Saturday, May 28, 2016

እኔ እና ዕድለቢሱ ትውልዴ


ሲራክ ተመስገን የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ተወልዶ ያደገ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነው፡፡ ሲራክ ብቻ ሳይሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ ሲራክ በዚህ ዕድሜው “እኔና ትውልዴን ጠፍጥፎ የሠራን ኢሕአዴግ ተስፋ አስቆርጦኛል” ይለናል፡፡ ቁጭቱን አንብቡለት፡፡


ማንም ሰው ወዶ እና ፈቅዶ ‹በዚህ ጊዜና እዚህ ቦታ ልወለድ› ብሎ አልተወለደም። እኔም ቀን
ሲጎልብኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.) ከበረሃ ተነስቶ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሲደርስ፣ በዚህች ምስኪን ድሃ አገር ተወለድኩ። እንደ መሰሎቼ ሁሉ የእኔን የፖለቲካ ማንነትም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተዓለማዊ ቅኝት በተቃኘች አገር ኢሕአዴግ ጠፍጥፎ ሠራው። የኢሕአዴግ ኢትዮጵያም፣ እኛም የግንቦት 20 ፍሬዎች ቀስ እያልን ማደግ ጀመረን። ዕድሜያችንም፣ ዕድልም 1997 አገራዊ ምርጫ ላይ አደረሰን። የተለያዩ የፖለቲካ ሐሳብ ያላቸው ቡድኖች መሐከል የሚካሄድ የአደባባይ የፖለቲካ ውይይት ለመጀመሪያ ጊዜ ለማዳመጥ ታደልን። እዚህ ላይ ነው እኔና የትውልዴ አባላት ነቃ ብለን ኢሕአዴግን በቆሪጥ ማየት የጀመርነው።

ኢሕአዴግ ልጆቹን እንዴት አሳደገን?

እኛ የኢሕአዴግ ልጆች ሁለት ተቃራኒ የማንነት ጥያቄዎች ከግራ እና ከቀኝ እየጎተቱን ነው ያደግነው። የአካባቢያዊ (የዘውግ) ማንነት እና አገራዊ (የዜግነት) ማንነት። አሳዳጊያችን ኢሕአዴግ መሠረቱን ያደረገው ፈግሞ በዚህ አካባቢያዊ ማንነት ላይ ነው። ገና በጨቅላ ዕድሜያችን አገራዊ ማንነነትን አፍሮሶ በአካባቢያዊ ማንነት የሚተኩ ንግግሮችን ከኢሕአዴግ አመራሮች አንደበት እየሰማን ነው ያደግነው። በእኔ እምነት እንሰማቸው የነበሩት እንደ “የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው?”፣ “ባንዲራ ጨርቅ ነው”፣ “የኢትዮጵያ ታሪክ የ100 ዓመት ታሪክ ነው”… የመሳሰሉት ንግግሮች አገራዊ ማንነትን በመተው አካባቢያዊ ማንነትን እንድንይዝ መሠረቱ ጥሏል ብየ አስባለሁ።

ካለፉ የታሪክ ኹነቶች ውስጥ አንድ ሊያደርጉን የሚችሉ ትርክቶችን ወደ ጎን በመግፋት፣ ሕዝቦችን ቅራኔ ውስጥ የሚከቱ ትርክቶች ብቻ ተመርጠው እየተመገብን ነው ያደግነው። ያለበሱን አገራዊ ማንነትን ሳይሆን አካባቢያዊ ማንነት ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል አሁን ላይ የካቲት ሃያ ሦስትን የማያውቁ፣ ሕዳር ሃያ ዘጠኝን በሽር ጉድ የሚያከብሩ የትውልድ አጋሮቼ የበረከቱት፡፡

የትውልዳችን ፈተና

(ለመግባባት እንዲያመቸን ትውልዳችን ስል ኢሕአዴግ አዲስ አበባ በደረሰበት ዓመት እና በቀጣዩ ዓመት የተወለዱ ልጆችን ማለቴ እንደሆነ ይታወቅልኝ።)

የእኔ ትውልድ ብዙ ፈተናዎች አሉበት። እስኪ ዘርዘር አድርገን ለማየት እንሞክር።

ሀ. ‘ጸጥ-ለጥ’ ብሎ የተገዛው ትውልዴ

ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ኢሕአዴግ ባወጣው ሕገ መንግሥት ላይ ቢካተትም በሀገራችን ላይ በተጨባጭ የምናየው ግን ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ከፍተኛ አደጋ ያለው እንደሆነ ነው፡፡ ብዙዎች ሐሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ተደብድበዋል፣ ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰደዋል። በአገራችንም ጠንካራ ‘ሚዲያ’ እንዳይፈጠር ቀን ከሌ’ት ገዢው ፓርቲ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።

ይህ የእኔ ትውልድ ከመንግሥት ጋር እንዲህ ዓይነት ቅራኔዎች ውስጥ አለመግባቱ የኢሕአዴግ ልጆች ‘ጸጥ-ለጥ’ ብለው እየተገዙ መሆኑን ያሳያል። ዘመናዊው ‘የማኅበራዊ ሚዲያ’ ላይ በጣም ጥቂቶች ሊባሉ የሚችሉ ግለሰቦች ፈራ-ተባ እያሉ መንግሥትን ሲተቹ ይታያሉ። ‘ጸጥ-ለጥ’ ብሎ የመገዛቱን ነገር የከፋ የሚያደርገው በእኔና ከእኔ ዕድሜ በታች ያሉ ሴቶች በአደባባይ መንግሥትን ሲተቹ አለማየት ነው።

ለ. ዕድለቢሱ ትውልዴ

ሌላው የእኔ ትውልድ ፈተና ዕድሎችን ማግኘት የሚችለው በብቃቱ ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ባለው ታማኝነት ወይም የገዢው ፖርቲ አካባቢ ተወላጅ ከሆነ ነው። ከ2005 ጀምሮ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የትውልድ አቻዎቼ ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች በየዓመቱ እየተመረቁ ነው። እኒህ ተመራቂ ተማሪዎች ትልቁ ፈተናቸው ሥራ ማግኘት ላይ ነው። ከመመረቂያ ሰርተፍኬታቸው ይልቅ ኢሕአዴግን ከመሠረቱት ከአራት ድርጅቶች የአንዱን በደም የሚመሳለውን መርጦ የአባልነት መታወቂያ ይዞ መገኘት የሥራ ዋስትና ነው። ኢሕአዴግን እየተቃወሙ የመንግሥት ሥራ የማግኘት ዕድል ያላቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው። በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች መቀመጥ የማይታሰብ ነው። ከቀበሌ ካቢኔ አንስቶ እስከ ሚኒስትር ድረስ በኢሕአዴጋዊያን የተሞላ ነው። ባንድ ወቅት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድን ሰው በአመራርነት ቦታ ለማስቀመጥ ብቃት ሳይሆን ለፓርቲው ያለውን ታማኝነት እንደሚመርጡ በአደባባይ ተናግረዋል። ይህ ትውልድ ሥራ ሊያገኝ የሚችለው ወይ አመራር ሊሆን የሚችለው በብቃቱ ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ባለው ታማኝነት አለበለዚያ የዘር ሐረጉ ከገዢው ፓርቲ የሚመዘዝ ከሆነ ነው።

“እኔ… ተስፋ የለኝም?”



መልዕክተ ዓብይ የ25 ዓመት ወጣት ስትሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ዘመን ተወልዳ አድጋለች፡፡ በሌላ አነጋገር መልዕከተ አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነች፡፡ መልዕክተ ብቻ ሳትሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ መልዕክተ በዚህ ዕድሜዋ የፖለቲካ መነቃቃቷን ጨምራ በስርዓቱ ያላትን ‹ተስፋ› እንዲህ ታስነብበናለች፡፡ እስኪ አንብቧት፡፡

“ፖለቲከኛ አይደለሁም፤ ፖለቲካ አይመቸኝም፡፡ የኔ የመኖር ዓላማ፤ መጀመሪያ እኔ እራሴን እና ቤተሰቤን ካለሁበት ችግር ማላቀቅ ነው፡፡ ፖለቲካ የደላው እና ኑሮን ያሸነፉ ሰዎች ችግር እንጂ የኔ አይደለም፡፡ እኔ ምን ያገባኛል?”

ይህ እስከቅርብ ጊዜ የነበረኝ የፖለቲካ አመለካከት ነበር፡፡ በርግጥ አሁን ላይ በፊት ከነበረኝ
አስተሳሰብ የተለየ አመለካከት እየተፈጠረብኝ መመጣቱ በራሱ ረዥም ሒደት ነው፡፡ ፖለቲካ የሁሉም ሰው የሕይወት ሕልውና እንደሆነ እየገባኝ ነው መሰል የማየውም የምስማውም የምኖርውም ብቻ ባጭሩ እኔም ሆንኩ ማንም ሰው ‘ከፖለቲክሱ’ ነጻ ሆኖ መኖር እንደማይችል የገባኝ አሁን ነው:: በ25 ዓመቴ:: ያሳዝናል:: ያደለው በ25 ዓመቱ የሆነ ለውጥ በራሱ ላይም ሆነ በቤተሰቡ ከዛም አልፎ ለሀገሩ ያበረክታል፡፡ እኔ ግን  በ25 ዓመቴ ገና ምንም እንደማያቅ ሕፃን ልጅ የፖለቲካ ፅንሰ ሐሳብ እዲገባኝ ‘ሀ’ ብዬ ለመጀመር እየተነሳሁ ነው፡፡ ለዚህ ግን ተጠያቂው ማን ይሆን?

አባቴ ይሆን?

አይ፤ የኔ አባት የ14 ዓመት ልጅ እየለሁ ነበር በሞት የተለየኝ፡፡ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ግን የቻለውን እና ያኔ በእኔ አቅም ልረዳው የምችለውን ይነግረኝ እና ያስተምረኝ ነበር፡፡ እሺ ታዲያ ማነው?

እናቴ ትሆን?

እናቴማ እኔን ለማሳደግ ደፋ ቀና ትበል ወይንስ ስለእኔ የፖለቲካ እና የሕይወት አመለካከት ትጨነቅ? በዚያ ላይ እንደሚታወቀው  የኛ እናቶች ከሕይወት ተሞክሯቸው ፖለቲካን በሩቁ ብናይላቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ እናም፣ እናቴ ላይማ አልፈርድም፡፡

መምህሮቼ ይሆኑ?

መምህሮቼ? ለምን እንደዚህ ዓይነት አመለካክት እንዲኖረኝ አድርገው አሳደጉኝ? በተለይ የሥነ-ዜጋ መምህሮቼ ለምንድን ነው የተሻለ አመለካከት እና አሰተሳስብ እንዲኖረኝ አድርገው እና የእውነትም ከዚያ ትምህርት ማግኘት የነበረብኝን ዕውቀት ያላስቀሰሙኝ? ለምንድን ነው ያለሁበት ስርዓት ብቻ ትክክል እና ያለፉት ስርዓቶች ላይ ጥላቻ ብቻ እንዲኖረኝ አድርገው ያስተማሩኝ? አሁን አሁንማ ሲገባኝ እነሱ የማያምኑብትን ሐሳብ እኔ እንዳምንበት ሲያደርጉ እንደነበር ነው የሚሰማኝ:: ይገርመኛል፡፡

ከዕድሜው በላይ ታሪክ የተሸከመው የኔ ትውልድ


ዓለማየሁ ደንድር የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ተወልዶ ያደገ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነው፡፡ ዓለማየሁ ብቻ ሳይሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሲገባ የ8 ወር ልጅ የነበረው ዓለማየሁ “ኢሕአዴግ ላይ ያለንን ተስፋ አንጠፍጥፈን ወደ ልኂቃኑ ማንጋጠጥ ጀምረናል” ይለናል፡፡ አንብቡት፡፡

የአሪስጣጣሊስ "Man is by nature a Political Animal" የሚለው ሐሳቡ፤ሳቡን ብቻ ሳይሆን
ጥሬ ትርጉሙን (literal meaning) ለመረዳት በኢሕአዴግ የኔታነት ለተማርነው ሊከብደን ይችላል። ጥቅልሳቡ 'ወደድክም ጠላህም ከፖለቲካ አታመልጥም' እንደማለት ይመስለኛል።አንተ ልጅ ፖለቲካ ማውራት ይቅርብህ ኢሕአዴግ ያስርሃል" ብለው የሚጨነቁልን ወዳጆች፤ በዛው አፋቸውተው አንተ የኢሕአዴግ ፖለቲካ... ልጁ ላይ አትድረስ" ማለት ቢችሉ መልካም ነበር። ከፖለቲካ ጋር ያለንን ኑሮ ለመረዳት ጊዜ ይወስዳል፤ ፖለቲካ ሲገነድስ እንጂ ሲሸርፈንና ሲጨርፈን አይታወቅም።

ፖለቲካ ሲጨርፈን

የጨረፈን የጫካ ጓዶች ከተማ ሲጣሉ ነው፤ በአገር ሥም ተዋጉ፣ አብሮ የኖረ ጎረቤት ተላቅሶ ተበታተነ። ልጅ ስለነበርን ፖለቲካ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ ወስዶብናል። ከተማ ሲገቡ 8 ወር ልጅ ነበርኩ፤ ሳንጎረምስ ተባሉ፤ ከልጅነት የጨዋታ ሚስቴዊንታ ለጋስ ጋር እንኳን የጉርምስና መተፋፈር ሳይሆን ፖለቲካ ነው የለየን ብል ማን ያምናል? እንደዛ ለመረዳት ግን ጊዜ ወስዷል። "ዳሕላክ ላይ ልሥራ ቤቴን ... ነጠለኝ ክፉ ዘመን ከምወዳት ባለቤቴ" ተብሎ ሲዘፈን እንኳን ፖለቲካ መሆኑን አልተረዳሁም ነበር።

ከስንት አንዴ ብልጭ ከሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞዎች በኋላ 97 ምርጫ የማንንም ቀልብ ይዟል፤ የትምህርት ደረጃ ሲባል 'ማንበብና መጻፍ' የሚለው ሁሉ ጋዜጣ ይገዛል፤ እየተቀበልን እናነባለን፡፡ ሙቀቱ እንጂ ጉዳዩ ብዙም አይገባንም፡፡ ያኔ 9 ክፍል ነበርኩ። ሙቀቱ ይስባል፤ እነ ልደቱአንከራከርም” ብለው ረግጠው ሲወጡ፤እንነጋገርበታለን”፤ቅንጅት ፓርላማ አልገባም” ሲልልክ ናቸው” እንላለን፤ ፖለቲካው ግን አይገባንም፡ ሙቀቱ ነውሚስበን።አዲስ ከተማዎች ቀወጡት” ሲባልእንዴት እኛስ ተበለጥን?” ይባላል፤ ይቀወጣል፤ ፌዴራል ይመጣል፤ ፀጉሩን ፍሪዝ ያረገ ሲቪል ፖሊስ፣ ፍሪዝ ያረገውንና የጠቆረውን ተማሪ እያንበረከከ በጫማ ጥፊ ይላል፤ እንዲይም ሆኖ ስለ ፖለቲካ መመታታችን ይግባን አይገባን እርግጠኛ አይደለሁም፤ በአዲስ ከተማ ተማሪዎች መበለጣችን እንጂ ምርጫ መጭበርበር ማለት ምን እንደሆነምምንረዳም አይመስለኝም።

Friday, May 27, 2016

የታናሽ ጥያቄ፣ ለኢሕአዴግ ታላቄ




እመቤት ግርማ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ተወልዳ ያደገች ነች፡፡ በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነች ማለት ነው፡፡ እመቤት ብቻ ሳትሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ እመቤት በዚህ ዕድሜዋ የአራት ዓመት ታላቋን ኢሕአዴግን “ታናሽ ታላቁን መጠየቁ ወግ ነውና” በማለት “ከቶ ምን ለውጥ አመጣህ ይሆን?” እያለች ትጠይቀዋለች፡፡ አንብቧት፡፡



 “…ሕፃናት እጅግ ደስ ብሎናል፣
 ግንቦት 20 ዛሬ ደርሶልናል፣
 ግንቦት 20፣ ግንቦት 20፣
 የሰላም ቡቃያ…”


ያኔ ነፍስ በማናውቅበት የሕፃንነት (የተማሪነት) ዕድሜያችን በአስተማሪዎቻችን መሪነት ይህን
መዝሙር በኅብረት ሆነን እና ‹ግንቦት 20› የሚል የካርቶን ኮፍያ አድርገን በየአደባባዩ እየዞርን ዘምረናል፡፡ የመዝሙሩ መልዕክት ምን ማለት እንደነሆነ ባይገባንም ለካርቶን ኮፊያ እና ለመንገድ ላይ ሰልፍ ስንል በደመ ነፍስ ላንቃችን እስኪሰነጠቅ እንዘምር ነበር፡፡ ልክ የትግራይ ሕፃናት ምኑም ሳይገባቸው ‹መሥመርዩ መሓርያ› እንደሚሉት፤ ወይም አርቲስቶቻችን በቅጡ ሳይረዱት “ምነው ሞት እንዲህ ጨከነ” ብለው እንዳቀነቀኑት፡፡ እንዲሁ በደመ ነፍስ ዛሬ አድገን እንኳን ትርጉሙ ያልገባንን መዝሙር ከመዘመር ባለፈ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.) ደርግ ይጠቀምበት የነበረ የሬዲዮ ጣቢያን ፣ ‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም› ሲባል ከተቆጣጠረበት በኋላ የተወለድን የዘመነ ኢሕአዴግ ልጆች ነንና፡፡ ዛሬ እኔ 21 ኢሕአዴግ ደግሞ 25 ዓመታችንን ይዘናል፡፡. እናም ታናሽ ታላቁን ያልገባውን ጥያቄ እንዲያስረዳው እንደሚጠይቀው እኔም ለአራት ዓመታት ታላቄ ኢሕአዴግ 25ኛ የልደት በዓሉን በሚያከብርበት በዛሬው ዕለት ጥቂት ጥያቄዎችን ላነሳ ወደድኩ፡፡ በርግጥ የጥያቄዎቼ መልስ “አትጨቅጭቂኝ ልማቴን ላፋጥንበት”’ አልያም “እነዚህን እኮ ከ25 ዓመታት በፊት መልሻቸዋለሁ” የሚሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባውቀውም በግንቦት 20 ‹በተረጋገጠው› ዴሞክራሲያዊ መብቴ ተጠቅሜ መጠየቄን እቀጥላለሁ፡፡

ታላቄ ኢሕአዴግ ሰፊው ሕዝብ ማነው? የሰፊው ሕዝብ ጥቅምስ ምንድነው? በየዓመቱ ለግንቦት 20 ዋዜማ በመንግሥታዊው ቴሌቪዥን የሚታየው አስከፊው የደርግ ስርዓት እና ዛሬ በእኛ ዘመን ያለው አገዛዝስ ልዩነታቸው ምንድን ነው? ግንቦት 20 ‹የነጻነት በዓል› የተባለበትስ ምክንያት ምንድን ነው? በርግጥ ጥያቄዎቼ የማያልቁ ቢሆኑም መልሱን ከኢሕአዴግ እንደማላገኝ አውቀዋለሁና በራሴ አረዳድ እና በጥቂት ተሞክሮዎቼ በመመርኮዝ ራሴ ለጠየኳቸው ጥያቄዎች እኔው ራሴው ምላሽ ለማግኘት እሞክራለሁ፡፡

ሰፊው ሕዝብ ማነው?

በኢሕአዴጋውያን አነጋገር የትጥቅ ትግሉ የተካሄደው፣ በትግሉ ወቅት ብዙ ወጣቶች የተሰዉት፣ አስከፊው የደርግ ስርዓት የተገረሰሰው፣ ኢሕአዴግ ለ25 ዓመታት በብቸኝነት፣ በመንግሥትነት ሥልጣን መንበር ላይ የኖረ ‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ሲባል› ነው፡፡ ታዲያ፣ ‹ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለት ነው ‹ሰፊው ሕዝብ› የተረጋገጠለት ጥቅምስ ምንድን ነው?› ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ የኢሕአዴግ የ‹ሰፊው ሕዝብ› ትርጓሜ ከተለመደው  ትርጉማችን በተቃራኒ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በቀጥተኛ ትርጓሜው ሰፊው ‹ሕዝብ› ማለት፡ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝ ብዝኻውን የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚወክለው ታላቅ ክፋይ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይሄን ክፋይ ማለትም ተማሪው፣ ምሁሩ፣ አርሶ አደሩ፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ወታደሩ… ከግንቦት 1983 ጀምሮ ጥቅማቸው ተከብሮ ሳይሆን ተረግጦ የሚገኝ መሆኑን ስንመለከት ‹ሰፊው ሕዝብ› በኢሕአዴግ መዝገበ ቃላት ሌላ ትርጉም የሚይዝ መሆኑን እንረዳለን፡፡ እዚህ ላይ የኢሕአዴግ ነባር ታጋይ የነበረው ኅላዌ ዮሴፍ ‹እያወገዙ መሆን› በሚል ርዕስ ለደርግ ባለሥልጣናት “‹ሕዝብ› ማለት ምን ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ለዛሬዎቹ ኢሕአዴግዎች በልክ የተሰፋ በሚመስል መልኩ ምላሽ የሰጠበትን ግጥም በቅንጭቡ እንመልከት፡-
                     

በርሶ ትርጉም ትንታኔ
ሕዝብ ማለት ምን ማለት ነው
ለአገር ለጎረቤትዎ በሬዲዮ የሚሉትን
የሚያወሩትን በትርጉም ሳይሆን
በልብ በሚያምኑበት
በራስዎ የሚስጢር ኪስ በማስታወሻዎ በያዝዋት
ምንም ሳያንገራግሩ
ገለጥለጥ አድርገው ያጫውቱን
እባክዎ ሕዝብ ማለት
ወዛደሩ፣ አርሶ አደሩ፣ … ናቸው አይበሉን
የለም የለም ይህ አይደለም
ስንተዋወቅ!
በርሶ ትርጉም በምናውቀው
በሚወራው ሳይሆን በሚሰራው
…በእናንተ እምነት ሕዝብ ማለት
ከበርቴ ፋሸስቶቹ
በላኤ-ሰቦች ጨፍጫፊዎቹ
የድርጅት ክቡር ሰዎች
የሥርዓቱ ባለሟሎች
እና ጓዶች …
እነዚህ ብቻ ናቸው፤
እናንተ ሕዝብ የምትሏቸው …


እናም የትናንት ደርግን አውጋዦቹ ኢሕአዴጋውያን ዛሬም እነሱ በደርግ ፈለግ ተጉዘው ‹ሰፊው ሕዝብ› የሚለውን ቃል ልማታዊ ባለሀብቶች፣ የድርጅት አባላት፣ የጊዜው ባለሥልጣኖች፣ የስርዓቱ ባለሟሎች… የሚል ትርጉም ሰጥተውት እናገኛለን፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ ዛሬ በአገራችን ውስጥ የአብዛኛውን ሕዝብ የሰቆቃ ኑሮና የጥቂት የስርዓቱ ባለሟሎች የቅንጦት ኑሮ መመልከት በቂ ነው፡፡ እናም ‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም› ሲል ደርግን የተፋለመው ኢሕአዴግ ዛሬም ‹በሰፊው ሕዝብ› ፍላጎት እና ድጋፍ እነሆ 25ኛ የልደት በዓሉን በማክበር ላይ ነው፡፡ ‹ብራቮ› ‹ሰፊው ሕዝብ›!

እኩይ ዕኩያዬ፣ ኢሕአዴግ


አገኝሁ አሰግድ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ተወልዶ ያደገ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነው፡፡ አገኝሁ ብቻ ሳይሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ አገኝሁ በዚህ ዕድሜው “የዕድሜ እኩይ ዕኩያዬ” ያለውን ኢሕአዴግን “ዴሞክራሲያዊ ሁን ማለት፤ እንደልቡ ይጋልብበት በነበረበት ልጓም ይግባልህ እንደማለት ነው። በጨለማ አድኖ ለሚበላ፣ ጨለማ በረከቱ ነው[ና]” ይለናል፡፡ አንብቡት፡፡

ኢሕአዴግ ተንዶ የማያልቀውን ሕገ መንግሥት ከመጻፉ በፊት፣ ከማርክሲስትነት ወደ ካራቲስትነት
ከመለወጡ በፊት፣ ብሔር ብሔረሰባዊ ሹፈት ከመጀመሩ በፊት… ተወልጃለሁ። በዛው ሥልጣን በያዘበት ዘመን። የፖለቲካ ወሬ እንደ ርዕስ ከጆሮዬ መግባት የጀመረው በአይረሴው ዘጠና ሰባት ወቅት ነው። በገርነታችን ዘመን።

የገር ልብ ናፍቆት

1997 በተለምዶ ሚኒስትሪ የሚባለውን የ8ኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተናና የአገር አቀፉን ምርጫ ውጤት የምጠብቅበት ወቅት ነበር። በጊዜው ውስብስብ የፖለቲካ አረዳድ ባይኖረኝም፣ በሰማኋቸው ክርክሮች፣ ባነበቡኳቸው ጋዜጦች… ሞቄያለሁ። ልቤን ‹ቅንጅት› ለተበለው ፓርቲ ‹ልብ ወደ ላይ› አስብዬ አስረከብኩ። አባቴ ያመጣቸው የነበሩ "ነፃነት"፣ "ሚኒልክ"… ጋዜጦች አበጀህ አሉኝ። መረዳቴም ወደ አንድ አቅጣጫ ዘመመ - ኢሕአዴግ ይህቺን ዓመት አይሻገርም! ዛሬ ሳስበው ይገርመኛል። የምርጫው ውጤት በየቀበሌዎቹ ይፋ ሲሆን ብዙ ቀበሌዎች በጊዜ ሄጄ ውጤቱን አይቼ ተመልሻለሁ። በከተማችን ቅንጅትን ወክሎ የተወዳደረው ሰው ማሸነፉን ለቤተሰቦቼ አበሰርኳቸው። ኢሕአዴግን ካለመረዳት የመነጨ ተስፋ ነበረኝ። ምናልባት ይሄን ‹ተስፋ› ከማለት ለ‹ሞኝነት› ይቀርብ ይሆናል። እንደማይደገም ግን እርግጠኛ ነኝ።

ንቦቹ ተናደፉ

በጊዜው የኢሕዴግን ቅፅበታዊ ወደ ጸበኝነት መቀየር፣ አንድ ጋዜጣ ‹ንቦቹ ተናደፉ› ብሎ ዘግቦት ነበር። በወቅቱ ንብም ከታታሪነቷ ተናዳፊነቷ አብዝቶ ታሰበ። ብዙ ወጣቶችም በአግአዚ ጥይት ተነደፉ። የአገሬን ፖለቲካ ከዛን ወቅት ጀምሮ እየጠላሁትም ከምሰማቸው ጉዳዮች አንዱ አደረኩት።

‹ከእኔ ውጪ ለሌላ መንግሥት እንዳትገዙ›

እንኳን ‹ፀሐይ ነኝ› ከሚል ዋሾ መንግስት ጋር ለዓመታት መቆየት፣ በሀሩር ፀሐይ ለሰዓታት መቆየት እንደሚከብድ ግልፅ ነው። ሕይወትን ሕይወት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ለውጥ ነው። ከለውጥም በጎ ለውጥ። ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ አገዛዝ ከምን ወደ ምን ተለወጠች?  የቱ ጨለማ ተገፈፈ፣ የቱ የብርሃን ምሰሶ ቆመላት? ሳያይ የሚያምን ብፁዕ ይኖር ይሆናል። ሳላይ በማመን ለብፁዕነት የምጓጓ ባለመሆኔ፣ መልሴ ‹ምንም› ነው። ከአንድ መንግሥት ጋር አድጌ፣ ከአንድ መንግሥት ጋር መኖሬን በሁለት መንገድ አየዋለሁ።