Monday, February 11, 2013

የካምፓስ ተማሪዎች የጎሳ ግጭት፤ ከመነሻው እስከ መድረሻው



ይህ ጽሑፍ ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በብሔር ሰበብ በተነሳ ፀብ ላይ ተመስርተው በተከታታይ ድረገጾች ላይ የተጻፉ ጽሑፎች መነሻነት የተጻፈ ማጠናከሪያ ሐተታ ነው፡፡ ስለሆነም እዚህ ውስጥ የተበታተኑት የሰዎቹ ውይይት አጽርኆት (summary) እና ተጨማሪ ሐሳቦች ይንፀባረቃሉ፡፡

ጃዋር መሐመድ (የፖለቲካ ተንታኝ) ነበር ውይይቱን የጀመረው፤ በጽሑፉ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ መንፈስ ተኮትኩቶ የሚያድግባቸው፣ እልፍ ገጽታ ያላቸውን ችግሮቻችን ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ሐሳቦች የሚፈልቁበት የላቀ እና ገንቢ ውይይቶች የሚካሔዱባቸው ቦታዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተቃራኒው ግን፣ የኢትዮጵያ ኮሌጆች የዘረኝነት፣ ጠባብነት እና አመጽ መፈልፈያ እየሆኑ ነው፡፡›› ይላል፡፡

እኔም በዚህ ጽሑፍ ይህንኑ ጉዳይ ከታሪክ እና ከወቅታዊ ጉዳዮች አንጻር እመላለስበታለሁ፡፡

ለመሆኑ መቼ እና በማን ተጀመረ?

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ዕድሜ አጭር በመሆኑ ብሔር-ነክ ግጭቶች መቼ እንደተጀመሩ የሚዘረዝር መረጃ ማግኘት ቢቸግርም እንኳን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ) እንደሆነ መገመት አይቸግርም፡፡ ሆኖም በቅርቡ በጆን ያንግ የተጻፈ፣ Peasants Revolution of Ethiopia የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ሳገላብጥ ያገኘሁት አንቀጽ አጀማመሩን የሚገልጽ መስሎኝ ወስጄዋለሁ፡፡

“…ዊንጌት ውስጥ … በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመሩ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች በቅርጫት ኳስ ጨዋታ ላይ በተነሳ አለመግባባት ከኦሮሞ ተወላጆች ጋር ተጋጩ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ መለስ በጣም አወዛጋቢ የነበረውን እና በአድዋ ጦርነት ወቅት የትግራይ ተወላጆች ከየትኛውም ብሔረሰብ የበለጠ የሕይወት እና የሰው ኃይል ከፍለዋል፣ ምኒልክንም ለድል አብቅተዋል የሚል የታሪክ ጽሑፍ አቀረቡ…(ገጽ 82) እያለ ይቀጥላል፡፡

Friday, February 8, 2013

የታክሲዎቻችን ነገር




ከሌላው የኑሯችን ሳንካ ባልተናነሰ የአዲስ አበባ ከተማ ታክሲዎች አሠራር ተጠቃሚዎችን ማማረር እና ማበሳጨት ሥራቸው ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከረዳትና ከሹፌር ጋር አተካሮ ሳይገጥም የሚሄድ ተሳፋሪ ያለበት ታክሲ ውስጥ መገኘት መታደል ነው፡፡ ባለታክሲ ስል ሾፌርንም ረዳትንም በጅምላ ወይም በተናጠል ማለቴ ነው፡፡ የፀቡ መንስኤ ሁል ጊዜ ባለታክሲ ነው  ብዬ አላስብም ተሳፋሪም  ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የዛሬ ርዕሴ  ባለታክሲዎችን የሚመለከት ነው፡፡

ባለቤት፣ ሹፌርና ረዳት

የታክሲ ሥራ ዋና ተዋናይ ሲሆኑ፤ ሁሉም አንድ የሚያረጋቸው የቀን ገቢያቸው ከፍ የሚልበትን ማንኛውንም መንገድ መጠቀማቸውና ለተሳፋሪም ርህራሄ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ የታክሲ ባለቤት ሹፌር በሚሆንበት ጊዜ ረዳቱ ለከፍተኛ ቁጥጥር አደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ሹፌሩ ተቀጣሪ በሚሆንበት ጊዜ ግን በአብዛኛው ሹፌርና ረዳት በመመካከርና በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ ረዳቱ የታክሲው ባለቤት የሚሆንበት ጊዜም አለ፡፡ ወይም የታክሲው ባለቤት ሹፌር ይቀጥርና የራሱ የቅርብ ሰው የሆነ ረዳት ይመድባል፡፡ (የባለቤቱ ዘመድ የሆኑትን ረዳቶች ሹፌሮች ‹‹ዕንባ›› ነው የሚሏቸው፤ ዕንባ ጠባቂ እንደማለት፡፡) ይህም ለሒሳብ ቁጥጥር ያመቸዋል፡፡ በሁለቱም መንገዶች ረዳቱ ሹፌሩን ሲመራ እና ሲያዝ ይስተዋላል፡፡ አብዛኛዎቹ ረዳቶች ሹፌር የሆነ ወቅት ያክል ከረዱ በኋላ የሹፌርነትን የሥራ መደብ ይይዛሉ፡፡

Monday, February 4, 2013

“መክሸፍ” እንደ ኢትዮጵያ ሚዲያ - መጽሔቶች




ወቅቱ መጽሔቶች እንደአሸን የፈሉበት፣ ጋዜጦች ደግሞ ቁጥራቸው የተመናመነበት ነው፡፡ ብዙዎቹ [የአማርኛ] መጽሔቶች የሚወጡት በየ15ቀኑ ቅዳሜ ቀን ነው፡፡ ጥቂቶች በወር አንዴ እና አዲስጉዳይ ብቻ በየሳምንቱ ይታተማል፡፡ በመጽሔቶቹ ታሪክ አንጻራዊ ደረጃ ሊሰጠው የሚችለው እና የራሱን ስም (ብራንድ) እየገነባ ነው ሊባል የሚችለው አዲስጉዳይ ነው፡፡ በየሳምንቱ መውጣቱ፣ የመጽሔት ቅርጽ (structure) መያዙ፣ በርካታ ጸሐፊያን እና አምደኛ ያሉት መሆኑ ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጎለታል፡፡ ሌላው ቀርቶ አዲስ ጉዳይ በየ15 ቀኑ፣ ከዚያም በየሳምንቱ መታተም መቻሉ በራሱ ሌሎቹንም ስቧቸዋል፡፡ ባለሙሉ ቀለም ለመሆንም የመጀመሪያ አርኣያቸው ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ አዲስጉዳይም ቢሆን በተለይ ከይዘት ጥንካሬ ትችት ማምለጥ አይችልም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አዲስ ጉዳይን እና ሌሎቹን መጽሔቶች በአንድ መስፈርት መመዘኑ ተገቢ ስለማይሆን እሱን ነጥለን ትተን ሌሉቹ /አብዛኛዎቹ መጽሔቶች/ ላይ ያሉትን ችግሮች እና “ከሽፈዋል”፣ በአዲስ መንገድ ትንሳኤ ያስፈልጋቸዋል ብለን እንከራከራለን፡፡

በማስተዋል አሳታሚ ከተገዛ በኋላ የተለየ ጥንካሬ ያላቸው ፖለቲካዊ ትችቶችን በበርካታ ጸሐፍት ያስተናግድ የነበረው አዲስ ታይምስ ጋዜጣም ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡ ነገር ግን የአዲስ ታይምስ ሕትመትም ለጊዜው በመቋረጡ በዚህ ጽሑፍ አንዳስሰውም፡፡

ይዘት

ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ያገላበጥናቸው መጽሔቶች ሁሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከአንድ፣ ሁለት በቀር ቋሚ አምድ የላቸውም፡፡ ይህም የተዘበራረቀ ሐሳብ ያላቸውን ጽሑፎች እዚህም እዚያም በመሰደር፣ የአንባቢን ሐሳብ በአንድ ማኖር እንዲሳናቸው አስገድዷል፡፡ ይህ ጉዳይ ተጽዕኖውን የሚያሳድረው በአንባቢዎቻቸው ብቻ ሳይሆን በመጽሔቶቹም በራሳቸው ላይ ነው፡፡ መጽሔቶቹ በየጊዜው የሚያወጧቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በተመለከተ ሦስት እና አራት ነገሮችን ብቻ ማስተዋል ይችላል፡፡ እነዚህም፡- የቴዲ አፍሮ የግል እና የግል ያልሆኑ ጉዳዮች፣ የሃይማኖት ልዩነት እና መከፋፈል አጀንዳዎች፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጉዳይ እና አሁን ደግሞ - ገበያው ይጠይቃልና - የአገር ውስጥ ፖለቲካ ጉዳዮች ናቸው፡፡

መጽሔቶቹ በነዚህ ጉዳዮች ላይ እንደየወቅቱ ወረት ‹‹መንደረተኛ›› ሊባል በሚችል መልኩ ጉዳዮችን ያራግባሉ፡፡ ነገር ግን በጽሑፎቻቸው አንጽሮተ-ዕይታ ለመጨመር አይሞክሩም፤ ሌላው ቀርቶ አንዱን አጀንዳ እጅግ በሚያሰለች መልኩ ለረዥም ጊዜ ይዘው ማመንዠክ ይወዳሉ፡፡ እንደምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ስለጤፍ መወደድ መንስኤ ብለው የተናገሩትን ብዙዎቹ መጽሔቶች እንደርዕስ መዝዘው ይይዙት እና ነገር ግን ምንም ፋይዳ የሌለው ትንተና ከርዕሱ የበለጠ ዋጋ በሌለው ሐተታ ያቀርባሉ፡፡ (ይህ ዜና ማመንዠክ አባዜ የቀድሞው ጠ/ሚኒስተር ሞትን እንዲሁም ተከትለው የመጡ የፓለቲካ ወሬዎችን ይጨምራል፡፡)

Sunday, February 3, 2013

“መክሸፍ” እንደተቃዋሚ ፓርቲዎች


በዘንድሮው የሟሟያ ምርጫ 29 ያህል ፓርቲዎች አንወዳደርም የሚል የጋራ አቋም ይዘዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ከምርጫ ቦርድ ጋር ለመደራደር ያወጧቸው ዝርዝር ጥያቄዎች ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ነው ላለመወዳደር የወሰነው ሲሉም አሳውቀዋል፤ እንደነርሱ አባባል ሚዛናዊ ምርጫ በማይካሔድበት እና እራሱ ምርጫ ቦርድም ሚዛናዊ ባልሆነበት መድረክ ተወዳድሮ ማሸነፍ ስለማይቻል፤ ተወዳድሮ ምርጫ አድማቂ ከመሆን አለመወዳደር ይሻላል፡፡ ኢሕአዴግም የእነዚህ ተቃዋሚዎች በምርጫ አለመሳተፍና መሳተፍ ለኢህአዴግ ትርፍም ኪሳራም እንደሌለው በግልጽ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚዎቹን አንድ ጥያቄ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡

የፓርቲዎች አባላት ጉዳይ

አንድነት ፓርቲ (በተለይ አንዱአለም ከመታሰሩ በፊት በቋሚነት) ምሁራንን እየጋበዙ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሕዝባዊ ውይይቶችን ለማካሔድ ሞክረዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም ይህንኑ ፈለግ በመከተል ጥቂት ውይይቶችን አካሄዷል፡፡ በነዚህ ስብሰባዎች ላይ ግን የሚገኙት ሰዎች ቁጥር በዛ ከተባለ አንድ መቶ ቢደርስ ነው የተለየ የሰዎች ቁጥር መጨመር ይታይበት የነበረው የአንድነት ፓርቲ የየሁለት ሳምንቱ ውይይትም በአጭሩ ቀርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድነት ፓርቲ ለፖለቲካ እና ሕሊና እስረኞች በወር አንድ ጊዜ የሚያደርገው የሻማ ማብራት ፕሮግራም ላይ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር 20 የማይሞላበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ ቁጥርም የታሳሪዎችን  ቤተሰብ ጨምሮ መሆኑንም ማስታወስ ያሻል፡፡ የሻማ ማብራት ፕሮግራም ማዘጋጀታቸው እና በወር አንድ ጊዜ እስረኞች እንዲታወሱ ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው ሆኖ በፕሮግራሙ ላይ የሚገኘውን ታዳሚ ቁጥር ማነስ እና ከዕለት ወደ ዕለት እየተመናመነ መሄድ የተሳታፊዎችንም የአዘጋጆችንም ተነሳሽነት እንደሚፈታተነው እሙን ነው፡፡

እነዚህ ፕሮግራሞች ላይ ሕዝቡ የማይገኝባቸውን ሁለት ዐበይት ምክንያቶች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ አንደኛ፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ያዘጋጀው ስብሰባ ላይ መገኘት ስለሚያስፈራ፣ ሁለተኛ፤ ስብሰባዎቹ በበቂ ሁኔታ ስለማይተዋወቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ሕዝቡ መካከል ያለው ርቀት ሰፊ ስለሆነ እንዲሁም ማስታወቂያ ስለማይሰራላቸው እና ስለማይሰሙ ነው፡፡ ሁለቱንም ችግሮች መቅረፍ ግን የተቃዋሚዎቹ ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡

Saturday, February 2, 2013

ስለግብ ጠባቂዎች እስኪ እንነጋገር



በኤፍሬም ማሞ

ለአሁኑየዋሊያዎቹን በአፍሪካ ዋንጫ 31 ዓመት በኋላ ተሳትፎ እንደመጨረሻ ግብ አድርገው ወስደው፣ አይ በእግር ኳስ የሚሆነው አይታወቅም ምናልባትም ወደሚቀጥለው ዙር ሊያልፉ ይችሉ ይሆናል ከሚሉት ወገን ነገርኩ፡፡ የልምድ ማነስ ያመጣውን ችግር ያው በሜዳ ላይ እስተውለነዋል፡፡ ኢትዮጵያን በመወከል በደቡብ አፍሪካ ላደረጉት የልብ ጥረት ሁሉም የቡድን አባላት ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ሞቅ ያለ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ይጠብቃቸዋል ብሎ ማስብ ስህተት አይመስለኝም፡፡

ግን ጥቂት ስለበረኞቻችን እንነጋገር፡፡ አንድ በረኛ የሚፈጽመው አስደናቂ የግብ ሙከራን የማዳን እንቅስቃሴ የቡድን አባላትን የማነቃቃቱን ያህል በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ ኳሶች ከመረብ ማረፋቸው ደግሞ ተስፋ መቁረጥን የመዝራት እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡በአህጉራዊ ውድድሮች በሶስት ጨዋታዎች ሁለት ግብ ጠባቂዎቿ ከሜዳ በቀይ ካርድ የተወገዱባት አገር ማየት እንዲህ የተለመደ ክስተት አይመስለኝም፡፡ ጀማል ጣሰው በዛምቢያው ጨዋታ ወደ ጎል ያላነጣጠረች ኳስን ይዞ ከመጣ ዛምቢያዊ ሲላተም ከቀይ ሌላ ዳኛው የሚያሳዩት ካርድ አልነበረም፡፡ የሲሳይ ባንጫም በናይጀሪያው ጨዋታ በቀይ መወገድ ሊወገድ የሚችል ስህተት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በረኞቻችን በአገር ውስጥ ክለብ

ታዲያ በረኞቻችን ይህንን ሁሉ ስህተት እንዲህ በመሰለ ታላቅ አህጉራዊ ውድድር መፈጸም ምንጩ ከየት ነው ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ወክለው በደቡብ አፍሪካው የአሃጉራዊ የእግርኳስ ውድድር የቀረቡት ግብ ጠባቂዎች በአገራቸው የክለብ እግር ኳስ ያላቸው ሚና ከወንበር ማሞቅ አንጅ የግብ መጠበቅ ተግባር ላይ አይደለም፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ዘሪሁን ታደለ ለኡጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንከራ የአንደኛ ደረጃ ግብ ጠባቂነትን ቢያስረክብ ብዙ የማቅማማት እድል አይኖረውም፡፡ አንድ ክለብ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ ያስመጣውን ተጫዋች አስቀምጦ የአገሬውን ተጫዋች ያሰልፋል ብሎ መጠበቅ የዋህ ቢያሰኝ ነው፡፡

የቡና ገበያ እግር ኳስ ቡድንም ዘካሪያ ኦንያነጎን ከኬንያ አስመጥቶ ለአገር ልጆች የግብ ጠባቂነት ሚና ወንበር ማሞቅን አድርጓል፡፡ ጀማል ጣሰውም ከደቡብ አፍሪካዊው ሞካሲ ጃኮብ ተመርጦ በጨዋታ የመሰለፍ እድሉን ያገኛል ማለት ዘበት ነው፡፡

የደደቢት የእግር ኳስን የተጫዋቾች ዝርዝር ላየ ጃኮብ ሞካሺ የተሰኘ እንግዳ ስም ለቁጥር አንዱ ቦታ ተሰጥቶ ያያል፡፡ ይህ ከደቡብ አፍሪካ የፈለቀ ግብ ጠባቂ ለአገር ልጆች በተጠባባቂ ወንበር መቆየት ተጠያቂ መሆኑን ልብም የሚለው አይመስለኝም፡፡