Saturday, September 5, 2015

ግብታዊ ጩኸት፣ ለቅስፈት....

Non-Violence for Dummies!
ግብታዊ ጩኸት፣ ለቅስፈት....


ሕወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነን መሆኑ ታውቋል፡፡ ምርጫ እንደሚያጭበረብር ታውቋል፡፡ የሲቪል ማኅበራት ፓርቲዎችን ገቢ በማሳጣት፣ መሪዎቻቸውን በማሰር፣ ውስጣቸው ክፍፍል በመፍጠር እንደሚያዳክማቸው ታውቋል፡፡ ነፃ ፕሬሶችን እንደሚያደናቅፍ ታውቋል፡፡ ሰላማዊ ትግሉ ከነዚህ በላይ ሆኖ የሚያሸንፍበትን መንገድ (Strategy) መንደፍ አለበት፡፡ ነገር ግን ያልታወቀም ነገር አለ፡፡ ኢሕአዴግ አስካሁን አልተፈተነም፡፡ ለቀላሏ ፈተና (ድኅረ ምርጫ 97 ለገጠመው ተግዳሮት) የሰጠው ምላሽ ያልተመጣጠነ ነበር፡፡ እርግጥ ያ አጋጣሚ ተቃዋሚው ሰላማዊነቱን ያጣበት ነበር፡፡ የመንግሥት እርምጃ ግን የቻይናውን (የታይናንሜን ስኩዌር) እርምጃ ያስታውሰናል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት አደባባይ ወጥተው አንገባም ያሉትን ሰልፈኞች የቻይና መንግሥት በታንክ ሳይቀር ነው የበተነው፡፡ ኢሕአዴግ የደርግን ያክል ቢፈተን ከደርግ አይብስም ወይ? እነዚህን ያወቅናቸውን እና ያሳወቅናቸውን የኢሕአዴግ ባሕርያት ማሰላሰል የሰላማዊ ትግሉን መሥመር ለመወጠን ወሳኝ ቁምነገር ነው፡፡ እስከአሁን የነበረው ዓይነት ሁሉም በየፊናው ያሰኘውን የሚያደርግበት፣ ያልታሰበበት መፍጨርጨር በአጭር በአጭሩ ከመሰበር በቀር ምንም አልፈየዱም፡፡ ብዙ ጊዜ አምባገነኖች የሰላማዊ ትግልን አከርካሪ ለመስበር የሚጠቀሙበት ዘዴ ሰላማዊ ያልሆነ ነገር እንዲሰሩ ማድረግን ነው፡፡ ሰላማዊ ትግሉ ሁለቱን እርከኖች (ማንቃት እና ማደራጀት) አልፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲጀምር ሰላማዊነቱ እና ደኅንነቱ እንዴት ይጠበቃል?
ሐዲስ አለማየሁ ‹‹የልምዣት›› ላይ ‹‹የጨለማው ንጉስ›› የተባለ በበሻህ ዘለሌ የሚመራ ቡድን ፈጥረዋል፡፡ ቡድኑ ሕዝብ የበደሉ ባለሥልጣናትን እየገደለ፣ ለምን እንደተገደሉ የሚገልጽ ማስታወሻ ጽፎባቸው ይሰወራል፡፡ ኋላ ግን ቡድኑ ከበሻህ ዘለሌ ቁጥጥር ውጭ ሆነ፡፡ የቡድኑ አባላት መነሻቸውን ረስተው ገንዘብ ለመዝረፍ ተሰማሩ፡፡ ይህንን ቁንፅል የመጽሐፉን ታሪክ እዚህ መጥቀሴ የግብታዊ ርምጃን የመጨረሻ ውጤት ከዚህ የተሻለ የሚያሳይልኝ ምሳሌ ስለሌለ ነው፡፡


መጀመሪያ የብብቷን.......!
በተቃዋሚው ጎራ የተለመደ ድክመት አለ፡፡ ተቃዋሚው የቱንም ያክል በትንሽ አቅም ቢንቀሳቀስ፣ የሚጠብቀው ውጤት ብዙ ነው፡፡ ይህ የስስት ባሕሪ የያዘውን ጭምር ያሳጣዋል፡፡ በምርጫ 97 ተቃዋሚው ከመቼውም የበለጠ (31.6% ያህል) የፓርላማ ወንበር እንዳገኘ ኢሕአዴግ አምኖለታል፡፡ ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ አልነበረም፡፡ ሆኖም ተቃዋሚው ‹ኢሕአዴግ ምርጫውን ቢያጭበረብርስ በማለት አማራጭ ውጥን  (Plan B) ያላዘጋጀ በመሆኑ የያዘውን ይዞ ማልቀስ ሲኖርበት የያዘውንም አጥቷል› በማለት አቶ ግርማ ሞገስ ‹ሰላማዊ ትግል 101 ላይ› ይከራከራሉ፡-
‹‹በትግሉ ሜዳ መቆየት ያለብህ ያገኘኸውን ድል ሳትነጠቅ ተጨማሪ ድሎችን ማግኘት የሚያስችል ተጨማሪ አቅም እንዳለህ እርግጠኛ ስትሆን ብቻ ነው፡፡›› (ገጽ 199)
‹‹....ተቃዋሚው የነበረውን የተሻለ አማራጭ በምርጫ ያገኘውን ፓለቲካዊና ድርጅታዊ ድል ከነእንከኑ መቀበል ነበር፡፡ (ገጽ 205)
የውሸት ምርጫ አምባገነኖች ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኛ የሚጠቀሙበት ‹ዕውቅና› መግዣ ነው፡፡ የፈለገውን ያክል ተፎካካሪዎቻቸውን ቢደፈጥጡም፣ እነርሱን መጣል የሚችል ሰላማዊ ስትራቴጂ መንደፍ የሚቻለውን ምርጫን አስታኮ ነው፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች የያዙትን ይዘው፣ በምርጫዎች መሐል ራሳቸውን ወንበር መነቅነቅ በሚያስችላቸው መንገድ ማደራጀት እና ማዘጋጀት አለባቸው-ከነፈተናው፡፡


‹‹ምን ተይዞ ጉዞ?››
ተቃዋሚው ዘንድ በችኮላ የሚወሰኑ ግብታዊ ርምጃዎች ለዘላቂ ክሽፈት መንስኤ እንደሚሆኑ ተመልከተናል፡፡ የተደራጀ እና የነቃ ማኅበረሰብ በሌለበት ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት-አንድም በሚገኘው ሰው ማነስ (ትግሉ የሕዳጣን እየመሰለ)፣ አንድም ለአገዛዙ ምት እየተመቸ ከሚጠራው የሚያባርረው ሰው እንዲበዛ ያደርጋል፡፡ (ከምርጫ 97 ወዲህ እንኳ አንድም ሰው ያልወጣባቸው ሁለት የአብዮት ጥሪዎች ተደርገዋል፡፡) በሌላ በኩል የተለያዩ አድማዎችን ለመጥራት ብዙ ነገሮችን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ አብዮት ባለታክሲዎች ያደረጉት አድማ ወደር የለውም፡፡ ጆን ያንግ ላይ ‹አዲስ አበባ ሽባ ሆና ዋለች› ብለው ጽፈዋል፡፡በአምስት ሣንቲም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አገር ተንቀጠቀጠ፡፡ ይህንን እያስታወሱ የታክሲ ሥራ ማቆም አድማዎች ተጠርተዋል፡፡ ችግሩ ግን እነሱን የሚመለከት መነሻ አልነበረውም፡፡ እንዲያውም በድኅረ ምርጫ 97 የተጠራው በራሳቸው ተነሳሽነት በመሆኑ በከፊል ተሳክቷል፡፡ ግን ያለምንም ትርፍ ከ5 ቀናት በኋላ ወደነበረበት ቀስ በቀስ ተመልሷል፡፡ ለምን?፡- ሾፌሮቹ፣ ባለቤቶቹ፣ ረዳቶቹ ምን ይብሉ? ኤርምያስ ለገሠ (‹‹የመለስ ትሩፋት›› ባለው መጽሐፉ ላይ ) ‹ሥራው እንዲቀጥል ከመንግሥት ጋር መሞዳሞድ የጀመሩት ሱስ ያናወዛቸው ተራ አስከባሪዎች ናቸው› ይላል፡፡ ዞሮ ዞሮ በመንግሥት ድል አድራጊነት አድማው ከሽፏል፡፡ ጥቁር አሜሪካውያን በሞንትጎምሪ ከተማ (አላባማ)የጥቁሮችን መገለል በመቃወም በከተማ አውቶቡስ ላለመሳፈር ሲያድሙ፣ ጥቁሮች የሚጓጓዙባቸውን አማራጮች አመቻችተው ነበር፡፡ በአገራችን ሕወሓት/ኢሕአዴግን የኢኮኖሚ ትብብር ለመንፈግ ሲባል ‹ከነእከሌ አትግዙ› የሚሉ የአድማ ምክሮች ብዙ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡ ግን አልተሳኩም፤ ምክንያቱም ሸማቹ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ አድማዎች የሚጠሩ ከሆነ፣ ጉዳታቸው (ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው) አድማ መቺው ላይ ሳይሆን አምባገነኑ አካል ላይ መሆኑን (ወይም መሆን የሚችልበት መንገድ) ማረጋገጥ የመጀመሪያው ሥራ ነው፡፡


መውጪያ
‹‹ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ እንደማንማር ነው›› የሚለው አባባል የመጣው ለሰዎች የሚቀለው የሚያውቁትን መደጋገም ስለሆነና ያንኑ ስለሚያደርጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው፡፡ እንኳን በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል፣ ልጅ ከአባቱ ሥልጣን የሚወስደው በጦርነት ወይም በኃይል ነው፡፡ (ታላቁ ንጉሥ ቀዳማዊ እያሱ በ17ኛው ክ/ዘመን መስክ ጉብኝት ደርሶ ሲመለስ ጎንደር በብዙ መልኩ ተቃውሳ ጠበቀችው፡፡ በዚያ ላይ የሚወዳት እቁባቱ ሞታለች፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ንጉሱ ጣና ደሴት ካሉ ገዳሞች ገብቶ መነነ፡፡ ልጁ ተክለሃይማኖት  አጋጣሚውን ተጠቅሞ ንግሥናውን አወጀ፡፡ ሆኖም ግን አባቴ ተመልሶ ንግሥናዬን ይቀማኛል በሚል ስጋት እዚያው ጣና ደሴት ላይ አስገድሎታል፡፡)
ይህ የታሪክ ዥረት ፈሶ ፣ ፈሶ እኛ ጋር ደርሷል፡፡ የእኛ ትውልድም፣ እንደቀድሞው ሁሉ በትረ-ሥልጣኑን በኃይል ከጨበጠው ፋይል ጋር ተፋጧል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ‹‹ዴሞክራሲ ማለት ሕዝቦች ከጦር ሰራዊት (የበላይነት) ነጻ ሲወጡ ማለት ነው፡፡ ይላል እንደ ኮስታሪካ የጦር ሰራዊታችንን በትነን እስካሁን (67 ዓመት)በሰላም መኖር ባይሆንልን እንኳን ጦር ሠራዊቱን፣ ፖሊስ እና የደህንነት አካሉን የማንፈራ እና የማናፍርበት እንዲሆን ብዙ መታገል አለብን፡፡ በመታደል የሚገኝ የለምና፡፡ ጥያቄው ከትግል ሒደቱ ‹‹ጨዋ›› ወይስ ‹‹ባለጌ›› ይወጣን ይሆን› የሚለው ነው፡፡ የተለመደውን የጦርነት ታሪክ እናስቀጥላለን ወይስ አዲስ ታሪክ ለመሥራት   ተዘጋጅተናል›


ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ እና የመጨረሻው ክፍል ነው፡፡
የቀደሙትን ጽሁፎች ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? ‹‹ሠላማዊ ትግል ስንል?›› ‹‹ከሕወሓት መማር›› እና 
የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ ማስፈንጠሪያዎቻቸውን በመጫን ማንበብ ይችላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment