Tuesday, January 19, 2016

“ልማታዊ” የትሮይ ፈረስ በኢትዮጵያ



በበፍቃዱ ኃይሉ

ጥንት፣ ዐሥር ዓመት ከዘለቀ የግሪክ እና ትሮይ ጦርነት በኋላ ግሪኮች ሰለቻቸው እና መላ ዘየዱ። ግዙፍ የጣውላ ፈረስ ገንብተው ውስጡ የተመረጡ ወታደሮችን አስቀምጠው ሸሹ። ይህንን እንደ ድል የቆጠሩት ትሮዮች ለድላቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ፈረሱን ጎትተው ከተማቸው መሐል አቆሙት፡፡ በውድቅት ለሊት፣ ፈረሱ ውስጥ የተደበቁት ግሪኮች ወጥተው የትሮይ ከተማን በማውደም በጦርነቱ አሸናፊነት ተቀዳጁ እስከወዲያኛው ይባላል። ዛሬ-ዛሬ በመላው ዓለም “የትሮይ ፈረስ” (Trojan Horse) የሚለው ሐረግ ‹ለእኩይ ዒላማ መሸሸጊያነት የሚሰጥ መልካም መሳይ ምክንያት› የሚለውን ለመግለጽ ይጠቅማል።


ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የገዢው ፓርቲ ብያኔ መሠረት የኢትዮጵያ ችግር የሠላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ (እንደ ቅደም ተከተላቸው) ነው። ሦስተኛው ለሁለተኛው፣ ወይም ሁለተኛው ለአንደኛው ሲባል ሊጨፈለቁ ይችላሉ። ሦስቱ አብረው እንደሚገኙ ሳይሆን፣ በተራ በተራ እንደሚረጋገጡ ይደሰኮራል፡፡ ሠላም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መኖር አለበት የሚለው የኢሕአዴግ መደምደሚያ የኦጋዴንን፣ የጋምቤላን እና በቅርቡ ደግሞ (በማስተር ፕላኑ ሳቢያ) የኦሮሚያን ሕዝባዊ ጭፍጨፋዎች ለማስተባበል (to justify) ከመዋሉም በላይ ብዙ የተሞተለትን የባድመን መሬት አሳልፎ መልሶ አስከመስጠት አስደርሷል። “ለሠላም” ሲባል! አንፃራዊ ሠላም ባለበት ጊዜ ደግሞ ዴሞክራሲ ለልማት በሚል ሰበብ እየደማ ነው። በሌላ በኩል የዚሁ ብያኔ ባለቤት ኢሕአዴግ “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ አይደለም፣ ግዴታ ነው” ይላል። ስለዚህ ‹ልማትና ዴሞክራሲን አብረን እያስኬድን ነው› የሚል ነቢብ እየደሰኮረ በሌላ አጀንዳ ደግሞ መልሶ ‹ለልማት ሲባል ዴሞክራሲ ይ ቆይ፤ የድኃ ሕዝብ ቀዳሚ ጥያቄ ዳቦ ነው› በሚል ዴሞክራሲን ጥያቄ እንደቅንጦት እቃ ጥያቄ ቸል ይለዋል። የሁሉም ነገር ታዛቢዎች ‹አለ የሚባለው ልማትስ የታለ?› ብለው መጠየቃቸው አልቀረም።

እውን ልማትና ዴሞክራሲ ይጋጫሉ?

ቻይናና ሕንድ፣ ሁለቱም፣ ልማታዊ አገረ-መንግሥት (developmental state) የሚል ማዕረግ አግኝተዋል። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ሕንድ ዴሞክራሲያዊ መሆኗ ላይ ነው። ፋሪድ ዘካርያ  “The Post-American World” ባሰኘው መጽሐፍ ሕንዶችን “በየዓመቱ በአማካይ 9 በመቶ የሚያድግ ኢኮኖሚ ይዘው በመሪዎቻቸው የማይደሰቱ ሕዝቦች ናቸው” ይላቸዋል። በየምርጫው መሪ ይቀያይራሉ። ቻይኖች ግን ለዚህ አልታደሉም። ነገር ግን እነሱ በፈንታው ‹ታድለናል› የሚሉለት ነገር አለ።

ፋሪድን አንድ የሕንድ ባለሥልጣን እንዲህ ብለውታል፡- “በፖለቲካው ረገድ ሕዝባዊነትን የሚያስገኙ ብዙ ቂላቂል ተግባሮችን መፈፀም አለብን።… እነዚህ ነገሮች የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕቅዶቻችንን ያደናቅፋሉ። ነገር ግን ደግሞ ፖለቲከኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ድምፅ ያስፈልጋቸዋል።…” አርክቴክት ኖርማን ፎስተር የተባለ ሰውም ይህንኑ የሚያጠናክር የሚመስል ነገር ለፋሪድ ነግሮታል። “በሕንድ፣ የኸርትሮው 5ተኛ ተርሚናልን ለመገንባት፣ የአካባቢ ተስማሚነት ቅኝት (environmental review) ለማድረግ የወሰደበት ግዜ፣ በቻይና ቢሆን የቤጂንግ አየር ማረፊያን (የኽርትሮው 5ቱንም ተርሚናሎች ቢደመሩ የሚበልጠውን) ጨምሮ ለመፈፀም የሚበቃ ጊዜ ነው።” ቻይናዎች የዴሞክራሲ “ጣጣ” የለባቸውም፤ ኮሚኒስቶቹ ይህንን እንደመታደል ይቆጥሩታል።

የሁለቱን ልዩነት ፋሪድ ዘካሪያ ሲደመድም “ዴሞክራሲ ለረዥም ጊዜ ልማት የራሱ የሆነ ተመራጭነት ሊኖረው ይችላል፤” ይላል። ሆኖም አውቶክራሲያዊ (ሕዝባዊ ተጠያቂነት የሌለባቸው) መንግሥታት “ትልልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማይቀናቀኑት  አቅም ዐቅደው፣ ማስፈፀም ይችልሉ፤” ይላል። ፋሪድ በመደምደሚያው ያልገለፀው አውቶክራሲያዊ መንግሥታት የሚሠሯቸው ፕሮጀክቶች ያለበቂ ‹ሴክተር ሪቪው› በመሆኑ ለዘለቄታው የሚያስከትሉት ችግር መኖር አለመኖሩን ቀድሞ መገመት የማይቻል መሆኑን ነው። እንዲያም ሆኖ የቻይናን ልማት “ተአምራዊ” የሚሉት ኢኮኖሚስቶች የሕንድን የዛን ያክል አያዳንቁትም። ሕንድ የቻይናን ያክል መገስገስ ያልቻለችው በከፊል የሕዝብ ብዛት ዕድገቷን (Population growth rate) እንደ ቻይና መቆጣጠር ስላልቻለች ነው። ዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት የሌለባት ቻይና የሕዝብ ብዛት ዕድገቷን ፍጥነት በጉልበት መቆጣጠር ችላለች። ይህንን ለማድረግ የነደፈችው ስትራቴጂ ብዙ ማኅበራዊ ቀውስ እና ሰብኣዊ እልቂት ያስከተለ ቢሆንም መንግሥቷ አውቶክራሲያዊ ተጠያቂነት አላስከተለም። ያለቀው አልቆ የቀረው በቁሳዊ ጥቅም አንፃር ይለፍለት የሚል አቋም ይመስላል። ሕንድ ዴሞክራሲያዊ በመሆኗ ይህንን ዓይነት ነገር ማድረግ አትችልም፤ “ቻይኖች በሁሉም ነገር ይበልጡናል፤ ከሕዝብ ብዛት ዕድገት ፍጥነት በቀር” የሚሉትን ዝነኛ አባባላቸውንም ያፈሩት ለዚያ ይመስላል።

ግብፆች (እ.ኤ.አ. በ2011) ለአብዮት አደባባይ ሲወጡ አንድ ወጣት የተናገረውን በማስታወስ ንፅፅራችንን እንደምድም። “እኛ ቻይናውያን አደለንም፤ ልማት ያለዴሞክራሲ አንፈልግም። እኛ ሕንዳውያን አይደለንም፤ ዴሞክራሲ ያለልማት አንፈልግም።” እንግዲህ፣ ለመንግሥታት ከሁለት አንዱን መምረጥ ይቀል ይሆናል። ለሕዝቦች ግን ከባድ ነው። ከዴሞክራሲና ልማት አንዱን መምረጥ (ማስቀደም) የቸገራቸው (እንደኔ) ዓይነቶቹ ደግሞ ዴሞክራሲና ልማት በቃልም፣ በዐሳብም እንዳይነጣጠሉ ሲሉ ‹‹ዴሞልማት›› የሚል ጥምር ቃል ይፈጥራሉ።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌደሰር የሆኑት አሰፋ ፍሰሐ ‹‹Development with or without freedom?›› በሚል ርዕስ FSS ያሳተመላቸው ጥናት ላይ ለኢትዮጵያ “ልማታዊ አገረ-መንግሥትነት” ተግባራዊ ትምህርት ሊሰጥ የሚችለው ከቻይና ይልቅ የሕንድ ተሞክሮ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹ሕንድ ብዙ ዘውግን (multiethnic) እና ብዙ ሃይማኖትን በተግባር ከተፈተሸ የፌደራል ስርዓት ጋር አጣምራ የያዘች አገር በመሆኗ ለኢትዮጵያ ከቻይና የተሻለ ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች። ሕንድ ዴሞክራሲና ልማት ተመጋግበው እንደሚኖሩ በኮንግረስ ፓርቲ የበላይነት ካስቻለች በኋላ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ተወልዶላታል።›

ዴሞልማትና የአንድ ፓርቲ የበላይነት

የልማታዊ አገረ-መንግሥት ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱት ምሥራቃውያን ናቸው። በ20ኛው ክ/ዘመን መባቻ ኢትዮጵያውያን ልሒቃን ሥልጣኔዋን ሊኮርጇት ይመኟት የነበረችው ጃፓን ቀዳማዊ እና ምናልባትም ልማታዊነትን ከዲሞክራሲያዊነት ጋር በተሳካ ሁኔታ በማጣመር ብቸኛዋ ናት። ሆኖም፣ ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ለአብዛኛው የ20ኛው ክ/ዘመን ጊዜ በጃፓን የበላይ (dominant) ነበር። ደቡብ ኮርያና ሲንጋፖር ወደ ዴሞክራሲ ከመሸጋገራቸው በፊት በአንድ ፓርቲ ፍፁማዊ እና አውቶክራሲያዊ የበላይነት ልማታዊ ኢኮኖሚን አራምደዋል። ቻይና እስካሁን ድረስ ከኮሙኒስት ፓርቲ በስተቀር በምድሯ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይንቀሳቀስ በሕግ አግዳለች፤ ሆኖም በልማቱ ስኬታማ ነች።

ኢሕአዴግአውያን ይህንን የምሥራቃውያን ሞዴል ወስደው ‹ለልማት ሲባል የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት የግድ ያስፈልገናል› ሲሉ እየሰበኩ ነው። ኢሕዲግአውያኑን ከጃፓን እና ከሕንድ የሚለያቸው የፖለቲካ የበላይነቱን እያገኙ ያሉት በሕዝባዊ ይሁንታ ሳይሆን በኃይል ወይም በማጭበርበር መሆኑ ላይ ነው። ይህ በራሱ ከልማታዊነት ጋር የሚፃረር ነው።

ኢትዮጵያ የተቀበለችው እና ልማትን እንደ ሰብኣዊ መብት የሚመለከተው የተባበሩት መንግሥታት ድንጋጌ (Declaration on the Right to Development) የልማትን ምንነት ሲበይነው፣ “የጠቅላላ ሕዝቡ እና ሁሉም ግለሰቦች ንቁ፣ ነፃ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ብሎም ተገቢ (Fair) የጥቅም ክፍፍልን መሠረት በማድረግ ለቋሚ የደኅንነት (well being) መሻሻል ዓላማ የሚሠራ ጥቅል ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ  እና ፖለቲካዊ ሒደት ነው” ይለዋል። ከዚህ ብያኔ ውስጥ ቢያንስ ‹የሁሉም... ንቁ፣ ነፃ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ› የሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ ፈፅሞ አይስተዋልም። ማይክል ቶዴሮ እና ስቴፈን ስሚዝ ባሳተሙት “Economic development” የተባለ መጽሐፍ ላይ በልማታዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የሕዝባዊ ተሳትፎን አስፈላጊነት “chief end of development” (‹የልማት መጨረሻ ግብ›) ሲሉ ገልጸውታል። የሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰለሞን ንጉሤ ለልማት የሰብኣዊ መብት አካታች አካሔድን ስለመከተል አስፈላጊነት በተነተኑበት (FSS ያሳተመላቸው) ጥናት ላይ ‹በኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲዎችን እና ፕሮግራሞችን ሕዝብን በማሳተፍ የመቅረፅ ፖለቲካዊ ባሕል እንደሌለ ገልጸው፤ ‹በየቀበሌው እና ወረዳው የሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ውሳኔዎችንና ፕሮግራሞችን በግድ ለማስፈፀም ከላይ ወደታች የሚወርዱበት (የሚጫኑበት) እንጂ አሳታፊነትን የሚያበረታቱበት አይደሉም› ይላሉ።

ኢሕአዴግአውያን ሕዝቡ በተሳትፎ ‹እፈልጋለሁ› ያለውን ሳይሆን፣ የፓርቲው ልሒቃን ‹ይበጅሃል› የሚሉትን ለመጫን እንዲመቻቸው የአንድ ፓርቲ የበላይነትን እንደብቸኛ አማራጭ ይወስዱታል። የአንድ ፓርቲ የበላይነት በይሁንታ መገኘት ስላልቻለ ደግሞ የፈጠሩት ይፋዊ ያልሆነ አሀዳዊ ፓርቲ ነው። ሆኖም ፓርቲው በአወዛጋቢ (contested) ሁኔታም ቢሆን አስመዘገብኳቸው የሚላቸው የኢኮኖሚ ዕድገት ቁጥሮች አሉ። ቁጥሮቹን እንመናቸው ቢባል እንኳን ኢኮኖሚስቱ ሎሬት አማርትያ ሴን “የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻውን እንደመጨረሻ ውጤት ሊታይ አይገባውም፤ ልማት የምንመራውን ሕይወት ማሻሻል እና የነፃነታችንን ልክ ማስፋት ላይ ማተኮር አለበት” የሚሉት የኢኮኖሚ ዕድገት ልማትን እንደማያረጋግጥ ለማመልከት ነው። ልማትን በአጭሩ “የምርጫ ነፃነት” ነው ይሉታል።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል  የኢሕአዴግ የበላይነት የሚሰበከው ‹‹ልማቱ እንዳይደናቀፍ›› በሚል ሰበብ ነው። ልማቱ በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ምክንያት እንደማይደናቀፍ ቢያንስ ሕንድ ማሳያ ትሆናለች። ይሁንና አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት፣ የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ተጋብዘው ‹‹ዴሞክራሲያዊ አለመሆን የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያደናቅፍ የሚያረጋግጥ ‹ኢምፔሪካል ሪሰርች› የለም›› ማለታቸው ይታወሳል። ዴሞክራሲ አገሪቱ ውስጥ አለመኖሩ ልማቱን ያጓድለዋል መባሉ ለእርሳቸው ‹የመኝታ ሰዐት ተረት› (“bed time story”) ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገትን ስለማያደናቅፍ ብቻ አውቶክራሲነት ከዴሞክራሲያዊነት የበለጠ የማይመረጥ ቢሆንም፣ የአቶ መለስ ድምዳሜም ስህተት እንዳለበት ማሳየት ያስፈልጋል። እነ ማይክል ቶዴሮ ከላይ በጠቀስነው መጽሐፋቸው ላይ ዴሞክራሲ ልማት ላይ የሚያሳደድረውን ተፅዕኖ በተመለከተ ‹ኢምፔሪካል› ጥናቶች የተለያየ ውጤት እንደሚያሳዩ ቢናገሩም፤ ከነዚህ ጥናቶች ውስጥ ሲሦዎቹ ብቻ ‹ዴሞክራሲ ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ› መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።ሲሦዎቹ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው ሲሉ፣ ቀሪዎቹ ሲሦዎች ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የለውም ብለዋል። ይህም ማለት 2/3ኛ ያክሉ ጥናቶች ዴሞክራሲ መኖሩ ልማቱን ባይጠቅመውም እንደማይጎዳው የሚያረጋግጡ ናቸው ማለት ነው።

“Why Africa is Poor” የሚል መጽሐፍ የጻፉት ግሬጅ ሚልስ የእነማይክል ቶዴሮን ሐሳብ የሚያጠናክር ነገር ጽፈዋል። “ዴሞክራሲ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሚሆነው ለሰብኣዊ መብት ሲባል ብቻ ‹ቢኖር ጥሩ የሆነ› ነገር ስለሆነ አይደለም። ከምሥራቅ እስያ ውጭ ባሉ ታዳጊ አገራት እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 2003 ባለው ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አገሮች ከአውቶክራሲዎች 50 በመቶ የፈጠነ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል።”

ኢትዮጵያ ልማታዊ አገረ-መንግሥት አላት?

ኢሕአዴግ አሁን-አሁን “ልማታዊ ዴሞክራሲ” እያለ የሚጠራው (የአብዮታዊ  ዴሞክራሲ) ርዕዮት ዓለሙ አማካኝነት ካፒታሊዝምን በኢትዮጵያ ካዋለደ በኋላ ‹እከስማለሁ፤ ሊበራል ወይም ሶሻል ዴሞክራት ሆኜ በሌላ ቅርጽ እመለሳለሁ› ይላል። (አቦይ ስብሐት ነጋ ለቪኦኤ ተናግረውታል በሚል አሰፋ ፍስሐ ቀደም ብለን የጠቀስነው ጥናታቸው ላይ እንዳጣቀሱት!) እንመነው ቢባል እንኳ በፖለቲካ የበላይነት ዘመኑ የልማታዊ አገረ-መንግሥት ባሕሪ አዳብሯልን? አሰፋ ፍስሐ ልማታዊ አገረ-መንግሥት “ጠንካራ፣ የተረጋጋ እና ማዕከላዊ፣ እርስ በርሱ የሚግባባ ቢሮክራሲ” ሊኖረው ይገባል ይላሉ።

ጥንካሬን መለኪያው አንዱ የሲቪል ሰርቪሱ አቅም ሲሆን፣ የእኛው ከሙያ ብቃተኞች ይልቅ በፖለቲካ ታማኞች የተሞላ በመሆኑ ጠንካራ ሊባል አይችልም። የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ‹ያሉትንም መያዝ ሆነ አዳዲስ ብቁ ሰዎችን ማፍራት አልቻለም›። “የተረጋጋ” (stable) የሚለውም ቢሆን በፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ሳቢያ የትጥቅ ትግልን መርጠው ያመፁ ኃይሎች በሁሉም አቅጣጫ አሉ። በምሥራቅ ኦ.ብ.ነ.ግ.፣ በሰሜን (ኤርትራ በኩል) ኦ.ነ.ግ.፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ ዴ.ም.ሕ.ት.፣ አ.ዴ.ኃ.ን… በጥቅሉ ሁሉንም ክልሎች እንወክላለን የሚሉ የታጠቁ  ኃይሎች በመኖራቸው ‹የተረጋጋች› የሚለው እንዲበዛባት ሆኗል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ማዕከላዊ (centralized) የሆነ አስተዳደር አትከተልም፤ ፌደራላዊት ናት። ፌደራሊዝም እና ልማታዊነት አብረው እንደማይሄዱ የኢትዮጵያን ምሳሌ በማጣቀስ ፕሮፌሰር ክላፋምን ጨምሮ ብዙ ምሁራን ገልጸውታል። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ቢያንስ በተጻፈ ሕግ ደረጃ “ማዕከላዊ” አስተዳደር የሚሻውን የልማታዊ አገረ-መንግሥት ባሕሪም አያሟላም ማለት ነው።

አሰፋ ፍስሐ “ልማታዊ አገረ-መንግሥት የገዛ መቃብሩን ቆፋሪ ነው ይባላል” ሲሉ ጽፈዋል። ልማታዊ አገረ-መንግሥታት ልማት ሲመጣ ሕዝቡ ዴሞክራሲን እንዲጠይቅ መገፋፋቱ አይቀርም ማለታቸው ነው። ፋሪድ ዘካርያም የምዕራባውያንን ዓይነት የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ደርሳ የነሱን ያክል ዴሞክራሲ ላይ ያልደረሰች ብቸኛዋ አገር ሲንጋፖር ነች ይላል። እሷም ብትሆን ትንሽ ከተማ የምታክል አገር በመሆኗ በተለየ ዓይን ልትታይ ትችላለች። ‹ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ፖለቲካዊ መሻሻልን በግድ ያስከትላል› የሚለውን አባባል የሻረች የምትመስለው ቻይና እንኳን የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ከ5,000-10,000 የአሜሪካ ዶላር ሲደርስ የዴሞክራሲ ጥያቄ ዓይኑን አፍጥጦ ይመጣባታል ባይ ነው ፋሪድ። ለዚህም ከወዲሁ ወጣት ፖለቲከኞቹን ወደ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር ልካ ‹ፖለቲካዊ ሪፎረም› እያስተማረች ነው።

በተቃራኒው ደግሞ፣ Foreign policy የተባለ የበይነመበረብ መጽሔት ተንታኝ የሆኑት Bruce Bueno de Mesquita እና George W. Downs በቻይና እና ራሽያ ምሳሌ የሚመሩት የአሁኖቹ አውቶክራሲያዊ መንግሥታት የኢኮኖሚ ዕድገት በውጤቱ ዴሞክራሲ አምጥቶ እነርሱን ጠርጎ እንዳያስወጣቸው ኢኮኖሚስቶች “coordination goods” እያሉ የሚጠሩትን እንደመገናኛ ብዙኃን እና ሲቪል ሶሳይቲዎች (በእኛ አገር እስከቴሌኮም አገልግሎት ይዘልቃል) የማገድ ሥራ እንደሚሠሩ ተከራክረዋል። ተንታኞቹ ከ150 በላይ አገራት ላይ ለ30 ዓመታት ያክል በተደረገ ጥናት መሠረት “በአንድ አገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃንና ሲቪል ማኅበረሰባት መኖር የአውቶክራሲያዊ መንግሥት ዕድሜን ከ15 እስከ 20 በመቶ ይቀንሰዋል”፤ የአውቶክራቶቹ ሥራ በተገላቢጦሽ ማቀድ ነው።

የኢሕአዴግ ፍፃሜ (የዴሞልማት ጅማሬ)?

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ (ዕትዕ) መባቻ ላይ ለ15 ዓመታት እንደሚቆይ እና ሦስት ደረጃ (phase) እንዳለው አልተነገረንም ነበር። አሁን ሰምተናል። የሚገርመው ተከታዮቹ ሁለት ዕትዕዎች አሁን ካለቀው ዕትዕ የተለየ (ያደገ) ግብ የሌላቸው መሆኑ ነው። ምናልባትም ዕትዕ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚሻ ዕቅድ በመሆኑ እስከ 2017 ድረስ የኢሕአዴግ ፍፁማዊ የበላይነት እንደሚዘልቅ በገደምዳሜ እየተነገረን ይሆናል። ምናልባትም ደግሞ አቦይ ስብሐት እንዳሉት ፓርቲው ካፒታሊዝምን አዋልዶ የሚያከስምበትን ዓመት እየነገሩን ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን (ከነሙሉ ክብሩ) የምናገኘው በኢሕአዴግ ፍፃሜ እንደሆነ ኢሕአዴግ ይገምታል።
ልማታዊ አገረ-መንግሥት በኢትዮጵያ ቢኖር የማይጠላበት ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች አሉ። አንድ፡- በእስያ እና በላቲን አሜሪካ እንደታየው ስር ነቀል የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ እና ድኅነትን ለማሸነፍ ሁነኛው መንገድ መሆኑ በመረጋገጡ፤ ሁለት፡- የዘውግ ብሔርተኝነት መክረር የመበታተን አደጋ ያጠላባትን ኢትዮጵያ በፈጣን ዕድገት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ትስስሮሽ ሊፈጥርላት የሚችል በመሆኑ። በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ግን ፈታኞቹ ጥያቄዎች፤ ‹እውን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ልማታዊ ነው? የመሆን አቅሙ እና ፍላጎቱስ አለው? ዴሞክራሲን ሳይጨፈልቅ ተፈላጊው ግብ ላይ ያደርሰናል?› የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው።

ኢኮኖሚስቱ ጄፍሪ ሳክስ ሥር የሰደደ ድኅነትን ከዓለም በ2025 ለማጥፋት በተመኙበት “End of Poverty” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “Clinical economics” የሚባል ዘዴ አስተዋውቀዋል። ሕመምተኞች እንዲድኑ መጀመሪያ አፋጣኝ (የነፍስ አድን ሕክምና)፣ ከዚያ ሁሉን ያገናዘበ (ለምሳሌ የቤተሰብ የጤንነት ሁኔታ/ታሪክ ሳይቀር፣…) በመመርመር ዘላቂ ሕክምና ይደረግላቸዋል። በርግጠኝነት ኢኮኖሚያችንም (ልማታችንም) ይህ ዓይነቱ ሥር ነቀል ሕክምና ያስፈልገዋል። ዴሞክራሲያችንም እንደዚያው። አለበለዚያ መንግሥታችን በሥመ ልማታዊ አገረ-መንግሥትነት የአምባገነኖች መሸሸጊያ - “የትሮይ ፈረስ” ሆኖ ይቀጥላል። ዴሞልማትም እንደናፈቀን ይቀራል።

No comments:

Post a Comment