Monday, December 28, 2015

አዲስ አባባ ስለምን ታወዛግባለች

 ዘላለም ክብረት

ሕሩይ ሚናስ አስደናቂ ሰው ነው፡፡ የገበሬ ልጅ፣ በአስራዎቹ መጨረሻ አዲስ አበባ የገባ፡፡ ከዛም የአብነት ተማሪ ሆነና ቅዳሴና ቅኔ ሞካከረ፡፡ እሱ አልሆን ሲለው ጎዳና ወጥቶ ጎዳና አዳሪ ሆነ፡፡ ቀጠለና የለማኝ መሪ (sighted guide) ሆነ፡፡ እሱም ሲያልፍ ‹ለምን አልማርም?› ብሎ ትምህርት ተማረና ዩንቨርሲቲ በገባ በዓመቱ ‹ማርክሲስት› ሆነ፡፡ ትምህርቱንም ለአቢዮቱ ሲባል ተወውና መፅሃፍ ነጋዴ ሆነ፡፡ ማርክሲስት ነጋዴ! ‹ከወገብ በላይ ታቦት፣ ከወገብ በታች ጣኦት› እንዲሉ የትናንት ቀዳሹ ሕሩይ ዛሬ ማርክስዚምን ወደደ፡፡ የሕሩይ ማርክሲዝም ከትናንት ማንነቱ እጅግ በተለየ መንገድ ወሰደው፣ የመፅሃፍ አርታኢነት፡፡ መፅሃፍ ሲያነብ፣ ሲተረጉም፣ ሲፅፍና የአርትኦ ስራ ሲሰራ ውሎ ጫት ይቅማል፤ በዛ ላይ አረቄም ይሞካክራል፡፡ በመጨረሻ አበደ፡፡ ከዛ በኋላ ያለው የሕይወቱ ምዕራፍ ብዙ ያሳዝናል፡፡

በኋላ ከአዕምሮ ሕመሙ ሲያገግም ግን የሚገርም ነገር አደረገ፡፡ ‹እብድ› እያለ ሲያደርጋቸው ነበሩትንና የሚያስታውሳቸውን ነገሮች ሁሉ በተርታ ፅፎ ‹እብዱ› በሚል ርዕስ መፅሃፍ አሳተመ፡፡ ይህ መፅሃፉ ለሕሩይ ከብዙ ስራዎቹ አንዱ ነው፡፡ ስለ አዲስ አበባ ለመፃፍ ከሕሩይ የተሻለ ምሳሌ ማግኝት ይከብዳል፡፡ እሱም ‹ወይ ዐዲስ ዓበባ› በሚል ርዕስ (እውነትን መሰረት ያደረገ) መፅሃፍ ፅፎ አዲስ አበባ ከሩቅ ሲያይዋት ምን እንደምትመስል ይተርካል፡፡ በሕሩይ የገጠር ሕይወት አይን አዲስ አበባ ገነት ነበረች፡፡ ሕሩይ እንዲያውም በመደነቅ ‹‹ለካ የዐዲስ ዓበባን ሰው ፎቶ እያነሱ ነው ወደ ገጠር ‹ምስለ መላዕክትና ሰማዕት› እያሉ የሚልኩልን›› በማለት እሱ ከሚያውቀው ገጠርና ሕዝቡ አንፃር አዲስ አበባ ገነት፣ ነዋሪዎቿም መልዓክት እንደሆኑ ይገልፃል፡፡ ገነት ሆና ከሩቅ የታየችው አዲስ አበባ ሲገባባት ጎዳና ላይ አስተኝታዋላች፣ ‹አቢዮተኛ› አድርጋዋለች፣  አሳብዳ አስለፍልፋዋለች … በስተርጅናውም ‹ከጋራ ኮንዶሚኒየም ቤቶቿ› በአንዱ ይኖር ዘንድ ፈቅዳለታለች፡፡ ሕሩይ አዲስ አባባን ከሩቅ አይቶ ጎምጅቶባታል፡፡ አዲስ አበባን ጉያዋ ስር ሆኖም ተሰቃይቶባታል፡፡ ዛሬ ደግሞ አዲስ አበባ ሕሩይን እንከባከብኻለሁ እያለችው ነው፡፡  ሕሩይ ሚናስ - ራሱን ‹አውግቸው ተረፈ› ብሎ የሰየመ ሰው፡፡

ይህ የሕሩይ ብቻ ታሪክ አይደለም፡፡ የብዙ ኢትዮጵያዊያንም እንጂ፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አዲስ አበባን ከከተማም በላይ የስልጣኔ ምልክት አድርጎ ነው የሚቆጥራት፡፡ እንዲያውም ሌሎች ከተሞች የሚለሙት ከአዲስ አበባ የሚመጡ ነዋሪዎች እንዲዝናኑባቸው ሁሉ እስኪመስል ድረስ የሌሎች ከተሞችን ዕድገት ሁሉ ወሳኟ አዲስ አበባ እየሆነች ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ‹የአዲስ አበባ እንግዶች መጥተዋል› ከተባለ ነገሩ ትልቅ ነው፡፡ አንዳንዴማ ‹እሷ እኮ አዲስ አበባ ቤት አላት› ሲባል ሁሉ ነው ሃብት የሚቆጠረው፡፡ 

አዲስ አበባ አንድ ከተማ ብቻ ነች ማለት ከባድ ነው፡፡ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ 3.6 በመቶው ብቻ ቢሆንም አዲስ አበባ የሚኖረው ቀሪው የሀገሪቱ ሕዝብ ያለ አዲስ አበባ ምንድን ነው? እስኪባል ድረስ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ለተባለው ዓለም የስበት ማዕከል (center of gravity) ናት፡፡ 

Monday, December 21, 2015

Government must stop the killings


The Ethiopian Government is using firearms to crowds of protesters to brutally suppress the large-scale Oromo students who are protesting government’s plan of expanding the capital city, Addis Ababa into Oromia Regional State. Over the last four weeks of sustained protests at least 70 people were killed, hundreds injured and several citizens are arrested. Instead of stepping back and examining the students protest in the context of constitutional framework, the Ethiopian government officials embarked on a propaganda campaign of demonizing the protesters. Particularly, we are disturbed to hear high ranking government officials such as the Prime Minister speak in an intimidating undertone using phrases such as ‘we punish protestors mercilessly’.

Over the last four weeks we believe the government has violated the following articles of the constitution:

1. Article 15 Right to Life  

“Every person has the right to life. No person may be deprived of his life except as a punishment for a serious criminal offence determined by law”. Reports have indicated that at least 70 citizens have been killed by live ammunitions fired by red beret wearing security forces. Countless others are beaten, arrested and are made to live in fear.

2. Article 24 Right to Honor and Reputation
 
“Everyone has the right to respect for his human dignity, reputation and honor.” In a government presser broadcasted on the state owned television the protestors have been called ‘demons’. They are   labeled criminals without any sort of due process of law.

3.       Article 30 Right of Assembly, Demonstration and Petition

“Everyone has the right to assemble and to demonstrate together with others peaceably and unarmed, and to petition.” From reports we have learned that the protests are largely peaceful. From the media reports and the images of the protests being circulating on social media we can witness that citizens are using their constitutional rights of nonviolent tactics such as  silence, turning their back, displaying symbols, putting their crossed hands in the air, marching and parading, but government is using its strong  security forces to disband them.

In this age of information and communication technology attempting to conceal government’s misconducts or refusing to recognize citizens’ constitutional right shall only bring embarrassment to the government that claims it has been elected democratically just six months ago. We believe absolute shutdown of the public space will only lead to further grievances and aggravate the situation. Hence we ask the government to:

 -Stop arresting and killing of innocent civilians

-Instead of shutting the public space the government must allow citizens to exercise their constitutional rights and express their thoughts and opinions about the Master Plan

-End impunity and bring those who have violated the constitutional rights of citizens to justice.

Zone9 has been always advocating for peaceful and non-violent ways of criticizing the government and demanding rights. This peaceful way of advocating for change is the one that we are living for, speak for, arrested for and exiled for too.  We are in solidarity with peaceful protesters and all nonviolent actors who works to bring perpetrators to justice and demands their rights.   


Respect the constitution. 

ሕገ መንግስታዊነት እንዲሰፍን የሚፈሰው ተጨማሪ ደም ይገደብ!

የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች በኦሮሚያ ክልል በርካታ ወረዳዎችና ከተሞች  እያቀረቡት ያለው ሠላማዊ ጥያቄ በሰከነ መንገድ መልስ ለመስጠት ከመሞከር ይልቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ ሀይል በመጠቀም ጥያቄውን ለማፈን እየተሞከረ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ለቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ሰሞኑን ከሚወጡት መግለጫዎችና የመንግስት ባለስልጣናት ቃለመጠይቆች እንደተረዳነው  ጥያቄዎቻቸውን በሃይል ለመመከት ከመዛትና ዜጎችን ከሰው በታች አውርዶ ቁጣን በሚጋብዝ መልኩ ከመጥራት በዘለለ ሀላፊነት እንደሚሰማው አካል ለችግሩ መፍትሔ  ለመፈለግ ዝግጁነት እንደሌለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሌም እንዲከበር የምንጠይቀውን የሀገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ-መንግስት የሚጻረር ነው፡፡
በዚህ ሂደት በጥቂቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የሕገ-መንግስቱ አንቀጾች ተጥሰዋል
1.    የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 15 የሕይወት መብት
‹‹ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡›› ቢልም ከሰላማዊ ሰልፉ ጋር በተያያዘ ከ8 ዓመት ልጅ አንስቶ እስከ የ80 ዓመት አዛውንት ድረስ ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፤ እስከዛሬ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በሶስተኛ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም ጉዳዬን  በቅርበት የሚከታሉ ሰዎች እንደዘግቡት ወደ መቶ እየተጠጋ ይገኛል፡፡
2.   የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 15 የአካል ደኅንነት መብት
‹‹ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመጠበቅ መብት አለው፡፡ ›› አሁንም ከሰላማዊ ሰልፉ ጋር በተያያዘ በጥይት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ ድብደባ እና አላግባብ አንግልት የደረሰባቸውንም ቤት ይቁጠራቸው፡፡
3.   አንቀጽ 24.1 የክብርና የመልካም ስም መብት
‹‹ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው፡፡ ›› እየሆነ ያለው ዜጎችን አጋንንት እያሉ መጥራት፣ ጥፋተኛ ተብለው በሕግ ያልተፈረደባቸውን አሸባሪ እያሉ ክብራቸውን በሚዲያ መግፈፍ ነው፡፡
4.   አንቀጽ 30.1 የመሰብሰብ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት
‹‹ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሔድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡ ››  ቢልም መንግስት ይህን የህገ መንግሰቱን አንቀጽ በመጣስ ብዙ ሰብዓዊ ጉዳቶችን አድርሷል፡፡

ዜጎች ለመረጃ ቅርብ በሆኑበት በዚህ ጊዜ መንግስት እያደረጋቸው ያሉትን ተግባራት መካድ፣ እንዲሁም እንደሌሉ አደርጎ ለማስተባበል መሞከር ብዙ ኃላፊነት የሚጠበቅበት መንግስት የሚያሰገምትና ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ይህ የመንግስት ግዴለሽነት ብዙኃን ዜጎችን እየገፋ ከመስመር እያስወጣ ነው፡፡ ሰላማዊውን የሕዝብ እንቅስቃሴ ወደ አመጽ እና ወደአልተፈለገ ዕልቂት ከመግፋት ይልቅ የተቀናጀ የጋር ማስተር ፕላኑን  መሰረዝ፣ በዚህ ሒደት ጥፋት የፈጸሙ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ፣ የግል ተበዳዮችን  መካስና ሌሎች አስፈላጊ የመፍትሔ እርምጃዎችን ሁሉ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡  ሁልጊዜም እንደምንለው በሰላማዊ መንገድ የመብት ጥያቄ ማቅረብ ወንጀል አይደለም፡፡  መንግሰት በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ከሚጠይቁ ዜጎች ጋር እልህ አይጋባ ፣ ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው ይከበሩ ፣ የመብት ጥሰት ድብደባ እና ግድያው ይቁም፡፡  ሕገ-መንግስታዊነት የታሰርንለት፣ ከሀገር የተሰደድንለት፣ ብዙ ዋጋ የከፈልንበትና አሁንም እየከፈልንበት ያለ ዐሳብ ነውና  በሀገሪቱ ህጋዊነት እንዲሰፍን ህይወታቸውን እስከመስጠት ድረስ ዋጋ ለከፈሉ ዜጎች ክብር እንሰጣለን፡፡ ለሕገ መንግስታዊ ስርዓት መስፈን ዜጎች የከፈሉት ዋጋ እጅግ ብዙ እና ከበቂ በላይ ነውና ተጨማሪ ሰብዓዊ ዋጋ መክፈል ሳያፈልገን ሕገ መንግስቱ እንዲከበር አንጠይቃለን፡፡

ሕገ-መንግስቱ ይከበር!  

Tuesday, December 8, 2015

ጋምቤላ: የፌደራሊዝሙ ክሽፈት ማሳያ?


በዘላለም ክብረት


ሐሙስ 20 – 01 – 2003፣ ጋምቤላ ከተማ፡

የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አዲሱን የስራ ዘመኑን የመጀመሪያውን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ በማጽደቅ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በመዝጊያው ስነ ስርዓት ላይ በጊዜው የክልሉ ፕሬዝደንት የነበሩት ኡሞት ኡባንግ ባደረጉት ንግግር፡

‹‹ጋምቤላን ወደ ቀድሞው ክብሯ እንመልሳታለን፡፡ ያችን አኙዋዎች፣ ኑዌሮች፣ መዠንገሮች፣ ኦፖዎች፣ ኮሞዎችና ደገኞች አንድ ላይ በሕብረት የሚኖሩባትን - ጋምቤላ፡፡ ሁላችንም አፍሪካዊያኖች ነን፡፡ ጥላቻና ልዩነት ለማናችንም አይበጁንም…››

በማለት የሁሉንም ተሰብሳቢዎች ልብ የሚነካ ሃሳብ አቀረቡ፡፡ 156 መቀመጫዎች ያሉት የክልሉ ምክር ቤትም በጭብጨባ ተናጋ፡፡ ኡሞት ይሄን ታሪካዊ ንግግር ሲያደርጉ ከኡሞት ጎን የተቀመጡት የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አሽኔ አስቲን ተከትለው ስለ ልማትና መከባበር ተናግረው አሁንም አዳራሹን በሌላ ጭብጨባ አናጉት፡፡ ከሚያጨበጭቡት የምክር ቤት አባላት መካከል ቁመተ ሎጋው የ50 ዓመቱ ከአኙዋ ዞን የተወከሉት አቶ በኳች ማሞ ይገኙበታል፡፡ 

እሁድ፡ 06 – 07 – 2007፣ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ፡

የቀድሞው የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ሆኑት አቶ አሽኔ አስቲን በኬኒያ ናይሮቢ አኝዋ ሰርቫይቫል፣ Bread for All እና GRAIN በተባሉ ዓለማቀፍ ተቋማት የተዘጋጀውን ዓለማቀፍ የምግብ ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከሌሎች አራት ግለሰቦች ጋር (የዓለም ባንኩን አስተርጓሚ ፓስተር ኡሞት አግዋን ጨምሮ) ተገኙ፡፡ ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆን ቀረና አምስቱም ግለሰቦች በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ተይዘው ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ተወሰዱ፡፡

ከአንድ ቀን በኋ ሰኞ፣ 07 – 07 – 2007፡ 

‹ምርጫ 2007› ሊደረግ ስልሳ ሰባት ቀናት ይቀሩታል፡፡ ‹አፈ-መንግስቱ› ኢቢሲ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን  ባወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ የአየር ጊዜ መሰረት የዕለቱ (በቴሌቪዥን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ዜና በኋላ) ተረኛ በጋምቤላ የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ በመሆን ክልሉን እያስተዳደረ ያለው የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕአዴን) ነው፡፡ ጋሕአዴን በዕለቱ እየቀሰቀሰበት የነበረው ጉዳይ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ሲሆን፤ በዚሁም መሰረት የክልሉ ህዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡ የፓርላማ አባላት በፌደራል እና በክልል ደረጃ እንደተወከለና የውክልና ዴሞክራሲም በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደላቀ ደረጃ እንደደረሰ ጠቅሶ ይቀሰቅሳል፡፡ በቅስቀሳው መሃል ከሚታዩት ምስሎች መሃል ግን አንዱ ጉዳዩን ለሚያውቅ ሰው ወይ ያስቃል አለያም ያስደነግጣል፡፡ አስቂኙ/አሳዛኙ ጉዳይ በ2002 ምርጫ የክልሉ ምክር ቤት ካለው 250 መቀመጫዎች መካከል አንዱን የያዙት የአኙዋ ዞን ተወካዩ አቶ በኳች ማሞ በክልሉ ፓርላማ ውስጥ የድምፅ አሰጣጥ ስርዓት ላይ እጃቸውን ሲያወጡ መታየታቸው ነው፡፡ ምክንያቱም አቶ በኳች ማሞ በቀን 07 – 07 – ’07 ‹‹መቀመጫውን ሀሬና፣ ኤርትራ ካደረገው ራሱን የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) ብሎ ከሚጠራ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት ፈጥረሃል፣ በሃላፊነትም እያገለገልክ ነው›› ተብለው በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ  አንቀፅ 7 (2) መሰረት ከ 20 ዓመት እስከ እድሜ ልክ ሊያስቀጣ የሚችል ክስ ቀርቦባቸው ያለመከሰስ መብታቸው እንኳን ሳይነሳ በእስር ላይ ይገኛሉና፡፡ በኳች ታስረዋል፡፡ ጋሕአዴን ደግሞ የውክልና ዴሞክራሲ መጎልበት ተምሳሌት አደርጎ ይቀሰቅስባቸዋል፡፡

ሰኞ፣ 17 – 09 - 2007፡ ጋምቤላ፣ ማጃንግ ዞን፡

በአስገራሚ ሁኔታ የቀድሞው የጋምቤላ ክልላዊ ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል አቶ አሽኔ አስቲን በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን መንድሽ የምርጫ ክልል በተካሔደው የክልል ምክር ቤት ምርጫ  ጋሕአዴንን በመወከል ምርጫውን በማሸነፋቸው የምርጫ ክልሉ ምርጫ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማቴዎስ ኤፍሬም የተፈረመ የተመራጭነት መታወቂያ የተዘጋጀላቸው ሲሆን ‹የተመራጩ ፊርማ› የሚለው ቦታ ላይ ግን ፊርማቸውን አላሳረፉም፡፡ 

ለምን? ምክንያቱም አቶ አሽኔ አስቲን ከመጋቢት 06 - 2007 ጀምሮ ‹‹መቀመጫውን ሀሬና፣ ኤርትራ ካደረገው ራሱን የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) ብሎ ከሚጠራ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት ፈጥረሃል›› ተብለው በፀረ-ሽብርተኝነት አቆጁ መሰረት ተከሰው በእስር ላይ ስለሆኑ፡፡ እንግዲህ አቶ አሽኔ አስቲን ምርጫ የተወዳደሩትም ያሸነፉትም በሌሉበት ሲሆን፤ በመጨረሻም በሌሉበት የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት  ተመራጭ ስለመሆናቸው በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የተመራጭነት መታወቂያ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

***

ኡሞት ኡባንግ በ2002 ምርጫ አሸንፎ ስልጣን የያዘውን የጋምቤላ ምክር ቤት አራተኛ የስራ ዘመን በ2003 መጀመሪያ ላይ ሲከፍቱ አሽኔ አስቲን በአፈ ጉባኤነት ከጎናቸው የነበሩ ሲሆን በኳች ማሞ ደግሞ የምክር ቤት አባል ሁነው ከፊት ለፊታቸው ተቀምጠው ነበር፡፡ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኡሞት ኡባንግ ከክልሉ ፕሬዝደንትነታቸው ተነስተው በፌደራል ደረጃ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ቢሾሙም የያዙትን ይዘው ከሀገር ኮበለሉ፣ የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል አሽኔ አስቲን በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ታስረው ይገኛሉ፣ የምክር ቤት አባሉ በኳች ማሞም እንዲሁ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

እውነት ይህ ሁሉ የሚሆነው ህግና ስርዓት ባለበት ሀገር ነው? ብሎ መጠየቅ እዚህ ጋር ተገቢ ነው፡፡ የጋምቤላ አበሳ ግን ከዚህም ይልቃል፡፡

1. ጋምቤላ

የኢፌዴሪ ሕገ - መንግስት በአንቀፅ 47 ካቋቋማቸው ዘጠኝ የክልል መስተዳደሮች አንዱ ነው፡፡ የሕዝብ ብዛቱ ትንሽ ከሚባሉ ክልሎች አንዱ ሲሆን (የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን የሃምሌ 2007 ግመታ የክልሉ ሕዝብ ብዛት ሶስት መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ እንደሆነ ያሳያል)፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙት አስር ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ‹በየካ ክፍለ ከተማ› ብቻ የሚኖረው ነዋሪ በአጠቃላይ በጋምቤላ ክልል ከሚኖረው ነዋሪ በእጅጉ ይበልጣል እንደ ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በጋምቤላ ክልል የሚኖረው ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 0.4 በመቶውን ብቻ ይሸፍናል፡፡ (የሕዝብ ቁጥሩ ላይ የተለያዩ የክልሉ ልሂቃን ጥርጣሬ አላቸው) የሕዝብ ብዛቱ ከቆዳ ስፋቱ አንፃር ሲታይ ግን በኢትዮጵያ እንደ ጋምቤላ ህዝብ ሰፊ መሬት ላይ የሰፈረበት (sparsely populated) ክልል የለም፡፡ በንፅፅር ሲቀርብም ሃምሳ ከሚሆኑት የአውሮፓ ሀገራት ጋምቤላ አስራ ሶስት የሚሆኑትን በቆዳ ስፋት ይበልጣል፡፡ ጋምቤላ መሬቱ ሰፊ፣ የሕዝብ ብዛቱ ትንሽ እና እጅግ ለም ክልል ቢሆንም እንደ ጋምቤላ ጭቆናው፣ የመብት ጥሰቱ፣ ስደቱና መከራው የበዛበት ክልል የለም ማለት ደግሞ ስህተት ነው አያስብልም፡፡ 

በ1980ዎቹ አጋማሽ Cultural Survival በጋምቤላ የሚኖረውን የአኙዋ ዘውግ ‹አደጋ ላይ ያሉ ቡድኖች› ዝርዝር (endangered groups list) ውስጥ ካስገባው ጊዜ ጀምሮ ስለ ጋምቤላ ስቃይና መከራ እንደ Genocide Watch, Survival International, Oakland Institute, Inclusive Development, Human Rights Watch, Amnesty International, International Consortium of Investigative Journalists (ICIJ) የመሳሰሉ ፖሊሲ አፍላቂዎች (think tanks)፣ የመብት ተከራካሪዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች ብዙ ሪፖርቶች፣ መግለጫዎችና ዘገባዎችን በተለያዩ ጊዜያት አውጥተዋል፡፡ የግጭት ተንታኞች (conflict analysts) የፌደራል ኢትዮጵያን የግጭት መንስኤና መፍትሄ ሲተነትኑ ከጋምቤላ የተሻለ ምሳሌ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ እዚህም እዛም ጋምቤላ ነው በምሳሌነት የሚቀርበው፡፡ ለምን ጋምቤላ?

2. ጋምቤላና: ‘የፌደሬሽኑ ፈተና’?

ኢትዮጵያ የዘውግ ፌደራሊዝምን (ethnic federalism) በሕገ መንግስት ደረጃ ተቀብላ ተግባራዊ ማድረግ በጀመረችበት ወቅት ሂደቱ ዘውግ ፌደራሊዝምን በሕግ ደረጃ ከከለከሉትና ዘውጌ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በሕግ ደረጃ ከሚያግዱት ከአብዛኖቹ የአፍሪካ ሀገራት የተለየ (divergent) በመሆኑ ትችትና ውዳሴ ከተለያዩ አካላት ይቀርብለት ነበር፡፡ ተችዎች ይህ ለአፍሪካዊያን መጥፎ ምሳሌ (precedent) ነው በማለት ከፋፋይ ነው ሲሉ ሲያጣጥሉት፤ አወዳሾቹ ደግሞ አፍሪካ ከተዘፈቀችበት የግጭት አዙሪት ለመውጣት ጥሩ መፍትሔ ነው በማለት ሲያሞግሱት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ዘውጌ ፌደራሊዝም ከሃያ ዓመታት በኋላ እንደ ተችዎቹ ሆነ ወይስ እንደ አወዳሾቱ የሚለው ኦዲቲንግ የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ባለመሆኑ በዚህ ፅሁፍ ለማየት አልተሞከረም፡፡

‹የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ብዙ ውይይት ሳይደረግበት ነው አሁን ባለው ደረጃ ሕገ መንግስታዊ የሆነው› የሚለው የምሁራን ትችት እንዳለ ሆኖ ዘጠኝ ክልሎችንና ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን (ድሬዳዋን በኋላ ሕገ መንግስቱን እንኳን ማሻሻል ሳያስፈልገው በአዋጅ የከተማ አስተዳደር አድርጎ ተቀብሏታል) ይዞ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይህ በዋነኛነት ዘውግን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ግን የግጭትና መንስኤ መሆን የጀመረው በተግባራዊነቱ ማግስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌደሬሽን ዋነኛ የግጭት መንስኤ የሆነባቸው ክልሎች ደግሞ አራቱ ብዙሃኑን የሚወክል ‹አውራ ዘውግ› (dominant ethnic group) የሌለባቸው ክልሎች ማለትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ በጋምቤላ ሕዝቦች ክልል እና በሀረሪ ሕዝብ ክልል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አራት ክልሎች ተፎካካሪ ዘውጎች (competing ethnic groups) ያሉባቸው በመሆናቸው የሃብትና የስልጣን ፉክክሩ ነገሮችን በቀላሉ ወደ ግጭት እንዲያመሩ ያደርጓቸዋል፡፡ እንግዲህ ጋምቤላም ከነዚህ አራት ክልሎች አንዱ ነው፡፡

2.1. ‘አኙዋ’  ከ‘ኑዌር’

በአሁኑ ወቅት ያሉት ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የፌደራሉን ሕገ መንግስት መሰረት በማድረግ (በአብዛኛው ከፌደራሉ ሕገ መንግስት ቃል በቃል የተቀዳ) ራሳቸው የክልል ሕገ መንግስት አላቸው፡፡ የጋምቤላ ሕዝቦች ክልልም የራሱ የሆነ ሕገ መንግስት አለው፡፡ የጋምቤላ ሕዝቦች ሕገ መንግስትን ከሌሎች ክልሎች ሕገ መንግስትም ሆነ ከፌደራሉ ሕገ መንግስት በተለየ ‹የክልሉ መስራች አባላት› (titular groups) የሚል ሀሳብ ማካተቱ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል ሕገ መንግስት አንቀፅ 46 መሰረት የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስራች ብሔር ብሔረሰቦች አምስት ሲሆኑ የአኙዋ ብሔረሰብ፣ የኑዌር ብሔረሰብ፣ የመዠንገር ብሔረሰብ፣ የኦፖና ኮሞ ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ ከነዚህ መስራች ብሔረሰቦች› መካከል የአኙዋና የኑዌር ብሔረሰቦች በድምሩ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውን የህዝብ ቁጥር ሲይዙ ከአጠቃላይ የክልሉ ነዋሪዎች መካከል ደግሞ እነዚህ ሁለት ብሔረሰቦች ከሁለት ሶስተኛ የሚልቀውን ይይዛሉ፡፡ በመሆኑም የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል ዋነኛ እጣ ፋንታ የሚወሰነው በሁለቱ ‹መስራች ብሔረሰቦች› ተፎካካሪ (competing) ግንኙነት ነው ማለት ነው፡፡

የተለያዩ የክልሉን ፖለቲካ ያጠኑ ግለሰቦች/ተቋማት ጋምቤላን ሰላም ካሳጧት ችግሮች አንዱና ዋነኛው በውስጡ ያሉት ዘውጎች የዕርስ በርስ ፉክክርና ግጭት (inter-ethnic conflict) ነው፡፡ ይህ ግጭትም የሃብት፣ የመሬት እና የስልጣን ፍክክር ነው በማለት ያብራራሉ፡፡ የግጭቶቹ መንስኤ በአጭሩ ይሄ ነው ማለት ከባድ ነገር ቢሆንም በዋናነት ግን ግጭቱና ቁርሾው በአኙዋና ኑዌር ዘውጎች መካከል እንደሆነ ጥናት ያደረጉ ቡድኖች ይገልፃሉ፡፡ የአኙዋ ዘውግ ልሒቃን ጋምቤላ በታሪክ የአኙዋ ምድር እንደሆነች ሌሎች ዘውጎች ከአሁኗ ደቡብ ሱዳንና ከአጎራባች ክልሎች በተለያዩ ጊዜያት እንደመጡ በመግለፅ የጋምቤላ ሃብትና ስልጣን ለባለታሪኩ (historical right) እንደሚገባ በመግለፅ ይሟገታሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አብዛኛው የዘውጉ አባላት በደቡብ ሱዳን የሚኖሩት የኑዌር ብሔረሰብ ልሂቃን ጋምቤላ የሁላችንም ናት ከሚል መነሻ “መጤ” የሚለው ስያሜ አይገባንም በማለት ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ መድሃኔ ታደሰ በተለምዶ የአኙዋ -ኑዌር ግጭት በኑዌሮች ‹ተስፋፊነት›ና በአኙዋዎች ከመሬታቸው ጋር ባለ ጥብቅ ቁርኝት መካከል የተፈጠረ አለመጣጣም እንደሆነ ሲገልፁ ‹‹Traditionally, the Anuak- Nuer conflict can be explained by the incompatibility (antithesis) of the expansionist nature of the Nuer and the Anuaks’ strong emotional ties with their land›› በማለት ነው፡፡

ይህን የተፎካካሪ ዘውጎች ውዝግብ ለመፍታት ተወሰደው ርምጃ ጋምቤላን የኑዌር፣ የአኙዋና የማጃንግ ዞኖች ብሎ በዘውግ መስመር በሶስት ዞኖች መክፈል ነው፡፡ ይህ መፍትሔ የበለጡ የድንበር ጥያቄዎችንና ከመፍጠር ባለፈ፣ የክልሉን ስልጣን ለመያዝ የሚደረገውን ፍክክር የበለጠ አጡዞ የባሰ ችግር ከማምጣት ባለፈ ለጋምቤላ ሕመም መድሃኒት ሊሆናት አልቻለም፡፡

2.2. ‘መስራቾቹ’ ከ’መጤዎቹ

ፖለቲካል ዲሞግራፊ በአካዳሚያው ውስጥ እንደ ጥናት መስክ ተቆጥሮ መጠናት ከጀመረ ከአንድ አስርት ዓመት ብዙም አላለፈም፡፡ ሳይንሱ በዋናነት የሚያጠናው በአንድ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ሰዎች (ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች ወዘተ)፣ የተለያዩ እምነቶች፣ የተለያዩ ዘውጎች ወዘተ በስልጣንና በሌሎች ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ ስለሚያሳድሩት ተፅዕኖ ነው፡፡

ስደት (migration) እና ሰፈራ (resettlement) የጋምቤላን ፖለቲካል ዲሞግራፊ በዋናነት ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ቀያይረውታል፡፡ ከላይ ያየነው የአኝዋ-ኑዌር የሻከረ ግንኙነት በደቡብ ሱዳን ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ግጭት ምክንያት ወደ ጋምቤላ በተሰደዱ የኑዌር ዘውግ አባላት ምክንያት ነው በማለት ብዙ ሊቃውንት ይገልፃሉ፡፡ በ1980ዎቹ የSPLA ወታደሮች የያኔው ኢሉባቡር የአሁኑ ጋምቤላ ምድር በመግባት በተለያዩ ጊዜያት የአኙዋ ብሔር አባላትን እንደገደሉ የጊዜው ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ የ SPLA ወታደሮች ወደ ጋምቤላ የመግባት አላማም ደቡብ ሱዳን ውስጥ በነበረው የነፃነት ትግል ምክንያት ከደቡብ ሱዳን ተሰደው ወደ ጋምቤላ የገቡ የኑዌር አባላትን በአካባቢው ካለ ጥቃት ለመከላከል የሚል ነበር፡፡ በአጠቃላይ ኑዌሮች ወደ ጋምቤላ በብዛት መግባት በጀመሩባቸው 1980ዎቹ ውስጥ የጋምቤላ ፖለቲካል ዲሞግራፊ መቀየር ጀመረ፡፡ ዛሬ ከክልሉ ነዋሪዎች (እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ቆጠራ) መካከል ወደ ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች የኑዌር ዘውግ አባላት ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ከሶቬት ሕብረት መንግስት የሰፈራ ፕሮግራም በመኮረጅ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ደርግ) መንግስት የ1977ቱን ድርቅና ረሃብ ተከትሎ 1.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን ከድርቅ ተጎጅ አካባቢዎች በማንሳት ወደ ምርታማ አካባቢዎች ለማስፈር ባወጣው እቅድ መሰረት በ1978 መጀመሪያ ጀምሮ ከሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍሎች (በተለይም ከወሎና ከትግራይ) አጋማሽ ላይ በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ እንደሚሉት በኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርምያና አቶ ለገሰ አስፋው ‹በግዴለሽነት› በተመረጡ ሰባት የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰዎችን ማጓጓዝና ማስፈር ተጀመረ፡፡ ከነዚህ ሰባት የሰፈራ ቦታዎች አንዱና ዋነኛው ጋምቤላ ሲሆን በ1978 ብቻ እንደ ካልቸራል ሰርቫይቫል ሪፖርት 17,553 አባወራዎችና እማወራዎች የሰፈሩ ሲሆን ይሄም በግለሰብ ደረጃ ታማኝ ቁጥሮች ከ60,000 እስከ 70,000 ሰዎች እንደሚደርስ ሲገልፁ አንዳንዶች ደግሞ እስከ 150,000 ይደርሳል በማለት ቁጥሩን ከፍ ያደርጉታል፡፡ ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የጋምቤላን ዲሞግራፊ ሁነኛ በሆነ መንገድ ቀይሮታል፡፡ 

የጋምቤላ ‹መስራቾች - መጤዎች/ደገኞች› (titulars verses non-titulars)  ፖለቲካም የተጀመረው ከዚህ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሰፋሪዎቹ ቁጥር በተለያዩ ምክንያቶች እጅግ የቀነሰ ቢሆንም ይህ ‹በደገኞች›ና ‹በመስራቾች› መካከል ያለ ግጭት በአብዛኛው በአኙዋና በማዣንግ ዞኖች ጎልቶ የሚታይ ሲሆን የ1996ቱን እልቂት ጨምሮ እጅግ በጣም የብዙ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፉ ግጭቶችን ያስከተለና እስከ አሁን ድረስም የቀጠለ ዂነት ነው፡፡ ባንዳንድ የክልሉ አካባቢዎችም በተሿሚ ባለስልጣናት አስተባባሪነት ሳይቀር ችግሮችና ለዘር ማጥፋት የቀረቡ ድርጊቶች እየተፈፀሙ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ የክልሉ ግጭቶች ምስክሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ዘውግን በዋነኛነት መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ሲወጥን በመስራቾችና በመጤዎች መካከል ሊፈጠር የሚችልን ችግር የማይፈታና ስንኩል ሁኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይሄን ስንኩልነት ዶ/ር አስናቀ ክፍሌ ‹Federalism and Ethnic Conflict in Ethiopia: A Comparative Study of the Somali and Benishangul-Gumuz Regions> ባሉት የዶክትሬት ማሟያ ፅሁፋቸው ላይ ‹‹The makers of the federal constitution did not foresee how the institutionalisation of ethnic federalism would affect relationships between titular and non-titular communities›› በማለት የፌደሬሽኑ አወቃቀር ያመጣው አንድ ችግር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

2.3. ጋምቤላ ከአዲስ አበባ

የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል የ2008 10ኛው የብሔር ብሄረሰቦች ቀን ተረኛ አስተናጋጅ ተብሎ አምና ቤኒሻንጉል ላይ በተከበረው 9ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ላይ ተመርጧል፡፡ እንግዲህ ጋምቤላ ሕዳር 29/2008 10ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ታከብራለች ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል ከተከበረ ከአራት ቀን በኋላ ታህሳስ 03/2008 ደግሞ የአኙዋ ዘውግ አባላት  12ኛውን የአኙዋ ሕዝብ ላይ የተደረገው በነሱ አጠራር ‹የዘር ጭፍጨፋ› (genocide) አስበው ይውላሉ፡፡ 

ታሕሳስ 03/1996 ለጋምቤላ ታሪክ ክፉ ቀን ነበር፡፡ የግጭት ቀን፡፡ ግጭቱ በዋናነት በክልሉ ‹መስራች› ዘውጎች (በተለይም በአኝዋ ዘውግ አባላት) እና ከሌላ የኢትዮጵያ ክፍሎች መጥተው በአካባቢው በሰፈሩ ሰዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት በርካታ የአኙዋ ዘውግ አባላት የተገደሉበት ነው፡፡ የግጭቱ መንስኤ በተለያዩ አካላት የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡትም ሁሉም ግን በክልሉ መስራች ዘውግ አኝዋና ከሌላ ክልሎች በመጡ ሰዎች መካከል ተጀምሮ የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባት ግድያ እንደፈፀመ ይስማማሉ፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ የነበሩት መለስ ዜናዊ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል እስከ ሁለት መቶ የሚደርሱ ሰዎች እንደሞቱ የገለፁ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በአዋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ማለትም በአዋጅ ቁጥር 398/1996 የተቋቋመው ‹ታሕሳስ 3 ቀን በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል የተከሰተውን ግጭት የሚያጣራ ኮሚሽን› ጉዳዩን በራሴ መንገድ አጣርቼ ሀምሳ ዘጠኝ ወንዶችና አንድ ሴት ብቻ ናቸው የተገደሉት፣ ነገር ግን የመንግስት ወታደሮች ከህግ አግባብ ውጭ በመሄድ ጉዳት አድርሰዋል› በማለት የችግሩን ዋነኛ ተዋናዮች ለመነካካት ሙከራ አድርጓል፡፡ ሒውማን ራይትስ ዎች በአካባቢው ጥልቅ ጥናት በማድረግ ‹Targeting the Anuak: Human Rights Violations and Crimes Against Humanity in Ethiopia’s Gambella Region› በሚል ርዕስ በ1997 ባወጣው ሪፖርት ደግሞ የሞቱት ሰዎች ብዛት 424 እንደሆኑ ገልጿል፡፡ የተለያዩ ነፃ ዓለማቀፍ ተቋማትም ከዚህ የሒውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ጋር ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸውን ሪፖርቶች ነው በተለያዩ ጊዜ የሚያቀርቡት፡፡

እንግዲህ ታህሳስ 03 – 1996 ያለፉትን አስር ዓመታት የጋምቤላ ፖለቲካ የወሰነች ክፉ ቀን ነች፡፡ ከዛች ቀን ወዲህ የጋምቤላንና የአዲስ አበባውን የፌደራል መንግስት ግንኙነት ይህችን ቀን ሳይጠቅሱ መተንተንም ሆነ መነጋገር አይቻልም፡፡ ይህም የፌደራል መንግስቱንና የክልሎችን የአለቃና ምንዝር ግንኙነት እንድናይ ያደርገናል፡፡ 

የአሁኑ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በፀደቀበት ዓመት 1987 ዓ.ም አሜሪካዊቷ የሽግግር ፖለቲካ (transitional politics) ሊቅ ማሪና ኦታዌ በNortheast African Studies ጆርናል ላይ ‹The Ethiopian Transition: Democratization or New Authoritarianism?› በሚል ርዕስ ባሳተሙት ፅሁፋቸው ‹ኢሕአዴግ ዴሞክራሲና ፌደራሊዝምን ለነገሩ ብቻ ነው የሚያወራው፣ ዴሞክራሲንና ፌደራሊዝምን አያውቃቸውም› የሚል ሃሳብ በመሰንዘር የፌደሬሽኑን ትክክለኛነት ተጠራጥረው ፅፈው ነበር፡፡ ከሃያ ዓመታት በኋላም ይህ እውነት ተቀይሯል ብሎ ደፍሮ የሚናገር ማግኝት ከባድ ነው፡፡ ክልሎች የፌደራል መንግስቱ ‹ቅልቦች› ከመሆናቸውም ባለፈ የፖለቲካ ነፃነታቸው አሁንም አጠያያቂ ነው፡፡ ይህ የክልሎችና የፌደራል መንግስቱ የጎንዮሽ የተንጋደደ ግንኙነት (vertical asymmetry) ደግሞ ከጋምቤላ ክልል የበለጠ ጎልቶ የሚታይበት ክልል አለ ማለት አይቻልም፡፡

ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ ከአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ወዲህ ጋምቤላን ካስተዳደሩት (የሽግግሩን ጊዜ ጨምሮ) ስድስት ፕሬዚደንቶች መካከል የመጀመሪያው አግዋ አለሙ በሃምሌ 1984 እቤታቸው በወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ አራቱ (ሶስቱ ኦኬሎዎችና ጋምቤላን ለረጅም ጊዜያት ያስተዳደሩት አቶ ኡሞት ኡባንግ) ከኢትዮጵያ ኮብልለው የወጡ ሲሆን ሁሉም የፌደራል መንግስቱ ጋምቤላን እንደ ‹እንጀራ ልጅ› በማየት በፈለገው ጊዜ የPDO (Peoples Democratic Organizations) ፕሮጀክቱን የሚያስፈፅምበት፣ የፈለገውን ፓርቲ/ግለሰብ/ዘውግ የሚነቅል - የሚተክልበት ክልል ነው በማለት፣ ክልሉ የስቃይና የመከራ ምሳሌ ነው እያሉ በተደጋጋሚ ሃሳበቸውን በተለያዩ ጊዜያት ገልፀዋል፡፡ ከቀድሞዎቹ ሁለት ፕሬዚደንቶች መካከል ሁለቱ (ኦኬሎ ኝጌሎና ኦኬሎ አኳይ) የኢትዮጵያን መንግስት ለሃይል ለማስወገድ ከሚሰሩ ሃይሎች ጋር እንደሚሰሩ አደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ታዲያ ያስተዳደሩት ሁሉ የተገደሉበትና የተሰደዱበት ክልል ከጋምቤላ ውጭ ማን አለ? 

2.4. ጋምቤላ ከIndia

በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2003 ዓመቱን ሙሉ እንደ የያኔው የኢትዮጵያ የግብርና እና የገጠር ልማት ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው ‹ቢዚ› የነበረ ሚኒስትር አልነበረም፡፡ አቶ ተፈራ የተለመደውን ባለ 20 አንቀፅ የመሬት ኪራይ ውል ስምምነት ከተለያዩ ዓለማት (በተለይም ከሕንድ) ከመጡ ባለሃብቶች እና ከሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር ሲፈራረሙ (ለምሳሌ ያክል እዚህእዚህ ይመልከቱ) ነው ዓመቱን ያሳለፉት፡፡ መሬቱ ደግሞ በዋነኛነት ጋምቤላ ክልል የሚገኝ ነው፡፡ 

የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40/6 ላይ ‹‹የመሬት ባለቤትነት የሕዝብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሁኖ የክልሉ መንግስት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወስነው ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል…›› ተብሎ በተደነገገው መሰረት ከክልሉ አጠቃላይ መሬት 42 በመቶውን (የኢትዮጵያ መንግስት በ2011 ለሂውማን ራይትስ ዎች በፃፈው ደብዳቤ ከክልሉ መሬት 36 በመቶውን ብቻ እንደሆነ ቢገልፅም) ‹ለግል ባለሀብቶች ያዘጋጀውት ነው› በማለት ለፌደራል መንግስቱ ‹ይሄን መሬት እኔን ሁነህ አስተዳድር-አከራይልኝ› በማለት  በ2001 አካባቢ የሰጠው ሲሆን፤ የፌደራል መንግስቱም በአቶ ተፈራ ደርበው አማካኝነት የተለመደውን ባለ ሃያ አንቀፅ ውል (ከ2058 እስከ 2061 ለሚደርሱ 50 ዓመታት) እየፈረመ (ይህ ፅሁፍ እስከተዘጋጀበት ሕዳር 2008 ድረስ) ለዘጠኝ የውጭና ለሶስት መቶ ሰማኒያ ሁለት/ሰማኒያ ዘጠኝ የግል ባለሃብቶች ሰጥቷል፡፡ ከነዚህ ኩባንያዎች መካከል እንደ Karituri (ካሪቱሪ በቅርቡ ለሽያጭ ጨረታ ቀርቧል), Ruchi Soya Saniti Agro Farm Enterprise (SAFE), BHO Agro Plc. Verdanta Harvest Plc የመሳሰሉት የሕንድ ኩባንያዎች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ነው ጋምቤላና ‹የመሬት ቅርምት› (land grab) ዓለማቀፍ ጩኸት ማዕከል ያደረጋት፡፡ 

ከክልሉ መሬት ግማሽ የሚሆነው (በሌላ አነጋገር የቤልጅየምን ግማሽ የሚያህል መሬት) ለግል ባለሃብት ሊሰጥ ተዘጋጅቷል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ 45,000 የሚጠጉ የክልሉ ነዋሪዎች በሰፈራ (villagization) ስም ከቀያቸው ተነቅለዋል፡፡ የሰፈራው ዋነኛ ዓላማም ‹ክልሉን ለግል ባለሃብቶች በስጦታነት ለማዋል ነው› በማለት ዓለማቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን መንግስት እየወነጀሉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የግል ባለሃብቶቹ ደን በማውደም የአካባቢውን ስነ-ምህዳር እያዛቡት ነው በሚል ተጨማሪ ውንጀላዎች ይቀርብባቸዋል፡፡ ባለሃብቶቹ ‹የCorporate Social Responsibility (CSR) መርሆቻችን ተግባራዊ እያደረግን ነው› ቢሉም፣ ፈቃድ ሰጭው የመንግስት አካልም ‹Environmental Impact Assessment (EIA) አድርጌ ነው ፈቃድ የምሰጠው› ቢልም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአካባቢው ማህበረሰብ ‹ይህ አውዳሚ ልማት (unwanted development) ነው› በማለት በባለሃብቶቹ ንብረት ላይ ጥቃት እያደረሰ ሲሆን የክልሉ መንግስትም ለፌደራል መንግስቱ ይህ የመሬት ቅሚያ እንዲቆም ጥያቄ ማቅረብ ጀምሯል፡፡ የፌደራል መንግስቱ ግን ጋምቤላ ‹የብሔር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን› እንድታከብር ከመምረጥ ባለፈ ለጥያቄዎቹ ምላሽ እየሰጠ አይደለም፡፡

ጋምቤላ እንግዲህ በነዚህ አስጨናቂ ሁኔታዎች መካከል እየቆዘመ ነው፡፡ የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ውጤት ደግሞ ክልሉን እጅግ ኋላ ቀር ያደረገው ሲሆን በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ዳታዎች እንደሚያመላክቱትም የጋምቤላ ክልል በውልደት መጠን (fertility rate) ከሀገሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር እንደያዘ ሲገልፅ ከሚወለዱት ሕፃናት መካከልም ብዙዎቹ የሚሞቱበት (infant mortality rate) ክልል ጋምቤላ ነው፡፡ በኤችአይቪ/ኤድስ ተጠቂነትም እንደ ጋምቤላ የተጠቃ ክልል የለም፡፡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከመቶ የክልሉ ነዋሪዎች ስድስቱ በኤችአይቪ ተጠቂ ናቸው ፡፡ በእናቶች ሞት፣ በመሃይማን ቁጥር፣ በመሰረተ ልማት ወዘተ ጋምቤላ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ክልሎች ጭራ ላይ ነው የምናገኝው፡፡ 

መፍትሔውስ? የተለያዩ አካላት ለመንግስት፣ ለለጋሽ ሃገራት፣ በክልሉ ለሚገኙ ልሒቃን፣ ለአፍሪካ ሕብረት የመሳሰሉት የጋምቤላን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመፍታት ይሆናሉ ያሏቸውን የተለያዩ ሃሳቦች በተለያዩ መንገዶች ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን ጋምቤላን በተለያዩ መንገዶች ጠፍረው ከያዟት ችግሮች ለማላቀቅ ይህ ነው የሚባል አንድ መፍትሔ ማቅረብ ከባድ ነው፡፡

3. ‹ኡሞትን አስራችሁ - ኡሞትን ፍቱልን›

በፈረንጆቹ 2005 ኖርዌይ የሚገኝው የኖቤል ኮሚቴ ‹ለኖቤል የሰላም ሽልማት› እጩ አድርጎ ካቀረባቸው ግለሰቦች/ቡድኖች መካከል የአሜሪካው Public International Law and Policy Group (PILPG) ይገኝበታል፡፡ ቡድኑ ለእጩነት የበቃው በሕግ ረገድ ለዓለም ሰላም ላበረከተው አስተዋፅኦ ነበር፡፡ ቡድኑ በ2005 ከሰራቸው ስራዎች መካከልም በዲሴምበር 2003 ጋምቤላ ውስጥ በአኝዋ ዘውግ አባላት ላይ በኢትዮጵያ መንግስት ለደረሰው በሰብዓዊነት ላይ ለተፈፀመ ወንጀል (Crimes Against Humanity) በሄግ ለሚገኝው ዓለማቀፉ የወንጀል ችሎት (International Criminal Court) ያቀረበው አቤቱታ ይገኝበታል፡፡ ባለ 26 ገፁ አቤቱታ የኢትዮጵያ መንግስት የፈፀማቸው ዓለማቀፍ ወንጀሎች በችሎቱ ተጣርተው የሚመለከታቸው አካላት እንዲጠየቁ የሚያሳስብ ነው፡፡ አቤቱታውን በጋራ በጁን 13, 2005 ፈርመው በጊዜው የፍርድ ቤቱ ዋና ዓቃቤ ሕግ ለነበሩት ለዝነኛው አርጀንቲናዊ ሉዊስ ሞሪንሆ ኦካምፖ ያስገቡት ደግሞ የAnuak Justice Council ሃላፊ አቶ ኦባንግ ሜቶ ናቸው፡፡

ይህ ከሆነ አስር ዓመታት ገደማ እየሆነ ሲሆን፤ የ2003ቱ ሁከትና ግድያ ሲፈፀም የክልሉ ፕሬዝደንት የነበሩትና ግድያውን በመቃወም የሚታወቁት ኖርዌጅያኑ አቶ ኦኬሎ አኳይ ዛሬ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ግድያውን አስተባብረዋል የተባሉትና በጊዜው የክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ሃላፊ ነበሩት አቶ ኡሞት ኡባንግ ከሃገር ኮብልለው ማኒላ፣ ፊሊፒንስ ከትመዋል፡፡ አቤቱታውን ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቶ ኦባንግ ሜቶ በሌሉበት በሽብርተኝነት ክስ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት 15 ዓመት ተፈርዶባቸዋል፡፡ የአኝዋን መጎዳት ለዓለም ማህበረሰብ ሲያሳውቁ የነበሩት ፓስተር ኦሞት አግዋም በሽብርተኝነት ክስ ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ 

ለግድያውና ለሁከቱ እስከ አሁን ድረስ የተጠየቀ አንድም አካል የለም፡፡ ለዚህም ነው የአኝዋ ልሂቃን ‹ኦሞት ኦባንግን አስራችሁ - ኦሞት አግዋን ፍቱልን› እያሉ የሚገኙት፡፡ ለዚህም ነው ‹በክልሉ ሰላምን ማምጣት ከተፈለገ የፍትህ መስፈን ቀዳሚ ነው› የሚለው ሃሳብን የሚሰነዝሩት፡፡ ለዚህም ነው ‹በክልሉ ውስጥ ግፍ የፈፀሙ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ሳይጠየቁ ንፁሃንን በግፍ በሽብርተኝነት እየከሰሰሱ ማሰር የክልሉን ችግር ቢያባብሰው እንጅ ሊያሻሽለው አይችልም› እያሉ የሚገኙት፡፡ ፍትህ ነው መፍትሄው?

4. ሊብራሊዝም? 

በታሕሳስ 2007 አስራ አንደኛው በበዓሉ አክባሪዎች አጠራር ‹የአኙዋ ጭፍጨፋ› መታሰቢያ በሚከበርበት ወቅት በተለያዩ የደቡብ ሱዳን ድረገፆች በአኙዋና - ኑዌር ልሂቃን መካከል ሞቅ ያለ ክርክርና ውይይት ነበር፡፡ የክርክሩና ውይይቱ መነሻ ደግሞ ኑዌሩ ዶ/ር Chuol Kompuok ‹Dancing with a wolf: A Reflection on Gambella Politics› በሚል ርዕስ የፃፉት ፅሁፍ ነው፡፡ ዶክተሩ ጋምቤላ ሰላም ትሆን ዘንድ የአኙዋና ኑዌር ግንኙነት ሰላማዊ መሆን እንዳለበት ገልፀው በመፍትሔነት ያስቀመጡት ጉዳይም እያንዳንዱን ግለሰብ ከቡድኑ ነጥለን እንደ ግለሰብ በማየት ፖለቲካልና ሲቪል መብቱን ማክበር የሚል ሊብራሊዝምን የሚያጣቅስ መፍትሔ ነው፡፡ ዶክተሩ በየዋህነት አክለውም አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለዚህ በመፍትሔ እንዲሰራ በመምከር ረጅሙን ፅሁፋቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ 

በተከታዮቹ ቀናት ግን ዶክተሩ ላቀረቡት ሃሳብ ከአኙዋ ልሂቃን ጠንካራና ተቃራኒ ሆኑ ምላሾችን ነበር ያስተናገዱት፡፡ (ከመልሶቹ በጥቂቱ እዚህእዚህ እና እዚህ ላይ ማየት ይችላሉ)፡፡ የአኙዋ ልሒቃን ያቀረቡት ሃሳብ ‹በአኙዋ ብሂል ግለሰቡ ከማህበረሰቡ ጋር የጠበቀ ግንኑነት (communal attachment) ያለው በመሆኑ ከማህበረሰቡ ነጥለን መፍትሔ ብናቀርብ አኙዋን እንጎዳዋለን› የሚል ነበር፡፡ እንዲያውም አንዱ መላሽ በብስጭት የአኙዋን መጉዳት ለዶክተሩ ሲያስረዱ፡ ‹‹For the time being it seems worst for Anwaa and excellent for Nuers, but it will come for Nuers the next day. Then no body survives at the end›› በማለት ነበር፡፡  

ዶ/ር Chuol Kompuok መሰረታዊ የሆነውን የሊብራል አስተምህሮ እንደመፍትሔ ሲያቀርቡ ከላይ እንዳየነው አሁን በኢትዮጵያ ያለው የዘውግ ፌደራሊዝም እንደ ጋምቤላ ያሉ ‹አውራ ዘውግ› የሌለባቸውን ክልሎች መፍትሔ የማይሰጥ መሆኑን ተረድተው ይመስላል፡፡ ታዲያ የፌደራል ስርዓቱ በዚህ ጉዳይ ላይ አርቆ አስተዋይነት የጎደለው (myopic) በሆነበት ሁኔታ ዶክተሩ ተሳስተዋል ማለት እንችል ይሆን?

5. ዴሞክራሲ! ዴሞክራሲ! አሁንም ዴሞክራሲ!

‹‹ፌደራሊዝም የአንድነት ሃይሎች (unionists) እና ተገንጣይ ሃይሎች (secessionists) አንድ ላይ እንዲኖሩ የሚያደርግ ስርዓት ነው›› የሚለው የፌደራሊዝም ትርጉም እንደኛ አይነት ሀገር ላይ በመርህ ደረጃ ለመጣው የፌደራል ስርዓት ተስማሚ ትርጉም ይመስላል፡፡ ይህ ሲባል ግን እውነተኛውን ፌደራሊዝምን መሰረት ያደረገ ጉዳይን ነው፡፡ ‹ዩጎዝላቪያን ያፈረሳት አሃዳዊ ስርዓት ሳይሆን የይስሙላ ፌደሬሽን (pseudo-federation) ነው› የሚለው ድምፅ በተደጋጋሚ ከተለያዩ ሃይሎች የሚሰማውም የይስሙላ ፌደሬሽን መዘዙ ብዙ እንደሆነ ለማስረዳት ነው፡፡ 

ፌደራሊስቱና ሶስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት የነበሩት ጀምስ ማዲሰን ስለ ፌደራል መንግስትና ክልሎች ግንኙነት ሲገልፁ ‹‹The Federal and State governments are in fact but different agents and trustees of the people, constituted with different powers, and designed for different purposes›› በማለት ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የማዕከሉና እና የክልል መንግስታት ግንኙነት ‹የአለቃና - ምንዝር› የሚሆን ከሆነ ፌደሬሽኑ ፌደሬሽን አይደለም ማለት ነው፡፡ ትክክለኛ ፌደሬሽን እንዲዘረጋና የማዕከልና የክልል መንግስታት የጎንዮሽ እኩልነት (horizontal equality) እንዲመሰርቱ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የግድ ነው፡፡ ያለ ዴሞክራሲ ትክክለኛ የፌደራል ስርዓት ሊኖር እንደማይችል Brian Galligan ‘Comparative Federalism’ ባሉት ፅሁፋቸው ሲያስረዱ፡

Can there be genuine federalism without democracy? The answer is negative if we are talking about modern or republican form of federalism. Moreover, it is hard to envisage alternative non-democratic bases to federalism that would be sufficient to anchor both spheres of government. If this is the case, successful federalism requires robust democracy in which citizens share membership of two political communities and participate politically in both.

በማለት ነው፡፡ ሲጠቃለልም ፌደራሊዝም ያለዴሞክራሲያዊ ስርዓት የይስሙላ ከመሆን ባለፈ የሚፈታው አንዳች ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ 

የጋምቤላን ጉዳይም ስንመለከት አብዛኞቹ ችግሮች የፌደራል መንግስቱ በጋምቤላ ሊጭነው ከፈለገው የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ የዘውግ ፌደራሊዝም ተነስተው፤ ኢሕአዴግ ለጋምቤላ በተለያዩ ጊዜያት የራሱን ፓርቲና የራሱን ግለሰቦች ሲሾም - ሲሽር የነበረበት ሂደት ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ የጋምቤላ ልሒቃንም ‹‹የፌደራል መንግስቱ እንደፈለገ ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ጣልቃ እየገባ ስለሚያውክ ነው የጋምቤላ አበሳ የበዛው፡፡ ክልሉን በዘውግ ደረጃ ከሶስት ከፍሎ፣ የጋምቤላን መሬት ለውጭ ባለሃብቶች እንደፈለገ እያከራየ፣ የፌደራል መንግስቱ ፖሊስና ወታደሮች በፈለጉት ጊዜ እየገቡና የፈለጉትን እየፈፀሙ፣ የፈለገውን ሰውና ፓርቲ ለክልሉ ከማዕከል እየሾመ ጋምቤላ ሰላም እንድትሆንና እድገት እንዲመጣ መመኝት ድካም ነው› በማለት በተለያየ ጊዜ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሊያጣጥም የሚገባውን የአንድነትና የተገንጣይ ሃይሎችን ፍላጎት ከመመለስ ይልቅ አዳዲስ ተገንጣይ ሃይሎች (secessionist movements) በማፍራት ዛሬ ጋምቤላን ከፌደሬሽኑ መገንጠልን እንደ ዓላማ በፕሮግራማቸው ይዘው የተነሱ ሃይሎችን ማየት ጀምረናል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ዶ/ር አስናቀ ክፍሌ የኢትዮጵያ ፌደሬሽን ‹‹… has neither granted political autonomy nor ended secessionist wars›› ብለው የፌደራል ስርዓቱን ከተቹበት አገላለፅ ባለፈ፤ አሁን ያለው ፌደሬሽን አዳዲስ ተገንጣይ ሃይሎችን እየፈጠረም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ‹ለዚህም መፍትሔው ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ነው› የሚለው ሃሳብ የብዙ የዘርፉ ምሁራን ሃሳብ ነው፡፡

ከላይ ያሉት ትችቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች እንዳሉ ሆነው፤ እንደ አሽኔ አስቲንና በኳች ማሞ ያሉ የክልሉ የፓርላማ አባላት እንዲሁም እንደ ኦባንግ ሜቶና ኦሞት አግዋ ያሉ የክልሉ ልሒቃንን ‹በሽብርተኝነት› ወንጀል እየከሰሱ፤ እያሰሩና ረጃጅም ፍርድ እየፈረዱ ክልሉን ‹የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን› በዓልን አክብር ቢሉት ጭፈራውና ደስታው ከቴሌቪዥን ማሞቂያነት ባለፈ ምንስ ፋይዳ ይኖረዋል?

Friday, December 4, 2015

የነዘላለም ወርቅአገኘሁ መከላከያ ምስክርነት ሒደት

በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝግብ ተከሰው የነበሩት 4 የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አብርሃም ሰለሞን ነፃ ቢባሉም በይግባኝ ታግደው ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት እየተመላለሱ እንደሆነ ይታወቃል። አሁንም ለቃል ክርክር ሕዳር 29, 2008 ተቀጥረዋል። ቀሪዎቹ፣ ማለትም ዘላለም ወ/አገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ባሕሩ ደጉ፣ ሰለሞን እና ተስፋዬ ከሕዳር 13–16, 2008 ድረስ ከፊል መከላከያዎቻቸውን ያስደመጡ ሲሆን ቀሪውን ዛሬ (ሕዳር 24, 2008) ያስደምጣሉ።
እነዘላለም ተከላከሉ የተባሉት በፀረ–ሽብር ሕጉ አንቀፅ 7/1 መሠረት የግንቦት 7 አባል በመሆን ሠርታችኋል በሚል ነው። በ5ቱም (ዘላለም፣ ዮናታን፣ ባሕሩ፣ ሰለሞን እና ነፃ ተብሎ በይግባኝ የተያዘው አብርሃም ሰለሞን) ላይ የመሰከሩት 3ተኛ የዐ/ሕግ ምስክር አቶ እዮብ ሲሆኑ፣ የምስክርነታቸው ጭብጥ በጥቅሉ ‘ዘላለም ወ/አገኘሁ መልምሏቸው ለግንቦት 7 ወታደርነት 3 ሰዎችን መልምለው ከወሰዱ በኋላ ጎንደር ላይ ባለመስማማታቸው እንደተመለሱ። ከ3ቱ አንዱ እዚሁ መዝገብ ላይ 8ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ሰለሞን መሆናቸውን። አቶ ዘላለም በባሕሩ እና ዮናታን ሥር የተደራጀ ቡድን መኖሩን እንደነገሯቸው’ የሚያስረዳ ነው።
አቶ ሰለሞን፣ ዮናታን እና ዘላለም ከፊል ምስክሮቻቸውን ያስደመጡ ሲሆን አቶ ተስፋዬ (10ኛ ተከሳሽ) ጉዳያቸው ከነዘላለም የተለየ ቢሆንም አንድ መዝገብ በመሆናቸው ምስክሮቻቸውን አስደምጠው ጨርሰዋል።
አቶ ሰለሞን ሁለት ምስክሮችን አቅርበው እዮብ "የተሻለ ሥራ አገናኝሃለሁ በሚል አቶ ሰለሞንን ወደጎንደር ከወሰዷቸው በኋላ ጎንደር ሲደርሱ ለግንቦት ሰባት ወታደርነት እንደሆነ ሲነግሯቸው" መመለሳቸውን አስመስክረዋል። ራሰቸውም በሰጡት ቃል እዮብ እየወሰዳቸው እያለ መቶ አለቃ እያለ ከሚጠራው ሰው ጋር በስልክ ይነጋገር እንደነበርና የዘላለምን ስም ጨርሶ እንዳልሰሙ ተናግረዋል። 
ዮናታንም በበኩሉ እስካሁን 4 ምስክሮችን አስደምጧል። የመጀመሪያው አብሮ አደግ ጓደኛው ሲሆን፣ ዮናታን ውጭ አገር ለሚደረግ የሰብኣዊ መብትና ሚዲያ ነክ ሥልጠና ሊሄድ መሆኑን ነግሮት እርሱም ከፈለገ ሲቪውን እንዲሰጠው ጠይቆት መስማማቱን፣ ነገር ግን ሥልጠናው ባልታወቀ ምክንያት መስተጓጎሉን ለችሎቱ አስረድቷል። በሁለተኝነት የቀረበው ምስክር አቶ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ ስለእነዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች ሠላማዊነት እና ሰጪዎቹም ዓለምዐቀፍ ዕውቅና የተቸራቸው ስለመሆኑ የባለሙያ ምስክርነቱን ሰጥቷል። በሦስተኝነት የቀረበው ምስክር አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ እዮብ ማዕከላዊ እያለ አናግሮት እንደነበር፣ ዮናታንን ፍፁም እንደማያውቀው፣ በኋላ ግን በድብደባ ብዛት እግሩ ተጎድቶ ማንከስ ሲጀምር እና ሥራ የሌላት ሚስቱና ልጁ ዕጣ ሲያሳስበው ተስፋ በመቁረጥ ሌሎቹ ላይ መስክሮ ሊፈታ መሆኑን እንደነገረው ለችሎቱ ነግሯል። በአራተኝነት ዘላለም ወ/አገኘሁ ቀርቦ እዮብ "ዘላለም በዮናታን ሥር ቡድን አለ ብሎ ነግሮኛል ያለው ሐሰት ነው" ብሏል።
ዘላለም ወርቅአገኘሁም ለራሱ እስካሁን 4 መከላከያ ምስክሮችን ያስደመጠ ሲሆን በቀዳሚነት የቀረበው ጥበቡ የተባለው አብሮ አደግ ጓደኛው ነበር። ጥበቡ፣ በክሱ ላይ የግንቦት 7 አመራር ተብሎ የተጠቀሰው ተድላ ደስታ አብሮ አደግ ጓደኛቸው እንደሆነና፣ እንግሊዝ አገር ከሄደ በኋላም ተማሩ እኔ ገንዘብ እልክላችኋለሁ ብሎ ገንዘብ ለሁለቱም እንደላከላቸውና ዘላለም ከመያዙ በፊት ማስተርሱን መማር እንደጀመረ ተናግሯል። የዘላለም እናት ወ/ሮ የኔእናትም በበኩላቸው ተድላ ደስታን ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያውቁት የልጃቸው ጓደኛ በመሆኑ መሆኑን ጠቅሰው በ2005 ብር ልኮለት እሳቸው ጨምረውበት ዘላለም ትምህርት መጀመሩን ለችሎቱ ገልጸዋል። ቀሪዎቹ ሁለት ምስክሮች ሙዘሚል እና አዲሱ የተባሉ በክሱ ላይ በዘላለም ለግንቦት 7 የተመለመሉ እንደሆኑ የተገለጹ ወጣቶች ናቸው። ሁለቱም ወጣቶች በየተራ ከዘላለም ጋር ያላቸው ዕውቂያ በሰፈር ልጅነት እንደሆነና ምንም ዓይነት የሚያውቁት ቡድን እንደሌለ እና በቁም ነገር ቁጭ ብለው ያወሩበት አጀንዳም እንደሌለ ተናግረዋል።
ዘላለምና ዮናታን በሰጡት መከላከያ ቃላቸውም ላይ ወደውጪ ለሰብኣዊ መብትና ሚዲያ ነክ ሥልጠናዎች ለመሄድ ክሱ ላይ የግንቦት ሰባት አመራር ተብሎ የተጠቀሰው እና እነርሱ በጋዜጠኝነቱ እንደሚያውቁት የተናገሩት አርጋው አሽኔ ጋር ከመነጋገራቸው በቀር ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። ዘላለም፣ ሌሎችን ላለማስፈራራት ሲል ዝርዝሩን እንደማይናገር ነገር ግን በሐምሌ ወር፣ በቀዝቃዛ እና ዘጠና ሳንቲሜትር በሆነች ጨለማ ክፍል ውስጥ 41 ቀን መቆየቱንና ጠባሳ የማይተው ነገር ግን የነርቭን ስርዓት በሚያዛባ ምት እየተመታ መመርመሩን ተናግሯል።
በጥቅሉ ዐ/ሕግ ያቀረበው ክስ እና ማስረጃ ጠቅላላ ምስል፣ «ከውጭ አገር ገንዘብ በሚላክለት ዘላለም አማካኝነት የተመለመለው እዮብ ለግንቦት ሰባት ወታደሮችን እየላከ፣ ዘላለምም በሠላማዊ ትግል ሥም ቡድኖችን እያዋቀረ እንደሆነ» ለማሳየት ሲሞክር፣ እነዘላለምም በመከላከያቸው «ከውጭ አገር የተላከው ገንዘብ የዘላለም አብሮ አደግ ጓደኛ ለዘላለም የግል ፍላጎት የላከው መሆኑን፣ እዮብ ለግንቦት ሰባት ወታደርነት [እያታለለ] በወሰዳቸው ሰዎች ውስጥ ዘላለም እጁ እንደሌለበት፣ ቡድን እየተባለ የሚጠራ ነገር እንደሌለ እና ዜጎች ሁሉ ቢወስዱት የሚመከር ሥልጠና ለመውሰድ መጻጻፋቸውን በዚያ መንገድ እንደተተረጎመባቸው» የሚያስረዳ የመከላከያ ምስል ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።