በፍቅር ለይኩን
በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ የሚገኙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣
ጓደኞቿና የነፃነት ትግሉ አጋሮቿም፡- ‹‹እናዝናለን ኤሚ…ፍቅርሽ፣ ርኅራኄሽ፣ ለሰው ልጆች ነፃነትና መብት መከበር ያለሽ ጽኑ አቋም በልባችን ለዘላለም ይኖራል፡፡ ትግላችን እንዳቺ
ያሉ የእውነት፣ የፍትሕ ጠበቃዎችንና ሐቀኞችን በአጥፍ ጨምሮ ይቀጥላል…፡፡ ኤሚ እንወድሻለን፣ ሁሌም
እናስታውስሻለን! አንቺ የዘረኞችን የመለያየት ግንብ የናድሽ ጀግናችን ነሽ፣ አንቺ በልባችን ውስጥ ለዘላለም ሕያው ነሽ…ሞት በአንቺ ላይ ስልጣን የለውም፣ ሞትን በሕይወት፣ ጥላቻን በፍቅር ያሸነፈሽ የሕዝባችን ታላቅ ሰማዕት ነሽና …!›› በማለት ወደ ትውልድ አገሯ አሜሪካ
በእንባና በመሪር ሐዘን ሸኟት፡፡
ውቧ፣ ማራኪዋና ከዓለማችን አስር
ምርጥ ከተሞች ተርታ የተመዘገበችው የደቡብ አፍሪካዋ የኬፕታውን ከተማ የደቡብ አፍሪካ የታሪክ፣ የቅርስ፣ የባህልና የፖለቲካ ማዕከል
ናት፡፡ የድኅረ ምረቃ ትምህርቴን የተከታተልኩባት ኬፕታውን ለአምስት መቶ ዓመታት ያህል አፍሪካውያን ያለፉበትን ውስብስብ የታሪክ
ጉዞ የሚያስቃኙ፣ የጥቁር ሕዝቦችን የአይበገሬነትና የነፃነት ተጋድሎ የሚዘክሩ በርካታ ቅርስና ሕያው አሻራ ያላት ታሪካዊ ከተማ
ናት፡፡
ኬፕታውን ታላቁ አፍሪካዊ የነፃነት
አርበኛ ኔልሰን ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ለ27 ዓመታት የተጋዙባትን ቀዝቃዛውን የአትላንቲክ ውቅያኖስንና የከተማይቱን ግርማና ውበት የሆነውን የቴብል ማውንቴንን ተንተርሶ
የተገነባው የሮቢን ደሴየት ግዞት ቤት/ወኅኒ ቤት የሚገኝባትም ናት፡፡
ይህን ለዘመናት በርካታ አፍሪካውያንና
ጥቁር ሕዝቦች ለሰው ልጆች ነፃነትና ሰብአዊ መብት ሲሉ የተጋዙበትን የሮቢን ደሴየት ግዞት ቤት/ወኅኒ ቤት በየቀኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ
ጎብኚዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች፣ ፖለቲከኞች፣ መሪዎች፣ ታላላቅ የሆኑ የዓለማችን የፊልም እንዱስትሪዎችና ባለሙያዎች
እንዲሁም ዝነኞችና ባለ ጠጋዎች ይጎበኙታል፡፡ እናም የደቡብ አፍሪካዋ ‹‹እናት ከተማ›› ኬፕታውን የቱሪስቶችና ውብ የመዝናኛ ከተማም
ጭምር ናት፡፡
በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ በትምህርት
ክፍላችንና የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሙን ነፃ የትምህርት ዕድልና አጠቃላይ ወጪያችንን የሸፈነልን የሮቢን ደሴየት ሙዚየም፣ በኬፕታውን
የሚገኙትን ቤተ መዘክሮችን፣ የደቡብ አፍሪካውያንን የነፃነት ተጋድሎ የሚያንጸባርቁ ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን መጎብኘት እንድንችል
ዕድልን አመቻችቶልን ነበር፡፡ በዚህ ዕድልም ከጎበኘኋቸውና በማስታወሻ ደብተሬ ከመዘገብኳቸው አስደናቂ ስፍራዎች መካከል አንዱ ለዛሬ
ጽሑፌ መነሻ ሆኖኛል፡፡
እኔና የክፍል ጓደኞቼ ጉብኝታችን
ፕሮግራሞች ውስጥ ካየናቸው የአፓርታይድ አገዛዝን ጭካኔና ክፋት ከሚዘክሩ ታሪካዊ ቦታዎች በኬፕታውን ከተማ የሚገኘው የጉጉሌቱ ታውን
ሺፕ አንዱ ነው፡፡ ይህ ታውን ሺፕ/መንደር በአብዛኛው ጥቁሮች የሚኖሩበት ነው፡፡