Monday, April 25, 2016

ኒምኦ እና ሂንዲያ



በማህሌት ፋንታሁን

በመጀመሪያ ጣውላ ቤት
 
ከታሰርኩበት ሚያዚያ 17/2006 አመሻሽ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሰማኒያ አራት ቀናት “የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ” (ማዕከላዊ) እኖርበት የነበረው ክፍል በተለምዶ ጣውላ ቤት ይባል ነበር። አምስት ክፍሎች አሉት። በፊት እነዚህ ክፍሎች የወንዶች እስረኞች ነበሩ። እኔ ከመግባቴ ከአራት ወር በፊት  እዛው አካባቢ የምትገኝ አንዲት ክፍል ውስጥ ነበር ሴት እስረኞች የሚኖሩት። ወይም ብቻቸውን እንዲሆኑ የሚፈለጉ ሴት እስረኞች ከአምስቱ በአንዱ ክፍል ለብቻቸው እንዲኖሩ ይደረጋሉ። ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ማዕከላዊ የቆየችባቸውን ጌዜ በሙሉ ከአምስቱ ክፍሎች  በአንዱ ብቻዋን ነበር የምትኖረው። ሴቶቹ የሚኖሩባት ክፍል ለእስረኞቹ  እየጠበበቻቸው ስትመጣ እዛ መኖራቸው ቀርቶ አምስቱ ክፍሎች ያሉበትን (ጣውላ ቤት) ሁለቱ (1 እና 2 ቁጥር) ተለይቶ በረንዳው ላይ በቆርቆሮ ተጋርዶ ፤ እንደታሳሪው ብዛት ሶስቱ ክፍል ላይ ሴቶች፤ ሁለቱ ላይ ወንዶች ወይም ሁለቱ ላይ ሴቶች ሶስቱ ላይ ወንዶች ይኖሩበታል። ጣውላ ቤት የሚኖሩ ወንድ እስረኞች በብዛት የመርማሪዎች ድብደባን መቋቋም ሲያቅታቸው በሌሎች እስረኞች ላይ (በተመሳሳይ የሽብርተንነት ወንጀል ተጠርጥረው ለታሰሩ) ለመመስከር በግዳጅ የፈረሙ ናቸው። አልፎ አልፎ አስም እና ተዛማጅ ህመሞች የሚጠቁ በሽብርተንነት የተጠረጠሩ እስረኞች ጣውላ ቤት እንዲኖሩ ይደረጋል። በአማካኝ 3 ሜትር በ4 ሜቴር ስፋት ያለው ሲሆን በመደበኛ ጊዜ ከ4 እስከ 20 እስረኞች ይኖሩበታል። 


ጣውላ ቤት ብዙ ነገር ለማየት እና ለማስተዋል አማካኝ ቦታ ነው። ከጣውላ ቤት ላይ ያለው ፎቅ ‘መመርመሪያ’ (መደብደቢያ) ክፍሎች ናቸው።  ከእያንዳንዱ ጣውላ ቤት አናት የየትኛው ‘መርማሪ’ ክፍል መሆኑን ለማወቅ ከሳምንት በላይ አይጠይቅም። መርማሪዎች ለመመርመር እያሉ በማታ እና በለሊት ጠርተውን ሊያሰቃዩን ከክፍላችን ከመወሰዳችን በፊት ክፍላችን ሆነን በኮቴያቸው እናውቃለን። አብዛኛውን ቀናት (በብዛት ከእሁድ በስተቀር) ጣሪያችን በኮቴያቸው እንደተሸበረች ነው። የጣሪያችን መሸበር እኛንም ጭንቀት ለቆብን  እንቅልፍ ይነሳናል። መርማሪዎች ከፎቁ (ወለሉ እና ደረጃው ጣውላ ነው) ሲወርዱ እና ሲወጡ ይሰማል ። በመርማሪዎች እስረኛ እንዲያመጡ የሚላኩ ፓሊሶች ኮቴ እና ከእጃቸው የማይለየው ካቴና ድምፅም ሌላው የስቃያችን ምንጭ ነው። 

ጨለማ ቤትና እና የሳይቤሪያ ክፍሎች እስረኞች ከጣውላ ቤት ፊት ለፊት ባለች መንገድ ነው ወደ ‘ምርመራ’ ክፍል የሚሔዱት እና የሚመለሱት፡፡ በቀን የምትፈቀድላቸውን የ10ቸደቂቃ ፀሃይ የሚሞቁትም መተላለፊያ መንገዱን ሸገር ብሎ ያለች በጣም አነስተኛ ሜዳ ላይ ነው። ይህች ሜዳም ጣውላ ቤት ለሚኖር እስረኛ ፊት ለፊት ናት። የጣውላ ቤት ነዋሪዎችም ተራችን ሲደርስ ፀሃይ የምንሞቀው እዛችው ሜዳ ላይ ነው። ከሜዳዋ አለፍ ብሎ ደግሞ ብቸኛዋ ክሊኒክ እና የጣውላ ቤት ነዋሪዎች ሽንት ቤት ይገኛል። ከክሊኒኩ ጎን ደግሞ በየሶስት ሰዓቱ እየተቀያየሩ ለ24 ሰዓት እኛን (የጣውላ ቤት እስረኞችን) የሚቆጣጠሩ ‘ዋርድያዎች’ ማማ አለ።

ስለሆነም በጨለማ እና በሳይቤሪያ የሚኖሩ እስረኞች ለምርመራ፣ ፀሃይ ለመሞቅ እና ለህክምና ሲወጡ እና ሲመለሱ እናያለን። በእያንዳንዱ የሳይቤሪያ እና ጨለማ ቤት የሚኖሩትን እስረኞች መለየት ጊዜ አይፈጅም። ምክንያቱም ፀሃይ ሲወጡ በየክፍላቸው እና በየተራ ስለሆነ ከጊዜ ብዛት እንለምዳቸዋለን። ከክፍሉ ልጆች ጋር ፀሃይ ለመሞቅ ያልወጣን እስረኛ እንለይና እንጨነቃለን። ወይ በድብደባ ብዛት መውጣት ሳይችል ቀርቶ ነው ወይ ‘ምርመራ’ ሄዶ ነው። አንድ እስረኛ ብቻውን ከሚጠብቀው ፓሊስ ጋር ፀሃይ ለመሞቅ ወጣ ማለት ጨለማ ቤት ነው የታሰረው ማለት ነው ወይም ሌሎች በክፍሉ የሚኖሩት ሁሉ ታመው ከክፍላቸው መውጣት አልቻሉም ወይም ደግሞ ‘ምርመራ’ ሄደዋል ማለት ነው። 

ከ11 እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ  ክፍሎቻችን ከተቆለፉ በኋላ በበራችን ቀዳዳ ወደ ምርመራ ክፍል የሚያልፉትን እና የሚመለሱትን እናያለን። አንዳንድ ጊዜ በቀንም በራችን የሚዘጋበት አጋጣሚ አለ። ይህ የሚሆነው ‘ዋርድያው’ ክፉ ሲሆን እና አጋጣሚ በር ላይ ቆመን ከታየን እንዲሁም ከክሊኒክ/’ምርመራ’ ቦታ ከውጪ አዲስ እስረኛ ወደ ሳይቤሪያ ወይም ጨለማ ክፍል ለማስገባት ሲፈለግ እና የእስረኛውን ማንነት/የደረሰበትን አደጋ እንዳናይ ለማድረግ ሲታሰብ ነው። ሆኖም ግን እኛ በቀዳዳ ማየታችን አይቀርም። በወቅቱ በር ተዘግቶብን ሳለ በቃሬዛ ተይዘው ወደ ሳይቤሪያ እና ጨለማ ቤት ሲወሰዱ ያየናቸው እስረኞች ነበሩ፡፡ በተረፈ ግን ምርመራ ሲሄዱ ጤነኛ ሆነው ሄደው ሲመለሱ እያነከሱ፣ እየተንፏቀቁ፣ ቆስለው እና በድጋፍ ወደ ክፍላቸው ሲሄዱ ማየት የለት ተለት የሚያም ትዕይንት ነው።
 
እኔ በገባሁበት ወቅት ከሴት እስረኞች ‘ምርመራ’ የሚበዛብን እኔና ጋዜጠኛ ኤዶም ብቻ ነበርን። ሌሎቹ ከአንድ ቀን በላይ የሚጠሩበት አጋጣሚ ጥቂት ነው። በተለይ በር ከተቆለፈ በኋላ በማታ እና ሌሊት የምንጠራው እኛ ብቻ ነበርን። በሌሊት እና በማታ በምንወጣበት ጊዜ ካጠገብ ያሉ ክፍሎች ያሉ እስረኞች በበር ቀዳዳ ያዩን ነበር። ስንወጣና ስንመለስም የሚያዋስነንን ግድግዳ ሲያንኳኩ ስለኛ መጨነቃቸውን እና ማሰባቸው ይገባን ነበር። ነግቶ ሲያዩንም "አይዟችሁ!" "በርቱ!" "ዱላው እና ማሰቃየታቸው ቢበዛም ቻሉት። ያላደረጋችሁትን ነገር አረግን ብላችሁ አንዳታምኑ!" እና የመሳሰሉ ማበረታቻ ቃሎችን በምልክት እና በአፍ እንቅስቃሴ ያስተላልፉልን ነበር። በተለይ ጣውላ ቤት ያሉ ወንዶች ይህን አይነት ምክር መምከራቸው የገረመኝ፤ እነሱ ምስክር መሆናቸውን ያወቅኩ ጊዜ ነው። በውሳኔያቸው ተፀፅተው ይሆን? እያልኩም አስባለሁ። 
 
ኒምኦ እና ሂንዲያ

ኒሞን እና ሂንዲያን ያወቅኳቸው ማዕከላዊ መጀመሪያ የገባሁ ቀን ነው። ሚያዚያ 17/2006 ከምሽቱ 1 ሰዓት። ኒሞ እና ሂንዲያ ሶማሌዎች ናቸው። እኔ የገባሁበት ክፍል ከኒሞ እና ከሂንዲያ ውጪ ሰው ወደ ውጪ ሃገር በመላክ ተጠርጥራ ታስራ የነበረች አንዲት ሴት (እኔ ከገባሁ ከሶስት ቀናት በኋላ ተፈታለች) ናት የነበረችው። ባጠቃላይ አራት እስረኞች ነበርን። ከገለፃቸው ኤዶም እዚህ ክፍል ገብታ እንደነበረ እና ከመምጣቴ ከደቂቃዎች በፊት ወደ ሌላኛው የጣውላ ቤት ክፍል መግባቷን ተረዳሁ። የተረበሸ ሁኔታ ውስጥ  ብሆንም የተረጋጋሁ ለመምሰል በጣም እጥር ነበር። በፍተሻ ወቅት እቤት ባለመኖራቸው ሳላገኛቸው የመጣሁት  እህት እና ወንድሜ መታሰሬን እንዴት እንደሚሰሙ? ሲሰሙስ እንዴት እንደሚሆኑ?  መታሰሬ ዜና ዱብ እዳ ለሚሆንባቸው ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ይህችን ምሽት እንዴት እንደምትነጋላቸው? ሌሎቹ የዞን 9 ጓደኞቼስ ታስረው ይሆን? አዳሬስ እንዴት ይሆን ይሆን? ይህን እና የመሳሰሉትን ሃሳቦች በጭንቅላቴ መመላለስ አላቆሙም። ይህን እያሰብኩ አንድ የሰፈሬ ልጅ ጣቢያ ታስሮ የመጀመሪያ ቀን ያጋጠመው ነገር ያጋጥመኝ ይሆን እያልኩ አስባለሁ። የሻማ ብር እንዲያዋጣ ብር ከሌለው ደግሞ የታዘዘውን ያክል ጊዜ ዘፈን እየዘፈኑ በክፍሉ ያሉ እስረኞችን እንዲያዝናና አማራጭ ተሰጥቶት በወቅቱ ብር ስላልነበረው ለመዝፈን እንደተገደደ አጫውቶኝ ነበር። የሻማ ያለኝም፣ ዝፈኝ  ያለኝም አልነበረም። ምክንያቱም ይህ የማሰቃያ ማዕከል የሆነው ማዕከላዊ ነው። ቀልድና ጨዋታ የሚታወስበት ጊዜ የለም። በገባኁበት ቀን የክፍሌ ልጆች እራት በልተው ጨርሰው ነበር። ሶማሌዎቹ ጥቂት እንደቆየሁ ምግብ እንድበላ እነሱ ካስቀሩት ሩዝ በስጋ አቀረቡልኝ እና ጥቂት ቀማመስኩ። ከሁለቱ ውጪ ያለችው ሴትዮ ተኝታለች። ከሁለቱ ሶማሌዎች ጋር ሳንተኛ ካርታ እየተጫወትን ቆየን። በመሃል ከላያችን ያለው ‘ምርመራ’ ክፍል እና ኮሪደሩ በኮቴ ሲናወጥ ሃሳባችንን ሰረቀው ። እነሱ በጣም የሃዘን እና የጭንቀት ፊት ይታይባቸው ነበር። እኔ አልገባኝም። ጠየኳቸው። "አይ ምንም አይደል"  አይነት ምላሽ ሰጡኝ። እኔ እንዳልጨናነቅ መሆኑ ገብቶኛል። የኔው ጓደኞች ወደ ‘መርማሪዎች’ ቢሮ ሲገቡ ነው ብዬ አሰብኩ። እኔም ጊዜዬን እንደምጠብቅ ጠርጥሬ ልጠራ እችል እንደሆነ ስጠይቃቸው "አይ ዛሬ አትጠሪም" አሉኝ። ይህም እኔን ለማረጋጋት ነው እንጂ የእውነት የሚሆን አልመሰለኝም ነበር። የምቀይረው የሌሊት ልብስ ሲሰጡኝ ‘መርማሪዎች’ ሲጠሩኝ በፒጃማ ከምወጣ ብዬ በዋልኩበት ልብስ ማደሩን መረጥኩ ። ከዛ በኋላ ባሉት ቀናትም በተመሳሳይ ምክንያት የሌሊት ልብስ አልብስም ነበር። ዱላውን፣ ቁጣውን እና ዛቻውን ለመቻል የቀን ልብስ ይሻላል። ይህን ምክንያቴን ስነግራቸው “ፓሊስ መጣ ነው። ነይ ነው። ቆይ ልብስ ቀይር ነው። ውጪ በር ቁም ነው። ቀይር ነው። ውጣ ነው።” ትለኛለች ሂንዲያ በሚቸግራት አማርኛ። ‘’ትወጫለሽ ፓሊስ ቢመጣም ልብስ ልቀይር ብለሽ ውጪ በር ላይ ይቆም እና ቀይረሽ መውጣት ትችያለሽ’’ ማለቷ ነው። እኔ ግን ‘ፓሊሶቹ ልብስ የመቀየሪያ ጊዜ ባይሰጡኝስ?’ ብዬ ‘ሪስኩን’ ላለመውሰድ ምክሯን ተግባራዊ አላደረኩትም ነበር። በተጨማሪም  በጃኬት እና ወፍራም ሻርፕ ተጀቧቡኜ ነበር የምወጣው ለምርመራ ስጠራ ። 

እነ ሂንዲያ ከታሰሩ 7ወር ሊሆናቸው እንደሆነ ያረዱኝ የዛኑ እለት ምሽት ነበር። በ2006 ጥቅምት ወር ላይ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አዲስ አበባ ስታዲየም በሚጫወቱበት ወቅት እና በሌሎች ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ከሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች ጋር  ቦንብ ሊያፈነዱ  ነበር ተብለው ተጠርጥረው በግብረ አበርነት ከተያዙት  ውስጥ ናቸው ኒሞ እና ሂንዲያ። ሂንዲያ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ "አጥፍቶ ጠፊዎቹ" ቦንቡ በድንገት ከፈነዳባቸው መኖሪያ ቤታቸው በፊት ተከራይተው ይኖሩበት የነበረው ቤት ጎረቤት ነበረች። ኒሞ  ደግሞ ቦምቡ ከፈነዳበት ግቢ ተከራይታ ትኖር ነበር። ኒሞ ማእከላዊ ስትመጣ እራሷን እንደማታውቅ እና በፍንዳታውም የግድግዳ ፍርስራሽ ወድቆባት ቆሳስላ እንደነበር አጫውታኛለች። ሁለቱም ከፈነዳው ቦንብ ጋር በተያያዘ የሚያቁት ነገር እንዳለ ተብለው ብዙ ድብደባ ደርሶባቸዋል። በሂንዲያ የደረሰው በጣም የከፋ ነው። ለብዙ ጊዜ ጀርባዋን በኤሌክትሪክ ገመድ ስለምትገረፍ ቁስሏን ይጠራርጉላት እንደነበር እና ለሽንት ቤትም ሆነ መንቀሳቀስ ስትፈልግ በሰው እርዳታ እንደነበረ ከሌሎች ሴት እስረኞች ሰምቻለሁ። እኔ ስገባ 7ኛ ወራቸውን ቢያስቆጥሩም የሂንዲያ ጀርባ ገመዱ ያረፈባቸው ቦታዎች ጠባሳ በጉልህ ይታያል። ይህን ሁላ ጉድ ችለው አዲስ መጪውን ሲቀበሉ ክስ ተመስርቶበት ቃሊቲ የሚገባውን እና የሚፈታውን ሲሸኙ አንጀት ይበላሉ። ‘ግብረ አበር’ እና ‘ተሳታፊ ናችሁ’ ተብለው ለተወነጀሉበት ክስ ምስክር እንዲሆኑ ተብሎ ነው በእስር ክስ ሳይመሰረትባቸው ብዙ ጊዜ የቆዩት። 

ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ለሽብር ተግባር ሊያውሉት አቅደው እዛው ቤታቸው ውስጥ ቦንቡ ፈንድቶ ህይወታቸው ካለፈ አጥፍቶ አጥፊዎች ጋር ግብረ አበር በመሆን ክስ ለተመሰረተባቸው እነ ሙሐመድ አብዱራህማን ሙሐመድ (8 በዜግነት ኢትዮጵያዊ እና ሶማሊያዊ የሆኑ ግለሰቦችና ሁለት ኢትዮጵያውያን ቤት አከራዮች) ለአቃቤ ህግ እንዲመሰክሩ ተብለው ነው ኒምኦ እና ሂንዲያ ያላአግባብ በእስር የተቀመጡት።

(በነገራችን ላይ እነ ሙሐመድ አብዱራህማን ሙሐመድ ከታሰሩ ሁለት አመት ከስድስት ወር ቢያልፋቸውም አሁን ድረስ አቃቤ ህግ ‘የጠፉ ምስክሮችን ልፈልግ’ በሚል ምክንያት ምስክሮቹን አሰምቶ አልጨረሰም።)  

ማዕከላዊ በገባሁ ከሳምንት በኋላ ሂንዲያ ከጎናችን የነበረ ሌላ የሴቶች ክፍል ተቀይራ ሄደች። ከኒምኦ ጋር ደግሞ ኤዶም እኔ ያለሁበት ክፍል መጥታ እሷን ኤዶም የነበረችበት ክፍል እስኪወስዷት ለ20 ቀናት ያክል አብረን ነበርንን። ከዛ በኋላ ግንኙነታችን ለሽንት እና ለፀሃይ ስንወጣ ስንተያይ (እኛ ክፍላችን እነሱ ለሽንት እና ለፀሃይ ሲወጡ ወይም በተቃራኒው) በርቀት በምንለዋወጠው ሰላምታ ተገደበ። ኒምኦ ሌላ ክፍል ስትሄድ ምንጣፏን ሰጥታኝ ነው የወጣችው። ከኔ  የበለጠ ምንጣፉ ለሷ እንደሚጠቅም ስለማውቅ (‘ሶላት’ ለማድረግ) እንድትወስደው ብጠይቃትም፤ ልትሰማኝ ፈቃደኛ ባለመሆን እያለቀሰች ወደ አዲሱ ክፍሏ ሄደች። ‘’ቀድመሽኝ ከወጣች ትሰጪኛለሽ’’ አለችኝ ። ከሶስት ወራት በኋላም ተከሰን ወደ ቃሊቲ ስንወርድ ምንጣፉን ይዘነው እንድንሄድ ሰጠችን። 

እኛ ከማዕከላዊ ቆይታ በኋላ ተመስርቶብን ቃሊቲ ስንወርድ ኒሞና ሂንዲያ እዛው ነበሩ። አስር ወር ሞላቸው ማለት ነው። ቃሊቲ ከወረድን ከሁለት ወር በኋላ ይሆናል መለቀቃቸውን የሰማነው። ያለምክንያት ለአንድ ዓመት ያህል በማዕከላዊ ስቃይ በተሞላው እስር ቆይተው እንደዋዛ ተለቀቁ ማለት ነው። በታሰሩበት ወቅት ኒምኦ አዲስ አበባ በሚገኝ የጤና ኮሌጅ በነርሲንግ የትምህርት ዘርፍ ተማሪ የነበረች ሲሆን፤ ሂንዲያ ደግሞ ትዳር መስርታ የምትኖር የአንድ ልጅ እናት ናት። የኢትዮጵያ መንግስት ባደረሰባቸው በደል በጣም ተማረው፤ በኢትዮጵያ የመኖር ጉዳይ ተስፋ አስቆርጧቸዋል። ሶማሌ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ (ሶማሊ ኢትዮጵያውያን) በማንኛውም አጋጣሚ ለእስር ሊዳረጉ እንደሚችሉ እርግጠኞች ናቸው። አብረን በነበርንበት ወቅት ኒምኦ ከዚህ በኋላ አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር በኢትዮጵያ አቋርጣ (በትራንዚት) ወደ ሌላ ሃገር ለማለፍ ደህንነት ሊሰማት እንደማይችል ነግራኛለች።
  
ኒምኦ የሰጠችንን ምንጣፍ በተፈታንበት ወቅት ቃሊቲ ለተተኪ አስረክበን ወጣን። ኒምኦ እና ሂንዲያ ማዕከላዊ በነበሩበት አንድ ዓመት ለገቡ እስረኞች መፅናኛ እና መካሪ ነበሩ። አድራሻቸውን ሳልይዝ በመውጣቴ እና አሁን ላገኛቸው አለመቻሌ ያሳዝነኛል።

No comments:

Post a Comment