Monday, June 15, 2015

የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎ

የዞን 9 ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች ሐምሌ 13 ለብይን ተቀጥረዋል። 1ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ሲ.ዲ በችሎት እንዳይታይ ታግዷል
በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያንና ሦስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች ዛሬ ሰኔ 8/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ፍርድ ቤቱ ግንቦት 19/2007 ዓ.ም በነበረው ችሎት ወቅት አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ የሲ.ዲ ማስረጃ አለኝ ባለው መሰረት ፍርድ ቤቱ በጽ/ቤት በኩል ሲ.ዲውን ተቀብዬ አያለሁ ማለቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሲ.ዲውን በጽ/ቤት ተመልክቶ ዛሬ ሲ.ዲው በግልጽ ችሎት ይታይ ወይስ በዝግ ችሎት የሚለውን ይወስናል ተብሎ ሲጠበቅ ጭራሽ ሌሎች ተከሳሾችም ሊመለከቱት እንደማይችሉ የሚገልጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በዚህም ፍርድ ቤቱ ‹‹ሲ.ዲውን በችሎት መመልከቱን ተገቢ ሆኖ ባለማግኘቱ….›› በሚል ድፍን ያለ ምክንያት በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ሲ.ዲ ዳኞቹ ብቻ በጽ/ቤት አይተውት እንደ አንድ ማስረጃነት ተቀብሎታል፡፡
ይህን ተከትሎ ተከሳሾች በብይኑ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን ጠበቆቻቸውም በጉዳዩ ላይ አለን ያሉትን አቤቱታ አስመዝግበዋል፡፡ ጠበቆቹ በአቤቱታቸው እንዳመለከቱት ሲ.ዲው ላይ የጠበቁት ብይን በግልጽ ችሎት ይታይ አይታይ የሚለውን እንጂ ሌሎች ተከሳሾችና ጠበቆቻቸውም እንዳያዩት ይከለከላል የሚል እንዳልነበር ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ክሱ በቡድን በማሴር…በማነሳሳት…›› የሚል ሆኖ ሳለ አንደኛ ተከሳሽ ላይ ቀረበ የተባለውን የሲ.ዲ ማስረጃ ሌሎች ‹‹ግብረ-አበሮች›› እንዳያዩት መከልከል ተገቢ የዳኝነት አሰራር አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ጠበቆቹ በሁለተኛነት በአቤቱታቸው ያስመዘገቡት ሲ.ዲው የቀረበበትን አግባብ በተመለከተ ነው፡፡ አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ በማስረጃ ዝርዝሩ ላይ ያልጠቀሰውን ሲ.ዲ አሁን በማስረጃነት ሲያቀርብ የማስረጃው አይነት የዶክሜንት ነው ወይስ የኤግዚቢት የሚለውንም በግልጽ አላስቀመጠም ብለዋል ጠበቆቹ በአቤቱታቸው፡፡ በተጨማሪም አቃቤ ህግም ሆነ ፍርድ ቤቱ ከአሁን ቀደም በነበረው ችሎት ውሎ አንድ ሲ.ዲ ብቻ እንደቀረበ ሲገልጹ የቆዩ መሆኑን በማስታወስና ተከሳሾችም የተገለጸላቸው አንድ ሲ.ዲ ብቻ ስለመቅረቡ ሆኖ እያለ ዛሬ ፍርድ ቤቱ ብይኑን ሲያሰማ ‹‹ሲ.ዲዎችን ተመልክተናቸዋል›› ማለቱ ግልጽ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ አስተያየቱን የተጠየቀው አቃቤ ህግ በበኩሉ ‹‹ብይን ባገኘ ጉዳይ ላይ አስተያየት አንሰጥም›› በሚል አልፎታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ቢሆን አቤቱታው ብይን ባገኘ ጉዳይ ላይ መሆኑን በመጥቀስ ‹‹ይግባኝ ማለት ትችላላችሁ›› በሚል አቤቱታውን ከመመዝገብ ውጭ በአቤቱታው የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ አመልክቷል፡፡
በመሆኑም ለአንድ አመት ከሁለት ወር ሲጓተት የዘለቀው የዞን 9 ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች የክስ ሂደት በቀጣይ ቀጠሮ ሐምሌ 13/2007 ዓ.ም ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ይኖርባቸዋል ወይስ በነጻ ይሰናበቱ የሚለውን ብይን ፍርድ ቤቱ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በእለቱ ችሎቱ ውስጥ ወደ 59 የሚጠጉ የሽብር ክስ ጋር ጉዳያቸው የተያዘ ሰዎች የቀረቡበት በመሆኑ ወላጆች ጋዜጠኞች እና ሌሎች ወዳጆች ችሎቱን ለመታደም አልታደሉም
የዞን 9 ማስታወሻ
እንደተለመደው ፍርድ ቤቱ የጓደኞቻችንን የመከላከል መብት በሚያጠብ መልኩ መወሰኑ የተለመደውን የአቃቤህግን ፍቃድ ብቻ መፈፀሙ እንዲሁም አለአግባብ የተራዘመ ቀጠሮ መስጠቱ በጣም አሳዝኖናል።
ሁልጊዜም እንደምንለው ንፁሃንን ለመፍታት አይዘገይምና ፍርድ ቤቱ ጓደኞቻችን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲያሰናብት ጥሪ እናስተላልፋለን።
ያልተሰራ ወንጀል ማስረጃ አይገኝለትም።
ስለሚያገባን እንጦምራለን ።
ዞን9

No comments:

Post a Comment