Friday, March 25, 2016

የኛ ኦማር አፊፊዎች የት ናቸው?በላይ ማናዬ

ኦማር አፊፊ (Photo: ahl-alquran.com)
ኦማር አፊፊ በለበሰው የፖሊስ የደንብ ልብስ ኩራት ይሰማዋል፤ ፖሊስነቱን ይወደዋል፡፡ በተለይ በሚከፈለው ደመወዝ እና በደህንነቱ ምክንያት ስራውን አብዝቶ ይፈልገው ነበር፡፡ ኦማር አፊፊ ግብጻዊ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1981 (ልክ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ወደ ስልጣን ሲመጣ) በ16 አመቱ ወደ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ገባ፡፡ ኦማር በፖሊስነት ስራው ለማህበረሰቡ አንዳች ነገር እንደሚያበረክት አምኗል፡፡

ሆኖም ወጣቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የደንብ ልብሱን ለብሶ ወደ ሰፈሩ ሲሄድ የሰዎች እይታ ተቀየረበት፡፡ ተንከባክበው፣ ሲያጠፋ መክረው ያሳደጉት የሰፈሩ ሽማግሌዎች ሳይቀር የፖሊስ ልብሱን ለብሶ ሲያዩት ከመቀመጫቸው ተነሱለት፡፡ ኦማር ድርጊቱ ከአክብሮት ይልቅ ፍርሃት ያዘለ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡
‹‹መንግስት ማንም ዜጋ ፖሊስን እንዲፈራ በመፈለግ በዚያ ሁኔታ ቀርጾታል፡፡ ፖሊስ በህብረተሰቡ ዘንድ አሸናፊነት (ተፈሪነት)ን አስርጹዋል›› ይላል ኦማር አፊፊ፡፡ ሁሉም ፖሊሶች ህዝብን የሚበድሉ እንዳልሆኑ ቢያውቅም ኦማር ለፖሊስነት ካለው አክብሮት ጋር የህዝቡ ምላሽ ደስ አላለውም፡፡ ኦማር በዚህ ስሜት ሁለት አመት እንደሰራ በሦስተኛ አመቱ ላይ አንድ ለየት ያለና ህሊናውን የሚፈታተን ነገር ገጠመው፡፡

 በኦማር ሦስተኛ አመት የስራ ዘመን አንድ የፖሊስ ባልደረባ ይገደላል፡፡ ወዲያውም የግብጽ ፖሊሶች ባልደረባቸውን የገደለውን ሰው መያዝ ዋና ስራቸው አደረጉት፡፡ ፖሊስ ገዳዩ ከካይሮ ከተማ ሳይርቅ የሆነ ቦታ መሸሸጉን መረጃ ደረሰው፡፡ ኦማር አፊፊ ገዳዩን ለመያዝ ከተሰማሩ ፖሊሶች መካከል ነበር፡፡ ገዳዩ አለ ወደተባለበት ቦታ ሲደርሱም እነ ኦማር ተጠርጣሪውን ያገኙታል፡፡ ፖሊስን የተመለከተው ተጠርጣሪው ታዲያ ወዲያው እግሬ አውጭኝ ይላል፡፡ ሆኖም ማምለጥ አልቻለም፡፡ ገዳዩ በፖሊስ ከበባ ሲያዝ አንዳችም መሳሪያ አልታጠቀም ነበር፡፡
አሁን የኦማር አፊፊ ፈተና ደረሰች፡፡ ይህን ሰው ለመያዝ የተሰማሩት ፖሊሶች አዛዥ ኦማርን ትዕዛዝ ሰጠው፡፡ ‹‹ግደለው!›› አለው አዛዡ ኦማርን፡፡ ኦማር አፊፊ መለሰ…‹‹እጁን የሰጠን ሰው እንዴት እገድለዋለሁ?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ‹‹ልገድለው አልችልም!›› ሲልም መለሰ ለራሱ፡፡ አዛዡም ተናገረ…‹‹አንተ ሆደ ቡቡ ነገር ነህ….ሂድ ከዚህ!›› ሲል አምባረቀበት፡፡ ኦማር አፊፊ ትንሽ እርምጃዎች ርቆ ከመጓዙ የጥይት ድምጽ ሰማ፡፡ ሰውየውን ገደሉት፡፡ ‹‹ይህ ጉዳይ በብዙ ለወጠኝ›› ይላል ኦማር፡፡

ኦማር አፊፊ በዚህ ገጠመኝ ብቻ ፖሊስነትን አላለፈበትም፡፡ በ1995 እ.ኤ.አ ግብጽ የፓርላማ ምርጫ ታደርግ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ ኦማር አፊፊ በአንድ እስር ቤት በጥበቃ ላይ ነበር፡፡ በጥበቃ ላይ እያለ ታዲያ አንድ የመንግስት ደህንነት ወደ መቶ የሚጠጉ ሰዎችን ይዞ ወደ ኦማር ይመጣል፡፡ ሰዎቹ ድብደባ የደረሰባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎችና አባላት መሆናቸው ኦማር አፊፊ ገብቶታል፡፡

የመንግስት ደህንነቱ ሰዎቹ ‹‹ረባሾች›› መሆናቸውን በመጥቀስ ኦማርን ወደ እስር እንዲያስገባቸው ይጠይቀዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ኦማር መስማማቱን ከገለጸ በኋላ አንድ ጥያቄ ጠየቀ…‹‹ህጋዊ የእስር ማዘዣ አሳየኝና ልሰራቸው›› አለው ኦማር ለመንግስት ደህንነቱ፡፡ ደህንነቱ ግን ‹‹ምንም ማዘዣ ወረቀት አያስፈልግም፤ ይህ ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው፣ አስቸኳይ ትዕዛዝ ነው›› ከማለት ውጭ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሳየት አልቻለም፡፡ በዚህም ኦማር በመንግስት ደህንነቱ ‹‹የግብጽ ጠላት ናቸው›› የተባሉትን ሰዎች ከህግ ውጭ አላስርም ብሎ በአቋሙ ጸና፡፡ በሰዓቱ ደህንነቱ ተቃዋሚዎቹን ወደ ሌላ እስር ቤት ከመውሰድ ውጭ አማራጭ አልነበረውም፡፡

የኦማር አፊፊ ሦስተኛ ገጠመኝ ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ የሆነ ነው፡፡ ምርጫ ከመደረጉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ማታ ላይ የያኔው የካይሮ ፖሊስ አዛዥ ሀቢብ ኤል አድለይ ወደ 800 የሚጠጉ ‹ሲኒየር› የፖሊስ አባላትን ሰብስቦ ነበር፡፡ ሀቢብ በዚህ ስብሰባው ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ለተሰብሳቢዎቹ አስተላለፈ፡፡ ‹‹በዚህ ምርጫ ተቃዋሚዎቹ ካሸነፉ ደመወዝ የሚከፍላችሁ የለም፡፡ ስራ ፈት ትሆናላችሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ምርጫ ልዩ ሚና መወጣት አለባችሁ›› በማለት ምርጫውን ሆስኒ ሙባረክ እንዲያሸንፍ እንዲሰሩ ፖሊሶችን በግልጽ አዘዘ፡፡ ከዚያም ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ማስረዳት ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ ኦማር አፊፊ ህሊናው የማይቀበለው፣ ህግ የማይፈቅደው ጉዳይ እንደሆነ በማመን የተለየ አቋም ያዘ፡፡

ኦማር አፊፊ ለካይሮ ፖሊስ አዛዡ ሊመለሱለት የሚሻቸው ጥያቄዎች መኖራቸውን ተናገረ፡፡ የተሰጠው ምላሽ ግን ‹‹ዛሬም አንተ! በል ውጣ!›› የሚል ትዕዛዝ ነበር፡፡ ኦማር አፊፊ ስብሰባውን ለቆ ሲወጣ ብቻውን አልነበረም፡፡ ሌሎች በአዛዡ ያልተስማሙ ፖሊሶችም ተከትለውት ነበር፡፡ በወቅቱ ምርጫውን ገዥው አካል በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉ ታውጇል፡፡ ኦማር አፊፊ ግን ከዚህ በላይ በፖሊስነት ስራው መቀጠል አልቻለም፡፡

የኦማር አፊፊን ታሪክ ሳስብ በእኛስ ሀገር እንደ ኦማር አይነት ፖሊሶች ይኖሩ ይሆን ብየ ራሴን ጠየቅሁ፡፡ መልሱንም ከራሴው ገጠመኞች ለመፈለግ ሞከርኩ፡፡ ከቅርቡ የ2007 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ክስተቶች ስዳስስ የምርጫ ቅስቀሳ ወረቀት ሲበትኑ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታሰሩ የተቃዋሚ አባላትን አገኘሁ፡፡ ለአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ደብዳቤ አስገብተው ሰልፍ በወጡ ዜጎች ላይ የተወሰደውን የጅምላ እስርና ድብደባ አስታወስኩ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊም ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ለዘገባ በተገኘበት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተይዞ ለሳምንት ታስሯል፡፡ በዚህ ወቅት እንደ ኦማር አፊፊ ‹‹የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሌለ አላስርም›› የሚል ፖሊስ አላየሁም፣ ወይም አልገጠመኝም፡፡

ኦማር አፊፊ ያልታጠቀ ሰው ተኩሸ አልገድልም አለ፡፡ እኛስ ሀገር ይህን የሚል ስንት ይኖራል እያልኩ ሳስብ በኦሮሚያ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ህጻናት፣ እናቶችና ሌሎች ሲቪል ዜጎች ትውስ አሉኝ፡፡ ለምን? ፖሊስ የሚፈራ ነው ወይስ የሚከበር ነው እንዲሆን የሚፈልገው? ፖሊስ የሚጠብቀውስ ማንን ነው?

መንግስታት ይለወጣሉ፡፡ ኦማር አፊፊ በፖሊስነት የሰራበት የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ መንግስት በህዝብ ተቃውሞ ከስልጣን ወርዷል፡፡ ኦማር ታዲያ በሚያልፍ መንግስት የማያልፍና ህዝብን የሚጎዳ ድርጊት ሳይፈጽም ለህሊናውና ለህግ ተገዥ ሆኖ አሳልፏል፡፡ ይህ ግን ኦማርን ዋጋ ሳያስከፍለው አላለፈም፡፡ ስራውን አጥቷል፡፡ በኋላ ላይ ህግ አጥንቶ በጠበቃነት ሲሰራ መንግስት አላሰራው ብሎ ከሀገር አሳድዶታል፡፡ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘውንና ዜጎች እንዴት ከፖሊስ ኢ-ፍትሃዊ አያያዝ መጠበቅ እንዳለባቸው የሚገልጸው መጽሀፉ ከሽያጭ ታግዶበታል፡፡ በያኔው የግብጽ መንግስት ዘንድ ኦማር አሸባሪ ተብሏል፡፡ በዚህም በስደት የሚኖርበት የአሜሪካ መንግስት ኦማርን አሳልፎ እንዲሰጠው የሆስኒ ሙባረክ መንግስት እስከመጠየቅ ደርሷል፣ አልተሳካለትም እንጂ፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገው አምባገነን መንግስት ሲወድቅ ግን ኦማር ለመታዘብ በቅቷል፡፡ ህዝብ ሲያሸንፍ በስደት ከሚኖርበት ሀገር ሆኖ ባገኘው አማራጭ ሁሉ ተመልክቷል፡፡ ኦማር አፊፊ ሁሌም ከህዝብ ጎን በመቆሙ ደስተኛ ነው፡፡

ክብር ለህሊናቸውና ለህግ ለሚገዙ ዜጎች!
---

ይህ ጽሑፍ መጋቢት 13፣ 2008 ለስርጭት የበቃው አዲስ ገጽ መጽሔት ላይ ታትሞ በጸሐፊው ፈቃድ ዞን ዘጠኝ ላይ በድጋሚ የወጣ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment