Monday, August 17, 2015

አጥናፉ እና ከማሳቅ ውጭ ሌላ ነገር የማያስረዱት ‹ማስረጃዎች›

‹‹5ኛ ተከሣሽ አጥናፉ ብርሃኔ አያሌው፡- ከግንቦት 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለሽብርና ለአመፅ በተደራጀው ህቡዕ ቡድን  ውስጥ መስራችና አባል በመሆን የህቡዕ ቡድኑ የተቀበለውን የግንቦት ሰባት እሥትራቴጂና አካሄድ በመቀበል ከሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር ካሉ የህቡዕ ቡድኑ መዋቅር አመራሮች ጋር በመገናኝት ተልዕኮና መመሪያ በመውሰድ በመመሪያው (sic) መሣካት የተለያዩ ሥልጠናዎች በመሠልጠንና በማሠልጠን ማለትም በህቡዕ ቡድኑ መካከል የሚደረገውን የመልዕክት ልውውጥ የመንግስት የፀጥታ አካላት እንዳይደርሱባቸው በመደበቅና በስውር በመገናኝት Security in box (sic) የህቡዕ ቡድኑ አመራሮች የሚሰለጥኑትን ስልጠና በመሰልጠን፡ በተጨማሪም ሀገር ውስጥ አመፅ እንዴት ማቀጣጠል እንደሚቻል የአመፅ መገልገያ መሣሪያዎች ቦንብ፤ ጭምብል፣ ድንጋይ፣ የፀጥታ አካልን በዘር በመለያየት የፀጥታ ኃይሎችን መተንኮስ የሚል ሥልጠና በመውሰድ ሁለንተናዊ የትግል አቅጣጫ የሚለውን የግንቦት ሠባት እስትራቴጂ በመቀበልና በማሠልጠን የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ ተይዟል፤››
ይህ ጦማሪ አጥናፉ ብርሃኔ ‹የህብረተሰቡን ሰላም ወይም ጤና ለመንሳት በማሰብ የሽብርተኝነት ድርጊት ሞክሯል፣ አቅዷል፣ አሲሯል፣ አነሳስቷልና ተዘጋጅቷል› በሚል ስለ ፀረ-ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3(2) እና አንቀፅ 4 ጥሷል በሚል በከሳሽ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ የቀረበበት ክስ ነው፡፡
ጉዳዩን እያየ ያለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ 19ኛ ወንጀል ችሎትም ከሳሽ ያቀረባቸውን የሰነድ ማስረጃዎች (በነገራችን ላይ ከሳሽ በአጠቃላይ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎችን ብቻ ነው፡፡ የቀረቡት የሰው ምስክሮች የሰነድ ማስረጃዎቹን ትክክለኛነት ለማስረዳት ብቻ የቀረቡ ናቸው) መርምሮ አጥናፍ ብርሃኔ መከላከል ሳያስፈልገው በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕግ 141 መሰረት ‹ከክሱ ነፃ መሰናበት አለበት› ወይስ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ 142 መሰረት ‹ክሱን ሊከላከል ይገባዋል› የሚለውን ለመወሰን ቀጠሮ ይዟል፡፡ እኛም አጥናፉ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች ከቀረበበት ክስ አንፃር መመልከቱ የክሱን ምንነትና ሊጠበቅ የሚችለው/የሚገባው ብይን ምን መሆን አለበት የሚሉትን ጉዳዮች ለመመለስ ይህን ፅሁፍ አቅርበናል፡፡
***
ኢንተርፕረነሩ Richard Branson እና ሙዚቀኛው  Peter Gabriel በተለያዩ ጊዜያት የግል ውይይት ሲያደርጉ አንድ ጉዳይ ሲያሳስባቸው ነበር፡፡ በሁሉም የዓለም ክፍል አዛውንቶች (elders) የተከበሩና በማህበረሰቦች ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች እንደዋነኛ የችግር መፍትሄዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፤ ታዲያ አሁን ባለው አንድ ትልቅ መንደር (global village) እነዚህ ሽማግሌዎች ዓለም ላይ ላሉ ችግሮች መፍትሄ ይሆኑ ዘንድ ስመጥር የሆኑ ታላላቅ ሰዎች አንድ ላይ ሁነው ለምን አይሰሩም; የሚለው ጥያቄ፡፡ ለጥያቄያቸው መፍትሄ ይሆን ዘንድም ይሄን ሃሳባቸውን ለኔልሰን ማንዴላ አቀረቡላቸውና በጁላይ 2007 ሽማግሌዎቹ (The Elders) የተባለው ዓለማቀፍ ቡድን ተቋቋመ፡፡ ቡድኑ በዋነኝነት የያዘው ዓላማም ዓለማቀፍ የሰው ልጆችን ትስስር ማበልፀግና ለዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መከበር መቆምን ሆነ፡፡ ይህ ቡድን ባለፉት 8 ዓመታት የተለያዩ ሰዎችን ወደ አባልነት እየቀላቀለ ከፍታውን እየጨመረ የመጣ ሲሆን በጁላይ 2013 ፓኪስታናዊቱን የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ኮከብ Hina Jilaniን በአባልነት አካቷል፡፡ ጂላኒ ሽብርተኝነትን አምርረው ከሚታገሉ ዓለማቀፍ ስብዕናዎች አንዷ ሲሆኑ፤ ለሽብርተኝነት ዋነኛ መታገያው ቦታም ፍርድ ቤቶች መሆን እንዳለባቸው ሲገልፁ፡
"When you put them [terrorists] on trial, you show the wickedness of their crime. Once it becomes abundantly clear that the terrorists' victims are almost entirely comprised of Pakistani civilians, only then will sympathy for their cause be lost. We have to deal with terrorism as a criminal element."
ነበር ያሉት፡፡ ጂላኒ የሰው ልጆችን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሰው ይሁኑ እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እርሳቸው የፃፉትን ፅሁፍ ይዞ መገኝት የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመፈፀም እንደመዘጋጀት ተቆጥሮ በማስረጃነት ለፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡ ማን ላይ? አጥናፉ ብርሃኔ ላይ፡፡ አጥናፉ ብርሃኔ ላይ በከሳሽ በዋነኛነት የቀረበው የሰነድ ማስረጃ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ በኖቬምበር 2013 ‹International Human Rights Law› በሚል ርዕስ ያሳተመው መፅሃፍ ሲሆን፤ በተለይም ከላይ በመግቢያችን የጠቀስናቸው ወ/ሮ ሂና ጂላኒ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ ናቪ ፒላይ እና የሂውማን ራይትስ ዎች ዋና ሃላፊ ኬኔት ሮዝ ለዚህ መፅሃፍ ሁለተኛ እትም (Second edition) የፃፉት መግቢያዎች (prefaces) ናቸው ከነእንግሊዝኛ ቅጃቸው በፍርድ ቤቱ የስራ ቋንቋ በአማርኛ ተተርጉመው ‹ከአጥናፉ ብርሃኔ ቤት የተገኙ የሽብር ሰነዶች› ተብለው የቀረቡት፡፡ ይህ ብዙ ሰዎችን ሊያስገርም ይችላል፤ ግን መራራው እውነት ይህ ነው፡፡
Aristotle, Eminem and Homer Simpson
ታላቁ Aristotle ከሁለት ሽህ ዓመታት በፊት ‹የሴቶች የጥርስ ብዛት ከወንዶች በቁጥር ያንሳል› ማለቱን ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው እጅግ የሚያስቅ ቢሆንምና ብዙዎቹም አሪስቶትልን ሲተቹ ይህን ሃሳቡን የሚመዙ ቢሆንም ነገር ግን አሪስቶትል ሪሂቶሪክን አስመልክቶ ከሚጠቀሱ ድንቅ አዕምሮዎች አንዱ ነው፡፡ … ለዚህ ዘመን ወጣቶች አዲስ ያልሆነ ስም ነው፡፡ በዘፈኖቹ ‹ብልግናን› ይሰብካል እየተባለም ቢተችም ቀልብ ሳቢነቱ ግን ብዙም የማይካድ ነው፡፡ … ላለፉት 35 ዓመታት እጅግ የተወደደው የሲምፕሰን ቤተሰብ አባዎራ (ገፀ ባህርይ) ሲሆን በተቃራኒው በሆሜር ሲምፕሰን ንግግሮች ተከፍተው ፕሮግራሙን በሀገራቸው እንዳይታይ የከለከሉ ሀገሮችም አሉ፡፡ Jay Heinrichs የተባሉ ፀሃፊም "Thank You for Arguing: What Aristotle, Eminem and Homer Simpson Can Teach Us About the Art of Persuasion" ባሉት መፅሃፋቸው ‹ተናግሮ የማሳመንን› ጥበብ ከነዚህ ሶስት የተለያዩ እንዴት መማር እንችላለን በማለት እጅግ የተወደደላቸውን መፅሃፍ ፅፈዋል፡፡ የእድል ነገር ሆነና ከዚህ መፅሃፍ ላይ የተወሰደ (adapted) ፅሁፍ (ስለ ‹ድርድር እና ተናግሮ የማሳመን ጥበብ› የሚያትት) አጥናፉ ብርሃኔ ቤት ተገኝ፤ አጥናፉ የሽብር ድርጊት ሊፈፅም በዝግጅት ላይ እንደነበር ያስረዳልም ተብሎ ለፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህ ፅሁፍ ቤቱ ተገኝቷል ተባለው አጥናፉ ላይ ብይን ለማሳለፍ በዛውም Aristotle፤ Eminem እና Homer Simpson በኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ህግ ከለላ ለመወሰን ቀጠሮ ይዟል፡፡
Internet Security
አጥናፉ የአይቲ ባለሙያ ከመሆኑ አንፃር ከኢንተርኔት እና መሰል ከሙያው ጋር የተገናኙ ነገሮችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉ የሚጠበቅ ነው፡፡ የአይቲ ባለሙያነቱ ግን በመጨረሻ አስገራሚ ነገር ይዞ መጣ፡፡ ክስ፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ማስረጃዎች በተጨማሪ አጥናፉ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች በሙሉ ከኢንተርኔት እና ኢንተርኔት ሰኪዩሪቲ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ማለትም መፅሃፍት፡፡ ፖሊስ እንደለመደው ካሰረ በኋላ ማስረጃ በመፈለግ ጥበቡ የአይቲ ባለሙያው አጥናፉ ቤት ብዛት ያላቸው ከኮምፒውተር ጋር የሚገናኙ መፅሃፍትና ፅሁፎች አገኘ፡፡ ስለኢንክሪፕሽን እና ጠንካራ ፓስዎርድ ስለመፍጠር (password generation) የሚያትቱትን ገፆች ኮፒ በማድረግ አጥናፉ ‹የሽብርተኝነት ድርጊት ሊፈፅም ሲዘጋጅ ያዝነው› ለሚለው ክሱ በማስረጃነት አቀረባቸው፡፡ ጠንካራ ፓስወርድ መፍጠር የሁሉም ኢንተርኔት ተጠቃሚ ፍላጎት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ እንዴት ጠንካራ ፓስወርድ መፍጠር ይችላሉ የሚል መፅሃፍ ይዞ መገኝት ደግሞ አሁን ባለው አካሔድ ለሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ማስረጃ ሁኖ የሚቀርብ ነገር ነው፡፡ ይሄ እብደት ቢመስልም እውነት ሁኖ አጥናፉ ላይ በዋነኛ ማስረጃነት የቀረበ ጉዳይ ነው፡፡ ስለኢንተርኔት ሰኪዩሪቲ ለማወቅ መጣር ኢንሰኪዩር ያደርጋል ነው ነገሩ፡፡
‹ሥልጠና›
ስለ ኢንተርኔት ሰኪዩሪቲ አንብበሃል - ሰልጥነሃል (‹የሽብር ሥልጠና›) ከሚለው አስገራሚ ክስ ባለፈ አጥናፉ ላይ የቀረበ በጣም አስገራሚ የሥልጠና አይነትም አለ፡፡ የከሳሽ ክስ እንዲህ ይለዋል፡
‹‹… በተጨማሪም ሀገር ውስጥ አመፅ እንዴት ማቀጣጠል እንደሚቻል የአመፅ መገልገያ መሣሪያዎች ቦንብ፤ ጭምብል፣ ድንጋይ፣ የፀጥታ አካልን በዘር በመለያየት የፀጥታ ኃይሎችን መተንኮስ የሚል ሥልጠና በመውሰድ …››
ይሄን የክስ ጭብጥ በሕግ አግባብ እና ለዚህ በማስረጃነት የቀረበውን ሰነድ መመልከቱ ነገሩን የበለጠ ግልፅ ስለሚያደርገው እንዲህ እንየው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 በተሰጠው አስገዳጅ ትርጉም የመስጠት ስልጣን በመዝገብ ቁጥር 77842 እና 77097 ላይ እንዳስረገጠው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 27 (2) መሰረት ለፖሊስ ተሰጠ የተባለ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 35 ለጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት የሚሰጥ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል እንዲሁም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 134 መሰረት ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚሰጥ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል ‹‹ተጠርጣሪው/ተከሳሹ ‹ጥፋተኛ ነኝ› ስላለ ብቻ ጥፋተኛ ነው ማለት አይደለም› ይልቁንም ቃሉን የሰጠበት መንገድና ጥፋተኛ ነኝ ያለበት ጉዳይ ተመርምሮ ነው ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባው›› በማለት አመክኖያዊውን ጉዳይ የሕግ መሰረት አስይዞታል፡፡
የአጥናፉን ጉዳይ ስንመለከት አጥናፉ ላይ ከላይ የተጠቀሰውን ‹ሥልጠና› ወስዷል ለማለት በማስረጃነት የቀረበው አጥናፉ በፌደራል ፓሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) በነበረበት ወቅት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 27 (2) መሰረት ለፖሊስ ሰጠው የተባለ ቃል ሲሆን፡፡ በመጀመሪያ አጥናፉ እንዲፈርም የተደረገው በሌሊት በተደጋጋሚ በተፈፀመበት ድብደባና እና ማሰቃየት (‹‹ጦማር የሚለው ምህፃረ ቃል ነው፤ ስለዚህ ‹ጦ› ምን እንደሆነች፣ ‹ማ› ምን እንደሆነች እንዲሁም ‹ር› ምን እንደሆነች ተናገር›› የሚለውን ጨምሮ) ምክንያት ሲሆን ይህ ‹ሰነድ› ከኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 19 (5) እና ከራሱ ከወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 27 (2) ጋር በግልፅ የሚጋጭ ነው፡፡ ምክንያቱም አጥናፉ በሕግ የተሰጡትን የታሰሩ ሰዎች መብቶት (በተለምዶ Miranda Rights የሚባሉት) ሙሉ ለሙሉ ተነፍጎት የተገኘ በመሆኑ፡፡
አስገራሚውና ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ በድብደባ አጥናፉ ‹የፈንጅ እና የአመፅ ስልጠና ወስጃለሁ› በማለት እንዲፈርም የተደረገው ቃል ላይ ይህን ስልጠና ሰጥቷል የተባለው ድርጅት ነው፡፡ ለአጥናፉ በክሱ የተጠቀሰውን ስልጠና ሰጥቶታል የተባለው ድርጅት በ1968 የተመሰረተው እና መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው International Research and Exchanges Board (IREX) ነው፡፡ ትምህርት፣ ሚዲያ እና ሲቪል ሶሳይቲን ዋነኛ አጀንዳው በማድረግ ዓለማቀፍ ልማትን ማምጣት ዓላማው ያደረገው IREX ለአጥናፉ የአመፅ ስልጠና ሰጥቶታል ተብሏል እንግዲህ (በነገራችን ላይ … ማን እንደሆነ ማወቅ ፍርድ ቤቱ በራሱ ቅቡል ግምት (judicial notice) ሊይዝበት የሚገባ ጉዳይ ነው)፡፡ ይህ እጅግ የሚያስቅም ጉዳይ ነው፡፡ ‹የአመፅ እና የተቀጣጣይ ፈንጅ ስልጠና IREX ከተባለ ድርጅት በማግኝቴ ጥፋተኛ ነኝ› የሚለው ቃል ‹እኔና ጓደኞቼ ፀሃይን ጨምሮ 10 ሌሎች ከዋክብትን ሰርቀን ወደ ውጭ ሀገር በመላካችን ጥፋተኛ ነኝ› ከሚለው ቃል በምን ይለያል; ከዚህ የበለጠ የሚያስቅ ነገርስ ምን ይኖራል; ፖሊስም ይሄን እንደማስረጃ ብሎ ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ ለፍርድ ቤቱ ያለውን ንቀት ቢያሳይ እንጅ ሌላ ነገርን የሚያመላክት አይደለም፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የሰበር ውሳኔዎችም ፍርድ ቤቶች እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የተከሳሾችን መብት እንዲያስከብሩ በማሰብ የተሰጡ አስገዳጅ ትርጉሞች ናቸው፡፡

እንግዲህ አጥናፉ ብርሃኔ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች (ማይክሮ ኢኮኖሚክስ ደብተሩን ጨምሮ) አስገራሚነታቸው እና አስቂኝነታቸው እጅግ የበዙ ከመሆናቸው ባለፈም ፍርድ ቤቶች እንዲህ አይነት ማስረጃዎች እየቀርቡላቸው የተከሳሹን ንፅህና ከማዎጅ ያነሰ ውሳኔ መስጠት ያስችላቸዋል ወይ ያስብላል፡፡ አጥናፉስ ንፁህ ሰው ከመባል በቀር ምን ሊባል ይችላል; ምንም! አጥናፉ ‹ተከላከል› ቢባል የሚከላከለውስ ምኑን ነው? Hina Jilani እና Navenatum Pillay አሸባሪ አለመሆናቸውን ነው? ወይስ Homer Simpsonን ምስክርነት ሊጠራ ነው? ወይስ የአይቲ ባለሙያ አይደለሁም ብሎ ሊከላከል ነው? ወይስ ‹IREX የኢትዮጵያ መንግስት ጨምሮ በመላው ዓለም ከተለያዩ አካላት ጋር ዓለምን መልካም ለማድረግ የሚሰራ ድርጅት ነው› ብሎ ነው? … አዎ አጥናፉ ነፃ ሰው ነው!
አጥናፉ ብርሃኔ

No comments:

Post a Comment