ይህን ጽሑፍ ከላይ ርዕሱን አይታችሁ ምን ለማለት ፈልጎ ነው? አሊያም ሁሌም ጠንካራ ጎናችን የሆኑትን መስማትና ማንበብ ስለለመድን ይህ ሐሳብ ግርታ የሆነ ስሜት ሊፈጥርባችሁ ይችላል። ሐቅ ቢመርም መዋጥን መልመድ አለብና የተሰማኝን ጻፍኩት የሚሰማችሁን በጨዋ ደንብ አክሉበት።
(ፀያፍ ካልተሳደቡ አስተያየት ያልሰጡ የሚመስላቸውን ታታሪ ተሳዳቢዎችን ነው ማሳሰቢያው የሚመለከተው!)
በኢትዮጵያችን ውስጥ ጥቁሩ ማኅበረሰብ (ከጠይም በላይ የጠቆሩትን ማለቴ ነው) በቆዳው ቀለሙ ብቻ መድልዖ ይደርስበታል የማግለልና በቀለም ብቻ የሚፈፀሙት በደሎችና መንስኤዋችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
፩፡-የሥራ
ዕድል
ሥራ ለማግኘት ከትምህርትና ከችሎታ መመዘኛዎች በተጨማሪ የምትጠየቀው ወይ የሚፈለግብህ/ሽ ነገር አለ፡፡ የት አገር እንዳትሉኝ በእኛዋ ኢትዮጵያችን ውስጥ መልከ መልካም መሆን አሊያም ጠይም የቆዳ ቀለም ሚዛኑን ትደፉ ዘንድ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። የስራ አመራር፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ሹመቶች ወዘተ... ግርማ ሞገስና ውበት ከብቃት ይልቅ ሚዛን ይደፋሉ። የቤት ሠራተኝነት የምትቀጠር አንዲት ሴት ጠቆር ካለች የመጥፎ ገድ ምልክት ተደርጋ፣ ልጆቻችን ሊፈሩ ይችላሉ ተብሎ፣ ያቺ ምስኪን የሥራ ዋስትና ታጣለች። በተፈጠሩበት አገር ላይ መገለል ጉዳቱ ምን ያህል መሆኑን ከቀመሱት በላይ ማን ሊሰማው ይችላል?
(አካላዊ ውበትና ቅርፅ የሚሹ የሥራ መስኮች የሉም እያልኩኝ ግን አይደለም!)
፪፡-የፍቅርና
የትዳር አጣማጅ ማግኘት ጫናዎች
አንዲት የአገራችን ልጅ ከናይጀሪያዊ ጓደኛዋ ጋር በፍቅር ከነፈች ሲበዛ በጣም ትወደዋለች እሱም በጣም ይሳሳላታል፣ የተማረ ስልጡን ባለሙያ ነው። በፍቅር የወደቀችለት ልጅን አግብቶ ቤተሰብ መመሥረት ይፈልጋል፤ እሷም ትፈልጋለች ግን ያደገችበት ማኅበረሰባዊና ቤተሰባዊ ጫና በትምህርት ያገኘችውን ዕውቀት በልጦ በጭንቀት ማዕበል ውስጥ በሰመመን እየተብከነከነች መኖርን አስመረጣት። ለምን እየወደደችው፣ እያፈቀረችው የትዳር አጣማጁ መሆንን አትሻም? መልሱ ቀላል ነው የቀለም ልዩነት ብቻ ነው። የቆዳው መጥቆር፣ የከንፈሩ መተለቅ አካላዊ ገፅታውን እሷ ብትወድለትም ቤተሰቦችዋ ግን እንደማይቀበሉት ታውቃለች፡፡
ያንንም በቀጥታም በተዘዋዋሪም ነግረዋታል የመካነ አዕምሮ (ዩንቨርሲቲ) መምህሩ ወንድሟ በፌስቡክ ላይ ምስሉን አይቶ ዘራችንን ልታበላሺ ላልጠፋ ወንድ ባርያ ትይዣለሽ? በማለት አሸማቋታል (ይህ ሰው ለተማሪዎቹ ምን ይሆን የሚያስተምራቸው? የዘር፣
የቀለም ልዩነት ወንጀል በሆነበት ዘመን ያልተለወጠ ሰው በተለይ መምህር መሆኑ ጥፋቱን ያሰፋዋል!)


