Monday, June 15, 2015

የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎ

የዞን 9 ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች ሐምሌ 13 ለብይን ተቀጥረዋል። 1ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ሲ.ዲ በችሎት እንዳይታይ ታግዷል
በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያንና ሦስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች ዛሬ ሰኔ 8/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ፍርድ ቤቱ ግንቦት 19/2007 ዓ.ም በነበረው ችሎት ወቅት አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ የሲ.ዲ ማስረጃ አለኝ ባለው መሰረት ፍርድ ቤቱ በጽ/ቤት በኩል ሲ.ዲውን ተቀብዬ አያለሁ ማለቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሲ.ዲውን በጽ/ቤት ተመልክቶ ዛሬ ሲ.ዲው በግልጽ ችሎት ይታይ ወይስ በዝግ ችሎት የሚለውን ይወስናል ተብሎ ሲጠበቅ ጭራሽ ሌሎች ተከሳሾችም ሊመለከቱት እንደማይችሉ የሚገልጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በዚህም ፍርድ ቤቱ ‹‹ሲ.ዲውን በችሎት መመልከቱን ተገቢ ሆኖ ባለማግኘቱ….›› በሚል ድፍን ያለ ምክንያት በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ሲ.ዲ ዳኞቹ ብቻ በጽ/ቤት አይተውት እንደ አንድ ማስረጃነት ተቀብሎታል፡፡
ይህን ተከትሎ ተከሳሾች በብይኑ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን ጠበቆቻቸውም በጉዳዩ ላይ አለን ያሉትን አቤቱታ አስመዝግበዋል፡፡ ጠበቆቹ በአቤቱታቸው እንዳመለከቱት ሲ.ዲው ላይ የጠበቁት ብይን በግልጽ ችሎት ይታይ አይታይ የሚለውን እንጂ ሌሎች ተከሳሾችና ጠበቆቻቸውም እንዳያዩት ይከለከላል የሚል እንዳልነበር ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ክሱ በቡድን በማሴር…በማነሳሳት…›› የሚል ሆኖ ሳለ አንደኛ ተከሳሽ ላይ ቀረበ የተባለውን የሲ.ዲ ማስረጃ ሌሎች ‹‹ግብረ-አበሮች›› እንዳያዩት መከልከል ተገቢ የዳኝነት አሰራር አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ጠበቆቹ በሁለተኛነት በአቤቱታቸው ያስመዘገቡት ሲ.ዲው የቀረበበትን አግባብ በተመለከተ ነው፡፡ አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ በማስረጃ ዝርዝሩ ላይ ያልጠቀሰውን ሲ.ዲ አሁን በማስረጃነት ሲያቀርብ የማስረጃው አይነት የዶክሜንት ነው ወይስ የኤግዚቢት የሚለውንም በግልጽ አላስቀመጠም ብለዋል ጠበቆቹ በአቤቱታቸው፡፡ በተጨማሪም አቃቤ ህግም ሆነ ፍርድ ቤቱ ከአሁን ቀደም በነበረው ችሎት ውሎ አንድ ሲ.ዲ ብቻ እንደቀረበ ሲገልጹ የቆዩ መሆኑን በማስታወስና ተከሳሾችም የተገለጸላቸው አንድ ሲ.ዲ ብቻ ስለመቅረቡ ሆኖ እያለ ዛሬ ፍርድ ቤቱ ብይኑን ሲያሰማ ‹‹ሲ.ዲዎችን ተመልክተናቸዋል›› ማለቱ ግልጽ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ አስተያየቱን የተጠየቀው አቃቤ ህግ በበኩሉ ‹‹ብይን ባገኘ ጉዳይ ላይ አስተያየት አንሰጥም›› በሚል አልፎታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ቢሆን አቤቱታው ብይን ባገኘ ጉዳይ ላይ መሆኑን በመጥቀስ ‹‹ይግባኝ ማለት ትችላላችሁ›› በሚል አቤቱታውን ከመመዝገብ ውጭ በአቤቱታው የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ አመልክቷል፡፡
በመሆኑም ለአንድ አመት ከሁለት ወር ሲጓተት የዘለቀው የዞን 9 ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች የክስ ሂደት በቀጣይ ቀጠሮ ሐምሌ 13/2007 ዓ.ም ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ይኖርባቸዋል ወይስ በነጻ ይሰናበቱ የሚለውን ብይን ፍርድ ቤቱ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በእለቱ ችሎቱ ውስጥ ወደ 59 የሚጠጉ የሽብር ክስ ጋር ጉዳያቸው የተያዘ ሰዎች የቀረቡበት በመሆኑ ወላጆች ጋዜጠኞች እና ሌሎች ወዳጆች ችሎቱን ለመታደም አልታደሉም
የዞን 9 ማስታወሻ
እንደተለመደው ፍርድ ቤቱ የጓደኞቻችንን የመከላከል መብት በሚያጠብ መልኩ መወሰኑ የተለመደውን የአቃቤህግን ፍቃድ ብቻ መፈፀሙ እንዲሁም አለአግባብ የተራዘመ ቀጠሮ መስጠቱ በጣም አሳዝኖናል።
ሁልጊዜም እንደምንለው ንፁሃንን ለመፍታት አይዘገይምና ፍርድ ቤቱ ጓደኞቻችን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲያሰናብት ጥሪ እናስተላልፋለን።
ያልተሰራ ወንጀል ማስረጃ አይገኝለትም።
ስለሚያገባን እንጦምራለን ።
ዞን9

Friday, June 12, 2015

አሸባሪዋ ማሂ

በአለማችን ላይ እንደሰውልጅ በገዛ ፍጡሩ ላይ የሚጨክን አውሬ የለም እስከዛሬ የምንሰማቸው አሰቃቂ እና አስነዋሪ በደሎች አንዱ ሰብአዊ ፍጡር በሌላው ላይ የፈፀማቸው ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉ ክፉ ተግባራት በፍትህ ሽፋን በዚህ ጊዜ በአደባባይ ሲፈፀሙ ማየት ደግሞ እጅጉን ያማል፡፡
ዘመኑን የማይመጥነውና እና የሚያደርገውን ነገር በአግባቡ ማከናወን የተሳነው በመርማሪነት ማዕረግ ማዕከላዊ የሚገኙት ገራፊዎቻችን በማኅሌት ፋንታሁን እና ጓደኞቻችን ላይ ራሳቸው ማስረጃ ማቅረብ ባልቻሉበት ጉዳይ ላይ አስገድደው ‹‹አመፅ ላነሳሳ›› ነበር የሚል  ቃል አንዲሰጡ ሲገደዱ ነበር ፡፡ ማሂም በዚህ “ምርመራ” ሂደት አመፅ አነሳሳች ተብላ አልፋለች፡፡ ከዱላቸው ውጪ አመጽ ተነሳሳ ብለው  ብለው የሚያቀርቡት ፅሁፍ ባይኖራቸውም ዜጎች ተገደው ያላደረግነው አደረግን ካሉ ገራፊዎችን ለመጠየቅ ጉልበትና አቅም የሌለው ፍርድ ቤታችን የፍትህ ስርአቱን  ፍርደ ገምድልነቱን ለማስመስከር ከበቂ በላይ ነው፡፡
እያደር አዲስ የሚሆንብን ወለፈንዲው የአገራችን የኅሊና እስረኞች ጉዳይ ሁሉም ንፅኅናቸውን የሚያረጋግጥላቸው የፍትሕ ሥርዓት ባይኖርም ከተጠረጠሩበት ጊዜ ጀምሮ አሸባሪዎች ናቸው፤ ማስረጃ ባይቀርብባቸውም አንዴ ተብለዋልና ንፁህ ሆነው እያለ ንፁህነታቸውን ማስመክር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን አሁንማ አሰራሩ የማረጋገጥ ሸክሙን ከከሳሽ ላይ አንስቶ ተጠርጣሪዎቸን ንጹህነታችሁን አረጋግጡ ይላል፡፡ ብዙዎች የፍርድ ቤት ክርክርን የሚያደርጉት ፍትሕን እናገኛለን በሚል ሳይሆን የሚደረገውን ድርጊት ሕዝብ እንዲያውቀው ሥርዓቱን ሁሉም እንዲረዳው ፤ ምናልባት የተጠራጠሩዋቸው ካሉ አንዲያውቁት እድል ለመፍጠርና ይህ እንደማይገባን ለማሳየት አጋጣሚውን መጠቀማቸው ነው፤ እንጂማ በግፍ እንደሚፈረድባቸው እያወቁ  ፍርድ ቤቱንም ሆነ አሰራሩን እውቅና መስጠት አምሯቸው አይደለም፡፡ ትሁቱ ናትኤል ፈለቀ እንዳለው እያደረጉ ያሉት “Judicial activism” ነው፡፡
የምርመራ ሂደቱ ደጋግመው ቢወሩ አንደአዲስ የሚያስገርሙ ብዙ ጉዶች አሉት ፡፡ ጥፋት አለብህ ብሎ ያሰረህ መርማሪ ‹‹ጥፋቴ ምንድን ነው ትላለህ?›› ብሎ ይጠይቅሃል፡፡ ‹‹ሕገ-መንግስቱ ተከብሮ እያለ ሕገ-መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ›› በል ብሎ ፍዳህን ያበላህ መርማሪ መልሶ ቢሮ አስጠርቶህ ስለሕግ አስጠናኝ የቤት ሥራም ሥራልኝ ይልሃል አንተን ‹‹አሸባሪውን››
ከፃፍነው፣ ስንጦምረው ከኖርነው ውጪ ሌላ አላማ ካላገኘንባችሁ ያሉ ገራፊዎቻችን ‹‹አላማችሁ ምንድነው?›› በተደጋጋሚ የሚያነሱት 24 ሰአት ሙሉ የሚደጋገም ጥያቄያቸው ነበር፡፡  ያላለቀው ግን ያለፈውን ምርመራ ዛሬ ላይ ማሂ ስትቀልድበት እንዲህ የምትል ይመስለኛል
አላማችሁ ምን ነበር?
ዓላማችን
·         የማዕከላዊ ምርመራን በመጎብኘት የምርመራ ሂደቱን ምጡቅነት እና ዘመናዊነት መታዘብ፡፡
·         ክስ ሲመሰረት እንዴት በተልከሰከሰ መልኩ እንደሆነ ለዓለም ማሳየት፡፡
·         አቃቤ ሕግ እና መርማሪ እንዲሁም ዳኛ የጆሮ ጉትቻ እና የአንገት ሃብል መሆናቸውን ማሳየት፡፡
·         የሽበር አዋጁ እንዴት abuse እንደሚደረግ በተግባር ማረጋገጥ (አንድ ሰው ከሱቅ ዳቦ ሲገዛ ቢገኝ ዳቦውን በልተህ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ልታስብ ስለነበር ተብሎ የፀረ ሽብር አዋጁ ተጠቅሶ መከሰሰስ እንደሚችል ማሳየት እና ለዚህ ዋናው እና አስፈላጊው ነገር የመንግስት ለመክሰስ የማሰብ ፍላጎት መኖር  ብቻውን በቂ መሆኑን ማሳየት ነው)
ግባችን ደግሞ፡- የፍትሕ ሚኒስቴር እንጂ ፍትሕ እንደሌለ ማሳየት ነው፡፡
 አሸባሪዋ ማሂ
በተለያየ አጋጣሚ ሰዎች በራሳቸው ጥፋት ሲቀየሙን አልያም ሲያኮርፉን “ጥፋቱ የእኔ ይሆን?” ከሚል በተለየ አንግል ለማየት እና ለመረዳት ብዙዎቻችን ሞክረን እናውቃለን፤ በአገራችን ሃሳብን በነፃነት መግለፅ መንግስትን እንደ መዳፈር፣ መብትን መጠየቅ አሸባሪ የሚል ካባ የሚያስደርብ ኖርም ከሆነ ሰነባብቷል፤ ብዙዎች ሃሳብህን በመግለፅህ የሚደርስብንን ነገር በመስጋት ያንን ስጋት የፈጠረውን ስርዓት ከመታገል ይልቅ የአቅማቸውን የሚሞክሩትን ማስፈራራት የእለት ተዕለት ተግባራችን ሆኗል፡፡
ይህ በአንባገነን ሥርዓት ውስጥ ዜጎች ላይ የተጫነው የፍርሃት ቀንበር ራስን ከማስገዛት አልፎ ሌሎችንም ዝም ለማሰኘት እርስ በርሳችን የሸበበን የማይገባንን ሥርዓት ተሸክምን ያለአግባብ ዜጎች ላይ በደል ሲደርስ ለምን ብለን ከመጠየቅ ይልቅ ‹‹አርፈው አይቀመጡም ነበር›› የሚል በጭለማ ውስጥ ያለ የውሸት እውነት ነው፡፡
ማሂን በዞን ዘጠኝ በነበረን ጓደኝነት የራስዋ አበርክቶ ያላት ለብዙ እንስቶቻችን ምሳሌ መሆን የምትችል ብሩህ ወጣት ናት ማሂን እኔ ሳውቃት ስልክ ደውላ አዲስ መፅሃፍ ወጥቷል ናና ሸማምት፣ የመፅሃፍት ምረቃ አለ ለምን አትመጣም፤ እና ሌሎች ይህን መሰል አስተያየቶችን ነበር የምትነግረኝ ፡። የስነጽሁፍ ፍቅሯንም ከራሷ አልፎ ለእኔም ታጋራ ነበር፡፡
ስርአቱ ስርኣት አልባ ነው፣ ዜጎችን ለማሸማቀቅ በዝምታ እንዲገዙ ለማድረግ የሚታትረው ስርኣት የሚሸማቀቁ እና ዝምታን የሚመርጡ እንደሚኖሩ ሁሉ የሕግ የበላይነት የሚባል ነገር እንደሌለ የሚታያቸው ስርዓቱን ለመሞገት ዴሞክራሲያዊ መንገድ አማራጭ እንደማይሆን የሚገለጥላቸው ብዙ ዜጎችም መፈጠራቸውም ሊስቱት አይገባም፤ ሥርዓት አልበኛውን ስርዓት መካሪ የለውም በዘር እና በጥቅማጥቅም እና የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነው የተያዙትም የስርኣቱን ስርዓት አልበኝነት እና ሕገ-ወጥነትን ጀስቲፋይ ሊያደርጉት ይዳዳቸዋል፡፡
የማይቻላቸውን ለቻልሽው ማሂ ይህ የማያልፍ የሚመስለው ክፉ ቀን ቶሎ እንዲያልፍ ምኞቴ ነው፤ በሰፊው እስርቤትም እስክንገናኝ እናፍቃለሁ፡፡


መልካም ልደት እንኳንም ተወለድሽ፡፡   

Tuesday, June 2, 2015

ፍርድ ቤቱ በአቤል ዋበላ ላይ የ4 ወር የእስር ቅጣት በ2 አመት ገደብ ወሰነ

በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ 7ኛ ተከሳሽ የሆነው ጦማሪ አቤል ዋበላ ዛሬ ግንቦት 25/2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ብቻውን ቀርቧል፡፡ አቤል ግንቦት 19/2007 ዓ.ም የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች በነበራቸው የፍርድ ቤት ውሎ ወቅት ‹‹ችሎት ደፍረሃል›› በሚል ጥፋተኛ ያደረገው ፍርድ ቤቱ ዛሬ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ በአቤል ላይ የ4 ወር የእስር ቅጣት የበየነ ሲሆን፣ አቤል ድርጊቱን የፈጸመው በስሜታዊነት መሆኑን በመገንዘብ ቅጣቱ በ2 አመት ገደብ እንዲወሰን በማድረግ ማቅለሉን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ላይ አመልክቷል፡፡ ጦማሪ አቤል ባለፈው የፍርድ ቤት ውሎ ወቅት ጥያቄ ለማንሳት እድል እንዲሰጠው ሲጠይቅ ‹‹ስነ-ስርዓት አድርግ!›› በሚል ኃይለ ቃል ፍርድ ቤቱ ሲናገረውና ሀሳቡን እንዳይገልጽ ሲገድበው፣ ዳኞችን ‹‹እናንተ ራሳችሁ ስነ-ስርዓት አድርጉ!›› በማለቱ ችሎት ደፍረሃል መባሉ ይታወሳል፡፡

ሌሎች የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ውስጥ በአቤል ላይ የጥፋተኛነት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ የእሱ ሃሳብ እኛንም የሚመለከት ስለሆነ ቅጣቱን አብረን እንቀበላለን፤ ስለሆነም በቅጣት ውሳኔው ዕለት እኛም ፍርድ ቤት እንድንቀርብ ይታዘዝልን ብለው የነበር ቢሆንም በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ሳያቀርቧቸው ቀርተዋል፡፡ አቤል ከጓደኞቹ ተለይቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻውን ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን፣ ፍጹም ልበ-ሙሉነትና ዘና ያለ ስሜት ታይቶበታል፡፡

ጦማሪ አቤል በቅጣት ውሳኔው ላይ ምንም ሀሳብ አልሰጠም፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ‹‹እስካሁን እንደነበረው አካሄድ ከስሜታዊነት በወጣ መልኩ ወደፊት ችሎቱን ተከታተል›› የሚል ‹ምክረ ሀሳብ› አቅርቦለታል፡፡

ችሎቱን የአቤል ቤተሰቦች፣ ወዳጆቹ፣ ጋዜጠኞችና ከአሜሪካና ጀርመን ኤምባሲዎች የመጡ ተወካዮች ተከታትለውታል፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሶስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች በቀጣይ ሰኔ 8/2007 ዓ.ም ለ30ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በአንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ አቃቤ ህግ አቅርቤዋለሁ ባለው የዶክሜንተሪ ማስረጃ ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተያያዘ ዜና ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ሁኔታ በቅሊንጦ ታስረው በሚገኙ የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ዞን ላይ ለውጥ የተደረገ ሲሆን ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ እና ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ወደ ተለያዬ ዞኖች ተዘዋውረዋል፡፡

በዚህም መሰረት
በዞን1 ጦማሪ ዘላለም ክብረት ፣ ጦማሪ አቤል ዋበላ እና ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ
በዞን2 ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ፣ ጦማሪ አጥናፍ ብርሃኔ እና ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
በዞን3 ጋዜጠኛ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ ይገኛሉ ፡፡

ስለሚያገባን እንጦምራለን !
ዞን9