(Zone 9 Update)
ሚያዚያ 17/2006 በድንገት ከያሉበት ተይዘው የታሰሩት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ጋዜጠኞች በሐምሌ 08/2006 የተፃፈ ክስ ሐምሌ 11/2006 ‹ስለ ፀረ-ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3/2/ እና 4 ተላልፋችኋል› በሚል ክስ ቀርቦባቸው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ክስ ከቀረበባቸው አስር ግለሰቦች መካከል አምስቱ ሐምሌ 01/2007 በድንገት ከሳሽ ክሱን አንስቻለሁ በማለቱ ከእስር የወጡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ አምስት ግለሰቦች ላይ ግን ከሳሽ የመሰረተውን ክስ ቀጥሎበት ያቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ጉዳዩን የያዘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት መርምሮ በጥቅምት 05/2008 በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ፣ 3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ፣ 5ኛ ተከሳሽ አጥናፉ ብርሃኔ እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ አቤል ዋበላ ‹የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳይገባቸው በነፃ ይሰናበቱ› በማለት ብይን የሰጠ ሲሆን፤ 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ መሰረት የቀረበበትን ክስ ወደ መደበኛው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 256/ሀ/ በመቀየር ክሱን እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡
በተሰጠው ውሳኔ መሰረትም ነፃ የተባሉት የዞን ዘጠኝ አባላት ከእስር የተለቀቁ ሲሆን በመደበኛው ወንጀል ሕጉ መሰረት ክሱን እንዲከላከል የተወሰነበት በፍቃዱ ኃይሉ በሃያ ሽህ በር ዋስትና ከእስር ተለቋል፡፡ ነገር ግን ‹በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቻለሁ› በማለት ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በታህሳስ 04/2008 የተፃፈ ይግባኝ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ይግባኝ አቅርቧል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ከሳሽ በፅሁፍ አለኝ ያለውን ቅሬታ በቃል ሰምቶና የተከሳሾቹን ምላሽ በማዳመጥ ለነገ መጋቢት 20/2008 ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምን ሊከሰት ይችላል?
በነገው የፍርድ ቤት ውሎ ችሎቱ መዝገቡን መርምሮ የጨረሰ ከሆነና ‹ተጨማሪ ማስረጃ አያስፈልገኝም› የሚል ከሆነ ሶስት የተለያዩ ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
የመጀመሪያው ነገር ‹የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው› በማለት የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማፅናት የተከሳሾቹን ነፃነት ማስጠበቅ ነው፡፡
ሁለተኛው ሊከሰት የሚችለው ጉዳይ ደግሞ ከመጀመሪያው በተቃራኒ የከሳሽ ቅሬታን ተቀብሎ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር ‹ተከሳሾቹ ክሳቸውን እንዲከላከሉ› የሚል ውሳኔ በመስጠት ተከሳሾቹን ዳግም ወደ እስር ቤት መመለስ ነው፡፡
ሶስተኛው የሚጠበቀው ጉዳይ የስር ፍርድ ቤት 2ኛ ተከሳሽን በፍቃዱ ኃይሉን የሚመለከት ሲሆን፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሰረት አንድ ሰው በተመሳሳይ ጉዳይ በተመሳሳይ ጊዜ በሁለት የተለያዩ ፍርድ ቤቶች ክሱን ሊከታተል ስለማይገባ ከሕግ አግባብ ውጭ በፍቃዱ ላይ የቀረበውን ይግባይ ውድቅ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እኛም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማፅናት ይህ በመናገር ነፃነት ላይ የተሰነዘረን ጥቃት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ይሰጠዋል የሚል ተስፋ አለን፡፡