Wednesday, February 18, 2015

20ኛው የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የ"ፍርድ ቤት" ውሎ

ፍቃዴ ለቅቄያለሁ ያሉት ዳኛ ደግመው ተሰይመዋል! 

ለሶስት መቶ ቀናት በእስር ላይ የቆዬት ጦማርያን ለ20ኛ ጊዜ "ፍርድ ቤት" ቀርበዋል፡፡ 

ትላንትና የካቲት 11 ቀን ገዥው ህወሃት 40ኛ ልደቱን ባከበረበት በተመሳሳይ ቀን በነሶልያን ሽመልስ የክስ መዝግብ "ፍርድ ቤት" የቀረቡት ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

"የፍርድ ሂደቱ" ጠዋት ሊጀመር ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ያለቅጥ ዘግይተው የተሰየሙት ዳኞች ተከሳሾቹ ለከሰአት ስምንት ሰአት ለሚጀምረው ችሎት አንዲገኙ ለከሰአት ተቀጥረው ነበር፡፡ ከሰአት ስምንት ሰአት ላይ ችሎቱ ከመጀመሩ በፊት ባሉት ሰአታት ልደታ ፍርድ ቤት ጊዜያቸውን ያሳለፉት ጦማርያን ከሰአት በኋላ "ፍርድ ቤት" ቀርበዋል፡፡ ችሎቱ ላይ ባለፈው ቀጠሮ አቤቱታ ቀርቦባቸው አቤቱታውን "ፍርድ ቤቱ" ባይቀበለውም በገዛ ፍቃዴ ከችሎቱ ለቅቄያለሁ ያሉት ዳኛ ሸለመ በቀለ መልሰው ችሎቱን ሰብስበዋል ፡፡ ከችሎቱ ለመነሳታቸውም ሆነ ላለመነሳታቸው የተሰጠ ማብራሪያ ሳይኖር ከሁለተኛ ተከሳሽ ከጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ጀምሮ እያንዳንዳቸው ተከሳሾች በስም እየተጠሩ የተጠረጠሩበትን ወንጀልመፈጸም እና አለመፈጸማቸውን ቃል አንዲሰጡ የተጠየቁት ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ሲመልሱ

በፍቃዱ ሃይሉ - እኔ ክሱን ከአምስት ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ አንብቤዋለሁ ምንም የሚገባ ነገር አላገኘሁበትም ሲል ዳኛው አቋርጠውት አሁን ምንም አይነት ዝርዝር ውስጥ አልገባም በማለታቸው "የሽብር ወንጀል ለመፈጸም አላሰብኩም አልፈጸምኩት አልፈጽምም ሽብር ተፈጽሞብኛል" ሲል መልሷል፡፡ ከበፍቃዱ በማስከተል ቃሉን የሰጠው ጦማሪ ናትናኤል "ህግ የሚከበርበት አገር ቢሆን ኖሮ ዛሬ እዚህ ቦታ መቆም የነበረባቸው አሳሪዎቼ ናቸው ፣ ምንም ወንጀል አልፈጸምኩም "ያለ ሲሆን ጦማሪ አጥናፍ "ወንጀል አልፈጸምኩም" ፣ ጦማሪት ማህሌት "ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸምኩም" ብላ ቃሏን ስትሰጥ ጦማሪ አቤል በበኩሉ "ክሱ ግልጽ አይደለም" ሲል ዳኛው ምንም አይነት ተጨማሪ ነገር ሳያስፈልግ ቀጥታ ቃል እንዲሰጥ ማሰጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም አቤል "የህብረተሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ምንም አይነት የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም አላሴርኩም" ሲል በቀጥታ ክሱ ላይ የተጠቀሰውን አንቀጽ ጠቅሶ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ጦማሪ ዘላለም በበኩሉ የተከሰሰበት ወንጀል አንዲብራራለት የጠየቀ ሲሆነ "ፍርድ ቤቱ" ወደኋላ አንመለስም የሚል ማስፈራሩያ በማሰማት በቀጥታ ቃሉን እንዲሰጥ ሲነገረው "የተከሰስኩበት ክስ ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ የእምነት ክህደት ቃሌን መስጠት አልችልም" በማለት በመናገሩ ቃሉን ሳይሰጥ ቀርቷል ፡፡ በህጉ መሰረትም ጥፋተኛ አይደለሁም አንዳለ ተቆጥሮ ተመዝግቧል፡፡
ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ -" ምንም ወንጀል አልፈጸምኩም እኔ ነጻ ሰው ነኝ " ስትል ጋዜጠኛ አስማመው "ወንጀል አልፈጸምኩም" ጋዜጠኛ ተስፋለም ደግሞ "እኔ ጋዜጠኛ ነኝ ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም እኔ ምንም ወንጀል አልፈጸምኩም" ብሏል፡።

የእምነት ክህደት ቃል መስጠቱነ ተከትሎ አቃቤ ህግ ምስክሮቸን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሎ በጠየቀው መሰረት ከአርባ ቀን በኋላ ለመጋቢት 21-23 ለሶስት ቀናት የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማቅረብ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ የተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው አለ የተባለው የሲዲ ማስረጃ ግልባጭ ስላልተሰጠን አንዲሰጠን ብለው የጠየቁ ሲሆን "ፍርድ ቤቱ" እንዲሰጣቸው ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

የተከሳሾች አያያዝ 

ባለፈው ችሎት ወቅት ጦማሪ አቤል ዋበላ ያቀረበውን አቤቱታ ተከትሎ ማረሚያ ቤቱ መልስ አንዲሰጥ መጠየቁ የሚታወስ ሲሆን የጦማሪው ጠበቃ ተከሳሹ ከማረሚያ ቤት አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ችግሩን ስለፈቱት አቤቱታውን መቅረቱን ለ"ፍርድ ቤቱ" ተናግረዋል፡፡ ጦማሪ አቤልም በበኩሉ ተጨማሪ የመብት ጥሰት አስካልደረሰብኝ ድረስ ባለፈውን አቤቱታዬን ትቼዋለሁ ያለ ሲሆን ባለፈው ተቀምቶ የነበረው የጆሮ ማዳመጫ መሳሪያም ተመልሶለታል ፡፡ ነገር ግን የሴት ተከሳሾች አያያዝ አንደአዲስ አስቸጋሪ እንደሆነ የሚያያቸው ሰው ገደብ እንዳልተነሳ እና አሁንም በጥቂት ሰዎች ብቻ አንደሚጠየቁ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ በማቅረባቸው የእነሱን አያያዝ አስመልክቶ ማረሚያ ቤቱ መልስ አንዲሰጥ ለመጋቢት 18 ጠዋት ቀጠሮ ተሰጥቶ ችሎቱ ተጠናቋል ፡፡

የዞን9 ማስታወሻ 

ሶስት መቶ ቀን እስር እና ከሃያ ቀጠሮ በኋላ የተጀመረው ይህ መደበኛ "የፍርድ ሂደት" እንደተለመደው መጓተቱ ሳያንስ በአንድ ወር በላይ የሚፈጅ ቀጠሮ መሰጠቱ ለክሱ ፓለቲካዊነት አንዱ መገለጫ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሶስት ወር በፈጀ ምርመራ ሂደት ውስጥ ተገኙ የተባሉትን ማስረጃዎች ለማቅረብ የ40 ቀን መዘጋጃ ጊዜ አንደማያስፈልግ ለማንም ሰው በግልጽ የሚታይ ሃቅ ነው ፡፡ በመሆኑም ባለፈው የቀረበው አቤቱታ ላይ አንደተገለጸው ዳኛውም ሆነ የፍትህ ስርአቱ አላግባብ መታሰራችን እና መከሰሳችን ሳያንስ አንድን "የፍርድ ሂደት" በማራዘም አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት መቀለጃ እየሆነ አንደሆነ እያሳዬን ነው፡፡ የዞን9 ነዋሪያንና አንባቢዎችም ይህ ፍትህ ስርአቱ ስም የሚደረግ ቀልድ አንደማይጠፋቸው አናምናለን ፡፡

የዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች በመልካም ጤንነት በጠንካራ ስነልቦና እና በራስ መተማመን ስርአቱን ፊትለፊት እየተገዳደሩ ያሉ ኩሩ ልበ ሙሉ ወጣት ዜጎች ናቸው ፡፡ የተለየ ሃሳብን በሚያራምዱ ጥቂት ወጣቶች የተሸበረውን መንግሰት የምናፍርበት ያህል በጓደኞቻችን አንኮራለን ፡፡

የዞን9 ኩራት ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ በድጋሚ መልካም ልደት
ስለሚያገባን እንጦምራለን ፡፡ 
Blogger Befeqadu Hailu drawing by Melody Sundberg


ዞን9
#Ethiopia #FreeZone9Bloggers @FreeEdom #FreeTesfalem #FreeAsmamaw 

Tuesday, February 3, 2015

የዞን 9 ጦማርያን አና ጋዜጠኞች ለ17ተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ለ16 ጊዜ ያህል ለስድስት ወራት ፍርድ ቤት የተመላለሱት እና ለ9 ወራት በእስር የሚገኙት የዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች ዛሬ ለ17ተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ፡፡
በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን አንዲሰጡ የተጠበቀ ቢሆንም በተቃራኒው ተከሳሾች አቤቱታ አለን አቤቱታችን የእምነት ክህደት ቃል ከመስጠታችን በፌት መቅደም አለበት ብለው ተከራክረዋል፡፡ ዳኛው ዛሬ የእምነት ክህደት ቀጠሮ ነው ሌላ አቤቴታ አንቀበልም ቢሉም ፍርድ ቤቱ የራሱን ቃል አጥፏል ስለዚህም የመሃል ዳኛው አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብታችንን ስለነፈጉን እንዲሁም ራሱ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትእዛዝ ሽሮ ያልተሻሻሉ ክሶችን በማካተት መከላከል የማንችልበት ሁኔታ ላይ ስላስቀመጡን መሃል ዳኛው የፍትህ ሂደቱን ዳኛ ሸለመ በቀለ ከቦታቸው ካልተነሱልን የእምነት ክህደት ቃላችንን ለመስጠት አንቸገራለን የሚል አቤቱታቸውን አቅርበዋል ፡፡
በዚህም መሰረት አቤቱታው ያልተጠበቀ የሆነባቸው ዳኛ የመገረም ፌት ያሳዬ ሲሆን አቤቱታው ላይ ለመወሰን ለነገ ጠዋት በ3 ሰአት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ችሎቱ ነገ ጠዋት ለ18ተኛ ጊዜ ደግሞ ይሰየማል፡፡


Thursday, January 29, 2015

አዲስ ዜና

አዲስ ዜና 
ሶስት ዞኖች እነዳሉት የሚታወቀው የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በአስቸኳይ አራተኛ ዞን እየተገነባ እንደሆነ ታወቀ፡፡ በሶስቱ ዞኖች ውስጥ በአማካይ ከ100 በላይ ያልተፈረደባቸው የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን የሚከታተሉ እስረኞች ሚገኙበት ሲሆን አሁን አራተኛው ዞን ግንባታ በፍጥነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ 

News update - Ethiopian government prison administration is expanding kilinto prison. according to the sources the prison is establishing new 4th Zone in addition to those three zones existing now. Currently, more than 100 male cell mates are under custody in each existing Zone.