Thursday, January 28, 2016

‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› (ክፍል ፪)

በናትናኤል ፈለቀ

(ካለፈው የቀጠለ)

የማታው የመፀዳጃ ሰዓት አብቅቶ እስረኞችን ቆጥረው በሩን የሚቆልፉት ፖሊሶች መጡ፡፡ ሼህ ጀማል ዘወትር እንደሚያደርጉት የመጡት ፖሊሶችን ሰዓት ጠየቋቸው፡፡ አልፎ አልፎ በቁጣ ተሞልተው ከሚመጡት ፖሊሶች በስተቀር ሰዓት ለመናገር አብዛኞቹ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ 12 ሰዓት ከ10 ደቂቃ እንደሆነ የተነገራቸው ሼህ ለመግሪብ ጸሎት የቀረው ግማሽ ሰዓት እንደሆነ ክፍሉ ውስጥ ለነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች አሳወቁ ኡመድ ለፈረሃን ተረጎመለት፡፡

Photo: HRW Report - "They Want Confession"
ደቂቃዎች አልፈው የፀሎት ዝግጅት ላይ እያሉ ከሳይቤሪያ ኮሪደር መግቢያ ላይ የሚንቆጫቀጭ የካቴና ድምፅ በከስክስ ኮቴ ታጅቦ ተሰማ፡፡ ድምፁ ምን ማለት እንደሆነ ክፍሉ ውስጥ ያሉት 14ቱም ይገባቸዋል፡፡ በእስር ለቆዩት ሰዎች ግር ያላቸው ነገር ተቆጥረው በር ከተዘጋ በኋላ በዚህ ፍጥነት ለምርመራ የሚጠራ ሰው መኖሩ ነው፡፡ የካቴናው ድምጽ 7 ቁጥር በር ላይ ሲደርስ ቆመና በሩ ተከፈተ፡፡ ‹‹ፈረሃን ኢብራሂም›› ከውጭ የመጣው ጥሪ አስተጋባ፡፡ ለምርመራ ሲጠራ የመጀመሪያው የሆነው ፈረሃን ምን ማድረግ እንዳለበት ግር ብሎት ተደናበረ፡፡ ተነስቶ ቆመ፡፡ ‹‹ፈረሃን ኢብራሂም እዚህ አይደለም?›› ከውጭ የቆመው ፖሊስ ጠየቀ፡፡ ኡመድ ፈርሃን እንዲወጣ በምልክት ወደበሩ ጠቆመው፡፡ ፈረሃን ኮፍያ ያለውን ሹራብ ደረበና ወጣ፡፡

ውስጥ የቀሩት ሰዎች እርስ በርስ ለምን በዚህ ሰዓት ሊጠራ እንደቻለና ምን ሊከሰት እንደሚችል የራሳቸውን መላምት እየሰጡ ክፍሉን በጫጫታ ሞሉት፡፡ በሼህ ጀማል የተመራው ፀሎት ተጠናቆ ብዙም ሳይቆዩ ወደ 7 ቁጥር እየቀረበ የመጣ የእግር ኮቴ ሰምተው ደግሞ ማን ይሆን ባለተራ ብለው በሰቀቀን በር በሩን ያዩ ጀመር፡፡ በሩ ተከፈተና ፈረሃን ገብቶ በሩ ተዘጋ፡፡ ከሄደ ግፋ ቢል ግማሽ ሰዓት ቢሆነው ነው፡፡ በዚህ ፍጥነት የሚጠናቀቅ የመጀመርያ ምርመራ የለም፡፡ ቢያንስ በምርመራ ወቅት እስኪሰለች ድረስ በተደጋጋሚ የሚጠየቀው የሕይወት ታሪክ ከ30 ደቂቃ በላይ መፍጀት አለበት፡፡

ፈረሃን በተፈጠረው ነገር እንደተገረመ ፊቱ ላይ ያስታውቃል፡፡ ኡመድ ምን እንደተከሰተ ሊጠይቀው ሲል ፈረሃን ቀድሞ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ‹‹እነዚህ ሰዎች የሚደንቁ ናቸው!›› አለ፡፡ ‹‹እንዴት?›› የኡመድ ተጠባቂ ጥያቄ ነበር፡፡ ፈረሃን ጭንቅላቱን መወዝወዙን ሳያቋርጥ፡ ‹‹ኮሪደሩን እንደጨረስን የለበስኩትን ሹራብ አስወልቆ ፊቴ ላይ አሰረው፡፡ በጣም አጥብቆ ስላሰረው እንዳመመኝ እና መተንፈስ እንደተቸገርኩ ብነግረውም ምንም ውጤት አልነበረውም፡፡ ከዛ እየመራ የሆነ ክፍል ውስጥ ከተተኝ፡፡ ስሜን፣ ከየትኛው የሱማሌ ጎሳ እንደሆንኩኝና ለምን ወደኢትዮጵያ እንደመጣሁኝ ጠየቁኝና ጨርሰናል ብለው መለሱኝ፡፡›› ብሎ በእጁ አንጠልጥሎት የገባውን ሹራብ መልበስ ጀመረ፡፡ ‹‹ሲያናግሩህም ፊትህን ሸፍነውህ ነበር?›› ኡመድ ተገርሞ ጥያቄውን ቀጠለ፡፡ ‹‹ኮሪደሩን ስንጨርስ እንዳሰረኝ መልሰውኝ እዛው ስደርስ ነው ከፊቴ ላይ የፈቱልኝ፡፡›› ነገርየው ይበልጥ እንቆቅልሽ የሆነበት ኡመድ ሌላ ጥያቄ አስከተለ ‹‹ስንት ሆነው ነው ያናገሩህ?››፡፡ ‹‹ሁለት ድምፆች መስማቴን እርግጠኛ ነኝ›› አለ ፈረሃን፡፡ ፈረሃን በጥያቄዎቹ መሰላቸቱን ኡመድ ቢረዳም ጉጉቱን ግን ማሸነፍ አልቻለም፤ ‹‹ሊያናግሩ የወሰዱህን ክፍል አቅጣጫ ታስታሰዋለህ?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ‹‹ደረጃ ይዘውኝ ስለወጡ ፎቅ ላይ መሆኑን ብቻ ነው የማውቀው፡፡›› ፈረሃን መለሰ፡፡ ኡመድ ማዕከላዊ በቆየባቸው አንድ ወር ከግማሽ ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥመው የመጀመሪያው ነው፡፡ በርግጥ እራሱም ወደ 11፡30 አካባቢ አንድ ቀን ተጠርቶ ነበር፡፡ የዛኔ ምርመራ ያደረገበት ምንም የማያውቅ ግን ብዙ የሚያውቅ ለማስመሰል የሚጥር ከደኅንነት መሥሪያ ቤት የመጣ ሰውዬ ነበር፡፡ ሰውየውን አይቶታል፡፡ ለምርመራ ሲወስዱትም ዓይኑን አልሸፈኑትም፡፡ ፈረሃን የነገረውን እየተረጎመ ለሌሎቹ ሲነግራቸው ፈረሃን በመኻል አቋረጠውና ‹‹የአንደኛው ሰውዬ ድምፅ ግን ካረፍኩበት ሆቴል ይዘውኝ ሲመጡ ሲቪል ለብሶ የነበረውን ሰውዬ ድምፅ ይመስላል፡›› አለ፡፡ ሁሉም በሰሙት ነገር ተገርመው እያወሩ እንቅልፍ አንድ በአንድ ጣላቸው፤ ሌንጂሳ እስኪጠራ ድረስ፡፡

በማግስቱ ማክሰኞ ፈረሃን በተመሣሣይ ሰዓት ተወስዶ ሩብ ሰዓት እንኳን የሞላ ምርመራ ሳይወስድ ተመለሰ፡፡ በዚህኛው ምርመራ ደግሞ ሲጠየቅ የነበረው ወደኢትዮጵያ አብሮት የመጣ የሚያውቀው ሰው እንዳለ እና ጢያራ ማረፊያ ተገኝቶ የተቀበለው አስጎብኚን ማን እንዳስተዋወቀው ነበር፡፡ ፈረሃን አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ጢያራ ማረፊያ ከመጣበት ጢያራ ሲወርድ ሰላምታ ከተለዋወጠው አንድ ሴንት ፓውል በመልክ ብቻ ከሚያውቀው ተለቅ ያለ ሱማሌ ውጪ ሌላ የሚያውቀው ሰው በመንገዱ ላይ እንዳላጋጠመው እና አስጎብኚ ያሉት ሰው የእናቱ የወንድም ልጅ እንደሆነ ፊቱን ሸፍነው ለሚመረምሩት ሰዎች አስረድቶ ተመለሰ፡፡ 

Tuesday, January 26, 2016

‹‹ማዕከላዊ ነው እንዴ ያለነው?›› (ክፍል ፩)


በናትናኤል ፈለቀ

እራሳቸውን ድንገት ስተው ‹‹ኮማ›› ውስጥ የገቡ ወላጅ አባቱን ለማስታመም እና በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈውን አሳዳጊ ሴት አያቱን እርም ሊያወጣ ከ15 ዓመት በላይ ወደተለያት ሀገሩ እየተመለሰ ነው፡፡ ለጉዞው ቀና ብሎ ያሰበው መንገድ ከሚኖርበት ሴንት ፖውል፣ ሚኒሶታ ወደካናዳዋ ቶሮንቶ አቅንቶ ከዛ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት እና በማግስቱ አውቶቢስ ተሳፍሮ አባቱን ወደሚያገኝበት የሱማሌ ክልል ከተማ ጎዴ ማምራትን ነበር፡፡

ወደ ሀገሩ ተመልሶ አባቱን ለማግኘት እጅግ ቸኩሏል፤ ተጨንቋል፡፡ ጭንቀቱን የሚያሳብቀው ገና ከተወለደች ሁለት ሳምንት ያልሞላትን ሁለተኛ ልጁን እና የሦስት ዓመት ወንድ ልጁን አራስ ባለቤቱ ላይ ጥሎ ጉዞውን መጀመሩ ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ እንዳቀደው ከሄዱለት በአንድ ወር ግዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ቆይታውን አጠናቆ ዜጋዋ አድርጋ ወደተቀበለችው አሜሪካን ይመለሳል፡፡

በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ግንቦት 29 ቀን፣ 2006 ዓ.ም ዕለተ ዓርብ የ31 ዓመቱ ፈረሃን ኢብራሂም አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የጢያራ ማረፊያ ደረሰ፡፡ አብረውት አዲስ አበባ እንዲደርሱ የሸከፋቸው ሻንጣዎች ግን አልደረሱም፡፡ ጉዳዩን ያስረዳቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ጓዙ የሚመጣው በሚቀጥለው በረራ እንደሚሆን፤ ይህ ማለት ደግሞ አዲስ አበባ የሚደርሰው ከሁለት ቀን በኋላ እንደሚሆን አስረዱት፡፡ የዕቅዱ መዛነፍ የመጀመርያ ምዕራፍ ይህ ሆነ፡፡ ነገርየው ብዙም የሚያስጨንቅ ሆኖ አላገኘውም፡፡ በሥራው ምክንያት የብዙ ግዜ የአየር ጉዞ ልምድ ስላለው እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያውቃል፡፡ አባቱን የሚያገኝበት ግዜ መራዘሙ ቢያሳስበውም አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት ቀን እንዲቆይ መገደዱ ከተማዋን ዞር ዞር ብሎ ለማየት የሚፈጥርለትን ዕድል በማሰብ ለመፅናናት ሞከረ፡፡

***

ፋይሰል ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የሁለተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ ነው፡፡ የትምህርት ወጪውን የሚሸፍንለት በፎቶ ብቻ የሚያውቀው የአጎቱ ልጅ ከአሜሪካን ሀገር ሲመጣ ተቀብሎ አዲስ አበባ ያለውን መስተንግዶ ጨርሶ ወደጎዴ ለመላክ ያለውን ኃላፊነት እሱ ወስዷል፡፡ የአጎቱ ልጅ ሲያገኘው እንዲኮራበትም በቅርቡ በላከለት ገንዘብ ያሰፋውን ጥቁር ሱፍ ግጥም አድርጎ ለብሶ፣ አበባ ይዞ ቦሌ ዓለም አቀፍ ጢያራ ማረፊያ መንገደኞችን ለመቀበል ከተደረደሩት ሰዎች መኻከል ተገኝቷል፡፡

እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 12፡30 ገደማ ፋይሰል ፈጽሞ ሊገባው ባልቻለ ሁኔታ እራሱን የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የተጠርጣሪዎች ማረፊያ ክፍል ቁጥር 9 ውስጥ አግኝቶታል፡፡ ከሱ አስቀድሞ ክፍሉ ውስጥ ነበሩትን ሰዎች ምን እየተፈጠረ እንደሆነ እንዲያስረዱት በሚችላት ትንሽ አማርኛ ተፍጨረጨረ፡፡ ሊገባው የቻለው ነገር ያለበት ቦታ በተለምዶ ማዕከላዊ እየተባለ እንደሚጠራ እና ያሉበት ክፍል የሚገኝበት ሕንፃ በቅዝቃዜው ምክንያት ‹‹ሳይቤርያ›› የሚል ስያሜ እንደተሰጠው
ብቻ ነው፡፡

***

ፈረሃን ለመጀመርያ ጊዜ በዕጁ ያጠለቀውን ካቴና ፈትተው አንድ ደብዛዛ ብርሃን ያለበት ክፍል በር ከፍተው ገፈተሩት፡፡ ከሻንጣው ውስጥ ወደማረፊያ ቤቱ ይዞት እንዲገባ የተፈቀደለትን አንድ ቅያሪ ቱታ እና የጥርስ ብሩሽ እና ሳሙና በቢጫ ፌስታል እንዳንጠለጠለ በሩ አጠገብ ቆሞ የገባበትን ክፍል ይቃኝ ጀመር፡፡ በር ድረስ አጅበው ይዘውት የመጡት ሰማያዊ ቀለም ያለው ሬንጀር የለበሱ ሰዎች በሩን ሲዘጉት የወጣው ድምጽ የክፍሉን ቅኝት አቋርጦ በድንጋጤ ከበሩ አካባቢ እንዲርቅ አስገደደው፡፡

Monday, January 25, 2016

የኢትዮጵያ ሙስሊም ፈተና በ224 ደቂቃዎች

በዘላለም ክብረት

ክፍሉ ከኮሪደሩ ላይ ከተንጠለጠለ አምፖል በሚመጣ ብርሃን ፈገግ ብሏል፡፡ እኔም ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ወደ ክፍሉ ስገባ ከክፍሉ አንደኛው ጫፍ ላይ አንድ ቀጠን ያለ ሰው ድምፁን በትንሹ ከፍ አድርጎ ቁርዓንእየቀራ› ነበር፡፡ በክፍሉ ሌላኛው ጫፍ ላይ ደግሞ አንድ ፍራሽ፣ አንድ የውሃ ጀሪካን እና ትንሽ ልብሶች በፌስታል ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ በሌላኛው የክፍሉ ጫፍ ደግሞ የሽንት ባልዲ - ሽታውን ለመቀነስ ሲባል በግማሽ ውሃ ተሞልቶ ተቀምጧል፡፡ ክፍሉ ውስጥ እንደገባሁ አንዱ ጫፍ ላይ ትንሽ ቆም ካልኩ በኋላ በክፍሉ ውስጥ ያገኝሁት ብቸኛው ሰው ፍራሹ ላይ እንድቀመጥ በእጁ ሲጠቁመኝ ቁጭ አልኩ፡፡ ፍራሽ ላይ እንደተቀመጥኩ በፍራሹ ጫፍ ላይ የጆን ግሪሻም ‘The Last Juror’ መፅሃፍ ተቀምጦ አየሁት፤ አንስቼ ስመለከተው ክፍሉ ውስጥ ያገኘሁት ሰው ቁርዓን መቅራቱን ጨርሶ እንግሊዝኛ እችል እንደሆነ ጠይቆኝ ማውራት ጀመረ፡፡ ስሙ ሐሰን ጃርሶ እንደሚባል ነግሮኝ፤ በመፅሃፍ እጥረት ምክንያት ይሄን መፅሃፍ ለአምስተኛ ጊዜ እያነበበው እንደሆነም አጫወተኝ፡፡ መፅሃፉን ቃሊቲ እስር ቤት በታሰረበት ወቅት እስክንድር ነጋ እንደሰጠውም ነገረኝ፡፡ እኔም ለምን እንደታሰርኩ እንደማላውቅ ነግሬው እሱ ለምን እንደታሰረ ስጠይቀው በዜግነቱ ኬኒያዊ፣ የቀድሞ የዓልሸባብ ወታደር እንደነበርና አሁን 17 ዓመት ፍርደኛ ሆኖ ከቃሊቲ የከፍተኛ ጥበቃ እስር ቤት ከጥቂት ሰዓታት በፊት ተዘዋውሮ እንደመጣ ነገረኝ፡፡ ይህ ሚያዚያ 17/2006 የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) በገባሁበት ወቅት የገጠመኝ ጉዳይ ነው፡፡

ስለ ሐሰን ጃርሶ ከመታሰሬ በፊት አንድ ሰሞን ከአዲስ ዘመን እስከ ኢቴቪ የተቀባበሉት ጉዳይ ነበርና ሁኔታዎቹን ሲተርክልኝ ትንሽ ነገር በጊዜው ማስታወስ ችዬ ነበር፡፡

የቀድሞው ኢቴቪ የአሁኑ ኢቢሲ ‹እስልምና› እና ‹ሽብርተኝነትን› አስመልክቶ በተለይም በአለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ ‹ዘጋቢ ፊልሞችን (documentaries)› ያቀረበ ሲሆን፤ እኔም ለአጭር ጊዜ በታሰርኩበት ወቅት ‹በዘጋቢ ፊልሞቹ› ውስጥ የተጠቀሱትን ግለሰቦችና ቡድኖች የማግኘትና በጉዳዩ ላይ የመነጋገር ዕድል አጋጥሞኝ ስለነበር ይሄን አጋጣሚ በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ‹እስልምና› እና ‹ሽብርተኝነትን› አስመልክቶ ከቀረቡ አምስት የተለያዩ ‹ዘጋቢ ፊልሞች› (አዲስ ግንባር፣ ጅሃዳዊ ሐረካት፣ ሐዘን ለመድረስ … ጉዞ ወደ ደሴ፣ የጥፋት መልዕክተኞች እና የማንቂያ ደወል) ጋር አያይዞ ማየት የዘጋቢ ፊልሞቹን ዓላማና የሙስሊሙን ፈተና ያሳየን ይሆናል በሚል ሐሳብ ነው ይሄን ፅሁፍ መፃፌ፡፡

ያለፉት አምስት ዓመታት በማሕበረሰብ ደረጃ ትልቅ ፈተና ከገጠማቸው ኢትዮያዊያን መካከል ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ፈተናው በዋነኛነት ከመንግስት በኩል የመጣ ሲሆን፤ ይሄን ተከትሎም የውስጥ ስነ መለኮታዊ እሰጥ አገባው ሙስሊሙን እጅግ ፈተና ውስጥ እንዲዘፈቅ አድርጎታል፡፡ በተለይም በታሕሳስ 2004 ገንፍሎ አደባባይ የወጣው የሙስሊሙ የመብት ጥያቄን ተከትሎ በተለያዩ አቅጣጫዎች ፈተናው የጨመረ ሲሆን መንግስት ጉዳዩ የመብት ጥያቄ ነው ብሎ ከመቀበል ይልቅ ‹የሽብርተኞች ስራ› ነው በማለት የመብቱን ጠያቂዎች የተለያዩ ስያሜዎች በመስጠት ጥያቄዎቹን አልቀበልም በማለት ቀጥሏል፡፡ ከዚህ እምቢተኝነት ጋር ተያይዞም መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ዘጋቢ ፊልሞች በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ በማስተላለፍ የፕሮፓጋንዳ ቀዳሚነቱን ለመያዝ አሁን ድረስ እየደከመ ይገኛል፡፡ ፕሮፓጋንዳውን በዋነኛነት እየመራው የሚገኝው ደግሞ መንግታዊው ቴሌቪዥን ነው፡፡

መንግስታዊው ቴሌቪዥን ባለፉት አመስት ዓመታት ‹እስልምና› እና ‹ሽብርተኝነትን› አስመልክቶ ካቀረባቸው ዘጋቢ ፊልሞች መካከል ቀዳሚው በመግቢያዬ የጠቀስኩት ‹አዲስ ግንባር› የተባለው ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ የፊልሙ ዋነኛ ማጠንጠኛም አሸባሪው አል ሸባብ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ሕዋስ (cell) ለመዘርጋት ያደረገውን ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄን ድርጊት ተከትሎም ነው በጊዜው ጠ/ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የአልቃይዳ ሕዋስ ተገኝቷል፡፡ የዚህ ሴል አባላት ሁሉም ሰለፊ ናቸው›› በማለት ነበር ፓርላማ ቀርበው ንግግር ያደረጉት፡፡ የሕዋሱ አመራር እንደሆነ በዘጋቢ ፊልሙ የተገለፀው ኬኒያዊው ሐሰን ጃርሶ ለፍርድ ቤትም ሆነ እኔ ማዕከላዊ ባገኝሁት ወቅት እንደነገረኝ የዘጋቢ ፊልሙን ድምፀት (tone) ከመጠራጠር በቀር የአል ሸባብ አባል እንደሆነ እሱም አይክድም፡፡ ሐሰን እጅግ ብዙ ለመስማት የሚከብዱ ሁኔታዎችን እንዳለፈ የገለፀልኝ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥር የሚበዛው ሙስሊም ነው ከሚል የራሱ እምነት ተነስቶ እዚህ መምጣቱን ገልፆልኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሐሰንም ሆነ ድርጅቱ አል ሸባብ ስለ ኢትዮጵያ ብዙም የጠለቀ ግንዛቤ አላቸው ለማለት በማያስችል ሁኔታ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ለማየት ፍላጎቱ ያላቸው አልመሰለኝም፡፡

‹አዲስ ግንባርን› አሁን ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ደግሜ ስመለከተው በቀጣይ ከመጡት ዘጋቢ ፊልሞች ጋር በማነፃፀር የዘጋቢ ፊልሙ ዋነኛው ማጠንጠኛ ሆኖ ያገኘሁት ወደ ስነ መለኮታዊው ጉዳይ ወርዶ ‹ሰለፊያ› ያለውን ቡድን ኢላማ አድርጎ መምታትን እና ነባሩ እስልምና ያለውን ‹ሱፊያ› አጉልቶ ማቅረብን ‹አል ሸባብ ሰለፊ ነው› በሚለው ገለፃው ውስጥ እናገኛለን፡፡ ብሎም ‹በዋህቢያ ወይም ሰለፊያ አስተምሮ እየተመሩ [ሊያጠፉን ነው] … እነዚህን ሰዎች ማጥፋት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ እንዲጠፉ እንጠይቃለን እኛ› በማለት ብይን ይሰጣል፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ አደባባይ የወጣበትን አንደኛ ዓመት በሚያከብርበት ጥር 2005 ደግሞ መንግስታዊው ቴሌቪዥን ብዙ ሰዎችን ያስቆጣውን እና ቴሌቪዥን ጣቢያውን በፍርድ ቤት እስከመቆም ያበቃውን ‹ጅሃዳዊ ሐረካት› ይዞ ብቅ አለ፡፡ በዚሕኛው ዘጋቢ ፊልሙ አማን አሰፋ በተባለ የአልሸባብ ወታደር የተመራን ‹ሐረካተይ ሸባብል ሙጃሂዲን ፊ ቢላድን ሒጅራቴይን› የተባለን አንድን ቡድን (እስከ አሁን ድረስ ጉዳዩ ገና የፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተሰጠበት ቢሆንም ከሶስት ዓመታት በፊት በጊዜው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሽፈራው ገ/ማርያም ‹ይህ ቡድን በኢትዮጵያ የተገኘው ሁለተኛው የአልቃይዳ ሕዋስ ነው› በማለት ፍርድ ሰጥተውበታል) የሙስሊሙን የመብት ጥያቄ ለመንግስት ለማቅረብ በሕዝብ የተወከሉትን የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ጋር (ገና ክስ በተመሰረተባቸው በሁለተኛ ወሩ) በማስተሳሰር የቀረበ ነው፡፡ 

ይሄን ዘጋቢ ፊልም አሁን በድጋሚ ስመለከተው እጅግ በጣም እያዘንኩ እና መጨረስ በተደጋጋሚ እያቃተኝ ነው፡፡ በእስር ላይ በነበርኩበት ወቅት በየእለቱ በዘጋቢ ፊልሙ ከቀረቡት ሰዎች ጋር እገናኝ ነበርና፡፡ አማን አሰፋ በተባለ የአልሸባብ ወታደር የተመራን ‹ሐረካተይ ሸባብል ሙጃሒዲን ፊ ቢላድን ሒጅራቴይን› የተባለውን ቡድን አስመልክቶ እኔ መናገር የምችለው በእስር ወቅት አግኝቻቸው ስለነበሩት ስለ አቶ አማን አሰፋ ብቻ ነው፡፡ አቶ አማን አሰፋ ለፍርድ ቤትም እንዳስረዱት እርሳቸውም ‹ሰልፉ እየተጎበኘ ነው› ባሉትና ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት ባቀረበባቸው መፅሃፋቸው እንደገለፁት የአልሸባብ ወታደር መሆናቸውን አልካዱም ነገር ግን በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ አንዳችም ጉዳት ለማድረስ እንዳልተነሱ ገልፀዋል፡፡ የዚህ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ ሌሎች ግለሰቦችን አስመልክቶ ብዙም የማውቀው ነገር አለ ማለት ባልችልም፤ ክሳቸውን ተመልክቼ እንደ ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ያሉ ወጣቶች ምንም በማይገባቸው ጉዳይ በግፍ እንደታሰሩ አምናለሁ፡፡

ጅሃዳዊ ሐረካትን ስመለከት እጅግ ያሳዘነኝ ጉዳይ በሕይወታቸው ተያይተው የማይተዋወቁ ግለሰቦችን እና በፍፁም ለተለያየ አላማ የቆሙ ግለሰቦችን አንድ ላይ ‹ሁለቱ ቡድኖች፡ ከአልቃይዳ፣ ሻዕቢያ፣ አልሻባብና ግንቦት ሰባት ጋር የቀጥታ እና ተዘዋዋሪ ግንኙነት በመፍጠር … › በሚል ዘጋቢ ፊልሙ የፍርድ ውሳኔ ከመስጠቱ እጅግ በጣም አስቀድሞ ብይን ሰጥቶባቸዋል፡፡ የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ (መአኮ) አባላት ከሆኑት እና አሁን በግፍ ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ከሚገኙት አቡበክር አሕመድ፣ ካሚል ሸምሱ፣ አሕመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ መከተ ሙሔ እና ያሲን ኑሩ (በመስከረም 2008 ከእስር የተፈታ)፤ እንዲሁም ከኮሚቴው ጋር ሰርታችኋል ተብለው የግፍ ሰለባ ከሆኑት በድሩ ሁሴን፣ ሙባረክ አደም እና አቡበክር አለሙ (በመስከረም 2008 ከእስር የተፈታ) ጋር በታሰርኩበት ወቅት እጅግ የቀረበ ግንኙነት ስለነበረኝ በዘጋቢ ፊልሙ ‹ሁለተኛው ቡድን› ተብሎ ስለተገለፀው ቡድን ብዙ መናገር እችላለሁ፡፡
የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እና ተባብራችኋል ተብለው የተፈረደባቸው ኢትዮጵያዊያን 
                                                     © ማሕበራዊ ሚዲያ
የኮሚቴው አባላትም ሆኑ ከኮሚቴው ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው የተከሰሱትን ግለሰቦች እጅግ የሚከበሩ እና አይነተኛ ዜጎች (ideal citizens) ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ የታሪክ፣ የፖለቲካ እንዲሁም የሐይማኖት ንፅፅራዊ (Comparative Religion) እውቀታቸው ከፍ ያለ፤ አይደለም ከሽብርተኝነት ጋር ከግለሰብ ፀብ ጋር እንኳን ስማቸው አብሮ መነሳት የሌለባቸው፤ ይሄ ሁሉ በደል ተፈፅሞባቸውና ስማቸው ጠልሽቶ እንኳን ቂም የሚባል ነገር ማንም ላይ የማይቋጥሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ለሳይንሳዊ እውቀት ትልቅ ክብር የሚሰጡ (ከበድሩ ሁሴን ጋር ከስምንት ወራት በላይ አንድ ላይ አንድ ቤት ስንኖር በተደጋጋሚ አንስተን ያወራነው እና ሊያስረዳኝ የሚሞክረው ጉዳይ እሱ እጅግ ስለሚያደንቀው የታላቁ ስኮትላንዳዊ ፊዚስት ጀምስ ክለርክ ማክስዌልMaxwell’s Equations› ነው፡፡ በድሩ ሀይማኖታዊ እውቀቱ ከፍ ያለ ከመሆኑ ባለፈ በእንደ ጋንዲ አይነት ሰዎች ታሪክ የሚመሰጥ፤ በእንደ ማክስዌል አይነቱ ፊዚስት የሚደመም ሰው ነው)፣ በየቀኑ የሚያነቡና የሚፅፉ (የኮሚቴው አባላት ከታሰሩ ወዲህ ከ20 በላይ መፅሃፍትን ከእስር ሆነው ማሳተማቸውን ማየቱ ብቻ ለዚህ በቂ ነው) እንዲሁም ለሌላ ሐይማኖት ተከታዮችም ሆነ ለእንደኔ አይነቱ ሐይማኖት አልባ (Atheist) ክብር የሚሰጡ ግለሰቦችም ናቸው፡፡ ይሄን ስፅፍ ብዙ ስሜታዊ የሚያደርጉ ነገሮች እየተፈታተኑኝ ነው፡፡

እንግዲህ መንግስታዊው ቴሌቪዥን ‹ጅሃዳዊ ሐረካት› በሚለው ዘጋቢ ፊልሙ ግፍ የሰራባቸው እነዚህን መልካም ሰዎች ነው፡፡ በእስር ላይ በነበርንበት ወቅት ስለ ‹ጅሃዳዊ ሐረካት› እያነሳን ብዙ ተሳስቀናል፡፡ አቡበክር አሕመድ በድብቅ ካሜራ የተቀረፀው በረመዳን የፆም ወቅት ያለማቋረጥ ከአስራ ሁለት ሰዓታት ለሚበልጥ ጊዜ ‹ምርመራ› እየተደረገበት እኩለ ሌሊት ላይ እንደሆነ እያነሳ ‹ሕዝብ እንደሆነ እውነቱን በማግስቱ አውቋል› እያለ የሚስቅ ሰው ነው፡፡

ለማንኛያውም ዘጋቢ ፊልሙ አሁንም ዋሃቢያ/ሰለፊያ ያለውን ቡድን የችግሮች ሁሉ መነሻ በማድረግ ነባሩ እስልምና ወይም ሱፊያውን በማወደስ ተጠንቀቁ ይለናል፡፡

ሶስተኛው በመንግስታዊ ቴሌቪዥኑ የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ደግሞ በኢትዮጵያ ፈርስት ዶት ኮም ባለቤት አቶ ቢኒያም ከበደ የተዘጋጀው ‹ሀዘን ለመድረስ … ጉዞ ወደ ደሴ የተባለው ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ ይህ ዘጋቢ ፊልም በዋናነት በደሴ ከተማ የተገደሉትን የሸህ ኑሩ ይማምን አሟሟት ለማሳየት የቀረበ ሲሆን፤ ሸህ ኑሩን ወሃቢስቶች ናቸው የገደሏቸው በማለት በጉዳዩ ላይ ገና ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦችን ‹ቅጥረኛው ነፍሰ ገዳይ እና የሽብር ቡድኑ መሪ› በማለት ስማቸውን እየጠቀሰ ራሱ ከሶ ራሱ ፍርድ እዛው የሚሰጥ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ግን እስከ አሁን ድረስ ጥፋተኛ ያልተባሉና ጉዳዩም ገና በሕግ ሒደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው (በእስር ላይ በነበርኩበት ወቅት በዚህ ጉዳይ (‹የደምፃችን ይሰማ የደሴ ክንፍ አባላት› ተብለው) ተጠርጥረው ከታሰሩት አንዋር አደም እና አብዱ ያሲን ጋር ብዙ አውርተናል፤ ‹መንግስት ዜጎቹ ላይ ለምን ወንጀል እንደሚያቀነባብር አልገባንም;› ይሉኝ ነበር)፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ የተለመደውን የሰለፊያ/ሱፊያ ክፍፍል ለማጉላት ከመሞከሩ ባለፈም አሁን ያለውን ‹የድምፃችን ይሰማ› እንቅስቃሴም ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራል፡፡

በመንግስታዊ ቴሌቪዥኑ የቀረቡት ከእስልምና እና ከሽብርተኝነት ጋር ተያይዘው በአራተኝነትና በአምስተኝነት ከቀረቡት ዘጋቢ ፊልሞች በግንቦት 2007 የቀረበው ‹የጥፋት መልዕክተኞች› እንዲሁም አሁን በጥር 2008 የቀረበው ‹የማንቂያ ደወል› ናቸው፡፡ ሁለቱም ዘጋቢ ፊልሞች በይዘታቸውም ሆነ በአላማቸው አንድ አይነት ሊባሉ የሚችሉ ናቸው፡፡

‹የዛሬዎቹ አክራሪዎች የሙሃመድ አብዱል ዋሃብ አስተምህሮ ከመጣ በኋላ ብቅ ያሉ ናቸው› ከማለት ጀምሮ፤ ‹የአክራሪዎቹ መፅሃፍት ሊቃጠሉ ይገባል› በማለት ስነ መለኮታዊ ብይን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሁለቱም ዘጋቢ ፊልሞች በ ‹ሀዘን ለመድረስ … ጉዞ ወደ ደሴ› ዘጋቢ ፊልም ላይ ዋነኛ የትኩረት ነጥብ የነበሩትን ሸህ ኑሩ ይማምን የአክራሪነት ሰለባ በማድረግ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከአዲስ ግንባር እና ከጅሃዳዊ ሐረካት ዘጋቢ ፊልሞች ላይ ምስሎችን በመውሰድ  ሒደቱ የቀደምቶቹ ዘጋቢ ፊልሞች ቀጣይ ክፍል የሆነ ያክል እንዲሰማን ያደርጋሉ፡፡ በአጭሩ ሁለቱም ዘጋቢ ፊልሞች ‹መንግስት በሐይማኖታዊ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም› ከሚለው ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በተቃራኒው መንግስት ለዜጎች ይህኛው ሴክት› ይስማማችኋል ወደ ሚል ምርጫ የገባባቸው ሆነው ነው የቀረቡት፡፡

በአጠቃላይ አምስቱ ዘጋቢ ፊልሞች በተመሳሳይ ድምፀት፣ አስፈሪ እና አስገምጋሚ ማጀቢያ ሙዚቃዎችን ከጀርባቸው አድርገው፤ እጅግ ተቃራኒ የሆኑ ግለሰቦችን በአንድ ቅርጫት በመክተት የሚፈርጁ ከመሆናቸውም ባለፈ በዜጎች ላይ ፖለቲካዊ ብይን በመስጠት ሙስሊሙን የበለጠ ግራ መጋባት ውስጥ የሚከቱ እንዲሁም ሙስሊም ያልሆነውን ሕብረተሰብ ደግሞ ፍርሃትና ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በድምሩ 224 ደቂቃ የሚረዝሙት እነዚህ ዘጋቢ ፊልሞች ስለመንግስት ፍላጎት እና ሕብረተሰቡ ውስጥ ሊፈጠር ስለሚችለው ውዝግብ ብዙ የሚናገሩ ናቸው፡፡ መሰረታዊዎቹን እንኳን ብናይ፡

ሱፊያን ማጉላት - ሰለፊያን ማጠልሸት

ሁሉም ዘጋቢ ፊልሞች በአጭሩ የሚገልፁትን ነገር ቢኖር ነባሩ እስልምና (ሱፊያው) መቻቻልን የሚሰብክ እንደሆነና መጤው ዋሃቢያ (ሰለፊያ) ደግሞ ሃገሪቱን ወደ ትርምስ ለመክተት ሙስሊሙንም ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየመሩት ስለሆነ ሰለፊያውን መፅሃፋቸውን ሳይቀር በማቃጠል ማስቆም አለብን የሚል ነው፡፡ እኔ ያገኝኋቸው የዘጋቢ ፊልሞቹ ሰለባዎች ‹ሱፊ ነኝ› - ‹ሰለፊ ነኝ› ሲሉ አልሰማሁም ሁሉም ‹ሙስሊም ነኝ› ይሉኛል እንጂ፡፡ ከዘጋቢ ፊልሞቹ ግን የአሁኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት እንቅስቃሴ አደባባይ ከመውጣቱ በኩል መንግስት በተለያዩ የፖሊሲ ሰነዶቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለን የእስልምና አክራሪነት መገለጫ ‹ሃዎርጅያ› የተባለው የእስልምና ሴክት ነው የሚለውን የቀድሞ ፍረጃውን ትቶ አሁን ነገሮችን በማስፋት ሰለፊያው (ውሃቢያው) ነው የአክራሪነቱ ሁሉ መገለጫ ወደሚል አጠቃላይ ፍረጃ እንደገባ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የሱፊን አስተምሮ ድጋፍ በመስጠት ማጎልበት የሽብርተኝነት ዋነኛ መዋጊያ መሳሪያ እንደሆነ እንደ RAND Corporation እና Heritage Foundation ባሉ የአሜሪካ ፖሊሲ አማካሪዎች መገለፅ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ከሞሮኮ እስከ ሩሲያአልጀሪያ እስከ ፓኪስታን ድረስ ይሄን መመሪያ የመከተል አዝማሚያ እንደሚታይ የቅርብ ጊዜ ሂደቶች ያመላክታሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት እየተጠቀሰ ያለው የሱፊው አስተምህሮ መቻቻልን የበለጠ ይሰብካል ከሚል መነሻ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ይሄን ጉዳይ በጥልቀት ያጠኑት የበትለር ዩንቨርስቲው ዶ/ር ፌት ሙይዲን በቅርቡ በፃፉት አንድ ፅሁፋቸው ላይ፡
Promoting Sufism, particularly at the expense of other Islamic traditions is highly problematic. The perception of Sufism as […] a moderate or tolerant form of Islam cements a dichotomy between ‘good’ and ‘bad’ understanding of religion. […] Categorization of good and bad Muslims rely not on sound judgments of behaviors and actions but, rather on simple labels based on the way in which people practices their faith. 
በማለት ‹ሱፊያው መልካም ነው፤ ሌላው ደግሞ ጥፋት ነው› የሚል የእስልምና አረዳድ በጣም አደገኛ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ Mark Woodward et al በበኩላቸው ‘Salafi Violence and Sufi Tolerance? Rethinking Conventional Wisdom’ በተባለና ደቡብ ምስራቅ እስያንና ምዕራብ አፍሪካን እንደማሳያ በማድረግ ባዘጋጁት ጥናታዊ ፅሁፋቸው ከዚህ የዶ/ር ፌት ሙይዲን ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ‹ሰለፊያው ጦረኛ ነው፤ ሱፊያው ሰላማዊ ነው› የሚለው አካሄድ ከእውነታው የራቀ እንደሆነ እና ስነ መለኮታዊ ልዩነትን መሰረት ያደረገ አካሔድም የባሰ ችግርን እንጂ መፍትሔን እንደማይወልድ ይገልፃሉ፡፡ ዶ/ር ፌት ሙይዲን ጉዳዩን በሚገባ አጥንተው በፃፉትና ብዙ ተቀባይነት ባገኝው ‘Sponsoring Sufism: How Governments Promote Mystical Islam in their Domestic and Foreign Policy’ በተባለው መጽሃፋቸው በተለይም አንባገነናዊ መንግስታት ሱፊያውን ደግፈው የሚቆሙባቸው ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች አሉ በማለት ያስረዳሉ፡

  1. ሱፊያው ማሕበረሰብ በባሕሪው ከፖለቲካ ራሱን ያራቀ (apolitical) በመሆኑ አንባገነናዊ መንግስታቱ ፀጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት ይቀላቸዋል እንዲሁም፤
  2. እስልምና በዋናነት ከሚታወቅበት ካሕን አልባነት (non-clergical) በተለየ መልኩ የሱፊ የሐይማኖት አባቶች በሱፊያው ማሕበረሰብ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው በመሆናቸው እና ማሕበረሰቡንም ከፖለቲካ እንዲርቅ ማድረግ በቀላሉ ስለሚችሉ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡
በመንግስታዊው ቴሌቪዥን የቀረቡትን አምስቱንም ዘጋቢ ፊልሞች የተመለከተ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ሱፊያን ለማጠናከር መንገድ የመጥረግ ስራ እየተካሔደ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል፡፡ ከአሁኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት እንቅስቃሴ ጋር ስማቸው በመጥፎ ከሚነሱት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት እስራኤላዊው ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊኸ ከአስር ዓመት በፊት ከሙስጠፋ ካባ ጋር በመሆን በ International Journal of Middle East Studies ላይ ‘Al-Ahbash and Wahhabiyya: Interpretations of Islam’ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ፅሁፋቸው የኢትዮጵያንና የሊባኖስን መመሳሰል ተመልክተው በመደምደሚያቸው ላይ እንደ አህባሽ ያሉ የሱፊ አስተምህሮቶች እንዲጎለብቱ ቢደረግ መልካም እንደሆነ በገደምዳሜ ገልፀው ነበር፡፡ የዘጋቢ ፊልሞቹ መደምደሚያም ከዚህ እውነታ ጋር ይቀራረባል፤ ዶ/ር ፌት ሙይዲን በሚገልፁት መልኩ የሚሔድ መሆኑም ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ዶ/ር ሙይዲን ግን ‹ይህ በጣም አደገኛ አካሔድ ነው፤ ተጠንቀቁ!› እያሉ ነው፡፡

የመብት ጥያቄን መሸሽ

ሌላው የዘጋቢ ፊልሞቹ መሰረታዊ ባህሪ ለመንግስት ያልተመቹትን  ሁሉንም አይነት እንቅስቃሴዎች በስመ ሙስሊም በአንድ ቅርጫት ውስጥ መክተታቸው ነው፡፡ ይሄም በተለይም ላለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እያደረጉት ያለውን እጅግ ሰላማዊና ፍትሃዊ ጥያቄ በዘጋቢ ፊልሞቹ ከነአልቃይዳ እና አልሸባብ ጋር አንድ ላይ ደምረው በማቅረባቸው የሚታይ ነው፡፡ ዜጎች ሕገ መንግስቱን ይዘው አደባባይ ወጥተው ሕግ ይከበርልን ሲሉ የሌለን ዓላማ ፈጥሮ አላማችሁ ሌላ ነው ማለት መብት ጥያቄን ላለመመለስ የሚደረግ ሙከራ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የጠየቁት ጥያቄ የማይመለስላቸውና መብታቸው የማይከበርላቸው ከሆነ ደግሞ መብታቸውን ለማስከበር መጣራቸው አይቀርም፡፡ የመብት ጥያቄን መንግስት በዘጋቢ ፊልም አጥላልቶ ማለፉ ዘላቂነት ካለመኖሩም ሌላ ለመብት ጠያቂዎቹ ክብር አለመስጠትም ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያመጣው አይታወቅም፡፡

‹የከሸፈ የሽብርተኝነት ትግል?›

መንግስት የመብት ጥያቄዎችን ከሃይልና ከሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎች ጋር አመሳስሎ በዘጋቢ ፊልሞቹ ማቅረቡ ከሁሉም በላይ የሚያመጣው መዘዝ ደግሞ፤ የሚባለውን አክራሪነትም ሆነ ሽብርተኝነትን ከመከላከል ይልቅ የሚያባብስ ተግባር መሆኑ ነው፡፡ የሙስሊሙ (መአኮ) አባላት በተደጋጋሚ እንደሚሉት አክራሪነትንም ሆነ ሽብርተኝነትን መከላከል የሚቻለው ከሕዝቡ ጋር አብሮ በመስራት እንጂ መብትን የጠየቀን ሁሉ ‹አሸባሪዎች ናችሁ› በማለት አይደለም፡፡ ሽብርተኝነትን በእጅጉ የሚፀየፉትን እንደ የኮሚቴው አባላት ያሉ ሙስሊሞችን ‹ከአልሸባብ አባላት ጋር አንድ ናችሁ› ብሎ ፈርጆ ሽብርተኝነትን እታገላለሁ ማለት መቼም ፍሬ የሌለው ስራ ከመሆን አያልፍም፡፡ መንግስት አሁን የያዘው ሁሉንም ተቃውሞ በሽብርተኝነት የመፈረጅ አባዜ እጅግ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ጦስ ይዞ መምጣቱም አይቀርም፡፡

Guilty until proven Innocent

ሌላው የዘጋቢ ፊልሞቹ ተመሳሳይ ባህሪ ደግሞ በፍርድ የተያዙ ጉዳዮችን ያለምንም ሐፍረት ብይን መስጠታቸው ነው፡፡ መንግስታዊው ቴሌቪዥን አሸባሪዎች ናቸው ብሎ በመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው አባላት ላይ ውሳኔ የሰጠው ገና ዓቃቤ ሕግ ክስ በከፈተ በሁለተኛው ወር ላይ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሰጠው ግን መንግስታዊው ቴሌቪዥን ከወሰነባቸው ከሁለት ዓመት ከሰባት ወራት በኋላ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም የመንግስትን ውሳኔ ቀድሞ እያወቀ ነፃ ናቸው ብሎ ለማሰናበት ምንም አቅም አይኖረውም፡፡ ይሄን ተገንዝበው የመአኮው አባላት እነሱን አስመልክቶ የተላለፈውን ‹ጅሃዳዊ ሐረካት› የተባለው ዘጋቢ ፊልም እንዳይተላለፍ ከፍርድ ቤት እግድ (injunction) አውጥተው ቢሔዱም ማንም ሊሰማቸው አልፈቀደም፡፡ በደንብ ከሚታወቀው ከመአኮው ሒደት ባለፈም የሸህ ኑሩ ይማም ገዳዮች ናችሁ የተባሉ ግለሰቦችም በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ቅጥረኛ ነብሰ ገዳይ እና ሽብርተኞች ተብለው ከተፈረጁ ሁለት ዓመታት ቢያልፉም ይህ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያላላቸውና ጉዳያቸውም በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ነው፡፡

በዘጋቢ ፊልሞቹ ገና ጉዳዩ ፍርድ ቤት በር እንደደረሰ የሚሰጠው ይህ የጥፋተኝነት ውሳኔ በአጠቃላይ በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ በሚዲያ ማራገብ ከሚያመጣው ተፅዕኖ ባለፈ እንደኛ አይነት የፍርድ ቤት ነፃነት በስራ አስፈፃሚው ጉያ ውስጥ ባለ ሀገር ደግሞ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ነፃ ይሆናል ብሎ ማሰብ ራስን ማድከም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ አይነቱ ፍረጃ ዜጎች ጥፋተኝነታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ በሕግ ፊት ጥፋተኛ ተብለው ያለመገመት (presumption of innocence until proven guilty) ሕገ መንግስታዊ መብትን በመጣስ፤ በተገላቢጦሹ ራሳቸው ንፅህናቸውን እስኪያረጋግጡ ድረስ ጥፋተኛ ናቸው (presumption of guilty until proven innocent) ወደሚል መደምደሚያ ያደርሰናል፡፡

በሙስሊሙ ውስጥ ያለውን የስነ መለኮት መሰነጣጠር መጨመር

ኢትዮጵያ በሙስሊም ሕዝብ ብዛት በዓለም ላይ ካሉት ቀዳሚ አስራ አምስት ሀገራት አንዷ ስትሆን በሕዳጣን ሙስሊሞችም ረገድ በዓለም ላይ ከሕንድ ቀጥላ በሁለተኝነት ብዙ ሙስሊሞች ሕዳጣን (largest minority) ሆነው የሚኖሩባት አገር ናት፡፡ በዚህ ትልቅ ማሕበረሰብ ውስጥ የስነ መለኮታዊ ልዩነቶች መኖራቸው ባይካድም በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ እየቀረቡ ያሉት የዘጋቢ ፊልሞች (በተለይም ‹የጥፋት መልዕክተኞች› እና ‹የማንቂያ ደወል› በተባሉት ዘጋቢ ፊልሞች) ግን ልዩነቱን የበለጠ በማጉላት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ልዩነቶቹ የጎሉ እንዲሆኑ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ መንግስት በዘጋቢ ፊልሞቹ አንዱን ሴክት ደግፎ ሌላኛውን ማጣጣሉ ሙስሊሙ እርስ በርስ ከሱፊያ - ሰለፊያ ውዝግብ ባለፈ ትናንሽ ልዩነቶችን እያነሳ እንዲጠቋቆም በር የከፈቱ ናቸው፡፡ ‹ይሄ ሽርክ ነው›፣ ‹ይሄ ቢድኣ ነው› የሚለውን ፍረጃ በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር መሰማት የጀመሩበት ጊዜ ነው አሁን፡፡ በሙስሊሙ ዓለም የሚገኙት ስነ መለኮታዊ ልዩነቶች ሁሉ ዛሬ በመፅሃፍት፣ በሶሻል ሚዲያ እንዲሁም በሌሎች የመገናኛ መሳሪያዎች ላይ በርከት ብለው ለኢትዮጵያ ሙስሊም በገበያ ላይ ቀርበውለታል፡፡ ኢኽዋን፣ ተብሊግ፣ ሰለፊ፣ ዋሃቢ፣ ተክፊር፣ መደኺላ፣ሐዳዲያ፣ አህባሽ፣ ተብዲዕ፣ ተፍሲቅ፣ ተድሊል፣ ኻዋሪጅ፣ ሺዓ፣ ሱፊያ፣ ቀደሪያ፣ ሙዕተዚላ፣ ሙርጂት፣ አሕመዲያ፣ ማቱርዲያ፣ አሻሪያ፣ ከራሚ፣ ጀኸሚ፣ ቲጃኒ … እያለ የማያልቅ ስም መሰጣጣትና ፍረጃው በርትቷል፡፡ መንግስት በዘጋቢ ፊልሞቹ የመጡበትን የመብት ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ ይሄን ክፍፍል ማጉላትን እንደ ግብ በመያዝ ነገ ሌላ ፈተናን ይዞ መጣ ዘንድ ዛሬ የተመቻቸ ሜዳ እያዘጋጀለት ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሙስሊም የመብት ጥያቄ እንዲሁ መንግስት በዘጋቢ ፊልም አጥላልቶት የሚያልፍ እንዳልሆነ ያለፉት አራት ዓመታት ጥሩ ምስክሮች ናቸው፡፡ መንግስት ለተደራጀ የሰላማዊ ተቃውሞ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት አሻፈረኝ ባለ ቁጥር ችግሮቹ የበለጠ እየተባባሱ የሀገሪቱን ፈተና የበለጠ ያንሩታል፡፡ ይባስ ብሎም ችግሩ ላይ ሌላ ችግር እየጨመረ ሕዝበ ሙስሊሙን የበለጠ ግራ መጋባት ውስጥ ሲከተው - ሙስሊም ያልሆነውን የሌላ እምነት ተከታይ የበለጠ ፍርሃት ውስጥ እያስገባው ነው፡፡ 


Thursday, January 21, 2016

ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፡ የግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞ

በዘላለም ክብረት

ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ ይሄው 25 ዓመታት እየሆነው ነው፡፡ ይሄም በጆን አቢኒክ ቋንቋ ኢሕአዴግን በኢትዮጵያ የሪፐብሊክ ታሪክ (ከዘውዱ አገዛዝ በኋላ) ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆየው ስርዓት ያደርገዋል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን በወጣበት ወቅት የዓለም ፖለቲካዊ ምህዳር ከግራ ወደ ቀኝ ያደረገው ሽግግር ኢሕአዴግ ይዞት የመጣውን ቀይ የፖለቲካ ጥብቆ ባንዴ አውልቆ የምዕራቡ ዓለም መለያ የሆኑትን ባለ ነጭ፣ ሰማያዊና ቀይ የፖለቲካ ጥብቆ በግድ እንዲለብስ የተገደደበት ነበር፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ይሄን የኢሕአዴግን የርዕዮተ ዓለም ግርታ (confusion) ‹የግራ ፍሬቻ እያሳዩ ደብረ ብርሃን የደረሱት የኢሕአዴግ መሪዎች በፍጥነት ወደ ቀኝ ታጥፈው አዲስ አበባ ገቡ› በማለት ውብ አድርገው ይገልፁታል፡፡ ይህ ድንገተኛ የፖሊሲ ለውጥ ነው በመጀመሪያዎቹ አስር የስልጣን ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱን ‹በግምት› ሊባል በሚችል መልኩ  ያለወጥ ፖሊሲ እንዲመራት ያደረገው፡፡ ዴሞክራሲን በሚመለከት ግን ከዚህም በባሰ ደረጃ እስከ አሁን ድረስ ወጥ ሊባል የሚችል ፖሊሲም ሆነ እርምጃ ማግኝት ከባድ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

እንግዲህ የመንግሥት ፖሊሲ የሌለ ወይም ግልፅ ባለሆነ ጊዜ መንግሥቱን የሚመሩት ግለሰቦች የሚሰጡት አስተያየትና ሐሳብ ውስጥ ነው ፖሊሲውንና ርምጃውን የምናገኝው፡፡ ኢሕአዴግን በሚመለከትም ይህ የመሪውን ግለሰብ ቃል መከተል የፖሊሲውን አመላካች ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግል ስሜትና ፍላጎትም የኢትዮጵያ ፖሊሲ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ዘልቋል ማለት ይቻላል፡፡ ችግሩ ግን የመለስ ስሜትና ፍላጎት በየጊዜው ተቀያያሪ መሆኑ ነበር፡፡

መለስ አንድ ኢትዮጵያን ከ1983 እስከ 1993 ለዐሥር ዓመታት የገዙ ሲሆን በዚህ ጊዜ በብቸኝነት ሥልጣን ለመቆጣጠር የማያስችሉ ውስጣዊ ሁኔታዎች የነበሩ በመሆኑ በአፍ ደረጃ የዚህ ጊዜው መለስ ‹ዴሞክራት› መስለው ይታዩ ነበር፡፡ መለስን አንድን ከዴሞክራሲ ጋር በተገናኝ በሚገባ የሚገልፃቸው በጥር 1983 በኢሕአዴግ የመጀመሪያው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ እንዲህ በማለት የተናገሩት ንግግር ነው፡ 
ሕዝቡ ያልተገደበ የዴሞክራሲ መብት አለው እስካልን ድረስ ይህ መብት የመናገርን መብት፣ የመደራጀት መብት፣ የመጻፍን መብት፣ የመቃወምን መብት ሁሉ ያካተተ መሆን አለበት፡፡ የፈለገውን ፖርቲ መመሥረት መብቱ ነው፡፡ አንድ ብቻ ይበቃሀል፣ ሦስት ብቻ ይበቃሀል ወይም አርባ አራት ብቻ ይበቃሀል ተብሎ የሚገደብ ነገር አይደለም፡፡ እንደፈለገው ራሱን በነጻ ማደራጀት ይችላል፡፡ የራሱን አቋም የሚያራምድበት፣ የፈለገውን ሀሳብ ይዞ ቢያስፈልገው ፓርቲ መመሥረት ይችላል፡፡ ይሄ የዴሞክራሲ መብቱ ነው፡፡

Tuesday, January 19, 2016

“ልማታዊ” የትሮይ ፈረስ በኢትዮጵያ



በበፍቃዱ ኃይሉ

ጥንት፣ ዐሥር ዓመት ከዘለቀ የግሪክ እና ትሮይ ጦርነት በኋላ ግሪኮች ሰለቻቸው እና መላ ዘየዱ። ግዙፍ የጣውላ ፈረስ ገንብተው ውስጡ የተመረጡ ወታደሮችን አስቀምጠው ሸሹ። ይህንን እንደ ድል የቆጠሩት ትሮዮች ለድላቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ፈረሱን ጎትተው ከተማቸው መሐል አቆሙት፡፡ በውድቅት ለሊት፣ ፈረሱ ውስጥ የተደበቁት ግሪኮች ወጥተው የትሮይ ከተማን በማውደም በጦርነቱ አሸናፊነት ተቀዳጁ እስከወዲያኛው ይባላል። ዛሬ-ዛሬ በመላው ዓለም “የትሮይ ፈረስ” (Trojan Horse) የሚለው ሐረግ ‹ለእኩይ ዒላማ መሸሸጊያነት የሚሰጥ መልካም መሳይ ምክንያት› የሚለውን ለመግለጽ ይጠቅማል።


ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የገዢው ፓርቲ ብያኔ መሠረት የኢትዮጵያ ችግር የሠላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ (እንደ ቅደም ተከተላቸው) ነው። ሦስተኛው ለሁለተኛው፣ ወይም ሁለተኛው ለአንደኛው ሲባል ሊጨፈለቁ ይችላሉ። ሦስቱ አብረው እንደሚገኙ ሳይሆን፣ በተራ በተራ እንደሚረጋገጡ ይደሰኮራል፡፡ ሠላም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መኖር አለበት የሚለው የኢሕአዴግ መደምደሚያ የኦጋዴንን፣ የጋምቤላን እና በቅርቡ ደግሞ (በማስተር ፕላኑ ሳቢያ) የኦሮሚያን ሕዝባዊ ጭፍጨፋዎች ለማስተባበል (to justify) ከመዋሉም በላይ ብዙ የተሞተለትን የባድመን መሬት አሳልፎ መልሶ አስከመስጠት አስደርሷል። “ለሠላም” ሲባል! አንፃራዊ ሠላም ባለበት ጊዜ ደግሞ ዴሞክራሲ ለልማት በሚል ሰበብ እየደማ ነው። በሌላ በኩል የዚሁ ብያኔ ባለቤት ኢሕአዴግ “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ አይደለም፣ ግዴታ ነው” ይላል። ስለዚህ ‹ልማትና ዴሞክራሲን አብረን እያስኬድን ነው› የሚል ነቢብ እየደሰኮረ በሌላ አጀንዳ ደግሞ መልሶ ‹ለልማት ሲባል ዴሞክራሲ ይ ቆይ፤ የድኃ ሕዝብ ቀዳሚ ጥያቄ ዳቦ ነው› በሚል ዴሞክራሲን ጥያቄ እንደቅንጦት እቃ ጥያቄ ቸል ይለዋል። የሁሉም ነገር ታዛቢዎች ‹አለ የሚባለው ልማትስ የታለ?› ብለው መጠየቃቸው አልቀረም።

እውን ልማትና ዴሞክራሲ ይጋጫሉ?

ቻይናና ሕንድ፣ ሁለቱም፣ ልማታዊ አገረ-መንግሥት (developmental state) የሚል ማዕረግ አግኝተዋል። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ሕንድ ዴሞክራሲያዊ መሆኗ ላይ ነው። ፋሪድ ዘካርያ  “The Post-American World” ባሰኘው መጽሐፍ ሕንዶችን “በየዓመቱ በአማካይ 9 በመቶ የሚያድግ ኢኮኖሚ ይዘው በመሪዎቻቸው የማይደሰቱ ሕዝቦች ናቸው” ይላቸዋል። በየምርጫው መሪ ይቀያይራሉ። ቻይኖች ግን ለዚህ አልታደሉም። ነገር ግን እነሱ በፈንታው ‹ታድለናል› የሚሉለት ነገር አለ።

ፋሪድን አንድ የሕንድ ባለሥልጣን እንዲህ ብለውታል፡- “በፖለቲካው ረገድ ሕዝባዊነትን የሚያስገኙ ብዙ ቂላቂል ተግባሮችን መፈፀም አለብን።… እነዚህ ነገሮች የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕቅዶቻችንን ያደናቅፋሉ። ነገር ግን ደግሞ ፖለቲከኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ድምፅ ያስፈልጋቸዋል።…” አርክቴክት ኖርማን ፎስተር የተባለ ሰውም ይህንኑ የሚያጠናክር የሚመስል ነገር ለፋሪድ ነግሮታል። “በሕንድ፣ የኸርትሮው 5ተኛ ተርሚናልን ለመገንባት፣ የአካባቢ ተስማሚነት ቅኝት (environmental review) ለማድረግ የወሰደበት ግዜ፣ በቻይና ቢሆን የቤጂንግ አየር ማረፊያን (የኽርትሮው 5ቱንም ተርሚናሎች ቢደመሩ የሚበልጠውን) ጨምሮ ለመፈፀም የሚበቃ ጊዜ ነው።” ቻይናዎች የዴሞክራሲ “ጣጣ” የለባቸውም፤ ኮሚኒስቶቹ ይህንን እንደመታደል ይቆጥሩታል።

የሁለቱን ልዩነት ፋሪድ ዘካሪያ ሲደመድም “ዴሞክራሲ ለረዥም ጊዜ ልማት የራሱ የሆነ ተመራጭነት ሊኖረው ይችላል፤” ይላል። ሆኖም አውቶክራሲያዊ (ሕዝባዊ ተጠያቂነት የሌለባቸው) መንግሥታት “ትልልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በማይቀናቀኑት  አቅም ዐቅደው፣ ማስፈፀም ይችልሉ፤” ይላል። ፋሪድ በመደምደሚያው ያልገለፀው አውቶክራሲያዊ መንግሥታት የሚሠሯቸው ፕሮጀክቶች ያለበቂ ‹ሴክተር ሪቪው› በመሆኑ ለዘለቄታው የሚያስከትሉት ችግር መኖር አለመኖሩን ቀድሞ መገመት የማይቻል መሆኑን ነው። እንዲያም ሆኖ የቻይናን ልማት “ተአምራዊ” የሚሉት ኢኮኖሚስቶች የሕንድን የዛን ያክል አያዳንቁትም። ሕንድ የቻይናን ያክል መገስገስ ያልቻለችው በከፊል የሕዝብ ብዛት ዕድገቷን (Population growth rate) እንደ ቻይና መቆጣጠር ስላልቻለች ነው። ዴሞክራሲያዊ ተጠያቂነት የሌለባት ቻይና የሕዝብ ብዛት ዕድገቷን ፍጥነት በጉልበት መቆጣጠር ችላለች። ይህንን ለማድረግ የነደፈችው ስትራቴጂ ብዙ ማኅበራዊ ቀውስ እና ሰብኣዊ እልቂት ያስከተለ ቢሆንም መንግሥቷ አውቶክራሲያዊ ተጠያቂነት አላስከተለም። ያለቀው አልቆ የቀረው በቁሳዊ ጥቅም አንፃር ይለፍለት የሚል አቋም ይመስላል። ሕንድ ዴሞክራሲያዊ በመሆኗ ይህንን ዓይነት ነገር ማድረግ አትችልም፤ “ቻይኖች በሁሉም ነገር ይበልጡናል፤ ከሕዝብ ብዛት ዕድገት ፍጥነት በቀር” የሚሉትን ዝነኛ አባባላቸውንም ያፈሩት ለዚያ ይመስላል።

Monday, January 18, 2016

ዴሞክራሲና የዘውግ ብሔርተኝነት



በናትናኤል ፈለቀ

በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1983 . በኋላ የሀገሪቱን ስልጣን የያዘው ሕወኃት/ኢሕአዴግ መራሹ አገዛዝ ሀገሪቱን መልሶ ለማዋቀር ትከክል ብሎ ያሰበውን በዋነኝነት ቋንቋን ማዕከል ያደረገ የዘውግ ፌደራል ስርዓት ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ይህም በቅርብ ጊዜ የሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የዘውግ ማንነት ተኮር ውይቶች ጎልተው አደባባይ እንዲወጡ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የሀገሪቱን የፖለቲካ ልሂቃን ውይይት መድረክ የተቆጣጠረው የዘውግ ማንነት ተኮር (ብሔርተኝነት) አጀንዳ ልሂቃኑ በሚያሳዩት የፅንፈኝነት ባህሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ መጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ አሁን ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ አምባገነናዊ ቢሆንም በለውጥ ምክንያት ከስልጣን ቢወገድ በሚፈጠረው ክፍተት (Vacuum) ጊዜ ውስጥ የዘውግ ማንነት ተኮር የእርስ በርስ ግጭት ሊነሳ ይችላል ብሎ በመፍራት አምባገነናዊ ባህሪውን ይዞም ቢሆን ሕወኃት/ኢሕአዴግ መራሹ አገዛዝይቆይልንየሚል አስተያየት ያላቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አሁን ሀገሪቱ ውስጥ አለ ብለው የሚያምኑትን የዘውግ ተኮር ግጭቶች ስጋት ለመቆጣጠርልፍስፍስ ስለሆነ አምባገነናዊ ስርዓት አሁን ላለንበት ተጨባጭ የማኅበራዊ-ፖለቲካ ሁኔታ ተመራጭ ነውየሚሉ ሃሳቦችም ይሰማሉ፡፡

በርግጥ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት አስተያየቶች የሚሰነዝሩ ሰዎች ሀገሪቱ እስከመቼ በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ ብትቆይ እንደሚሻልና ምን ሲከሰት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግር ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ግልፅ የሆነ የመፍትሄ ሀሳብ አብረው ሲሰነዝሩ አይሰማም፡፡ አንድ ነገር ግን ግልፅ ነው፡፡ ሀገሪቱን ለአምባገነናዊ ስርዓት ለተራዘመ ጊዜ መተው መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች የዘውግ ማንነት ተኮር የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን የሚነሱ ጥያቄዎችን የሀገሪቱን ሉዓላዊ ግዛት አደጋ ውስጥ በማይከት ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚችሉ በማሳየት ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሚያስፈልጋት ይሞግታል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስለተፈጠረ ብቻ በዘውግ ብሔርተኝነት ምክንያት የሚፈጠር የግጭቶች ስጋት ተኖ ይጠፋል ማለት አይቻልም፡፡ ጽሑፉ ለማስረዳት የሚሞክረው ዴሞክራሲያዊ መንግስት (ስርዓት) በኢትዮጵያ ውስጥ ሲገነባ ችግሩ አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ አስጊ እንደማይሆን እና ከኢትዮጵያ በፊት ተመሳሳይ ስጋት የነበረባቸው ሀገራት ዴሞክራሲን ተጠቅመው ችግሩን እንዴት እንዳለፉት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴትና በማን ይመጣል የሚሉት ጥያቄዎች በዘውግ ብሔርተኝነት ጥያቄ መልስ ማግኝት ውስጥ ግብዓቶች ቢሆኑም ከዚህ ጽሑፍ ወሰን (Scope) በላይ ናቸው፡፡

የዘውግ ማንነት ተኮር የፌደራል ስርዓት ለምን ኢትዮጵያን ይበታትናል?

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የሚባል ድርጅት በአዲስ መልክ አደራጅተው ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የተመለሱት ሌንጮ ለታ በጻፉት አንድ ጽሑፍ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ወደስልጣን ሲመጣ የነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ (setting) የዘውግ ማንነት መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርዓትን እንዲከተል ከታሪክ የተረከበው የውዴታ ግዴታ እንደነበር እና ብቸኛ ሀገሪቱን ከመበታተን ለማዳን የሚችል ስርዓት እንደነበር አስረድተዋል፡፡ እንደሌንጮ ትንተና ከሆነ የዘውግ ማንነት ጉዳይ ገዢ ሕዝብን የማደራጅያ (mobilizing) ሀሳብ አድርገው የፈጠሩት በዘውግ ማንነታችን ምክንያት ጭቆና ደርሶብናል ብለው የዘውግ ማንነት ተኮር ድርጅቶችን የመሠረቱ ቡድኖች ሳይሆኑ ከዛ በፊት ዘውግ ተኮር ጭቆናን የፈፀሙ ሀገሪቷን ይገዙ የነበሩ ቡድኖች ናቸው በማለትዘውግ ማንነት ተኮር ንቅናቄዎችን ቀድሞ ለተፈጠረ ችግር ምላሽ ብቻ እንደሆኑ ያስቀምጣሉ፡፡

ሌንጮ በጽሑፋቸው የፌደራል ስርዓቶች በተፈጥሯቸው የአገር ግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ ጥንካሬ እንደሚያንሳቸው፣ የፌደራል ስርዓቱ የተዋቀረው ደግሞ የዘውግ ማንነትን (ቋንቋን) መሠረት አድርጎ ከሆነ የበለጠ ደካማ እንደሚያደርገው አትተዋል፡፡ የሌንጮን ሃሳብ የሚያጠናክር ተሞክሮ ለመጥቀስም የዓለም ግዙፏ ዲሞክራሲ ህንድ ከታላቋ ብሪታኒያ ቀኝ ግዛት ተላቃ ከፓኪስታን ጋር ፍቺ ከፈጸመች በኋላ ሃገሪቷን በጠቅላይ ሚነስትርነት ያስተዳድሩ የነበሩትጆዋሃርላል ኔህሩየገንጣይነት ስሜትን ያበረታታል እና ሀገሪቷን ወደ በለጠ መከፋፊል ያመራልበሚል ምክንያት የሕንድ ፌደራል ስርዓትን ቋንቋን መሠረት አድርጎ መልሶ ለማዋቀር ይነሱ የነበሩ ምክረ ሃሳቦችን ለመቀበል ፍላጎት እንዳልነበላራቸው አቱል ኮህሊ የተባሉ የሕንድ ማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ “Can Democracies Accommod-ate Ethinic Nationalism? Rise and Decline of Self-determination Movements in India” በሚልርዕስ ባስነበቡት የጥናት ጽሑፍ ውስጥ ጠቅሰዋል፡፡ ኔህሩ የኋላ ኋላ ግን የታሚል ቋንቋ ተናጋተናጋሪዎች የራሳቸው ፌደራል ግዛት (Tamil Nadu) እንዲኖራቸው ያነሱትን ጥያቄ ተቀብለው የታሚል ቋንቋ ተናጋሪዎች ግዛት እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡ የሰጉት የመበታተን አደጋ ግን አልተከሰተም፡፡