Monday, December 21, 2015

ሕገ መንግስታዊነት እንዲሰፍን የሚፈሰው ተጨማሪ ደም ይገደብ!

የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች በኦሮሚያ ክልል በርካታ ወረዳዎችና ከተሞች  እያቀረቡት ያለው ሠላማዊ ጥያቄ በሰከነ መንገድ መልስ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ ሀይል በመጠቀም ጥያቄውን ለማፈን እየተሞከረ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ለቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ሰሞኑን ከሚወጡት መግለጫዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ቃለመጠይቆች እንደተረዳነው  ጥያቄዎቻቸውን በሃይል ለመመከት ከመዛትና ዜጎችን ከሰው በታች አውርዶ ቁጣን በሚጋብዝ መልኩ ከመጥራት በዘለለ ሀላፊነት እንደሚሰማው አካል ለችግሩ መፍትሔ  ለመፈለግ ዝግጁነት እንደሌለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሌም እንዲከበር የምንጠይቀውን የሀገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ-መንግስት የሚጻረር ነው፡፡
በዚህ ሂደት በጥቂቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የሕገ-መንግስቱ አንቀጾች ተጥሰዋል
1.    የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 15 የሕይወት መብት
‹‹ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡›› ቢልም ከሰላማዊ ሰልፉ ጋር በተያያዘ ከ8 ዓመት ልጅ አንስቶ እስከ የ80 ዓመት አዛውንት ድረስ ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፤ እስከዛሬ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በሶስተኛ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም ጉዳዬን  በቅርበት የሚከታሉ ሰዎች እንደዘግቡት ወደ መቶ እየተጠጋ ይገኛል፡፡
2.   የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 15 የአካል ደኅንነት መብት
‹‹ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመጠበቅ መብት አለው፡፡ ›› አሁንም ከሰላማዊ ሰልፉ ጋር በተያያዘ በጥይት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ ድብደባ እና አላግባብ አንግልት የደረሰባቸውንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡
3.   አንቀጽ 24.1 የክብርና የመልካም ስም መብት
‹‹ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው፡፡ ›› እየሆነ ያለው ዜጎችን አጋንንት እያሉ መጥራት፣ ጥፋተኛ ተብለው በሕግ ያልተፈረደባቸውን አሸባሪ እያሉ ክብራቸውን በሚዲያ መግፈፍ ነው፡፡
4.   አንቀጽ 30.1 የመሰብሰብ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት
‹‹ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሔድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡ ››  ቢልም መንግስት ይህን የህገ መንግሰቱን አንቀጽ በመጣስ ብዙ ሰብዓዊ ጉዳቶችን አድርሷል፡፡

ዜጎች ለመረጃ ቅርብ በሆኑበት በዚህ ጊዜ መንግስት እያደረጋቸው ያሉትን ተግባራት መካድ፣ እንዲሁም እንደሌሉ አደርጎ ለማስተባበል መሞከር ብዙ ኃላፊነት የሚጠበቅበት መንግስት የሚያሰገምትና ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ይህ የመንግስት ግዴለሽነት ብዙኃን ዜጎችን እየገፋ ከመስመር እያስወጣ ነው፡፡ ሰላማዊውን የሕዝብ እንቅስቃሴ ወደ አመጽ እና ወደአልተፈለገ ዕልቂት ከመግፋት ይልቅ የተቀናጀ የጋር ማስተር ፕላኑን  መሰረዝ፣ በዚህ ሒደት ጥፋት የፈጸሙ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ፣ የግል ተበዳዮችን  መካስና ሌሎች አስፈላጊ የመፍትሔ እርምጃዎችን ሁሉ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡  ሁልጊዜም እንደምንለው በሰላማዊ መንገድ የመብት ጥያቄ ማቅረብ ወንጀል አይደለም፡፡  መንግሰት በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ከሚጠይቁ ዜጎች ጋር እልህ አይጋባ ፣ ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው ይከበሩ ፣ የመብት ጥሰት ድብደባ እና ግድያው ይቁም፡፡  ሕገ-መንግስታዊነት የታሰርንለት፣ ከሀገር የተሰደድንለት፣ ብዙ ዋጋ የከፈልንበትና አሁንም እየከፈልንበት ያለ ዐሳብ ነውና  በሀገሪቱ ህጋዊነት እንዲሰፍን ህይወታቸውን እስከመስጠት ድረስ ዋጋ ለከፈሉ ዜጎች ክብር እንሰጣለን፡፡ ለሕገ መንግስታዊ ስርዓት መስፈን ዜጎች የከፈሉት ዋጋ እጅግ ብዙ እና ከበቂ በላይ ነውና ተጨማሪ ሰብዓዊ ዋጋ መክፈል ሳያፈልገን ሕገ መንግስቱ እንዲከበር አንጠይቃለን፡፡

ሕገ-መንግስቱ ይከበር!  

No comments:

Post a Comment