Thursday, November 1, 2012

የውሃ-ፖለቲካ እና የአባይ ጉዳዮች፡ ወፍ በረር ቅኝት



በዘሪሁን አበበ ይግዛው 
እንደ መነሻ
ባለቅኔ እና ጸሐፌ-ተውኔት ጸጋዮ ገብረመድህን ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ባሳተመው የግጥም ካሴት አዋሽ ለሚለው ግጥሙ መግቢያ ማብራሪያ ሲሰጥ… “በማናቸውም የዓለም ህዝብ ባህል ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የየአገሩ ወንዝ ጉዞ በተለይ የታላላቅ ወንዞች ጉዞ፤ የየአገሩ የሰፊው ህዝብ ጉዞ፤ የየትውልዱ ጉዞ ተምሳሌት ሆኖ ይቀረፃል፡፡” ይለናል፡፡ በርግጥ የእያንዳንዱ ሀገር ወንዝ የእያንዳንዱን ህዝብ ጉዞ ታሪክ ይናገራል፡፡ እውነት ነው ከዶን በራይን እና በቴምስ እስከ ዳኑብ በአውሮጳ፣ ከዮርዳስ እስከ ኤፍራጠስ እና ጢግሮስ በመካከለኛው ምስራቅ፣ ከኮሎራዶ እስከ ሚሲሲፒ በሰሜን አሜሪካ፣ አማዞን በደቡብ አሜሪካ፣ ኢንደስ-ጋንጅስ በህንድ፣ ፓኪስታንና ባንግላዴሽ፣ ያንገቲዝ በቻይና፣ እንዲሁም ጉዳያችን የሆነው አባይ በአፍሪካ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ ወንዞች የሚያልፉባቸውን የሚያገናኟቸውን ህዝቦች እና ሀገሮች ስናይ ከወንዙ ጋር የሚያቆራኛቸው እጅግ በጣም አያሌ ምክንያቶች አሉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ወንዞች ህይወትን፣ ስልጣኔን እና ማንነትን ገንብተዋልና፡፡ እርግጥ ነው ኤፍራጠስ የሚባል ከገነት የሚፈስ ወንዝ ባይኖር የአሲሪያም ሆነ ሞሶፖታሚያ ወይም የባቢሎን ስልጣኔ ባልኖረ፤ እርግጥ ነው አባይ የሚባል ህይውትን ያዘለ ከኤደን የሚመነጭ ወንዝ ባይኖር ግብጽ የሚባል ሀገርም ሆነ ህዝብ ባልኖረ፡፡ ወንዞች የሀገራት ስልጣኔ መሰረቶች እና ማማዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በአካባቢ ጥናት-ጅኦግራፊ እይታ ወንዞች አንድ ወጥ የሆኑ ስነ-ምድራዊ ክስተቶች ቢሆኑም በዘመናት በሰው ልጆች በተፈጠሩት ወሰኖች እና ድንበሮች መሰረት ወንዞች ከተፈጥሯቸው በተለየ ፖለቲካዊ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህንም ወንዞች ወሰን ተሸጋሪ ብለን እንጠራቸዋልን፡፡

ወሰን ተሸጋሪ ወንዞች ለግጭት ወይስ ለትብብር? 
ወሰን ተሸጋሪ ወንዞች በተፍጥሯቸው የሀገራትን ወሰን አያውቁም፡፡ ነገር ግን ባያውቁም ለአገራት እና ህዝቦች ካላቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊ እና ባህላዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጥቅም አኳያ በአገራት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ውጭ ጉዳይ ፖሊስ ዋና አካል ይሆናሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የአስኳላው ዓለም በእንደዚህ አይነት ወሰን ተሸጋሪ ወንዞች ባህሪ ላይ ጫፍ እና ጫፍ የቆመ አቋም አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ለግጭት እና ለጦርነት መሰረቶች፣ መሳሪያዎች እና ምክንያቶች ናቸው ሲሉ (ለምሳሌ ግሌክ፣ ክሌር) ሌሎቹ እንደ አሮን ወለፍ እና መሰሎቹ ደግሞ ወሰን ተሸጋሪ ወንዞች በአገራት መካከል ግጭት መቀነሻ እና የትብብር እና አንድነት ማቀጣጠያ መሰረቶች ናቸው ይላሉ፡፡ ዋናው ነገር ወሰን ተሸጋሪ ወንዞች የግጭት ምንጭ/ምክንያት እንዲሁም የትብብር መሰረት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዋናው እና ትልቁ ነገር በአገራት መካከል ያለ ታሪካዊ ግንኙነት፣ የአቅም ሚዛን፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ/ሃይማኖታዊ መስተጋብሮች  እንዲሁም የአገዛዝ ዓይነቶች እና የመንግስታት ባህሪ ዋና ዋና ጉዳዮች እና ተጽእኖ አሳዳሪ ነገሮች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ወሰን ተሸጋሪ ወንዞችን ስንመረምር ኤፍራጠስ-ጢግሮስ፣ ዮርዳኖስ እንዲሁም አባይ/ናይል ከትብብር ይልቅ ለግጭት ቅርቦች ናቸው፡፡ 
አባይ-ናይል
እንደ አባይ-ናይል ተፋሰስ እጅግ በጣም መራራ ጦርነቶችን ያስተናገደ አለ ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ጦርነቶች ይካሂያዳሉ፡፡ ባህርያቸውም አይቀየርም ምክንያታቸው እና አድራጊያቸው ይለያይ እንጅ፡፡ የአባይ ተፋሰስ የጦርነት ማስተናገድ ልዩ የሚሆነው ምክንያት ግን እራሱ አባይ የጦርነቱ ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ ከታሪክ ማህደር እንደምንረዳው ከ1832 እስከ 1876 ድረስ ብቻ እንኳን በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል 16 ታላላቅ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ በሁሉም ጦርነቶች አሸናፊዋ ግን ተወራሪዋ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ግብጽ ሱዳንንም ወርራ ነበር፡፡ በኬዲቭ እስማኤል ጊዜም የነጭ ናይል ተፋሰስ አገራትን ለመውረር እጅግ በጣም ጉገቱ ነበራት፡፡ አንድም በኢትዮጵያ መሸነፏ ሁለትም የቅኝ ግዛት በአፍሪካ መስፋፋት ይህ እንዳይሆን ምክንያት ሆነ፡፡
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ያለው የተፋሰሱ አገራት ግንኙነትም በውጥረት የተሞላ እና በግጭት የታጀበ ነበር፡፡ በግብጽ እና በሱዳን የተከወነው እና በኢትዮጵያና በሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገራት ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የ1959 ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ሁለቱ ተፈራራሚ የግርጌ አገራት ወደ ጦርነት ሊያመሩ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ለግብጽ ጓደኛ የሆነ መንግስት በመፈንቅለ መንግስት አማካኝነት ወደ ስልጣን በመምጣቱ ፊርማዉ ሊከናወን ችሏል፡፡ በግብጽና በሌሎቹ የላይኛው ተፋሰስ አገራትም ግንኙነቱ ሸካራ ነበር፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቱ ሙሉ በሙሉ የግጭት ነበር፡፡ የመልክዓ-ምድራዊ ርቀት ገድቦን ተነፈስን እንጂ ሁሉቱ አገራት ጎረቤቶች ቢሆኑ ኖሮ ማለቂያ የሌለው የቀጥታ ጦርነትን በተመለከትን ነበር፡፡ ምስጋና ለርቀት፡፡ ይህ ርቀት ግን ኢ-ቀጥተኛ ጦርነትን በተለይም የውክልና ጦርነትን ሊያስቀር አልቻለም (ይህን በሰፊው ከስር እናየዋለን)፡፡
ከነጭ አባይ አገራት ጋር በመጠኑ የትብብር ግንኙነት ለመጀመር የሞከረችው ግብጽ ሙከራዋ የራሷን ፍላጎት ለመጫን እንጅ ለተፋሰስ አቀፍ ልማት ባለመሆኑ ሙከራዎቹ በሙሉ ከሽፈዋል፡፡ ሀይድሮሜት፣ ኡንድጉ እና መሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን እኤአ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ኢትዮጵያ በውሃ መጋራት/ክፍፍል ዙሪያ ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም የትብብር መድረኮች አልሳተፍም በማለቷ እና ግብጽ በውሃ ለመደራዳር ፈቃደኝነት በማሳየቷ እንዲሁም በዓለምአቀፍ የለጋሽ አገራት ቡድን ግፊት አዲስ ምዕራፍ በናይል ተፋሰስ ተከፈተ፡፡ ይህም ሁሉን የተፋሰሱን አገራት ኤርትራን አይጨምርም የያዘ የውሃ መጋራት/ከፍፍል ድርድር እና የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ /Nile Basin Initiative/NBI በ1999 እኤአ ተቋቋመ፡፡ ኢኒሼቲቩ በዋናነት የቴክኒክ ስራዎችን እየሰራ እንዲሁም የየአገራቱ ተደራዳሪዎች ውሃ መጋራትን/ክፍፍልን እየተደራደሩ እስከ 2007 ቀጠሉ፡፡ በመሐል ግን የላይኛው እና የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ጫፍ ለጫፍ ያቆመ ክስትት ተፈጠረ፡፡
የናይል ወንዝ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ / Nile Basin Cooperative Framework Agreement/
የናይል ተፋሰስ አገራት በዚህ የስምምነት ማዕቀፍ ድርድር ወቅት በአንዱም በሌላውም ሲስማሙ ሲነታረኩም ለ10 ዓመታት ዘልቀዋል፡፡ በዋናነት የስምምነት ማዕቀፉ ይዘት የተፋሰሱ አገራት በናይል ወንዝ ላይ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የሁሉም አገራት የውሃ ዋስትና በእኩል እንዲጠበቅ ነው፡፡ ይህም ሲሆን በአንድ አገር ላይ የሚከናወን የውሃ ልማት ስራ የሌላውን አገር የውሃ ዋስትና በጣም የሚጎዳ  መሆን የለበትም ይላል የስምምነት ማዕቀፉ፡፡ በጥቅሉ ፍትሐዊ እና ምክኒያታዊ የውሃ መጋራት/ክፍፍል የዚህ ስምምነት አንኳር እና የማእዘን ድንጋይ ነው፡፡ ይህንም ለማሳካት የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽንን ማቋቋም የስምምነቱ ዋና ተግባር ነው፡፡  በርግጥ በሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ የተፋሰሱ አገራት ከተስማሙ በኃላ በመሐል አንቀጽ 14ን በተመለከተ ግን ስምምነት አልነበረም፡፡ በመጀመሪያ ይህ አንቀጽ ያወራ የነበረው ስለ “ቀደምት ስምምነቶች” (previous agreements) ጉዳይ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንል ይገባል፡፡ የናይል/አባይ ተፋሰስ በታሪኩ ሁሉንም የተፋሰሱን አገራት ያቀፍ ስምምነት አይቶ አያውቅም፡፡ አሉ ከተባሉ ያሉት በአንድ ወቅት አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ እንዳተትኩት የቅኝ ግዛት ውጤት የሆነው የ1929 ግብጽ-እንግሊዝ (እንግሊዝ ሱዳን በመወከል እንደ ቅኝ ገዥ) እና የ1959 ግብጽ-ሱዳን ስምምነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ አይደለም የወንዙ የራስጌ አገራት በተለይ ኢትዮጵያ እየተቃወሟቸው አይደለም ከዓለምአቀፍ ህግ አፈጣጠር እና አተገባበር አንጻር ስናያቸው ምንም አይነት የሞራልም ሆነ የህግ ገዥነት የላቸውም፡፡ ደግሞስ 86 በመቶ በላይ ውሃ የምታበረክተው አገር ያልተገኘችበት ስምምነት እንዴት በውሃ ተቀባይ አገራት ብቻ ተከውኖ ሁሉን ገዥ ስምምነት ይሆናል?
ወደ ጉዳያችን ስንመለስ አንቀጽ 14 ይህን ነባር ስምምነቶች የሚዳስስ የነበረ ቢሆንም በውል እንኳን በሳይንሱ ዓለም ያልዳበረ የውሃ ዋስትና(water security) በተሰኘ ጭንጋፍ ሃሳብ ተተካ፡፡ በመሆኑም የራስጌ እና የግርጌ አገራት በዚህ አንቀጽ 14 ንዑስ-አንቀጽ (ለ) መስማማት አቃታቸው፡፡ ኢትዮጵያ እና የነጭ አባይ አገራት(ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ኡጋንዳ) አንቀጽ 14 ንዑስ-አንቀጽ (ለ) እንደሚከተለው ይነበብ በማለት ተስማሙ፡፡
“የማንኛውንም የናይል ተፋሰስ አገር የውሃ ዋስትና በጎላ መልኩ እንዳይጎዳ” 
በተቃራኒው ግብጽ ደግሞ እንደሚከተለው ይሁንልኝ አለች
“የማንኛውንም የናይል ተፋሰስ አገር የውሃ ዋስትና እና የአሁን አጠቃቀም እና መብት በጎላ መልኩ እንዳይጎዳ”
ግብጽ አሁን አለኝ የምትለው ውሃ እና መብት ለአስርት ዓመታት አገራቱ እንዲቀየር ሲደራደሩበት የነበረውን ስርዓት ሌሎቹን የተፋሰሱን አገራት ያገለለ እና ፍለጎታቸውን እንዲሁም ጥቅማቸውን ያላገናዘበ የ1959 ስምምነት ነው፡፡ ይህን ሃሳብም የ1959 ስምምነት ባለ እዳ ናትና ባትፈልገውም ሱዳን እንደ በቀቀን አስተጋባችው፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው ግብጽ እና ሱዳን ይህን ጭንጋፍ ሃሳብ የውሃ ዋስትና ስምምነት ላይ በመሸንቆር የነበረው የዜሮ-ድምር ውጤት ባለመለዮ የናይል ተፋሰስን ስርዓት በጀርባ በር በኩል ለማስገባት ጣሩ፡፡ ስለዚህ ትግሉ እና ፍጭቱ ያለው አምባገነናዊ እና ኢፍትሐዊ የሆነ እንዲሁም ጥቂት አገራትን ብቻ በተለይም ግብጽን በሚጠቅም  ስርዓት እና ሁሉንም የተፋሰሱን አገራት እኩል የሚያከብር እንዲሁም እንደየድርሻቸው በእኩልነት ተጠቃሚ በሚያደርግ ስርዓት መካከል ነው፡፡ በዚህም ልዩነት ምክንያት ግብጽ እና ሱዳን በአንድ በኩል ኢትዮጵያ እና የነጭ አባይ አገራት ደግሞ በሌለ በኩል ተሰለፉ፡፡ ይህ የሆነው በ2007 ኡጋንዳ ላይ በተካሄደው የናይል ውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በተለያዩ የተፋሰሱ አገራት ከተሞች ስብሰባዎች ተካሄዱ፡፡ ግብጽ እና ሱዳን ግን የአባ ቢላዋ ልጅ ብለው ወይ ፍንክች አሉ፡፡ እንዲህ ከሆነማ ምን እንጠብቃለን በማለት የላይኛው ተፋሰስ አገራት (ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ታንዛኒያ) በግንቦት 4 ቀን 2010 እኤአ በኢንቴቤ ኡጋንዳ ተፈራረሙ፡፡ በኋላም በቀናት ልዩነት ኬንያ እንዲሁም ጥቂት ወራት በኋላ ቡሩንዲ ተቀላቀሉ፡፡ እንደ ስምምነት ማዕቀፉ ከሆነ 6 አገራት ስለፈረሙት ህግ ሊሆን የሚቀረው በየአገራቱ ህግ አውጭ አካላት/ፓርላማ ቀርቦ መጽደቅ ብቻ ነው፡፡ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክም ስምምነቱን እንደምትቀላቀል ይጠበቃል፡፡ 
ግብጽ-ጉራ እና ጉራ
ግብጽ ከመሀመድ አሊ ጀምሮ እስከ ኬዲቭ እስማኤል ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ ኢትዮጵያን ወርሮ በመያዝ ቅኟ ለማድረግ ብዙ ጥራለች፡፡ ቅጥረኛ ወታደሮችን ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ቀጥራ ተዋግታለች፡፡ በገዳሪፍም ገባች በአፋር፤ በጉንደትም መጣች በጉራ ግራ የሚያጋባ ሽንፈትን እየተጎነጩ ከመመለስ በቀር አማራጭ አልነበራትም፡፡ በ1875 እና 1876 የተደረገውን ዘመቻ ልዩ የሚያደርገው “ሁሉንም የአባይ ሸለቆ በአረንጓዴው የግብጽ ባንዴራ ስር ማዋል” በሚል መፈክር ታጅቦ በሙሉ አቅም የተደረገ መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ጉራ (ይህ ጉራ ይጥበቅ) ጉራ ላይ ጉራ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በአጼ ዮሐንስ መሪነት በራስ አሉላ አባ ነጋ  አዝማችነት ግብጽ የኢትዮጵውያን ሰይፍ የቀዳላትን ተጎንጭታ ተመልሳለች፡፡
አባይን በተመለከተ የግብጽ ኢትዮጵያ ፖሊስ የተቀረጸው በ1860ዎቹ መጨረሻ በ1870ዎቹ መጀመሪያ ነበር፡፡ ዋርነር ሙዚነገር በተሰኘ የስዊዝ ቅጥረኛ፡፡ ዋና የፖሊሲ ምክሩ ይህን ይመስላል፡፡ “ግብጽ የአባይ ውሃ ሳይጓደል እንዲደርሳት ከፈለገች አንድም ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ካልሆነም በሃይማኖትና በብሔር ክፍፍል የምትታመስ እንድትሆን ማድረግ አለባት፡፡” የዚህ ፖሊስ ቀራጺ ይሙት እንጅ ይህ ፖሊስ በጥሬ ነገሩ ሳይቀየር ስልቱን ብቻ እየቀያየረ አለ፡፡ ጉራ ላይ ያልተሳካላት ግብጽ ዛቻውን/ጉራውን እና የእጅ አዙር ውጊያውን/ የውክልና ጦርነትን ስራዬ ብላ ከያዘችው አምስት አስርት ዓመታ አለፉ፡፡  
የዊኪሊክሱ ጦማር ጉራ ወይስ . . .
ባፈው ሰሞን ወሬና “ሚስጢር” አሹላኪው ዊኪሊክስ ከአሜሪካው የደህንነት ድርጅት ስትራትፎር ሾልኮ እጄ የገባው የበየነ መረብ መልዕክት መሰረት ግብጽ በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች የምፈልገውን በእነ ኢትዮጵያ ላይ ካልጫንኩ በሚሳኤልም፣ በኮማንዶም፣ በጄትም በመጠቀም በሰዓታት ልታጠቃን አንዳሰበች በሊባኖስ የሚኖሩ ዲፕሎማቷን ጠቅሶ ገልጾልናል፡፡ የግብፃውያን ከአባይ ጋር በተያያዘ ዋናው ችግራቸው በማስፈራራት እና ኃይል በመጠቀም የራሳቸው የሚያደርጉት ይመስላቸዋል፡፡ ይህም የሆነው በዋናነት የአባይ ወንዝ መነሻና ብዙውን ውሃ አበርካች የሆነችው ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በጦርነት በመኖሯ እና አቅሟን የማጠናከር ጉዞዋ ያልተስተካከለ በመሆኑ ለውስጥ የደህንነት ጉዳዮች ትኩረት መስጠቷ ውሃውን እንዳትጠቀም እንቅፋት መሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግብጽ ሱዳንን በመዛት ማስበርገግ መቻሏ እና ከካምፕ ዴቪድ ስምምነት በኋላ ከአሜሪካ የሚጎርፍላት ረብጣ ዶላር እና ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ልቧ እንዲያብጥ ስላደረገው ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው የጦርነት ክዋኔ በዘመናት ይለያያል እንጅ ባህሪው ባለመለወጡ ምንም መሳሪያ ብታከማች ግብጽ በታሪኳ አትዮጵያን አንድም ጦርነት አሸነፍ አታውቅም፡፡  ከዚህ አንጻር ስንመለከተው በዊኪሊክስ በኩል የሾለከው ጦማር ተራ ወሬ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሆኖም ግን ስንገጣጥማቸው ሙሉ ትርጉም የሚሰጡን ክስተቶችን ስላየን ይህን ጦማር ማቅለል ዋጋ ሊያስከፍል ስለሚችል በአንክሮ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ምንአልባት ምንአልባት አንዳች ክፉ ነገር የህዳሴ ግድቡ ላይ ብታደርስ የማያቋርጥ የውሃ ጥማትን ለሚመጣው የግብጽ ትውልድ ትተዋለች፡፡ እጅግ በጣም ውስብስብ በሆነው መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ እየኖረች የእስራኤል እና የአረቦች ጉዳይ ባልለየለት ሁኔታ እንዲህ አይነት እስጣ ገባ ውስጥ መግባት የሚበላው ራሷን ግብጽን ነውና፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ግብጽ ኢትዮጵያን በሽርክ ለማጥቃት ኩርሲ በተባለች ዳርፉር ሱዳን ውስጥ በምትገኝ ቦታ የሚስጢራዊ ወታደራዊ ማዘዣ እያቋቋመች እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይህ ምን ያክል እውነት ነው? ወደፊት የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡ 
የዳርፉሯ ኩርሲ እና የእስራኤል ዱላ በያርሙክ-ሱዳን ለአባይ ምኑ ነው?
ባሳለፍነው ሳምንት ጆሯችንን ከነልቡ የሚይዙ ሁለት ዋናዋና ጉዳዮችን ሰምተናል፡፡ አንደኛው የእስራኤል በያርሙክ ካርቱም አቅራቢያ “የሱዳንን” የጦር መሳሪያ ፋብሪካ መምታቷ ነው፡፡ ይህ የጦር መሳሪያ ፋብሪካ በተገኘው መረጃ መሰረት ግብጽም ኢራንም በጋራ የሚሰሩበት ነው፡፡ የእስራኤል ይህን እርምጃ መውሰድ ወስዳ ከሆነ ሀማስ የሚያገኛቸውን የሮኬቶች ምንጭ ለማድረቅ ነው፡፡ በጎሪጥ የሚተያዩት ኢራን እና ግብጽን (በተለይ በአሁን ሰዓት)  አንድ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር ቢኖር  የፍልስጤም-እስራኤል ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሱዳን ጋር አብረው መስራታቸው አይደንቅም፡፡ ወደ ሐማስ የሚጎርፉ መሣሪያዎችን አመጣጥ ስንመለከት ኢራንን፤ ሱዳንን እና ግብጽን እናገኛለን፡፡ ከዚህ አንጻር የእስራኤል እርምጃ እንዲሁ አይደንቅም፡፡ የእኛ ጉዳይ የሚሆነው ግን ይህ የጦር መሣሪያ አብሮ ማምረት ነገን መሰረት ያደረገ ሊሆን ስለሚችል የማንቂያ ደወል ነው፡፡ እስራኤል ሆይ ስላነቃሽን እናመሰግናለን፡፡
ሁለተኛው ጄኔራል ኒኮላይ ማካሮቭ የተባሉ የሩሲያ ጦር ኃይሎች አዛዥ ለፕሬዝዳንታቸው ለቭላድሚር ፑቲን ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት የግብጽ አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶችን ኩርሲ ወደተሰኘችው ሚስጢራዊ ቦታ እያጓጓዘች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የአገራችን ሰው ሲተርት ያልተፈሳ አይሸትም ይላል፡፡ ከኩርሲ ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ አንጻር ግብጽ ይህን አላደረገችም ለማለት ይከብዳል፡፡ ሱዳንም ይህን ወታደራዊ አገልግሎት ሰጠች ለማለትም እንዲሁ፡፡ ምክንያቱም ለሱዳን እጅግ የሚበጃት ከግርጌ አገር ግብጽ ጋር ማበር ሳይሆን ከራስጌ አገር ኢትዮጵያ እና የነጭ አባይ ተፋሰስ አገራት ጋር መተባበር እና ለፍትሐዊ የውሃ መጋራት መስራት ነውና፡፡ ለግብጽም በእርግጥ የሚበጀው ይሄው ትብብር ነው፡፡ የሆነ ሆኖ አንዳንድ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ባገኝ ብዬ በመካነድር የታገዘ የሳተላይት ምስሎችን ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም፡፡ በዚህ አጋጣሚ  አጅግ ለረቀቀ ሳተላይት መሣሪያዎች ቅርበቱ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ይህንን ነገር ቢያካፍሉን አይከፋም፡፡ (የቦታ ስም ኩርሲ ዳርፉር) 
የውክልና ጦርነት
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በቀጥታ ውጊያ ላይ ሽንፈትን እንደጋቢ የተከናነበችው ግብጽ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የተከተለችው ሙዚንገር የነገራትን ስልት ነው፡፡ ኢትዮጵያን በእርስበርስ ውጊያ እና ፍጅት ደካማ ማድረግ፡፡ ሁሌም ኢትዮጵያን ለመውጋት ለተነሳ ቡድን ይሁን አገር የግብጽ ድጋፍ አለው፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባደረገቻቸው ውጊያዎች በሙሉ ጦርነቱ በእጅ አዙር ከግብጽ ጋር ነበር፡፡ ሻዕቢያ፣ ጀብሃ እና መሰሎቻቸው እርዳታ ይቸራቸው የነበረው ከካይሮ ነበር፡፡ በርግጥ ሻዕቢያ የአረብ አሽከርነቱን አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ጸጥታው ምክር ቤት በውሳኔ ቁጥር 1724/2006 እንዳሳሰበው የድሮው አል ኢትሀድ አል ኢስላሚያ የኋላው የኢስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት የአሁኑ አል ሸባብ በግብጽ ይረዱ እንደነበር ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የሚያሳየን ግብጽ ኢትዮጵያን ለሚያተራምስ ማንኛውም አካል ቀዳሽ እና አጉራሽ መሆኗን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ልማት ስራዎች ከመዞር ይልቅ እንዲህ አይነት ቁስሎችን ታሰታምማለች፤ አባይም ያለከልካይ ሲፈስ ይኖራል፡፡ የዚህ መንገድ አዋጭነት ያከተመ ይመስላል፡፡ የሆነ ሆኖ እንዲህ አይነት ከፍተቶችን ኢትዮጵያ የምትሞላው በመሳሪያ ሳይሆን የውስጥን ጉድፍ በማንሳት፣ የውስጥን ቀዳዳ በመሙላት ነው፡፡ በርግጥ በመሳሪያ መቀጣት ያለበት የውጭ ቅጥረኛ ካለ መቀጣት አለበት፡፡ ነገር ግን ዜጋ አኩርፎ የውጭ ቅጥረኛ ከመሆኑ በፊት የሚያሰኮርፉትን ነገሮች ለይቶ እንዳያኮርፍ ማድረግ ብልህነት ነው፡፡
ከዚሁ የውክልና ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በሶስት አቅጣጫዎች ፈተና ይበዛባታል፡፡ አንድም የግብጽ አሽከርነቱን ባስመሰከረው በኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት በኩል ሲሆን ይህም እጅግ በጣም አደገኛው ነው፡፡ ሁለተኛው ሶማሊያ ነው፡፡ ሶማሊያ ሰላም እንዳያገኝ ከሚሰሩት አገራት መካከል ግብጽ አንዷ ናት፡፡ በ1990ዎቹ አጋማሽ ኢትዮጵያ የሶማሊያ አንጃዎችን ሶደሬ ላይ በመሰብሰብ ተስማምተው የራሳቸው መንግስት ቢያቋቁሙም ካይሮ ላይ በተደረገ ሌላ ስምምነት አዲሱ መንግስት ሊፈርስ ችሏል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ከመጥፎ ይሻላል፤ ነቅቶ መጠበቅ ግን ሸጋ ነው፡፡ ሶስተኛው በደቡብ ሱዳን በኩል ሊመጣ የሚችል ነው፡፡ ይህ የሆነው በደቡብ ሱዳን ፍላጎት ሳይሆን ሀገሪቱ ካላት አቅም  ማነስ አንፃር ድንበሯን መቆጣጠር የማትችል ደካማ መንግስት በመሆኗ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ እነዚህን ሁነቶች መሰረት ያደረገ ፖሊሲ መቅረጽ ግድ ይላታል፡፡
ሱዳን በሁለት ቢላ መብላት . . .ግራ መጋባት 
ሱዳን እና ኢትዮጵያ ግንኙነታቸው በውጣ ውረድ የታጀበ ነው፡፡ አንዳንዴ ሰላም እና ፍቅር ሌላ ጊዜ ደግሞ በቁርሾ እና በግጭት የተሞላ ነው፡፡ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ሸካራ የሚባል ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ግን ሁለቱ አገራት በፍቅር ከንፈው አይተናል፡፡ ለዛ ይመስላል ኢትዮጵያ የሱዳኑ መሪ አል በሽር ላይ በዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የወጣባቸውን የእስር እዝ ያላከበረችው፡፡ ሱዳን በበኩሏ የህዳሴው ግድብ መጀመር ይፋ ከሆነበት ጊዜ እሰከ አሁን ድረስ ጊዜ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አላሰማችም፡፡ ከዚህ አልፎም ለግንባታ የሚውሉ የተለያዩ ማሽኖችን ለኢትዮጵያ አበርክታለች፡፡ ከዚሁ ባሻገር ደግሞ ግብጽና ሱዳን እጅግ በጣም በፍቅር የተሞላ ባይሆንም ወዳጅ የሚያስብል ግንኙነት አላቸው፡፡ በ1959 ስምምነትም ሱዳንን የግብጽ እስረኛ አድርጓታል፡፡ ከሙባረክ መንግስት ጋር የነበራቸው ግንኙነት ለዘብተኛ የሚባል ነበር፡፡ ሆኖም ግን አዲሱ የሞሐመድ ሙርሲ መንግስት ለሱዳን ያለውን ወገንተኝነት ለመግለጽ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ ዓመት በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት የግብጹ መሪ ሱዳን ብዙ መሰዋዕትነትን ከፍላ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ችላ ብሏታል በማለት አጋርነታቸውን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ልብ ልንለው የሚገባ ነገር ቢኖር የሱዳን እና አሁን ስልጣን ላይ ያለውን የግብጽ መንግስት አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ሁለቱም “አክራሪ” ኢስላማዊ መሆናቸው ነው፡፡ ሁሉም ሙስሊም ወንድማማቾች አሏቸው፡፡ ልዩነቱ የሱዳኑ በስውር መስራቱ ነው፡፡ የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሀሰን አል ቱራቢ ዋናው የሱዳን ሙስሊም ወንድማማቾች መሪ መሆናቸው እና የለየላቸው ጸረ-ኢትዮጵያ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ሌላው ጉዳይ የአል በሽር መንግስት ግብጽን ማንኛቸውንም ጥያቄ ተጠይቆ እምቢ ቢል የግብጽ መፈንቅለ መንግስት ሰለባ ሊሆን ስለሚችል መፍራቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚሁ ባሻገርም የአረብ ነን ባይነት ስሜት ልባቸውን ወደ ግብጽ ይወስዳቸዋል፡፡ ሱዳኖች ከአባይ ውሃ ተጠቃሚነት አንጻር ግን ከላይኛው ተፋሰስ አገራት ጋር መተባበርንም ይፈልጋሉ፡፡ ግን እስረኞች ናቸው፡፡ እናም ሱዳን በሁለት ቢላ እየበላች ግራ ተጋብታ ትታያለች፡፡ የትኛውን ትመርጥ ይሆን? ጊዜ ይፈታዋል፡፡
ደቡብ ሱዳን እንኳን ደህና መጣሽ!
በአጠቃለይ ለአምስት አስርት ዓመታት በሁለት ዙር በተካሄደ ጦርነት ደቡብ ሱዳን ራሷን ከካርቱም ካፋታች አንድ ዓመት ሆናት፡፡ የዚች ሀገር መፈጠር የአንዲት ሀገር መፈጠር ብቻ አይደለም ውጤቱ፡፡ እጅግ እየቆዩ የሚወጡ ብዙ ጉዳዮች አሉ አንድምታቸው ለምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ጎላ ብሎ የሚታይ፡፡ የእለሚ ትሪያንግልን ጨምሮ አንዳንድ የደንበር ጉዳዮች ከጎረቤት አገራት ጋር ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ትልቁ እና ከዚህ የበለጠው ጉዳይ ግን አባይ ላይ ሊመጣ የሚችለው አንደምታ ነው፡፡ የእስር ቤቱን ድባብ ያቅልልላቸውና የግብጽ የቀድሞ መሪ ሆስኒ ሙባረክ የራስጌ አገራት አዲሱን የአባይ ስምምነት ማዕቀፍ ሊፈራረሙት እንደሆነ ግልጽ ሲሆንላቸው ወደ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ‘የደቡብ ሱዳን የሪፈረንደም ሂደት ከተያዘለት ጊዜ ይዘገይ የሚል’ የድረሱልኝ ጥሪ አስተላለፈው ነበር; አሜሪካም እንደማይሆን አሳሰበች እንጂ፡፡ ግብጽ ይህን ያደረገችው ደቡብ ሱዳን የራስጌ አገራትን እንደምትቀላቀል እርግጠኛ በመሆኗ ነው፡፡ ለደቡብ ሱዳን መጨቆን እና ፍትህ ማጣት የግብጽ አጅ ከፍተኛ ነበርና ቢለምኑም እሺ እንደማይባሉ ያውቁታል፡፡ የመጀመሪየው ጉዳይ የ1959 ስምምነት ጉዳይ ሲሆን ደቡብ ሱዳን ይህን ስምምነት ከሱዳን ጋር የምትጋራበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ስምምነት በሚፈረምበት ጊዜ ‘አኛ አኛ ንቅናቄ’ ከካርቱም ጋር ለነፃነት እየተዋጋ ነበር፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ የስምምነቱ ወራሽ ሀገር ሱዳን እንጅ ደቡብ ሱዳን አለመሆኗ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ግብጾች ሁሌም እንደሚሉት የውሃ ስምምነቶች እንደ ድንበር ስምምነቶች ናቸው አዲስ አገራት የሚወርሷቸው ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ደቡብ ሱዳን ይህን ስምምነት ልትቀበል የምትችልበት ምንም ዓይነት አስገዳጅ ምክንያት የለም፡፡ ለዚህም ይመስላል ወደ ነፃነት የወሰዳቸው እና ለ6 ዓመታት ስልጣን እና ሐብት አጋርቷቸው የነበረው የሰላም ስምምነት የውሃን ጉዳይ ሳይነካ ያለፈው፡፡ ያም ሆነ ይህ ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል የመወሰን ስልጣኑ የራሱ የደቡብ ሱዳን ነው፡፡ ዋናው ነገር ከአባይ ድርሻ የሚጠይቅ አዲስ አገር ተፈጥሯል፡፡ ይህም በላይኛው ተፋሰስ አገራት ዘንድ ደቡብ ሱዳን መጣሽ… እንኳን ደህና መጣሽ አስብሏል፡፡ ለታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ግብጽ እና ሱዳን ግን ሌላ ፈተና እና መጥፎ ዜና ነው፡፡
 ኢትዮጵያ 
የገነት ማስረሻን “ጭስ አልባው ነዳጅ-አባይ” የሚል ሙዚቃ ልብ ብሎ ላደመጠ ሰው የሚገራርሙ መልዕክቶችን ይዟል፡፡ ቁጭት፣ እልህ፣ የሀገር ፍቅርን እንዲሁም በተፋሰሱ አገራት መካከል የሚኖርን ትብብር እና ግጭት ይተርካል፡፡ የውሃ ፖለቲካ ሀልዮትን በአጭሩ የሚተነትን ታላቅ ሙዚቃ ነው፡፡ (ይህን እና ሌሎች የአባይ ሙዚቃዎችን በተመለከተ አንድ ቀን እንመለስበት ይሆናል፡፡) ሆኖም ግን ይህን ሙዚቃ በመስማት አንድ ሰው የኢትዮጵያን አባይ ላይ ያላትን አቋም፤ ፖሊሲ እና ስልት/ስትራተጂ መገንዘብ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ አቋም ውሃውን በጋር በመጠበቅ በጋር እየተጠቀምን በጋራ እንበልጽግበት ነው፡፡ ለዚህም የትብብር ፖሊስ ስኬት መፍትሄ ስልቱ ራሱ ትብብር ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ትብብር አልቀበልም የሚል ካለ ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ በማልማት የህዝቧን ኑሮ የማሻሻል ሙሉ መብት እና ግዴታ ስላለባት ከመጠቀም ወደ ኋላ አትልም፡፡ ያንንም እያደረገች ነው፤ ከጣና-በለስ እስከ ተከዜ፣ ከዲዴሳ እስከ ፊንጫ፣ እንዲሁም ህዳሴ ግድብ በመቀጠልም ከካራ ዶቢ በመንዳያ ቤኮ-አቦ እያለማች ነው፤ ልታለማም ነው፡፡ ይህንም ስታደርግ አገሪቱ በዋናነት መከላከልን መሰረት አድርጋ ነው፡፡ ግብጽ በየለጋሽ አገራቱ ብድር እና እርዳታ ስታስከለክል በራስ ወጪን በመሸፈን (ጣና-በለስና ህዳሴን እንዲሁም ተከዜን ልብ ይሏል) ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እየሰራች ነው፡፡ ሌላው አገሪቱ ተጠንቅቃ ደጋግማ አስባ የገባችበት ነገር ቢኖር ግብጽ ደጋግማ እንደምትለው ጦርነት ካማራት ምን ያክል ተዘጋጅተናል የሚለው ነው፡፡ ዋናው ነገር አጥርን ሳያጠብቁ እንዲህ አይነት ፕሮጄክት አይጀመርምና ወደ ዝርዝሩ አልገባም፡፡ ሆኖም ግን ሁለት ነገሮችን ማለት ያሻል፡፡ አንድ የኢትዮጵያን መንግስት በመሳሪያ ለመጣል እየታገሉ ያሉ ታጣቂዎችን መፍትሔ መፈለግ ጥሩ ነው፡፡ ሳያውቁትም ይሁን አውቀው የጠላት አሽከር መሆናቸው አይቀርምና፡፡ ከዚህ አንፃር ሰሜን እና ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ የሀገሪቱ ኃይል በተጠንቀቅ ሊቆም ይገባዋል፡፡ ሁለተኛ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ነዳጅ የምታስገባው በዋናነት ከሱዳን ነው፡፡ ይህ ነገር ምንን ይነግረናል ብለን ስንጠይቅ አሁንም የማንቂያው ደወል እያቃጨለ ነው፡፡ የጦርነትን ከበሮ ወዲያ ይጣልልን እና አሁንም ጦርነት ውስጥ ብንገባ እንዴት ነው የኃይል ፍላጎትን የምንሸፍነው? መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ አሁንም ባህሩን ባህሩን እንድንል ያደርገናል፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት ከዚያ ባህር ላይ ውሃ እየጠጡ ያሉት ግመሎች ባለ አራት እግሮቹ ሳይሆኑ ባለ ሁለት እግሮቹ በዋናነት ግብጽ እና ኢራን ናቸውና፡፡ ፡፡

ማጠቃለያ
የአባይን ጉዳይ እንዲህ ጀምሮ እንዲህ ማጠቃለል መመኮሩ ራሱን አባይን በጭልፋ እንደማለት  ነው፡፡ ባይሆን ለዛሬው ወጋችን ገደብ እናበጅለት እንጂ፡፡ የአባይ ውሃ ለአገራቱ የትብብር መሰረት መሆን የሚችል ታላቅ የስልጣኔ መሰረት ነው፡፡ ሆኖም ግን በግርጌ አገራት ግትርነት  በተለይ በግብጽ ግትርነት ምክንያት የፍትሐዊ የውሃ ክፍፍልና ትብብር ስርዓት ለጊዜው ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ ይህም አንዳንድ ምስሎችን ስንገጣጥም ትርጉም በሚሰጥ መልኩ በተፋሰሱ አገራት መካከል ግጭት ሊኖር እንደሚችል ይነግረናል፡፡ ያ ግጭት ቀጥተኛ ባይሆንም የእጅ አዙር/የውክልና ጦርነት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በጊዜውም ሆነ ያለ ጊዜው የሚዘንበውን ዝናብ ለመከላከል ኢትዮጵያ ጠንካራ ዳስ መስራት አለባት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ጠንካራ ኢኮኖሚ እና ጦር ኃይል ሲኖር ጥቅሙ የትየለሌ ነው፡፡ እናም ዘገር ለሚነቀንቅ በሰዓቱ ዘገርን ማሳየት መብትም ግዴታም ነው፡፡ በተቻለ  መጠን ግጭትን ለማስወገድ መጣር ደግ  ነው፤ትብበርን ማስቀደም ለብዙሀኑ ጥቅም ነው፡፡ ትብብር አያሻንም የሚሉ ካሉ ግን ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርምና እኔም እንደ ገነት ማስረሻ እንዲህ አልኩ
ፍሰስበት እና በሀገርህ ሜዳ
የሚቆጣን ካለ ያበጠው ይፈንዳ!!

ዘሪሁን አበበ ይግዛው፤  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተርስ ድግሪ በዓለምአቀፍ ግንኙነት የተመረቁ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በጄኔቫ ዓለምአቀፍ ልማት ጥናት ተቋም ድህረ-ምረቃ ተማሪ ናቸው፡፡ ዋና ዋና የጥናት ጉዳዮቻቸውም በዋናነት የአባይ ውሃ ፖለቲካ፣ ግጭት፤ ጦርነት እና ሰላም ግንባታ፣ ሃይማኖቶች እና የሀገር ግንባታ ሲሆኑ “Hydropolitics of Eastern Nile Basin” የተሰኘ መጽሐፍም ለንባብ አብቅተዋል፡፡ይህን ጦማር በኢትዮጵያ እንዳይነበብ ለታገደው ዞን ዘጠኝ ጦማር አዘጋጅተውታል፡፡

ጸሐፊውን በዚህ አድራሻ  zerihun.yigzaw@graduateinstitute.ch ማግኘት ይቻላል፡፡

3 comments:

  1. Thank you Ato Zerihun! This article made a huge impact on my knowledge about Abaye!! Hopefully I will see more articles about it in the future.
    Zone9,,, where are u taking me?

    ReplyDelete
  2. በጣም በጣም ድንቅ የሆነ ትንታኔ ነው:እንደነዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ የዚህ አይነት ሰፊ ማብራሪያ ማግኘት በጣም አስፈላጊና ግድ ነው:በእውነት በጣም እናመሰግናለን: ለወደፊቱም እንደሚቀጥሉበት አልጠራጠርም: እግዚአብሄር ይስጥልን!!!!

    ReplyDelete
  3. ጽኃፊዉ ክልብ ላደንቅህ እወዳለሁ!!! የእርስ በእረስ ጥላቻና መቃቃር በማስወገድ ለጋራ ራዕያችን በጋራ ከሠራን ከቶ እኛን ሊደፍር የሚችል አንዳች ነገር ኖራልን? አሁን ዘመኑ በልዩ ሁኔታ በዘመነበት አስተሳሰቡ በኃይል ሳሆን ከዚህ በወጣ መልኩ በሆነበት ዓለም አይደለም ለግብጽ የሚያዋጣት እኮ አደደለም ሁሉም በደጄ ኢትዮጵያ --------!!ቀድሞም ያዉቁናል፡፡ ይልቁንስ የዛፉ አይነት------የእኛዉ ጠማማ ነዉ፡፡ድሮም ባንዳ አልጠፋምና በታሪክ ይህንን ካስወገድን በእጃችን በቀያችን የሚፈስ ዉኃን ከመጠቀም የሚከለክልን ከቶም አይኖርም ዛሬም ሆነ ነገ ገና እንጠቀማለን!!

    ReplyDelete