱ኞች?›› አለቻቸው፡፡ ስሟ ሒሩት ክፍሌ ይባላል፤ በግንቦት 7 አባልነት ቃሊቲ የወረደች ‹አሸባሪ ሴት› ናት፡፡ ብላቴናዎቹ ግራ ገባቸው፤ ‹ይህች ሴት እብድ ናት እንዴ?› ሳይሉ አይቀሩም፡፡ በእርግጥ በጠባብ አጥር ውስጥ ከብዙ ቶርቸርጋር መኖር ሊያሳብድ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ባሕታዊ እንዳይሏት ቃሊቲ ገዳም አይደለም፡፡
ርዕዮት አለሙ ብዙ እንዲጨነቁ አልፈቀደችም፡፡ በዝርዝር የ‹አሸባሪዋን ሴት› ንግግር ተረጎመችላቸው፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ቃሊቲ ማረሚያቤት በስምንት ዞን የተከፋፈለ ነው፡፡ ለካ የቃሊቲ ታሳሪዎች እኛን ከማረሚያ ቤቱ አጥር ውጭ የምንኖረውን ዜጎችን ‹ዞን ፱ኞች› እያሉ ነው የሚጠሩን፡፡ ስለዚህ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ አንድ የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ ‹ልማታዊው አርቲስት ሸዋፈራው ደሳለኝ› ቢያዘጋጅ እንዲሁም ለተወዳዳሪዎቹ ‹‹ሰፊውና ብዙ እስረኛ ያለበት ዞን የትኛው ነው?›› ብሎ ቢጠይቅ መልሱ ‹‹ዞን ፱››የሚል ይሆናል፡፡ ሚስጥሩ ግልጽ ነው፤ በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ሁሉም ዜጋ እስረኛ ነው፤ ሁሉም ዜጋ የፈርዖን ግዞተኛ ነው፡፡
በበየነመረብ ለሚያደርጉት ዝግጅት ማን እንበለው? እያሉ ሲያነሱ ከብላቴኖቹ አንዱ ጆማኔክስ ‹የአሸባሪዋን ሴት› ቃል ‹‹ለምን ዞን ፱አንለውም?›› የሚል ሐሳብ አቀረበ፤ በሙሉ ድምጽ ጸደቀ (እንደ ኢህአዴግ ፓርላማ እንዳትሉ አደራ)፡፡ ብላቴኖቹ ‹‹ስለሚያገባን እንጦምራለን!›› የሚል መሪ ቃል ይዘው ዘመቻቸው ጀመሩ፡፡ ዘመቻው ፍጹም ሰላማዊ፣ ብዕር እንጅ ጥይት ያልያዘ፣ ሰላምን እንጅ ጥፋትንያልሻተ፣ በፊትም በኋላውም ምንም ኮልኮሌ የሌለው ነበር፡፡
ልጆቹ በጋራ ‹‹የሚያገባው ትውልድ ፍለጋ›› የሚል በጋራ ስለሀገራችን እንነጋገር፤ የጋራ ትርክት እንፈለግ የሚል ይዘት ያለው ጽሁፍ ጻፉ፡፡ድረ ገጹ በተከፈተ በ15ኛ ቀኑ ሀገር ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዳያዩት ታገደ፡፡ ለፈርዖን ምን ይሳነዋል? ጌታውን አመስግኖ ማደር ያለበትን ምስኪን ሕዝብ ስለምን የእነዚህን ብላቴኖች ወግ ያነባል? በቃ ተከለከለ፡፡ ያም ሆኖ አራት ተከታታይ የበየነ መረብ ዘመቻዎች ተካሄዱ፡፡አንደኛው ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበትን 18ኛ ዓመት በዓል ሲዘከር ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይከበር›› ያልተከበሩ የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች ዘርዝረው ተቹ፡፡ ‹‹ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት አሁኑኑ ለሁሉም!›› በማለት አንቀጽ 29ን መሰረት በማድረግ ዘመቻውን ደገሙት፡፡ሦስተኛም ‹‹የሰላማዊ ሰልፍ መብታችን ይመለስ!›› ሲሉ ሠለሱት፡፡ 4ተኛም ‹‹ኢትዮጵያዊ ሕልም ኑ አብረን እናልም!›› ሲሉ ድምጻቸውን አሰሙ፡፡
የልጆቹ ድምጽ ቀልቃላ ነበር፤ ብዙ ርቀት ብዙ በጣም ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ የሚሰማ፡፡ እንቅልፍ የሚቀሰቅስ ድምጽ! ፈርዖንን የማያስተኛ፡፡እነዚህ ነገረኞች ‹‹የዞን ፱ ዐመታዊ መጽሐፍ›› ብለው በነጻ አደሉ፡፡ አዲስ ራዕይ በገንዘብ በሚቸበቸብበት አገር በነጻ አንብቡብሎ መስጠት ምን ይሉታል? ግን ሆነ፡፡ መጽሐፉ በደረ ገጻቸው በነጻ ተለቀቀ፡፡
ከዚህ በኋላ ፈርዖን ትዕግዙ አለቀ፡፡ በመጀመሪያ በጓደኞቻቸው ማስፈራሪያ ተላከባቸው፡፡ ‹ፈርዖን አምርሯል፤ ከዚህ በኋላ ውርድ ከራሴ›ተባሉ፡፡ በ2006 ዓ.ም. ሁለቱን ብላቴኖች ከመላእክት የፈጠኑ ደህንነቶች ጠርተው ‹‹ስለምን አትሰሙም? ጌቶቻችን ስለምን ታስደነብራላችሁ? ካላረፋችሁ ቀሳፊ መልኣክ እንልካለን›› አሏቸው፡፡
መደናገጥ ተፈጠረ፡፡ ልጆቹ አሁንም ጠየቁ- የሠራነው ወንጀል ምንድን ነው? አሉ፡፡ መልሱ ግን ምንም ነው፡፡ ሙሴስ ቢያንስ ወገኖቹን ለማዳን የሌላ ሰው ሕይወት አጥፍቶ ነው የተሰደደ፤ እኛ ግን ምንም አልሰራንም፡፡ ስለዚህ የጌቶች ንዴት እስኪበርድ እንጠብቅና እንቀጥል ሲሉ መከሩ፡፡ ያም ሆኖ ምርጫ 2007 እየቀረበ መጣ፡፡ ይህ ምርጫ ዝም ብሎ መሆን የለበትም፤ ምንም እንኳ ጌቶች ባይወዱትም ዜጎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ሕዝብ የማንቃት ሥራ እንጀምር አሉ- በምክር ቤታቸው፡፡ የነዚህ ልጆች ምክር ቤት 547 ወንበር ላይ ከተጎለቱ ሰዎች በላይ ማነቃቃት የሚችል ከቶ ምን አይነት ታምር ቢሆን ነው? ያስብላል፡፡
በሚያዚያ2006 ዓ.ም በብሎጋቸው ምርጫ 2007ን በተመለከተ በሰፊው እንደሚሰሩ ባበሰሩ በሳምንቱ ከሚያዚያም በ17ኛው ቀን ከፈርዖን ዘንድ የጥፋት መልእክተኞች 9 ልጆችን ለቃቅመው ወሰዱ፡፡ ስድስቱ ከጦማርያን ወገን ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ ሐሳባቸውን የሚደገፉ ጋዜጠኞች(ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይሉና ኤዶም ካሳዬ) የጥፋት መልእክተኞች ሰለባ ሆኑ፡፡ ከጦማርያኑ ሦስቱ ደግሞ ከጥፋት ውሃ እንዲድኑ እግዚአብሔር ስለፈቀደ ከነነዌ ወጥተው ነበር፡፡ ለወሬ ነጋሪ ሶልያና ሽመልስ፣ ጆማኔክስ ካሳዬና እንዳልካቸው ኃ/ሚካኤል ቀሩ፡፡ ‹ሙሴም ከምድያም ምድር የተመለሰው ፈርዖን እንደማይጎዳው ባወቀ ጊዜ ነው፤ እኛም የፈርዖን ብርታት እስኪደክም ወደ ነነዌ አንመለስም› ብለው ይመስላል እንደወጡ ቀሩ፡፡
የታሰሩት ግን የእድሜያቸው 84 ቀን በማዕከላዊ አለፈ፤ አንዲት አራስ ሴት ልጇን ወልዳ ክርስትና አስነስታ እንግዶቿን ሸኝታ ወደ ባሏ የምትመለስበትን ጊዜ ያክል፡፡ 75 ቀናት ግን በጨለማ ክፍል ውስጥ ፀሀይ የማታውቀው ሀገር - ማዕካላዊ ሳይቤሪያ፡፡ በሳይቤሪያ ጥፊና በትር የእለትምግባቸው ሆኖ ስድብ እንደ ምርቃት እየቆጠሩት ቶርቸር ከፈጣሪ የተላከላቸው መና ሆኖ፣ ከባድ ስፖርት እየሰሩ ያን ያክል ጊዜ ቆዩ እንጅ እንደ አራስ አጥሚት እየጠጡ ገንፎ እየሰለቀጡ አልነበረም፡፡
በ2006 ሐምሌ በገባ 11ኛው ቀን ሲሆን ክስ ተፈጠረባቸው፡፡ ሲያንስ 15 ዓመት በእስር በሚያቆየው ሲበዛ ደግሞ ከመሬት በሚስወግደው በሐሙራቢ ሕግ ጨካኝ አንቀጽ ‹ሽብር ማነሳሳት፣ ለማነሳሳት ማሰብ፣ ማሴር…› በሚለው ተወንጅለው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ‹‹የቀለም አቢዮት ለማስነሳትአስባችኋል›› አሏቸው፡፡ ምስክሮች ቀረቡ፡፡ ሠልስቱ ደቂቃን በናቡከደነፆር ዙፋን በቀረቡ ጊዜ ምስክሮቹ የተናገሩትን የመሰለ ነበር፡፡እነዚያ ምስክሮችስ ቢያነስ ለቆመው ምስል እንደማይሰግዱ ያውቃሉ፡፡ አለመስገድም ወንጀል የሆነበት ዘመን ነበር፡፡
ፍርዱ እየተጓተተ አንድ አመት አለፈ፡፡ እድሜም እንደዋዛ ቆጠረ፡፡ የጓጉለት ምርጫ ድራማ በቃሊቲ ሆነው አለፈ፡፡ በየጊዜው ፍርድ ቤት ይመላለሳሉ ግን ምንም ውሳኔ የለም፡፡ ምርጫ ካለፈ በኋላ ለብይን ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተያዘ፡፡ ቀደም ብሎ ግንሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ክሱ ተቋርጦ 5ቱ ልጆች ማለትም በክስ መዝገብ 4ኛ ተከሳሽ ማህሌት ፋንታሁንና 6ኛ ተከሳሽ ዘላለም ክብረት (ሁለቱም ጦማርያን) እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ አስማማው ኃ/ጊወርጊስ፣ 9ኛ ተከሳሽ ኤዶም ካሳየና 10ኛ ተከሳሽ ተስፋለም ወልደየስ(ሁሉም ጋዜጠኞች) ወጡ፡፡
ጥቅምት5 ቀን 2007 ዓ.ም. ደግሞ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በኋላ 1ኛ ተከሳሽ ሶልያና፣ 3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል፣ 5ኛ ተከሳሽ አጥናፍ እና 7ኛ ተከሳሽ አቤል በነጻ ተሰናበቱ፡፡ 2ኛው ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ጽሑፎችህ ሽብር ያነሳሳሉ ተብሎ ተለይቶ ቀረ፡፡ የበፍቃዱ ክስ ወደ ወንጀል ተቀይሮ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 257/ ሀ ከአስር ቀን እስከ 6 ወር እስር ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳ የተከሰሰበት ወንጀል ሊያስቀጣ የሚችለውን ሦስት እጥፍ በእስር ቢያሳልፍም በ20000 ብር (ሃያ ሽህ ብር) ዋስ ከ544 ቀናት በኋላ በቂሊንጦ የተሰጠውን የሊዝ ቦታ ለተረኛ አስረክቦ ወጥቷል፡፡
ዞን ፱ኞች በአንድ ዓመት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ 39 ጊዜ ፍርድቤት ተመላልሰዋል፡፡ በፈቃዱ ለ40ኛ ጊዜ የፊታችን ህዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡

በጨረሻም አልን ‹‹ኢትዮጵያዊ ህልም ኑ አብረን እናልም!››

አበቃሁ

(ይህጽሁፍ የተዘጋጀው ከእስር የወጡ የዞን 9 ጦማርያን ጋር በተደረገ ውይይት ነው፡፡) 

Sunday, October 25, 2015

Thank you!

Our release was as surprising as our detention. Five of us were released as the charges were ‘withdrawn’ in July. While four of us were released because we were acquitted (save the appeal against our acquittal). Still one of our member, Befeqadu, was released on bail and he is yet to defend himself later this year in December. Even though we were released in different circumstances; one thing makes all of us similar – our strong belief that we didn’t deserve even a single day of arrest. Yes, it is good to be released, but we were arrested undeservedly. All we did was writing and striving for the rule of law because we want to see the improvement of our country and the lives of its citizens. However, writing and dreaming for the better of our nation got us detained, harassed, tortured and exiled. Undeservedly.
It makes us happy when we hear people are inspired by our story. But it also makes us sad when we learn people are scared to write because they have seen what we have gone through for our writings. Our incarceration makes us experience happiness and grief at the same time. The bottom line is it is good to know we have inspired people while it is saddening that we have learnt the fact that people have left the public discourse as a result of our detention. Yes, it is sad to know the fact that our detention has a chilling effect on public discourse.
Our incarceration made us feel our lives pass by us. It is true we have missed and lost things. But, we also have increased our learning curve. We have learnt a lot. Our detention tells a broader story of our country. We were able to witness the price of Freedom of Expression is dearly expensive. We are firsthand witnesses of injustice. More than anything we have learnt the fact that a nation which is rampant with injustice is the foremost enemy of its law abiding citizens.
We are victims of institutionalized misconducts. But, it is not beyond our forgiveness. Our incarcerators who gave us those ordeals, even if you are not asking us for our forgiveness, here we are. Please forgive us for we are law abiding citizens who refuse to live in your terms.
For all people who were with us both in good times and in bad times, those of you who stood by us not only in our successes but also in our failures, YOU are awesome! You are our friends, you are our family you were our lawyers, you campaigned for us, and you defended our cause. Thank you! Media organizations, rights groups and the entire community who showed solidarity and concerns for our cause. Thank you! You all deserve our heartfelt gratitude for you have reduced the lengthy prison time and eased the boredom of imprisonment.


Saturday, October 24, 2015

እናመሰግናለን!

በድንገት ከያለንበት ተይዘን እንደታሰርነው አፈታታችንም ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውብን እያለ ግማሾቻችን ‹ክስ ተቋርጦላችኋል› ተብለን ተፈታን፣ ግማሾቻችን ደግሞ ‹ነፃ ናችሁ› (ከሳሽ በነፃነታችን ላይ ይግባኝ መጠየቁ እንዳለ ሁኖ) ተብለን ይሄው ወጥተናል፡፡ ቀሪ ክስ ይዘን በዋስ ወጥተን እየተከራከርንም ያለን አለን፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል የሁላችንም ዕምነት ግን አንድም ቀን ሊያሳስረን የሚገባ ወንጀል አለመፈፃችን ማመናችን ነው፡፡ መፈታታችን ጥሩ ሁኖ፤ መታሰር በፍፁም የማይገባን ነበርን፡፡ መፃፋችን እና ሕግ እንዲከበር መጠየቃችን ሀገሪቱ አገራችን እንድትሻሻል እና ሁላችንም ዜጎች የተሻለ ህይወት አንዲኖራቸው ከመሻት ባለፈ ሌላ ነገር አልነበረውም/የለውም፡፡ ነገር ግን ይህን በማድረጋችን ተገርፈናል፣ ተዘልፈን-ተሰድበናል፣ ታስረናል ተሰደናልም፡፡ ይህ በፍጹም አይገባንም ነበር፡፡
የእኛ መታሰር ፖለቲካዊ ንቃት የፈጠረላቸው ሰዎች እንዳሉ ሲነግሩን ደስ ይለናል፡፡ በእኛ መታሰር ምክንያት ለመጠየቅና ለመፃፍ በጣም እንደሚፈሩ የሚነግሩን ሰዎች ስናገኝ ደግሞ እናዝናለን፡፡ የመታሰራችን ጉራማይሌ ስሜት እንደዚህ ነው፡፡ ሳይገባን በመታሰራችን የነቁ መኖራቸውን በማወቃችን የምነደሰተውን ያክል፤ ሳይገባን በመታሰራችን የተሰበሩና ከተዋስኦ መድረኩ የራቁ እንዳሉ ስናውቅ እጅግ እናዝናለን፡፡
መታሰር በደል ነው፡፡ ብዙ ነገር ያጎድላል፡፡ መታሰር መልካም ነው፡፡ ብዙ ነገር ያስተምራል፡፡ እኛ በመታሰራችን ሀገራችን የበለጠ እንድናውቃት ሁነናል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነት አሁንም ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተረድተናል፡፡ ሕግን መከታ አድርገው የኖሩ ‹ስም የለሽ› ዜጎች ሕጉ ሲከዳቸውና እነሱ ላይ ‹በላ› ሲያመጣባቸው ታዝበናል፡፡ ከሁሉም በላይ ፍትህ የሌለባት ሀገር ለዜጎቿ የማትመችና አገር እንደሆነች አይተናል፡፡
በእስራችን ወቅት የተለያዩ በደሎች በተቋም ደረጃ ደርሰውብናል፡፡ ግን አገር ነውና ከይቅርታ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ለበደላችሁን አካላት እናንተ ይቅርታ ባትጠይቁንም፤ እናንተ የፈለጋችሁትን ባለማድረጋችንና ሕግን መሰረት አድርገን በመኖራችን ስላስከፋናችሁ እባካችሁ ይቅር በሉን፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል ግን እናንተ አላችሁ፡፡ ጓደኞቻችንም ናችሁ፤ ዘመቻ አድራጊዎችም ናችሁ፤ ቤተሰቦቻችንም ናችሁ፤ ጠያቂዎቻችንም ናችሁ፤ ጠበቆቻችንም ናችሁ፣ የመንፈስ አጋሮቻችንም ናችሁ ርቀት ሳይገድባች የጮሃችሁልን አለም አቀፍ የመብት ጠያቂዎችም ናችሁ … በመታሰራችን የተረዳነው አንዱ ትልቅ ነገር የናንተን መልካምነት፣ የናንተን አጋርነት እና የናንተን የማይሰለች ድካምና ፍቅር ነው፡፡ እናንተ ባትኖሩ ‹አጭሩ› የእስር ጊዜያችን ይረዝምብን ነበር፤ ‹ቀላሏ› እስር ትከብድብን ነበር፡፡ ምስጋና ለናንተ፤ እስራችን ‹አጭር› - ፈተናችን ‹ቀላል› እንዲሆን አድርጋችሁልናልና፡፡
እናንተ ወዳጆቻችን ለሁሉም ነገር - እልፍ ምስጋና

እናመሰግናለን!
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች

የእናቴ ልጅ ነኝ!

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ (ከቤቱ)
በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ከእናቱ ወ/ሮ ዘነበች ይመኑ ጋር፡፡

እቤቴ ከገባሁ ጀምሮ ወዳጅ ዘመዶቻችን ሁሉ ‹‹እንኳን ለቤትህ አበቃህ›› እያሉኝ ነው፡፡ የ‹እንኳን ለቤትህ አበቃህ› መልዕክቶቹ ግን ብዙውን ጊዜ በተጨማሪ ምክሮች ይታጀባሉ፡፡ በነገራችን ላይ፣ በተለይ እንደኔ በዕድሜ የገፉ ወላጆች ላሉት ሰው መታሰር የሚከፋው የእነርሱ እንግልት ባሰበ ጊዜ ነው፡፡ እኔ ትልቅ ፈተና ገጥሞኛል ካልኩ፣ የእነርሱ፣ በተለይም በየሳምንቱ ‹‹አልቀርም›› እያለች የምትመላለሰው እናቴ ነገር ነው፡፡ እናም ‹እንኳን ተፈታህ› ባዮች ሁሉ የማይዘነጓት የእስር ቤት ሕመሜን፣ እናቴን ነው፡፡ ‹‹እባክህን፣ ለእናትህ ስትል እንዲህ ዓይነቱ ነገር ይቅርብህ›› ይሉኛል፡፡ 


እናቴ፣ የተወለደችው እና እስከ ዐሥራምናምን ዕድሜዋ ድረስ የኖረችው ሰሜን ሸዋ (መንዝ አካባቢ) ነው፡፡ በአካባቢው ባሕል መሠረት (አሁንም ድረስ) ሴቶችን ያለዕድሜያቸው በቤተሰብ ፈቃድ መዳር የተለመደ ነገር ነው፡፡ እናቴም ከዚህ ዓይነቱ ወግ ማምለጥ የምትችልበት ዕድል አልነበራትም፡፡ ወላጆቿ ገና በጨቅላነቷ ዳሯት፡፡ እናቴ፣ ዕኩያዋ ያልሆነውን ባሏን አልወደደችውም ነበር፡፡ በአካባቢው ባሕልና ወግ መሠረት አለመውደድ ደግሞ አይፈቀድላትም ነበር፡፡ ስለዚህ የወላጆቿን ፈቃድ ሽራ የራሷን ዕጣ ፈንታ በራሷ ለመወሰን ወሰነች፡፡ ይህ ውሳኔዋ ወላጆቿን የሚያስከፋ ብቻ ሳይሆን፣ ጭራሹኑ ተቀባይነት የማያገኝ ውሳኔ እንደሆነ አልጠፋትም፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈሪ ዕቅድ አውጥታ ተገበረችው፡፡ የልጅነት ስሟ ገበያነሽ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ያደረገችው ስሟን ወደ ዘነበች መቀየር ነው (በነገራችን ላይ በእኔና በአባቴ ስም መሐል የምጽፋትን ‹ዘ› የወሰድኩት ከሷ ስም ነው)፡፡

ከዚያም አገሯን ጥላ ኮበለለች፡፡ የኮበለለችው ደግሞ ምንም፣ ማንንም ወደማታውቅባት፣ ማንም ወደማያውቃት አዲስ አበባ ነው፡፡ ዝርዝሩ የማያልቅ ፈተና ያለበት ውጣ ውረድ ነው፡፡ የሆነ፣ ሆኖ ነፍሷን አትርፋ ራሷን አዲስ አበባ ላይ ማደላደል ቻለች፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ነበር ከአባቴ ጋር የተገናኙት፣ የተዋደዱት፣ የተጋቡት እና ልጆች ያፈሩት፡፡ ወላጆቿ በወቅቱ አዝነውባት ይሆናል፤ ነገር ግን ተጨንቀው እሷን ፍለጋ ብዙ ሲንከራተቱ እና ሲንገላቱ እንደነበርም በታሪክ ስትናገር አውቃለሁ፡፡ ሲያገኟትም ከአባቴ ትዳር ይዛ የመጀመሪያ ልጇን ወልዳ ነበር፡፡ ከመደሰት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ለእናቴም የእራሷን ሕይወት ለመምራት፣ እነርሱን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሚያስከፋ እና የሚያስጨንቅ ውሳኔ መወሰን ነበረባት፤ መጨረሻውም አስደሳች ሆኗል፡፡ መጨረሻው ምንም ሆነ ምን እናቴ የማትፈልገውን ሕይወት ‹‹እምቢ አልኖረውም›› ብላ መጀመሯ ተገቢ ነበር፡፡

እኔም የወላጆቼ ልጅ ነኝ፤ ታሪካቸውን በተለያየ ቀለም በተደጋጋሚ እየሰማሁ ነው ያደግኩት፡፡ የተሠራሁትም ከነርሱ ታሪክ እና ከሌሎችም ብዙ የሕይወት ልምዶች ነው፡፡ የናቴን እምቢተኝነት፣ የማይፈልጉትን ላለመሆን አደጋ መጋፈጥ፣ ይመጥነኛል የሚሉትን ሕይወት እስከሚገኝበት አጥናፍ ድረስ መፈለግ ተፈልፍዬ የተቀረፅኩበት ‹ሳይኮአናሊቲካዊ› ሥረ-መሠረቴ ነው፡፡ እናቴ፣ ወላጆቿን ታከብራለች፣ ትወዳለች፤ ሕይወቷን ግን ስለነርሱ አልኖረችም፡፡ እኔም በሕይወቴ የምወስዳቸውን እርምጃዎች የምረዳቸው በዚሁ ቋንቋ ነው፡፡ እናቴን እወዳታለሁ፤ ነገር ግን ‹የሱን ሕይወት ትቶ የኔን ድርሻ ይኑርልኝ› ትለኛለች ብዬ አልገምትም፡፡ ማረሚያ ቤት እያመላለስኩ ባስቸገርኳት ግዜም ይሁን ሰዎች በወቀሱኝ ጊዜ ለራሴ የምሰጠው ምክንያት ይኸው ነው፡፡ እኔ የናቴ ልጅ ነኝ፤ እራሴን የምሆነውም ከርሷ በወረስኩት ባሕሪዬ ነው፡፡

(ይህንን ጽሑፍ የጻፍኩት እናቴን አስፈቅጄ ነው፡፡)

Wednesday, October 21, 2015

በፍቃዱ ኃይሉ በዋስ እንዲወጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላለፈ

ዛሬ በልደታ ፍርድ ቤት 19 ወንጀል ችሎት የበፍቃዱን ኃይሉን የአመጽ የማነሳሳት ክስ ዋስትና መብት አስመልክቶ ባስቻለው አጭር ችሎት ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ የዋስትና መብቱ ተጠብቆ በውጪ ሆኖ አንዲከላከል ወስኗል ፡፡ በዚህ መሰረት 20,000 ብር ዋስትና እና ከአገር እንዳይወጣ እገዳ ተጥሎበታል፡፡ ለጥቅምት 27 ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠ ሲሆን በቀጠሮው በፍቃዱ መከላከያውን ያቀርባል ፡፡ በፍቃዱ የዋስትና ሂደቱን አጠናቆ በእለቱ ከእስር ወጥቷል፡፡

በተያያዘ ዜና አቃቤ ህግ 19 ወንጀል ችሎቱን ውሳኔ በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱ ተሰምቷል።

Monday, October 19, 2015

የማእከላዊ ምርመራ የማሰቃየት ምርመራ መዘዝ - በጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ላይ

የ2007 አገር አቀፍ ምርጫ መቃረብን ተከትሎ መስዋእት ከሆኑት  የዞን ዘጠኝ ጦማር አባላት ውስጥ የሽብር ክሱ ወደ ወንጀል ክስ ተቀይሮ ዛሬም በግፍ እስር በብቸኝነት የሚገኘው በፍቃዱ ዘ ኃይሉ አመጽ ለመቀስቀስ አስበህ ነው የጻፍከው የተባለውን ጽሁፍ እንዲከላከል ተወስኖበታል፡፡ ይህ የአመጽ መቀስቀስ የተባለው ጽሁፍ ራሱን ሳይሆን የበፍቃዱን የማእከላዊ ምርመራ ቃል ብቻ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ቃሉን ብቻ መሰረት በማድረግ ይከላከል በማለት የማእላዊ ምርመራን በማሰቃየት ውስጥ የተሰጠ ቃል ተቀብሎታል ማለት ነው ?

በአስገዳጅ ሁኔታ የተገኘ ማስረጃ እንደማስረጃ አይቆጠርም የሚለው የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው የሚገባለው እና በፍቃዱ ከጓዶቹ ጋር ሆኖ ይከበር! ሲል የነበረው ሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 19.5 እንዲህ ይላል

‹‹የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ  በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችልየእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነትአይኖረውም፡፡››

ከወራት በፊት የጦማርያኑን እስር አንደኛ ዓመት አስመልክቶ የመብት ጥሰቶችን ዞን ዘጠኝ ጦማር ባስታወሰበት ወቅት በበፍቃዱ የደረሰበት የማሰቃየት ወንጀል እንዲህ ገልጾት ነበር ፡፡

‹‹ማዕከላዊ ምርመራ በቆየሁባቸው ቀናት ከእሁድ በስተቀር ጠዋት ከሰአትማታ እየተጠራሁ በዛቻ በአጸያፊ ስድብ ጭካኔ የተሞላበት ግርፊያ ጥፊና እርግጫ አንዲሁም ከአቅሜ በላይ የሆነ ስፓርት እየሰራሁቃሌን እንድሰጥ ተገድጃለሁ፡፡ የተያዝክበትን ድብቅ አጀንዳ ንገረን በማለት ራሴን እንድወነጅል ተገድጃለሁ፡፡
  1. መርማሪው በመጀመሪያ ቀን ምርመራ በጥፊ መማታት የጀመረ ሲሆን እያንዳንዱን ጥያቄ ከጠየቀኝ በኋላ በጥፊ ይመታኝ ነበር
  2. የዞን9 ዓላማ ጠይቆኝ ስነግረው ድብቁን አውጣ በማለት መሬት ላይ አንድቀመጥ እና ያደረኩትን ነጠላ ጫማ እንዳወልቅ አዞኝ በኮምፒውተር ገመድ እግሬን መግረፍ ጀመረ፡፡ በተጨማሪም በሆዴአንተኛ በማዘዝ እና እግሬን አጥፌ ከፍ አንዳደርገው በማድረግ ውስጥ እግሬን ገርፎኛል፣ግርፊያው ውስጥ እግሬን ሲለበልበኝ ነበር ፡፡
  3. ድብቁን አጀንዳህን ካልተናገርክ ነገ እዘለዝልሃለሁ በሚል አስፈራርቶኛል፡፡
  4. ድምጽ እንዲያፍን ሆኖ ወደተሰራው የስብሰባ አዳራሽ ተወስጄ በጥፌ እየደበደቡኝ የዞን9አላማ ተናገር ተብዬ ተደብድቤያለሁ፡፡ ስቃዬ ሲበዛብኝም የፈጠራ ታሪክ እንዳወራ ተገድጃለሁ፡፡ እኔ የምጽፈው ኢትዮጵያ ውስጥ አብዬት ለማስነሳት ነው ብዬ እንድፈርምም አስገድደውኛል››
  5. በምርመራ ወቅት እጄ በካቴና እነደታሰረ ለሰአታት ቁጭ ብድግ አንድል ተገድጃለሁ፡፡
  6. መርማሪው በአንድ ወቅት አራት የዞን9 አባላት ሆናችሁ ስለአላማው የተወያያችሁትን በቃል መስጫው ክስ ላይ ልጽፍ ነው ሲለኝ አንደዛ አይነት ውይይት ማድረጋችንን አላስታውስም ስለው እንዴት አታስታውስም ብሎ በጥፊ መማታት ጀመረ። በተደጋጋሚ ከመደብደብም በላይ እስክስታስታውስ እዚሁ ታድራታለህ በማለት ድብደባው በመቀጠሉ አስታውሳለሁ ብዬ ተገላገልኩ ፡፡ የሰጠሁት ቃል ላይም እንደፈለገው አድርጎ ጻፈው፡፡  እኔም በድብደባ ብዛት መርማሪው አለ ብሎየጻፈውን ፈርሜያለሁ ፡፡
  7. ዞን9 ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሌለው ከሆነ ይህንን ህዝብ አንዴት ነው ነጻ የምታወጡት በሚል ሲጠይቁኝ የነጻ አውጪነት ሚና የለንም ስላቸው ከወንበሬአንድነሳ አዘዙኝ፡ ከዚያም በቆምኩበት ግራ ብብቴን እና እጄን በአንድ እጁ አንዳልወድቅ ወጥሮ ይዞ በእግሩ ጭኔን በሃይል ደበደበኝ ፡፡ ከድብደባው በማስከተል ደግሞእግሬ መሃል እግሩን በማስገባት ወደግራ እና ወደቀኝ በመምታት ተዘርጥጬ እንድቆይ በማድረግ እጄን ወደላይ አድርጌ እግሬ ግራና ቀኝ ተዘርጥጦ ( በተ<a></a>ለምዶ ስፕሊት ሚባለው) በግራ እና ከቀኝ በመደብደብ እጄን ወደላይ አድርጌ እነድመረመር ተደርጌያለሁ፡፡ከዚህ ምርመራ በኋላ ለሁለት ቀን እያነከሰኩ ነበር፡፡››
በፍቃዱ ሃሳቡን በነጻነት በመግለጹ ብቻ እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ እስካሁንለ542 ቀናት አግባብ ባልሆነ እስር ላይ ይገኛል፣ በዚህ ሁኔታ የተሰጠ ቃል ተቀባይነት ማግኘት ስለማይገባው በፍቃዱ ሃይሉእሮብ ከቤተሰቡ ጋር ሊቀላቀል ይገባል ፡፡

Saturday, October 17, 2015

ሕጉ ለበፍቃዱ ነው - ውሳኔውስ?

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ፤ 19ኛ ወንጀል ችሎት በስድስት ጦማርያን እና በሶስት ጋዜጠኞች ላይ በ08/11/2006 ዓ.ም ከፍትህ ሚኒስትር የቀረበለትን ክስ በቀን 11/11/2006 በይፋ አንብቦ ክሱን ከከፈተ ወዲህ መሰረታዊ ውሳኔ ያሳለፈው ጥቅምት05/2008 ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይሄውም ክሳቸው በሰኔ 30/2007 ተቋርጦ ከተፈቱት ሶስት ጋዜጠኞች እና ሁለት ጦማርያን ውጭ ክሳቸው ቀጥሎ ከነበሩት አምስት የዞን ዘጠኝ ጦማርያን መካከል አራቱ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱና ከጦማርያኑ መካከል በፍቃዱ ሃይሉ ግን የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ተጠቅሶበት የተከሰሰው ክስ ተሰርዞ በመደበኛው ወንጀል ሕግ አንቀፅ 257/ሀ መሰረት‹‹[ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል የመናድ ወንጀል] … እንዲፈፀም ለማድረግ … በንግግር፣ በሥዕል ወይም በፅሁፍ አማካይነት በግልፅ የመቀስቀስ ወንጀል ክስ›› በሚል ተሻሽሎ ክሱን እንዲከላከል ብይን መስጠቱ ነው፡፡
ነፃ የተባሉትና በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት አቤል ዋበላ፣ አጥናፉ ብርሃኔና ናትናኤል ፈለቀ ምንም እንኳን ፍርድቤቱ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም ይህ ፅሁፍ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ አልተፈቱም፡፡ አቃቤ ሕግ እግድ አስወጥቶ ይግባኝሊጠይቅባቸው ይችላል የሚል ከፍተኛ ግምትም በብዙዎች ዘንድ አድሯል፡፡ ይሄም በትናንትናው እለት በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ‹የነፃናቸው› ውሳኔ ትርጉም አልባ የሚያደርግና የጦማርያኑንም ሕገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ ተግባር ከመሆን አይዘልም፡፡ (ይሄን ጉዳይበሚመለከት ሌላ ፅሁፍ ይዘን እንወጣለን)፡፡
በዚህ ፅሁፍ ለማየት የተሞከረው ግን ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ‹ተከላከል› ስለተባለበት ጉዳይ እና ለረቡዕ ጥቅምት10/2008 ለዋስትና ጉዳይ ስለተቀጠረው ጉዳይ ነው፡፡ በፍቃዱ የሚከላከለው ምኑን ነው የሚለውን የፍሬ ነገር (substantive)ጉዳይ በዚህ ፅሁፍ ለማየት አልተሞከረም፡፡ ይልቁንም የበፍቃዱ የዋስትና ጥያቄ ምላሽ ምን መሆን አለበት? እና በፍቃዱ የተከሰሰበት የሕግ አንቀፅ ምን ይነግረናል? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ ፅሁፍ ነው፡፡

ዋስትና ሕገ መንግስታዊ መብት ነው?

አዎ! የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በአንቀፅ 19 ላይ የተያዙ ሰዎች መብት ሲደነግግ፤ ንዑስ አንቀፅ 6 ላይ እንዲህ ይላል፡
የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ ይችላል፡፡
ለመሆኑ በአንቀፁ እንደ ልዩ ሁኔታ (exception) ፍርድቤቱ ዋስትና ላለመቀበል የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

ዋስትና በኢትዮጵያ ሕግ በምን አግባብ ነው የሚፈቀደው? የሚከለከለውስ?

አንድ ሰው የተከሰሰበትን የወንጀል ክስ ከእስር ቤት ውጭ ሆኖ መከታተል ይችል ዘንድ እና ጥፋተኛ ላልተባለበት የወንጀል ድርጊት ታስሮ መቆየት ስለሌለበት ዋስትና ከታሰሩ ሰዎች መብቶች አንዱና ዋነኛው በመሆን ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ይህ ህገ መንግስታዊ መብት ለሁሉም ተከሳሾች እንዲሁ (for granted) የሚሰጥ አይደለም፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያ ሕግ ዋስትና የሚያስፈቅዱ (bailable)እና ዋስትና የሚያስከለክሉ (non-bailable) ወንጀሎች በተለያ ቦታዎች በግልፅ ተደንግገዋል፡፡ ዋስትና በመርህ ደረጃ የሚያስከለክሉ ወንጀሎች ምን አይነት ናቸው? የሚለውን ስንመለከት፤ በመጀመሪያ የምናገኝው የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር63ን ሲሆን፣ በዚህ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር 1 መሰረትም፡

ማንኛውም የተያዘ ሰው የተከሰሰበት ወንጀል የሞት ቅጣትን ወይም አስራ አምስት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ፅኑ እስራት የማያስቀጣው ከሆነና ወንጀል የተፈጸመበት ሰው በደረሰበት ጉዳት የማይሞት የሆነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ወረቀት አስፈርሞ ለመልቀቅ ይችላል፡፡
  ይህ ለሁሉም የወንጀል አይነቶች የሚሰራ መርህ ሲሆን አንድ ሰው የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት ከአስራ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት በላይ የሚያስቀጣው በሆነ ጊዜ እና ወንጀል የፈፀመበት ሰው የሞተ እንደሆነ የዋስትና መብቱን ይነፈጋል ማለት ነው፡፡ከዚህ አጠቃላይ መርህ ባለፈ በተለያዩ ህጎች ላይ ዋስትና በመርህ ደረጃ ተከልክሎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህም መሰረት በተሻሻለው የጸረሙስና ልዩ ስነ ስርአትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀፅ 4 መሰረት የሙስና ወንጀል አስር ዓመትና ከዛ በላይየሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትና ያስከለክላል ፡፡ እንዲሁም የሽብርተኝነት ወንጀልም በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ20 መሰረት ዋስትና የማያሰጥ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ እንግዲህ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የሕግ ስርዓት የዋስና መብት በመርህ ደረጃ የሚከለከለው በነዚህ ሶስት ሁኔታዎች ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

ይህ ማለትም በመርህ ደረጃ ዋስትናን ከሚከለክሉት የሕግ ድንጋጌዎች ውጭ ያሉ ሌሎች የወንጀል ክሶች ዋስትና የሚያስፈቅዱ(bailable) ናቸው ማለት ነው፡፡ እዚህም ላይ ግን ሌላ እቀባ አለ - የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ67፡፡ በዚህ የስነ ስርዓት ሕጉ አንቀፅ መሰረት አንድ ሰው የተከሰሰበት ወንጀል በመርህ ደረጃ ዋስትና የማያስከለክል ቢሆንም (ማለትም ከአስራ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት በታች የሚያስቀጣ ቢሆንም፣ ከአስር ዓመት በታች የሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል ቢሆንም፣ ከሽብርተኝነት ወንጀል ውጭ ቢሆንም) ፍርድ ቤቱ በሶስት የተለያዩ ምክንያቶች ተከሳሹን ዋስትና ሊከለክለው ይችላል፡፡ ይሄውም፡
  1. መጥፋት (Disappearance)፡ተከሳሹ በዋስትና ቢወጣ ይጠፋል ተብሎ ሲገመት፣
  2. ማጥፋት (Commits another offense)፡ ተከሳሹ በዋስና ቢወጣ ሌላ ወንጀል ይፈፅማል ተብሎ ሲገመትና፣
  3. አሁንም ማጥፋት (Witness Interference)፡ ተከሳሹ በዋስትና ቢወጣ ምስክሮች ላይ ጫና ይፈጥራል፣ ሌሎች ማስረጃዎችንም ያጠፋል ተብሎ ሲገመት ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ምንም እንኳን ተከሳሹ የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት በመርህ ደረጃ ዋስትና የማያስከለክል (bailable) ቢሆንም ከነዚህ ሶስት ምክንያቶች አንዱ አለ ብሎ ካመነ ተከሳሹን ፍርድ ቤቱ ዋስትና ሊከለክለው ይችላል፡፡  

የበፍቃዱ የዋስትና ጉዳይ

እንግዲህ በመግቢያችን እንዳነሳነው ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ተከሶበት የነበረው የሽብርተኝት ወንጀልን ለመፈፀም ማቀድ፣ ማነሳሳት፣ መሞከር፣ መዘጋጀትና ማሴር ክስ ውድቅ ተደርጎ በፃፋቸው ፅሁፎች ‹‹[ሕገመንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል የመናድ ወንጀል]… እንዲፈፀም ለማድረግ … በንግግር፣ በሥዕል ወይም በፅሁፍ አማካይነት በግልፅ የመቀስቀስ ወንጀል›› ፈፅመሃል፣ ክሱንም ተከላከል መባሉን አይተናል፡፡ ታዲያ በፍቃዱ አሁን ተከላከል የተባለበትየወንጀል ክስ በፍቃዱን የዋስትና መብት ያስከለክለዋልን? ከላይ ካነሳናቸው አጠቃላይ የኢትዮጵያ የዋስትና ሕግ መርሆዎች አንፃር እንመልከት፡፡

የቀረበበት ክስ Bailable ነው ወይስ Non-bailable?
Bailable ነው፡፡ ምክንያቱም፡

 አሁን በፍቃዱ ተከላከል የተባለበት የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257 በአጠቃላይ የሚያስቀጣው ከአንድ ቀን እስከ አስር ዓመት ፅኑ እስራት ሲሆን፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‹‹…ግልፅነትና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መልኩ ውጤታማና ተገማችነት ያለው ቅጣት የሚሰጥበትን ስርዓት…›› ለመመስረት በማሰብ በጥቅምት 2006 ዓ.ም ያወጣው የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 02/2006 አንቀፅ 9 ላይ በማያሻማ ሁኔታ እንደደነገገው ደግሞ በፍቃዱ ሃይሉ የተከሰሰበት የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257/ሀ ማለትም አጥፊው ድርጊቱን በንግግር፣ በስዕል፣ ወይም በፅሁፍ አማካኝነት በግልፅ የቀሰቀሰ እንደሆን የእስራት ቅጣቱ ሁለት እርከን ነው ይላል፡፡ ይሄም ማለት በመመሪያውአባሪ አንድ ላይ አንደተገለፀው እርከን ሁለት የሚያስቀጣው ከአስርቀን እስከ ስድስት ወር እስራት ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በፍቃዱ ጥፋተኛ እንኳን ቢባል ሊቀጣ የሚችለው ከፍተኛ ቅጣት የስድስትወራት እስራት ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ በፍቃዱ የተከሰሰበት ወንጀል ከ15 ዓመት ፅኑ እስራት በላይ የሚለውን የመከልከያ መርህ አያሟላም፡፡
በበፍቃዱ ላይ ተመስርቶ የነበረው ‹የሽብርተኛ ድርጅት በማቋቋም የሽብርተኝነት ወንጀልን ለመፈፀም ማቀድ፣ ማነሳሳት፣ መሞከር፣ መዘጋጀትና ማሴር› ክስን ፍርድ ቤቱ ‹ዞን ዘጠኝ የሽብርተኛ ድርጅት አይደለም የጦማርያን እና የአራማጆች ቡድንእንጂ› በማለት በብይኑ በግልፅ ውድቅ ስላደረገው፤ የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉ ከዚህ በኋላ በበፍቃዱ ላይ ተፈፃሚነት የለውም፡፡
 ሶስተኛውና በኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ ዋስትና የሚያስከለክለው የወንጀል አይነት ከአስር ዓመት ፅኑ እስራት በላይ የሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል (grand corruption) ሲሆን፤ የበፍቃዱ ክስደግሞ ከሙስና ወንጀል ጋር ፈፅሞ ግንኙነት የሌለው ነው፤
በአጠቃላይ በመርህ ደረጃ በፍቃዱን ዋስትና ሊያስከለክል የሚችል ምንም አይነት የህግ አግባብ የለም፡፡

መርሁ ሲፈቅድ፤ ዳኝነቱ ይከለክለዋልን?
በፍፁም ሊከለክለው አይችልም፡፡ ምክንያቱንም እንመልከት፡፡
በኢትዮጵያ ሕግ ዋስትና በመርህ ደረጃ ተፈቅዶ በዳኞች ስልጣን (discretionary power) ሊከለከል የሚችልባቸውሶስት ምክንያቶች የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 67 መደንገጉን ከላይ ተመልክተናል፡፡ የበፍቃዱን ጉዳይም ከዚህ አንፃር ስንመለከት፡

  1. ‹ይጠፋል› ፡ ተከሳሾች ይጠፋሉ ተብለው የሚገመቱት በተከሰሱበት ድርጊት ጥፋተኛ ከተባሉ ውሳኔው የሚያስከትልባቸውን እስር ለማምለጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በፍቃዱ የተከሰሰበት የሕግ አንቀፅ (የወንጀል ሕጉ አንቀፅ257/ሀ) ሊያስቀጣ የሚችለው ከአስር ቀናት እስከ ስድስት ወራት እስራት ብቻ ሆኖ እያለ በፍቃዱ ደግሞ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በላይ በእስር ላይ ያለ ነው፡፡ ይሄም መታሰር ከሚገባው ከእጥፍ በላይ ታስሯል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ለምን ይጠፋል?
  2. ያጠፋል ፡ ተከሳሹ ቢፈታ ሌላ ጥፋት ያጠፋል ተብሎ ሲገመት ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ዋስትና ሊከለክለው ይችላል፡፡ ይህ ክልከላ በዋናነት ለደጋጋሚ ወንጀለኞች (recidivists) የተደነገገ ነው፡፡ በፍቃዱ እንኳን ደጋጋሚ ወንጀለኛ ሊሆን በሕይወት ዘመኑ አንድም ክስ ተመስርቶበት የማያውቅ መልካም ጠባይ ያለው ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ቢፈታ ሌላ ወንጀል ሊፈፅም ይችላል የሚለው መከልከያ በፍፁም እሱ ላይ አይሰራም፡፡
  3. አሁንም ያጠፋል ፡ ሌላው ዋስትና ሊያስከለክል የሚችለው ምክንያት ተከሳሽ ከእስር ቢፈታ እሱ ላይ ሊቀርቡ የሚችሉ ምስክሮችን እና ሌሎች ማስረጃዎችን ያጠፋል ተብሎ ሲገመት ነው፡፡ በፍቃዱ ላይ ደግሞ ዓቃቤ ህግ አለኝ ያለውን ሁሉ ማስረጃ አሰምቷል/አቅርቧል፡፡ ሊጠፋ የሚችል ምንም ነገር የለምና እሱ ላይ ይሄ ምክንያት እይሰራም፡፡

በአጠቃላይ በፍቃዱ ሃይሉ የተከሰሰበት ወንጀል በመርህም ሆነ በዳኝነት ደረጃ ዋስትና ሊያስከለክል የሚችል አንዳችም ሕጋዊ ምክንያት የለውም፡፡ እንዲያውም የዋስትና መብቱን የሚከለክል አንዳችም ሕጋዊ ምክንያት ካለመኖሩም ሌላ የበለጠ የዋስትና መብቱን መከበር የሚገፋ ምክንያት አለ፤ ይሄውም በኢትዮጵያ ህግ አንድ ሰው ያላግባብ ለታሰረበት የእስር ጊዜ ካሳ የሚያስከፍል ስርዓት በሌለበት እና በፍቃዱ ደግሞ ጥፋተኛ እንኳን ቢባል ሊታሰር ከሚችለው ከአስር ቀናት እስከ ስድስት ወራት እስራት ከእጥፍ በላይ ታስሮ እያለአሁንም ዋስትና በመከልከል ሌላ ተጨማሪ እስር እንዲታሰር ማድረግ እጅጉን ኢፍትሃዊነት ከመሆኑም በላይ የወንጀል ህግ መርሆዎችን በሙሉ የሚገረስስ በመሆኑ ነው፡፡

257 - ያልተዘመረለት ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ጠላት

በፍቃዱ ሃይሉን ዋስትና ሊያስከለክል የሚችል አንዳችም ህጋዊ ምክንያት አለመኖሩን ከላይ ተመልክተናል፡፡ በዚህም መሰረት በፍቃዱ መብቱ ተከብሮለት በቀላል ዋስትና እንደሚወጣ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ይሄን ፅሁፍ ከመቋጨታችን በፊት አሁን በፍቃዱ ተከላከል ስለተባለበት የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257 ትንሽ ነገር ብለን እንጨርስ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት ስድስት ዓመታት የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን አዋጅ ቁጥር 652/2001 ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለመደፍጠጥ እየተጠቀመበት እንደሆነ ከተለያዩ አካላት ትችት እየተሰነዘረበት ይገኛል፡፡ የተለያዩ ጋዜጠኞች እና ፀሃፊዎችም የዚህ አዋጅ ሰለባ መሆናቸው በየቀኑ የምናየው እውነታ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ አዋጅ ባለፈ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መደበኛውን የወንጀል ሕግ እንደገና ወደመጠቀሙ ያዘነበለ ይመስላል፡፡ ዋነኛው የህግ አንቀፅ ደግሞ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257 ነው፡፡

ይህ የሕግ አንቀፅ ተጠቅሶ ነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የሶስት አመት እስራት የተፈረደበት (ጥቅምት 2007)፣ይህ የሕግ አንቀፅ ተጠቅሶ ነው ማስተዋል አሳታሚ ድርጅት የአስር ሺህ ብር  የገንዘብ ቅጣት ተቀጥቶ የተዘጋው ፣ ይህ የሕግ አንቀፅ ተጠቅሶ ነው የአዲስ ጉዳይ መፅሄት ስራ አስኪያጅ እና ጋዜጠኛ እንዳልካቸው ተስፋዬ ላይ የሶስት ዓመት ከሶስት ወራት እስራት የተፈረደበት (መስከረም 2007)፣ ይህ የሕግ አንቀፅ ተጠቅሶ ነው የሎሚ መፅሄት ዋና ስራ አስኪያጅና ጋዜጠኛ ግዛው ታየ ላይ የሶስት ዓመት ከሶስት ወራትእስራት የተፈረደበት (መስከረም 2007)፣ ይህ የሕግ አንቀፅ ተጠቅሶ ነው የፋክት መፅሄት ስራ አስኪያጅ ፋጡማ ኑሪያ ላይ የሶስትዓመት ከአስራ አንድ ወራት እስራት የተፈረደባት (መስከረም 2007)፣ ይህ የሕግ አንቀፅ ተጠቅሶ ነው የቀድሞው የዕንቁ መፅሄትዋና አዘጋጅና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ላይ ክስ ተመስርቶበት በአሁኑ ወቅት ክሱን እየተከታተል የሚገኘው … አሁን ደግሞ በፍቃዱ ሃይሉ በፃፋቸው ፅሁፎች ምክንያት ይህ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257 ተጠቅሶበት ተከላከል ተብሏል፡፡ የበፍቃዱን ከሌሎች ለየትየሚያደርገው በአንቀፁ ቀላል ቅጣት (ከአስር ቀናት እስከ ስድስት ወራት ብቻ) የሚያስከትለው አንቀፅ 257 ንዑስ አንቀፅ ‹ሀ› የተጠቀሰበት መሆኑ ነው፡፡

እንግዲህ ይህ የሕግ አንቀፅ ነው የቅርብ ጊዜ ሃሳብን ከመግለፅ ነፃነት ጋር በተያያዘ እየቀረቡ ላሉ ክሶች ዋነኛ መሰረትእየሆነ ያለው፡፡ በፍቃዱ ሃይሉም የቅርቡ አንቀጽ ሰለባ ነው፡፡
በፍቃዱ ሃይሉ 

Friday, October 16, 2015

ከዞን ዘጠኝ የተሰጠ መግለጫ

በዛሬው ዕለት የልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ፩ኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ፪ተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ሃይሉ ፫ተኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ ፭ተኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃኔ እና ፯ተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ ተጠርጥረው ከነበረበት የሽብርተኝነትና የኅብረተሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ የመጣል ክስ ነጻ መውጣታቸውን በበጎ መልኩ የምንቀበለው ቢሆንም 
  1. ፪ተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ሃይሉ በሃይል ተገዶ ማዕከላዊ ምርመራ ውስጥ በማሰቃየት ስር የሰጠው ቃል ተቆጥሮ አመጽን በማነሳሳት ወንጀል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 257 መሰረት አንዲከላከል መባሉን አጥብቀን እንቃወማለን ፡፡ 
  2. ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ከአንድ አመት ከአምስት ወር በላይ በእስር የቆዬት የዞን9 ጦማርያን የመፈቻ ወረቀት ከችሎቱ መጠናቀቅ በኋላ በአስቸኳይ በፍርድ ቤቱ አማካኝነት ተጽፎ ለማረሚያ ቤቱ ተወካይ ቢሰጥም ማረሚያ ቤቱ እስከ አርብ የስራ ሰዓት መጠናቀቂያ ድረስ መፈቻው አልደረሰኝም በሚል ሰበብ ሶስቱን ጦማርያን በእስር ማቆየቱን አስጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ 
ይህ ተግባር ከዚህ በፊት እንደታየው ሁሉ አቃቤ ህግ ለይግባኝ ጊዜ አንዲገዛ ከማረሚያ ቤቱ የሚደረግለት የጓሮ ትብብር አንዳይሆን እጅግ ከፍተኛ ስጋት አለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለመደው የፍርድ ቤቶችን ስልጣን ዝቅ አድጎ የማየት እና የማረሚያ ቤቶች የእጅ አዙር ፍርድ ሰጪነት ማሳያም ነው ፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት አንደታየው በአደባባይ በሕግ አግባብ የተሰጠን ነጻነት በጓሮ ከሕግ ውጪ ሊነጠቅ የሚችልበት ከፍተኛ ስጋት አሁንም የዞን9 ጦማርያን ፊት ተጋርጧል ፡፡
539 ቀናት ያለአግባብ እስር መቆየታችን ሳያንስ በራሱ መቆም የማይችል እና ምንም ማስረጃ ያልቀረበበትን ክስ አቃቤ ሕግ በጓሮ ከማረሚያ ቤት ጋር በመመሳጠር የመንፈግ ሌላ ተጨማሪ ግፍ አንዳይሰራብን አጥብቀን እንጠይቃለን ፡፡

ስለሚያገባን አንጦምራን!
ዞን9

የዛሬውን ችሎት አስመልክቶ ከዞን9 ጦማር የተሰጠ ማስታወሻ

ዛሬ ጥቅምት 5 2007 በዋለው ችሎት አንድ አመት ከ5 ወር እስር ቤት የቆዪት አራት የዞን9 ጦማርያን ላይ ውሳኔ አስተላልፏል።
በውሳኔው መሰረት አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ መከላከል ሳያስፈልጋት ከክሱ ነፃ
ሶስተኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ መከላከል ሳያስፈልገው ከክሱ ነፃ
አምስተኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃኔ መከላከል ሳያስፈልገው ከክሱ ነፃ
ስድስተኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ መከላከል ሳያስፈልገው ከክስ ነፃ የተባሉ ሲሆን
ሁለተኛ ተከሳሽ ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ከሽብር ክስ ነፃ የተባለ ሲሆን መአከላዊ ምርመራ በሃይል እና በማሰቃየት የሰጠው ቃል ላይ አመፅ እንዳነሳሳ አምኗል በሚል በወንጀል ህጉ 257 መሰረት እንዲከላከል ግን ዋስትና መጠየቅ እንደሚችል ተገልፇል።
የጦማርያኑ ጠበቃ በፍቃዱ ይግባይ እንዲሰጠው የጠየቁ ሲሆን አቃቤ ህግ ተቃውሞ አሰምቶ ይግባኙ ላይ ለጥቅምት 10 ለማየት ቀጠሮ ሰጥቷል።
ባለፉት 1 አመት ከ5 ወራት በማንኛውም በቻላችሁት አቅም ሁሉ ከጎናችን ለቆማችሁ ከፍተኛ ምስጋና እያቀረብን በፍቃዱ ይፈታ የሚለው ጥያቄያችን እንደሚቀጥል ለማሳወቅ እንወዳለን።
የዞን 9 ጦማርያን ከማረሚያ ቤት ሲወጡም የምናሳውቅ ይሆናል።
‪#‎FreeBefekadu‬ ‪#‎Ethiopia‬
እልፍ ምስጋና ለዞን9 ነዋርያንና ወዳጆች
ስለሚያገባን እንጦምራለን!
ዞን9

Thursday, October 8, 2015

ጦማርያኑ ለውሳኔ በድጋሚ ለጥቅምት 5/2008 ዓ/ም ተቀጠሩ

በዛሬው ዕለት በነሶልያና የክስ መዝገብ በዞን ዘጠኝ ጦማርያን ላይ ማለትም በሶልያና ሽመልስ በሌለችበት፣ አቤል ዋበላ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና በፍቃዱ ኃይሉ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ችሎት ዳኞች አዳማ ስልጠና ላይ ናቸው በሚል ባለመገኘታቸው ምክንያት ለጥቅምት 5/2008 ዓ/ም ቀጠሮ መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በእስር 531ኛ ቀናቸውን እያሳለፉ የሚገኙት ጦማርያኑ ይህ የፍርድ ቤት ቀጠሮአቸው ለ38ኛ ጊዜ የተሰጣቸው ነው ፣ ጥፋተኛ ናቸው ወይም አይደሉም የሚለውን ውሳኔ ለማሰማት ፍርድ ቤት የዛሬውን ጨምሮ ለ5ኛ ጊዜ የተሰጠ ቀጠሮ ነው፡፡

ስሜት የማይሰጡ ክሶች እና የተራዘሙ የፍርድ ሂደቶች ዜጎችን በአገራቸው የበለጠ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጋቸው ከመሆኑም በላይ ያለዋስትና በፍርሃት እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው፣ ይህ እንዲሆን ካልተፈለገ በቀር በቀጠሮዎች መራዘም ንጹሃንን ጥፋተኛ ማድረግ አይቻልም፡፡

ባልተፈጸመ ወንጀል፣ ባልቀረበ ማስረጃ ዜጎችን ማንገላታት ይቁም፡፡


Tuesday, October 6, 2015

ናት

‘The First 100 Days’ለተፈቺም ይሆናል እንዴ ናት? ‹የመጀመሪያዎቹ መቶ የፍቺ ቀናት› ብዬ ብፅፍስ? ብዬ ራሴን እጠይቅና፤ 400 ቀናት ብቻ ታስሮ ሰለ100ቀናት መፃፍ ጉራ መስሎ ሲታየኝ ጊዜ እተወዋለሁ፡፡ ዛሬ ግን ያንተ ልደት ነውና እስኪ የአጭር አጭር ማስታወሻ ልፃፍ ብየ መጣሁ፡፡
ናት! ዛሬ ከታሰርክ 529ኛ ቀንህ ነው፡፡ ይሄን የምነግርህ እዛ እስር ቤት ቀኑን እንደማትቆጥር ስለማውቅ ነው፡፡ የታሰሩበትን ቀን መቁጠር ለእስረኛ ‹እስሩን ያከብድበታልና› ቀን አይቆጠርም አይደል? እኔ ግን ይሄው ‹የሆደ ሰፊነቱ› ተጠቃሚ በመሆን የታሰሩበትን ቀን ከማይቆጥሩት እስረኞች ተርታ ወጥቼ‹ከነፃዎቹ› ቀን ቆጣሪዎች ተርታ ተሰልፌያለሁ፡፡ ለኔ ‹ሆደ ሰፊ› (magnanimous) የሆነ አሳሪ-ፈቺ አንተና ሌሎች ጓደኞች ላይ ይሄ ‹ሆደ ሰፊነት› አልታይ ማለቱ እንዲሁ ሁሌ ያስገርመኛል፡፡
ናት! ‹ሆደ ሰፊው› እየተጫወተ ያለው ጨዋታ ‹አይጥ ነሽ? እዩት ክንፌን፤ ወፍ ነሽ? እዩት ጥርሴን› አይነት ሁኖ ሲያስቀኝ ይውላል፡፡ ‹‹ያለወንጀላቸው ነው ያሰርካቸው ፍታቸው? እሱ በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ነው፤ ግማሾቹን ፈተህ ግማሾቹስ? እሱ የመንግስት ልዕልናና ሆደ ሰፊነት ነው›› እያለ የማይበርበትን የዶሮ ክንፉን ያራግባል፣ የማያኝክበትን denture ጥርሱን ያገጣል፡፡ የዚህ ጨዋታና ሕመም ዋነኛ ተጠቂ መሆንህ ሁሌም ያንገበግበኛል፡፡ ግን ምን ይደረግ?
ናት! እነዚህን ሁሉ ቀናት ለምን በእስር እንዳሳለፍክና እያሳለፍክ እንደሆነ ለመግለፅ እንኳን እኔ አሳሪህ እንኳን የሚችል አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ከሰውየው ወስደን፤‹ወጣትነት ጥሩ ነው፡ ቢገሉህም አትሞትላቸውም፣ ቢያስሩህም ሕሊናህን ነፃ ታወጣዋለህ› እንላቸዋለን እንጅ አንሞትም! አንታሰርም!
ናት! ቅንነት ዋጋ እንደሚያስከፍል ካንተ በላይ ምን ምሳሌ ይኖራል? እጆችህ መንቀሳቀስ እስኪያቅታቸው ድረስ ከፍ አድርገህ በቅጣት ውስጥ ‹ምርመራ› ላይ የቆየህባቸው የማዕከላዊ ሌሊቶች ስለቅንነት ምንም የማያውቁ ግዑዛን ነበሩ ለካ?! እነዛ ‹Made in England› የተፃፈባቸውን እጀ ሙቆች ቅንነትህ እንዴት እንዳልበጠሳቸው ይገርመኛል፡፡ እነዛን ማጎሪያዎች ከብበው የቆሙት የእስር ቤቱ አጥሮች ስለቅንነትህ ሲባል አለመፍረሳቸው፤‹ለካ ቅንነት አቅመ ቢስ ነው› ያስብሉኛል፡፡ ቅንነትህ ‹የሆደ ሰፊውን› ልብ አለማራራቱ ‹ይሄ ሆደ ሰፊነት እንዴት ነው?› ያስብለኛል፡፡ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር ቅንነትህ ከተቀመጥክበት ዛሬም እያስነሳ በዝምታ ያስቆምሃል፤ ቅንነትህን የሚያይ የሚሰማ የለም አንጅ፡፡
ናት! ሁሌም ተይዘህ በታሰርክበትቢሮ በር ሳልፍ ‹እዚህ በጣም ቅንና ደግ ወንድም ነበር› እላለሁ፡፡ እንዳንተ ያለ ሰራተኛን ከስራው፣ ነጋዴን ከንግዱ፣ አሳ አስጋሪን ከባህሩ… አንስቶ እስር ቤት የሚጥል ጊዜ ነውና ለጊዜው ከሀዘን በላይ ምን እንላለን? ተስፋ ግን ሁሌም የኛው ነች፡፡
ናት! ያንተን ግጥም ጠቅሼ ልሰናበትህ፡፡አዎ! ያችን በ17 ዓመትህ ፅፈሃት ቤትህ ሲፈተሸ የልጅነት ደብተርህ ውስጥ የተገኝችውን አሁን አንተ ላይ በዋነኛ የሰነድ ማስረጃነትየቀረበችውን በከሳሽ አገላለፅ ‹አንድ ገፅ የሽብር ሰነድ› እኮ ነው የምልህ፡፡ እንዲያውም ይሄው ልጥቀስልህ፡

‹ኢትዮጵያ እንድታድግ፣ ረሃብ እንዲጠፋ፤
መንግስት ያስፈልጋል፤ ላገሩ ‘ሚለፋ፡፡›
መቼም ዛሬ 28ኛ ዓመትህን ስታከብርከአስራ አንድ ዓመት በፊት የፃፍካትን ግጥም መጥቀሴ ነውር የለውም አይደል፡፡ እንዲያው ዘንድሮ ‹7.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ተርበዋል›ብሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መግለጫ ማውጣቱን ለመግለፅ ያክል ነው፡፡ ‹…ብንናገር እናልቃለን› ሁኖብኝ ነው ዳር ዳሩን መዞሬ፡፡
ናት! ሁሌም በተስፋ መልካም ዜናንእናፍቃለሁ፡፡

መልካም ልደት ወንድሜ!

በኋላ በባቡር መጥቼ የምጠይቅህወንድምህ - ዘላለም
Natnael Feleke