Tuesday, January 5, 2016

“በመጨረሻም ፍትሕ ከጎናችን ትቆማለች”



በበቀለ ገርባ

(ይህ ጽሑፍ በቀለ ገርባ በቀድሞ ክሱ እንዲከላከል በተወሰነበት ጊዜ የሰጠው የተከሳሽነት ቃሉ ነው፡፡)

ነሐሴ 21/2003 ከምሠራበት ቦታ በስልክ ተጠርቼ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ ከሚጠራው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ተወስጄ ከአንዲት ትንሽ ጨለማ ክፍል ውስጥ ከተወረወርኩ በኋላ በማግስቱ አራዳ ወረዳ ፍ/ቤት ቀርቤ የሃያ ስምንት ቀን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆብኝ ተፈቅዶላቸው፣ ያም ሲያልቅ እንደገና ሌላ ቀጠሮ ተጠይቆ ተፈቅዶላቸው፣ የማይመለከቱኝን ጥያቄዎች ስጠየቅና ስመልስ ቆይቼ ጥቅምት 3/2004 በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቤ የክስ ወረቀት ደርሶኝ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተልኬ እነሆ እስከዛሬ ድረስ ዞን አንድ ቅጣት ቤት ተብላ በምትጠራው ቤት እገኛለሁ፡፡

የቀረበብኝ ክስ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 የተመለከተውን በመተላለፍ የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት ወንጀል ሲሆን ዝርዝሩ፡- “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦ.ነ.ግ./ አባል በመሆን ሶሎሎ ጎልቦ ሥልጣን ወስደሃል፤ በጥር ወር 2002 በአምቦ ከተማ ኦ.ነ.ግ. በቅርብ ወደ ሀገር ውስጥ አሸንፎ ይገባል፤ ከጎኑ ቆመን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት መጣል አለብን ብለህ መመሪያ ሰጥተሀል፤ በሐምሌ 2003 ተማሪዎችንና ሕዝቡን ለአመጽና ለብጥብጥ እንዲነሳሱ ቅስቀሳ አካሂደሀል፤ እንዲሁም በ2004 በመላው ኦሮሚያ አመጽና ብጥብጥ በማነሳሳት በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት መጣል አለብን በማለት ትዕዛዝ አስተላልፈሀል፤ በዚሁ ወር የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህርነትህን ሽፋን በማድረግ ቢሮህ ተገኝተው የመመረቂያ ጽሑፍ ሊሰጡህ የመጡትን ተማሪዎች በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በኃይል ከሥልጣን እናውርድ በማለት መመሪያ ሰጥተሀል” የሚል ነው፡፡

እነዚህ የቀረቡብኝ ክሶች ፈፅሞ የሐሰት ውንጀላዎች መሆናቸውን ለማስረዳት በመጀመሪያ ደረጃ ትጥቅ ትግልና ሠላማዊ ትግልን አስመልክቶ ያለኝን አቋምና እምነት ባጭሩ ከገለጽኩ በኋላ በቀረቡብኝ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃ ላይ ያሉትን እውነታዎች አቅርቤ በአጭሩ የማጠቃለያ ሐሳብ እደመድማለሁ፡፡

(1) የትጥቅ ትግል በአንድ ወገን ድል አድራጊነት የሚጠናቀቅ እንደመሆኑ አሸናፊውን ወገን ክብርና የበላይነትን ሲያጎናጽፍ ተሸላሚውን ወገን ደግሞ የውርደትና የበታችነት ስሜት ይፈጥርበታል፡፡ በዚሁ የተነሳ ተሸናፊው ወገን ቂም አርግዞ ጊዜውን ጠብቆ አድፍጦ የሚያደባበት ስለሆነ እውነተኛ ያልሆነ አሉታዊ ሠላም የሰፈነበት ነው፡፡ ፖለቲካውም የምሬት፣ የጥላቻ የበቀልና የጠላትነት ስለሚሆን እስራት፣ ስደት፣ ከሥራ መፈናቀልና ሌሎች ምስቅልቅሎችን ያስከትላል፡፡ ይህን የትግል ዘዴ በታሪካችን ደጋግመን ሞክረነዋል፡፡ መዘዙንም ቀምሰነዋል፤ ለኋላ ቀርነታችን አንደኛው ምክንያት ሆኗልና፡፡ በአንፃሩ ግን ሠላማዊ ትግል አሸናፊ ተሸናፊ ስለሌለው መቋጫው እርቅ ወንድማማችነትና ዘላቂ ሠላም ነው፡፡ አዎንታዊ ሠላም የፖለቲካውንም ልዩነትና ብዙኃነትን ስለሚያስተናግድ የሚማረር ወገን አይኖርም፡፡ ስለዚህ ተመራጭ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ የትግል ዘዴ መሆን አለበት የሚል እምነት ስላለኝ ሕጋዊ በሆነ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ የድርሻዬን በማበርከት ላይ እገኛለሁ፡፡

(2) የትጥቅ ትግል አሸናፊው ቡድን የአልበገር ባይነት ስሜት እንዲሰማውና እብሪተኛና ጨካኝ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ድሉን ለማግኘት ለከፈለው መስዋዕትነት ካሣ ፈላጊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሥልጣንንና የሀብት ምንጮችን ጨምድዶ በመያዝ በትግሉ ያልተሳተፉትን በማግለል ፍትሐዊ ክፍፍልን አዛብቶ የዜጎችን የዕኩልነት መብት ወደ መርገጥ ያመራል፡፡ ውሎ ሲያድርም ይህን ክስተቱን ማረም ስለሚያሳነው የሐሳብ ልዩነትን የማይቀበል አምባገነን ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት መብታቸውን የሚጠይቁ ዜጎችን በጠላትነት ፈርጆ ሊያጠፋባቸው ሕጋዊ የሚመስል ሕገወጥ ድርጊቶችን በስውርና በግልጽ በመፈፀም ለሌላ ትጥቅ ትግል በር ይከፍታል፡፡ ይህን የትጥቅ ትግል ዑደት አንድ ቦታ ላይ ሰብሮ በማቆም አገሪቱን ከትርምስና የመገዳደል ባሕል መታደግ የሚቻለው ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ሳይገድሉ እየሞቱ እየታሠሩና ከሥራ እየተፈናቀሉ በሠላማዊ መንገድ ብቻ በሚታገሉ ኃይሎች አማካኝነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መርጬ እየተጓዝኩበት ያለሁትም ይህን ነው፡፡

(3) የትጥቅ ትግል ሰብኣዊና ቁሳዊ ሀብትን ከማውደሙም በላይ ጊዜያዊም ቢሆን ስርዓት አልበኝነትን ያስከትላል፡፡ በጣም ውስን በሆነች የሀገር ሀብት አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ የሚሄድ ከሆነ መጨረሻችን የት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ የትጥቅ ትግል ለዜጎች ስንዴና ዘይት እንኳን ማቅረብ የማይቻል እንደኛ ያለ አገር ቀርቶ የሚዋጉበትን በጦር መሣሪያ ለሚያመርቱ አገሮች እንኳን አዋጭ ስላልሆነ ዘለው አይገቡበትም፡፡ ብጥብጥና ሁከት በሚነሳባቸው አገሮች ዋነኞች ተጎጂዎች ተራ ዜጎች እንጂ እንደከሳሾቼ ያሉ ባለሥልጣናት ወይም የመንግሥት መሪዎች አይደሉም፡፡

በኛ አገርም ይህ ሁኔታ ቢከሰት ግንባር ቀደም ሰለባ መሆን ከሚችሉት ውስጥ እኔና ቤተሰቤ እንገኛለን፡፡ ምክንያቱም የምንጓዘው በተራ ትራንስፖርት፤ የምኖረው በተራ መንደር፣ በተራ ቤት፣ ልጆቼ የሚማሩት በተራ ትምህርት ቤት ሲሆን ከሳሾቼ ግን ይህ ሁሉ የማይመለከታቸውና የማያሰጋቸው በመሆኑ ከነሱ የበለጠ ሠላም ለኔ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ስለዚህ ነው ምንም ዓይነት ዜግነት፣ ቀለም ወይም ዘር ይኑረው ሰብኣዊና ቁሳዊ ውድመትን የሚያስከትል ጦርነትም ሆነ ብጥብጥ ከሚያራምድ አካል ጋር የማልተባበረው፡፡

(4) በትጥቅ ትግል ወደ ሥልጣን የሚመጡ መንግሥታት ከውይይትና ድርድር ይልቅ በኃይል መፍትሔ ስለማያምኑ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ከማቀጨጭ አልፎ እስከነአካቴው ይፃፀራረሉ፡፡ ለይስሙላ በሚገኙባቸው የድርድር መድረኮችም ሌላም ወገን እንዲቀበል የሚፈልጉትን ለመንገር እንጂ ሰጥቶ ለመቀበል ስላልሆነ በድርድሩ ማግስት ወደቀድሞ የኃይል ተግባራቸው ይመለሳሉ፡፡ ሕዝቡ የጦር ሜዳ ገድሎቻቸውን አይቶና ሰምቶ አይበገሬነታቸውን ተረድቶ በፍርሐት እንዲገዛላቸው ሜዳውን በጦርነት ወሬ ያደምቃሉ፡፡

በሠላማዊ ትግል አግባብ ሥልጣን የሚይዙት ግን የሥልጣናቸው ምንጭ የሆነው ሕዝብ ጥቅሙና መብቱ ካልተጠበቀለት ነገ ደግሞ ለሌላ መስጠት እንደሚችል ስለሚገነዘቡ ዜጎቻቸውን ያከብራሉ፤ ከመፍራት ይልቅ መከበርን ይሻሉ፤ ከመናገር ይልቅ ማዳመጥን ያስቀድማሉ፡፡ እውነተኛ ዴሞክራሲን በማስፈን ሕዝባቸውን ወደ ዘላቂ ሠላምና ዕድገት ይመራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሠላማዊ ትግል ነው እንዲካሄድ የምሻውና ዋጋ እየከፈልኩበት ያለው፡፡

(5) በእምነት ዝንባሌዬ ነፍስ የፈጣሪዋ ብቻ ስለሆነች የሰውን ልጅ ነፍስ ማጥፋት ከወንጀል አልፎ ሀጢያት መሆኑንና ይህን ክቡር ነገር በኃይል ከሰው የሚነጥቁ ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ እንደሚነጠቁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ሠይፍ የሚመዙ በሠይፍ ይጠፋሉ” የሚለውን መለኮታዊ ቃል አምናለሁ፡፡ ስለዚህ የኃይል ተግባርን እንደአማራጭ ወስጄ አላውቅም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፈጣሪ እውነት ነው፤ በፈጣሪ የሚያምን ሁሉ እውነትን ያመነ ማለት ይገባዋል፡፡ “እውነትን ሲሻና ለፍትሕ ሲከራከር በፍቅር ብቻ ማድረግ አለበት” የሚለውን የጋንዲ “ሳትያግራህ” ፍልስፍና እቀበላለሁ፡፡ “‹ሳትያግራህ› የእውነት ኃይል፤ የፍቅር ኃይል” ማለት ሲሆን ጥቃት ለሚሰነዘር ሰው አፀፋ ሳይመልሱ በፍቅር ቀርቦ በውስጥ ያለውን መልካም ነገር በማንቀሳቀስ በሕሊና ወቀስ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ማድረግ ይቻላል የሚል ፍልስፍና ነው፡፡

ይህ የሠላማዊ ትግል የመጨረሻ ተሞክሮ በሠላማዊ ታጋዩ ወይም ሳትያግራሂው ላይ ከፍ ያለ ሥቃይን የሚያስከትል እንደመሆኑ በአስተሳሰቦች በሞራላዊነታቸውና በትዕግስታቸው የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች ብቻ የሚተገብሩት ነው፡፡ ከሳትያግራህ የሠላማዊ ትግል ስልቶች አንዱና ዋንኛው ከክፉ ሥራ ጋር ያለመተባበር ነው፡፡ እኔም አንድን ዓላማ ለማሳካት ኃይልን ከመጠቀም የበለጠ ክፉ ነገር አለ ብዬ ስለማላስብ ከእንዲህ ዓይነት ተግባር ጋር ተባብሬ አላውቅም፡፡ እንግዲህ ትጥቅ ትግል ውስጥ ያልተሳተፍኩት እላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች እንጂ በማንምና በምንም ፍራቻ አሊያም አጋጣሚ አጥቼ አልነበረም፡፡ ከሳሾቼ እንደሚሉት ልጆቼ ሳላፈራና በትምህርት ሳልገፋ በአፍላ የወጣትነት ጊዜዬ ያላሰብኩትን ድንገት በሃምሳኛ ዓመት ዕድሜዬ ላይ በተራ የኦ.ነ.ግ. ተዋጊነትና ካድሬነት ለመሠልጠን ኬንያና ሰሎሎ አልሄድኩም፡፡

ነፍስ ካወቅኩ ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች መብት እነንዲከበር ጽኑ ፍላጎትና አቋም የነበረኝ ቢሆንም ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ መሆን አለበት የሚል እምነት ስላልነበረኝ እስከ 2002 ድረስ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኜ አላውቅም፡፡ ተሰጥኦውና ዝንባሌው ያላቸው ጥቂቶች የፖለቲካ ማኅበር መሥርተው ለሥልጣን ተወዳድረው ሕዝባቸው በፍትሐዊነት ማስተዳደር ከቻሉ ሌሎች ዜጎች በተለያየ ሙያ ተሰማርተው አገራቸውን ማገልገል አለባቸው ብዬ ስለማምን እኔም በመምህርነት ሙያ ብቻ ተሰማርቼ ተግባሬን በትክክል ስወጣ ኖሬያለሁ፡፡

ይሁን እንጂ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰዎች ስብስብ እንደመሆናቸው መጠን ሁሉን ነገር ያለእንከን ይፈፅማሉ ብሎ ማመን ስለማይቻል ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በመረዳት ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ፓርቲ የሚሰብከውን መተግበር እየተሳነው ሲሄድ ወይም በተፃራሪው ሲተገበር ሆን ብሎ አለመሆኑን ለራሴ ለማሳመን ሃያ ዓመታት ያህል ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በመጨረሻም በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል ዝም ብሎ መመልከትን ሕሊናዬ አልቀበል አለኝ፡፡

  • ሦስት መቶ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ጥያቄ እንኳን ሳይቀርብላቸው በአንድ ቀን ሲባረሩ
  • በየዩንቨርስቲው ያሉ ሌሎች ደግሞ በዓመቱ ሲደበደቡና ሲንገላቱ
  • የፋብሪካ ዝቃጭ አተላዎች በማንአለብኝነት ሕዝብ ወደሚጠጣቸው ወንዞች ሲለቀቁና አደጋ ሲያስከትሉ
  •  ለፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛውን ገቢ የሚያስገባ ሕዝብ በአንፃሩ ግን በነፍስ ወከፍ እጅግ ዝቅተኛው የፌዴራል በጀት ድጎማ ሲመደብለት
  •  መሬቱ በሰበብ አስባቡ በግፍ እየተወሰደ ተቸብችቦ ሌሎችን ባለፀጋ ሲያደርግ፤ የሱ ቤተሰቦች ግን የትም ሲበተኑ
  • ቋንቋው ቀድሞ ሲነገር ከነበረበት ቦታ እየጠፋ ሲሄድ
  • ከኤኮኖሚው ዘርፍ ወጥቶ የበይ ተመልካች ሲሆን
  • የዛሬ 120 ዓመት የኦሮሞ መንደር በነበረችው ፊንፊኔ በቋንቋው የሚማርበት አንድ ትምህርት ወይም አንድ የእምነት ሥፍራ እንኳ ሲነፈገው
  •   የፌዴራል ሠራተኞች ቅጥርና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራር ብሔራዊ ተዋጽኦ አግባብ ባልሆነ መልኩ ሲከናወን
  • ከሁሉም በላይ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ሥልጣን ሲይዝ በእስር ቤት ከነበሩ ኦሮሞ፣ ዛሬ በብዙ እጥፍ የሚሆኑት በፌዴራል ወህኒ ቤቶች ሲማቅቁና ቤተሰቦቻቸው በረሀብ አለንጋ ሲገረፉ እያየሁ ዝም ማለት እንዴት ይቻለኛል?

እነዚህ ነገሮች እንዲስተካከሉ ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠራት በሠላማዊ መንገድ አስተዋፅኦ ለማድረግ የአንድ ፓርቲ አባል መሆንን ሳውጠነጥን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኦ.ፌ.ዴ.ን./ ጥሪ አድርጉልኝ በ2002 ለመጀመሪያ ጊዜ አባል ሆንኩ፡፡ ከዚያም የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆንኩ፡፡ በ2002 ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኜ መላው ሕዝባችን በሚያውቀው ሁኔታ ተሸነፍኩ፡፡ በምርጫ ዘመቻ ወቅትም በግልና በቡድን የተካሄዱብኝን ትንኮሳዎች ተቋቁሜ መንግሥት ባሰማራቸው ሁከት ፈጣሪዎች መካከል ቆሜ ለሠላማዊ ትግልና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን ያለኝን ቁርጠኝነት አስመስክሬያለሁ፡፡ ምርጫውን እንደማላሸንፍና መጨረሻዬም አሁን ያለሁበት እስር ቤት እንደሆነ እየተነገረኝ አንድ ሠላማዊ ታጋይ ማድረግ ያለበትን አድርጊያለሁ፡፡

በፓርቲዬ ውስጥ በተሰጠኝ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ድርሻ ምክንያት በእስር ላይ ስላሉ ኦሮሞዎች ሁለት ጊዜ ያህል ለውጪ ሚዲያዎች ቃለ መጠይቅ በመሰብሰብ ከሳሾቼን እንዳላስደሰታቸው ከራሳቸው ተነግሮኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰጠሁት መረጃ ሐሰትም፣ ምሥጢርም እንዳልሆነ ነግሬያቸው በተያየን በሃያ ቀናት ከቢሮዬ ተጠርቼ ታሰርኩ፡፡ ከመታሰሬ ጥቂት ቀናት በፊት ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመጡ ሰዎች አነጋግረውኝ ነበር፡፡ የእነዚህ ነገሮች ድምር ነው “የሀገር የሕዝብን አንድነት በማፍረስ” ወንጀል አስከስሶ ለእስራት የዳረገኝ፡፡

በሕዝቦች መካከል ግልጽ ልዩነት እየፈጠረ አንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር ኅብረቱ እንዲላላና አንድነቱ እንዲፈርስ እያደረገ ያለ ስርዓቱ ነው ወይስ ይህ ሁኔታ እንዲስተካከል በሠላማዊ መንገድ እያሳሰበ በመታገል ላይ ያለ ሰው ነው የአገሪቱን የግዛትና የፖለቲካ አንድነት በማፍረስ ወንጀል የሚጠረጠረው? ሕገ-መንግሥቱን በተግባር እየጣሰ ያለውስ መብቴ ይከበር የሚለው ነው ወይንስ መብቱን የተነፈገው ነው?

ድርጅታችን በኦ.ፌ.ዴ.ን ሕዝቦች መብታቸው እስከተከበረላቸው ድረስ የመገንጠል ጥያቄ አያነሱም መለየትንም አይፈልጉም የሚል እምነት ስላለውና የሀገር አንድና ቁልፍ እውነተኛ ዕኩልነት የሰፈነበት ስርዓት ማስፈን መሆኑ ያምናል፡፡

ስለዚህ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ያለው እስከመገንጠል የሚለው ሀረግ ጠቃሚ አይደለም በሚል እምነት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ መለስተኛ የፖለቲካ ፕሮግራም ውስጥ እንዲካተት ከፈረሙት አባል ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እኔም የድርጅቱ አባልና አመራር ይህን ለማሳመን ጎንበስ ቀና በምልበት ሰዐት የሀገር አንድነትን ለማፍረስ በመሞከር እንዴት ልከሰስ እችላለሁ?

ማንኛውም ኦሮሞ መብቱን የመጠየቅ አዝማሚ ወይም ከስርዓቱ ጋር ያለመተባበር ዝንባሌ ያሳየ እንደሆነ በኦነግነት ፈርጆ ማናቸውንም የግፍ ተግባር መፈፀም ከተጀመረ ሃያ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ይህ አድራጎቱ በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ሲታይ ወደር የለሽ ነው፡፡ ናይጄሪያ በየጊዜው ፍንዳታ እየደረሰ ኃላፊነት በሚወስደው የቦኮሃራም ድርጅት አግባብ ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩና ተመሳሳይ እምነት የሚከተሉ ዜጎቿን ቁም ስቅል አላሳየችም፡፡ የወደቀው የግብጽ መንግሥት እንኳን ሕገወጥ ነው ብሎ በፈረጀው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አመካኝቶ ተቀናቃኞችን ለማጥፋት ዘመቻ አልከፈተም፡፡ ከአንድ የዘር ሀረግ የተገኘ ሁሉ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት አለው ብሎ የሚገምት ቢኖር በሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ይመስለኛል፡፡ ሀገር የሚያፈርሰው እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነው፡፡ እኔ ግን ይህን በመርህም ተቀብዬ በተግባርም ሞክሬ አላውቅም፡፡

ነገር ግን ለስርዓቱ ካለመመቸት ውጪ በሀገሬና በሕዝቤ ላይ አንዳች ጥፋት እንዳልፈፀምኩ ጠንቅቀው የሚያውቁት ከሳሾቼ በወህኒ ቤቶች አካባቢ “አዳፍኔ” በመባል የሚታወቁ የሐሰት ምስክሮችን አቅርበው አስመስክረውብኛል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ 1ኛ ነገሥት ምዕራፍ 21 ላይ አጽመርስቴን አልለቅም ስላለ “ንጉሡንና እግዚአብሔርን ሰድቧል” ብለው የሐሰት ምስክሮችን አስመስክረው ናቡቴን በድንጋይ አስወግረው እንዳስገደሉት የአክአብ ባለሥልጣኖች የሰው ልጆች መብት ይከበር ባልኩ ኢትዮጵያዊው ናቡቴ ሆኜ ቀርቤያለሁ፡፡ ይህ ድርጊት ከዚህ በፊት የማሞ መዘምር ከሳሾች እራሳቸው ሲኒማ ቤት ውስጥ የእጅ ቦምብ ወርውረው ብዙ ሰዎችን ካቆሰሉ በኋላ ይህን ያደረገው ማሞ ነው በማለት በሐሰት አስመስክረው ሞት ተፈርዶበት ዓለም በቃኝ እስር ቤት ውስጥ በስቅላት ተቀጥቷል፡፡

በኔ ላይ ያቀረቡት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በቁጥር አራት ሲሆኑ ሁለቱ ቤቴ ሲፈተሽ ታዛቢ የነበሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም ያዩትን በመመስከራቸው በምስክርነት ቃላቸው ውስጥ ወንጀለኛ የሚያሰኘኝ ነገር ባለመኖሩ ሌሎች ሁለት ምስክሮች በሰጡት የሐሰት ምስክርነት ቃል ላይ አተኩራለሁ፡፡ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሆኖ ያቀረበብኝ አንደኛው ሰው በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዬ ሆኖ የተመደበ የክረምት ተማሪ ኢዮስያስ አበራ ማሞ ከሌሎች ተማሪዎች ተነጥሎ ቢሮዬ መጥቶ የገዥው ፓርቲ አባል እንደሆነ ይህን ያደረገውም የደኅንነት አባል የሆነውን አባቱን በመፍራት እንደሆነ አሁን ግን በፓርተው ውስጥ የሰፈነውን ኢፍትሐዊነት በመፀየፍ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን እንደሚፈልግ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክን እንደሚያደንቅ ነግሮኝ እንድመለምለው ጠይቆኝ ነበር፡፡ እኔም እኔ ያለሁበት ፓርቲ የኦሮሞ ድርጅት እንደሆነና የመድረክ አባላት ከሆኑ የኅብረብሔር ፓርቲዎች ውስጥ ወስኖ አንዱን መጠየቅ እንደሚችል ነግሬው የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባል የሆነውን የአቶ አንዱዓለም አራጌን ስልክ ቁጥር ሰጠሁት፡፡ ግለሰቡ ክቡር ፍ/ቤቱ ፊት ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ ተማሪዬ እንደሆነ ኮርስ ሰጥቼው እንደማላውቅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው ሐምሌ ወር 2003 የመመረቂያ ጽሑፉን ሊያስረክብ ቢሮዬ በተገኘንበት ዕለት መሆኑን በዚሁ የመጀመሪያ ግንኙነታችን “መንግሥት የኦሮሞንና የደቡብን ሕዝብ ስለሚጠላ ይጨቁናቸዋል፣ ስለዚህ ተነሳስተን በአመጽ እናስወግደው” እንዳልኩት ተናግሯል፡፡ ሌሎችንም ተማሪዎች ጨምሮ እንደተወያየን አስመስሎ መስክሯል፡፡

ይህ ግን ፈፅሞ ሐሰት ነው፡፡ ግለሰቡ አግኝቶኝ የማያውቅ ከሆነ በሐምሌ 2003 ሊያስረክበኝ የመጣው የመመረቂ ጽሑፍ ማን ያማክረው ነበር? ከአማካሪው አንዳች ግንኙነት ሳያደርግ ምንነቱ ያልታወቀ የመመረቂያ ጽሑፉን ይዞ ከመጣ ተማሪ ጋር ያውም በመጀመሪያው ግንኙነት ከአካዳሚ ነክ ጉዳዮች ወጥቶ ስለ መንግሥት ግልበጣ ማውራት ይታሰባል ወይ? ለአንድ የዩንቨርስቲ መምህር ተመካሪ ተማሪዎች የሚመደቡት በሚመለከተው ትምህርት ክፍል እንደመሆኑ የተለያየ ፖለቲካ ዝንባሌ እንዳላቸው እየታወቀ አንድ ወገን ብቻ በሚመለከት ፖለቲካ ውይይት መክፈት እንዴት ይታሰባል? የተከሰስኩት በአሸባሪነት ከተፈረጀ የኦሮሞ ድርጅት ሆኖ ሳለ ግለሰቡ ደግሞ የዚህ ማኅበረሰብ አባል አለመሆኑን በግልጽ እየተናገረ፤ ኦሮሞዎች ተበድለዋልና በመንግሥት ግልበጣ ተባብረን ልል እንዴት እችላለሁ? ይህ ሰው ኦሮሞዎችን ከጭቆና ለመታደግ ከሰማየ ሰማያት የተላከ አዳኝ ነው ብዬ ልገምት አልችልም፡፡ ይልቅ እሱስ ፍትሕን ሲገድል የተመደበ የአክአብ ምስክር ኖሯል፡፡

ሌላኛው ስሜን እንኳን በትክክል ያላሥጠኑት የዐቃቤ ሕግ ምስክር አመና አርኮ በክቡር ፍ/ቤቱ ፊት ቀርቦ ቃሉን ሲሰጥ “በጥር ወር 2002 አቶ ጉቱ ሙሊሳ ቤት ተገናኝተን ለአመጽ አነሳስቶኛል” ሲል ተናግሯል፡፡

እኔ ይህን ግለሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ከዚሁ ፍ/ቤት ውስጥ ነው፡፡ ነገሩ የማይታመንና ዱብዕዳ ስለነበረ በዕለቱ ጥያቄም አላቀረብኩለትም፤ ስለማንነቱ ለማወቅ ባደረግሁት ጥረት በቂና ተጨባጭ መረጃዎችን ለማግኘት ችያለሁ፡፡ ግለሰቡ እውነተኛ ማንነቱ ኢመና ኢርኮ ሳይሆን ሽፈራሁ ኤቢዳ ሲሆን የትውልድ ስፍራው በምዕራብ ሸዋ ዞን ሸነን ወረዳ ሆኖ አድራሻዬና የሥራ ቦታዬ ነው ያለውን ነቀምቴ ከተማ 01 ቀበሌን ረግጦ እንኳን አያውቅም፡፡

ይህ ግለሰብ የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ /ኦ.ሕ.ኮ./ አባል የነበረ ሲሆን በ1997 የምርጫ ታዛቢ ስለነበር በ1998 ታስሮ የተሰቃየ በ1999 አጣሪ ኮሚሽን ፊት ቀርቦ ቃሉን የሰጠ በ2000 ኦሕኮን ወክሎ ለወረዳና ለቀበሌ ምርጫ የተወዳደረ፤ በ2003 እንደገና ታስሮ የነበረ ሲሆን ይህን ሁሉ ያደረገው በእውነተኛ ሥሙ ነበር፡፡ በመጨረሻም ከደረሰበት ስቃይ የተነሳ እንዲሁም የሚሉትን እሺ ካላለ መኖር እንደማይችል ስለተገለጸለት ያሉትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብቶ በመፈታት በኔ ላይ በምስክርነት የቀረበ ነው፡፡ ይህንን የመከላከያ ምስክሮች ያስረዱልኛል፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት ከግለሰቡ ጋር በአካልም ሆነ በማንኛውም የመገናኛ ዘዴ ተገናኝተን የማናውቅ ከመሆን አልፎ ቤቱ ተገናኘን ያለውን አቶ ጉታ ሙሊካን እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ማረሚያ ቤት ሁለታችንም እስረኞች ሆነን ነው፡፡ ይህንንም ምስክሮቼ ያረጋግጡልኛል፡፡ ለመሆኑ 2002 ሕገ-መንግሥቱን አምኜና አክብሬ በምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ የነበርኩ ሰው እንዴት ሆኖ ለአመጽ ቅስቀሳ ማካሄድ የምችለው?

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ግለሰቡ በኔ ላይ ስለመሰከረው ነገር ብቻ ሳይሆን ማንነቱንና አድራሻውን ጭምር እንዲዋሽ የተገደደ እንደመሆኑ መጠን ክቡር ፍ/ቤቱ ይህን ተመልክቶ የሰጠውን የምስክርነት ቃል ውድቅ እንዲያደርግልኝ እጠይቃለሁ፡፡

ዐቃቤ ሕግ ወንጀለኛ ለመሆኔ እንደአስረጂነት ያቀረበው ሌላው የሰነድ ማስረጃ በ1989 መጀመሪያ ላይ የተነሳሁት የኦነግ አርማ ተሰቅሎ የሚታይበት ፎቶግራፍ ነው፡፡ በ1983 መጨረሻ ደርግ እሠራበት የነበረችውን አሰበ ተፈሪ ከተማ ለቅቆ ሲሄድ ብዙ ሰዎች አካባቢውን ለቀው ሲሰደዱ ሠላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የተቋቋመውን ኮሚቴ እንድመራ በሕዝብ ተመርጬ እስከ 1984 መጨረሻ ድረስ ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ ወቅት በከተማው ፍ/ቤት ከፍተው በይፋ ይንቀሳቀሱ ለነበሩ ሁለት የኦሮሞ ድርጅቶች ኦሕዴድና ኦነግ ስብሰባዎችን እየጠራሁና እየመራሁ በገለልተኝነት ስሠራ ቆይቻለሁ፡፡ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ለኦሕዴድ በርካታ ስብሰባዎችን ለኦነግም ጥቂት ስብሰባዎችን ከተማው መሐል በሚገኝ የወረዳው አስተዳደር ጊቢ ሜዳ ላይ መጥራቴን አስታውሳለሁ፡፡ ከነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ የተወሰደ ነው የተሰቀለው ፎቶግራፍ፡፡ ያ ወቅት ሁለት ድርጅቶች እንኳን በመሰብሰቢያ ቦታዎች ቀርቶ በየምሶሶዎቹ ዛፎቹ አርማዎቻቸውን ይሰቅሉ የነበረ የትኩሳት ጊዜ ነበር፡፡

በፎቶግራፍ ላይ እንደሚታየው ቁጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብ ሜዳ ላይ ተሰብስቦ ይታያል፡፡ እንደሚታወቀው ኦነግ በ1984 በመጨረሻ ሽግግር መንግሥቱን ለቆ ከወጣ በኋላ እንዲህ ዓይነት ስብሰባ በመሐል ከተማ አደባባይ ሊደረግ ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በፎቶግራፉ ላይ የሚታዩ ሰዎች ብዙዎች በሕይወት የሉም፡፡ በፎቶግራፉ ላይ የሚታየው የራሴ ገጽታም ከዛሬ ጋር ሲስተያይ የፎቶውን ዕድሜ ይናገራል፡፡ በፎቶግራፉ ላ የሚታየው ቦታም አሰበ ተፈሪ (ጭሮ) መሆኑ ተለይቶ ይታወቃል፡፡ እኔ ደግሞ በ1985 ከዚያ ተዛውሬ ስለሄድኩ እና ወደዚያ ለመመለስ ዕድሉ ስላልነበረኝ፣ ቢኖረኝ ኖሮም ያንን ስብሰባ ማካሄድ እንደማልችል ይታወቃል፡፡

በአጠቃላይ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት በወቅቱ ሕጋዊ የነበረና በሚኒስትሮች ም/ቤት አራት የካቢኔ ሚኒስትሮች የነበሩበትና መዲናዋን (አዲስ አበባን) ጨምሮ በአርማዎቹ አጥለቅልቆት በነበረ ደርጅት አርማ ጋር የተነሳኸው ፎቶ ግራፍ የሀገር ግዛትና ፖለቲካዊ አንድነት ለመንካትህ ማስረጃ ነው ተብሎ ሊቀርብብኝ ስለማይገባ ክቡር ፍ/ቤቱ ውድቅ እንዲደረግልኝ እጠይቃለሁ፡፡

ማጠቃለያ
ያለመታደል ሆኖ በአገራችን መልካም አስተዳደር አፍአዊ እንጂ ተግባራዊ ሆኖ ስለማያውቅ አንዱ የሠራውን ሌላው እያፈረሰ በዓለም ፊት በኩራት አንገታችንን ቀና የምናደርግበት ሳይሆን በሐፍረት የምንሸማቀቅበት፤ ለልጆቻችንም ተስፋን ሳይሆን የስጋት ቅርስ እየተውንላቸው አበሳን እንደ ዱላ እየተቀባበልን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ እንዳይቀጥል የሳተው በጊዜ እንዲመለስ የተጣመመው እንዲቃና የተበላሸው እንዲስተካከል ጎረቤት ሳይሰማ፣ ፈረንጅ ገመናችንን ሳያውቀው አድብተን ስንጠፋፋ ችግራችን ገለጥለጥ አድርገን ተወያይተን ተከራክረን ተወቃቅሰን መፍትሐ እናበጅለት፡፡ ይህንንም አንዱ ባንዱ ላይ ዱላ ሳይሰነዝር ቃታ ሳይስብ፣ ወደ እስር ቤት ሳይጎትተው በሠላማዊ መንገድና በፍቅር እናድርገው የሚል ጽኑ አቋም ነው፡፡ እኔና ድርጅቴ የምናራምደው፤ ይህ በኛ በጎ ጥረትና ፍላጎት ብቻ የሚሳካ ባይሆንም እኛ ግን በዚሁ መንገድ እንጓዛለን፤ ኢፍትሐዊነት አድልኦን አሜን ብሎ ውርደት ከመቀበል መከራና ስቃይን በክብር ማስተናገዳችንን እንቀጥላለን፡፡ በመጨረሻም ፍትሕ ከጎናችን ትቆማለች፡፡
---
ምንጭ፡- ኃይለማርያምን ፍለጋ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉራንጉር ቅያሶች (ሰለሞን ስዩም፣ 2006)

15 comments:

  1. This comment has been removed by the author.

    ReplyDelete
  2. Namaste, I am Rabin Gurung Trekking Guide in Nepal, from west part of Kathmandu Nepal. Well

    I have been more than 20 years Trekking, tour and Peak climbing as Annapurna base camp, Ghorepani Poon hill, Nar Phu Valley, Upper Mustang,

    Manaslu Circuit, Tsum Valley, Langtang Valley, Goshaikunda Lake, Everest base Camp, Everest Chola Pass and Gokyo lake Trekking in Nepal. Some of

    most adventures as Island Peak, Mera Peak, Lobuche peak and Chulu West Peak Climbing that is my real adventures in Nepal.
    I was mountain guide in Nepal fully satisfied those who were with me and freelance Trekking guide in Nepal. The many people are searching independent trekking guide who directly concern with client and guide to Trekking in Himalaya.

    That is main point and handle client. My further planning is Trekking and Expedition main priory Lot’s Trekkers and Climber Go to every trekking

    Region in Nepal. So if any one interest trekking in Nepal can call or do not hesitate to email us, Since my Mountain guide experienced is mostly

    sharing all customer because this is such a great opportunity my life. Thank you very much my client feedback make me huge help. Adventure Mountain Guide in Nepal Rabin gurung.

    ReplyDelete
  3. We are well established IT and outsourcing firm working in the market since 2013. We are providing training to the people ,
    like- Web Design , Graphics Design , SEO, CPA Marketing & YouTube Marketing.Call us Now whatsapp: +(88) 01537587949
    : UK Business Listing Sites List
    good post Mobile XPRESS
    Free bangla sex video:Delivery Companies in UK
    good post Mobile XPRESS

    ReplyDelete