ሁለት የጎንዬሽ አቤቱታዎችን አስመልክቶ ዛሬ የተሰየመው ችሎት ከሌላ ጊዜው በባሰ ሁኔታ የወንጀል ስነስርአትና የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ ሲቀልድ ውሏል፡፡ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ እና ጦማሪት ማህሌት ፋንታሁን በጎብኚዎች የመጠይቅ መብታቸው መነፈጉን በቀን 20 ደቂቃ ብቻ ከሌሎች እስረኞች ከቅርብ ቤተሰብ ውጪ ሌላ አንዳይገባ እንደተከለከሉ መሰረታዊ መብቶቻቸው እስር ቤት ውስጥ አንደሚጣሱ ባለፉት ስድስት ወራት በተደጋጋሚ አቤቱታ ሲያቀርቡ የከረሙ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የመብት ጥሰቱን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ አልቀረበም፣ ከማረሚያ ቤቱ ጋር ያለውን አስተዳደራዊ ችግርን የመፍቻ መንገድ አልተጠቀሙም በማለት በውሳኔው የህገ መንግስቱን አንቀጽ 21 ሽሮታል፡፡ አያያዛቸው መሰረታዊ መብቶቸን የሚያስጠብቅ ይሁን ብሎ የተለመደውን የለበጣ ትእዛዝ አንኳን መስጠት ያቃተው የዛሬው "ፍርድ ቤት" የሁለቱን ወጣት ሴቶች መሰረታዊ የመብት ጥያቄ እነደዋዛ አጣጥሎታል፡፡
ሁለተኛው ጉዳይ የነበረው አቃቤ ህግ የሲዲ ማስረጃዎቹን ለተከሳሾች ሊሰጥ አንደሚገባ ሲጠይቅ የወንጀሉ ኤግዚቢት ነው በማለት ያቀረበውን መከላከያ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ ለተከሳሾች ሊሰጥ አይገባም ሲል ሌላ አስገራሚ ብይን አሰምቷል፡፡ ብይኑን ተከትሎ የተከሳሽ ጠበቆች የወንጀል ኤግዚቢት ከሆነ ሲዲው በአቃቤ ሀግ እጅ መገኘት አንደማይገባና በህጉ መሰረት ፍርድ ቤቱ እጅ መቀመጥ አንዳለበት በመሆኑም ሲዲው የት አንደሚገኝ የጠየቁ ሲሆን "ፍርድ ቤቱ" በጠበቆች ስላልተጠየቀ ሲዲው ሬጅስትራር ጋር መሆኑ እና አለመሆኑን እነዳላጣራ አስገራሚ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ይህንን አስተያት ተከትሎ የህግ ባለሞያው ዘላለም ክብረት ለፍርድ ቤቱ አጠር ያለ የወንጀል ስነስርአት ሂደትን የሚያስረዳ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ "በዚህ ሂደት ፍርድ ቤቱ በግልጽ ሲዲው የማስረጃው አካል ነው ወይስ ኤግዚቢት ነው የሚለውን አሁን ይንገረን ፡፡ ኤግዚቢት ነው ከተባለም አቃቤ ሀግ የማስረጃ አካል አድርጎ እንዳያቀርበው አሁን ብይን ይሰጥልን በማለት ጠይቋል"፡፡ "ፍርድ ቤቱም" ይህንን መወሰን ያለበት አቃቤ ህግ ነው የሚል የእለቱን አስገራሚነት የጨመረ መልስ ሰጥቷል፡፡ ይህንን ተከትሎ አቃቤ ሀግ ማስረጃ ነው ካለም በማስረጃ መስማቱ ወቅት በሂደት የሚታይ ነው ያለ ሲሆን ብይኑን ከጠበቆች እና ከተከሳሾች በቀረበበት ተከታታይ ጥያቄዎች ሲያምታታ ተስተውሏል፡። ተከሳሾች ተቃውሞ ካላቸው ይግባኝ ማቅረብ ይችላሉ የተባለ ሲሆን ጦማሪ ናትናኤል በበኩሉ አቃቤ ህግ ያለውን ብቻ በመስማት ተከሳሾች ላይ ተጽእኖ እያደረጋችሁ ነው ሲል "ፍርድ ቤቱን" ከሷል፡፡
በእስር ላይ አንድ አመት ሊሞላቸው አንድ ወር የቀራቸው የዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች በጠንካራ መንፈስ እና ፈገግታ ችሎቱን የታደሙ ሲሆን በፍርድ ቤቱ ውጥንቅጥ ምንም አይነት መገረም አልታየባቸው፡፡
የዞን9 ማስታወሻ
ከዚህ በፌት በተደጋጋሚ አንዳልነው የዞን9 ጦማርያን ፍርድ ቤት የሚሄዱት የፍትህ ስርአቱን ህጋዊ እውቅና እና ቅቡልነት ለማሰጠት ሳይሆን በቃል ስንለው የከረምነውን የፍትህ ስርአቱን ውድቀት በተግባር ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሁሉንም የህግ አማራጮች በመጠቀም ፍርድ ቤቱን በማጋለጣችን በእስርም ሆነ በስደት የምንገኘው የዞን9 አባላት በኩራት አንገታችንን ቀና በማድረግ የምንናገረው ጉዳይ ነው፡፡ በየቀኑ የራሱን መሰረታዊ መስፈርት እና ጥቃቅን የወንጀል ስነስርአት ህግ አንኳን መከተል ያቃተውን ፍርድ ቤት የሚመሩት ዳኞች ከችሎቱ ሲወጡ እና ከህሊናቸው ጋር በግልጽ ሲነጋገሩ የስራ አስፈጻሚው መሳሪያነታቸውን ቀን ከቀን በአሳፋሪ ሁኔታ እያጠናከሩ መሆኑን እነደሚያውቁት እርግጠኞች ነን፡፡ ራሳቸውን ከችሎቱ አግልያለው ብለው አስካሁንም ችሎቱን እየሰበሰቡ ባሉት አቶ ሸለመ በቀለ ለሚመራው ችሎት በተደጋጋሚ ጥሪ ስናደርግ እነደነበረው የፍትህ ስርአቱን ስም የማደስ እድላቸውን እየተጠቀሙበት ካለመሆኑም በተጨማሪ የነርሱ ከፍትህ እና ከታሪክ በግራ በኩል መቆም ከማሳየቱም በላይ የወጣት አስረኞቹን ልእልና ቀን ከቀን ከፍ ብሎ እነዲታይ እያስቻሉ ነው፡፡አገራቸውን በጨዋነት የሚያገለግሉ ምሁራን የዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች አምባገነንነት እና የተቃውሞ ድምጽ ማፈኛ መሳሪያ የሆነው የፍትህ ስርአት ያልፈታቸው ጨዋዎች መሆናቸውን በማስመስከራቸው እንኮራለን፡፡ የህሊና እስረኞቹ በማንኛውም መስፈርት ቢለኩ ከደረጃቸው በታች በሆኑ ዳኞች ፌት መቆም ያልነበረባቸው የቤተሰብና የአገር ኩራቶች ናቸው ፡፡
የፍትህ ስርአቱን ውድቀት ማጋለጡ ይቀጥላል፡፡
ዞን9