Monday, September 19, 2016

ማኅበራዊ ሚዲያው እና የመንግሥት ስጋት



በተስፋዬ ዓለማየሁ

የማኅበራዊ ሚዲያውን አጠቃቀም በተመለከተ ተከታታይ ዘመቻዎች እና ማጥላላቶች በተለያዩ ግዜያት በሕትመት ሚዲያው ሳነብ፣ በብሮድከስት ሚዲያውም ሳደምጥ ቆያቻለሁ፡፡ እነዚህን የአጠቃቀም ጉድለቶች ላይ ያተኮሩ ዘመቻዎች ታዲያ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስመለከታተቸው ነው የሰነበትኩት፡፡ ምክንያቱም መሰል ፈራጅ ዘጋቢ ፊልሞች በሕትመት ሚዲው ላይ ይሠሩ እና ጠንከር ያለው እርምጃ ይከተል ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በመጀመሪ የኮረኮረኝ ጽሑፍ "ከማኅበራዊ ሚዲያው በስተጀርባ" በሚል ርዕስ በሪፖርተር ገዜጣ ላይ ከወጣ በጣም ቆየት ብሏል፡፡  የጽሑፉ ዋና ዓላማ የነበረው ከማኅበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታ ‹በስተጀርባ ያለውን አደጋ ነው ማመመልከት› ነበር፡፡ የጽሑፉ አዘጋጅም በሚገባ አስረጅ ምሳሌዎችን አስቀምጠው ጠቀሜታውንም ለመዳሰስ ሞክረው ጽሑፋቸውን ቢያበቁም፣ ከዚያ በኋላ በተከታታይ እንዲሁ በተለያዩ ግዜያት ቅኝታቸው ማኅበራዊ ሚዲያው ከጥቅሙ ባሻገር ጉዳቶቹ ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን አንብቤያለሁ፡፡ እርግጥ ነው በተነሱት ሐሳቦች ዙሪያ የማኅበራዊ ሚዲያው፣ በዋነኛነትም ፌስቡክ ከጥቅሙ በዘለለ ባሉት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ላይ መሠረታዊ ልዩነት ከጸሐፊዎቹ ጋር የለኝም፡፡ "የጥላቻ ንግግሮችን ማስተላለፊያ ነው""አሉባልታ ማሰራጫ ነው""የሠራ ግዜን ይሻማል"፣ "በቅርባችን ካሉ ወዳጅ ጓደኞቻቸችን ጋር ይለያየናል"፡፡ ሌሎችም የፌስቡክ እንከኖችን እያስታወስን መዘርዘር አንችላለለን፡፡
  
ማኅበራዊ ሚዲያው ግን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ልንዘነጋው አይገባም፡፡ የማኅበራዊ ሚዲውን ችግሮች ማሳየቱ ለተጠቃሚው አጠቃቀሙን እንዲፈትሽ ስለሚያደርጉ መልካም ሊባል ቢሆንም፡፡ ችግሮቹን ማጉላቱ ላይ ግን አልስማማም፡፡ ከሚጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ለራሳችን በጣም ተስማሚ የሆኑ ችግሮች አይጠፉምና በአግራሞት ወይም በድንጋጤ "ይህማ የእኔም ችግር ነው" የምንለው እና ለችግሩም ተጋላጭ እንደሆንን፣ በደንብ እንዲሰማን የሚያደርጉን ማሳያዎች ስለሚዘረዘሩ ሊያሸማቅቁን ይችላለሉ፡፡ ይህንን ስሜት ከመፍጠር ተሻግረው ግን በሕትመት ሆነ በብሮድካስት ሚዲያ የሚተላለፉት መልዕክቶች ውጤታቸው  (ኢፌክታቸው) ምን ያህል እንደሆነ ትዝብቱን ለየግላች ልተወውና፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ንበማስተዋል መጠቀም የሚለው ምክር ላይም እንስማማና፣ ፌስቡክ በአሁኑ ሰዐት ሁነኛ አማራጭ ሚዲያ እንደሆነ ለማሳየት የሚከተለውን እጽፋለሁ፡፡

መነሻ፤ በአገራችን የሕትመት እና የብሮድካስት ሚዲያ ሁኔታ ወፍ በረር ቅኝት

በአገራችን ውስጥ ያለት የብሮድካስት እና ሕትመት ሚዲያዎች ከሚጠበቅባቸው አንፃር ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ በአግባበቡ እያገለገሉን አይደለም፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን ልንደረድር እንችላለለን፤ የጋዜጠኞች ብቃት ማነስ፣ የጋዜጠኞች የሥነ ምግባር ጉድለት፣ የጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለቤቶች የፖለቲካ ፍላጎት እና አመለካከከት፣ የገበያው ትርፋማነት እያልን በርካታ ምክንያቶችን ብንደረድርም "የእናቴ መቀነት…" ከመሆን አይዘልም፡፡  ምክንያቱም በእነዚህ ሰበቦች ወይም ችግሮች ውስጥ እንኳን የጋዜጠኝነት መርሖዎችን ለማክበር ከመሞከር ይልቅ ሲጥሷቸው በግልጽ ይስተዋላሉ እና ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ጠንከር ባሉ ሁሉን ዐቀፍ ተሳትፎ እና ውይይት በሚፈልጉ አገራዊ፣  ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም በዕኩል ደረጃ አያሳትፉም አያገልግሉም፡፡ አብዛኛዎቹ የአገራች ሚዲያዎች በጣም የተካኑባቸው እና የሚሽቀዳደሙባቸው ዘገባዎች በጣም ለስለስ ያሉ ማኅበራዊ፣ የመዝናኛ እና የስፖርት፣ የኪነ ጥበብ፣ የፊልም እና የፋሽን ጉዳዮች ናቸው፡፡

Friday, September 16, 2016

በይነመረብ እና አፋኝ መንግሥታት


ኢንተርኔት ወይም በይነመረብን በየቀጠናው እና በየመተግበሪያው ዓይነት ብልጭ ድርግም በማድረግ የመረጃ ፍሰትን በሚፈልገው መልኩ ለመቆጣጠር ይፋዊ እንቅስቃሴ የጀመረውን የኢትዮጵያ መንግሥት የበይነመረብ ቁጥጥር (censorship) አካሔድ በመታዘብ አጥናፉ ብርሃኔ አገራችን ውስጥ ያለውን የበይነመረብ አፈና ከዓለምዐቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር በዚህ መጣጥፉ ግልጥልጥ አድርጎ ያሳየናል

አፋኝ ወይስ አዳኝ?

በ2014 (እ.ኤ.አ.) በቱርክ አንካራ ከመናገር ነጻነት መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ‹Committee to Protect journalists› (ሲ.ፒ.ጄ.) እና ‹International Press Institute› (አይ.ፒ.አይ.) ጋር ስብሰባ የተቀመጡት ጋዜጠኞችን በማሰርና የተለያዩ ሚድያዎችን በማፈን የሚታወቁት የቱርኩ መሪ ሪሴፕ ጣይብ ኤርዶሃን ለብዙዎች አማራጭ ሚዲያ እየሆነ የመጣውን የማኅበራዊ ሚድያ ወይም ኢንርኔትን (በይነመረብ) አንደሚጠሉ በግልጽ ተናግረው ነበር።

ኤርዶሃን ይህን ከተናገሩ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በገዛ ወታደሮቻቸው መፈንቅለ መንግሥት ተሞከረባቸው። የቱርክ ወታደሮች ከካምፓቸው ወጥተው የቱርክ መንግሥት አፈቀላጤ የሆነውን የቱርክ ራዲዮ ጣብያና ቴለቭዥን ማሰራጫን (TRT) ተቆጣጠረው፣ የመፈንቅለ መንግሥቱን ዜና አወጁ። ኤርዶሃን ይህን እርምጃ አውግዘው ደጋፊዎቻቸውን ለማሰባሰብ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ከሁለት ዓመት በፊት “ጠላቴ” ብለው የፈረጁት በይነመረብ (ኢንተርኔት) ሥልጣናቸውንና ሕይወታቸውን ለማዳን ብቸኛ አማራጫቸው ነበር።

በቱርክ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊ ወታደሮች የተረሳው የአገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ በኤርዶሃን ታማኝ ደጋፊዎች እጅ ስለነበር በይነመረብን ተጠቅመው ሕዝቡ “የቱርክን ዴሞክራሲ” ከመፈንቅለ መንግሥት ለመከላከል አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ከተደበቁበት ቦታ ሆነው ነበር ብሔራዊ ጥሪ ያቀረቡት። የሚድያ ጠላት ተብለው የሚፈረጁት ኤርዶሃን መፈንቅለ መንግሥት እየተደረገ ባለበት ሰዐት ደጋፊዎቻቸውን ለማስሰባሰብ በበይነመረብ ከቲውተር (Twitter) እስከ ፌስታይም (Facetime)  የተጠቀሙ ሲሆን በአንድ ወቅት በቱርክ መንግሥት ከፍተኛ የታክስ ቅጣት የተጣለበት ዶሃን ሚድያ ግሩፕ (Doğan Media Group) እና የታይም ዋርነር (Time Warner) ጥምረት የሆነው ሲ.ኤን.ኤን. ተርክ (CNN Turk) የዜና ተቋም ጋር በቀጥታ በአይፎን ስልክ የሚሠራውን ፌስታይም (Facetime) አፕሊኬሽን በመጠቀም ቃለ ምልልስ አርገው ሕዝባቸው ለመፈንቅለ መንግሥቱ እንቢታውን እንዲገልጽ ብሔራዊ ጥሪ በማድረግ የታንክን አፈሙዝ በበይነመረብ ወይም ኢንተርኔት ጠምዝዘው ሕይወታቸውንም ሥልጣናቸውንም ከአደጋ ታድገዋል።

በይነመረብ ሥልጣን አልለቅ ብለው ወንበር ላይ ዐሥርት ዓመታትን ሙጭጭ ብለው ለተቀመጡ አምባገነን መሪዎች ጠላት ነው። በቅርቡ በኡጋንዳ በተደረገው አገራዊ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት “ምርጫው ሠላማዊና የተረጋጋ ሆኖ እንዲጠናቀቅ” ወይም  በትክክለኛው ትርጉሙ፣ የተቃዋሚ ኃይሎችን ድምፅ ለማፈን የዩጋንዳ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ማኅበራዊ ሚድያዎችንና የአጭር ጽሑፍ መለዋወጫ መተግበሪያዎችን አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ ነው። ይህ ዓይነት እርምጃ በአምባገነን መንግሥታት የሚወሰደው በአገሪቱ ውስጥ በመሪው አካል የሚወሰዱ ሕግን የጣሱ እርምጃዎች ወደ ሚድያ ወጥተው ለዓለም እንዳይደርሱ ነው። የተለያዩ የሰብኣዊ መብት አራማጆችም ምርጫው ይህ ግድፈት ታየበት፣ መንግሥት ይህን አስሯል፣ ምርጫውን አጭበርብሯል እና አደባባይ ወጥተን ደምፃችንን ማሰማት አለብን የሚሉ መልዕክቶች ከማስተላለፍ ይልቅ፣ መንግሥት ይህን ደረገጽ ዘግቷል፣ ይህን ሚድያ አፈነ ከማለት ውጪ ስለምርጫው ወቅታዊ ሁኔታ እንዳይከታተሉ አድርጓቸዋል።

Sunday, September 4, 2016

የቂሊንጦ ወኅኒ ቤት ቃጠሎ ጉዳይ…

በናትናኤል ፈለቀ
(አርታኢ፤ በፍቃዱ ኃይሉ)

በምርጫ 1997 ማግስት የአደባባይ አመፆች ተበራክተው ነበር፡፡ በጥቅምት 24፣ 1998 አዲስ አበባ በሕዝባዊ አመፅ ስትናወጥ፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥም ሊሰጠው ይገባው የነበረውን ያክል ትኩረት ሳያገኝ ያለፈ ትራጄዲ ተከስቶ ነበር፡፡ በወቅቱ እልፍ በኦ.ነ.ግ. ሥም ተወንጅለው የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች የቃሊቲ ግቢ ውስጥ ታጉረው ነበር፡፡ ታዲያ ግቢው ውስጥ በተፈጠረው ግርግር ‹ሊያመልጡ ሞክረዋል› በሚል 163 የሚደርሱ ታራሚዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸውን አጥተው ነበር፤ መንግሥት የሟቾቹ ቁጥር ዐሥር እንኳን እንደሚሞላ አላመነም ነበር፡፡

‹ሻዕቢያ› በቂሊንጦ እና ቃሊቲ ወኅኒ ቤቶች እጅግ ዝነኛ ሥም ነው፡፡ ‹ሻዕቢያ› በሚባል ቅፅል ሥም የሚጠራው የዋርድያዎች ኃላፊ፣ በቂሊንጦ የሚገኙ ተመላላሽ እስረኞች በፍርሐት ይርዱለታል፡፡ ‹ሻዕቢያ› ከ1998ቱ የቃሊቲ እስረኞች እልቂት ጋር ሥሙ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በወቅቱ የተነሳውን ግርግር ተከትሎ አግድም በመተኮስ ለብዙ እስረኞች እልቂት ምክንያት የሆነው ይኸው ‹ሻዕቢያ› የተባለ ግለሰብ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ ቃሊቲ እስር ላይ የነበሩ ሰዎች እንደሚናገሩት፣ ሊፈቱ ጥቂት ቀናት የቀራቸው ሰዎች ሳይቀሩ ክፍላቸው በተቀመጡበት ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አግድም የተተኮሰው ጥይት ክፍላቸው ውስጥ አርፈው የተቀመጡትን እስረኞች የወኅኒውን የቆርቆሮ ግድግዳዎች እየበሳ በተቀመጡበት ጭንቅላታቸውን ስለመታቸው ነው፡፡ (‹ሻዕቢያ› በዚህ ዓመት አጋማሽ በከባድ የውንብድና ወንጀል ተጠርጥሮ ከሥራ ታግዷል)

ይህ በሆነ ማግስት እና በተከታዩ ሳምንት የቤተሰብ መጠየቂያው አጥር የቀብር ቦታ ይመስል እንደነበር በወቅቱ እዚያ የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ እስረኛ ቤተሰብ የነበረው ሰው ሁሉ ይመጣና ‹እከሌን አስጠሩልኝ› ሲል የሞት መርዶ ይመለስለት እና ‹ዋይታ› መጠየቂያውን ቦታ ያጥለቀልቀው እንደነበር በሐዘን ያስታውሳሉ፡፡


‹ዋይታ› ራሱን ደገመ!

ዛሬ (ነሐሴ 29፣ 2008) ቂሊንጦ የታሰሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ሊጠይቁ የሔዱ ሰዎች እስረኞቹ ሁሉ የሉም የሚል መልስ እየተሰጣቸው በዋይታ እና ለቅሶ እየታጠቡ ግማሾቹ ተስፋ ባለመቁረጥ እዚያው አካባቢ በፖሊስ እየተዋከቡ ሲቆዩ፣ ቀሪዎቹ መሔጃ በማጣት እና በተስፋ መቁረጥ ወደቤታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ መንስዔ ትላንት በወኅኒው ግቢ የተነሳው ከፍተኛ የእሳት አደጋ ነው፡፡

ቅዳሜ (ነሐሴ 28 ቀን 2008) ጠዋት 2፡30 ጀምሮ እስከ 10፡00 ሰዐት ድረስ ቂሊንጦ የሚገኘው ‹በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የአዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ› በእሳት ተያይዞ ሲነድ እና ከባድ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ ውሏል፡፡ በወቅቱ የተነሱ የምስል ማስረጃዎች እደሚያረጋግጡት እና በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች እንዳስረዱት እሳቱ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ሲነድ እና ከውስጥ የፍንዳታ ጩኸትም ይሰማ እንደነበር፣  ጭሱ እስከ 10 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት ላይ ሲታይ እንደነበር ነው፡፡


የአደጋው ሪፖርት

የእሳት አደጋውን የአገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛ እየተከታተሉት ሲዘግቡ ውለዋል፡፡ በገዢው ፓርቲ አባላት የሚዘወረው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድረ-ገጹ እንደዘገበው በአደጋው ምክንያት አንድ ሰው እንደሞተ እና እሳቱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በቦታው የተገኙ 3 ‹የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሥልጣን› ባልደረቦች ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው፤ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬትን ጠቅሶ ዘግቧል (በምሽት የሬድዮ ዘገባው ቀላል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር 6 አድርሶታል)፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣም በዘገባው እሳቱ እስረኞች ማቆያ ግቢ ውስጥ ከሚገኝ የመመገቢያ ቦታ (ካፌ) እንደተነሳ እና ዞን 3 ድረስ ደርሶ እንደ ነበር በሥም ያልጠቀሳጨውን ምንጮች ጠቅሶ ዜና የሠራ ሲሆን እስረኞች ለማምለጥ ሙከራ ከማድረግ እዲቆጠቡ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ለማስፈራራት ወደ ሰማይ ሲተኩሱ ነበር ብሏል፡፡ ገዥውን ፓርቲ የተመለከተ ካልሆነ የፖለቲካ ዘገባ ሲሠራ የማይታወቀው እና በእግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተመው ሳምንታዊው ፎርቹን ጋዜጣም አደጋውን በመከታተል ሲዘግብ እሳቱ ሆን ተብሎ በታራሚዎች የማምለጥ ሙከራ የተቀሰቀሰ እንደሆነ በድረ-ገጹ አስነብቧል፡፡ ፎርቹን ማምሻውን የድረ-ገጹ ዘገባ ላይ አዲስ መረጃ ሲያክል ‹20 የሚደርሱ ታሳሪዎች ተተኩሶባቸው እንደሞቱ› ዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቴሌቭዥን አደጋውን እስረኞች ያስነሱት አድርጎ ዘግቧል፡፡

የእሳት አደጋው ሲደርስ በእሰረኞች ማቆያ አካባቢው የነበሩ የእስረኛ ቤተሰቦች እና ታዛቢዎች እሳቱ የተነሳው የቤተሰብ መጠየቂያ ሰዐት ከመድረሱ በፊት እንደነበር እና ጭሱ ጎልቶ መታየት ከመጀመሩ በፊት የማረሚያ ፖሊሶች ከቦታው እንዳስለቀቋቸው ይናገራሉ፡፡ ማምሻውን የኦሮሞ መብት ተከራካሪው ጃዋር መሐመድ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ‹22 የታሸጉ አስከሬኖችን ከቂሊንጦ ወኅኒ እንደተረከበ እና አስከሬኖቹ በወታደር እየተጠበቁ እንደሆነ› መረጃ እንደደረሰው ዘግቧል፡፡ ለአደጋው ሽፋን የሰጠው የበይነ-መረቡ ሬድዮ ዋዜማ በበኩሉ አካባቢው ላይ ከነበሩ የዓይን እማኞች አገኘሁ ያለውን መረጃ ጠቅሶ የማረሚያ ፖሊሶች ከመጠበቂያ ማማ ላይ ሆነው ወደ እስረኞች ሲተኩሱ እንደነበር ዘግቧል፡፡


የቂሊንጦ ወኅኒ ቤት ገጽታ

ቂሊንጦ የሚገኘው የአዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው የሚከታተሉ 3,100 በላይ የሚሆኑ ወንድ እስረኞች የሚገኙበት ሲሆን፣ በአራት ዞኖች የተከፋፈለ ነው፡፡ ከአራቱ ዞኖች መካከል ሦስቱ እያንዳንዳቸው ለእስረኞች የትኩስ መጠጥ አገልግሎት የሚሰጡበት አነስተኛ ካፌ ያላቸው ሲሆን፣ እነዚህ ካፌዎች ለማብሰል (ለማፍላት) የሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዞን 4 በቅጣት ምክንያት ከሌሎች እስረኞች እዲገለሉ የተወሰነባቸው እስረኞችን ማቆያ ነው፡፡ በዚህ ዞን ውስጥ ካፌ የለም፡፡ ዞን 1፣ 2 እና 3 እያንዳንዳቸው 130 የሚጠጉ እስረኞችን የሚያሳድሩ ስምንት-ስምንት ክፍሎች ሲኖሯቸው፣ ዞን 4 ውስጥ ሁለት የእስረኛ ማቆያ ቤቶች ይገኛሉ፡፡

እስር ቤቱ በቀን ሦስት ግዜ ለእስረኞች ምግብ ያቀርባል፡፡ ይህ ምግብ የሚበስለው በተለምዶ እስረኞች ሜንሲ ቤት ብለው የሚጠሩት ከዞኖቹ ተገልሎ ካለ ቦታ ሲሆን ምግብ የሚታደልበት ሰዓት ሲደርስ ከየቤቶቹ ውስጥ በወር አነስተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው በተለምዶ ሰፌድ እና ጎላ ሠራተኞች ተብለው የሚጠሩ እስረኞች ሜንሲ ቤት ድረስ በመሔድ ምግቡን እስረኞች ክፍል ድረስ ተሸክመው ያመጣሉ፡፡

እስር ቤቱ ውስጥ ሲጋራን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡ ሆኖም ሱስ ያለባቸው እስረኞች በዋነኝነት ከማረሚያ ፖሊሶች ጋር በመመሳጠር ሲጋራና አጤፋሪስን የመሳሰሉ አደንዛዥ ዕፆች አስገብተው ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህን ዕፆችን በእስር ቤቱ ውስጥ ለማስገባት እና ለማከፋፈል በአንዳንድ እስረኞች መካከል ከፍተኛ የሆነ የቡድን ፀብ የሚያስነሳ ፉክክር የሚካሔድ ሲሆን ከኮንትሮባንድ ንግዱም የሚገኘው ገቢ እጅግ ከፍተኛ ነው (የአንድ ኒያላ ሲጋራ ዋጋ ቢያንስ 20 ብር ነው)፡፡

ዕፅ ለማጨስ መለኮሻ የሚሆን እሳት ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ስላለ፣ የተለያዩ አልባሳትን ቀዶ በመግመድ ወይንም ለመተኛ ከሚገለገሉበት ፍራሽ ስፖንጅ በመቅደድ እና በማያያዝ አንዴ የተገኘውን እሳት ለቀናት ሳይጠፋ ያቆዩታል፡፡

በአሁኑ ወቅት እስር ቤቱ ውስጥ በመላው ኦሮሚያ እየተካሔደ ካለው የፀረ-አምባገነን ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ታስረው የሽብር ክስ የተመሠረተባቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት  አቶ በቀለ ገርባ እና የመብት ተሟጋቹ ዮናታን ተስፋዬ፣ የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ሽፈራው እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የነበሩ ሌሎች ወጣቶች፣ በሚያዝያ 2006 የታሰሩት ኦሮሞ ተማሪዎች እና ወደኤርትራ ሊኮበልሉ ሲሉ ተያዙ የተባሉት የአየር ኃይል ጓዶች (በእነመቶ አለቃ ማስረሻ መዝገብ) እንዲሁም ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞ ይገኛሉ፡፡

በቃጠሎውና በተኩሱ ምክንያት የተጎዱ እስረኞች ቁጥር ስንት እንደሆነና ጉዳት የደረሰባቸው እስረኞች ማንነት ባለመገለጹ ምክንያት፣ እንዲሁም እስረኞቹ ወደሌላ ወኅኒ ቤት ተዛውረዋል በሚል ቤተሰቦች የዘመዶቻቸውን ደኅንነት ባለማረጋገጣቸው በእስር ቤቱ ውስጥ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በፖለቲካ እስረኞች ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ ወይንም ስለ ደኅንነታቸው ማረጋገጫ መንግሥት የማይሰጥ ከሆነ ከፍተኛ አፀፋዊ የሕዝባዊ የአመፅ እርምጃ እንደሚወስዱ የኦሮሞ መብት አራማጆች ትላንት ማምሻውን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

እያገባደድን ባለው ዓመት ሕዳር 21 ቀን በጎንደር በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ በተነሳ እሳት17 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡