Friday, August 29, 2014

ይድረስ ለወዳጄ ከ6ተኛ ተከሳሽ- ክፍል ሁለት (በዘላለም ክብረት)

ይድረስ ለወዳጄ

ከ6ተኛ ተከሳሽ

ዘላለም ክብረት
የኔ ፅጌረዳ  ሰላም ላንቺ ይሁን! እንዴት ነሽልኝ? ባለፈው የፃፍኩልሽን ቧልታይ የበዛበት ደብዳቤ አነበብሽው ይሆን? ዛሬ ደግሞ ስለክሴ፣ ስለከሳሼና ስለአጠቃላይ ሁኔታዎች ልጽፍልሽ አሰብኩ፡፡ እንግዲህ በዚህ ደብዳቤ ትንሽ ኮስተር ሳልል አልቀርምና ከወዲሁ ይቅርታን እለምናለሁ፡፡

ግርምቴ
ከታሰርኩበት ሚያዝያ 17/2006 ጀምሮ በጣም ሲገርመኝ የነበረው ነገር የፖሊስ/የመንግስትና የሕግ ታላቅ እኩያ ከተያዝኩበት ደቂቃ ጀምሮ አውቆ በሚመስል መልኩ የተለያዩ የፍትሕ አካላት እያንዳንዱን የሕግ አንቀፆች በተግባር ሊጥሷቸው ማየቴ ነበር፡፡
 ለሕጎቹና ለሕግ አካላቱ ቅርብ በመሆኔ ምክንያት የመንግስት አካላቱ ይወስዷቸው የነበሩትን የተለያዩ ርምጃዎች በሕጉ አይን በማየቴ ሊሆን ይችላል የሕግ ጥሰቱ እጅግ ጎልቶ የታየኝ፡፡

የፍተሻ ፈቃድ (Search Warrant) ከእስር ማዘዣ (Arrest Warrant) ጋር በአንድ ወረቀት ላይ ተደባልቆ በመምጣቱ ገና ከመታሰሬ ነው የሕጉ ነገር ያሳሰበኝ የጀመረው፡፡ ሕግ ስንማር የፍተሻ ፈቃድ ከእስር ማዘዣ ተለይቶ እንደሚመጣ፣ በፍተሻ ፈቃዱ ላይ ሊፈተሽ የተፈለገው ነገር በግልፅ ሊቀመጥ እንደሚገባ፣ ፍተሻ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት መከናወን እንዳለበት …ብንማርም ‹ፖሊስ› በታሰርኩበት ወቅት አንዱንም የሕግ አንቀፅ ላለማክበር ያሰበ በሚመስል መልኩ የፍተሻ ፈቃድን ከእስር ፈቃድ ሳይለይ፣ ፍተሻውን ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ በመጀመር፣ በፍተሻው ምን ማግኘት እንደሚፈልግ የማይገልፅ የፍተሸ ፈቃድ በማሳየትና እኔ ስጠይቅም ለመናገር ፍቃደኛ ባለመሆን… ሕጉን‹ንዶ ንዶ› የኔን የግለሰቡን መብቶች በዜሮ በማባዛት ‹ወንጀልን የመከላከል እርምጃውን› ጀመረ፡፡ በፍተሻ ወቅት የሚፈለገው ነገር ምንነት አለመገለፁም ፖሊስ ‹ለጠረጠረኝ› ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል፣ በዛቻና በአድማ የመናድ ወንጀል እንደ ኤግዚቢት የያዛቸው ‹ማስረጃዎች› ምንነት ይገልጣቸዋል፡፡
በፍተሻ ወቅት ፖሊስ ከቤቴ በኤግዚቢትነት ከያዛቸው ‹እቃዎች› መካከል 90 በመቶው ገበያ ላይ ያሉ መጽሐፍት ሲሆኑ ከነዚሀም መካከል የPaulo Coelho “By the river paedra I set down and wept’ PV.I.Lenin ‘what is to be done’ የአፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል፣ የፍቅረስላሴ ወግደረስ ‹እኛና አብዮቱ›… ጨምሮ ሌሎች መፅሀፍት የሚገኝበት ሲሆን፤ የተለያዩ የሙዚቃ ሲዲዎችም በኤግዚቢትነት ተይዘዋል፡፡

(የሚገርመው ፍተሻው ሕገወጥ መሆኑን ‹ለፖሊስ› በተደጋጋሚ ብናገርም ‹ብርበራ ከጀመርን በኋላ ልናቋርጥ አንችልም›፣ የሚያስፈልገንን ነገር አንተ ልትነግረን አትችልም… የሚሉ መልሶች በመስጠት ‹አዲዮስ ሕግ› የሚል አሰራር ከመከተላቸውም በላይ በቤቴ የተገኘ እንደ ‹አዲስ ራእይ› አይነት መፅሄቶችን የብርበራው መሪ የሆኑ ግለሰብ ለበታች መርማሪዎች ‹ተዉት እሱ የኛ ነው› የሚል አመራር እየሰጡ ግርምቴን አብዝተውት ነበር፡፡ ጉዳዩን አስቂኝ የሚያደርገው ደግሞ በፍተሸው ወቅት ቤቴ ውስጥ ከተያዙት ‹ኤግዚቢቶች› መካከል አንዱም እንኳን ለክስ ማስረጃ ሁነው አለመቅረባቸው ነው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ለህግ ት/ቤት ‹search is not a fishing expedition in which the police grabs every thing › ተብለን የተማርነው፡፡)

የእስርና የምርመራ ጊዜ ደግሞ ፖሊስ ሕጉን ለመጣስ ሆን ብሎ የተጋ በሚያስመስለው መልኩ ሕጉ ግድ ሳየሰጠው የፈለገውን ሲያደርግ የከረመበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ነው ‹እኛ የሚያሳስበን የአንተ የአንድ ግለሰብ መብት ሳይሆን፣የሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብ ደህንነት ነው› የተባልኩት (ውዴ! Ayn Rand እንኳንም ይሔን ሳትሰማ ሞተች አላልሽም?)፡፡ በዚህ ወቅት ነው ‹የሽብር ሕጉን ጥርስ አውልቃችሁ አምጡ የሚለን ከሆነ ጥርስ ከማውለቅ ወደኋላ አንልም› ብሎ ፖሊስ ሕገ-መንግስቱንና የዜጎች መብትን በአንድ ላይ ሲቀብራቸው የተመለከትኩት፡፡ (‹ሕገ -መንግስቱ የሀገሩ ህጎች በሙሉ የበላይ ሕግ ነው› የሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ በምድረ በጋ የተደነገገ እንደሆነ ግንዛቤ ለመጨበጥ ችያለሁ)፡፡ በዚህ ወቅት ነው፡ የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እንዲፈፀምልኝ ለጠየኩት ጥያቄ ‹ሂድ ከዚህ!የማነው?! ፍርድ ቤት ማነው እኛን የሚያዘው? ከፈለገች ዳኛዋ ራሷ ትፈፅምልህ…› የሚል መልስ ‹ከህግ አስከባሪ ፖሊስ› የተሰጠኝ፡፡
            ‹‹ምን አይነት ዘመን ነው ፣ የተገላቢጦሽ፤
            አህያ ወደ ቤት፣ ውሻ ወደግጦሽ፡፡
ይሏል እንዲህ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ነው፤ ምንም አይነት ሕጋዊ መብቶቼ ሳይነገሩኝ ‹ለምርመራ የተቀመጥኩበትና ብሎግ ላይ የተፃፉ ፅሁፎች የእኔ ‹የእምነት ክህደት ›ቃል እንደሆኑ ተደርገው መፃፍ እንዳለባቸው ትእዛዝ የተሰዘጠኝና በእምነት ክህደት ቃሌ ውስጥ ወይ ‹ጥፋተኛ ነኝ› ማለት አለያም ባዶውን መተው እንጂ ‹ጥፋተኛ አይደለሁም› የሚል ነገር መስፈር እንደማይችል የተረዳሁትና ‹ለምን?› ብዬ ስጠይቅም ‹ከበላይ አካል የመጣ ትዕዛዝ› እንደሆነ የተነገረኝ፡፡ (ማሬ፣ ዕድለኛ ባልሆን ኖሮ እንደ ‹አንድ› አባሪዬ ‹ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ፣ ሕገ-መንግስቱ ይከበር ‹በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ› ብለህ ፈርም ተብዬ መከራዬን አይ ነበር፡፡)በዚህ ወቅት ነው፤ መንግስቴ በመጀመሪያ ‹በሽብር ወንጀል› ባይጠረጥረኝም የፀረ-ሽብር ሕጉ አንቀፅ 14 በሚያዘው መሰረት ስልኬን ከግንቦት 2005 ዓ.ም ጀምሮ በመጥለፍ ንግግሬን ሁሉ ሊያደምጥ እንደነበር የተረዳሁትና ‹‹እንዴ ‹የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም የማሴር ወንጀል› የተጠረጠርኩት ከታሰርኩ ከ23 ቀናት በኋላ ነው፤ ይሄም ፖሊስ እስከታሰርኩበት 23ኛ ቀን ድረስ በሽብር ጉዳይ ምንም አይነት ጥርጣሬ ያልነበረው ሲሆን ታዲያ ስልኬን አንድ አመት ለሚሆን ጊዜ እንዴት የፀረ ሽብር-ሕጉን ጠቅሶ ሊጠልፍ ቻለ?›› ብዬ ለጠየኩት ጥያቄ መልሱ ዝምታ እንደሆነ የተረዳሁት፡፡ (በነገራችን ላይ ስልኬ ለረጅም ጊዜ ቢጠለፍም ለማስረጃነት የቀረበብኝ ከአባሪዎቼ ጋር ‹ሻይ-ቡና እንበል እስኪ ብለን ያወራናቸው ወሬዎች ሲሆኑ፤ካንቺ ጋር ያውራናቸው ወሬዎች በማስረጃነት ባለመምጣታቸው ቅር መሰኘቴን በዚህ አጋጣሚ እገልፃለሁ፡፡)

  ግርምቴ ብዙ ቢሆንም እንዳይሰለችሽ በማሰብ አንድ የመጨረሻ ግርምቴን ልንገርሽና ሌላ ጉዳይ ላይ እናልፋለን፡፡ የእስር፣ የምርመራ፣ የብርበራ … ሁሉ ዓላማ ተጠርጥረው የተጠረጠረበትን ወንጀል የሚያረጋግጥ መረጃ ለማግኘት ቢሆንም ከሁለት ወራት ለሚበልጥ ጊዜ፣ እጅግ የተራዘመ ምርመራ ተደርጎብኝ የቀረበብኝን ክስ ስመለከት ብዙ ነገሮች አስገረሙኝ፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ የተከሰስኩበትን ‹የሽብር ተግባር ለመፈፀም የማሴር ወንጀል› በሚመለከት በምርመራ ወቅት አንድም ጥያቄ ያልቀረበልኝ ሲሆን፤ ይሄም ነገር ታዲያ የምርመራው አላማ ምን ነበር? እንድል አድርጎኛል፡፡ ሌላው ገራሚው ጉዳይ የሀገሪቱ ከፍተኛ የምርመራ ሂደት እንዲህ ቧልትና እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን ከሕጉ ጋር በመላተም እንደሚያከናውን መገንዘቤ ነው፡፡ ታዲያ ‹ፖሊስ› ህግን ለመጣስ ካለው ትጋት የበለጠ ምን አስገራሚ ነገር አለ ውዴ?!

 The Fridgegate Scandal እና ሌሎችም …

እኔ አሁን ደግሞ ወደ ክሴ ልውሰድሽ እስኪ ክሴን ባጭሩ ለማስረዳት ያክል (ምንም እንኳን ክሱ ግልፅ ባይሆንም፣ እኔ እንደመሰለኝ)፤ ‹የሽብር ቡድን በማቋቋም (ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ለማድረግ የሚልም ‹ይመስላል›)በሀገር ውስጥ የተለያዩ የሽብር ድርጅቶችን (ሰውን ለመግደል የሕብረተሰቡን ጤና ለከፍተኛ አደጋ ለማጋለጥ፣ እገታ ወይም ጠለፋ ለመፈፀም፣ ንብረት ለማውደም፣ በተፈጥሮ፣ በታሪካዊና በባሕላዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ የህዝብ አገልግሎቶችን ለአደጋ ለማጋለጥ ወይም በቁጥጥር ስር ለማዋልና ለማበላሸት) በመዘጋጀት፣ በማሴር፣ በማነሳሳትና በመሞከር የሚለው የመጀመሪያውና ዋነኛው ክሴ ሲሆን፤ሁለተኛው ክሴ ደግሞ ያች የፈረደባት ‹ሕገ-መንግስትንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን የመናድ ወንጀል ነው፡፡
            ሁለቱም ክሶቼ የቅጣት ጣሪያቸው እስከ ሞት ድረስ መሆኑን መግለፄም አያስከፋሽም ብዬ አስባለሁ፡፡ (ዘጠኝ ሞት መጥቶ ከደጅ ቁሟል ቢለው፣ ስምንቱን ተውና አንዱን ግባ በለው› አለ የሞት ዳኛ፡፡ እንደዳኛው ‹አንዱን ሞት ግባ› ብዬ ከመጋበዜ በፊት ብዙ የማጫውትሽ ጉዳይ አለኝና አስኪ ተከተይኝ ውቤ)

ከሳሼ ‹የሽብር ተግባራትን› ልፈፅም እንደተዘጋሁና እንዳሴርኩ እንዲሁም ‹ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ› እንደሞከርኩ ለማስረዳት ያቀረቡልኝ የማስረጃ ዝርዝርን ስመለከት ግን የአሳሪዎችን ፍላጎት ‹ወዲህ› መሆኑን የተረዳሁት፡፡

በምርመራ ወቅት አንድም ጥያቄ ያልቀረበልኝ ‹የሽብር ድርጊት› ዋና ‹ወንጀሌ› ሁኖ ሲመጣ አሳሪዬ ጋር ያለው ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ የወንጀል እንዳልሆነ ያስረዳኝ ሲሆን፤ በሰነድ ማስረጃነት ከቀረቡብን ብዙ ገራሚና አስቂኝ ‹ማስረጃዎች› መካከል ‹የሽብር ተግባራትን ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለመፈፀም እንዳሴርን› ያስረዳል ተብሎ የቀረበው ዋነኛና ብቸኛ ማስረጃም ከጓደኛዬና አባሪዬ አንደኛ ተከሳሽ፣ ሶልያና ሽመልስ (ክሷ In Abesntia) እየታየ ያለችና በአንድ ቀጠሯችን ፖሊስ ከ Interpol ጋር በመሆን ለመያዝ ጥረት እያደረገ እንደሆነ የገለፁት በጥብቅ የምትፈለግ ‹አሸባሪ› ቤት በሌለችበት ፖሊስ ላደረገው ብርበራ ማቀዝቀዣ  Fridge ዙሪያ ‹አገኘሁት› ያለው ግንቦት ሰባት የተባለ ፓርቲ በታህሳስ 2005 የወጣ የአባላት የውስጥ Newsletterና ቀኑ በሰነዱ ላይ ያልተመለከተ ሌላ የዚሁ ፓርቲ ሰነድ ነው፡፡

ውዴ ለመረጃ አንች ከእኔ ትቀርቢያለሽና ከላይ ስለጠቀስኩት ‹ሰነድ› ጉዳይ ብዙ ሰምተሻል የሚል ግምት አለኝ፡፡ እኔ ያለኝን መረጃ እና የዚህ ሰነድ ስለክስ ሒደቱ ሊኖረው ስለሚችለው አመላካችነት አንዳንድ ወሬዎችን እያመጣን እንተክዝ እስኪ፡፡

መቼም አሜሪካ ግሩም ሀገር ነው፡፡ ብዙ ነገሮች እንደቅሌት (Scandal) እየሆኑ ሲወጡ የምናይበት የቅሌቶች ሁሉ ቅሌት ድሞ የRichard Nixon ነው   ‘The Watergatge scandal’ ይሉታል፤ ኒክሰን በ1972 ለተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መረጃ ለማግኘት በማሰብ በ Washington DC የሚገኘውን የዲሞክራቲክ ፓርቲ ICT ዋና መሥሪያ ቤት Watergate የተባለው ሕንፃ ውስጥ) እንዲበዘበዝ በማስደረጋቸውና ይሄም ድርጊታቸው በፕሬሱ ይፋ በመሆኑ ኒክሰን ከስልጠናቸው ተዋርደው እንዲለቁ ሆነ፡፡

የWatergate ብዝበዛን ተከትሎ ብዙ ሐረጎች ለብዙ ሁነቶች መግለጫ በመሆን ይቀርቡም ጀመር ለምሳሌ ‘The Watergate Burglars’ ‘The Saturday Night Massacre:- ‘United States Vs Nixon’…. (የእያንዳንዷን ዝርዝር Google እያደረግሽ እንደምታይው ተስፋ አለኝ አበባዬ)፡፡ ከዛም በኋላ የተለያዩ ቅሌቶችን ከWatergate ጋር እያያያዙ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ አሁንም ሌላ ምሳሌ  ‘The Monicagate’ የፕሬዚዳንት ክሊንተንን የወሲብ ቅሌት ለመግለጽ)፣( ‘The Nipplegate’ (በ2003 ዓ.ም ጃኒት ጃክሰን በLive የቴሌቪዥን የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ባልታሰበ ሁኔታ ያጋጠማትን የጡት ጫፍ (Nipple) መራቆትና በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ታሪክን የቀየረ ሁነት ለመግለፅ)፤

ይሔን ሁሉ ማለቴ ወዴት ለመሔድ አስቤ እንደሆነ ሳትረጂው አትቀሪም ፍቅር፡፡ ከላይ ወደጠቀስኩልሽ ግንቦት 7 የተባለ ፓርቲ ሰነድ ጓደኛችን ቤት ተገኝ ስለመባሉ ጉዳይ ላስረዳሽ አስቤ ነው፡፡ ተገኘ የተባለው ሰነድ ላይ ጓደኛችን ወክለው ቤቷን ሲያስፈትሹ የነበሩት እናቷ ‹ይህ ሰነድ ፖሊስ ከፋይሉ ጋር ይዞት የመጣው ሰነድ ነው፡፡ እዚህ ቤት የተገኘ አይደለምና እዚህ ቤት ተገኘ ብዬ ልፈርም አልችልም› ማለታቸው በሰነዱ ላይ በግልጽ የተመለከተ ሲሆን፤ ሰነዱ ተገኘ የተባለበት ቦታ ደግሞ የጉዳዩን አስገራሚነት ያንረዋል- ማቀዝቀዣ (Fridge)!  (በነገራችን ላይ ፖሊስ የወንጀል ‹ማስረጃ› ከውጪ ይዞ ቤት ውስጥ በመጣል ‘Eureka’ ‹ማስረጃ› አገኘሁ የሚልበት ልማድ አዲስ አይደለም፤ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጉዳይ የተከሰሱ ብዙ ሰዎች የዚህ ዓይነት ‹ፖሊስ አመጣሽ› ማስረጃዎች ሰለባ መሆናቸውን እያነበብን/እየሰማን ነው የጎለመስነው፡፡ ፖሊስን ወደቤታቸው ፈትሸው ከማስገባት ጀምሮ የተለያዩ ፖሊስን የመጠበቅ አስቂኝ ተግባራትን በቤት ብርበራ ወቅት እንደሚያከናውኑ ስንለውም ኖረናል፡፡ አስቢው እስኪ ውዴ፤ ሕዝብ ፖሊስን ሲጠብቀው የሚኖርበት ሀገር!)

ለማንኛውም ይህ ‹ Fridge ማስረጃ› ‹አገኘሁ› የሚለው የፖሊስ ተግባር ነው… ‘The Fridgegate Scandal’ እንድል ያደረገኝ፡፡ እስርም፣ ክስም፣ ‹ማስረጃም›…. ከአሳሪዬ በኩል መምጣቱ ‹ፍርድም› ከአሳሪዬ በኩል ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ ቢከተኝም ተስፋ አልቆርጥም! ወዳጄ ‘The Fridgegate scandalን’ እንደ አንድ የክስ ሒደቱ ማሳያ ማቅረቤ ‘The Fridgegate Burgalrs’ ለፍትሕ ይቀርባሉ ብዬ በማሰብ አይደለም ወይም በባለስልጣኖቻችን መካከል ‘The Renaissance Massacre’ ተከስቶ ስልጣን ይለቃሉ የሚል ቅዠትም የለኝም፤ይልቁንም (በክርክሩ ሒደት የምናየው ቢሆንም) የቀረቡብን የሰነድ ማስረጃዎች አስቂኝነትና ምን እንደሚያስረዱ ካለመታወቃቸው አልፎ እንዲህ የአሳሪዎቻችን የቅሌት ተግባራት ውጤት መሆናቸውን ከ Alexander Hamilton የFederaliot Paper Number 78:

“The Judiciary is ‘beyond comparison the weakest of the three department of power”
ቃል ጋር አንድ ላይ ስመለከተው ‹ማስረጃ› ፈጣሪው› እና ጠንካራው አሳሪያችን ‹ደካማውን› ፍርድ ቤት እንዳይጫነው ብሰጋ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ሁሌም ተስፈኛ ነኝ፡፡ ማሬ በሕግ ቋንቋ (በልሳን) ትንሽ አውርተን ወደ ሌላ ጉዳያችን እንሂድ፡፡ ያን ረጅም የምርመራ ሂደት አልፈንና ሕግ-አስፈፃሚው ሂደቱን እንዲያስጠብቁ በሕግ-አውጭው የወጡትን የስነ-ስርዓትና መሰረታዊ የመብት መጠበቂያ (Procedual and substantive) ሕጎችን አንድ በአንድ እየሰባበረ ለሕግ ተርጓሚው አካል ያቀረባቸውን ‹የወንጀል ድርጊት ማሳያ ማስረጃዎችን› በሕግ ትምህርት ቤት ‘The Fruits of Poisonous free’ የተባሉት ሲሆኑ፤ ተስፋዬም ከሶስቱ የመንግሥት አካላት ደካማ የተባው ሕግ ተርጓሚው አካል የቀረበለት ነገር በትክክል ‹ፍሬ› እንዳልሆነ ይገነዘባል የሚል ሲሆን፤ ያ ካልሆነም ‹ፍሬው› ከተመረዘ ዛፉ ለሕግ ተርጓሚው አካል በግድ ካልገመጥ አይለውም አይባልም፤ ዛፉን ለመመረዝ አካል ፍሬውን ለማስገመጥ አይሰንፉምና፡፡ ፍቅር! ለማንኛውም ተስፋ ጥሩ ነው፡፡

መንግስቱ ኃይለማርያም ደሳለኝን (MHD) አየኋችሁ

የኔ እመቤት! እውነት እውነት እልሻለሁ እንደ መታሰር ያለ አስተውሎትን የሚያሳድግ ነገር የለም፡፡ ምክንያቴን ከነማስረጃዬ አቀርባለሁ፡፡ ያኔ በዞን ዘጠኝ እያለሁ (ከመታሰሬ በፊት) ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን አጠር አድርገን ‘HMD’ በሚል አፅርሆት እንጠራቸው ነበር፡፡ መታሰሬ ግን ዓይኔን አበራልኝና የእስከዛሬው አጠራራችን የፊደል መፋለስ እንዳለበት ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እንዴት?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሽብር፣ ስለእስርና ስለመንግስታቸው አቋም በቅርቡ ተጠይቀው የሰጡትን ምላሽ በኢቲቪ ተመለከትኩ፡፡ ‹‹እነዚህ አሸባሪዎች ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ የተዘረጋው የሽብር ሰንሰለት አካላት ናቸው (በነገራችን ላይ በቅርቡ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ከደቡብ ሱዳን ጁባ ተይዘው መምጣታቸውን ተከትሎ የሽብር ሰንሰለቱ ከአስመራ-ሞቃዲሾ-ጁባ ተለጥጦ ሶስት ማዕዘን መስራቱን መንግስት እየገለፀ ነው) ጋዜጠኛ ነኝ፣ ብሎገር ነኝ እያሉ የሽብር ዓላማን ማንገብ አይቻልም፡፡ እናንት ጋዜጠኞችም ተጠንቀቁ….›› አይነት ዱላ ቀረሽ ዛቻ ሲያሰሙ ተመልክቼ እንደሰውየው ‹ ኃይለማርያም አሁንስ መንግስቱን መንግስቱን መሰልከኝ ማለቴ አልቀረም፡፡ ለዛም ነው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግስቱ ኃይለማርያም ደሳለኝን (MHD) የሚለውን ስያሜ አፌ ላይ አልጠፋ ያለው፡፡

እንደዱሮው ‹ይሄ በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ አስተያየት መስጠት አልፈልግም› ማለት ቀረና እንደዳኛ ግራና ቀኝ የተቀመጡትን ጋዜጠኞች እየገላመጡ ቢሯቸው ውስጥ ፍርድ ስጡኝ፡፡ ሌላው ሁሉ ይቅር በሕግ ፊት ነፃ ሆኖ የመገመት ሕገመንግስታዊ መብቴን ያክብሩ አላልኩም፡፡ ባይሆን የቀረበብኝን ‹ማስረጃ› ተመልክተው ፍርድዎችን ይስጡም አልልም፡፡ ግን ግን ‹ለባንዲራ ፕሮጀክታችን› (የሕዳሴው ግድብ) ማሰሪያ ይሆን ዘንድ የሁለት ወር ደመወዜን ለቦንድ መግዣ (ምንም እንኳን ለቦንድ ግዢ ጠቅላላ ክፍያ ሳልጨርስ ከስራ በመሰናበቴ ምክንያት ደመወዜ ቢቋረጥም) መስጠቴን እንደውለታ ቆጥረው በቤተ-መንግስት የዘረጉት ‹የፍርድ ችሎት› ላይ ምህረት ቢያደርጉልኝ ምን አለ? ‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ እህል ላበደረ አፈር› ይሰጡታልን?
ውቤ! ለማንኛውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተበየነብንን የሽብርተኝነት ካባ በፍርድ ቤት እንደማይፀናብን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

‹የነሲቡ ችሎት›

አፈ ንጉስ ነሲቡ መስቀሉ ከ1874 ዓ.ም ጀምሮ ወደ 30 ዓመት ለሚሆን ጊዜ በዳኝነት የተለያዩ የኢትዮጵያን ነገስታት ያገለገሉ ሲሆን ፍርዳቸው እጅግ ከባድና ጠንካራ ስለነበር በዘመኑ ‹እባክህ ከነሲቡ ፊት አታቁመኝ› እየተባለ ይለመን እንደነበር መርስኤ ሀዘን ወልደቂርቆስ በዓይን ያዩትን፤ በጆሮ የሰሙትን፤ ከትበው ይነግሩናል፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ በንጉሱ ዘመን አርሲ፣ አሰላ ላይ እጅግ ጨካኝ ደኛ ተሹመው ፍርዳቸው ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ‹አቤት አቤት፤ የአሰላው ፍርድ ቤት› እስከመባል ደርሶ እንደነበር አሁንም ማስረጃችን ታሪክ ነው፡፡

ውዴ! ይሔን የምፅፍልሽ የእኛው ዘመንን ‹የነሲቡ ችሎት› አስመለክቶ ትንሽ ነገር ብዬሽ ደብዳቤዬን ልቋጭልሽ በማሰብ ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 652/2001 (የፀረ-ሽብር አዋጅ) ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በሽብር ጉዳዮች ላይ ስልጣን (Juridiction) ያለው የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንደሆነ በመደንገጉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ተኛ ወንጀል ችሎት የተለያዩ በፀረ-ሽብር ሕጉ የተከሰሱ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ጉዳይ እያየ የቆየ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹የፀረ-ሽብር ሕጉ ሰለባዎች› እየተበራከቱ በመሔዳቸው ምክንያት 4ተኛውን ወንጀል ችሎ ለማገዝ በማሰብ 19ኛ ወንጀል ችሎ የሽብር ጉዳዮችን በማዬት ላይ ይገኛል፡፡

በፀረ ሽብር ሕጉ ተከሰውኖ 4ተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ነፃ የወጡ (Acquit) ሰዎች ብዛት ለጊዜው ለማወቅ ባልችልም እጅግ በጣም ትንሽ እንደሆኑ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህ የሆነው ችሎቱ ከሌሎች ችሎቶች የተለየ በመሆኑ እንዳልሆነም አስባለሁ፡፡ ይልቁንም ችሎቱ የሚይዛቸው ጉዳዮች በፀረ-ሽብር ሕጉ አግባብ ለማየት ስለሚገደድ ነው፡፡ መቼም የፀረ-ሽብር ሕጉን አሳፋሪነትና ጅምላ ጨራሽነት ላንች እንዳዲስ በመንገር ጊዜሽን አላባክንብሽም፡፡ ለዛም ነው በዚህ ዘመን ‹እባክህ ከ4ተኛ ወንጀል ችሎት ፊት አታቁመኝ› ወይም ‹አቤት አቤት፣ 4ተኛው ወንጀል ችሎት› ብንል ብዙም የማያስገርመው፡፡ የፀረ-ሽብር ሕጉ ከሚሰጠው ሰፊና ጠቅላይ የሆነ የወንጀል ትርጉም አንፃር ከልብ ወለዳዊው ‘Moratorium on the Brain’ አዋጅ ጋር በተነፃፃሪ መቆም የሚችል ከመሆኑም በላይ በሽብር ጉዳይ የተሰየወን ችሎትም እጅግ አሳፋሪ ያደርገዋል፡፡

እንግዲህ የእኛም ጉዳይ የ4ተኛ ወንጀል ችሎት እህት ከሆነው 19ነኛ ወንጀል ችሎት እየታዬ የሚገኝ ሲሆን የፀረ-ሽብር ሕጉም ‹ሰለባ› ፍለጋ በችሎታችን ተገኝቷል፡፡ እንግዲህ አበባዬ ጉዳያችን በፀረ-ሽብር ሕጉ ከመታየቱ ጋር ተያይዞ ስራ አስፈፃሚው አካል ‹ማስረጃ› ፈጥሮ የከሰስን መሆኑ ነው ችሎቱን ‹የነሲቡ ችሎት› ያደረገው፡፡ ለማንኛውም ግን ይሄን ስታነቢ ታዲያ ‹ከአንበሳ መንጋጋ፣ ማን ያወጣል ስጋ› ብለሽ ተስፋ እንደማትቆርጪ አምናለሁ፡፡ እኔና አንች እኮ ተሸንፈን አናውቅም ውዴ፡፡ ሁሌም ማሸነፍ፣ ሁሌም ሌላ ተስፋ ማድረግ፣ ሁሌም ደስተኛ መሆን፣ ሁሌም መዋደድ የሕይወት ግባችን አይደለምን ? ታዲያ ይችን ክስ በድል እንዳንወጣት ማን ያግደናል? ምን አልባት አሳሪያችን፡፡ Hamilton በድጋሚ ጠቅሼልሽ ተስፋችንን አለምልመን እንለያይ፡

‘The Judiciary (…) has no influence over either the sword or the purse (…) It may truly be said to have neither force nor will, but merely judgement’


Amen!


                                                                                                                        ያንችው ዘላለም
                                                                                                                        ከብዙ ፍቅር ጋር!

Thursday, August 21, 2014

‹‹ይድረስ ላንቺ›› ተፃፈ ከስድስተኛ ተከሳሽ - በዘላለም ክብረት

ዘላለም ክብረት 

ወዳጄ ልቤ ከቶ እንደምንድን ነሽ? እውን እኔና አንቺ በአለም ስንኖር ሌላ የመገናኛ ዘዴ አጥተን ወደ snail mail እንመላለሳለን ብለሽ አስበሽ ታውቂያለሽ? ለማንኛውም እንዲህ ሆነ፡፡ ጥጋበኛ ሰው ያስቀናኝ ጀምሮልሻል፣ ጥጋበኛ እንዲህ የሚለው ትዝ አለኝ፡፡

‹‹ ….ደብዳቤ ቢጽፉት እንደ ቃል አይሆንም፣
እንገናኝ እና ልንገርሽ ሁሉንም….››

የደላው! ቢያሻው በደብዳቤ፣ ሲፈልግ በአካል እያማረጠ እኮ ነው፡፡ ለእኔ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ሁለቱም ቅንጦት ነው (ወይ ደብዳቤው አይደርስሽም ወይም አንቺን ማየቴ ሊገደብ ይችላል)፡፡ ቆይ ትንሽ የጎን ወሬ ላዋራሽና ምክንያቱን እነግርሻለሁ፡፡ ‹‹አንቺ›› ተብለሽ በዚህ ደብዳቤ ስለተጠቀስሽው ‹‹አንቺ››ና ይሄን ደብዳቤ ለሚያነቡ ወዳጆች የዕምነት ክህደት ቃሌን በትንሹ ላስፍር፡፡

እመቤት ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ፍቅረኛ (Ethiopian by choice) ዱቼ ሞሶሎኒ እትዮጵያን በወረረ ጊዜ፤ ወራሪው ሃይል በመላው ኢትዮጵያ ‹‹ የኢትዮጵያን ስም እያነሱ መፃፍ ክልክል ነው›› የሚል ያልተፃፈ አዋጅ አውጆ እንደነበር ይነግሩናል፡፡ በዚህም ምክንያት ፀሀፍቱና አዝማሪያኑ ስውር መጠሪያ መጠቀም ስላስፈለጋቸው እስከ ዛሬ ድረስ ተወዳጁ ሕዝባዊ ዘፈን አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ እንደ ስውር የፍቅር ዘፈን ተበርክቷል፡፡ በዘፈኑ ‹‹አንቺ ልጅ ›› የተባለችውም ኢትዮጵያ ናት፡፡ እኔስ በዚህ ዘመን ‹ይድረስ ለባለ ታሪኩ›፣ ‹ይድረስ ለባለ ንብረቱ›… እንደሱ የሀዘን ደብዳቤ ርእስ ‹ይድረስ ለኢትዮጵያ › በማለት ፋንታ ‹ይድረስ ለአንቺ› ለማለት ስውር መጠሪያ ተጠቅሜያለሁ? ፤ በፍፁም! ጌቶች እንደሚሉት ሕገ መንግስቱ የመናገር ነፃነቴን ሙሉ ለሙሉ አስከብሮልኛልናi
ቧልቱ ይቆየንና በዚህ ደብዳቤ ርዕስ ዙሪያ ያለማንም አስገዳጅነት የእምነት ክህደት ቃሌን ላስፍር አንቺ የተባለችው ኢትዮጵያ አይደለችም፡፡ ‹አንቺ› የኔዋ ሀቢቢ ግን ባለሽበት ይድረስሽ፡፡ ውዴ እንግዲህ በዚህ ደብዳቤ ያለፈውን እያነሳሁ እነግርሻለሁ፡፡ወይ ትስቂያለሽ (ሳቅሽ እንዴት ያምራል?) ወይ ደግሞ ታዝኛለሽ (እኔን!)

ይህንን ደብዳቤ የመፃፍ መብት
እነሆ ላንቺ ስለሆነው ሁሉ ላጫውትሽ ስጀምር፤ በመነሻው ያሰብኩት ነገር ይሄን ደብዳቤ የመፃፍ ሕጋዊ መብት አለኝን? የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም መነሻዬ አሁን ያለሁበት ሁኔታ ነው፡፡ በመጀመሪያ “ሕገ-መንግስታዊ ስርአቱንና ሕገ-መንግስቱን በሀይል ፣በዛቻና በአድማ ለመናድ በመምከር/ በመናድ” ወንጀል ተጠርጥሬ የታሰርኩ ቢሆንም፤ በታሰርኩ በ23ኛው ቀን ወንጀል ወንጀልን፤ ጥርጣሬ ሌላ ጥርጣሬን እየወለደ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም ለማሴርና ለማነሳሳት ወንጀል ተጨማሪ ጥርጣሬ በፓሊስ ዘንድ በማሳደሬ የክፋት ልኬ ከፍ ያለ ሲሆን፤ በመጨረሻም ሕገ-መንግስቱን እንደ እያሪኮ ግንብ ለመናድ በመሞከር፤ ሕብረተሰቡን ደግሞ ከሚተነፍሱት የሰላም አየር ለማቆራረጥ ከማሰብ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ ተይዟል በሚል ወንጀሎች ተከስሼ በማረፊያ ቤት እገኛለሁ፡፡ ይሄን ሁሉ የምነግርሽ ‹ለ አንቺ› አዲስ ነገር ነው በማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ያለሁበት የእስር ሁኔታ ደብዳቤ ካንቺ ጋር እንዳልፃፃፍ ይከለክለኛልን?  የሚለውን ለማስረዳት በማሰብ ነው፡፡

መቼም አሁን ያለሁበት ሁኔታ ተገቢ ነው ብዬ ባላምንም ‹ ዋስ ጠበቃዬ ነውና› ስለመብቴ ስናገር ያን የፈረደበት ህግ መጥቀሴ አልቀረም፡፡ ታዲያስ በእስር ላይ ያለ ሰው ከወዳጁና በሕይወቱ ጋር ደብዳቤ ሊፃፃፍ ምን ገደብ አለበት? ይላል ስል፤ ስለፌደራል ታራሚዎች አያያዝ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/1999 በአንቀፅ 18 ላይ "ታራሚዎች (ተጠርጣሪዎች) ከማረሚያ ቤቱ (ከማረፊያ ቤቱ) ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር መፃፃፍ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ሆኖም ለጥበቃ ስራ ተቃራኒ የሆነ ተግባር እንዳይፈፀም በፅሁፎቹ ላይ ቁጥጥር ይደረጋል" በማለት የኔና አንቺ ደብዳቤ መፃፃፍ በሕግ የተፈቀደ ነገር እንደሆነ ደንግጎልናል፡፡ አሜን! (እንዲያው ይሄ ልጅ አሁንስ ተስፋዬ.. ማነው ? ሕጉ አይደለምን... የሚል የጅል ዘፈኑን አላቆምም እንዴ? ብለሽ እንደማታሾፊብኝ እምነቴ ነው)  ጓድ ሌኒን በዛች የፒተርስበርግ እስር ቤት ውስጥ ደብዳቤ መፃፃፍ አትችልም ተብሎ ተከለከለ እርሱ ግን የ Russia Social Democratic Party ን ፕሮግራም መፅሀፍ ውስጥ በየመስመሮቹ መሀል በ Invisible Ink በመፃፍ ታሪክ ስራ፡፡ እነሆ እኔ ግን በትናንት ሌኒኒስቶች (ፋና)፤ በዛሬ አሳሪዎቻችን መልካም ፈቃድ ደብዳቤ የመፃፃፍ ሕጋዊ መብቴ ተከብሮልኝ ይሔው በነጩ ወረቀት ላይ እንደ ሕዳሴው ባቡር እፈነጭበታለሁ፡፡

እንዲህ ሆነልሽ
አበባዬ- አፄ ሀይለስላሴ ከማንኛውም ባለስልጣን በሕይወት ዘመናቸው የበለጠ የቀረቧቸው የነበሩት ከ1934-1948 ድረስ ለ14 ዓመታት በፅህፈት ሚንስትርነት ያገለገሏቸውን ፀሀፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዎርጊስ ወልደ ዮሀንስን እንደ ነበር ነግሬሻለሁ? ወዳጅነትና ፍቅር ያልፋልና ሀይለስላሴና ወልደ ጊዎርጊስ ተጣሉ፡፡ የአፄ ሀይለስላሴ መንግስት መፅሀፍ ፀሀፊ አቶ ዘውዴ ረታ የወልደጊዎርጊስን መጨረሻ ሲተርኩ፡፡

‹‹ ፀሃያማው ሚያዚያ 17/1948 ቀን ለ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሀንስ እንደ ሌሎቹ ቀናት ብሩህ ሁና ነበር የነጋችው፡፡ ብሩህ ሁና እንደምታመሽም አልተጠራጠሩም ነበር፡፡ ምን ያደርጋል! ያች ክፉ ሰኞ የወልደጊዎርጊስ ከፍተኛ ስልጣን መጨረሻ ሆነች፡፡ በእኩለ ቀን ገደማ ቤተ መንግስት ተጠርተው ከፅህፈት ሚንስተርነታቸው ተነስተው የአሪሲ ጠቅላይግዛት ደረሳቸው››
(መፅሀፉ አጠገቤ ስለሌለ ቃል በቃል አልጠቀስኩም)

ወልደጊዮርጊስ ተሽረው ከቤተ-መንግስት እንዲርቁ የተደረገበት ምክንያት የሀይለስላሴን ወንበር በሰዒረ መንግስት ለመገልበጥ አስበዋል በሚል ምክንያት ነበር፡፡ወልደጊዎርጊስን እዚህ ጋር ማንሳቴ የሚያዚያ 17 ስለት እኔም ጋር በመድረሷ ነው፡፡ ውዴ! የእኔዋን ሚያዚያ 17/2006 ዓ.ም ውሎ እንደ ዘውዴ ረታ ስተርክልሽ ይሔን መሳይ ይሆናል፡፡

 ‹‹ ፀሃያማዋ ዓርብ ሜያዚያ 17/2006 ዓ.ም አጀማመር እንደ ወትሮው አልነበረም፡፡የጠዋት ትምህርት ክፍለ ጊዜ እንዳይረፍድብኝ እየተቻኮልኩ ወደማስተምርበት (የመጨረሻ ክላስ ነበር) አምቦ ዩንቨርሲቲ ስሄድ፤ ተማሪዎች አዲስ የተዘጋጀውን የአዲስ አበባ ከተማ መሪ እቅድ ‹ሕገ-መንግስታዊ አይደለም በሚል መነሻ የተለያዩ መፈክሮችን እያሰሙ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር፡፡ ሰልፉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ እንደተጠናቀቀ በሰልፍ ምክንያት የቀረውን የመጨረሻ ክላስ ሚያዚያ 18/2006 ዓ.ም ለማካሄድ ተማሪዎቼ ጋር ቀጠሮ ይዤ ብለይም ‹ሰው ያቅዳል ፣ እግዜር ይስቃል› እንደሚባለው ሆነና በዛች ሚያዚያ 17/2006 ዓ.ም ማምሻ ላይ እንደ ወልደጊዎርጊስ ወልደ ዮሃንስ ‹የመንግስትን ዙፋን በሕዝባዊ አመፅ ልትነጥቅ አሲረሀል› በሚል ክስ በቁጥጥር ስር እንደዋልኩ የደህንነት ግሪሳዎች (8 ወይም 9 የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አባላት ) አበሰሩኝ፡፡

 ነገሩ ብዙም አልገረመኝም፡፡ ትንሽ ያበሳጨኝ አቶ ዘላለም ለጥያቄ ስለምንፈልጎት አዲስ አበባ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማእከላዊ) ነገ ጠዋት 3 ሰዓት እንዲገኙ ብለው በስልክ ቢጠሩኝ ‹እሺ ነገ ሶስት ሰአት ላይ ክላስ አለኝ ከክላስ ወደ 9 ሰዓት አካባቢ አመጣለሁ › ብዬ የምቀርበውን ሰው ይሔን ሁሉ ሀይል ከሁለት መኪና ጋር በመመደብ ላከበረኝ መንግስቴ ‹ጉዳት› ባሰብኩ ግዜ ነው፡፡ ላክባሪዬ ውለታ መላሽ ያርገኝ i

ዓለሜ- ደብዳቤዬን እያነበብሽው እንደሆነ ተስፋ አለኝ፡፡ በቁጥጥር ስር ውሏል የምትለው ሀረግ ድሮም ትንሽ ፈገግ ታደርገኝ ነበር፤ አሁን ደሞ እኔን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከአዲስ አበባ የመጣው የደህንነት ቡድን መሪ የመሰለኝ እድሜው ትንሽ ገፋ ያለ ሰው አንድ ሶስቴ ስልክ እየደወለ (ለማን ይሆን) ‹በቁጥጥር ስር አውለነዋል› እያለ መልክት ሲያስተላልፍ ስሰማ ፈገግ ማለቴ አልቀረም፡፡ ሀሳቤ ልቤ ፣ ይሄውልሽ ከስራ ቦታዬ  ‹ሀገር ሰላም› ሕዝባዊ አመፅ ለመቀስቀስ አስበሃል በሚል ጥርጣሬ በቁጥጥር ስር የዋልኩት እንዲህ እንደገለፅኩት ነበር፡፡ ከሚያዚያ 17/2006 -ሀምሌ 11/2006 ዓ.ም ያሉት 84 ቀናት የተደጋገሙና ሕይወት አልባ በመሆናቸው እንዲሁ ከማሰለችሽ 5 ሁነቶችን ልፃፍልሽና ዘና በይ፡፡ ከሁነቶቹ በፊት ግን ስለ 84 ቀናቱ አጭር መግለጫ ልስጥሽ፡፡

የመጀመሪያዎቹን 75 ቀናት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ጥብቅ ጥበቃ ክፍል (Siberia) ውስጥ 5 ቁጥር የተባለ 4 ሜትር በ5 ሜትር የሆነችና 5 ፍራሾችን በምትይዝ ክፍል ውስጥ ከረምኩ፡፡ ክፍሉ የተፈጥሮ ብርሀን በምንም አይነት መንገድ (ቀንን ጨምሮ) የማይገባበት ሲሆን፣ ለ24 ሰዓታት የመብራት ብርሀን ይበራበታል፣ መብራት ሲጠፋ በጄኔሬተር ሀይል ይተካል፡፡ ጄኔሬተሩ ነዳጅ ሲጨርስ ደግሞ ቀንም ሆነ ማታ ጨለማ ነው ባትሪ፣ ሻማ፣ ማንኛውንም አይነት ሰዓት መያዝ አይቻልም፡፡ ጠዋት 12 ላይ ለ10 ደቂቃ ፤ ማታ ከ10 ሰዓት አስከ 12 ሰዓት ለ 10 ደቂቃ ሽንት ቤት ለመጠቀም የክፍላችን በር የሚከፈት ሲሆን፤ በቀን ውስጥ ከ15 – 20 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ ደግሞ ከክፍላችን በየተራ ወጥተን ነፋስ/ፀሀይ እናየለን፡፡ ከዛ ውጭ በቀን ውስጥ ከ23 ለሚበልጠው ሰዓት የክፍሉ በር ዝግ ሲሆን ጮክ ብሎ ማውራትና መዝፈንም ቅጣት ያስከትላል፡፡

ወዳጄ በነዚህ 75 ቀናት ስንት ‹አሸባሪ› ወዳጆችን አፈራሁ መሰለሽ፡፡ መንግስቴ የ 15 እና የ14 ዓመት ልጆችን በአሸባሪነት ጠርጥሮ እንደሚያስርም ለመረዳት ችያለሁ፡፡ አብረውኝ በእስር የነበሩት ወዳጆቼ ጥርጣሬ አጅግ የተለየ ነው፡፡ ከአል-ሸባብ አስከ ኦብነግ እስከ ኦነግ እስከ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ሕዝቦች ነፃ እውጭ ግንባር እስከ አቂዳ(አዲስ የሽብር ቡድን)… ስቃይን መማር ጥሩ ነውና ሁለት ለሚሆኑ ቀናት ብቻዬን በመታሰሬም solitary confinement ን experience ለማድረግ ‹ታድያለሁ›፡፡ በርግጥ ብቻዬን ታስሬ ነበር ከምል ካንቺ ሀሳብ ጋር ታሰርኩ ብል ይቀለኛል፡፡

አምስቱን ሁነቶች ዘንግቼ ስለ ስቃዬ ተንዛዛሁብሽ ይሆን? ለዚህ ተግባሬ በእስረኛ ቋንቋ ‹ተፀፅቻለሁ›፡፡ በቃ ወደ ጉዳዮቹ፡፡ ከዚህ በታች የምገልፃቸው ሁነቶች የ84 ቀናቱ የእስር ወቅት (የምርመራ) ጊዜ ምን እንደሚመስል እንደነበር ያስረዱሻል ብዬ አስባለሁ፡፡ (ሁሉም በእውነት እኔ ላይ የደረሱ ጉዳዮች ናቸው)፡

1.    ተማሪዎቼን እንዳላበላሻቸው በማሰብ በቁጥጥር ስር ስላዋለኝ አመሰግናለሁ
ሚያዝያ 17/2006 ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ከምኖርበት አምቦ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከደህንነቶች ጋር በቤት አውቶሞቢል እየተጓዝኩ ነው፡፡ አንድ ልጅ እግር ደህንነት ጠየቀኝ
‹‹ዘላለም የህግ መምሕር ነህ አይደል..››
            እኔ፡ አዎ
            ደህንነቱ  "ስንት ጠበቆች ዳኞች ማፍራት ሲጠበቅብህ አንተ ‹ልማቱን ካላደናቀፍኩ› ማለትህ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ለማንኛውም እንኳን ተማሪዎቹን ሳታበላሻቸው በጊዜ በቁጥጥር ስር ዋልክ፡፡ ኧረ                  ለመሆኑ ከውጭ ስንት ሽህ ደላዮችን አግኝተሻል? Any way በልማታችን ቀልድ የለም" አለኝ፡፡ (እኔም ባስተማርኩባቸው 4 አመታት ስንት ተማሪዎችን ‹እንዳበላሸሁ › እያሰብኩና ልማታችን                  በወለደው የአስፋልት መንገድ ፏ ብዬ ከምሽቱ 3፡50 ላይ ማዕከላዊ ከቸች፡፡

2.   አላማችሁ ምንድን ነው?
እመቤቴ - መንግስት ሕዝባዊ አመፅ ለመቀስቀስ አሲራችኋል፤ ለዚህም በቂ ማስረጃ አለኝ በማለት ያሰረን ቢሆንም መንግስት ሀሳቡ እውነት ይሆንለት ዘንድ የእኛን ‹አዎ አሲረናል› የሚል መልስ በማባበልና በሀይል ለማግኘት ከመሞከር ውጭ ሌላ ያቀረበው አንዳችም ማስረጃም ሆነ መረጃ(በጠ/ሚንስትሮች ቋንቋ) አልነበረም/የለምም፡፡ ለዚህም ይመስላል በማእከላዊ የቆየሁባቸው ቀናት ምርመራው በሙሉ ‹አላማችሁ ምንድን ነው? በሚል ሕይወት አልባና አሰልቺ ጥያቄ የተሞላው፡፡ እኔም የዚህ ጥያቄ ሰለባ ሁኜ ከረምኩልሽ፡፡ እንዲህ ላጫውትሽ፣
           መርማሪ ፖሊስ (በተደጋጋሚ) - እንደ ዞን 9 አላማችሁ ምንድን ነው?
           እኔ፡ ዓላማችን ግልፅ ነው፡፡ ማንም ብሎጋችንን የተመለከተ ሰው በቀላሉ ሊረዳው ይችላል፡፡ባጭሩ የተለያዩ ተረኮችን የሚያስተናግድ እና ሕብረተሰባዊ ተዋጾን የሚያሳድግ ፕሮፋይል ነው፡፡
           መርማሪ ፖሊስ፡ እሱ ሽፋን ነው፤ እውነተኛ ዓላማችሁን ተናገር?
           እኔ፡ ከዚህ የተለየ አላማ የለንም!

መርማሪ ፖሊሱ እንድንመልስለት የሚፈልገው ‹ከበላይ አካል› ይዞ እንዲመጣ የታዘዘውን መልስ፤ “አላማችን እንደ ጭቃ ተረግጦ፤ እንደ ገል ተቀጥቅጦ የሚገኘውን ጭቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተጫነበት ቀንበር ነፃ ማውጣት ነው፡፡ ለዚህም መሳካት ሕዝባዊ አመፅ ማደራጀትን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርገን ነው የተቋቋምነው፡፡”
ሲሆን ይህ ደግሞ ከአላማችን ጋር የማይገናኝ መንግስታዊ ፍላጎት በመሆኑ እንዲህ አይነት መልስ ከእኔ ማግኘት እንደማይችል የተረዳው መርማሪ በተደጋጋሚ አስብበት በማለት ይሰናበተኝ ነበር፡

3.   ከመርማሪዎች ጋር የነበረኝ ቆይታ
የእኔ ፅጌሬዳ አላማችን እንደ ቡድን ባይጠይቁኝ ኑሮና የግል ዓላማዬን ቢጠይቁኝ አላማዬ ‹አንቺ› እንደሆንሽ ከመናገር ወደኋላ እንደማልል ታውቂያለሽ አይደል? የሆንሽ ‹አሸባሪ› ነገር፡፡ Any way ምርመራዬ ቀጥሎልኛል፡፡ ሁለት መርማሪዎች እየተፈራረቁ ገራሚ ገራሚ ጥያቄዎችን እየጠየቁኝ ነው፡፡ እነሆ ፡
         መርማሪ ፖሊስከአለም መሪዎች ማን ማንን አግኝተህ ታውቃለህ?
         እኔ፡ ማንንም
         መርማሪ ፖሊስእኛ እኮ ያለመረጃ አይደለም እየጠየቅን ያለነው፡፡ ጉድ ሳይመጣብህ ብትናገር ይሻላል፡፡
         እኔእስኪ አስታውሱኝና ምን እንደተነጋገርን ልናገር፡፡ በርግጥ ባለፈው የኔልሰን ማንዴላ ማስታወሻ ፕሮግራም በ አፍሪካ ህብረት በተከበረበት ወቅት ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ሌላ         የማስታውሰው የለም፡፡
        መርማሪ ፖሊስ፡ ህም! እሺ ዘንድሮ ኦባማ ፊት ንግግር ለማድረግ ከተመረጡ 3 ኢትዮጵያውያን አንዱ አንተ አይደለህም? አሜሪካ በ አፍሪካ ጉዳይ ምን አግብቷት ነው፡፡ ወጣት አመራሮች ምናምን             እያለች የምታሰለጥነው?
        እኔ፡ ‹‹እንዴ ኦባማ ፊት ንግግር ነው ያልከኝ? ድንገት ከታሰርኩ በኋላ ተመርጬ (በማሾፍ ድምፀት) ከሆነ አላውቅም፡፡ወይ በስም መመሳሰል ሊሆን ይችላል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ጉዳይ ምን አግብቷት           ነው? ላልከኝ ግን ወጣቶችን Empower ማድረግ ችግር ያለው አይመስለኝም ፤ ደግሞ በረሀቡም በድርቁም ጊዜ ርዳታ የምታደርገው እኮ አሜሪካ ነች፡፡ ምን አግብቷት ነው የምትረዳው አይባልም               መቼም?!››
        መርማሪ ፖሊስ፡ አሁን ዘመኑ የልማት ነው፤የምን ረሀብ ነው የምታወራው? በል ተወው፡፡

            (‹ፈሪ ውሃ ውስጥ ያልበዋል› ሰምተሻል ውቤ? መንግስቴ ብቻውን እየሮጠም ፍርሃቱና ስጋቱ ብዛቱ፡፡ የሚቆጨኝ ነገር ከዓለም መሪዎች ማን ማንን አግኝተሃል? ‹ስባል› ከሲሪላንካ ፕሬዜዳንት ጋር ተገናኝቼ ወደ ደቡብ አሜሪካ ፔሩ በመጓዝ ማቹፒቹን ጎብኝቻለሁ ብዬ ብናገር ኑሮ፤ ክሳችን ላይ ‹ከሲሪላንካ መንግስት ባገኘው የገንዘብና የመሳሪያ ድጋፍ ወደ ፔሩ በመጓዝ ሕገ-መንግስት እንዴት እንደሚናድ በማቹፒቹ ኮረብታ ስልጠና ወስዶ ተመልሷል፡፡ ለዚህ እንደ ማስረጃ ይሆን ዘንድ ላፕቶፔ ውስጥ የተገኙት ከ300 በላይ የቼጉቬራ ምስሎችና Machu Pichu: The Mecca of Hippies” የሚል ባለ 22 ገጽ ‹ሰነድ› አብሮ ይያዝልኝ ነበር፡፡ ሲያበሳጭ

4.   ‹አሸባሪው› ገብረሕይወት ባይከዳኝና ሀገሪቱን በሀራጅ የመሸጥ ጉዳይ
ፍቅር አደከምኩሽ አይደል?! ልጨርስ ስለሆነ ትንሽ ታገሺኝ፡ በዛውም ‹ፍቅር ታጋሽ ነው› የሚለውን Paulian ወንዴነት፤ ‹ፍቅር ታጋሽ ናት› በሚል ማስተካከያ እንድናርመው፡፡ የዚህ የምርመራ ነገር እኮ አላልቅልኝ አለ፡፡ በእስሬ ወቅት ሌላው በተደጋጋሚ እንዳስረዳ ስጨቀጨቅበት የነበረው ጉዳይ ‹ኒዮ-ሊብራልነቴና ልማትና ዲሞክራሲ ጎን ለጎን አብረው ይሄዳሉ ማለቴ ነበር፡፡
መርማሪ ፖሊሶቹ እየተቀያየሩ ስለኢህአዴግ የፖሊሲ ትክክለኛነት ‹ያስረዱኝ› ነበር፡፡ “አንተ ምን ጎደለብኝ ብለህ ነው ነጭ አምላኪ የሆንከው ? ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል ስናይ አንተና ጓደኞችህ አይናችሁ ለምን እንደሚቀላ እስኪ ንገረን ? ይህች አባቶቻችን ‹በደምና በጾም› ያቆዩልንን አገር አንተና ያንተ ትውልድ ግን ውበቷ እና ድንቅነቷ ላስጎመጃቸው ነጮች ለመሸጥ መደራደር ጀመራችሁ….” እያሉ ‹በባንዳነት› ሲከሱኝ ከረሙ፡፡ የሀገሪቱ ውበትና የነጮች በውበቷ መጎምጀት ነገር ሲነሳ ጊዜ ‹አንቺ› ትስቂ ዘንድ የሚከተለውን አንቀፅ አሻግሬ ታደሰ የተባሉ ፀሐፊ ከ 50 ዓመት በፊት ‹እኔና አንተ› ካሉት ጽሁፋቸው ላይ እጠቅስልሻለሁ

"ኢትዮጵያ እጅግ ያማረች፤ የተዋበች ፤የተደነቀች፤ላያት ሁሉ የምታማልል፤የምታዘናጋ…….ናት፡፡ ዓይኗ የብር አሎሎ መለሎ ከአጥቢያ ኮከብ የተፎካከረ….. ነው፤ አገራችን ኢትዮጵያ ፅጌረዳ መስላ የሰኔን ቡቃያ ትመስላለች፡፡ የመስከረም አበባ ሆና በሩቅ ትስባለች፤የመስህቧ ኃይል ማግኔት ምስጋን ይንሳው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ጥርሷ እንደ በረዶ ሆና ለፈገግታ ያህል ትንሽ ከንፈሯን ስትገልፀው እንኳንስ ለሰው ግብዙ መልዓክ ያብዳል፡፡ ኢትዮጵያ ፀጉሯ የሀር ነዶ ነው፤ኢትዮጵያ አጠረች ፤ረዘመች፤ወፈረች፤ብሎ ስለአካሏ መናገር አይቻልም፡፡ እንዲያው ዝም ይሻላል፡፡ በጠቅላላው ኢትዮጵያ ውበቷ ሰነፉን ይገድላል፡፡ ብርቱውን አነሁልሎ ያሳብዳል፡፡ እግዚአብሔር፤ኢትዮጵያን ሲፈጥር በብዙ ተራቋል፤ተጠቧል፤ ውበቷ በሩቅ ይስባል፤ አጥንትም ይሰብራል፤አዕምሮን ይሰውራል፡፡ ይገርማል!" ይላሉ፡፡

 ምንም እንኳን ውበት እንደተመልካቹ ነው ቢባልም፤ መርማሪዎቹ በዚህ ዓይነት Vulgar Natioanlism ሰክረው እኔና የእኔ ትውልድ ሀገሪቱን ‹በውበቷ ለሰከሩ› ነጮች ልንሸጣት እንደተዋዋልን እየነገሩኝ ነው፡፡ ይገርማል! ዲሞክራሲን ከልማት እኩል ማስኬድ ነውር የለበትም፤ ተገቢም ነው ማለት እንደ አገር ሽያጭ ውል የሚቆጠርበት ብሎም ‹ሩቅ አስባ ሩቅ ለማደር እየተጋች ያለችን አገር› መንገድ ላይ በጠረባ ለመጣል የተደረገ ሙከራ ተደርጎ የሚወለድባትና ‹አሸባሪ› የምንሰኝባት፣ ‹ለፈገግታ ያህል ትንሽ ከንፈሯን ስትገልጠው እንኳን ሰውን ግብዙን መልዓክ የምታሳብደው ኢትዮጵያ!

ሊቁ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ‹ልማትን ሲተች›  “እውቀት በሌለው ሕዝብ አገር መንገድና የምድር ባቡር ቢሰራ ሕዝቡ እንዲደኸይ ያፋጥናል እንጂ አይጠቅመውም፡፡ ጥቅሙ ከርሱ ጋር የሚገበያዩ አዋቂ ሕዝቦች ነው”  በማለት ‹ልማት ብቻውን ዋጋ የለውም› ሲል ይበይናል፡፡ ገብረሕይወት የእኛው ትውልድ አባል ቢሆን ኖሮ  “የኢኮኖሚ እድገቱን በመካድ፤ ሕዝቡ በአዕምሮ መናወጥ ምክንያት የዘረጋነውን የባቡር ሀዲድ ፈነቃቅሎ እንዲጥልና ሌሎች የሽብር ተግባራትን እንዲፈፀም በማነሳሳት ‹ወንጀል›” መመርመሩና መከሰሱ አይቀሬ ነበር፡፡
ውዴ! ያን ‹አሸባሪ› ሳቅሽን ሳስብ በፀረ-ሽብር ሕጉ መሠረት ጉዳይሽ ሊታይ ይችላል የሚል ስጋቴ የበዛ ነው፡

5.   ናፍቆቴ ሆይ!
እንዲያው ለዚህ 84 ቀናት ውስጥ የሆንኩትን ሁሉ እንዳልፅፍልሽ እንዳትሰለችብኝ ፈራሁ፡፡ እያንዳንዱን ሁነት በ Diary መልክ ከትቤ እንዳልክልሽ በነዛ ቀናት ውስጥ ብዕርም ሆነ ነጭ ወረቀት ይዞ መገኘት ‹ከፍ ብሎ አንገትን፣ ዝቅ ብሎ ባትን› ባያስቆርጥም ዛቻና ዱላን ማስከተሉ አይቀርም ነበርና ልከትብ አልቻልኩም፡፡ እንዲሁ በደፈናው ግን አንዳንድ ጉዳዮችን ብዘረዝርልሽ፡
  •  በነዛ ክፉ ቀናት ከምሽቱ 12 ሰዓት እንቅልፍ መተኛትን ለመድኩ፡፡ ይሔም ነገር መልካም እንደሆነ አየሁ፡፡ ምክንያቱም ሌሊት ከእንቅልፍ ተቀስቅሰው ራቁታቸውን ሲደበደቡ አድረው ከ 3 እና 4 ሰዓታት ቆይታ በኋላ በነፍስ ወደ መኝታ ክፍላችን የሚመጡ የእስር ጓደኞቼን  (Cellmates) ስቃይና ሰቆቃ ላለመስማት፡፡
  •  በ2004 ዓ.ም የፌዴራል ፖሊስ ‘Cyber crime Laboratory’ ተቋቁሟል መባሉን ሰምቼ ‹እንግዲህ cyber criminal ሁሉ የት ትገቢ? አለቀልሽ!› ብዬ ነበር፡፡ በጊዜ ቀጠሮ ጊዜ እንደተረዳሁት ደግሞ ‹ያለችን አንዲት ኮምፒውተር ናት የእነዚህ ልጆች ዳታ በአንድ ኮምፒውተር መርምረን መጨረስ ስላልቻልን የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠን› ሲባል ነው፡፡ አረ እንዲያውም ‹እስኪ Anti-virus ካለህ ኮምፒውተሬ ላይ ጫንልኝ› ተብዩ ሁሉ ነበር፡፡ ‹ለሽብር ተግባራት› መመርመሪያ ያልሆነ ‘Cyber crime laboratory’ ለመች ሊሆን ነው?
  • አንድ ቀኑንና ወሩን በማላስታውሰው ቀን አንድ ጎልማሳ የታሰርንበትን ክፍል አስከፍተው ገቡና እያንዳንዳችን መጠየቅ ጀመሩ፡
-   ‹አንተ ከየት ነው የመጣኸው?› (አንድ ተማሪ ወዳጄን)
-   ‹ከሀሮማያ ዩኒቨርስቲ›
-   ‹አሀ እናንተ ናችኋ…..›
****
-   ‹አንተኛውስ ከየት ነው የመጣኸው?!›
-   ‹ከወለጋ ዩኒቨርስቲ›
-   ‹አሁን ኦሮሚያ ብትለማ ምን የሚያስከፋ ነገር አለው?!....›
*****
-   ‹አንተስ ከየት ነው የመጣኸው› (እኔን ነው)
-   ‹ከአምቦ ዩኒቨርስቲ›
-   ‹ሕዝቡን እርስ በርስ አጋጭታችሁ ከተማዋን በደም ያጠባችኋት እናንተ….›
-   ‹አረ እኔ ከግጭቱ በፊት ነው የታሰርኩት›
-   ‹በእውነት ነው የምልክ እድለኛ ነህ፡፡ የኦሮሚያን ልማት ተቃወመ ተብለህ በታሪክ አለመስፈርህ በጣም እድለኛ አድርጎሀል፡፡›
(ለመሳቅ ሁላችንም የጎልማሳውን ከክፍል መውጣት እየተጠባበቅን እኮ ነው ውዴ) - ሁሉ ቧልት የሆነበት ሀገር!

በነዚህ ሁሉ የጉድ ቀናት ለምን እንደታሰርኩ ትክክለኛውን ምክንያት የሚነግረኝ አካል ፍለጋ ሁሌም አስብ ነበር፡፡ መታሰሬ ግን አያስገርመኝም፤ አያስከፋኝም! ደስታን በሔድኩበት ሁሉ እፈልጋለሁ፤ የእድል ነገር ሆኖ ደስታም ከእኔ አይርቅም፡፡ ፍቅሬ ለረጅም ዘመናት ‹የሰው የመኖር አላማ ማወቅ ነው› የሚለውን Aristotlian (አሪስቶትሊያን) አስተምህሮ በልቤ ይዤ እኖር ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ‹የመኖር ዓላማ መደሰት ነው› የሚለው አስተምህሮ በአርስቶትሉ ‹የማወቅ ዓላማ› ደባልቄ ይሔው እየተደሰትኩልሽና እያወቅሁልሽ እገኛለሁ፡፡ ‹አንች› የደስታዬ ምንጭ፡

‘‘Thanks to you….For you exist’
Clézio

ስለክሴና ስለተስፋዬ ሌላ ደብዳቤ እፅፍልሻለሁ፡፡
P.S አሳሪዬ ሆይ ልብ ይስጥህ!
                                                            ያንችው ዘላለም
                                                                        ከብዙ ፍቅር ጋር!

Wednesday, August 20, 2014

የዛሬው ችሎት የዞን9 ጦማርያኑን እና የጋዜጠኞቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አደረገ

#Ethiopia #FreeZone9bloggers #FreeEdom #FreeTesfalem #FreeAsemamaw 

የልደታ ፍርድ ቤት 19 ወንጀል ችሎት የዞን9 ጦማርያኑን እና የጋዜጠኞቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አደረገ 

ስድስቱን የዞን ዘጠኝ አባላት ማለትም በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ፣ ማኅሌት ታሁን፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ዘላለም ክብረት እና አጥናፍ ብርሃነ እንዲሁም በሌለችበት ክሷ እየታየ ያለው በሶልያና ሽመልስ እንዲሁም በጋዜጠኞቹ ኤዶም ካሳዬ፣ ተስፋለም ወልደየስ እና አስማማው /ጊዮርጊስ በልደታ 19ኛው የወንጀል ችሎት ዛሬ ጠዋት የተሰየመ ሲሆን ከሙስሊም ኮሚቴ አመራሮች ጋር በአንድ ችሎት እንዲታደሙ በመደረጉ የታሳሪዎችን ቤተሰቦችም ሆነ ወዳጆችን ለማስተናገድ ቦታ የለም በሚል ለጋዜጠኞች ብቻ የፍርድ ሂደቱ እንዲታይ በፖሊስ ተፈቅዶ ነበር፡፡

በሌለችበት የተከሰሰችው ሶልያና ሽመልስ መጥሪያ በጋዜጣ መውጣቱን ፍርድ ቤቱ ያረጋገጠ ሲሆን የዋስትና መብትን በተመለከተ በዛሬው ዕለት ተሰይሞ የነበረው ችሎት በጸረ ሽብር አዋጁ መሰረት በአንቀጽ 3 የሽብር ተግባራት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ አንድም ወይም ሁለትም ከዚያም በላይ ወንጀል የፈጸመ መሆኑ ወይም ለመፈጸም ያቀደ ለመሆኑ ተገልጾ ክስ ሲቀርብ ነው በተመሰረተባቸው ክስ ዋስትናን ሊያሳጣቸው የሚችለው ብለው ጠበቆቻቸው የተከራከሩ ሲሆን ደንበኞቻቸው በአዋጁ መሰረት የሰሩት የሽብር ተግባር ክስ አልቀረበባቸውም ስለዚህ በአዋጁ ተጠቀሰ ማለት በአዋጁ መሰረት ክስ ቀርቧል ማለት ስለማይቻል የዋስትናው ጥያቄ በመደበኛ ስርዓት እንጂ በጸረ-ሽብር ሕጉ መሰረት ሊታይ አይገባም፤ በተጨማሪም አዋጁ ዋስትና ይከለክላል ተብሎ ቢተረጎምም ከሕገ-መንግስቱ ጋር ስለሚጋጭ ዋስትና ሊፈቀድላቸው ይገባል ቢሉም፤ ፍርድ ቤቱ አንቀጽ ተጠቅሶ መከሰሳቸውን እንጂ በዚህ መከሰስ ነበረባቸው ወይም አልነበረባቸውም ብሎ ለማየት ፍርድ ቤቱ አይገደድም እንዲሁም የጸረ-ሽብር አዋጁ ከሕገ-መንግስቱ ጋር አይጋጭም ብለዋል በዚሁም መሰረት የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ ተደርጎ ለጥቅምት 5 ቀን 2007. ቀጠሮ በመስጠት የዛሬው ችሎት የተጠናቀቀ ሲሆን ጠበቆቻቸውም የዋስትና ጉዳይ በተመለከተ ለጠቅላይ ፍረድ ቤት ይግባኝ እንደሚያቀርቡም ታውቋል፡፡

ችሎት ውስጥ መግባት የቻሉት ጥቂት ጋዜጠኞች እና ጉዳዩን ለመታዘብ የተገኙ ዲፕሎማቶች ብቻ ናቸው፡፡

በቦታው በመገኘት አጋርነታችሁን ላሳያችሁ ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡