Sunday, June 26, 2016

የስቃይ ሰለባዎች


በዞን ዘጠኝ

ዓለማቀፍ የማሰቃየት ተግባር ተጠቂዎችን የመደገፍ ቀን (International Day in Support of Victims of Torture) ከጎርጎሮሳዊያኑ 1998 ጀምሮ በየዓመቱ ጁን 26 ቀን ይከበራል፡፡ ቀኑ ጁን 26 ላይ የሚከበርበት ሁለት ምክንያቶች ሲኖሩ፤ አንደኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር በመስራች አባል አገራት ቻርተሩን የፈረሙበት ቀን ጁን 26 1945 ሲሆን በሁለተኝነት የተባበሩት መንግስታት የፀረ ማሰቃየትና የጭካኔ የቅጣት ተግባር ኮንቬንሽን (Convention against Torture and Other Cruel, Inhuman or Degrading Treatment or Punishment) ወደ ስራ የገባው ጁን 26 1987 በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የቻርተሩም መስራች ፈራሚ ስትሆን ኮንቬንሽኑን ደግሞ በፓርላማ አጽድቃ ተቀብላለች፡፡

Torture’ በSergei Tunin


የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ የማሰቃየት ተግባር እንደሚፈፅም ለሚቀርብበት ትችት በጥቅሉ ‹‹ውሸት ነው›› ከማለት ውጭ ሁኔታዎቹን ለማሻሻል ምንም አይነት እርምጃ እየወሰደ ካለመሆኑም በላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ነገሮች እየተባባሱና በተለይም የፖለቲካ እስረኞች ላይ ጠንክረው ቀጥለዋል፡፡ እኛም በኢትዮጵያ ያለውን የማሰቃየት ተግባር ስፋት ያሳያል ይሆናል በሚል መነሻ ቀኑ የሚከበርበት ጁን 26 ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አማካኝነት ክስ ተመስርቶባቸው ታስረው የሚገኙና ታስረው የነበሩ ግለሰቦች የደረሰባቸውን የማሰቃየት ተግባራት ራሳቸው በተለያዩ ጊዜያት እንደተረኩት በማሰባበሰብ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

የተራኪዎቹን ማንነት በጽሁፉ ግርጌ ላይ ያገኙታል፡፡