Sunday, November 1, 2015

የተዘለለው ምዕራፍ

 በበፍቃዱ ዘ ኃይሉ
የሰለሞን ስዩምን ‹‹የኦሮሞ ጉዳይ እና የኢትዮጵያ ብያኔ›› የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ (ሁለተኛ እትም) አነበብኩት፡፡ በጥቅሉ ወድጄዋለሁ፡፡ ጥቂት ቅሬታዎች ግን አሉኝ፡፡ ሰለሞን በአማርኛ የኦሮሞ ጉዳይን ከጻፉ (እና እኔ ካነበብኩላቸው) ጸሐፍት ሁሉ በተሻለ ልለው በምደፍረው ደረጃ ምሁራዊ ታማኝነት (intellectual honesty) ተስተውሎበታል፡፡ አልፎ፣ አልፎ ግን ምሁራዊ ታማኝነቱ ከሚጎድላቸው ምሁራን ማጣቀሱ ሚዛን አስቶ ያንገዳገደው ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የታቦር ዋሚ ‹‹የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች››ን ማንሳት ይቻላል፡፡ ታቦር ትልቅ ርዕስ ይዞ ትንንሽ ክርክር የተከራከረባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አንዱ የቋንቋ ተናጋሪዎች ብዛትን በተመለከተ የሚሰጠው ምንጭ አልባ ድምዳሜ ነው፡፡ ሰለሞን ያንን በኦሮሞ ጉዳይ ላይ ያንፀባርቀዋል፡፡ ‹‹. . . መረጃዎች አሉ›› በሚል ብቻ፡፡ በተጨማሪም አጠራጣሪ (አከራካሪ) ሁኔታዎች ላይ እምነቱን ለዘውግ ብሄርተኞቹ ትርክት ወደመስጠቱ አዘንብሎብኛል፡፡

ይህ በእንዲህ አያለ፣ መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ የጎደለ ነገር ያለ-ያለ ተሰማኝ፡፡ ታዲያ የጎደለ የመሰለኝን ምዕራፍ ለምን አልጽፈውም አልኩና ተነሳሁ፡፡ ጽሑፉን የምጽፈው የሰለሞንን ሐሳብ እየተዋስኩ፣ የኔን እየጨመርኩበት ነው፡፡ እሱም ይጭንብኛል፤ እኔም እጭንበታለሁ፡፡ ስለዚህ ከታች የማሰፍረው ጽሑፍ ላይ ‹እኔ›› እኔ አይደለሁም፡፡ ሰለሞን ስዩም ነው፡፡ እኔ ሁን እንዳልኩት፡፡

የተጣመመው የብሔርተኝነት ቅርንጫፍ
በኢትዮጵያ ቀኝ ዘመሞች አና ግራ ዘመሞች ሁሌም እርስ በርስ እንደተዋቀሱ ነው፡፡ እነዚህ ‹‹ትምክህተኛ ብሔርተኞች ፍፁም አሀዳዊ አገር ለመፍጠር ሊፍጨረጨሩ አገሪቱን ይበታትኗታል፡፡ ሲሉ፣ እነዚያ ‹‹ጠባብ ብሔርተኞች ሁሉንም ነገር በዘውግ ዓይን እያዩ አገሪቱን ሊበጣጥሷት ነው›› ይላሉ፡፡ መጽሐፉ በኦሮሞ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ማተኮር የምፈልገው የዘውግ ብሔርተኞች የሚከሰሱባቸው ችግሮች እና መፍትሔዎች ላይ ነው፡፡

አማራ-ሰግነት (Amhara Phobia)
ኦሮሞ ብሔርተኝነት ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል አንዱ የኦሮሞ-ሰግነት እንደሆነ የሆነ ቦታ ገልጫለሁ፡፡ የአማራ ልሒቃን ያለውን ስርዓት ለማንበር ከመፈለግ ይሁን የኦሮሞ ልሒቃን ወደ ሥልጣን ከመጡ የቀድሞ የአማራ ገዢዎች በአባቶቻችን ላይ አድርሰውታል ለሚሉት በደል ‹ይበቀሉናል› በሚል ፍራቻ ኦሮሞ-ሰግነት ልንለው የምንችለው የኦሮሞ ብሔርተኝነትን የመፍራት ሥነ ልቦና አዳብረዋል፡፡ የይስሃቅ ኒውተን ሦስተኛ ሕግ በዚህም ይፈፀም ዘንድ፣ የአማራ ልሒቃን የአፀፋ ፍራቻ በኦሮሞ ልሒቃንም ዘንድ እየተንፀባረቀ ነው፡፡ ቀኝ እና ግራ ጠርዝ ላይ ቆመው በፍራቻ መተያየታቸው በመሐል ቤት የጠቀመው ሕወሓት መራሹን ቡድን ነው፡፡ የሁለቱንም ወደመሐል መምጣት መፍትሔ የሚያደርገውም አንዱ የዚህ ችግር መኖር ነው፡፡ ነገር ግን የተጣመመው እያልኩ የምጠቅሰው የኦሮሞ ብሔርተኝነት አራማጅ ልሒቃን የፈጠሩት የፖለቲካ ትርክት ከአማራ-ሰግነትም አልፎ ወደ አማራ-ጠልነት እያመዘነ ነው፡፡ የኦሮሞን ብሔራዊ ማንነትን ለመገንባት አስተዋፅፆ አድርጓል ያልኩት ‹የጋራ የመበደል ታሪክ ወለድ ሥነ ልቦና› በልሒቃኑ የተሳለበት መንገድ ‹ከታሪክ እንደምንረዳው ከአማራዎች ጋር መተማመን አንችልም፡፡ ስለዚህ አብረን አንኖርም› ዓይነት መደምደሚያ አዝሎ ነው፡፡ ድምዳሜው በአሜሪካ የባሪያ አሳዳሪ ወይም በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት የተበደሉ ጥቁሮች ከደረሱበትም የከፋ ድምዳሜ ነው፡፡ በጣም አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ የዕኩልነት፣ የፍትሕ እና ርትዕ ተጋድሎ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ ቅጠል እያፈራ የመጣው ቅርንጫፍ ይህንኛው ጠማማ ቅርንጫፍ መሆኑ ነው፡፡

አማርኛ-ሰግነት
የአማራ ጠልነት ጦስ የአማርኛ ቋንቋንም ሰለባው አድርጎታል፡፡ ‹‹ሊንጓፍራንኳ›› (ባሕሩ ዘውዴ(ፕ/ር) እንዳለው) በመሆን የክልል መንግሥትን (ሕዝቦቹን) አንዱን ካንዱ እንዲያግባባ የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋነት ማዕረግ ቢቸረውም፣ የተጣመመው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ቅርንጫፍ አራማጅ ልሒቃን ግን የአማርኛ ትምህርት ክፍለጊዜን እንዳይታደሙ (አቋርጠው እንዲወጡ) ተማሪዎቹን ያነሳሷቸዋል፡፡ የፌደራል ቋንቋው በኦሮሚያ ክልል ከ5ተኛ ክፍል መጀመሩ (ቀድሞ አለመጀመሩ) በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ኦሮሚያን ‹‹ሐሳባቸውን እና አቋማቸውን መግለጽ በማይችሉ፣ ነገር ግን፣ በኮታ ብቻ የሚወከሉ፣ ግዑዝ ፖለቲከኞች ይሞሏታል ማለት ነው›› ያልኩት ላይ ተጨማሪ ችግር አከሉበት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ልሒቃን ይህንን የሚያደርጉት ‹አማርኛን ከኦሮሚያ ክልል ውስጥ በ2020 ለማጥፋት› ካላቸው ምሥጢር መሆን ያልቻለ ምሥጢራዊ ዕቅዳቸው በመነሳት ነው፡፡ ኦሮምኛ ሁለተኛ የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን መሥራት ሌላ፣ አማርኛን ለማጥፋት መሥራት ሌላ፡፡ አንድ ግለሰብ (ወይም ማኅበረሰብ) ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆን ተጠቃሚው ራሱ መሆኑን የዘነጋ አካሄድ ነው፡፡ ክርክሩ ምን ያህል ውኃ እንደሚያነሳ ለአንባቢ በመተው የአማራ ልሒቃንን ከዚህ የተገናኘ ሙግት ላንሳ፡- ‹አማርኛ የፌደራል ቋንቋ በመሆኑ የተጎዳ ካለ ዋነኛው አማራ ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች ያሉ ዜጎች ከአፍ መፍቻቸው ውጪ አማርኛን ሲማሩ፣ የአማራ ክልል ሰዎች ግን ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ አይማሩም፡፡ ይህም የአማራ ልጆችን ሌላ ክልል ተዘዋውሮ የመሥራት ዕድል አጥብቦታል› ይላሉ፡፡

ወደ መነሻችን ስንመለስ፣ አማርኛን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁሉም የበለጠ የበለፀገ እንዲሆን ያደረገው ‹‹ዕድል›› ነው፡፡ (በነገራችን ላይ በኢሕአዴግ ዘመንም የተናጋሪዎቹ ቁጥር በፍጥነት እያደገ ነው፡፡) ባሕሩ ዘውዴ “The Changing Fortunes of the Amharic Language” በሚለው ድርሳኑ ‹‹አማርኛ መበልፀጉን የቀጠለው ታሪካዊ ክስተቶች ቀድሞውኑ እንዲበለፅግ ስላደረጉት ነው›› ይላል፡፡ እውነት ይመስለኛል፡፡ መርጌታ ግሩም ተፈራ የተባለ ፀሐፊ (‹የደብተራ ታሪክ› ነው ካላላችሁብኝ) የአማርኛን ታሪክ ሲያነብር ‹የአክሱም መግባቢያ የነበረው ግዕዝ ነው፡፡ ደብተራዎች አሁንም ድረስ ‹‹ነገረ - ደብተራ›› የሚባል የሚስጥር መግባቢያ በየጊዜው ይፈጥራሉ፡፡ [በከተማ ‹የአራዳ› ወይም ‹የዱርዬ› /እንደሰሚው/ የሚባለው ዓይነት ቋንቋ ማለት ነው፡፡] ኋላ ዮዲት [አስቴር ይሁዲት] ባመፀች ጊዜ፣ አክሱማውያን መኳንንት ሸሽተው ሰሜን ሸዋ አንኮበር ተሸሸጉ፡፡ እዚያም ለሚስጥራዊነት ሲባል መኳንንቱ ‹‹ነገረ-ደብተራን›› ይጠቀሙ ጀመር፡፡ ሌላው ሰፋሪም የመኳንንት ቋንቋ አገኘሁ ብሎ ይናገረው ጀመር፡፡ በዚህ መንገድ የተወለደው አማርኛ ዕድል ቀንቶት ዕድገቱ ተፋጠነ› ይላል፡፡ (ወሬሳው ካሳ፣ 2005፡230 ላይ) የባሕሩ ዘውዴ ድርሳንም አማርኛ የተወለደው በዚሁ የ13ኛው ክ/ዘመን ገደማ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በሌላ በኩል ዶናልድ ሌቨን (ዶ/ር) በሠራው አንድ ጥናቱ ‹አማርኛ የተፈጠረው የኦሮሞ ተወላጆች ግዕዝ ለመናገር ሲሞክሩ ነው› በማለት ያትታል፡፡ የመርጌታ ግሩም ተፈራን ትርክት ማመን ከቻልን ይህ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ዶናልድ ሌቪን የአማርኛ ቋንቋ ቅርፅ (Synatax) የኩሽ ቋንቋዎች ባሕሪ ያለው መሆኑን ጠቅሶ ነው እንዲያ ያለው፡፡ ባሕሩ ዘውዴም ‹‹[አማርኛ] ተገንጥሎ ወጥቷል ተብሎ በጥቅሉ ከሚታመንበት ሴማዊው ግዕዝ ይልቅ ከኩሻዊው ኦሮምኛ ጋር ብዙ የሚጋራው ጠባይ አለው›› ብሎ ጽፏል፡፡

በዚህ ትርክት መሠረት የተጣመመው ብሔርተኝነት ቅርንጫፍ አራማጅ ልሒቃን የሚጠሉት አማርኛ፣ ምናልባትም የኦሮሞ ሕዝብ ራሱ የፈጠረው ወይም በፈጠረው ወቅት አስተዋፅዖ ያደረገለትን ቋንቋ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚያም በላይ ኋላ የአማርኛ ተናጋሪ በመሆናቸው ‹‹አማራ›› የሚል የዘውግ ብሔር ስያሜ የሰጠናቸው ሰዎች የጥንት ዘራቸው ኩሻዊ እና አክሱማዊ (አክሱማውያን /አግኣዚኣዊያን/ ራሳቸው ኩሻውያን ነበሩ የሚባል ትርክት አሁን፣ አሁን እየገነነ ነው) የነበሩ ናቸው ማለት ነው፡፡ ፀቡ ዞሮ፣ ዞሮ ወደ ኋላ መለስ ባልን ቁጥር ከራስ የዘር ግንድ ጋር መሆኑ የተረጋገጠ እውነታ ቢሆንም የዚህን ያህል በቅርብ የሚታይ (Traceable) መሆኑ ግን የራሱ የሆነ የከንቱ ጥላቻ ፖለቲካን አስተዛዛቢ ማጋለጫ ነው፡፡

የአማራ እና የአማርኛ ጥላቻው በጥቅሉ አማራ ብለን በአሁኑ የብሔር ብያኔ መሠረት የምንጠራው ሕዝብ የሚጠቀምበትን ነገር በሙሉ በጋራ አለመጠቀም የጠማማው ቅርንጫፍ አራማጆች የላቲን ፊደሎች* ለኦሮምኛ የተመረጡት እንደ እውነቱ ከአማርኛ-ጠልነት በመነጨ ምክንያት ቢሆንም፣ ኋላ ላይ ለማስተባበል ከተጻፉ ጥናቶች የጥላሁን ጎምታን ጠቅሻለሁ፡፡ እዚያ ላይ ምናልባት አሳማኙ ‹‹ለኦሮሞ ሕዝብ የሥነ-ልቦና ነጻነት ወሳኝ ነው›› የሚለው ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጥረቱ የቴክኒክ ጉድለቶቹን የመቅረፍ ጉዳይ ብቻ ቢሆን ኖሮ የሼክ በክሪን የአፋን የኦሮሞ ፊደል ገበታ ለመጠቀም የተደረገ ጥቂት እንኳን ሙከራ (consideration) እናይ ነበር፡፡ (*በነገራችን ላይ መጽሐፌ ውስጥ የ‹ላቲን ፊደሎች› ምንጭ ነው ብዬ ‹‹የኩሽ ፊደል›› እያልኩ የጠራሁበት ቦታ አለ፡፡ ያንን ያክል ምንጭ ፍለጋ መሄዴ፣ ከሌሎች ሙግቶቼ አንፃር ምን ያክል አመክኖአዊ እንደሚያደርገኝ ራሴን በራሴ ያጠራጥረኛል፡፡ የፊደሉ ምንጭ የኔ ነው ለማለት ያንን ያክል ርቄ መሄዴ ካልቀረ ‹‹ጨቋኝ፣ ተጨቋኝ›› የምላቸውን ዘውጎችንም የሩቅ ምንጭ ቀድቼ ‹የአቤል እና ቃዬል› መጠፋፋት ዓይነት መሆኑን መግለጽ ነበረብኝ፡፡)

በነገራችን ላይ በጥላሁን ጎምታ ጥናት ላይ የተጠቀሰው በግዕዝ ፊደላት ሊቀረፍ አይችልም ከተባሉት ችግሮች አንዱ የሚጠብቁና የሚላሉ ፊደሎችን መለየት አለመቻሉ ነው፡፡ ሲጠብቁ እና ሲላሉ እንዲሁም ሲጎተቱ የተለየ ትርጉም የሚሰጡት የአፋን ኦሮሞ ቃላቶች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ችግሩ አማርኛንም የገጠመው ችግር ነው፡፡ ቁቤን በመጠቀም ይህን ችግር ለመፍታት የተደረገው ሙከራም ራሱን የቻለ ሌላ ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡ በግዕዝ ፊደላት አንድ ገጽ የሚጻፈው ጽሑፍ በቁቤ (ከአናባቢዎቹ መብዛት የተነሳ) ሁለት ገጽ ገደማ ይሆናል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በግዕዝ ሆሄያት ፈንታ ‹‹dha,dhi . . .›› እያልኩ ጽፌያለሁ፡፡ ለምሳሌ ‹ይላማ dheeሬሳ› የሚለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን ድምፅ የሚገልጽ የግዕዝ ሆሄ የሌለ መስሎኝ የተፈጠረ ስህተት ነው እንጂ፣ ምንም እንኳ ድምፁ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ባይኖርም፣ በፊደል ገበታው ላይ ግን አለ፡፡ በነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) ታሪክ ‹ዳንዺ› ላይም ‹ዺ›ን ለመፃፍ ‹ዲ› ከጻፉ በኃላ በእስክርቢቶ አናቷ ላይ ጭረት አድርገውባታል፡፡ ነገር ግን ፊደሉ የኮምፒውተር የፓወር ግዕዝ የፊደል ሰሌዳ ላይ ‹shift key + d› ስንጫን ይገኛል፡፡ ፊደሉ ከ‹ጰ› ጋር ይመሳሰላል፤ ነገር ግን በ‹ደ› እና ‹ጸ› መካከል ያለውን ልዩነት ከተረዳን በሁለቱ ፊደሎች መካከል ያለውም ልዩነት ግልጽ ይሆንልናል፡፡ መጽሐፉ ላይ ያሉትን መሰል ግድፈቶች፣ ምናልባትም ቀጣዩ እትም ላይ አርመዋለሁ፡፡ . . . (የኦሮምኛ የግዕዝ ፊደላትን የመጠቀም ጉዳይ መሐል ሰፍረን ለምናቀነቅነው አንድነት ወይም ኅብረት ራሱን የቻለ /የአንድነት የጋራ መገለጫ/ ቅመምመሆን ስለሚችል ነው የምንቆጨው እንጂ ይህንን የምለው ወደኋላ እንመለስ ለማለት አይደለም፡፡ አንዳንዴ በአማርኛ ሆሄያት ኦሮምኛን መጻፍ ሲያስፈልገን፣ አንዳንድ የአማርኛ-ኦሮምኛ መዝገበ ቃላቶች ላይ ‹ፈፅሞ አይቻልም› እንደሚሉት ብዙም እንደማንቸገር ለማስታወስ ያክል ነው፡፡)

በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ብያኔ አማራ የሚባለው ክልል ሕዝቦች ራሳቸውን በወንዛቸው (የኦሮሞ ሕዝብ በአብዛኛው ራሱን በብሔሩ ሥር ባለው ጎሳው መጥቀስ ነው የሚወደው)፣ አሊያም በኢትዮጵያዊነታቸው ለይተው መጥቀስ ይወዳሉ፡፡ ይህንን ግን ‹በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የተደበቀ (pseudo Ethiopian) አማራነትን› ለማራመጃነት እንደሚጠቀሙበት መሣሪያ የሚመለከቱባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ መጽሐፌ ውስጥ የአማራ ሕዝብ ራሱን በአንድ የዘውግ ብሔር ማንነት ለምን እንደማይጠራ ጠቅሻለሁ፡፡ በተጨማሪም ቀድሞ ‹አማራ› ይባል የነበረው ‹አማራ ሳይንት› የሚባለው አካባቢ ብቻ እንደሆነና የአማርኛ ቋንቋ መስፋፋት ነገሩን ቀይሮ አማርኛ ተናጋሪው በሙሉ አማራ መባል እንደጀመረ› ብዙ ድርሳናት ይተርካሉ፡፡ እስከቅርብ ግዜ ድረስም ‹ማነው አማራ?› በሚለው ላይ መግባቢያ ላይ መድረስ አይቻልም ነበር (አሁንም ተችሎ መሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም)፡፡ ለምሳሌ በፊታውራሪ ተ/ሐዋርያት ‹አውቶባዮግራፊ› ላይ ‹አማራ› የሚለው ቃል ‹ክርስቲያን› ለማለት (ገጽ 278፣ 292)፣ ‹መልካም ሰው› ለማለት (ገጽ 306) ላይ ተጠቅሷል፤ ‹የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀ/ወልድ ማስታወሻ› ደግሞ ‹‹…የአማራ የሚባለው›› ይልና በቅንፍ ‹‹ጎጃም፣ ጎንደር›› ብሎ ‹‹ትግራይ››ን ይጨምራታል (ገጽ 10)፤ ጆን ስፔንሰር ትርሚንግሃም እ.ኤ.አ. በ1952 ባሳተመው ‘Islam in Ethiopia’ በሚለው መጽሐፉ ላይ ስለአገው ሕዝቦች ሲያወራ ‹‹አሁን ትግራይ፣ ቤጌምድር፣ ደምቢያ፣ ጎጃም፣ አገው-ምድር፣ ዳሞት እና አማራ የሚባሉት አካባቢዎች ላይ የሰፈሩ ሕዝቦች ነበሩ›› (ገጽ 48) በማለት ጎጃምና ጎንደርን (ቤጌምድርን) ሳይቀር ‹አማራ› እንዳልሆኑ ይጠቅሳል፡፡ ዛሬ ላይ ‹አማራ› ማለት በአሁኑ ብያኔ መሠረት የአማራ ክልል ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ሒደቱ የብሔርተኝነት ብያኔን ተለዋዋጭነት ያስረዳናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ‹የጋራ ተበዳይነት ስሜት ለኦሮሞ ብሔራዊ ማንነት እንደሰጠው› በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ፡፡ በተመሳሳይ፣ የኦሮሞ ልሒቃን አማራ-ጠልነት አዝማሚያ አማራን (በተሠመረለት ድንበር ላይ ተመሥርቶ) ቀድሞ ከነበረበት እና ምናልባትም የዘመናዊ ሰውነት መጀመሪያ ነው ከሚባልለት የግለሰባዊነት (individualism) ስሜት ወጥቶ የብሔራዊ ስሜት እንዲያዳብር እያስገደደው ነው፡፡ ይህ የምሥራች አይደለም፡፡

ደም አዳኝነት
‹‹ኦሮሞነትን በደም የሚገልጽ ካለ ለኔ ሞኝ ነው›› ብያለሁ፡፡ ሞኝ ብቻም አይደለም፤ አደገኛም ነው፡፡ የተጣመመው የብሔርተኝነት ቅርንጫፍ አንዱ አደገኛ መገለጫ ይኸው ኦሮሞነትን በደም ለመግለጽ መሞከር ነው፡፡

ኦሮሞ ማነው?
ሀ) ኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ከኦሮሞ ወላጆች ተወልዶ ያደገ፣ ቋንቋውን የሚችል፣ ባሕሉን የሚረዳ፤
ለ) ኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ኦሮሞ ካልሆኑ ወላጆች ተወልዶ ያደገ፣ ቋንቋውን የሚችል፣ ባሕሉን የሚረዳ፤
ሐ) ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ውጪ ከኦሮሞ ወላጆች ተወልዶ፣ ቋንቋውን የማይችል፣ ባሕሉን የማይረዳ፤
መ) አፋን ኦሮሞ የሚናገር፣ ባሕሉን የሚረዳ ማንኛውም ሰው፤
ሠ) ኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው፤
ረ) . . .

በጣም አደገኛ የሚባለው መልስ ማንነትን በደም ለመግለጽ መሞከር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሙከራ ንፁህ ዘር፣ ድቅል ዘር... ወደሚል መደምደሚያ ያመራል፡፡ ቀድሞ በነበረው ጅምላ ፍረጃ (stereotyping) ላይ ተመስርቶ፣ በክፉ ቀን፣ ውጤቱ ዘር ማጥራት ነው፡፡ Genocide! ማንነትን በደም ለመግለጽ መሞከር ማንነት በአንድ በኩል የቋንቋ፣ የባሕል እና የሙያ ውህድ ውጤት፣ በሌላም በኩል በትምህርት፣ በጉብኝትና ልምምድ የሚለዋወጥ (ተፈጥሯዊ ያልሆነ ሥሪት) መሆኑን ሰርዞ ‹በዘር ሐረግ የሚመዘዝ ነገር ነው› እንደማለት ነው፡፡ ‹ሰውዬው፣ ለምሳሌ ኦሮሞነትን በደሙ፣ ከወላጆቹ ካልወረሰ አፍ መፍቻ ቋንቋውም ሆነ የሚያውቀው ባሕል የኦሮሞ ብቻ የሆነ ሌላ ቋንቋ የማያውቅ ሰው ኦሮሞ አይደለም ሊባል ነው› እንደማለት ነው፡፡ በርካታ የኦሮሞ ብሔርተኝነት አራማጅ ድረ-ገፆች ላይ የሚታየው ግን ይህ ነው፡፡ አንድ የኦሮምያ ክልል ባለሥልጣን በተሾመ ቁጥር ድረ-ገፆቹ የሰውዬውን ወላጆች ማንነት ጎልጉለው በማውጣት ‹‹ኦሮሞ አይደለም›› ብለው ይጮሃሉ፡፡ ሰውዬው ‹‹ኦሮሞ ነኝ›› ካለ፣ ‹ኦሮሞ ነው› ያለው የኦነጉ በያን አሶባ (ፒ.ኤች.ዲ) አባባል፣ አባባል ብቻ ሆነ ማለት ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥም እንደተገለጸው ሙክታር ‹‹የም›› ነው ይባላል፡፡ እሱ ‹‹ኦሮሞ ነኝ›› ማለቱ የጠማማው ቅርንጫፍ አራማጆች እንዲቀበሉለት አላደረጋቸውም፡፡ መረራ ጉዲና የአምቦ ሰዎች ‹‹ኦህዴድ አልጋችን ላይ የተወለደ ዲቃላ ነው›› አሉኝ ሲል፣ ‹በደም ኦሮሞ አይደሉም› በሚል ኦሮሞነት እየተነፈጉ ነው ማለቱ መሆን አለበት፡፡ ይህ በራሱ በጉዲፈቻ እና ሞጋሳ፣ የደም ውርስ ሳያስፈልግ ኦሮሞነትን ለሚያጎናጽፈው ጥንታዊ ባሕል ዲቃላ አስተሳሰብ ነው፡፡ የደም ቆጠራ አደገኛ አዝማሚያ የሚንፀባረቀው ራሱን የኦሮሞ ብሔርተኝነትን በሚጎዳ መልኩ ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ የሙክታር ከድር እና የአስቴር ማሞ አመራር ‹‹የጅማ መንግሥት›› መባሉ፣ ቀድሞ ደግሞ ኤርሚያስ ለገሰ እንደነገረን ‹‹አርሰናሎች›› (የአርሲ ሰዎች) አመራር በዛ መባሉ የዘር ቆጠራው፣ ብሎም የሥልጣን ክፍፍሉ ወደ ወንዝ ቆጠራ እንደሚወርድ አመላካች መርዶ ነው፡፡ (እንደጉዳይ የተነሳው የሥልጣን ክፍፍሉ አለመማከል ሳይሆን የሰዎቹ የትውልድ ቀዬ ጉዳይ በመሆኑ!) ዞሮ፣ ዞሮ የዘር ቆጠራው ዓላማ የቡድን መብትን ማስከበር ሳይሆን ‹‹ብሔርተኞች›› የሚፈልጉት አካል ሥልጣን እስኪቆጣጠር የሚመዙት ካርድ ሆኖ እንደሚቀጥልም ማመላከቻ ይሆናል፡፡

ዘውገኝነትን ወይም ብሔርተኝነትን (ጥቂት ነው ልዩነታቸው) ምሁራን በሁለት ሊከፍሉት ይሞክራሉ፣ በመልካምነቱ እና በክፋቱ፤ ዘውጌኝነት /ዘውጌ እኝኝነት/ (ethnocentrism) እና ዘውጌኛነት /ዘውጌ እኛነት/ (Nationalism) - ሁለቱም ትርጉሞች ለዚሁ ጽሑፍ ሲባል፣ መጽሐፉ ላይ የበፍቃዱ ሞረዳ ‹ማነው ዘረኛ?› ግጥም በመዋስ ፈጥሬ የተጠቀምኩባቸው ናቸው፡፡ ዘውጌኝነት ‹እኔ የምወከልበት ዘውግ ከሌሎች ዘውጎች ሁሉ ምርጡ ነው› በማለት ከሌሎች ጋር በዘር ላለመቀየጥ መሞከር፣ ሌሎችን ማግለል እና መጠየፍ እንደመፍትሔ የሚወስዱትን የሚወክል ሲሆን፤ ዘውጌኛነት ግን ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ‹እኔም ሆንን ሌሎች ዕኩል የሰው ዘሮች ነን፤ ሆኖም እኔ ይወክለኛል የምለውን ዘውግ መምሰል ነው የምፈልገው› በሚል የዘውጉን ቋንቋ፣ ባሕላዊ አለባበስ እና አኗኗር ዘዬ የሚያዘወትሩትን የሚወክል ነው፡፡ በዘመነ ሉላዊነት (globalization) ግን ይህ የሚቻል ዓይሆንም፤ ሰዎች እንደኩሬ ውኃ በአንድ ቦታ ረግተው በሚኖሩበት ዘመን፣ ከሌሎች ጋር አለመቀየጥ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነበር፡፡ ለሰዎች ዓለማቸው አካባቢያቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ሰዎች፣ ግለሰዎች እየሆኑ ነው፡፡ ይንቀሳቀሳሉ፤ ይቀየጣሉ፤ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ወግና ሥልጣኔ ይወራረሳሉ፤ ያሻቸውን ካላሻቸው ይመርጣሉ፡፡ እንደየዘመኑ አንዱ ባሕል፣ ቋንቋ ወይም ሥልጣኔ ከሌላው የበለጠ የገነነ እና ተቀባይነት ያለው ይሆናል፡፡ የዘመኑ ሰዎችም (ትውልዶችም) የበለጠ የገነነውን እና ተቀባይነት ያለውን በመምረጥ የበለጠ ተጠቃሚ ሆነው ያልፋሉ፡፡ 

መጽሐፉ ውስጥ የሆነ ቦታ የገለጽኩላችሁ የባስክ ፖለቲከኞች አባዜ (የተጣመመው ቅርንጫፍ) ብሔርተኞችም አባዜ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት (ወይም የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢያዊ ትብብር) መጠናከርን እየፈለጉ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ግን አብረን አንኖርም የሚል እርስበርስ የሚጋጭ አስተሳሰብ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመትን አስመልክቶ የታተመው ‹‹Unite or Perish›› የሚል የጥናቶች መድብል ላይ ‹‹Separatist Movements, Insurgencies, and Integeration in Africa›› በሚል ርዕስ በHanji A. Diyal የተሠራ ጥናት እንዲህ ይላል፡-
‹‹በመላው አፍሪካ ልሒቃን የመንግሥት ሥልጣን ለመቆጣጠር በማለም በግጭቶች ተጠምደዋል፡፡ የመንግሥትን ሥልጣን የመያዝ ግልጽ ዓላማው የገዛ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሻሻል ነው፡፡ በአፍሪካ የመንግሥት ሥልጣን ለልሒቃኑ እውነተኛ የሀብት ማፍሪያ እና ማስጠበቂያ ሰርተፍኬት ሆኗል፡፡ በርግጥ፣ የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ማለት የዘውግን ጥቅም ማስተማመን ከሚለው ጋር ትርጉሙ አንድ ሆኗል፡፡›› (የኔ ትርጉም፣ ገጽ 322)
መራር እውነት ነው፡፡ ስለዚህ በስመ ብሔርተኝነት (ወይም ዘውገኛነት) የሚቀነቀኑ ‹‹የደም›› ማጣራቶች አላማ ለግል ጥቅም የመንግሥትን ሥልጣን መሆኑ መጋለጥ ይኖርበታል፡፡ ብሔርተኝነት ፍትሕ እና ርትዕን ለማረጋገጥ እንጂ በማኅበረሰቦች መካከል ሐሳባዊ መለያ መሥመር ለማኖር መዋል የለበትም፡፡

በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በግልፍተኝነት እና በግልብነት በተደረሱ ድምዳሜዎች ተነሳስቶ አንዱ ዘውገኛ፣ ሌላውን ሲገፋ - ዛሬ፣ ዛሬ መሠረታዊ የሰው ልጅነት በአገራችን ዋጋ አጥቶ በብሔርተኝነት እና ተጠቃሚነቱ የጎደለ የሚሉት ዘውግን ጥቅም በማስከበር ሥም የራስን ጥቅም ማሳደድ የተለመደ ሆኗል፡፡ ልብበሉ! ችግሩ የኦሮሞ ልሒቃን ብቻ አይደለም፤ በተለይ ከበፊቱ በከፋ አሁን፣ አሁን እያቆጠቆጡ ያሉት የአማራ ብሔርተኛ ልሒቃንም (አቀራረቡ ቢለይ እንጂ)፣ የሌሎችም ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ የሚባሉትም ሳይቀሩ የዘውግ ብሔርተኞቹን እሴት የኢትዮጵያውያን አድርጎ የመቀበል የተሳሳተ ዕይታ እየተጋረጠባቸው ማየት የተለመደ ነው፡፡ የተጣመመው የብሔርተኝነት ቅርንጫፍ ወረርሽኝ እያጠቃ ያለው ሁሉንም ነው፡፡ …በአገራችን ሁሉም ጎጡን ሲያሳድድ እንደፖለቲካው ሁሉ ተራው የሸቀጥ ግብይት በዘውገኝነት እንዲመራ እያደረገ ያለው የተጣመመ ብሔርተኝነት ነው፡፡ በአገራችን የሰውዬውን ስም ሰምቶ ብቻ የፖለቲካ አመለካከቱን ብቻ ሳይሆን ገንዘብ የሚያስቀምጥበትን ባንክ፣ የሚጠጣውን የቢራ ዓይነት፣ የሚደግፈውን የአገር ውስጥ የእግር ኳስ ቡድን ሳይቀር መገመት እየተቻለ ነው፡፡

ለራሳችን ከእንግሊዝ፣ ስፔን፣ ላቲን አሜሪካ ድረስ የሚካሄዱ የእግርኳስ ሊጎችን እየተከታተልን፤ የቻይናና ሕንድ ጅንሶችን እየለበስን፤ የሆሊውድ፣ ቦሊውድ እና ኖሊውድ ፊልሞችን እየኮመኮምን፤ ከሶቅራጠስ እስከ ዘርዐያቆብ እያጣቀስን እንኳን የዘውግ ብሔርተኝነት፣ ዘውጎቹን ያቀፋቸው ኢትዮጵያዊነትም ይጠበናል፡፡ ዓለማዊ፣ ሰብኣዊ ነን፡፡ የተጣመመ ብሔርተኝነት ያመጣብን አባዜ፣ መፍትሔው ወደኋላ በመጓዝ ከታሪክ አይቀዳም፡፡ ጥላቻም ተረኛ ጨቋኝ ይፈጥር እንደሆን እንጂ መልስ አይሆነንም፡፡ ዶ/ር ሌቪን ‹ትልቋ ኢትዮጵያ› በሚለው መጽሐፉ ‹‹በልዩ ልዩ ቀለማት አሸብርቃ እንደተጠለፈች የጥልፍ ሥራ ሁሉ ኢትዮጵያም ፈፅሞ የተለያዩ ሕዝቦች ጥልፍ ትመስላለች ብሎ ማሰብ ሕዝቦቿ ለዘመናት እርስ በርሳቸው የነበሯቸውን በርካታ ግንኙነቶች፣ በጋርዮሽ የተካፈሉትን መከራና ደስታ መዘንጋት ነው›› ይላል፡፡ ...ኢትዮጵያ ለተበደሉት ሕዝቦቿም፣ ለጨቋኝ ልሒቃኖቿም ከተራ ጥልፍ በላይ የማይተረተር የብሔረሰቦች የርስበርስ ትስስር ነች ነው ነገሩ፡፡ ሼክ በክሪ ሳጳሎ ደግሞ ‹‹የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሕልውና የሚወሰነው በኦሮሞ ሕዝብና በሌሎች ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዕኩልነት እና አንድነት ነው›› ብለው ነበር፡፡ ልብ በሉ! ‹‹በሕዝቦቹ እኩልነት እና ዕድገት ነው›› ያሉት፡፡ ሁለት በአንድ! ይህ እውን የሚሆነው ጠማማው ቅርንጫፍ ዛፉን ከማጉበጡ በፊት እንዲቃና ማድረግ (righting the wrong) ከቻልን ነው፡፡
---
ማስገንዘቢያ: በጽሑፉ የተጠቀሱት ምሁራን አንቱ ያልተባሉት ጽሑፉ ‹የኦሮሞ ጉዳይ› ለተሰኘው መጽሐፍ ምላሽ እንደመሆኑ የመጽሐፉ ደራሲ በተጠቀመት መንገድ ለመጻፍ ሲባል ነው፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጅ በጥቅምት 20/2008 በኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ ላይ የታተመ ነው፡፡ 

No comments:

Post a Comment