በበፍቃዱ
ኃይሉ
ከ18 ወራት እስር በኋላ ስንፈታ ዐ/ሕግ
ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ በሁለት “ምክንያቶች” በወንጀል ሕጉ (አንቀጽ 257/ሀ) ግዙፍ ያልሆነ “በጽሑፍ ለአመፅ የማነሳሳት” ጥፋት
ተከላክዬ ነጻ መሆኔን የማረጋገጥ ሸክሙን ወደ እኔ አዙሮታል፡፡ ምክንያቶቹ እነዚህ ናቸው፤
፩) “የግብጽ ዓይነት አብዮት ኢትዮጵያ
ውስጥ እንዲነሳ የሚቀሰቅስ ጽሑፍ መጻፉን ለፖሊስ በሰጠው ቃል …‹የእውነት ቃል መስጠቱን› አምኗል” የሚልና፣
፪) ዐ/ሕግ ባቀረባቸው ሰነዶች “በፌዴራሉ
ሕገ-መንግሥት የተቋቋመውን ስርዓት ለማፍረስ በጽሑፍ አማካኝነት የቀሰቀሰ ለመሆኑ የተጠቀሱት ማስረጃዎች የሚያስረዱ በመሆኑ” የሚል
ናቸው፡፡
የእምነት
ወይስ የእውነት ቃል?
ሳይቤሪያ (የማዕከላዊ ጨለማ እስር ቤት)
ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ለምርመራ ወጥቶ ሲመለስ ክፍሉ ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች በሙሉ የሚጠይቁት የመጀመሪያው ጥያቄ “አመንክ?” የሚል
ነው፡፡ ታሳሪዎቹ ስለምርመራው የሚያውቁት ነገር ስላለ አይደለም ይህንን ጥያቄ የሚጠይቁት፡፡ ነገር ግን የማዕከላዊ ምርመራ በተፈጥሮው፣
በተለይ በሽብር ለተጠረጠረ ሰው “አንዳች ወንጀል እመን” በሚል ስለሆነ ነው፡፡ ሒደቱም፣ በዱላ ነው፡፡ ማዕከላዊ ቆይተው ክስ የተመሰረተባቸው
ብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች ፍርድቤት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ “ተከላከሉ” የሚባሉት ለፖሊስ የሰጡት የእምነት ቃል ነው፡፡ ፖሊስ በሥነ
ስርዓት ሕጉ ቁጥር 27 መሠረት የተጠርጣሪ ቃል የሚቀበልበትን ሰነድ ሲያስፈርም
“… ይህንን በነጻ የሰጠሁትን የእምነት ቃሌን አንብቤ ወይም ተነቦልኝ ፈረምኩ” የሚል ዓ/ነገር ከግርጌው ይጨምርበታል፡፡
ማዕከላዊ ውስጥ የተከሳሽን ቃል በነጻ
አእምሮው በፈቃደኝነቱ እንዲሰጥ ማድረግ ነውር ነው፡፡ አንድ ሰው ማዕከላዊ ውስጥ ሲመረመር፣ ክብሩ በስድብ ተዋርዶ፣ እየተደበደበ
ነው፡፡ የሥነ ስርዓት ሕጉ አንቀጽ 27/2 ‹ማንኛውም ተጠርጣሪ ለፖሊስ ቃሉን ሲሰጥ በነጻ ፈቃዱ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት፤ ቃል
ያለመስጠት መብቱም የተጠበቀ እንደሆነ› ይደነግጋል፡፡ ይህን ግን የማዕከላዊ ፖሊሶች የሚያውቁት አይመስልም፡፡
እኔ ላይ የደረሰው ብቻ ሕግ ለይስሙላ
የሚወጣባት እንጂ በሕግ አስከባሪው አካል እንኳን የማይከበርባት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምንኖር ያሳያል፡፡ ማዕከላዊ ውስጥ ቃሌን ለፖሊስ
ስሰጥ እንኳን እንደዕቅድ ይዤ ልንቀሳቀስባቸው፣ በመርሕ ደረጃ እንኳን የምቃወማቸውን ነገሮች “አዎ፣ ላደርግ አስቤ ነበር (ማለትም ‹አመፅ ላነሳሳ ጽፌያለሁ›)” ብዬ መርማሪ ፖሊሶች ሲያሻቸው እኔ የተናገርኩትን
ወንጀል ሊሆን በሚችልበት መንገድ እየጠመዘዙ፣ ሲያሻቸው ደግሞ ጭራሹኑ እኔ ያላልኩትን ፈጥረው እየጻፉ ያመጡትን የእምነት ቃል አስፈረምውኛል፡፡
ሲደበድቡኝ የከረሙት ሕሊናቸውን በወር ደሞዝ የሸጡ መርማሪዎቼ ያለምንም የሕሊና ወቀሳ የእኔ ቃል ከተባለው ከራሳቸው ቃል ግርጌ
“የእውነት ቃሌ ነው” ብለው ጽፈውበታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምንም እንኳን በማዕከላዊ የተጠርጣሪ ቃል በነጻ እንደማይገኝ ከበቂ በላይ
በብዙ ተከሳሾችን ጉዳይ በመመልከቱ የሚረዳ ቢሆንም፣ መረዳት ስላልፈለገ “አምኗል” ብሎኛል፡፡ እርግጥ ነው አምኛለሁ፤ በኃይል ፊት
ጀግና መሆን ስላልቻልኩ ያላሰብኩ፣ ያላደረግኩትን አምኛለሁ፡፡ እምነቴ ግን እውነቴ አልነበረም፡፡ ወትሮም እኔ የኃይል ትግል ውስጥ
አይደለሁምና ኋላም ሆነ ወደፊት በኃይል ፊት የመጀገን ጀብደኛ ሕልም የለኝም፡፡ እስከአቅሜ ጠብታ ድረስ ለፍትሐዊነት የምታገለው
ስመታ እየወደቅኩ ነው፤ እረፍት ሳገኝ እየተነሳሁ!
ፍ/ቤቱም ይሁን ከሳሼ መንግሥት ግን መከላከል
ሳያስፈልገኝ ቃሉ የኔ አለመሆኑን ሊረዱ የሚችሉባቸው በርካታ ዕድሎች ነበሯቸው፡፡ ጥቂቶቹን ቀጥሎ እንመለከታለን፣