Saturday, March 30, 2013

#Ethiopia: ሁለት ማስታወሻዎች ለኢሕአዴግ


-------------------
በዋሲሁን አወቀ
-------------------

አንድ፡- ኢሕአዴግ ሆይ የምትናገረውን የምትተገብር ድርጅት ያድርግህ!!!

የፌደራሊዝም ነገር

እነሆ ከጥቂት ወራት በኋላ 22ኛ የልደት በዓሉን የሚያከብረው ኢሕአዴግ በአባላቱ እና በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን አስተያየትና ትችት ለመቀበል አሻፈረኝ እንዳለ የአንድ ወጣት ዕድሜ ሞላው፡፡ ኢሕአዴግ በተለያዩ ጊዚያትና አጋጣሚዎች የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እንዳስከበረ፣ በብሄራዊ ድርጅቶች መካከል ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል እንዳደረገ እና በክልሎች መካከል ተመጣጣኝ የዕድገት ደረጃ እንዳለ ሲናገር ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በተግባር ያለውና በኢሕአዴግ እየተነገረ ያለው አልገናኝ ብሎ ያስቸገረኝ እኔን ብቻ አይመስለኝም፡፡የብሔር ብሔረሰቦች መብት ተከበረ ሲባል ሁሉም ብሔር በሔረሰቦችና ሕዝቦች በዕኩልነትና በመፈቃቀድ በጋራ የሚኖሩበት ሁኔታ ሲመቻች እና በሀገሪቱ ባለው አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ እኩል ተሳታፊ መሆን ሲችሉ ነው፡፡ ይህ ግን ከንድፈ ሐሳብ ባለፈ ሲተገበር አላየሁም፡፡

አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት አንድን መንግሥት እንደመንግሥት ፀንቶ እንዲቆይ ከሚያስችሉት ነገሮች መካከል የመንግስት ጠንካራ መዋቅር ዋነኛው ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ መከላከያ፣ ደኅንነት፣ ውጭ ጉዳይ ፣የጠቅላይ ሚኒስቴር/ፕሬዚዳንት ስልጣን (እንደየሀገራቱ የመንግሥት አወቃቀር ይወሰናል) ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡በኢሕአዴግ የስልጣን ዘመን እነዚህ አራቱ ክፍሎች ከአንድ ብሔር በተገኙ ግለሰቦች እጅ ለበርካታ ጊዜ የቆዩና አሁንም የቀጠሉ ናቸው፡፡ መከላከያን ለምሳሌ ብንወስድ እንኩዋን ከጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ያሉ አመራሮች በአብዛኛው ከአንድ ብሔር የተገኙ መሆናቸው አስፍኜዋለሁ ያለውን ዕኩልነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ የደኅንነት ቢሮው እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መ/ቤቶችም ቢሆን በተመሳሳይ ሁኔታ መታማታቸው አልቀረም፡፡እንደውም ሁለቱን ቦታዎች ከእነሱ ውጭ ለመያዝ የሚያስብ ውጉዝ ከመአርዮስ የተባለ ይመስል እንደ አባት ርስት እየተፈራረቁ በውርስ መልክ ይዘዋቸዋል፡፡ ጠ/ሚኒስቴርነቱም ቢሆን በሰው እንጅ በአሠራር እና በአስተሳሰብ ነጻነቱን አላወጀም ብየ አምናለሁ፡፡

በኢኮኖሚ ጥቅምና በአጠቃላይ የእድገት ምጣኔ በክልሎች መካከልም ልዩነቶች ጎልተው ይታያሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ስብጥሩን እንኳ እንደምሳሌ ብንወስድ ልዩነቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ ለዚህ ልዩነት በኢሕአዴግ በኩል የሚሰጠው የማሳመኛ ምክንያት ደግሞ በክልሎች የመሠረተ ልማት አውታሮች በዕኩል ደረጃ ባለመስፋፋታቸው የኢንዱስትሪ ስብጥሩ እንዳይመጣጠን አድርጎታል የሚል ነው፡፡ ይህንን ልዩነት ማጥበብ ደግሞ 21 ዓመት ሲመራ የቆየው ኢሕአዴግ እንጅ የማንም ኃላፊነት አልነበረም፡፡

ኢኮኖሚውም ቢሆን በኑሮ ውድነቱ መናርና በኢኮኖሚው ቅጥ ያጣ ጡዘት ሕዝቡ እየተማረረ ቢሆንም ኢሕአዴግ ግን ተከታታይ ዕድገት እያስመዘገብኩ ነው ይላል፡፡ ይህ አባባል ጉም እንደመጨበጥ የሆነባቸው አንዳንድ ሰዎች መንግሥትን ያሙታል፡፡ አንዳንድ አካላት መንግሥት ነጋዴ፣ ደላላ አና አረጋጊ ሆኖ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ዓይነት ሥራ እየሠራ ኢኮኖሚውን እያጦዘብን ነው ይላሉ፡፡ ምክንያት ብለው የሚያስቀምጡት ደግሞ ትእምት (EFFORT)ን በመሳሰሉ የንግድ ድርጅቶቹ ኢሕአዴግ /በተለይም ህወሓት/ በእጅ አዙር እየተጠቀመ በመሆኑ የኢኮኖሚውን መረጋጋት እና የኑሮ ውድነቱን መለዘብ አይፈልገውም ነው፡፡ እንደውም ትልቁ ደላላ መንግሥት እንጅ ሌሎቹ አይደሉም የሚል ማማረርም መስማት አዲስ አይደለም፡፡

መቼም አንድ 21 ዓመት የሞላው ወጣት ምን ማድረግ እንዳለበት መካሪ የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ ኢሕአዴግ ግን እንደመንግስት ዕድሜ መቁጠር እንጅ መጎልመሱን እንድጠራጠር ስላደረገኝ የሚከተሉትን ምክሮች ለመለገስ ተነሳሁ


  • የፌዴራል /የሚኒስቴሮች/ የሥልጣን ክፍፍል በዕኩልነት ላይ የተመሠረተ ይሁን፡፡ በተለይም ደግሞ 4ቱ
  • ዋና ዋና ብዬ የጠቀስኳቸው ክፍሎችን በተመለከተ የተያዘው ጠቅላይነት ይቁም፡፡
  • የብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት ይረጋገጥልን፡፡ ዕኩልነታችን በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የጋራ ተጠቃሚነት
  • መርሕ በተግባር ይታይ፡፡
  • የክልሎች ዕድገት በዕኩል ደረጃ የሚሄድበት ሁኔታ ይመቻችልን፡፡ የኢንዱስትሪ ስብጥሩና የመሠረተ ልማት አውታሮች ሽፋን በእኩል ደረጃ ይዳረስልን፤
  • ሁሉም ብሔር፣ በሔረሰቦችና ሕዝቦች በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ በዕኩልነት ላይ እንድንወስንና እንድንሳተፍ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አጋጣሚዎች ይመቻቹልን፡፡

ኢትዮጵያ የሁላችንም እንጅ የጥቂት ግለሰቦች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ንብረት አይደለችም፡፡ ስለዚህ አሁን ስላለችው ብቻ ሳይሆን ስለወደፊቷ ኢትዮጵያም የሚያስቡ ዜጎችን ለመፍጠር ያስችል ዘንድ ኢሕአዴግ ጥርጊያውን ማስተካከል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡

ሁለት፡- ከድርጅታዊ በዓል እና ከብሔራዊ በዓል የቱ ይበልጣል?

ኢትዮጵያ ሀገራችን የአኩሪ ታሪክ ባለቤት መሆኗን ማንም የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡ ራሷን ለነጭ ቅኝ ገዥዎች
ሳታስገዛ፣ ዳር ድንበሯን አስጠብቃ ኖራለች፡፡ ለዚህ ደግሞ የአያቶቻችን እና የአባቶቻችን ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ሚናቸውን የምንዘክርባቸው የተለያዩ በዓላት ቀበሌያዊና አካባቢያዊ በሆኑ
በዓላት እየተተኩ አዲሱ ትውልድ እንዳይዘክራቸው እየተደረጉ ነው፡፡ ግንቦት 20፣ ህዳር 11፣ የካቲት 11……ወዘተ የመሳሰሉ የእርስ በእርስ ጦርነቶችን ውጤት የሚዘክሩ ሕዝባዊነት የሌላቸው በዓላት ከብሔራዊውና ሕዝባዊው የአድዋ በዓል በበለጠ መልኩ ሲከበሩ ማስተዋል ከጀመርን ይሄው 22 ዓመት ሊሆነን ነው፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በመርዝ፣ በእሳት፣ በጦር መሣሪያና በአካፋ በአሰቃቂ ሁኔታ በፋሺስት ኢጣሊያ የተጨፈጨፉበት ዕለት የሚዘከርበት የካቲት 12፤ ለእናት አገራቸው ዳር ድንበር መከበር እና ሉዓላዊተቷን ይዛ እንድትቀጥል ውድ ሕይወታቸውን የሰዉት ኢትዮጵያውያን የሚዘከሩበት የካቲት 23 በየትኛውም መስፈርት ብንለካው አሁን በመንግሥት (በኢሕአዴግ) ደረጃ ከሚከበሩት ግንቦት 20 እና መሰሎቹ አንጻር ያለው ሀገራዊ ፋይዳና ብሔራዊነቱ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ (መቼም ወንድሙን የገደለና የአገር ወራሪ ጠላትን የገደለ በእኩልነት የሚመዝን ካለ አዕምሮው በትክክል ስለመሥራቱ እጠራጠራለሁ፡፡)

ልዩነታቸውን ለማየት ያህል

አድዋ

  • ሕብረ ብሔራዊ በሆነ መልኩ የውጭ ወራሪ ጠላትን ለመመከት የተደረገ ታላቅ ተጋድሎ ነበር፤
  • ዳር ድንበርን ለማስከበርና የኢትዮጵያውንን ነጻነት እንደተጠበቀ እንዲኖር ለማድረግ መስዕዋትነት የተከፈለበት ነበር፤
  • የተረጋጋች እና አንድነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም የነጮችንበተንኮል የተሞላ የድንበር ማካለል ሥራ ለመግታት የተደረገ ጦርነት ነበር፤
  • ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ እንድትታወቅ ያደረገ፣ በርካታ አውሮፓውያን ቆንስላዎቻቸውን በአዲስ አበባእንዲከፍቱ ያደረገ ነበር፤
  • ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ ሲሉ መስዕዋትነትን መክፈል፣ ለሆዳቸው ሳይሆን ለነጻነታቸው እነዲታገሉ፣ ኢትዮጵያ የጥቂቶች ሳትሆን የሁሉም መሆኗን በተግባር ያሳየ ነበር፡፡

ግንቦት 20 ና መሰሎቹ
  • ወንድም በወንድሙ ላይ ጦርነት ያወጀበት፣ የኢትዮጵያውያንን ደም ያፋሰሰ የእርስ በእርስ ጦርነት ነው፤
  • ዳር ድንበርን ለማስጠበቅ ሳይሆን ስልጣን ለመቆናጠጥ የተደረገ ታሪካዊ ስህተቶችን የፈጠረ እልቂትነው፡፡ (ምጽዋና አሰብን ከእጃችን ያስወጣ በመሆኑ)፤
  • አንድነትንና መረጋጋትን ሳይሆን ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳ መስመር የከፈተ ነው፤
  • 21 ዓመት ሙሉ የኢትዮጵያን ሰራዊት (በደርግ ጊዜ የነበረውን) በጠላትነት የፈረጁ ሰዎች በአል ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ባለ ግንቦት 20ዎቹ ለኢትዮጵያዊነት ሳይሆን ለጎሰኝነት ያላቸውን አድልዖኦ ነው፡፡
  • ታሪክን ማንቋሸሽ ዋነኛው ዓላማቸው አድርገው መነሳታው ሳያንስ ሌላውን በመውቀስ ራሳቸውን ለማክበር
  • የሚጥሩ የምስኪኖች ስብስብ እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ አሁን ካለው ጋር ከመወዳድር ይልቅ ወደኋላ ተጉዘው ራሳቸውን ከጥንት ጋር በማወዳደር ለውጥ አመጣን ሊሉን ይፈልጋሉ፡፡ (በዲሞክራሲ፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በማኅበራዊ ዕድገት ወዘተ ጎረቤት አገሮች የደረሱበትን እየተመለከቱ እንኳ አያፍሩም!?)

እንደማጠቃለያ

የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯን አስጠብቃ፣ ታፍራና ተከብራ እንድትቆይ ያደረገ ታላቅ ድል ነው፡፡ በዓለም
ዙሪያ የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ራሳቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲሄዱና ለነጻነታቸው አንዲታገሉ ያስቻለ ነው፡፡

አሁን እየተሄደበት ያለው ታሪክን የማንቋሸሽ ተግባር በሕዝቦች መካከል ቅራኔን የሚፈጥር አንጅ
ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሌለው አጉል ኪሳራ ስለሆነም ኢትዮጵያዊ ነን የምንል ትውልዶች በሙሉ ይህንን ስህተት ሲፈጸም እያየን ማለፍ፣ የአባቶቻችን ውርስ አይደለም፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም የአያቶቻችን እና የአባቶቻችን ሚና የሚያንሰራራበትን መንገድ መፈለግ አንዱ መፍትሄ ይመስለኛል፡፡ የካቲት 12 ፋሺስት ኢጣሊያ የጨፈጨፋቸው ሰማዕታት መታሰቢያ፣ የካቲት 23 የአድዋ ድል በዓል መታሰቢያ፣ ሚያዚያ 27 የአርበኞች መታሰቢያ በመሳሰሉ በዓላት ላይ በመገኘት ታሪካቸውን መዘከር የኛ ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበን በድምቀት የምናከብበትና ከጥቃቅን እና አነስተኛ በአላት አከባበር የምንወጣበት ጊዜ ሩቅ እንዳሆን እመኛለሁ፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ከጨለመ መንጋቱ አይቀርም!
-----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው wasgreat03@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment