Wednesday, November 7, 2012

የትምህርት ጥራት ነገር (ክፍል አንድ)



በመልማት ላይ ያሉ ሀገራት ካላቸው የመዋለ-ነዋይ ውስንነት አንፃር መንግስቶቻቸው የትኛው መስክ እና የትኛው ስራ ቀድሞ መከናወን እንዳለበት ለመወሰን አስቸጋሪ የሆነ አጣብቂኝ ያጋጥማቸዋል፡፡ ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ እና ፈጣን ውጤት የሚያስመዘገቡት መስኮች እና ተግባራት ወይንም ደግሞ ከሌሎች መስኮችና ተግባራት ይልቅ አንገብጋቢ ለሆኑት ችግሮች መፍትሄ መስጠት  የሚችሉት የመዋለ-ነዋይ ፍሰት ከሚደረግባቸው ተግባራት የመጀመርያውን ረድፍ ያገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ ተግባራት ግን አይጠቅሙም ወይንም አያስፈልጉም ከሚል መነሻ ሳይሆን ድሀ ሀገራት በሚለዩባቸው የአቅም ውስንነት ብቻ ሳይተገበሩ ይቀራሉ፡፡


ሀገራችን ኢትዮጵያ ደሀ ናት፡፡ ከፍተኛ የሆነ የመዋለ-ነዋይ ውስንነት፣ ቢሰራ ህዝቡን ይጠቅማል ብሎ መንግስት የሚያስባቸውን ተግባራትን እውን እንዳያደርግ ማፈናፈኛ ያሳጡታል፡፡ (በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከዚህም በላይ በብልሹ አሰራር እና በሙስና ምክንያት ሀገሪቱ እጅግ አድርጋ የምትፈልገው ነዋይ ያለ አግባብ ይባክናል፡፡) የኢትዮጵያ መንግስትን የአቅም እጦት አጣብቂኝ ውስጥ ከሚከተው ተግባራት መካከል የትምህርት ጥራት ከተደራሽነት ጋር እኩል ማራመድ አለመቻሉ ይጠቀሳል፡፡ በርግጥ ለትምህርት ጥራት መጓደል ሌሎች አያሌ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል፡፡ ነገር ግን የአቅም ውስንነት ትልቅ ሚና እንዳለው የማይካድ ነው፡፡


ዜጎች ለሀገራቸው ዕድገት ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ዕውቀታቸውን በመጠቀም የየራሳቸውን አስተዋፅዎ ያደርጋሉ፡፡ የላቀ ዕውቀት ባለቤት የሆኑ ዜጎች የበዙባት ሀገር ከድህነት ለመላቀቅ መንገዱ እጅግ የቀለለ ይሆንላታል፡፡ ዜጎቿ ዕውቀታቸውን በመጠቀም ከድህነት የምትወጣበትን ውጤታማ መንገድ ይቀይሳሉ፣ ሀገር ተረካቢውን ትውልድ በሚገባ ይቀርፃሉ፡፡ የተማሩ ዜጎች የተመሰረተ ቤተሰብን መጥኖ መውለድ ስለሚሰጠው ጥቅም ለማገንዘብ ብዙ ወጪ አያስፈልገውም፡፡ በቤተሰቡ ውስጥ የሚወለዱ ህፃናትም እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ትምህርት ቤት የመግባታቸው እድል ያልተማሩ ዜጎች በመሰረቱት ቤተሰብ ውስጥ ከተወለዱት ህፃናት አንፃር ሲገመገም የጎላ ልዩነት አለው፡፡


በአሁኑ ወቅት እድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ ከሆኑት ኢትዮጵያዊያን መካከል 30 በመቶ የሆኑት መሰረታዊ የሆነውን ዕውቀት ማንበብና መፃፍ ይችላሉ፡፡ ቀሪዎቹ ግን ጣቶቻቸውን ፊደላትን ለመከተብ እና አይኖቻቸውን ከወረቀት ላይ ተክለው ፊደል ቆጥረው መረጃ ለማግኘት አይቻላቸውም፡፡ ላቅ ያለ ዕውቀት ኖሯቸው ሀገራችን ከድህነት አረንቋ ለመውጣት በምታደርገው ሩጫ ንቁ ተሳታፊ ሆነው የጎላ አስተዋፅዎ ማድረግ የሚችሉት ዜጎች ደግሞ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡


ኢሕአዴግ መራሹ መንግስት ፈፀምኩ ብሎ ከሚኩራራባቸው ተግባራት መካከል የትምህርት ተደራሽነት ከግንባር ቀደምቶቹ መካከል ይመደባል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የልማት መርሃ-ግብር (UNDP) እንዳወጣው ዘገባ እ.ኤ.አ በ2011 እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ኢትዮጵያውያን ህፃናት መካከል 82 በመቶ የሚሆኑት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ዕድል አግኝተዋል (እ.ኤ.አ በ1990 ይህ ሽፋን ከ30 በመቶ አይበልጥም ነበር)፡፡ ለዚህም የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ሽፋን እምርታ ትልቁን አስተዋዕፆ ያደረገው እ.ኤ.አ በ2011 በሀገሪቷ የሚገኙት አጠቃላይ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከአስር አመት በፊት ከነበሩበት ቁጥር ከእጥፍ በላይ በልጠው ማደጋቸው ነው፡፡

 
ምንም እንኳን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር እና ይህንንም ተከትሎ በየዓመቱ ወደ ትምህርት ቤት የሚገቡት ህፃናት ቁጥር በእጅጉ ቢጨምርም፤ ሁሉም ህፃናት የጀመሩትን ትምህርት አይጨርሱም፡፡ ደግነት እና አሰፋ የተባሉ የምጣኔ-ሃብት ባለሙያዎች በሀገር ውስጥ ፍልሰት እና የህፃናት ትምህርትን ግንኙነት ባጠኑበት ምርምራቸው፣ በገጠር የሀገሪቱ ክፍሎች ትምህርት ከጀመሩ አምስት ህፃናት መካከል አንዱ የትምህርት አመቱ ሳይጠናቀቅ ትምህርቱን እንደሚያቋርጥ ጠቁመዋል፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ሁለቱን ዑደት አጠናቀው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገቡት ተማሪዎች ቁጥርም ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ሲነፃፀር 34 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ይኸው ቁጥር ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገቡት ተማሪዎች ከተሰላ ወደ 4 በመቶ ብቻ ዝቅ ይላል፡፡

የኢትዮጵያ የትምህርት ችግር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሁለተኛ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡት ተማሪዎች ቁጥር አናሳ መሆን ብቻ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ የሚነሳው እና መንግስትም የሚያምንበት የጥራት ችግር ሌላኛው ዋነኛው ለዜጎች እውቀት ማግኘት እንቅፋት ነው፡፡

ሌጋተም የተሰኘ ተቋም የ110 ሀገራት አጠቃላይ ሀብት ገምግሞ ባወዳደረበት ዘገባው በትምህርት ጥራት እና ሽፋን ኢትዮጵያን ከ110ሩ ሀገራት 107ኛ አድርጓታል፡፡ እንደ ዋቢነትም፤ 48 በመቶ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ልጆቻቸው እያገኙ ባሉት ትምህርት እንደሚረኩ ጠቅሷል - ዘገባው፡፡ የአለም ባንክ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ዳይሪክተር ሆነው ለ4 ዓመታት ያገለገሉት ጃፓናዊው ኬን ኦሃሺ የአገልግሎት ዘመናቸው መጠናቀቅን ተከትሎ በእንግሊዘኛ ቋንቋ በሚታተመው ፎርቹን ጋዜጣ ላይ ካሳተሙዋቸው ተከታታይ ፅሑፎች በአንዱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጥራትን በሚመለከት አስደንጋጭ ሊባል የሚችል የጥናት ውጤት ጠቅሰው ነበር፡፡ የአለም ባንክ፣ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚንስቴር እና ሌሎች ትምህርት ላይ የሚሰሩ ተቋማት በ9 ክልሎች በሚገኙ 338 የህዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ 13ሺ ህፃናት ላይ ባካሄዱት ጥናት ከተካተቱት የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በአንድ ደቂቃ ውስጥ 60 ቃላት ያሉበት አረፍተ ነገር ማንበብ የቻሉት ተማሪዎች መጠን (አለም አቀፍ መለኪያ ነው) ከ10 በመቶ አይበልጥም (በ8ቱ ክልሎች ከአዲስ አበባ 14.5 በመቶ በስተቀር)፡፡ ይበልጥ የሚያሸማቅቀው የጥናቱ ውጤት ከ60 ቃላት ውስጥ አንዱንም በትክክል ማንበብ ያልቻሉት ህፃናት መጠን 34 በመቶ መሆኑን ይናገራል፡፡

የንባብ ክህሎት ለተማሪዎች ያለው ፋይዳ አሌ አይባልም፡፡ ተማሪዎች መምህር የሚሰጠውን ማስታወሻ እና የመማሪያ መፃህፍትን አንብበው መረዳት ካልቻሉ ማግኘት የሚገባቸውን ዕውቀት አግኝተዋል ማለት ያዳግታል፡፡ ትምህርት አሀዱ ባሉበት የመጀመርያ አመታት መደናበር የጀመሩት ተማሪዎች ከፍ ሲሉ የትምህርት ፍላጎት ኖሯቸው ንቁ እና ትምህርትን የሚወዱ ይሆናሉ ማለት ከመልካም ምኞት ማለፍ አይችልም፡፡

ኬን በፅሁፋቸው ከጠቀሷቸው ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች መካከል የተማሪዎች ‹‹አልገባኝም›› ብሎ ለመጠየቅ አለድፈርን ነው፡፡ አስቡት፤ ህፃናቱ በማንበብ ክህሎት ማጣት ምክንያት ግልፅ ያልሆነላቸውን ፍሬ ሃሳብ እንኳን ለመጠየቅ አይደፍሩም፣ አይበረታቱም፡፡ ይህ በርግጥ የህብረተሰቡ ልጆችን የሚያሳድግበት መንገድ ግልጽ ውጤት ነው፡፡ ይህም የትምህርት ሥርዓቱ ማነቆዎች በተወሰነ ደረጃ ከመንግስት ደጃፍ ውጭም እንዳሉ ይነግረናል፡፡

ዜጎች የተሻለ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ብዛት ያላቸው በመስኩ የተደረጉ የምርምር ውጤቶች እንደሚጠቁሙት ልጆች ትምህርት ቤት በሚቆዩበት ዓመታት እና በህይወት ዘመናቸው በሚያገኙት ገቢ ተያይዞም ለሀገራቸው ምጣኔ ሃብት በሚያደርጉት አስተዋፅዎ መካከል ቀጥተኛ ግኙነት አለ፡፡ ነገር ግን በዚያው ልክ ትምህርት ቤት የሚውሉት ህፃናት ዕውቀት እና ክህሎት እያዳበሩ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ያስፈልገዋል፡፡ ይህንን ለመፈተሽ እንደ ‹‹Program for International Students Achievement›› እና ‹‹Trends in International Mathematics and Science Study››ን የመሳሰሉ አለም-ዓቀፍ መለኪያዎች ቢኖሩም ለኢትዮጵያ ምዘና ማግኘት አይቻልም፡፡

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጥራት ላይ ላሉት ችግሮች፤ የተማሪ አስተማሪ እና የመማሪያ መጽሐፍ ጥምርታ እጥረት እና ኢትዮጵያዊ መምህራን በስራ ሁኔታ እና በሚከፈላቸው ደሞዝ ደስተኛ አለመሆን እና የብቃት ማነስ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የቀን ቀመር 2003 ዓ.ም የተማሪ አሰተማሪ ጥምርታ ለሃምሳ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች አንድ አስተማሪ ደርሷል፡፡ አንድ አስተማሪ ሃምሳ አንድ ተማሪዎች የሚሰጠውን ትምህርት እየተከታተሉት እንደሆነ ብሎም እንደገባቸው መከታተል ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ እንኳን ነብስ ያላወቁ ሃምሳ አንድ ልጆችን ይቅርና ነብስ ያወቁትን አዋቂዎች እንኳን በአግባቡ መከታተል ምን ያህል እንደሚከብድ ለማናችንም ግልፅ ነው፡፡ ክትትሉን የሚሰጡት አስተማሪዎች ደግሞ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ላይ እና ብሎም የሚሰጡት ትምህርት ይዘት ላይ የዕውቀት እጥረት ሲኖርባቸው ችግሩን ያባብሰዋል፡፡

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ለ2003 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ በመጀመሪያ ደረጃ የመጀመሪያ ዑደት ከሚያስተምሩት መምህራን መካከል የብቃት ማረጋገጫ ያገኙት 20.1 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ለሁለተኛው ዑደት ሲሰላ 83.33 በመቶ ይደርሳል፡፡

የመምራን በስራ ሁኔታ እና በሚከፈላቸው ደሞዝ ደስተኛ አለመሆን አኻዝ ተጠቅሶ ምስክር የሚቀርብለት ጉዳይ አይደለም፡፡ እነዚህን ህይወታቸውን ማሸነፍ የሚከብዳቸው መምህራን ማስተማርን ከዕለት ጉርሻቸው ማግኛ በላይ የትውልድ መቅረጭያ መሆኑን ተገንዝበው አስፈላጊውን መስዕዋትነት እንዲከፍሉ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡

የሁለተኛ ደረጃ እና የከፍተኛ ትምህት ችግሮችንና ላነሳኋቸው ችግሮች መፍትሄ የምላቸውን ጨምሬ በሌላ ጽሑፍ እመለሳለሁ፡፡ 

No comments:

Post a Comment