Tuesday, January 26, 2016

‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› (ክፍል ፩)


በናትናኤል ፈለቀ

እራሳቸውን ድንገት ስተው ‹‹ኮማ›› ውስጥ የገቡ ወላጅ አባቱን ለማስታመም እና በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈውን አሳዳጊ ሴት አያቱን እርም ሊያወጣ ከ15 ዓመት በላይ ወደተለያት ሀገሩ እየተመለሰ ነው፡፡ ለጉዞው ቀና ብሎ ያሰበው መንገድ ከሚኖርበት ሴንት ፖውል፣ ሚኒሶታ ወደካናዳዋ ቶሮንቶ አቅንቶ ከዛ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት እና በማግስቱ አውቶቢስ ተሳፍሮ አባቱን ወደሚያገኝበት የሱማሌ ክልል ከተማ ጎዴ ማምራትን ነበር፡፡

ወደ ሀገሩ ተመልሶ አባቱን ለማግኘት እጅግ ቸኩሏል፤ ተጨንቋል፡፡ ጭንቀቱን የሚያሳብቀው ገና ከተወለደች ሁለት ሳምንት ያልሞላትን ሁለተኛ ልጁን እና የሦስት ዓመት ወንድ ልጁን አራስ ባለቤቱ ላይ ጥሎ ጉዞውን መጀመሩ ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ እንዳቀደው ከሄዱለት በአንድ ወር ግዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ቆይታውን አጠናቆ ዜጋዋ አድርጋ ወደተቀበለችው አሜሪካን ይመለሳል፡፡

በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ግንቦት 29 ቀን፣ 2006 ዓ.ም ዕለተ ዓርብ የ31 ዓመቱ ፈረሃን ኢብራሂም አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የጢያራ ማረፊያ ደረሰ፡፡ አብረውት አዲስ አበባ እንዲደርሱ የሸከፋቸው ሻንጣዎች ግን አልደረሱም፡፡ ጉዳዩን ያስረዳቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ጓዙ የሚመጣው በሚቀጥለው በረራ እንደሚሆን፤ ይህ ማለት ደግሞ አዲስ አበባ የሚደርሰው ከሁለት ቀን በኋላ እንደሚሆን አስረዱት፡፡ የዕቅዱ መዛነፍ የመጀመርያ ምዕራፍ ይህ ሆነ፡፡ ነገርየው ብዙም የሚያስጨንቅ ሆኖ አላገኘውም፡፡ በሥራው ምክንያት የብዙ ግዜ የአየር ጉዞ ልምድ ስላለው እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያውቃል፡፡ አባቱን የሚያገኝበት ግዜ መራዘሙ ቢያሳስበውም አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት ቀን እንዲቆይ መገደዱ ከተማዋን ዞር ዞር ብሎ ለማየት የሚፈጥርለትን ዕድል በማሰብ ለመፅናናት ሞከረ፡፡

***

ፋይሰል ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የሁለተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ ነው፡፡ የትምህርት ወጪውን የሚሸፍንለት በፎቶ ብቻ የሚያውቀው የአጎቱ ልጅ ከአሜሪካን ሀገር ሲመጣ ተቀብሎ አዲስ አበባ ያለውን መስተንግዶ ጨርሶ ወደጎዴ ለመላክ ያለውን ኃላፊነት እሱ ወስዷል፡፡ የአጎቱ ልጅ ሲያገኘው እንዲኮራበትም በቅርቡ በላከለት ገንዘብ ያሰፋውን ጥቁር ሱፍ ግጥም አድርጎ ለብሶ፣ አበባ ይዞ ቦሌ ዓለም አቀፍ ጢያራ ማረፊያ መንገደኞችን ለመቀበል ከተደረደሩት ሰዎች መኻከል ተገኝቷል፡፡

እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 12፡30 ገደማ ፋይሰል ፈጽሞ ሊገባው ባልቻለ ሁኔታ እራሱን የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የተጠርጣሪዎች ማረፊያ ክፍል ቁጥር 9 ውስጥ አግኝቶታል፡፡ ከሱ አስቀድሞ ክፍሉ ውስጥ ነበሩትን ሰዎች ምን እየተፈጠረ እንደሆነ እንዲያስረዱት በሚችላት ትንሽ አማርኛ ተፍጨረጨረ፡፡ ሊገባው የቻለው ነገር ያለበት ቦታ በተለምዶ ማዕከላዊ እየተባለ እንደሚጠራ እና ያሉበት ክፍል የሚገኝበት ሕንፃ በቅዝቃዜው ምክንያት ‹‹ሳይቤርያ›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው
ብቻ ነው፡፡

***

ፈረሃን ለመጀመርያ ጊዜ በዕጁ ያጠለቀውን ካቴና ፈትተው አንድ ደብዛዛ ብርሃን ያለበት ክፍል በር ከፍተው ገፈተሩት፡፡ ከሻንጣው ውስጥ ወደማረፊያ ቤቱ ይዞት እንዲገባ የተፈቀደለትን አንድ ቅያሪ ቱታ እና የጥርስ ብሩሽ እና ሳሙና በቢጫ ፌስታል እንዳንጠለጠለ በሩ አጠገብ ቆሞ የገባበትን ክፍል ይቃኝ ጀመር፡፡ በር ድረስ አጅበው ይዘውት የመጡት ሰማያዊ ቀለም ያለው ሬንጀር የለበሱ ሰዎች በሩን ሲዘጉት የወጣው ድምጽ የክፍሉን ቅኝት አቋርጦ በድንጋጤ ከበሩ አካባቢ እንዲርቅ አስገደደው፡፡

ደቂቃዎች አለፉ፤ ፌስታሉን በዕጁ እንዳንጠለጠለ ቆሟል፡፡ ቀድመው ክፍሉ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ቆጠራቸው፣ 13 ነበሩ፡፡ ‹‹ቁጭ በል›› ብለው ቢጋብዙትም አልገባውም፡፡ በቋንቋ እንዳልተግባቡ ሲረዱ ከመካከላቸው ተኝቶ የነበረ አንድ ልጅ ቀሰቀሱና ‹እንግዳ ተቀበል› አሉት፡፡ ከንቅልፉ የተቀሰቀሰው ልጅ ከፍራሹ ተነስቶ ወደቆመው ሰውዬ አመራና እጁን ለሰላምታ ዘረጋ፡፡ ኡመድ ብሎ እራሱን አስተዋወቀ;; የቆመው ሰውዬ ለሰላምታ የተዘረጋለትን እጅ በቸልታ እየጨበጠ ‹‹ፈረሃን እባላለሁ›› አለ፡፡ ኡመድ ሌላኛውን እጁን ፌስታሉን ለመቀበል እየሰደደ እንግዳውን እንግሊዘኛ መናገር ይችል እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ፈረሃን ጭንቅላቱን ላይ ታች ወዝውዞ መለሰለት፡፡ ሊግባባው ሚችል ሰው ማግኘቱ ቢያስደስተውም አሁንም ፈፅሞ ደኅንነት እየተሰማው አይደለም፡፡ ለማየት የሚረዳውን መነጽር ከዓይኑ ላይ አወረደና በእጁ ያዘ፡፡ አንድ ጊዜ እንደገና ክፍሉን ቃኘ፡፡ በኮንክሪት የተሰራ ጣራ እና ግርግዳ፣ ለአየር መውጫና መግቢያ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ብርሃን የሚገባበት በፍርግርግ ብረት የተገደበ ከበሩ በስተግራ በኩል ጣራውን ታክኮ ያለ ትንሽ ክፍተት፣ ክፍሉ ውስጥ ባሉ ሰዎች ቁጥር ልክ የሚመስል ጥግ ይዘው የተደረደሩ የውኃ ማሸጊያ ላስቲኮች፣… ከላስቲኮቹ መኻከል አንዳንዶቹ ውስጥ ያለው ፈሳሽ ሽንት ስለመሰለው በመጠየፍ መራቅ ፈለገ፡፡ ኡመድ ተኝቶ ወደነበረበት ፍራሽ ተመለሰና ‹‹ፈረሃን፣ ወደዚህ ና›› ሲል ጋበዘው፡፡ ከላስቲኮቹ መራቅ የፈለገው ፈረሃን በትክክለኛው ሰዓት የመጣለትን ግብዣ ተቀብሎ ጫማውን አወለቀና በፍራሾች ላይ ተረማምዶ ከኡመድ አጠገብ ተቀመጠ፡፡

ክፍሉ ውስጥ ያሉት ሌሎች ሰዎች የኡመድ እና የፈረሃንን ዓይን አፈራርቀው እያዩ ለኡመድ በጥያቄ አጣደፉት፡፡ ኡመድ ወደፈረሃን ዞሮ ‹‹ሱማሌ ትመስላለህ?›› አለው፡፡ ፈረሃን በመስማማት በመስማማት ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡ ኡመድ አብረውት ከታሰሩ ሶማሌዎች ካስተማሩት የሚያስታውሳትን ሱማልኛ ተናገረ ‹‹ማፊዓንታሃይ?›› ፈረሃን ክፍሉ ውስጥ ከገባ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ፈገግ ብሎ መልስ ሰጠ - ‹‹ፊዓን›› ሲል፡፡ የሚችለውን ሱማልኛ የጨረሰው ኡመድ በእንግሊዘኛ መናገር ቀጠለ፡፡ ‹‹ከየት ነው የመጣኸው?›› ፈረሃን ጥያቄውን ለመመለስ ጥቂት ሰከንዶች ከወሰደ በኋላ የሚኖረው አሜሪካን ሀገር እደሆነ፣ ለጥቂት ግዜ እረፍት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ አስረዳ፡፡ ኡመድ ጥያቄውን ቀጥሎ ለምን እንደታሰረ ያውቅ እደሆነ ጠየቀው፡፡ ፈረሃን ግራ መጋባቱን በሚያሳብቅ ሁኔታ ዓይኑን ግራና ቀኝ ካንከባለለ በኋላ ትከሻውን ሰብቆ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገለፀ፡፡ አብረዋቸው ያሉት ሰዎች ጥያቄዎቻቸውን እያዥጎደጎዱ እንዲያስተረጉምላቸው ቢፈልጉም ከዚህ በላይ ፈረሃንን ማስጨነቅ ያልመረጠው ኡመድ ‹‹አሁን ተረጋግተህ እረፍት አድርግና ጠዋት እናወራለን፡፡ ለሁላችንም የሚበቃ ፍራሽ ስለሌለ ከኔ ጋር ፍራሽ እንጋራለን፡፡ ሽንት መሽናት ከፈለክ ከነዛ ላስቲኮች አንዱን ተጠቀም፡፡›› አለውና አንሶላ አነጠፈለት፡፡ ፈረሃን ‹‹አመሰግናለሁ›› አለና እንደማመንታት ብሎ ማውራት ቀጠለ፡፡ ‹‹ታውቃለህ? መጀመሪያ እዚህ ሲያስገቡኝ የምትደበድቡኝ መስሎኝ ነበር፡፡ እኔ የምኖርበት ሀገር እስር ቤት ውስጥ አዲስ ሰው ሲገባ የቆዩት እስረኞች በድብደባ ነው አቀባበል የሚያደርጉለት፡፡›› ኡመድ ጮክ ብሎ ሳቀ፡፡ ሌሎቹ እስረኞች ምን እንዳሳቀው ለማወቅ ጓግተው ጠየቁት፡፡ ፈረሃን የነገረውን ተረጎመላቸው፡፡ ሁሉም እየተሳሳቁ ፍራሾቻቸውን ማንጠፍ ጀመሩ፡፡ ኡመድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሌሎች እስር ቤቶች ውስጥም ተመሳሳይ ነገር ሊከሰት እንደሚችል ለፈረሃን አስረዳው፡፡
ፈረሃን ለመተኛት ትንሽ ሲገላበጥ ቆየና የረሳው አንድ ነገር ድንገት ትዝ አለውና ኡመድን ‹‹ፀሎት ማድረግ እችላለሁ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ኡመድ፤ በክፍሉ ውስጥ የነበሩት የእስልምና ዕምነት ተከታዮች የመግሪብ ፀሎት እንዳደረጉ፣ ትንሽ ከቆየ አብሯቸው የኢሻ ፀሎት ማድረግ እንደሚችል አልያ ግን ብቻውን ቢፀልይ ችግር እንደሌለው እና ቦታ ሊያመቻችለት እንደሚችል ነገረው፡፡ ፈረሃን ቆይቶ በጋራ ፀሎት ማድረጉን መረጠ፡፡

***

ከእንቅልፉ ነቅቶ አይኑን ሲገልጥ ግር ተሰኘ፡፡ ዙሪያውን ሲያይ የማያውቀው ቦታ እራሱን ስላገኘው ተደናገጠ፡፡ ዓይኖቹን አሻቸው፤ የተለወጠ ነገር ግን አልነበረም፡፡ ቀስ ብሎ ለማስታወስ ሞከረ፡፡ ደስ የማይል ስሜት ውስጡን ሲወረው ተሰማው፡፡ ከ17 ሰዓታት በፊት የተፈጠረውን ነገር አስታወሰ፡፡ በህልሙ ቢሆን ምርጫው ነበር፡፡

***

የዘገዩት ሻንጣዎችን ለማምጣት እሁድ ረፋድ ላይ ካረፈበት ሆቴል ታክሲ ተኮናትሮ ወደቦሌ አቀና፡፡ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ለተፈጠረው ስህተት እና መጉላላት ይቅርታ ጠይቀው ሻንጣዎቹን አስረክበው ሸኙት፡፡ ወዳረፈበት ሆቴል እየተመለሰ ለፋይሰል የስልክ ጥሪ አደረገና የዘገዩት ሻንጣዎች በእጁ መግባታቸውን ከነገረው በኋላ ወደጎዴ የሚወስደውን የአውቶቢስ ትኬት ለመቁረጥ ሰኞ ጠዋት ለመገናኘት ተቀጣጠሩ፡፡ ፋይሰል ያረፈበት ሆቴል ድረስ መጥቶ አብረው ሄደው ትኬቱን እንደሚገዙ ነበር የተሰማሙት፡፡

የሚያደርገው ስላልነበረው ዕረፍት ለማድረግ አስቦ ጋደም አለ፡፡እንቅልፉ መኻል ላይ ያረፈበት ሆቴል ክፍል በር ሲንኳኳ ሰማ፡፡ የሚጠብቀው እንግዳ አልነበረም፤ ከፋይሰል በስተቀር ያረፈበትን ቦታ የሚያውቅ የቅርብ ሰው የለውም፡፡ ከፋይሰል ጋር ደግሞ ከሰኞ በፊት ሌላ ቀጠሮ አልነበራቸውም፡፡ በሰመመን ሆኖ የሆቴሉ ሰራተኞች ለፅዳት ወይንም ሌላ አገልግሎት መግባት ፈልገው ሊሆን እንደሚችል ገመተ፡፡ ከእንቅልፉ ጨርሶ መንቃት ስላልፈለገ የበሩን ጥሪ ትቶ ወደእንቅልፉ ለመመለስ ሞከረ፡፡ ከቆይታ በኋላ ግን በሩ እንደገና ተንኳኳ፡፡ ይኼው መንኳኳት እንደቀደመው ሊተወው የሚችለው አልነበረም፡፡ በከፍተኛ ድምጽ እና ቶሎ ቶሎ ነበር በሩ የሚደበደበው፡፡ በንዴት ሱሪውን እንኳን ሳያጠልቅ ከአልጋው ወረደና ወደበሩ ሄዶ ከፈተው፡፡ በሩ ላይ ቆመው መከፈቱን ይጠባበቁ የነበሩት  ብዛት ያላቸው መሣርያ የታጠቁ ዥንጉርጉር ሰማያዊ መለዮ የለበሱ ሰዎች እና አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው ፈረሃንን ገፍትረው ወደክፍሉ ገቡ፡፡ የሚያየውን ማመን ከብዶት ነበር፡፡ የታጠቁት ሰዎች የክፍሉን ጥግ ጥግ ይዘው ቆሙ፡፡ ሲቪል የለበሰው ሰውዬ የፈረሃንን ክንድ ይዞ እንዲቀመጥ ጎተተው፡፡ ሰውየው ቤቱን ዞር ዞር ብሎ ካየ በኋላ ፊት ለፊቱ ተቀመጠ፡፡ ሰውየው በተሰባበረ እንግሊዘኛ ፖሊሶች መሆናቸውን እና ያረፈበትን ክፍል ሊፈትሹ እንደሚፈልጉ ገልፆ ሻንጣዎቹን የት እንዳደረጋቸው ጠየቀው፡፡ ፈረሃን በአገጩ ወደሻንጣዎቹ ጠቆመ፡፡ ሰውየው በተጠንቀቅ ወደቆሙት ወታደሮች ዞሮ በዓይኑ ምልክት ሰጣቸው፡፡ ሁለቱ መሣሪያቸውን ወደጀርባቸው አዙረው አዘሉና ሻንጣዎቹን መበርበር ጀመሩ፡፡ ላፕቶፕ ኮምፒውተሩን፣ ለዘመዶቹ ይዟቸው የመጣው አራት ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎች እና ሻንጣው ውስጥ ያገኟቸውን ወረቀቶች በሙሉ ለብቻ ለብቻ ዘረገፏቸው፡፡ ሲቪል የለበሰው ሰውዬ ወረቀቶቹን አለፍ አለፍ እያለ ገረበባቸው እና ወደፈረሃን ዞሮ ‹‹ፓስፖርትህ የት ነው ያለው?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ፓስፖርቱን ከሱሪ ኪሱ አውጥቶ ሊሰጠው ከተቀመጠበት ፈረሃን ብድግ ሲል ሰውየው ከፍ ባለ ድምጽ ተቆጥቶ እንዲቀመጥ አዘዘው፡፡ ‹‹ፓስፖርቴ ያለው ሱሪ ኪሴ ውስጥ ነው፡፡›› አለ በድንጋጤ ተውጦ ሱሪው ወዳለበት ቁምሳጥን እየጠቆመ፡፡ ሰውየው እራሱ ሳጥኑን ከፍቶ ሱሪውን ፈተሸ፡፡ ጥቂት የኢትዮጵያ ብሮች፣ ብዛት ያለው የአሜሪካን ዶላር እና የአሜሪካን ዜጋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ፓስፖርቱን ካወጣና ሌላ ምንም እንዳልቀረ ካረጋገጠ በኋላ ሱሪውን ለፈረሃን ወረወረለት፡፡ ፈረሃን በተቀመጠበት ሆኖ ታግሎ ሱሪውን አጠለቀ፡፡

ከሻንጣዎቹ የወጡትን ንብረቶቹን ለብቻ አድርገው ሻንጣዎቹን ዘግተው ይዘዋቸው ወጡ፡፡ ሲቪል የለበሰው ሰውዬ እንዲነሳ አዝዞ ወደበሩ በአገጩ ጠቆመው፡፡ ዝም ብሎ ከዚህ በላይ መሄድ ያልፈለገው ፈረሃን ምን እየተካሄደ እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ሲቪል ከለበሰው ሰውዬ ‹‹ፖሊሶች ነን›› ከሚል ምላሽ ውጪ ምንም ተጨማሪ መረጃ ማግኘት አልቻለም፡፡ ገፍትረውት ከገቡት ክፍል እየገፉ ይዘውት ወጡ፡፡

***

የረፈሃንን ስልክ ጥሪ ተቀብሎ ለሰኞ ቀጠሮ ከሰጠው በኋላ ፋይሰል ወትሮ እሁድ ከሰዓት እንደሚያደርገው ከጓዶቹ ጋር ኳስ እየተጫወተ ለማሳለፍ ከሚኖርበት ቦሌ ሚካኤል የጋራ መኖርያ ቤቶች አቅራቢያ ወደሚገኘው የእግርኳስ ሜዳ አመራ፡፡ ቀድመውት ከደረሱት ጓደኞቹ ጋር ኳስ እየተጫወቱ ወደማጠናቀቁ ሲቃረቡ ያልተለመደ ሁኔታ አካባቢው ላይ አስተዋለ፡፡ ሁሉም ጓደኞቹ ቆመው ኳሷ ብቻዋን ሜዳው ላይ ተንከባለለች፡፡ አስር የሚደርሱ ፌደራል ፖሊሶች ኳስ መጫወቻ ሜዳውን ከበው እያጠበቡ እየተጠጓቸው ነበር፡፡ የፖሊሶቹ ጣቶች ያነገቡት መሣርያ ቃታ አካባቢ ተሰድሯል፡፡ ፋይሰል አብረውት ኳስ ከሚጫወቱት ጓደኞቹ መካከል አንደኛውን እንደሚፈልጉ ገምቶ ነበር፡፡ የመጡት ፖሊሶች ‹ፌደራሎች› መሆናቸው የመጡበት ጉዳይ ቀላል እናዳልሆነ ጠቁሞታል፡፡ ይህ እያሰላሰለ ለጥቂት ሰከንዶች ከገባበት ሐሳብ ስሙ ሲጠራ ሰምቶ ባነነ፡፡ የከበቧቸውን ፖሊሶች ከኋላ ሆኖ የሚመራው ሲቪል የለበሰ ሰውዬ ነበር ሥሙን የጠራው፡፡ በፍጥነት ነገሩ ሁሉ ተደበላለቀበት፡፡ ስሙ ድጋሚ ሲጠራ መደናገሩ ስላለቀቀው ቆሞ ከማፍጠጥ ውጭ ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ የጓደኞቹ ዓይኖች በሙሉ እሱ ላይ አነጣጠሩ፡፡ ለሦስተኛ ግዜ ስሙ ሲጠራ የሚማርበት ክፍል ውስጥ ጥያቄ ለመመለስ እንደሚያደርገው የግራ እጁን ወደላይ አነሳ፡፡

***

ሊነጋጋ ሲል ያደሩበት ክፍል በር ተከፍቶ በሽንት የተሞሉትን ላስቲኮች እያንጠለጠሉ እየተጣደፉ ሲወጡ ምን እንደተፈጠረ እንዲያስረዳው ፈረሃን ኡመድን ጠየቀ፡፡ በቀን ውስጥ ሽንቱን መሽናት እና ውሃ ለመቅዳት ከሚያገኛቸው ሁለት አጋጣሚዎች አነደኛው መሆኑን፤ ይህ አጋጣሚ ግፋ ቢል ለ20 ደቂቃዎች ብቻ ስለሚቆይ ፈጠን ብሎ ተነስቶ ጉዳዩን እንዲጨርስ ከማሳሰቢያ ጋር ኡመድ መለሰለት፡፡ ፈረሃን ያገኘው መልስ ባይዋጥለትም ማሳሰቢያውን ተቀብሎ ወደመጸዳጃ ቤቱ አመራ የሽንት ሰዓቱ አብቅቶ በሩ ተመል እንደተዘጋ ጉዳዩን እንዲያብራራለት በድጋሚ ኡመድን ጠየቀው፡፡ ኡመድ የተለየ መል አልነበረውም፡፡

ኡመድ እና ጓደኞቹ የፈረሃንን ቁርስ ተቀበሉለት እና አብሯቸው በላ፡፡ ሁሉንም በሥም ተዋወቃቸው፡፡ በዕድሜ፣ በተክለ ሰውነት፣ በፊታቸው ቀለም ይለያያሉ፡፡ ሁሉም እዛው የተዋወቁ እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ነገር ግን ከእንቅልፉ ሲባንን ነጭ አንሶላ የመሰለ ልብስ ተከናንበው ቆመው በቃላቸው ሲያነበንቡ የነበሩት ሽማግሌ ሰውዬ ከትግራይ የመጡት ቄስ ጎይቶም፣ ከኡመድ ቀጥሎ ግርግዳውን ታክኮ ያለው ፍራሽ ላይ ለሁለት የተኙት ወጣቶች የጅማና የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምህንድና ተማሪዎቹ ሌንጂሳ እና ቢልሱማ፣ ከራሱ በስተቀኝ በኩል ተኝቶ ያደረው ወጣት የ16 ዓመቱ የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ታጋይ አብዱ፣ ከሱ በተቃራኒው ከቄሱ አጠገብ የተኛው ጎስቋላ ጎልማሳ የቤጊው ገበሬው በሊስ (አስፋው)፣ ከነሌንጂሳ በተቃራኒ ያለውን ፍራሽ የሚጋሩት የጅማው ኢማም ሼህ ጀማል እና ጣሂር፣… ባጠቃላይ ከኤልያስ በስተቀር ሲገባ ከቆጠራቸው 13 ሰዎች ውስጥ 12ቱ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በምርመራ ላይ ያሉ መሆናቸው ገና አልገባውም፡፡

ቁርሳቸውን ጨርሰው ሁላቸውም ፍራሾቻቸው ላይ ቁጭ ቁጭ ብለው በዝምታ ተዋጡ፡፡ ማታ ሲቀላቀላቸው በጨዋታ ደምቆ የነበረው ክፍል ለምን በዝምታ እንደተዋጠ አልገባውም፡፡ ምናልባት ወደኋላ እየሞቃቸው ሲሄድ ዝምታው እንደሚጠፋ ገመተ፡፡ በአብዛኞቹ ጭንቅላት ውስጥ ገብቶ ዝምታውን ያሰፈነው ሰኞ ጠዋት መሆኑ ነበር፡፡ እሁድ ቀን ከምርመራ ሚያርፉባት ናት፡፡ ሰኞ ጠዋት ደግሞ ምርመራው የቆመው ምን ጋር እንደነበር እያስታወሱ እንዴት እንደሚቀጥል እና ከግርፋት እና ከእንግልት የሚድኑበት መልስ ምን እንደሆነ የሚያሰላስሉባት ናት፡፡

ፈረሃን ዝምታን ለመስበር ለኡመድ ጥያቄ አነሳ፡፡ ‹‹አሁን ምንድነው የሚሆነው? ምንድን ነው የምሆነው?›› ኡመድ ረጋ ብሎ ለፈረሃን መመለስ ጀመረ ‹‹ዛሬ ምናልባት ፍርድ ቤት ይወስዱህ ይሆናል፡፡ ለምን እዚህ እንዳመጡህ ለፍርድ ቤት ሲያስረዱ ትሰማለህ …›› ፈረሃን ኡመድን አቋረጠውና ‹‹ፍርድ ቤት በእንግሊዘኛ ነው የሚሰራው?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ኡመድ ፈገግ ብሎ ‹‹ፍርድ ቤት በእንግሊዘኛ አይሠራም፡፡ ሱማልኛ አስተርጓሚ መጠየቅ ግን ትችላለህ፡፡›› አለው፡፡ ማስረዳቱን ቀጥሎም ‹‹በደረቅ ወንጀል ከሆነ የጠረጠሩህ እስከ 14 ቀን የሚደርስ ቀጠሮ አለበለዚያ በሽብር የሚጠረጥሩህ ከሆነ ደግሞ …›› ፈረሃን በድጋሚ ኡመድን ቋረጠውና ‹‹ይህ ሊሆን አይችልም!›› አለ፡፡ ኡመድ ፈገግ ብሎ ‹‹በጣም ጥሩ›› ብሎ መለሰ፡፡ በልቡ ግን ፈረሃን ፍርድ ቤት ከሄደ የ28 ቀን ቀጠሮ ይዞ እንደሚመጣ ጠንካራ ግምት ነበረው፡፡

ትንሽ እንደተጨዋወቱ ያሉበት ክፍል በር ተከፈተና ኡመድ ተጠራ፡፡ እየተቻኮለ እየወጣ ወደፈረሃን ዞሮ ‹‹ምርመራ መሄዴ ነው፡፡›› አለው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ፈረሃንም ተጠርቶ ወጣ፡፡ ለምሣ ሰዓት ጥቂት ግዜ ሲቀረው ፈረሃን ተመልሶ መጣ፡፡ ፊቱ ላይ የመቆጣት ስሜት ይነበብበት ነበር፡፡ ምርመራውን ጨርሶ ከፈረሃን በፊት ወደክፍሉ ተመልሶ የነበረው ኡመድ ‹‹ፈረሃን፤ እንኳን በደህና ተመለስክ፡፡ ፍርድ ቤት ወሰዱህ እንዴ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ተስፋ በቆረጠ የተሰላቸ ድምጽ ‹‹28 ቀን ቀጠሩኝ፡፡›› ብሎ ፍራሹ ላይ በደረቱ ተደፋ፡፡

***

የክፍሉ መቀርቀሪያ በኃይል ተወርውሮ ሲከፈት ያወጣው ድምጽ ሁሉንም ከእንቅልፍ ቀሰቀሳቸው፡፡ በርግጥ ከመካከላቸው ገና ወደበሩ እየቀረበ የነበረውን የእግር ኮቴ እና ሲንቀጫቀጭ የነበረውን የካቴና ድምጽ ሰምተው ከእንቅልፋቸው አስቀድመው የነቁ ነበሩ፡፡ በሩ ተከፍቶ ‹‹ሌንጂሳ አለማየሁ›› የሚል ድምጽ ተጣራ፡፡ ሁሉም ዓይናቸውን ወደሌንጅሳ ወረወሩ፡፡ ‹‹አቤት›› ብሎ ብርድ ልብሱን ከላዩ  ላይ እየገፈፈ ተነሳ፡፡ ከመውጣቱ በፊት የመተኛ ሱሪው ላይ ሌላ ሱሪ ደረበ፡፡

ፈረሃን ክፍሉ ውስጥ የቀሩት ሰዎች ሌንጂሳን ያዩ የነበረበት ሁኔታ የሆነ ክፉ ነገር እንዳለ ነግሮታል፡፡ ከእንቅልፍ አስቀስቅሶ የሚያስወስድ አሳሳቢ ነገር ምን ይሆን ሲል አሰበ፡፡ ስንት ሰዓት እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ኡመድ በግምት ሶስት ሰዓት አካባቢ እንደሚሆን ሲናገር ፈረሃን ቀና ብሎ የክፍሉን አራት ማዕዘን ግርግዳዎች ቃኘ፡፡ የፈለገውን አላገኘም፡፡ ‹‹እዚህ ምንም ሰው ሰዓት የለውም?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ኤልያስ የፈረሃን ጥያቄ ያለአስተርጓሚ ስለገባው ተሰባበረ እንግሊዘኛ ወደማረፊያ ቤት ሰዓት ይዞ መግባት የተከለከለ መሆኑን አስረዳ፡፡ ፈረሃን የበለጠ ግራ በመጋባት ‹‹ታድያ የፀሎት ሰዓት ሲደርስ በምንድን ነው የምናውቀው?›› ኤልያስ ጥያቄውን መረዳት ስላቃተው የኡመድን ዓይን ያይ ጀመር፡፡ የኤልያስ ችግር የተረዳው ኡመድ የፈረሃንን ጥያቄ ተርጉሞ ነገረው፡፡ ‹‹አሃ…›› ኤልያስ መልሱን በእንግሊዘኛ ሲያደረጅ ቆየና ተሰላችቶ ኡመድን በቃ አንተ ንገረው በሚል አኳኻን አይቶት ዝም አለ፡፡ ጠዋት እና ማታ የሚቆጥሯቸው ፖሊሶች ሲመጡ ስንት ሰዓት እንደሆነ እንደሚጠይቋቸው እና ከዛ የቀረውን ግዜ በግምት እንደሚያሟሉት ኡመድ አብራራ፡፡ ፈረሃን ያለበት ቦታ ሲዖልነት ቀስ በቀስ እየገባው ነው፡፡ ቀጥሎ በጠየቃቸው ጥያቄዎች የተረዳው ነገር ደግሞ ለደህንነቱ አብዝቶ እንዲጨነቅ አስገደደው፡፡ ሌንጂሳ እና ጓደኛው ቢልሱማ ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ በቁጥጥር ስር የዋሉት መንግሥት ሊተገብረው ያቀደውን የአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞኖች የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎች ላይ ተሳትፋቹኻል እና  ተቃውሞውን አስተባብራቹኻል በሚል ምክንያት ሲሆን በተለይ ሌንጂሳ ጅማ ዩኒቨርስቲ ደጃፍ ላይ በደህንነቶች ከተያዘ በኋላ አዲስ አበባ እስኪመጣ ድረስ የነበረውን 3ቀን እህል የሚባል እንዳልቀመሰ፣ አሁን ያሉበት ቦታ ካመጡት ጀምሮ ደግሞ በየቀኑ ማታ ማታ ተጠርቶ ሌሊቱን ክፉኛ እየተደበደበ በምርመራ እንደሚያጋምስ ነበር የተነገረው፡፡ ምርመራ ተወስዶ መደብደብ ማንም ሰው ላይ ሊከሰት እንደሚችል፣ ክፍሉ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል ጨዋታ ከሚወደው ባለ ደንዳና ሰውነቱ የቡና ነጋዴ ኤልያስ በስተቀር ሁሉም ክፉኛ ድብደባ የደረሰባቸው መሆኑን ኡመድ አንድ በአንድ እየጠቆመ ነገረው፡፡

እንቅልፍ አጥቶ ሲገላበጥ ብዙ ሰዓት አለፈው፡፡

የክፍሉ በር ተከፈተና ሌንጂሳ በፖሊስ ተደግፎ ወደክፍሉ ገባ፡፡ እራሱን ችሎ መራመድ ስላቃተው ቢልሱማ ተነስቶ ድጋፍ ሆኖት ወደፍራሹ አደረሰው፡፡ ሁሉም ድጋሚ ከእንቅልፋቸው ተነስተው በትካዜ ተዋጡ፤ የተከሰተው ለሁሉም ገብቷቸዋል፡፡ ፈረሃን አንድ ነገር ድንገት ጭንቅለቱ ውስጥ አቃጨለ፡፡ አንድ ጓደኛው ከወራት በፊት በአግራሞት አውርቶለት የነበረ ‹‹Human Rights Watch›› የተባለ የመብት ተሟጋች ቡድን ‹‹They Want Confession›› በሚል ርእስ ያወጣው ዘገባ ትዝ አለውና ወደኡመድ ዞሮ ‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› ሲል ጠየቀ፡፡

***

ፋይሰል ፍርድ ቤት የተከሰተው ነገር ጭራሽ ግርታውን አብሶበታል፡፡ ከሱ እና ከአጎቱ ልጅ በተጨማሪ አይቷቸው የማያውቃቸው ሶስት ወንድ እና አንድ ወጣት ሴት ሱማሌዎች አብረዋቸው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ሶስቱ ወንድ ሱማሌዎች የሚያመሳስላቸው ነገር እንዳለ ፋይሰል አስተውሏል፡፡ የአነጋገር ዘይቤያቸው ልክ እንዳጎቱ ልጅ ውጭ ሀገር ቆይተው እንደመጡ ያስታውቃል፡፡ 18 ዓመት እንኳን የሞላት የማትመስለው አብራቸው ፍርድ ቤት የቀረበችው ሴት ደግሞ ከአነጋገሯ የኢትዮጵያ ሱማሌ እንዳልሆነች ገብቶታል፡፡

ከፍርድ ቤት እንደተመለሰ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ጥያቄ ያጣድፉት ያዙ፡፡ ፍርድ ቤት የተከሰተውን ለማስረዳት ሞከረ፡፡ ስድስት ሆነው እንደሄዱ፣ ችሎት ውስጥ ለሁለት ከፍለው ሦስት ሦስት አድርገው ይዘዋቸው እንደገቡ፣ እሱን በዕድሜ ሸምገል ካለው ሰውዬ እና ከወጣቷ ጋር ችሎት ፊት እንዳቀረቡት ነገራቸው፡፡ በጥሞና ሲያዳምጡት የነበሩት ሰዎች በምን ወንጀል እደተጠረጠረ ለማወቅ ነበር፡፡ ፋይሰል በረጅሙ ትንፋሽ ወስዶ ‹‹አል ሸባብ ከተባለ ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ይዣቸኋለው፡፡›› የሚል ክስ ይዟቸው የሄደው ፖሊስ አንብቦ የ28 ቀን ቀጠሮ እደጠየቀና  መነፅራቸውን ዝቅ አድርገው ጥያቄውን የሰሙት አዛውንት ሴት ዳኛ የ28 ቀን ቀጠሮውን መፍቀዳቸውን አስረዳቸው፡፡ ከጠበቁት ብዙም የራቀ ነገር አልነገራቸውም፡፡ ምንም የመደንገጥም ሆነ የመሸሽ ዓይነት ስሜት ስላላየባቸው እረፍት ቢሰማውም ሽብርን የሚያክል ትልቅ ክስ ቀረበብኝ ሲላቸው አለመገረማቸው ግር አሰኝቶት ነበር፡፡ ኋላ ላይ ሲረዳ ግን ማዕከላዊ የገባ ሰው ከሱማሌ ከሆነ አልሸባብ ወይንም ኦብነግ ተብሎ፣ ኦሮሞ ከሆነ ኦነግ፣ ከትግራይ ከሆነ ትሕዴን፣ ሙስሊም ከሆነ አልቃይዳ፣ አማራ ከሆነ አርበኞች ግንባር፣ ጋዜጠኛ ወይንም የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆነ ግንቦት 7 ተብሎ መከሰሱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

***

ምሣ በልተው እንደጨረሱ በሩ ተከፈተና የፋይሰል ስም ተጠራ፡፡ ‹‹አለሁ›› ሲል ለጥሪው መልስ፡፡ ‹‹ዕቃህን ይዘህ ውጣ›› የሚል ትዕዛዝ ተከተለ፡፡ የተባለው ስላልገባው እንዲደገምለት ‹‹እእ…›› አለ፡፡ በሩ ላይ የቆመው ፖሊስ ቁጣ በተቀላቀለበት ድምጽ ‹‹ዕቃህ ይዘህ ውጣ!›› ሲል ደገመለት፡፡ ከኳስ ጨዋታው መልስ ታጥቦ ሊቀይር ይዞት የነበረውን ልብስ በስስ ፌስታል ይዞ ወጣ፡፡

በር ላይ ቆሞ የነበረው ፖሊስ ካቴና አለመያዙን ሲያስተውል ተስፋ ቢጤ ተሰምቶት ነበር፡፡ ግን የተሰማው የተስፋ ስሜት በፍጥነት ወደተስፋ መቁረጥ ተለወጠ፡፡ ከሰው ጋር አብሮ ይታርሰር ከነበረበት ማረፊያ ቁጥር 9 የወጣው ብቻውን ወደሚታሰርበት ጨለማ ክፍል ቁጥር 8 ለመዘዋወር ነበር፡፡

***

በተለምዶ ሳይቤሪያ ተብሎ የሚጠራው የማዕከላዊ ሕንጻ ቁጥር 84 በረጅም ኮሪደር ለሁለት የተከፈለ ሲሆን የእስረኛ ማቆያ ክፍሎቹ ከኮሪደሩ ግራና ቀኝ የተደረደሩ ናቸው፡፡ ኮሪደሩ ሲጀመር በግራና በቀኝ 2ቁጥር እና 10 ቁጥር ማረፊያ ክፍሎች ፊት ለፊት ተፋጠዋል፡፡ በግራ በኩል ከ2ቁጥር አንስቶ እስከ 6ቁጥር የሚዘልቅ ሲሆን በስተቀኝ በኩል ደግሞ ከ10 ቁጥር ጀምሮ ቁልቁል እየቆጠረ እስከ 7ቁጥር ይሄዳል፡፡ ከ7 ቁጥር ማረፊያ ክፍል ቀጥሎ ደግሞ ዘጠኙ ክፍሎች ውስጥ የሚታሰሩት ሰዎች በየተራ ክፍሎቹ እየተከፈቱ በቀን ሁለት ግዜ (ጠዋት እና ማታ) ቢበዛ ለ20 ደቂቃዎች የሚጠቀሙበት ባለ6 የሽንት ቤት ክፍል እና አንድ መታጠቢያ ክፍል ያለው መጸዳጃ ቤት ይገኛል፡፡

ሳይቤርያ ውስጥ የሚገኙት ክፍሎች በስፋት ካልሆነ በቀር አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ ከሁሉም ክፍሎች የሚለየው 8ቁጥር ነው፡፡ ከውጪ በሩ ተዘግቶ ለሚያየው ሰው 8 ቁጥርም ቢሆን ከሌሎቹ የሚለይበት ነገር የለም፡፡ በሩ ተከፍቶ ወደውስጥ ሲገባ ግን በግራና በቀኝ በኩል ሁለት ሁለት የራሳቸው በር ያላቸው ሌላ ከፍሎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ክፍሎች ጠንከር ያለ ምርመራ እየተደረገባቸው ላሉ መንፈሰ ጠንካራ ሰዋች የተዘጋጀ ነው፡፡ እነዚህ ክፍሎች ውሰጥ የሚታሰር ሰው በቦታ ጥበት፣ በጨለማ እና ብቸኝነት ይፈተናል፡፡

---
ይህ ታሪክ ለአንባቢ ምቾት ሲባል ከተደረገለት ዘይቤያዊ ማስተካከያ በስተቀር እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡
---
(ይቀጥላል)

No comments:

Post a Comment