Thursday, January 31, 2013

የኢትዮጵያዊነት መንፈስና የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ


በፍቅር ለይኩን

There are two things that can bring this planet closer together: love and football.
--Iran coach Afshin Ghotbi

ይህ ለዚህ ጽሑፌ መግቢያ ይሆነኝ ዘንድ የመረጥኩትን ኃይለ ቃል በ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ባለንጣዎቹ የዛሬዋ ልዕለ ኃያል አሜሪካና በአስር ሺህ ዘመናትን በሚያስከነዳ ግዙፍ ስልጣኔዋና ታሪኳ ምትኩራራው ኢራን በተፋጠጡበትና የእግር ኳስ መድረክ የኢራኑ አሰልጣኝ ስለዚህ አስደናቂ አጋጣሚ በአድናቆት የተናገረው ነው፡፡ የአሜሪካው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትም the mother of all games በሚል አጭር ቃል ነበር ሁለቱን አገራት ግጥሚያ የገለፁት፡፡ እስቲ ስፖርት በፖለቲካው መድረክ ካለው አዎንታዊ ሚና በመነሳት ስለ ሰሞኑ የአፍሪካ ዋንጫ ጥቂት ነገሮችን ልበል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከሦስት አሠርት ዓመታት በኋላ ተሳታፊ በሆነችበት በዘንድሮው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፈጠረብን ደስታ፣ ሐሴትና ሞቅታ ገና ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችንን የምታበስረውን የመጨረሻዋን ፊሽካ ከሰማንባት ቅጽበት ጀምሮ የተፈጠረ ውብና ልዩ ስሜት ነው፡፡

ይህ ብሔራዊ ስሜታችን ከኢትዮጵያዊነት ምሉዕ ኩራት፣ ስሜትና ትኩሳቱ ጋር አብሮን ዘልቆ በእግር ኳሱ መድረክ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ አብዝተን ከምንታወቅበት ‹‹የራብና የጦርነት ምድር›› ከሚለው ገጽታችን ባሻገር ኢትዮጵያ ‹‹የኳስ ጥበብን የተካኑ የውብ ሕዝቦች አገር ናት!›› የሚለውን ሌላውን ውብና ተወዳጅ ገጽታችንን ለዓለም ሕዝብ አሳይቶ አልፏል፡፡

ይህን ብሔራዊ ቡድናችን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ ባሉ ኢትዮጵያውያን መካከል የነበረውን የኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ፍቅርና የአንድነት ውብ ስሜት የታዘበ አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ወዳጄ በኢሜይል ባደረሰኝ መልእክቱ እንዲህ ሲል ነበር አድናቆቱንና ትዝብቱን ያካፈለኝ፡-


ጆሐንስበርግ እንደ ኢትዮጵያን ሀበሾች የቁልምጫ አጠራር ‹‹ጆዚ››፣ በርካታ ስደተኛ ኢትዮጵያን በሚበዙባት ከተማ ነች፡፡ በዚህች ጭንቅንቅና ትርምስምስ በሚበዛባት የደቡብ አፍሪካዊ የቢዝነስ ከተማ በሰሞኑን እያየሁት ያለው ነገር በእጅጉ የሚያስደምም ነው፡፡ ‹‹ጆዚ››/ጆሐንስበርግ በኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቀ ዓላማ ደምቃ ተውባለች፡፡

የኢትዮጵያን ሱቆች፣ መኪናዎች፣ መኖሪያ ሕንጻዎች… ሁሉ በዚህ የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት በሆነ የኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ ደምቀዋል፣ አሸብርቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሦስት አሠርተ ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ መብቃቱ የፈጠረው የደስታ ስሜት በእጅጉን ከፍተኛ ነው፡፡ ዋልያዎቹ ከዛምቢያ ጋር የመጀመሪያውን ፍልሚያ ለማድረግ ወደ ጆሐንስበርግ ከገቡበት ዕለት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ፊት ላይ የሚታየው ደስታና ጉጉት በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዛምቢያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታና ዋልያዎቹ በእኩል ውጤት ከተለያዩ በኋላም የነበረው ስሜት በእጅጉ የሚያስደንቅ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የሆነ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ ብሔራዊ ስሜትና ፍቅር የፈጠረው ትእይንት ለእኔ፣ ለበርካታ ደቡብ አፍሪካውያንና የሌሎች አገር ዜጎች እንግዳ ነው፡፡ በአጠቃላይ ትእይንቱን በቃል ለመግለፅ በእጅጉ የሚያዳግት ነው፡፡

በአብዛኛው አፍሪካውያንና ምዕራባውያን ዘንድ ‹‹በርሃብና በጦርነት›› የምታወቀው ኢትዮጵያ በስፖርት መድረክ በእንዲህ ዓይነት የደመቀ፣ ያማረ ብሔራዊ ስሜት፣ አንድነትና አገር ፍቅር ስሜት ብቅ ማለቷ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ሲል በኤሜይል መልእክቱ ገልፆልኛል፡፡እንዲሁም የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪና በአሁን ወቅት በጆሐንስበርግ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ጓደኛዬ ቴዎድሮስም የኢትዮጵያዊነት ጠንካራ መንፈስ ያስተሳሰራቸው ደጋፊዎች በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማ ስር አንድ ሆነው ስሜታቸውን የገለጹበትን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልፆልኛል፡-

መላው ስታዲዮም በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቀ ዓላማችን ደምቋል፡፡ ሰንደ ዓላማችን እንዲያ በምቦምቤላ ስታዲዮም ከፍ ብሎ ሲውለበለብ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ፊት ላይ ይታይ የነበረውን የደስታ ስሜት፣ ጭንቀትና ጉጉት ሳይ የተሰማኝ ስሜት በቃላት ለመግለፅ በእጅጉ ያዳግተኛል፡፡

የአፍሪካውያንና የመላው የዓለማችን ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መገለጫ የሆነው ሰንደቀ ዓላማችን እንዲያ በስታዲዮም ውስጥ ከፍ ብሎ ሳየው አባቶቻችን ለዚህች ሰንደቀ ዓላማ የከፈሉት ክቡር የሆነ መስዋዕትነት በዓይነ ህሊናዬ ገዝፎና ገኖ ታየኝ፡፡

አረንጓዴ፣ ቢጫውና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማችን በመላ አፍሪካዊና በጥቁር ሕዝቦች መካከል ያለውን ከበሬታ ለአፍታ ሳስበው ልዩ ስሜትን ነው የፈጠረብኝ፡፡ በእውነት ነው የምልህ በዛ የነበረውን የኢትዮጵያውያኑን ስሜት በአካል ተገኝተህ ብታየው ሊፈጥርብህ የሚችለውን ስሜት ለመግለጽ ቃላት በእጅጉ ያጥርህ ነበር፡፡ በእውነት ነው የምልህ በኢትዮጵያዊነቴ በእጅጉ የኮራሁበት ቀን ነው፡፡ ሲል ገልፆልኛል ‹‹ከጆዚ›› ከደቡብ አፍሪካዊቷ የንግድ ከተማ ጆሐንስበርግ፡፡

የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ የኢትዮጵያችን መለያ ሰንደቀ ዓላማ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት፣ የነፃነትና የልዑላዊነት ተምሳሌት መሆኑ በብዙዎች ዘንድ የተመሰከረለት ነው፡፡ አዛውንቱ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን የክህደት ቁልቁለት በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለፁትም፡-

…ኢትዮጵያዊነት በቄጤማ ጉዝጓዝ ላይ የሚታየው መተሳሰብና መፈቃቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የአስተዋይነት፣ የሚዛናዊነት የጨዋነት ባሕርይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ረጅምና ተጽፎ ያላለቀ ታሪክ ነው፤ ብዙ ሰዎችም የተሰዉለት ስሜት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ስቃይና መከራ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ክብርም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጭቆናና ጥቃት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት አሻፈረኝና እምቢ ባይነትም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ሊያስተምረን እንደሚችለው ኢትዮጵያዊነት እንደ ላስቲክ ነው፡፡ ሲስቡት ይሳባል፣ ሲለቁት ይሰበሰባል፡፡ ማለት ይሳብና ይሳሳል እንጂ አይበጠስም…፡፡

ይህ ታሪካዊ እውነታ ነው የደቡብ አፍሪካውን የነፃነት ታጋይ፣ የሰላም አርበኛ፣ የእርቅ አባትና የፍቅርና ወንድማማችነት ተምሳሌት የሆኑትን ማንዴላ/ማዲባ ረጅሙን የትግል ዘመናቸውን በተረኩበት Long Walk to Freedom በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ እንዲሉ ያስገደዳቸው፡-

“Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly than a trip to France, England, and America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African.”

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያንና ለኔልሰን ማንዴላ እናት ምድራቸው ብቻ ሳትሆን የትናንት አባቶቻቸው፣ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻው፡- ‹‹የአፍሪካዊነት፣ የጥቁር ሕዝቦች፣ በአጠቃላይ የሰው ልጆች ግዙፍ ስልጣኔ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ቅርስ መገለጫም እንደሆነች አድርገው ነው የሚያስቧት፡፡››

ወንድማችን በፍቄም በፌሰ ቡክ ገጹ በደቡብ አፍሪካው የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ መላው መንፈሷና ሰውነቷ በኢትዮጵያ ባንዲራ ተውቦ ዓይኖቿን ወደ አርያም አንስታ ለዋልያዎቹ ድል ማድረግ ስትጸልይና መልካም ምኞቷን ስትገልጽ የነበረችውን የፕሪቶሪያዋን ጸሐይን፡-

‹‹በእናት ምድሯ በኢትዮጵያ ውበት፣ ፍቅር፣ አንድነትና ኩራት ያበደች የዘመናችን ጣይቱ፣ የጥቁር አፈር ውብ ፈርጥ፣ የኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ውብ ኅብር ታላቅ ተምሳሌት ናት፡፡›› ሲል ያሞከሻት፡፡

በዚህ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ በታየበት በደቡብ አፍሪካ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያሰደመመኝና በእጅጉ ስሜትን የነካው ደግሞ በጠላትነት የተፈረጁ፣ መንግሥቶቻቸው እርስ በርሳቸው የሚካሰሱና የሚወነጃጀሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን፣ ለዋልያዎቹ/ለጥቋቁሮቹ አንበሶች ድጋፋቸውን ለመስጠት የተገናኙበትና ባለፈው ሳምንት በፌስ ቡክ ገፆች ‹‹አስታራቂም የለ፣ እኛው እንታረቅ›› በሚል መልእክት የብዙዎቻችንን የፌሰ ቡክ ገጽ አድምቆ የከረመው የኢትዮጵያውያኑና ኤርትራውያኑ ውብ ሴቶች ምስል ነው፡፡

እነዚህ በባህል፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በደም የተሳሳሩ ሕዝቦች በመንግሥቶቻቸው መካከል ያለውን የጠላትነት መንፈስ ወደጎን ትተው በስፖርቱ መድረክ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለወንድማማችነት… ያላቸውን አዎንታዊ ስሜትና ፍላጎት የገለጹበት ሁኔታ በእጅጉ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡

በተቃራኒው እስካሁን ድረስ እያሰገረመኝ ያለው ነገር ደግሞ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- ‹‹ከኤርትራ ጋር ለመደራደርና ሰላምን ማውረድ አስመራም ድረስ ቢሆን እንኳን እሄዳለሁ፡፡›› ባሉ ማግስት፣ ‹‹በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለቱ አገራት የሚያድረጉትን ጨዋታ በሌላ ሦስተኛ አገር እንጂ በአስመራ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለንም፡፡›› የሚለውን መረር ያለውን መግለጫ ሳስብ ደግሞ የመንግሥታችን ለሰላም አለኝ የሚለው ናፍቆቱና አቋሙና ግራ ያጋባኛል፡፡

እናም ‹‹ሰፖርት ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለወንድማማችነትና ለአንድነት…!›› የሚለው መርህ በመንግሥት ባለስልጣኖቻችንና በስፖርቱ መስክ ባሉ ኃላፊዎች ዘንድ ትርጓሜው ምን እንደሆነ በግልፅ ያስረዱን ዘንድ ደግመን ደጋግመን እንድንጠይቃቸው እንገደዳለን፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያዊነት ኅብር በጎላበት፣ ኢትዮጵያዊነት ውበትና አንድነት በደመቀበት በዘንድሮው ከሦስት አሠርተ ዓመታት በኋላ ተሳታፊ በሆንበት በደቡብ አፍሪካው የእግር ኳስ ዋንጫ፣ በተቃራኒው ደግሞ በዚህ ውድድር የታዘብነው፣ የሆነውና ያየናቸው ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ መከፋፈልና እልኸኝነት… ገና በመካከላችን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ብሔራዊ እርቅንና መግባባትን ለማስፈን ረጅም ጉዞ እንደሚጠብቀን ያሳየ ነው ብል ብዙም ከእውነታው የራቅኹ አይመስለኝም፡፡

ለዚህ ጉዞአችን መሳካትና ውጤት ደግሞ ሀገራዊ/ብሔራዊ ራእይ፣ ጠንካራና በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ የማይናወጽ ጽኑ መንፈስ ያላቸው፣ ከዘረኝነት፣ ከጥላቻና ከአድልዎ የጸዱ ኢትዮጵያውያን ማንዴላዎች፣ ጋንዲዎች፣ ሉተሮች… ወዘተ በእጅጉ እንደሚያስፈልጉን አስባለሁ፡፡

ሰላም! ሻሎም!   
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ይጻፉላቸው::

No comments:

Post a Comment