Monday, June 16, 2014

በዞን 9 ጦማሪያንና በጋዜጠኞቹ 4ኛ የፍ/ቤት ውሎ ላይ ያለኝ የህግ አስተያየት 2


 በእዩብ መሳፍንት 

ጦማርያንን እና ጋዜጠኞችን ጉዳይ ለማየት የተሰየመው ችሎት ለ4ኛ ግዜ የተቀጠረው ፖሊስ ምርመራዬን አልጨረስኩም፤ ያልተያዙ ግብራበሮቻቸው አሉ፤ እንዲሁም ማስረጃዬን አጠናቅሬ አልጨረስኩም በማለቱ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩት ሁሉም ቀጠሮዎች ፖሊስ ለተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ በምክኒያትነት ያቀረበው እነዚሁኑ ምክኒያቶች ነበር፡፡

ከሶስተኛው ቀጠሮ ጀምሮ ክሱ ወደ “ሽብርተኝነት” የዞረ በመሆኑ ጉዳያቸውና የቀጠሮ አሰጣጡ በዚሁ ህግ መሰረት መካሄድ አለበት፡፡ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 20/3/ መሰረት ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ የ28ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ሊሰጠው እንደሚችልና ይህ ግዜም በድምሩ ከ4 ወር ሊበልጥ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ የዚህ አንቀፅ ዋናው አላማውም ለፖሊስ በቂ የምርመራ ጊዜ መስጠትና ተጠርጣሪውም እንዳይጎዳ የፖሊስን የምርመራ ጊዜ መገደብ ነው፡፡
ፖሊስ የጠረጠረው ወንጀል ምንም ያህል ውስብስብ ቢሆን ከ4 ወር በላይ ሊፈቀድለት አይችልም፡፡ እስከዛሬ ቀን ድረስ ጓደኞቻችን ለ52 ቀናት የታሰሩ ሲሆን ፖሊስ ግን በነዚህ ቀናት ይህን ሰርቻለሁ ያለው አንድም ነገር የለም፡፡ አንድ አይነት ምክኒያት በመስጠት ብቻ ይጠይቃል ፍ/ቤቱም ይፈቅዳል፡፡ ባሁኑ ችሎት ለየት የሚለው ነገር ዳኛዋ ለፖሊስ ቀጠሮውን የሰጡት ከከባድ ማስጠንቀቅያ ጋር መሆኑ ነው፡፡ (ግዴላችሁም ሴት ዳኞች ሳይሻሉን አይቀሩም)


 
ፖሊስ የሽብር ህጉን አላማ በማሳት የምርመራ ጊዜውን በአግባቡ እየተጠቀመበት አለመሆኑን ከዚህ በላይ ማሳያ አያስፈልግም፡፡ በተደጋጋሚ ቀጠሮዎች አንድ አይነት የማይረባ ምክኒያት በማቅረብ ቀጠሮ ማራዘምን መጠቀም የክሱን ፓለቲካዊነት ያጎላዋል፡፡ ለዚህ ነው የፍትህ አካላት ፖሊስን ጨምሮ ከገዢው ፓርቲ ተፅኖ ነፃ አይደሉም የምንለው፡፡ የገዢዎችን ፊት እያየ የሚሰራ የፍትህ አካል መቼም ገለልተኛ ስራ መስራት አይችልም፡፡ ኢህአዲግም ከሀገር አንድነት በመቀጠል በእምብርክክ ያስኬደው እና ለፓለቲካዊ ጥቅሙ እየተጠቀመበት ያለው የፍትህ ስርአቱን ነው፡፡

የሆነው ሆኖ ፖሊስ በማይረባ ምክኒያትም ቢሆን ባቀረበው ጥያቄ ሌላ የ28 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡ የሰው ክብር እና ሉአላዊነት (autonomy) በረከሰበት ሀገር የ28 ቀናት ተጨማሪ እስር ምንም ላይመስል ይችላል፡፡ ምክኒያቱም እውነተኛውን ነፃነት በተመለከተ እኔና የዞን ዘጠኙ አጥናፍ ሁለታችንም ታሳሪዎች ነን፡፡ የእስር ቤቱ ስፋት እና ያለንበት ዞን ቢለያይም፡፡
ከምሬቱ ወደ ህግ አስተያየቱ ስመለስ ፍ/ቤቱ የዛሬ 28ቀንም በዚሁ ሰንካላ ምክኒያት ተጨማሪ የግዜ ቀጠሮ አይሰጥም የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኔም ገራም የሆነውን የጠበቃ አምሀን ቃል ልዋስና ሂደቱን በሚመለከት

“ብሩህ ነገር ይታየኛል ለማለት ባለመቻሌ አዝናለሁ”

ከአምባገነን ስርአት ፍትህን መጠበቅ ሞኝነት ነውና፡፡ ኢህአዴግ ማሰር እንጂ መፍታት የሚያስችል የሞራል የበላይነት የለውም፡፡ ተፈጥሮውም አይፈቅድለትም፡፡
ብዙ ወገኖች ጥሩ ዜና ጠብቀው ፍ/ቤት መገኘታቸውን ሳይ አዝኛለሁ ለእኔ የዋህነት እና የስርአቱን ባህሪይ ጠንቅቆ አለማወቀ ነው፡፡ በሚቀጥለውም ከዚህ የተሻለ ነገር ይጠበቃል ብየ አላስብም፡፡ የዚህን የአምባገነን ስርአት ባህሪ የታሰሩ ጦማሪያኑም በሚገባ ያውቁ ነበር፡፡ እኔ ጀግኖች ናቸው የምላቸው የሚደርስባቸውን እያወቁ ይህንን መንገድ በመምረጣቸው ነው፡፡
ውጤ ቱ ምንም ይሁን ምን አሁንም ቢሆን ጩኀታችንን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ዝም የሚያስብል ህሊና የለንምና፡፡ 

ማስታወሻ
በመጨረሻም ፅሁፉ በብስጭት፤ በቁጭት፤ በንዴትና እና በአቅም ማጣት የተፃፈ ስለሆነ ከህጉ ይልቅ በፖለቲካ ላይ ካተኮርኩ አትዘኑብኝ፡፡ (ለነገሩ ጉዳዩን ቀድሞ የቀላቀለው ራሱ ኢህአዴግ ነው) 

#FreerZone9bloggers #FreeEdom #FreeTesfalem #FreeAsemamaw #Ethiopia

No comments:

Post a Comment