Friday, September 4, 2015

የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ

Understanding Dictators
የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ
ጂን ሻርፕ የአረቡ አለም አብዮት የሚባለውን እንዲቀጣጠል ነዳጅ ጨምሯል የተባለለትን ‹‹ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ›› የተሰኘ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ መጽሐፍ ውስጥ አብዛኛዎቹ አስረጂ ምሳሌዎች አምባገነኖች መሰረታቸው ሕዝብ መሆኑን ነው የሚነግሩን፡፡ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም በተደጋጋሚ ‹‹ጭቆና የሚሸከመው ትከሻ ይፈልጋል›› የሚሉን ይህንን ነው፡፡ አምባገነኖች ሕዝብ ጭቆና ለመሸከም ትከሻውን እንዲሰጣቸው ብዙ መንገዶቸን ይጠቀማሉ፡፡ የ‹ሠላማዊ ትግል 101› ጸሐፊ ግርማ ሞገስ ሶስት ነገሮችን የጠቅሳሉ፡- እነዚህም ፈቃደኝነት፣ ፍራቻ ወይም ግዴለሽነት ናቸው፡፡ የሚኪያቬሊ ፍልስፍናም (The Prince ላይ እንደተገለጠ) ‹‹ነገሥታት በመወደድ ብቻ ሳይሆን በመፈራትም ነው የሚኖሩት፡፡›› ከተቻለ ወዶ እና ፈቅዶ የሚተባበር፣ የሚታዘዝና ለምዶበት የሚታመንላቸውን፤ ይህ ሲከብድ ትልቅ ሠራዊት በመገንባት ወይም የደህንነት መረባቸው ትልቅ፣ ብልህ እና አስተማማኝ እንደሆነ በማስወራት ሕዝባቸውን እያስፈራሩ ትከሻው ላይ ይወጣሉ፡፡ ይህ ብቻውን ስላማያቆማቸው ያገኙትን ሞኝ ለማታለል ተቀባይነት የሚያስገኝላቸውን ዘዴም መዘየዳቸው አይቀርም፡፡
መንግሥታት ሥልጣን ላይ የሚቆዩት የተወሰነ ቅቡልነት (Legitimacy) እስካላቸው ድረስ ነው፡፡ የቀድሞ ነገሥታቶቻችን ራሳቸውን ‹‹ስዩመ እግዚአብሄር ›› በማለት ቅቡልነትን ለማግኘት ይጥሩ ነበር፡፡ ጳጳሳቱም (ሲሦ ቀላዳቸውን ለማግኘት) ይህንኑ ለሕዝቡ ይሰብኩ ነበር፡፡ ለአሁኖቹ መሪዎች ይህ አያዋጣም፡፡ ሕዋሓት የዘውግ ብሄርተኝነትን (ዕኩልነትን አስጠብቃለሁ በሚል ስም) ቅቡልነትን ሊገዛበት ሞክሮ ነበር፡፡ ብዙም አላስኬደውም፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ልማታዊነት›› የተባለውን ጨብጧል፡፡ ድሃ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተስፋዎች እንደሚያዘናጉት በመረዳት ‹‹መጀመሪያ ዳቦ›› እያለ እስከዚያው የመጨቆኛ ካርድ ለማግኘት ይጥራል፡፡ በዚህ አካሄድ ዊኒ ማንዴላ ተናግረውታል እንደሚባለው ‹‹ወፍራም ባሪያ›› መፍጠር ይፈልጋሉ፡፡  

አባገነኖች፣ ልዩ ፍጡሮች?
አምባገነንነት የሚፈጠረው ሰዎች ያልተገደበ ስልጣን ሲገጥማቸው ራሳቸውን መግዛት ስለሚከብዳቸው ነው፡፡ ብዙዎች የዓለማችን አምባገነኖች መጀመሪያ ምስኪን ነፃ አውጪዎች ነበሩ፡፡ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን እንኳን ብንወስድ ዐፄነት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት የድሀ አባት ነበሩ፤ ያውም ከበዝባዥ ፊውዳል ባለሀብቶች እየዘረፉ ለድሀ የሚያከፋፍሉ፡፡ ኋላ በትረ ሥልጣኑን ሲይዙ ግን በገዳይነት የሚወዳደራቸው አጡ፡፡  ‹‹የአገሬ ሕዝብ ስራት ያዝ ብለው እምቢ አለኝ›› እያሉ በስርዓት ማስያዝ ስም ሕዝቡን ፈጁት፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን ውስጣቸው የነበረው ቅንነት እየወቀሳቸው ‹‹አቤቱ አምላኬ፣ እባክህን ግደለኝ እና ሕዝብህን ነፃ አውጣ›› እስከማለት ደርሰው እንደነበር እንግሊዛዊ እስረኞቻቸው ጽፈዋል፡፡ሰዎች ሰላማዊነትን መምረጥ የሚኖርባቸው ከራሳቸው ድብቅ አውዳሚነት ራሳቸውን መጠበቅ ስለሚከብዳቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ- አምባገነንነት ባሕል ነው ማለት ይቻላል፡፡ አምባገነኖቻችን በቁልምጫ ነው የሚታወሱት፡፡ ‹‹መንጌ››ን መጥቀስ ይቻላል! አባወራዎች በቤተሰቡ ላይ ፍፁማዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ መምህራን በክፍል ተማሪዎቻቸው ላይ ፍፁም የበላይ ተደርገው ይሾማሉ፡፡ አለቆችም በምንዝሮቻቸው ላይ እንዲያው ናቸው፡፡ ሁሉም አቅሙ በፈቀደው ላይ ፍፁማዊ ኃይልን እና የበላይነትን መጠቀምን ባሕላችን ያበረታታል፡፡ ዘበኛው በደጅ ጠኚው ላይ፣ አሠሪው በሠራተኛዋ ላይ ኃያል ነው፡፡ ዕድሩ ስብሳቢው አይለወጥም፤ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ እስኪሞት አይሻርም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲው ሊቀመንበር አይቀየርም በዚህ ባሕል ውስጥ እየኖርን የአገር መሪ ብንቀያየርም ‹‹ተረኛ ጨቋኝ›› እንጂ ዴሞክራሲን አናመጣም፡፡
የአምባገነኖች አንድነት
አምባገነን አገር ወይም ብሔር የለውም፡፡ ቋንቋ የለውም፡፡ ሁሉም ያልሠለጠኑ ሕዝቦች ውስጥ ያለ ዕዳ ነው፡፡ አማር ቦንጎ ጋቦንን ለ42 ዓመታት ገዝቷል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎችን ለቤተዘመዱ አከፋፍሏል፡፡ ልጁ እሱ ሲሞት ሥልጣኑን ወርሷል፡፡ ሴት ልጁ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ነበረች፡፡ ባሏ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፡፡ በስሙ ያልተሰየመ ነገር የለም፤ ቦንጎ ዩኒቨርስቲ፣ ቦንጎ አየር ማረፊያ፣ ቦንጎ ሆስፒታል.... ሌላው ቀርቶ የትውልድ ከተማው ቦንጎቪል ተብላለች፡፡ እኛም አገር ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እስከ መለስ ዜናዊ እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡
የኮትዲቯሩ ሆፎኤት-ቦይኚ 6 ጊዜ የፕሬዚዳንት ምርጫን አሸንፏል፡፡ ያውም 99.7 በመቶ አማካኝ ድምፅ አግኝቶ! የአንዱን አምባገንነት ታሪክ መስማት፣ የሌላኛውን እንደመስማት ነው፡፡
አምባገነኖች ሥራቸውን ልባቸው ስለሚያውቀው ይፈራሉ፡፡ የደህንነት ሠራተኞችም ፍርሐታቸውን ለማረጋጋት የውሸት መረጃ ይሰጧቸዋል፡፡ የዩጋንዳው ኢዲ አሚን ዳዳ ለምሳሌ ‹‹ሕዝቡ በፕሬዚዳንቱ ፍቅር አብዷል›› የሚል የደኅንነት ሪፖርት ደርሶት እንደነበር ተነግሯል፡፡  አሁን፣ አሁን የአገራችን ባለሥልጣኖችም በጋዜጣ መግለጫዎቻቸው የሚያሳዩት ባሕሪ እንዲህ ዓይነት ሪፖርት የደረሳቸው በሚመስል መልኩ ነው፡፡
የራሺያው የቦልሼቪኮች ፓርቲ (እ.ኤ.አ በ1917 ጀምሮ እስከ 1940 ብቻ) በ23 ዓመታት ውስጥ ከ24 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ የቀረው አንድ ጆሴፍ ስታሊን ብቻ ነበር፡፡ 8ቱ ተገደሉ፣ 7ቱ ‹‹በተፈጥሮ አጋጣሚ ሞቱ›› ተባለ፣ 7ቱ ‹‹የደረሱበት ጠፋ›› ተባለ፣ አንዱ ታሰረ፡፡ ቀሪው አንድ አምባገነን ብዙ ሚሊዮኖችን ፈጀ፡፡ ይህንን ስታሊኒስታዊ አመራር (ተቀናቃኞችን ማጥፋት) ከልባቸው ያሳደሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንደስታሊን ማዕከላዊ ኮሚቴውን ባዶ ከማድረግ ይልቅ ፣ ታዛዥ አላዋቂዎች እንዲሰበሰቡበት አደረጉ፡፡ ልዩነቱ ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን ሞት ቀደማቸው፡፡ የቀሩት አባላት የሚያደርጉት ጠፋቸው፡፡ ስለዚህ የሟቹን ሌጋሲ (‹‹ትሩፋት››) እናስቀጥላለን በማለት በመለስ የተሾሙለትን ዓላማ እያስፈፀሙ ነው፡፡

ምርጫ በአምባገነኖች አገር
በአምባገነኖች አገር ምርጫ ማለት አሸናፊውን (ገዢውን) አጅቦ ለድል ማብቃት ማለት ነው፡፡ ወይም አምባገነኖቹ የሚፈልጉት እንደዚያ እንዲሆን ነው፡፡ The Dictator የተሰኘው ፊልም ነገሩን ግልጽ አድርጎታል፡፡ ሳላዲን የተባለው የዋዲያ መሪ የራሱን ኦሎምፒክ አዘጋጅቶ፣ ራሱ ተወዳድሮ ያሽንፋል፡፡ ውድድሩን ተኩሶ የሚያስጀምረው ራሱ ነው፡፡ የሚቀድሙትን ተወዳዳሪዎች እየተኮሰ ይጥላቸዋል፡፡ መጨረሻ ላይ ራሱ ያሸንፋል፡፡ ምርጫ ለአምባገነኖች እንዲህ ቀላል ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቹ አሸንፌ ድሌ ይከበርልኛል፡፡ ብለው ከሚያስቡ የሳላዲንን ሽጉጥ የጨበጠ እጅ ቢይዙ የተሻለ ያዋጣቸው ነበር፡፡ የአምባገነን መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የአምባገነንነት መንግሥት እጅ መያዝ አለባቸው፡፡
አገዛዙ ወይም የአገዛዙ ልሒቃን በምን ጥገኛ እንደሆኑ መለየት እና ያንን መንፈግን እንደትግል መሣሪያ (መደራደሪያነት) መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የእኛ አምባገነኖች ተፎካካሪዎቻቸውን የሚጥሉት በየትኛው እጃቸው ነው? የኃይል ምንጫቸው ምንድን ነው? ሠላማዊ ትግሉ ሊሠራው የሚጠብቀው የቤት ሥራ ነው፡፡ …ይቀጥላል፡፡

ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የቀደሙት ጽሁፎች ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? ‹‹ሠላማዊ ትግል ስንል?›› ‹‹ሓት መማር›› ማስፈንጠሪያዎቻቸውን በመጫን ማንበብ ይችላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment