መንገድ ላይ ነዎት፤ አንድ ከተማን ለቀው ወደ ሌላ ከተማ እየተጓዙ ነው፤ ቢጓዙ ቢጓዙ ቀጥለው የሚጠባበቁት ከተማ አልደረሱም፤ ገጠሩ ረዝሞብዎታል፤ ‹እንዴ ይህ ሀገር ገጠር ብቻ ነው እንዴ?› ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ እባኮትን ዝም ብለው ይጓዙ ገና ብዙ የገጠር መንገድ ይቀርዎታል፡፡ ትንሽ ከተማ ነገር ያገኙ መስሎዎ ፈገግ ሊሉ ይችላሉ፤ አይሞኙ ፈገግታዎት ከከንፈርዎት ዘሎ፤ ፊትዎትን ከማዳረሱ በፊት ያች እያለፉትት ያለችው ከተማ ከመቅፅበት ከእይታዎት ተሰውራ በድጋሚ ከማያልቀው ገጠር ተቀላቅለዋል፡ እንግዲህ መበርታት ነው፡፡
ፍጡራን በዓለም ሲኖሩ መሰላቸውን ፈልገው እና ተፈቃቅደው አንድ ላይ መኖራቸው ሀቅ ነው፡፡ ሰው ልጅ ባህሪም ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች ይሄን ቁርኝት እና አብሮ መኖር አጠናክረው እና የበለጠ አጥብቀው በአንድ አብረው ይኖሩበታል፡፡ ከተሞችም የዚህ ግንኑነት ቀጥተኛ ውጤቶች ናቸው፡፡ በግንኙነቱ የሚፈጠሩት ከተሞች ሲመሰረቱ እና ሲወድሙ እንደገና ሲመሰረቱ፤ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ የሚበልጠው በከተማ እንደሚኖር አወጀ፡፡ ከተሜው ዓለምን ከገጠሬው ተረከበ፡፡
ከተሜ (Urbanism)
የዓለም እድገት እየጨመረ በመጣ ቁጥር በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ቁጥርም እየጨመረ እንደሚመጣ፤ መረጃዎቹን ተመልክቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይሄም ከተሜነትን ከእድገት ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ ማስረጃ ነው፡፡ ብዙ የከተማ ነዋሪ በተፈጠረ ቁጥር የዛች ሀገር እድገት በተሻለ መስመር ላይ ነው እንደማለት፡፡ Bert Hoselitz, የተባሉ ምሁር 'The Role of Cities in the Economic Growth of Underdeveloped Countries' ባሉት መፅሃፋቸው:
“Cities are sources of innovation, loci of and providers of motivation for change, and centers where a peasant may go to remove himself from the constricting political organization and static economy of the countryside.”
ይላሉ፡፡ ከተሞች የሀሳብ መፍለቂያ፣ የፈጠራ መመንጫ እንደሆኑ እና ለገጠሬውም ገጠር ከተሰኝው ‹እስር ቤ›ት ወጥቶ ወደ ‹ነፃነት ምድር› የሚገባበት በር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ይሄም ስልጣኔ ከከተማ እንጅ ከገጠር አትቀዳም የሚለውን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ ከተሜ ሰፊውን ዓለም በማወቁ ተጠቃሚነቱ ይጎላል፤ ዓለምንም ለመከተል ያተጋዋል፡፡
ገጠሬ
በሌላ በኩል ዓለምን ለረጅም ዘመናት ነግሶባት የኖረው የገጠሬነት ይትበሃል ነበር፡፡ በገጠሬ ባህል ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የተበተነ አኗኗር፣ ለለውጥ ድንጉጥ መሆን (Change Resistant)፣ የንፅረተ አለም (World Outlook) መጥበብ ዋነኛዎቹ እንደሆኑ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ የኑው መበተንም ሀሳብ በጋራ እንዳይብላላ እና የሀሳብ ፍጭቶች (Thesis Vs. Antithesis) አዲስ ሀሳብ (Synthesis) እንዳይፈጥሩ ያግዳቸዋል፡፡ ለውጥን መፍራቱ ደግሞ በትናንት በሬ ለማረስ መሻትን፣ ዛሬን መርሳትን እንዲሁም ለነገ ባዕድ መሆንን ይፈጥርበታል ለገጠሬው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የገጠሬው ዓለም ከአራቱ ጋራዎች አለመዝለሉ የታፈነ እና ሌላውን ዓለም የማያውቅ፤ ራሱንም ከሌላው ዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማያዋህድ ‹ደሴት› ያደርገዋል፡፡ አዎ ሕይወት በገጠር በባህር ተከበበች ደሴት ላይ ያለች ሚጢጢ ነገር ነች፡፡ ይህ ማለት ግን ገጠሬ ሁለ-ጭፍን እና በግምት የሚኖር ነው ለማለት አይደለም፡፡
ገጠሬው ከተማን ሲሻ
በተለያዩ መንገዶች ገጠሬው ወደ ከተማ መግባቱ አይቀርም፡፡ የስበት ሀይሉ (Center of Gravity) ከተማ ነውና ገጠሬው በከተማ ሀሳብ ይሳባል፤ ከተማም ይገባል፤ ራሱንም በከተሜ ሀሳብ ለመቅረፅ ይጥራል ከተሜም ይሆናል፡፡ ገጠሬው ከተሜ ሲሆን ምን ይፈጠራል? ስንል May Diaz and Jack Potter የተባሉ ፀሃፍት 'Introduction: The Social Life of Peasants', in Peasant Society ባሉት መፅሃፋቸው ላይ ‹‹የመንግስት ቁጥጥር ይበጣጠስል፤ መንደሩ ግን ይኖራል›› - “The state apparatus could disappear overnight and an individual village could still manage to survive” ይሉናል፡፡ ይህም ማለት ገጠሬው በከተማ መሻቱ ‹ግለሰቡን ሰው› ከትቢያ ፈልጎ የማውጣትን መላ ይማራል፤ ዓለምን ያውቃል፤ እንደገናም ዓለምን ያሰፋል፡፡
ገጠር እና ከተማ በኢትዮጵያ
የከተማ አመሰራረት እና እድገት በቀዳሚዎቹ ዘመናት በኢትዮጵያም የተለየ ታሪክ አልነበረውም፡፡ ከአክሱም ስልጣኔ መክሰም በኋላ በሀገሪቱ ከተማ የሚባለው ፅንሰ ሀሳብ ጨርሶ ጠፍቶ ነበር፤ የነገስታቱ ግዛትም እጅግ የጠበበ እና ከመንደር ያልዘለለ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ በጦርነትም የነገስታቱ መቀመጫ የሆኑትን ‹ዓምባዎች› ሰብሮ የገባ ሀይል ስልጣኑን ለመያዝ ይቀልለት ነበር፤ ድሉንም ዓምባዎቹን ሙሉ ለሙሉ በማውደም ይገልፅ ነበር፡፡ ይሄም ዓምባዎቹ ጎልብተው ወደከተማነት የሚሸጋገሩበትን እድል በእጅጉ አቀጭጮታል፡፡ በነገስታቱ ወንዝን እና ተራራን መሰረት በማድረግ የሚመሰረቱት የመናገሻ ‹ከተማዎችም› ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ እና እዚህ ግባ ሊባሉ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ በዚህም ምክንያት ከተማና ከተሜነት ያልነበረ፤ ብቅ ሲልም በነገስታቱ ግብግብ ‹‹ጨርሶ አጠፋ› በሚባል ሁኔታ አመድ ሲሆኑ ነበር፡፡ ለዚህም ነው “During the past millennium in Ethiopia, the state and not the city has been 'the decisive criterion of civilization” ሲሉ Eric Wolf የሚናገሩት፡፡
ይሄም ማለት ኢትዮጵያዊያን በገጠር መኖራቸው፤ በከተማ የሚገኝውን ጥቅም ከማጣታቸውም በተጨማሪ የመንግስት ‹ሎሌ› ሁነው ኖረዋል እንደማለት ነው፡፡ መንግስት ‹ነጭ-ኑግ፤ጥቁር ወተት; ውለድ እያለ ‹እርፍ አሸክሞ-ጅራፍ አንግቶ› ኢትዮጵያን ሲሰራና ሲያፈርስ ነበር እንደማለት፡፡
ከፊውዳሉ ወደ ላብ አደሩ ወደ አርሶ አደሩ
በፊውዳላዊ ስርዓቱ ወቅት ገጠሬው እንደ ገባር ለመኳንንቱ ተደልድሎ በጉልበቱ እና በላቡ የመሳፍንቱ ሎሌ ሆኖ ኖረ፡፡ ለምን እረገጣለሁ? ከማለት ይልቅ ‹ግብር በዛብኝ› የሚሉ ትንሽ አመፆችን በየቦታው አስነስቶ ከሸፈ፡፡ ሙሉ የመብት ጥበቃ ይደረግልኝ ሊል አልቻለም፤ ገጠሬ ነውና፡፡ ይልቁንስ ተማሪዎች ‹መሬት ለአራሹ፣ ለላብ አፍሳሹ› ብለው የገጠሬው መብት ይጠበቅ ዘንድ ተነሱ እናም ፊውዳላዊውን ስርዓት ገረሰሱት፤ በላባደሩ የሚመራ ከተማ-ተከል አብዮትም ታወጀ፤ ወታደሩ በመሃል ገብቶ ነገሩን ሁሉ አፈረሰው፤ ህልሙን አደፈረሰው፤ ለስሙ ግን እኔም ለላባደሩ ነኝ ብሎ ገጠሬውን ገሸሽ ያደረገ ስርዓትም ዘረጋ፡፡ገጠሬውን ለማዘመን ወታደራዊው መንግስት በሰፈራ ፕሮግራሙ አማካኝነት ትናንሽ አዳጊ መንደሮችን ለመፍጠር ሙከራ አደረገ - አልተሳካም፡፡ ነገር ግን የገጠሬው ቁጥር በፊውዳሉ ስርዓት ጊዜ ከነበረው በትንሹ ሊቀነስ ችሎ ነበር፡፡
በወታደራዊው መንግስት የተተካው በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢሕአዴግ) አርሶ/አርብቶ-አደሩን በሌላ ቋንቋ ገጠሬውን መሰረት ያደረገ ዲሞክራሲያዊት እና የበለፀገች ኢትዮጵያን እፈጥራለሁ በማለት ግብርና መር የኢንደስትሪ ስትራቴጂን ነደፈ፤ ስንቶች የከተማ ትግል ብለው እንደወጡ ሲቀሩ እኔ አርሶ አደሩ ዛፍ ፍሬ አፈራሁ አለ፡፡ ገጠሬውም ሀገሪቱን በአጠቃላይ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን በተለይ ለመምራት በትረ - ሙሴውን ጨበጠ፡፡
ገጠሬው ይመራልን?
ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ገደማ (በ1959 ዓ.ም) በማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን በወጣው መረጃ መሰረት የዛሬዋን ኤርትራ ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ 248 ከተሞች የነበሩ ሲሆን የከተማው ሕዝብ ብዛትም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ 8 በመቶውን ብቻ ይይዝ ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም በወጣው የማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ መሰረት ደግሞ ደግሞ በመላ ሀገሪቱ 973 ከተሞች ያሉ ሲሆን ከአጠቃላይ ሕዝቡም 17 በመቶ የሚሆነው በነዚህ ከተሞች ውስጥ ይኖራል፡፡ ይህም ማለት ቀሪው 83 በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም ገጠሬ ነው ማለት ነው፡፡
ኢሕአዴግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ከነበረው 86 በመቶ የገጠር ነዋሪ በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በ3 በመቶ ብቻ ነው የተቀነሰው፡፡ በአብዛኛው የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ገጠሬዎች በአሁኑ ወቅት ድህረ-ገጠሬ (Post-Peasant)፤ ማለትም ከከተማ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት የሚፈጥሩ ነዋሪዎች ደረጃ ላይ እንደ ደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሄም ማለት በቀጣይ ወደ ከተሜነት ራሳቸውን ለመቀየር አንድ እርምጃ ወደፊት ሂደዋል ማለት ነው፡፡ መንግስት የኢትዮጵያ ገጠሬ ይሄን ደረጃ መውጣት ጀምሯል ቢልም፤ በ20 ዓመታት ከታየው የከተሜነት ጉዞ አንፃር ተመልክተው ‹አይ አይመስለንም› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
Frederick Gamst ስለ ኢትዮጵያ የከተማ-ገጠር ተወስኦ ሲያወሱ:
“Lack of urbanism is found to be hindering the rate of modernization in Ethiopia where nonliterate [sic] people are still gradually making the transition into peasants.” በማለት ነው፡፡ የከተሜነት አለማደግ ኢትዮጵያን ከዘመናዊነት ጉዞዋ አቅቧታል፤ ያልተማረው ሕብረተሰብም ገጠሬ እየሆነ ነው እያሉ ነው፡፡
መንግስት በበኩሉ በተደጋጋሚ እንደሚገልፀው ‹መሰረቴ፤ ሰፊው አርሶ አደር ነው› ይላል፡፡ ‹የዲሞክራሲ ተቋማትን እና የልማት አውታሮችን የምዘረጋው ይሄን አርሶአደር መሰረት አድርጌ ነውም› ይላል፡፡ በአወዛጋቢ የምርጫ ወቅት እንኳን ‹አመኔታ በገጠሬው ላይ ነው› ይላል፡፡ ነገር ግን ገጠሬነት ለሀገር እድገት ‹እዳ› ነው ይሉታል ምሁራን በበኩላቸው፡፡ ‹‹የተበተነ፣ ለውጥ-ጠል እና ዓለመ-ጠባቡን ገጠሬ እንደ መከታ መያዝ አይገባም፤ ይልቁንም ገጠሬውን አዘምኖ ከተሜ ማድረግ ነው ድሉ›› ይላሉ እነዚህ አካላት፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው Frederick Gamst ‘Peasantries and Elites without Urbanism: The Civilization of Ethiopia’ ባሉት ፅሁፋቸው ላይ የከተሜነት አለማደግን ጠቅሰው የሚያቀርቡትን ሂስ እንደገና እንጥቀስ፡
“Lack of urbanism prevents in Ethiopia the beginnings of a concentration of a pool of laborers who are without bonds to the land. Such a labor pool is necessary for industrialization, and thus for the ensuing general modernization of all of the ways of life in Ethiopia. Lack of urbanism will […] insulate Ethiopia and its peasants from fundamental changes in traditional ways of life.”
መንግስት እንደሚለው ጉዟችን ወደ ኢንደስትሪ ከሆነ መግስት በፍቅር የወደቀለት ገጠሬው ትልቅ መሰናክል ነው ማለት ነው፡፡ መንግስት በአንድ በኩል የኢንደስትሪ ልማትን (Industrialization) አመጣለሁ ብሎ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹ገጠሬውን አትንኩብኝ› እያለ መንታ መንገድ ላይ ቆሞል፤ አንድ እግሩን በግራ፣ አንድ እግሩን በቀኝ በኩልም እየለጠጠ ይገኛል፡፡ መጨረሻውስ? የለውጥ ፈር ቀዳጁን ከተሜስ መች ይቀርበዋል? መቸስ ገጠሬውን ከተሜ ያደርገዋል? ነው ጥያቄው፡፡