በታዬ ዘሐዋሳ
በሃገራችን በነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ ወይም አመለካከት የተነሳ
በርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት እንደሚኖሩ ይታወቃል:: የሚኖሩበትም ሃገር ብዛትና ስብጥር በራሱ ከሌሎች ሃገራት ዜጎች የተለየን ያደርገናል ብዬ
አስባለሁ:: እንደ ሃገራቱ ስብጥር እና ብዛት ሁሉ የሃበሻ አመለካከትም እጅግ
ብዙ ነው:: ይህ ብዛት ያለው ስብጥር ደግሞ ወጥ የሆነ አመለካከት እንዳይኖረን አድርጓል::
ክፍፍላችንም እንደዚያው
ብዙ ነው:: ፍረጃችንም ጭምር::
የዛኑ ያክልም ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ
ለመፈራረጅ ወይም
ለመሞጋገስ ከንፋስ
የፈጠነ ነው:: ፍረጃው ከተለያዩ አካላት ይጀመር እንጂ አብዛኛዎቹን ፍረጃዎች በማዳነቅና በማሟሟቅ ረገድ የሁሉም ድርሻ አለበት:: አንዲት የፌስቡክ ወዳጅ ስለፍረጃዎች ብዛት
እና ጥልቀት ትዝብቷን አካፍላን ነበር:: ከነዚህ የርስ በርስ ፍረጃዎች ውስጥ የሚከተሉት በስፋት
የምናስተውላቸው ናቸው:-
.
ኢቲቪ ወይም ኢሳት
.
ኢህአዴግ ወይም ተቃዋሚ
. አይጋ
ፎረም ወይም ኢትዮጲያን ሪቪው
. አዲስ
ዘመን ወይም ፍትህ
. ኢትዮጲያ
ወይም ሞት ወይም ገንጣይ ተገንጣይ
. እምየ
ሚኒሊክ ወይም አፄ ዮሃንስ
. ኢትዮጲያ
ፈርስት ወይም ኦሮሞ ፈርስት
. ልማት
ወይም ሰብአዊ መብት
. ንኡስ
ከበርቴ ወይም ደሃ
. ኪራይ
ሰብሳቢ ወይም ልማታዊ
. ሰለፊስት
ወይም አህባሽ
. የውጪ
ሲኖዶስ ወይም የሃገር ውስጥ ሲኖዶስ
. የምርጫ
ትግል ወይም የትጥቅ ትግል
. ጠባብ
ወይም አገር ወዳድ
. ባንዳ
ወይም ጀግና
. የባንዳ
ልጅ ወይም የጀግና ልጅ
. X ወይም
Y እያለ ይቀጥላል::
ይህን የፍረጃ ብዛት እና አይነት ለግዜው በዚህ እናብቃው:: የፅሁፌ መነሻ ርዕሥ በርካታ ሃሳቦችን ማስነሳት እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራን
በተመለከተ የተለያዩ
ሃሳቦችን ማንሳትና ማወያየት እንደሚችል ግልፅ ነው:: አነሰም በዛም እነዚህን ሃሳቦች እያነሱ መወያየትም ሆነ መተራረም ስለ ድክመታችን አውቀን የማስተካከያ እርምጃ እንድንወስድ ይረዳናል:: ድክመቱን በገደምዳሜ እያየን
የምናልፈው ከሆነ
ግን ለሃገራችንም ሆነ ለህዝባችን ፋይዳ አናመጣም:: መፅሃፉ እንዳለውም አስቀድሞ በአይናችን ያለውን ምሰሶ ማውጣት ስንችል ነው የጓደኛችንን ጉድፍ ማየት የምንችለው:: ነገር
ግን የኛ ዳያስፖራ እሱ ያለው እንጂ ሌላው የሚለው ትክክል አይደለም ብሎ የማሰብ አዝማሚያ
ያሳያል::
እናም ምናልባት የኔ ሃሳቦች ከተወደደው ዳያስፖራ
ሃሳብ ጋር ካልተስማሙ የማይስማሙበትን ሁኔታ ለመስማት ዝግጁ መሆኔን አስቀድሜ ልግለፅ:: የባህርያችንን ጥልቀት ለማሳየትም ይመስላል "ኢትዮጵያ
የገባ አንድ ፀሃፊ በማግስቱ ስለ ኢትዮጵያውያን ከአንድ በላይ መፅሃፍ ሊፅፍ ይችላል:: በሁለተኛው ቀን ምናልባት ከተሳካለት ለጋዜጣ
የሚሆን መጣጥፍ ሊፅፍ ይችላል:: ሳምንት ሲቆይ ግን ያ ሰው ስለ ኢትዮጵያውያን አንድ
አረፍተ ነገር እንኳ መፃፍ አይችልም" አለ
የሚባለው:: ለማንኛውም ለዛሬ የሚከተሉትን "እዛም እዛም የረገጡ" ሃሳቦችን
ላንሳ:: ነገር ግን የማነሳቸው ሃሳቦች ከጥቂት ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች
ጋር ግንኙነት የሌላቸው እና እንደማይመለከታቸውም ባውቅም ብዙሃኑን ይወክል ዘንድ እነዚያን ጥቂቶችም የፅሁፌ አካል አድርጌያቸዋለሁ:: ለዚህ
አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ::