Friday, February 12, 2016

ነገረ ‹ቀለም አብዮት›


በዘላላም ክብረት

ሁለቱም ሃገራት በይፋ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጀመሩ መቶ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሁለቱም በተመሳሳይ ወቅት  ከኮሚኒስታዊ አስተዳደርና ስርዓት መፋታታቸውን ባወጁ ማግስት ዴሞክራሲን ተግባራዊ የማድረግ ፈተና አጋጥሟቸዋል፡፡ ሁለቱም ሃገራት በተመሳሳይ ወቅት ባፀደቁት ሕገ መንግስታቸው የምርጫ ዴሞክራሲን (electoral democracy) አውጀዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ሃገራት ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስታቸውን ካፀደቁ ወዲህ ተቃዋሚዎቻቸው ስልጣን ሊይዙ አልቻሉም፤ የመያዝ እድላቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መጥቷል፡፡ ሁለቱም ሃገራት በአሁኑ ወቅት የአንድ ፓርቲ የበላይነት በእጅጉ የጎላባቸው ሃገራት ናቸው፡፡ ሁለቱም ከምዕራቡ ዓለም ጋር (በተለይም በአለፉት 10 ዓመታት ውስጥ) በዴሞክራሲ ጉዳይ እየተጨቃጨቁ እና ምዕራቡን ዓለምም እያንጓጠጡ ቀጥለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ሃገራት እየመሩ ያሉት መንግስታት ትልቁ ፍርሃታቸው አድርገው የሚያቀርቡትም በምዕራባዊያን የሚደገፍ በእነሱ ቋንቋ ‹የቀለም አብዮትን› ነው፡፡ የሁለቱም ሃገራት የጊዜው ገዥዎች ምዕራቡ ዓለም በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ከስልጣን እነሱን ለማውረድ ቀን ከሌሊት እንደሚሰራና ይሄንም እስከ መጨረሻው እንደሚፋለሙት ይገልፃሉ፡፡ የምዕራቡን ዓለም ጣልቃ ግብነት ለመከላከልም ሕጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመራቸውን ገልፀው፤ ጠበቅ ያሉ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያድ) እና የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጎችን በስራ ላይ ማዋላቸውንም በኩራት ይገልፃሉ፡፡ በተለይም የመያድ ሕጋቸው ‹የውጭ ሐይሎችን› ከፖለቲካዉ ምህዳር ለማራቅ ያደረጉት እንደሆነ ሁለቱም በኩራት ይገልፃሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሩሲያ፡፡

ያለፉትን አስር ዓመታት ምስራቅ አውሮፓንና የካውካስስ አካባቢን የሚገልፀው የፖለቲካ መገለጫ ‹አብዮት› ነው፡፡ ከአብዮትም ‹የቀለም አብዮት›፡፡ የኢትዮጵያም የፖለቲካ ምህዳር በተመሳሳይ ጊዜ ባጋጠመው ትኩሳት ምክንያት ከዚህ የአብዮት ተረክ (narrative) ጋር በእጅጉ የሚጋራው ነገር አለ፡፡ አብዮተኞቹ በኬየቭ አደባባይ ሲቆሙና ሲቀመጡ፣ አብዮተኞቹ ቲብሊሲን ሲያጥለቀልቋት ኢሕአዴግ እዚህ ያነጥሳል፤ የአደባባዮቹን ጥበቃ ያጠናክራል፣ አይናቸው በአብዮት ቀልሟል የሚላቸውን ግለሰቦች ያስራል፣ እጅግ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ስለ ቀለም አብዮት አስከፊነት በመንግስቱ ሚዲያዎች ይለቀቃሉ፡፡



በሜይ 23፣ 2014 የቀለም አብዮትን ዋና አጀንዳው አድርጎ ከተካሔደው ሶስተኛው የሞስኮ የዓለማቀፍ ደህንነት ስብሰባ ላይ የሩሲያ ተቀዳሚ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ጀኔራል ቫለሪ ጋሪስሚዮቭ ካቀረቡት መወያያ ላይ የተወሰደ 

(የዩክሬን ሁለተኛው አብዮት በ2014 ሲከሰት በሚያዚያ ወር ውስጥ ብቻ ከታተሙት ሐያ ስድስት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እትሞች ውስጥ ‹ዩክሬንን ያ በእሳት አይጫወትም›፣ ‹ዩክሬን ወደአደገኛ ሁኔታ በመሸጋገር ላይ ናት›፣ ‹ሩሲያ ዩክሬንን አስጠነቀቀች›፣ ‹አይሲሲ በዩክሬን ጉዳይ ምርመራ ሊጀምር ነው› የሚሉ ፅሁፎችን ጨምሮ በአስራ ሁለቱ እትሞች ለውጡን አጣጥሎ፤ ፑቲንን አጀግኗቸው እናገኛለን)

Sunday, February 7, 2016

እከላከላለሁ!


በበፍቃዱ ኃይሉ

ከ18 ወራት እስር በኋላ ስንፈታ ዐ/ሕግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ በሁለት “ምክንያቶች” በወንጀል ሕጉ (አንቀጽ 257/ሀ) ግዙፍ ያልሆነ “በጽሑፍ ለአመፅ የማነሳሳት” ጥፋት ተከላክዬ ነጻ መሆኔን የማረጋገጥ ሸክሙን ወደ እኔ አዙሮታል፡፡ ምክንያቶቹ እነዚህ ናቸው፤

፩) “የግብጽ ዓይነት አብዮት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲነሳ የሚቀሰቅስ ጽሑፍ መጻፉን ለፖሊስ በሰጠው ቃል …‹የእውነት ቃል መስጠቱን› አምኗል” የሚልና፣

፪) ዐ/ሕግ ባቀረባቸው ሰነዶች “በፌዴራሉ ሕገ-መንግሥት የተቋቋመውን ስርዓት ለማፍረስ በጽሑፍ አማካኝነት የቀሰቀሰ ለመሆኑ የተጠቀሱት ማስረጃዎች የሚያስረዱ በመሆኑ” የሚል ናቸው፡፡

የእምነት ወይስ የእውነት ቃል?

ሳይቤሪያ (የማዕከላዊ ጨለማ እስር ቤት) ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ለምርመራ ወጥቶ ሲመለስ ክፍሉ ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች በሙሉ የሚጠይቁት የመጀመሪያው ጥያቄ “አመንክ?” የሚል ነው፡፡ ታሳሪዎቹ ስለምርመራው የሚያውቁት ነገር ስላለ አይደለም ይህንን ጥያቄ የሚጠይቁት፡፡ ነገር ግን የማዕከላዊ ምርመራ በተፈጥሮው፣ በተለይ በሽብር ለተጠረጠረ ሰው “አንዳች ወንጀል እመን” በሚል ስለሆነ ነው፡፡ ሒደቱም፣ በዱላ ነው፡፡ ማዕከላዊ ቆይተው ክስ የተመሰረተባቸው ብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች ፍርድቤት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ “ተከላከሉ” የሚባሉት ለፖሊስ የሰጡት የእምነት ቃል ነው፡፡ ፖሊስ በሥነ ስርዓት ሕጉ ቁጥር 27 መሠረት የተጠርጣሪ ቃል የሚቀበልበትን ሰነድ ሲያስፈርም “… ይህንን በነጻ የሰጠሁትን የእምነት ቃሌን አንብቤ ወይም ተነቦልኝ ፈረምኩ” የሚል ዓ/ነገር ከግርጌው ይጨምርበታል፡፡

ማዕከላዊ ውስጥ የተከሳሽን ቃል በነጻ አእምሮው በፈቃደኝነቱ እንዲሰጥ ማድረግ ነውር ነው፡፡ አንድ ሰው ማዕከላዊ ውስጥ ሲመረመር፣ ክብሩ በስድብ ተዋርዶ፣ እየተደበደበ ነው፡፡ የሥነ ስርዓት ሕጉ አንቀጽ 27/2 ‹ማንኛውም ተጠርጣሪ ለፖሊስ ቃሉን ሲሰጥ በነጻ ፈቃዱ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት፤ ቃል ያለመስጠት መብቱም የተጠበቀ እንደሆነ› ይደነግጋል፡፡ ይህን ግን የማዕከላዊ ፖሊሶች የሚያውቁት አይመስልም፡፡



እኔ ላይ የደረሰው ብቻ ሕግ ለይስሙላ የሚወጣባት እንጂ በሕግ አስከባሪው አካል እንኳን የማይከበርባት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምንኖር ያሳያል፡፡ ማዕከላዊ ውስጥ ቃሌን ለፖሊስ ስሰጥ እንኳን እንደዕቅድ ይዤ ልንቀሳቀስባቸው፣ በመርሕ ደረጃ እንኳን የምቃወማቸውን ነገሮች “አዎ፣ ላደርግ አስቤ ነበር (ማለትም ‹አመፅ ላነሳሳ ጽፌያለሁ›)” ብዬ መርማሪ ፖሊሶች ሲያሻቸው እኔ የተናገርኩትን ወንጀል ሊሆን በሚችልበት መንገድ እየጠመዘዙ፣ ሲያሻቸው ደግሞ ጭራሹኑ እኔ ያላልኩትን ፈጥረው እየጻፉ ያመጡትን የእምነት ቃል አስፈረምውኛል፡፡ ሲደበድቡኝ የከረሙት ሕሊናቸውን በወር ደሞዝ የሸጡ መርማሪዎቼ ያለምንም የሕሊና ወቀሳ የእኔ ቃል ከተባለው ከራሳቸው ቃል ግርጌ “የእውነት ቃሌ ነው” ብለው ጽፈውበታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምንም እንኳን በማዕከላዊ የተጠርጣሪ ቃል በነጻ እንደማይገኝ ከበቂ በላይ በብዙ ተከሳሾችን ጉዳይ በመመልከቱ የሚረዳ ቢሆንም፣ መረዳት ስላልፈለገ “አምኗል” ብሎኛል፡፡ እርግጥ ነው አምኛለሁ፤ በኃይል ፊት ጀግና መሆን ስላልቻልኩ ያላሰብኩ፣ ያላደረግኩትን አምኛለሁ፡፡ እምነቴ ግን እውነቴ አልነበረም፡፡ ወትሮም እኔ የኃይል ትግል ውስጥ አይደለሁምና ኋላም ሆነ ወደፊት በኃይል ፊት የመጀገን ጀብደኛ ሕልም የለኝም፡፡ እስከአቅሜ ጠብታ ድረስ ለፍትሐዊነት የምታገለው ስመታ እየወደቅኩ ነው፤ እረፍት ሳገኝ እየተነሳሁ!

ፍ/ቤቱም ይሁን ከሳሼ መንግሥት ግን መከላከል ሳያስፈልገኝ ቃሉ የኔ አለመሆኑን ሊረዱ የሚችሉባቸው በርካታ ዕድሎች ነበሯቸው፡፡ ጥቂቶቹን ቀጥሎ እንመለከታለን፣

Wednesday, February 3, 2016

የአንድ ሰው ኃይል፤ በአንዲት ሴት ገድል ሲፈተሽ



በበፍቃዱ ኃይሉ

አንድ ሰው ብቻውን የሚወስደው እርምጃ፣ እሺታው ወይም እምቢታው ለብዙኃን ለውጥ ያመጣ ይሆን?

ልክ የዛሬ 97 ዓመት (ጥር 26፣ 1905) አላባማ/አሜሪካ ውስጥ ሮዛ ፓርክስ ስትወለድ፣ ከ97 ዓመት በኋላ እና ከትውልድ አገሯ ብዙ ሺሕ ማይሎች እና ሦስት ትውልዶች በላይ ርቄ የምገኘው እኔ ታሪኳን በጨረፍታ ለመጻፍ የኮምፒዩተር የቁልፍ ሰሌዳ እንደምነካካ ማን ሊገምት ይችላል? የአንዲት ነጠላ ሮዛ፣ የአንዲት ነጠላ ቀን፣ ነጠላ እምቢታዋ ግን ይህንን የማይገመት ታሪክ ሊፈጥር ችሏል፡፡

ሮዛ ፓርክስ የዛን ዕለት “እምቢ” ባትል ኖሮ፣ ምናልባትም የጥቁሮች የሲቪል መብቶች ትግል ባልታወቀ አቅጣጫ ሊጓዝ ይችል ነበር፡፡ ምናልባትም ደግሞ ዛሬ በሠላማዊ ታጋይነቱ አርኣያ የምናደርገው ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) ጭራሹን ይህንን መክሊቱን የሚያወጣበት አጋጣሚ ሳያገኝ ተድበስብሶ ያልፍ ነበር፡፡

ቀኑ ኅዳር 21፣ 1948 ነበር፤ ሐሙስ ዕለት፡፡ ጀምበር ስታዘቀዝቅ ሮዛ ከሥራዋ ወጥታ ወደቤቷ ለመሄድ የሞንቶጎምሪ ከተማ የሕዝብ አውቶቡስን ክሊቭላንድ ጎዳና ላይ ተሳፈረች፡፡ የአውቶቡሱ ሹፌር “እሱ በሚነዳው አውቶቡስ ሁለተኛ አልሳፈርም” ብላ የማለችለት ጄምስ ብሌክ መሆኑን ሮዛ አላወቀችም ነበር፡፡ ከ12 ዓመት በፊት ሮዛ፣ ጀምስ በሚነዳው አውቶቡስ ውስጥ ገንዘቧን ከፍላ በመሳፈር ለጥቁሮች በተከለለው ቦታ ሄዳ ስትቀመጥ፣ ‹የገባሽበት የፊተኛው በር የነጮች መግቢያ ነው ውጪና መልሰሽ በኋላ በር ግቢ› ሲላት “አላደርገውም” በማለት በዝናብ ውጪ ቆማ ጥሏት ሄዷል፡

የሞንቶጎምሪ ከተማ አውቶቡሶች በዘመኑ ሕግ መሠረት የአውቶቡስ ውስጥ መቀመጫዎች የጥቁሮች እና የነጮች ተብለው ተከፋፍለው ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራት መደዳዎች ለነጮች ብቻ የተከለሉ ናቸው፡፡ ለጥቁሮች ወደኋላ ላይ አንዳንድ ወንበሮች ይተዉላቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳን 75 በመቶ የሚሆኑት ተሳፋሪዎች ጥቁሮች ቢሆኑም መሐል አካባቢ ያሉት ወንበሮች ነጮች የራሳቸውን መደዳ እስኪሞሉ ድረስ ጥቁሮች እንዲቀመጡ ይፈቀድ ነበር፡፡ በልምድ ግን የአውቶቡስ ውስጥ ተቆጣጣሪዎች ባሱ ውስጥ ያሉ ነጮች በሙሉ መቀመጫ እስኪያገኙ ድረስ ጥቁሮችን ከወንበራቸው ያስነሷቸው ነበር፡፡ ይህ ልምድ እና ኢፍትሓዊ ሕግ ግን ለእምቢ ባይዋ ሮዛ ፓርክስ እያደር የማይለመድ ነገር ነበር፡፡ ለሮዛ ፓርክስ በልጅነቷ አውቶቡሶች “የጥቁር” እና “የነጭ” ሁለት ዓለም መኖሩን ያረዷት የልዩነት ማሳያዎቿ ናቸው፡፡

ጄምስ ብሌክ ዝናብ ላይ ጥሏት ከሄደ ከ12 ዓመታት በኋላ ሹፌሩ እሱ መሆኑን ሳታውቅ ሮዛ ፓርክስ ጄምስ በሚያሽከረክራት አውቶቡስ ውስጥ ገባች፡፡ ለ“Colored” (ነጭ ያልሆኑ) ተሳፋሪዎች መቀመጥ የሚፈቀድላቸው ቦታ ላይ ሄዳ ተቀመጠች፤ ከሷ ሌላ ሌሎች ሦስት ጥቁሮችም እዚያው ተቀምጠዋል፡፡ ሌሎች ሁለት ነጮች ባሱ ከሞላ በኋላ ገቡ እና ቆሙ፡፡ ጀምስ ብሌክ መጥቶ “Colored” የሚል ምልክት ያለበትን ተንቀሳቃሽ መጠቆሚያ ወደኋላ አንቀሳቀሰውና ሮዛ ፓርክስና ሌሎቹ ጥቁሮች ለነጮቹ ወንበራቸውን እንዲለቁ ጠየቃቸው፡፡ ሮዛ ፓርክስ ያንን ቅፅበት ከዓመታት በኋላ ስታስታውሰው እንዲህ ነበር ያለችው፤

“When that white driver stepped back toward us, when he waved his hand and ordered us up and out our seats, I felt a determination cover my body like a quilt of a winter night.” (“ያ ነጭ ሹፌር ወደእኛ መጥቶ ከወንበራችን ሊያስነሳን እጆቹን እያወናጨፈ ሲያዘን፣ የቁርጠኝነት ስሜት ልክ እንደክረምት ድሪቶ እላዬ ላይ ሲከመር ነው የተሰማኝ፡፡”)

“ተነሱ” ለሚለው ትዕዛዝ ሌሎቹ ሦስት ጥቁሮች በእሺታ ወንበራቸውን ለቀቁ፡፡ ሮዛ ፓርክስ ግን በመነሳት ፈንታ ወደመስታወቱ ጥግ ወዳለው ወንበር ፈቀቅ አለች፡፡