Monday, March 25, 2013

#Ethiopia: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የመደራደር አቅማቸው (ክፍል 1)



በዳዊት ተ. ዓለሙ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የመደራደር አቅም (Bargaining power) ለዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ስርአት ግንባታም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ ተመስርቶ ለሚደረጉ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ስኬታማነት ወሳኝ ነው:: ሁሉን የፖለቲካ ቡድኖች ያማከለ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ምስረታም ሆነ የተቋማቱ ዘላቂነት በዋናነት የሚወሰነው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚኖራቸው የመደራደር አቅም ልክ ነው:: ሚዛናዊ ያልሆነ የመደራደር አቅም ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መሀካል በሚደረግ ስምምነት የሚፈጠሩ ተቋማትና ስርዓቶች በአመዛኙ ሊያስጠብቁ የሚችሉት ይበልጥ ጠንካራ የመደራደር አቅም ያለውን የፖለቲካ ኃይል ፍላጎቶች ነው:: ይበልጥ የዴሞክራሲ ስርአት ሰፍኖባቸዋል በሚባሉ ሀገራት ውስጥ በትንሹ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑና የተቀራረበ የመገዳደር አቅም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገኙባቸው ናቸው:: የተቀራረበ የመገዳደር አቅም ባላቸው ፓርቲዎች (መሪዎች) ድርድር የሚመሰረቱ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በአብዛኛው የሁሉንም ፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎቶች የማንጸባረቅ እዳላቸው የሰፋ ነው:: ለምሳሌ ያህልም ሮበርት ፑትናም Making Democracy Work ብሎ በሰየመው የምርምር ስራው ለ20 አመታት የኢጣሊያንን ፖለቲካ በቅርብ ከተከታተለ በኋላ ይህንን እውነታ በሰፊው አመልክቷል:: ስለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቀራረበ የመደራደር አቅም ለሰላማዊ ፖለቲካና ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ወሳኝ ነው::

በሀገራችን የፖለቲካ ቡድኖች (ፓርቲዎች) የመደራደር አቅማቸው የማይመጣጠን በመሆኑ የመገዳደር ፖለቲካ ባህላችን በአፈሙዝ የበላይነት የሚደመደምበት እንዲሆን አድረጎታል:: በዚህም የተነሳ በየወቅቱ ሲገነቡ የነበሩት ተቋማት በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ጥቅምና ህልውና የሚያስጠብቅ ባህሪና ቁመና የተላበሱ ሆነዋል:: የፖለቲካ ፓርቲ እሳቤና ተሞክሮ የሀገራችን የፖለቲካ ባህል ከተዋወቀበት ጊዜ አንስቶ የተመሰረቱ ፓለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም ሊያስብል በሚችል መልኩ የመደራደር አቅማቸው በጉልበት ላይ ወይም በተወሰ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተነጠለጠለ ነው:: ይህም በመሆኑ በሀገራችን ደካማ ወይም ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የራቀው ፖለቲካዊ ባህል እንዲሰራፋ ሆኗል::

የመደራደር  አቅም ሲባል

የመደራደር አቅም (Bargaining power) በተለያዩ ጸሃፊዎች በተለያዩ የአረዳድና እውቀት ዘርፎች የተለያየ ትርጓሜ ተሰጥቶታል:: በግርድፉ የመደራደር አቅም ሲባል በአንድ በተወሰነ ሁኔታ ላይ አንድ ተቋም/ግለሰብ በሌሎች ተቋማት/ግለሰቦች ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የሚያስችለው አንጻርዊ የተቋማት/ግለሰቦች አቅም ማለት ነው:: ጊዲዮን ዳሮንና እቲኢ ሰንድ በጋራ ባዘጋጁት መጸሃፍ (Poltical Bargaining: Theory, Practice and Process) ፖለቲካል የመደራደር (Political Bargaining) አቅምን ትርጓሜ ሲሰጡት:- „a tangible effort made by two or more agents with some conflict of interests to reach an agreement over an authoritative allocation of scarce resources“ በማለት ነው:: በዚህ አረዳድ ውስጥ ፖለቲካ የታየበት አግባብ ወሳኝ ሃብቶችን ስርጭት መሰረት ያደረገ ነው:: ይህም ከክላሲካል „ፖለቲካ“ ትርጓሚ ማለትም „ፖለቲካ ማለት ከስልጣን ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲሆን ስልጣንም የሀብት ክፍፍልን የሚመለከት ነው“ ከሚለው ዕሳቤ የመነጨ ነው:: ስለዚህም የመደራደር ሂደት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ወይም ቡድናዊ ፍላጎቶችን ለማስታረቅና ስምምነት ላይ የተደረሰበት የወሳኝ ሃብቶች ስርጭት ስርዓት መዘርጋት ማለት ነው:: በዚህም የተነሳ የመደራደር አቅም በፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ የምንረዳበት አግባብ አንጻራዊነትን የሚላበስና ብዙ አላባውያንን (elements) የሚያቅፍ መሆኑን ነው:: የመደራደር አቅም ከሚታይበት አላባውያን መካከል ወሣኞቹ ድርጅታዊ ጥንካሬ፣ ፍላጎቶችን የማስታረቅና ተጽእኖ የመፍጠር አቅም፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለቸው የቅቡልነት ደረጃ፣ፖለቲካል ታክቲክ እንዲሁም ፖለቲካል ውሳኔያቸው ተተንባይነት ነው:: እያንዳንዱን ጉዳይ ብቻ በመያዝ ብዙ ሊያጽፍ ቢችልም፣ በዚህ ጽሁፍ ተከታታይ ጽሁፍ ለሁለት ከፍለን በተወሰነ መልኩ እንደሚከተለው እንዳስሳቸዋለን::  
          

ድርጅታዊ ጥንካሬና የመደራደር አቅም ውስኑነት

ድርጅታዊ አቅም የተለያዩ ፍቺዎች ቢኖሩትም በሶስት ቁምነገሮች ላይ ያተኩራሉ:: እነርሱም የሰው ኃይል፣ አደረጃጀት እና አሰራር ናቸው:: ኢትዮጵያ በፖለቲካ ፓርቲ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ባህል ውስጥ የገባችው የ1960ዎቹንፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ ነው:: ይህም ሁናቴ በኢትዮጵያ ውስጥ የተመሰረቱት ፖለቲካ ፓርቲዎች በግራ ዘመም ባህል በተለይ ደግሞ ጆሴፍ ስታሊን „የሌኒን ፓርቲ“ ብሎ በሰየመው አረዳድ ላይ የተመሰረቱ ናቸው:: ይህ ግራ ዘመም የፓርቲ ፖለቲካ ባህል በፓርቲዎች ርዕዮተ-ዓለማዊ አቋም ብቻ የሚንጸባረቅ ሳይሆን እንደብረት በጠነከረ የፓርቲ ስነ-ስርዓት፣ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ ጥብቅ ከላይ ወደታች የዕዝ ሰንሰለት ጭምር የሚታይ ነው:: በዚህ ፓርቲ ፖለቲካ ባህል መሰረት <ጠንካራና በዲሲፒሊን የታነጸ ድርጅት በማኅበረሰብ ውስጥ ፖለቲካዊ ተቀባይነትን ለማግኘትና በፖለቲካዊ ትግል አሸናፊ ለመሆን ወሳኝ ነው::> ብሎ ያምናል:: ምንም እንኳን የሃገራችን ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ርዕዮተ አለምን የሚከተሉ ቢሆንም ይህ አስተሳሰብ በከፍተኛ ሁኔታ የተጫናቸው ናቸው:: በዚህ የአስተሳሰብ ማዕቀፍ ውስጥ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድርጅታዊ ጥንካሬና የመደራደር አቅም የሚታየው::

እንደማንኛውም ታዳጊ ሀገር ፖለቲካ በአብዛኛው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሰረቱት ዘመናዊ ትምህርት በቀሰሙ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው:: አብዛኛዎቹ ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ የተሳተፉና በተለያዩ የአመራር ደረጃ የነበሩ ናቸው:: ይህም የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ልምድና ዕውቅት እንዲኖሯቸው አስችሏቸዋል:: በሌላ መልኩ ደግሞ አብዛኞቹ አመራሮች በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ተሳታፊ ስለነበሩና እርስ በራሳቸው በአይነ ቁራኛ የሚጠባበቁና በከፍተኛ ጥላቻና ቂም በቀል  ስሜት የተዋጡ እንዲሆኑ ስላረጋቸው ከጊዜያዊ ትብብር የዘለለ በመርህ ላይ የተመሰረት አንድነትን መፍጠር እንዳይችሉ አድርጓቸዋል:: በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እግጅ በጣም ትናንሽ በሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሞላቱ የሚያመለክተው ቁምነገር የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከፍተኛ አመራሮች በራሳቸው ዙሪያ የተገነቡ ፓርቲዎችን እንጂ በመርህ ላይ የተመሰረተና የጋራ ፖለቲካዊ አጀንዳ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ፓርቲዎችን መመስረት አለመቻላቸውን ነው:: ይህም ወደአንድ ላይ መሰባሰብ ቢችሉ ሊያመጡ ከሚችሉት ውጤት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ውጤት እንዲያመጡ ሲያደርጋቸው፤ ልምድ ያላቸው ከፍተኛ አመራሮችም እንዲበታተኑ ሆነዋል::

መሃከለኛ አመራር ደረጃ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው የሰው ኃይል አቅም በጣም ትንሽ ነው:: አንደኛ ተምሯል ከሚባለው አጠቃላይ ኢትዮጵያዊ አንጻር ሲታይ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ሰው እጅግ በጣም አናሳ ነው:: ሁለተኛ ከፍተኛ አመራሮች መሀከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ፓርቲዎች ሲሰነጠቁ ከፖለቲካ ትግሉ የሚርቀው ከሁለቱም ወገን ከቀረው የሰው ኃይል አንጻር በጣም ከፍተኛው ነው:: ይህም የሚታየው ፓርቲዎች ከተሰነጠቁ በኋላ እንደቀድሞአቸው ለመሆን አለመቻላቸው ላይ ነው:: ሶስተኛ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአብዛኛው አቅምና እውቀት ላይ ሳይሆን በጥቅመኝነት (Patronage) ላይ የተመሰረቱ ስለሆነ መካከለኛ አመራሮቹ ደካማ አቅም ያላቸው ይሆናሉ:: በአባላት ደረጃም ቢሆን የሚታየው እውነታ የሰው ኃይል ልማት ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸው አነስተኛ አቅም ነው::

በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀትና አሰራር በጣም ደካማ ነው:: አደረጃጀት በመሰረቱ የመጨረሻ ውጤትን ለማሳካት፣ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ለማስፈን እንደግብአት የሚታይ ነው:: በአብዛኛው የተቃማዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ግልጽነት የጉደለውና የፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸውን ከማሳካት ይልቅ ቁጥጥርና የከፍተኛ አመራሮችን ተክለ-ስብዕና በሚያጎላ መልኩ የሚቀረጽ ነው:: እንደምሳሌ ሊታይ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል የተለያዩ ጥናቶች እንዳመለከቱት አብዛኛዎቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስምና ፖለቲካዊ ፕሮግራም ሳይሆን የመሪዎች ስም ነው በስፋት የሚታወቀው:: አሰራር (internal working system) ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት የፖለቲካ ስራዎቻቸውን እንቅስቃሴዎቻቸውን እንደሚያከናውኑ የሚመለከት ነው:: በአብዛኛው የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት (democratic centralism) የሚለው የአደረጃጀትና አሰራር እሳቤ ጎልቶ የሚታይ ነው:: ይህም በመሆኑ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣም ምስጢረኛነት የበዛው አሰራር፣ የገነነ ማዕከላዊነትና ጥብቅ ከላይ ወደታች አደረጃጀት እንዲሁም ግልጽነት የሚጎላቸው የውስጥ አሰራር ድንጋጌዎች ያሏቸው በመሆናቸው ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ ባህል የጎደላቸው ናቸው:: በዚህም የተነሳ ተራ አባሎቻቸውንና ዜጎችን በተለምዷዊ የፖለቲካ ፓርቲ ስራዎች በሚባሉት ውስጥ የማያሳትፉና በማህበራዊ መሰረቶቻቸው ከሞላ ጎደል አየር ላይ የተንሳፈፉ ናቸው::

ይኸም በመሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው የመደራደር አቅም እጅግ አናሳ ነው:: አንደኛ፣ እርስ በራሳቸው ያላቸው ድርጅታዊ ግንኙነት ሻካራና ጥርጣሬ ላይ የተተመሰረተ ስለሆነ በአብዛኛው „አንድ-ለብዙ“ በሚደረጉ ከገዢው ፓርቲ ጋር የመገዳደር ሂደቶች እስካሁን ውጤታማ ሊሆን አልቻሉም:: ለምሳሌ „28ቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች“ ብለው እራሳቸውን የሰየሙት ከገዢው ፓርቲ ጋር በምርጫ ስነ-ስርአቱና በሌሎች አጀንዳዎች መወያየት ቢፈልጉም እስካሁን ያሰቡት ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ማስፈጸም ይቅርና ከኢህአዴግ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት አልቻሉም:: ይህም የሚያመላክተው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ አጀንዳ ቀርጸው ህዝቡና በማስተባበር ገዢውን ፓርቲ የማስገደድ አቅማቸውን መገንባት አለመቻላቸውን ነው::

„አንድ-ለአንድ“ በሚደረጉ የመደራደርና የመገዳደር ሂደቶች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸው አቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ከ1997 ምርጫ በፊትም ሆነ በኃላ ከገዢው ፓርቲ ጋር የተደረጉ የተለያይ ድርድሮች ውጤት አልባ ከመሆናቸውም በላይ ለገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ ጥቅም ለተቃዋሚዎች ደግሞ ፖለቲካዊ ክስረትን ያስከተሉ ናቸው:: ለምሳሌ መድረክ ከምስረታው ጀምሮ ከኢህአዴግ ጋር መደራደር እፈልጋለው እያለ በተለያዩ ወቅቶች ፍላጎቱን ቢገልጽም እስካሁን ከኢህዴግ ጋር መደራደር አልቻለም:: እዚጋ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ ገዢው ፓርቲ የመንግስትን፣ የመከላከያን፣ የደህንነትንና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን በበላይነት ስለተቆጣጠር በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በአጀንዳዎቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል የሚል ይሆናል:: ነገር ግን ላለፉት ሁለት አስርተ-አመታት የተቃውሞ ጎራው የገዢውን ፓርቲ አካሄድ ተረድቶ ይህንኑ የሚመጥንና አሸናፊ ወይም ተገዳዳሪ የሚያደርጋቸውን አቅም አለመገንባታቸው ሙሉ በሙሉ በገዢው ፓርቲ ሁሉን-አቀፍ አቅም (overwhelming power) የሚገለጽ አይደለም:: ወሳኝ በሆነ መልኩ ውስጣዊ ድክመታቸውን የሚያሳይ እንጂ:: ፈረንጆቹ እንደሚሉት ወረራ በራሱ የድክመት ማሳያ ሲሆን በወረራ ተሸናፊነት ምንጩ ደግሞ ውስጣዊ ድክመት ነው:: የገዢው ፓርቲ ተጽእኖ ውጤታማነት ምንጩ የተቃማዊ ኃይሎች ውስጣዊ ድክመት ነውና:: 

በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች እርስ በራሳቸው ያላቸው ድርጅታዊ ግንኙነት ሸካራና ጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በረጅም ጊዜ በሚደረጉ ግንኙነቶችና መስተጋብሮች (Isomorphic process) ሊፈጠሩ የሚችሉ የጋራ አጀንዳዎችና ሊደረስበት ይችል የነበረው በጋራ አብሮ የመስራት ተቋማዊ ዝግጅት አናሳና ዘገምተኛ እንዲሆን ሆኗል:: በተቃዋሚ ፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ አመራሮች ምንም እንኳን በአካዳሚክ ዕውቀታቸው አንቱ የተባሉ ቢሆኑም የመሰረቷቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛዎቹ ውስጣዊ መረጋጋትና አንድነት የጎደላቸው ናቸው:: ይህም በመሆኑ በሚደረጉ ድርድሮች አብዛኞቹ አንድም ያነሷቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎችውን ከገዢው ፓርቲ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ለማሳካት በሙሉ አቅማቸው በመሳተፍ፤ ሁለትም የገዢውን ፓርቲ ሌሎችን ፓርቲዎች በማዳከም የሚያረገውን እንቅስቃሴ ከመግታት አንጻር „ታማኝ ተቃዋሚ“ በመሆን መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገቡና የሚዋዥቁ ናቸው:: በዚህም የተነሳ የተቃዋሚዎች የመደራደር አቅም ባላቸው ውስጣዊ ድርጅታዊ አቅም እየተሸረሸረ የማስገደድ አቅማቸው እየተመናመነ ከገዢው ፓርቲና እርስ በራሳቸው በሚያደርጓቸው ድርድሮች ተቀባይ አሊያም ከድርድሩ የሚርቁ ሆነዋል:: 

ከላይ እንደጠቀስኩት የድርጅታዊ አቅም ውስንነት ከመደራደር አቅም አላባውያን አንዱና ዋነኛው ሲሆን በተከታዩ ክፍል ቀሪዎቹን ሁለቱን አላባውያን ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታና ማጠቃለያ ጋር እንመለስበታለን፡፡
----
ፊው አቶ ዳዊትለሙ የUniversity of Passau Governance and Public Policy ድረ ምረቃ ተማሪ ናቸው፡፡ ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይላቸው dhabesha@hotmail.com
ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment