Tuesday, November 13, 2012

የመለስ ውርስ እና ራዕይ


ሰሞኑን በመስቀል አደባባይ ሳልፍ የአዲስ አበባን 125ተኛ አመት አከባበር አስመልክቶ (የበአሉ አከባበር ራሱ ሌላ ጽሁፍ ይወጣዋል) አዲስ ቅርጻ ቅርጾች ተቀምጠው ተመልክቼ ነበር፡፡ እነዚህ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾች (125 የሚል ጽሁፍ ሌላ 31 የሚል ምን ለማለት እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ የፈጀብኝ ሌላ ጽሁፍ የቀድሞው መሪ አቶ መለስ ፎቶ በእያንዳንዳቸው ላይ የተቀመጠባቸው ሌሎች ቅርጾች) ከሌላ ጊዜው በተጨማሪ የመለስን መንፈስ በአደባባዩ ሞልተውታል፡፡ በትልልቅ ባነሮች ብቻ ይታይ የነበረው የሟች ጠ/ሚኒስትሩ መስቀል አደባባይ ላይ መገኘት አሁን አደባባዩን መሬት ሞልቶታል፡፡ይህ በመስቀል አደባባይ እና በመላው አዲስ አበባ የሚታዩት የመለስ ምስሎችሁሉም ማለት ይቻላል ውርሳቸውን ለማስቀጠል እና ራእያቸው ስለማሳካት የሚያወሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ጥቂት መንፈሳዊ መልእክት መሰል መልእክት የያዙ ጽሁፎችም አልጠፉም( “ለህዝብ የተፈጠረ ለህዝብ የኖረ እና ለህዝብ የሞተ…”ከነዚህ ውስጥ ይጠቀሳል)

የአቶ መለስ ሞት በይፋ ከታመነበት ጊዜ አንስቶም ከፓስተሮች ጀምሮ እስከ ፓርላማው ውይይት ድረስ የሚነሳው ቃል ራእይ እና ውርስ(ሌጋሲ) ሆኗል፡፡ አገሪቷም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራእይን የማሳካት ታላቅ የማሃላ ስነ ስርአት ላይ ያለች ይመስል ከሩጫ እስከ ቢሮ ስራ ከእንጀራ መጋገር እና ዝቅተኛ የስራ መስኮች ጀምሮ እስከ ታላላቅ ቦታዎች ተተኪ አመራሮች ድረስ  “የእናሳካለን መሃላ”ን ስራችን አድርገን ይዘነዋል፡፡ የማይተማመን ባልጀራ ………ነገር ነው ብለን መደምደማችንን ብንተወው እንኳን ሁላችንም የምንግባባበት የአቶ መለስ ውርስ እና ራእይ አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡

የውርስ እና ራዕይ ስብከት

አቶ መለስ ሞት በፊት ሲያቆጠቁጥ የነበረው ግለሰባዊ ገጽታ ግንባታቸው ተጠናክሮ ከሞታቸው በኋላ በሁሉም የመንግስት ሚዲያዎች አልፋና ኦሜጋ ሁሉን ቻይ ሆነው ቀርበዋል፡፡ በከፍተኛ የመንግስት አመራር ደረጃ ሳይቀር ከእርሳቸው ውጪ የሚሰራ ምንም ነገር እንዳልነበር ሲነገረን ከርሞአል፡፡ይህ የሃዘን ማግስት የሟች ገጽታ ግንባታ ደረጃውን በፍጥነት በማሳደግ ራእይህን እናሳካለን ውርስህን እናስቀጥላለን ወደሚል አገራዊ መሃላም ተቀይሯል፡፡ ይህ የራእይ እና የውርስ ማስቀጠል ማሃላ እና ስብከት ከተባበሩት መንግስታት ስብሰባ እስከ ፓርላማ፣ ከዜና እስከ ወረዳዎች አመራር ንግግር ሳይቀር ሲነገር እና ሲወራ ነበር፡፡ ሚዲያውም የካድሬዎችን ንግግር ቅርጽ በማስያዝ የራሱን ሚና ሲወጣ ነበር፡፡ ኢቲቪ እንኳን ከዜናው ጀርባ ታላቁን መሪ ካስቀመጠ ስንት ጊዜው?ለዛውም “ታላቁ አባታችን መከረን ……”ከሚል ጽሁፍ ጋር!!

“የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጠ/ሚኒስትር”

በሚዲያው መሪነት በታላላቅ ባለስልጣናት ፊትአውራሪነት ሲመራ የነበረው የውርስ እና ራእይ ስብከት ሌላ ጠ/ሚኒስትር መተካታችንን ማስታወስን ራሱ ነውር ሲያደርገው ተመልክተናል፡፡ በስህተት የቀድሞው ጠ/ሚኒስተር የሚሉ የነበሩ የከተማው ፓስተሮች እንኳን በፍጥነት ጠ/ሚኒስተር በሚለው የአቶ መለስ “ዘላለማዊ ማእረግ” ተተክተዋል፡፡ ዘንድሮም ሞታቸው ከስልጣናቸው እንዳስወገዳቸው ማመን ያቃታቸው ሚዲያዎች የቀድሞን የሚል ቃል ለመጠቀም አልደፈሩም፡፡ አንደውም አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በፓርላማ ንግግራቸው አቶ መለስን “ክቡር ጠ/ሚኒስትራችን” በማለት ደጋግመው በመጥራት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሌላ ጠ/ሚኒስትር እንዳላቸው በይፋ አጠናክረው ነግረውናል፡፡ ይህ መለስን ከመሪነት ቦታ ለማንሳት ያለመፈለግ አባዜ በዚህ አያያዙ ከቀጠለ ከቀናት እና በአላት ስያሜነት ባለፈ የአቶ ለመስን ውርስና ራእይ ምንነት ሳንጠይቅ እንድንቀር እንዳያደርገን ያሰጋል፡፡

የአቶ መለስ ራዕይ 

ለመሆኑ ባለራእዩ መሪ” ራእያቸው ምን ነበር የሚለወን ጥያቄ ለራሴ ሳነሳ የሚታወሰኝ ትልቅ እቅድ እና ራእይ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ እንዲሁ ስጠረጥር ግን የእርሳቸው ራእይ አሳኪዎች ሊያነሱዋቸው የሚችሉዋቸው ነገሮች ከምስላቸው ጀርባ ያለው የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት እና  የባቡር መስመር ዝርጋታው እንዲሁም የመንግስት እቅድ ሆኖ የምናውቀው(ከህልፈታቸው በኋላ ሙሉ ለሙሉ የእርሳቸው እቅድ የሆነው)  የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ይመስሉኛል፡፡ከእነዚህ ላይ ከተጨመረ የሚጨመረው መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገሮች ተርታ እንድንመደብ ያደረጉት ጥረት እየተባለ የሚወራው አወዛጋቢውን የኢኮኖሚ እድገት የማስቀጠል ወሬ ነው፡፡ እነዚህ የመንግስትን ፕሮጄክት እና የግለሰብን ራእይ ማቀላቀል ጉዳዩች ወደጎን ትተን ብናስበው እንኳን ማንኛውም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ የተቀመጠ መሪ ሊያደርግ የሚገባውን የመንግስትን ስራ የመምራት የማቀድ እና የማስፈጸም ስራ እንደ ራእይ ማሰቡ አልተዋጠልኝም፡፡አቶ መለስ ላለፉት 21 አመታት አገዛዛቸውም ቢሆን አገራችን ብለው ጠርተዋት የማያውቋትን ኢትዮጲያን በምግብ ዋስትና ራስን ስለማስቻል በተለያየ ጊዜ ከተናገሩት ውጪ (እርሱም መንግስታዊ ሃላፊነት እንጂ ራእይ ሊሆን አይችልም) ስለወደፊትዋ ኢትዮጲያ የሚታወስ ራእይ ማስቀመጣቸውን እጠራጠራለሁ፡፡

ምንም እንኳን አቶ ለመለስ ታላቅ መሪ ለመባል የመፈለግ  ራእይ ሊኖራቸው እንደሚችል ብዙዎች ቢጠረጥሩም እንደ እኔ እንደእኔ የአቶ መለስ ራእይ ከዚያም በተጨማሪ በዋናነት የራሳቸውን እና የፓርቲያቸውን የስልጣን ዘመን ማስቀጠል እንደነበር ይሰማኛል፡፡ ከላይ የዘረዘርኳቸው የማንኛውም መንግስት ሃላፊነቶችን ማከናወን የተለመደ የመንግስት ተግባር ቢሆንም የተለየ እመርታ ስናሳይ እንደከረምን እና አስደናቂ አገራዊ ለውጥ ላይ እንዳለን ተደርጎ ሲቆጠር አስተውያለሁ፡፡ ባቡር ለመስራት ያሰቡ ግድብ ለመገንባት ያቀዱ እና የመንግስትን እቅድ ያወጡ መሪዎች ባለራእይ ሲባሉ ሰምተን የማናውቀውም የመንግስት ስራቸውን መስራታቸው ባለራእይ ስለማያሰኛቸው ብቻ ነው፡፡(አቶ መለስ እንኳን ደሞዙን ሰልጣኑን እና ስሙን ለያዙት ስራ ቀርቶ ባለቤታቸውን ለማገዝ ለኤፈርትሰ ሲያቅዱ አልነበር አንዴ?) እኔ በግሌ ብጠየቅ አቶ መለስ ራእይ የፓርቲያቸውን አገዛዝ እና የስልጣን እድሜ ማራዘም፣ሞተው እንኳን “የቀድሞው” ለማለት ለመድፈር ያልቻለ የእርሳቸው አምላኪ የፓርቲ ስርአትን ማጠናከር፣ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ የራስን ገጽታ መገንባት እንዲሁም የመድብለ ፓርቲ ስርአት እና የነጻ ፕሬስን በማንኛውም ሁኔታ እንዳይኖር ማድረግ የመሳሰሉት ናቸው፡፡አቶ መለስ ያለሟት ኢትዮጲያ ሲቪል ማህበረሰብ የማይኖርባት ሰብአዊ መብት የማይወራባት ጋዜጠኞች በተሰጣቸው ልክ ብቻ የሚንቀሳቀሱባት ግልጽ ቀይ መስመር የተሰመረባት ነበረች፡፡ የራእይ ማሳካት ማሃላችን እነዚህንም አብሮ እንደሚጨምር ማስተዋሉ አስፈላጊ ነው፡፡

የአቶ መለስ ውርስ

አቶ መለስ ለ21 አመት አገር እንደመግዛታቸው የሚያስቀሩት ውርስ ያስለመዱት ስርአት የፈጠሩት አካሄድ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ጥያቄው ውርሳቸውን ምንድነው ማስቀጠሉስ ለማን ይበጃል ውርሱስ ምንድነው የሚለው ነው?

ቁጣ እና ንቀት - ውርስ 1

ከአቶ መለስ ውርሶች አንዱ እና ሁሌም ከእርሳቸው ጋር ተያይዞ የሚታሰበኝ ማንንም ቢሆን ከመቆጣት ያለመመለሳቸው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ማንንም አልፈራም አባዜ ከፓርላማ አንስቶ እስከ ጋዜጠኞች የሚነሱ ጥያቄዎች መልስ እስከመስጠት ድረስ ይታያል፡፡አቶ መለስ በፓላማም ሆነ ጥያቄ በሚመልሱበት ወቅት ተቃዋሚዎችን ያስፈራራሉ፣ህዝቡን ንቀት በሚመስል መልኩ አግባብ ዛቻዎችን ሲያሰሙ ይስተዋላሉ፡፡ ማንኛውንም እርሳቸው ያሉትን መንገድ የማይደግፍ የመሰላቸው አካል ላይ ዘለፋን ያሰማሉ፡፡ ይህ የአቶ መለስ ውርስ ነው፡፡ ውርሱን እናስቀጥላለን ስንል ደሞ ተተኪው ጠ/ሚኒስትርን ተሳዳቢ በንቀት ተናጋሪ እና በፓርላማው በስተቀኝ በኩል በዛቻ ጣቶቹን የሚያወዛውዝ ይሁን እያልን መሆኑ ነው ማለት ነው፡፡

በድን ፓርላማ - ውርስ 2

አቶ መለስ ያወረሱን ሌላው ነገር አሳፋሪ እና በድኑ ብቻ የሚንቀሳቀስ ፓርላማ ነው፡፡ይህ የአገሪቷን ህዝብ ወክያለሁ የሚል ፓርላማ የማይናገር የማይሰማ የሃሳብ ልዩነት የማይታሰብበት ከመሆኑም በላይ  በበድንነቱ የማያፍር ግን የሚያሳፍር ፓርላማ የአቶ መለስ ውርስ ነው፡፡ ይህ “የታላቁ መሪ” ውርስ ፓርላማ ለመልካም ምኞት መግለጫ የሚያላግጥ፣ ላልተቀለደ ቀልድ የሚስቅ፣ የመስማት እና መናገር እንዲሁም ማሰብ የተሳናቸው ስብስብ ከመምሰሉም በላይ በታየ ቁጥር የሚያሸማቅቅ ብሄራዊ ሀፍረት ነው፡፡ (እግዜር ይስጣቸውና በአፍሪካ እና በአለም መድረክ የሚያኮራ ፓርላም ብለው ዜና ነግረውን አለማወቃቸው ያስመሰግናቸዋል) የአቶ መለስን ውርስ ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ማስቀጠል ይህንን በድን ፓርላማ ይዞ መንቀሳቀስን ይጨምራል፡፡

የምርጫ ድራማ - ውርስ 3

ምርጫ የሚባለውን ሃሳብ ወደ ድራማ እና ቀልድነት ብሎም ወደ አገራዊ ጨዋታ የቀየርነው፣ ከተስፋ ምንጭነት ወደ አገራዊ ኪሳራነት የለወጥነውም በዚሁ በአቶ መለስ አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ ይህ “ምርጫ የሚሉት ጨዋታ ምን ያደርጋል?” ወደሚል አገራዊ አስተሳሰብንም ያመጣነው በዚሁ ዘመን ላይ ነው፡፡ የአቶ መለስን ውርስ ስናስቀጥል ምርጫን የማጨበርበሪያ እና የአለም አቀድ ድጋፍ ማግኛ መድረክ ከመሆኑ ውጪ ለማሰብ ያለመቻላችንንም አብረን እናስቀጥላለን ማለት ነው፡፡

የወረቀት የመድብለ ፓርቲ ስነ ስርአት - ውርስ 4

የመድብለ ፓርቲ ስርአት በኢትዮጲያ የወረቀት ብቻ እንዲሆን ያደረጉት አቶ መለስ ናቸው፡፡ የተቃዋሚን ፓርቲን መምራት እና በተለመዱ መንገዶች ማህበረሰቡን መድረስ የማይቻልባት ጠንካራ ተቃዋሚ ማግኘት ምኞት የሆነባት ኢትዮጲያ መፈጠር የአቶ ለመለስ አስተዋእጾ ከፍተኛ ነው፡፡ እንኳን በተቃዋሚ ፓርቲ ደረጃ ቀርቶ በኢህአዴግ ስርአት ውስጥ እንኳን የአጋር ፓርቲዎችን በነጻ የመቆም መብት የማይታሰብ መሆኑም የእርሳቸው አመራር ውጤት ነው፡፡ የግለሰቦችን አቅም ተጠቅሞ ውስጠ ፓርቲ አቅሙን ያላጠናከረው ኢህአዴግ ዛሬ በመሪው ሞት ብዙ ነገር እንዳጣ ሲያወራ ይስተዋላል፡፡ የአንድ ግለሰብ አቅም እና ገጽታ ግንባታ የሚያሳስበው የአንድ ፓርቲ ረዥም ዘመን አገዛዝን ለማጠናከር የሚሰራው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖር የሚያሰጋው፣ አጋር ፓርቲዎች ልዩነት ሳይኖራቸው እንዲገዙ የሚያደርገው አሃዳዊ ስርአት የአቶ መለስ ውርስ ነው፡፡

የተሽመደመዱ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት - ውርስ 5

የህዝብ አግልግሎት ተቋማት አገልግሎት ተሸመድምዶ “አገልግሎት ለመሆኑ አለ?” በሚያስብል ደረጃ የ የምትገኘው አገራችን የአቶ መለስ አመራር ውጤት ናት፡፡በ21 አመታት አገዛዛቸው አቶ መለስ ደካማ አገልግሎት ሰጪውን ኢትዮ ቴሌኮምን፣ በቋሚነት መብራት ማቋረጥ ስራው የሚመስለውን የኢትዮጲያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽንን አውርሰውን አልፈዋል፡፡እነዚህ የተሸመደመዱ ተቋማት ምሳሌዎች ጠቀስን እንጂ ደንበኛ የሚያስለቅሱ የመንግስት ተቋማት የኚሁ መሪ ውርስ ናቸው፡፡ እንግዲህ ይህንንም ማስቀጠላችን ነው ማለት ነው?

የተቀላቀሉ ፓርቲ እና መንግስት - ውርስ 6

በደንብ ያልተነገረለት እና በሚገርም ሁኔታ ልዩነቱን ማሳየት የማይቻለው የፓርቲ እና የመንግስት መጋባትም የአቶ መለስ ውርስ ነው፡፡ በየትኛውም የመንግስት ስራዎች ውስጥ የፓርቲ አገልጋዮችን ማየት የማይገርምበት የመንግስት ሃብት ለአንድ ፓርቲ ግላጋሎት ሲውል ሃይ ባይ የሌለበት ስርአት አቶ መለስ የፈጠሩት ስርአት ነው፡፡የህዝብ ሃብት በማንአለብኝነት የሚጠፋበት ስርአት የአቶ መለስ ውርስ ነው፡፡ከውርሱ መቀጠል ጋር ተያይዞ እንግዲህ ኢህአዴግ የመንግስትን ሃብት እንደፈለገ ሲጠቀም እንዲኖር መፍቀዳችን ነው ማለት ነው፡፡

ሊሞት አንድ ሐሙስ የቀረው የግል ሚዲያ እና ለውሸት ቆርጦ የተነሳ የመንግስት ሚዲያ - ውርስ 7

መንግስትን የሚተች፣የሚያስተምር አቅጣጫ የሚጠቁም የግል ሚዲያ ኢትዮጲያ ውስጥ የሚታገሱት ነገር እንዳይሆን የተደረገው በአቶ መለስ የአገዛዝ ዘመን ሲሆን እስካሁንም ውርሳቸው ሆኖ ተተኪዎቻቸው እያስቀጠሉት ይገኛል፡፡ይህ ምንም አይነት ትችት ያለመታገስ ባህሪይ የአገሪቷን የህትመት ሚዲያ በየቀኑ የሚሞት እና ጠራርጎ ሊጠፋ አንድ ሃሙስ የቀረው ሆኗል፡፡ ጋዜጠኞችን የሚያሰድደው፣ የሚያስር እንዲሁም ለህይወታቸው የሚያሰጋ(በአለም አቀፍ ደረጃ የመሰከረለት) ስርአት የአቶ መለስ ውጤት ሲሆን ይህንንም እንግዲህ ልናስቀጥል መሆኑ ነው፡፡

ሰብአዊ መብትን የማያወሩ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት - ውርስ 8

ስለሰብአዊ መብት ማውራት እንደሃጥያት የሚቆጠርባት ኢትዮጲያ የአቶ መለስ ዘመን ላይም ለውጥ አላሳየችም፡፡ ድሮም በነጻነት መደራጀት የማይፈቀድላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ከ1997 በኋላ ደግሞ በጠቅላላው ሰብአዊ መብት ደህና ሰንብት እንዲሉ ተገደዋል፡፡ በነጻነት መደራጀት የምቾት ጥያቄ እንደሆነ የሚቆጠርባት “ዳቦ ቅድሚያ” ተብሎ ሰብአዊነት የተረሳባትን ኢትዮጲያ አቶ መለስ ውርስ ስትሆን እናስቀጥላለን ብለን ስንምል ይህንንም ጨምረን መሆኑ ነው፡፡
የፍርሃት ትውልድ - ውርስ 9

ፍርሃት የግል ባህሪያችን ሆኖ የቀረበት ይህ ዘመን የአቶ መለስ ውርስ ነው፡፡ በትንሹ እንኳን ሃሳባችንን መግለጽ የምንፈራበት፣ ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት ሲገልጹ የምናሳቅቅ ሰዎች የተፈጠርነው በእነዚሁ 21 አመታት ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ጥቂት አመታት በአቶ መለስ ስብእና ግንባታ ልክ እያደገ የመጣው የፍርሃት መጠን ማህበረሰቡን የፍርሃት ማህበረሰብ ለማለት እስክንደፍር ድረስ ተጋኗል፡፡ይህንንም ማስቀጠል ማሃላው ውስጥ መጠቃለሉን አለመርሳትም ጥሩ ነው፡፡

የኑሮ ውድነት እና የከተማ ድህነት - ውርስ 10

ቀን ከቀን የሚሻሻል የማይመስል ልብ የሚሰብር እና የከፋ የከተማ ድህነት የኑሮ ውድነት፣ የእለትን ጉርስን የማግኘት ትግል፣በደሃውና በሃብታሙ መካከል የሚታይ ከፍተኛ የኑሮ ልዩነትም ቢሆን የአቶ መለስ ውርስ ነው፡፡መጓጓዥ አገልግሎት ችግርን መፍታት ያቃተው አሰራር ትራንስፓርት ማግኘት እድል እንደሆነ የሚቆጠርበት ከተማ ከአቶ መለስ የተረከብናቸው ውርሶቻችን ናቸው፡፡

ራእይ እና ውርስን የማስቀጠል መሃላው ቢለይልን ብናውቀው እና ብንረዳው ቢያንስ ለሚዛናዊነት ይረዳናል፡፡ካልሆነም እኔ ከጠቀስኩት ውጪ ሌላ ውርስ እና ሌላ ራእይ  የሚጨምር ካለ ለመስማት ዝግጁ ነኝ፡፡

3 comments:

  1. No comment.
    Go Forward...

    ReplyDelete
  2. የአቶ መለስ ራዕይ... ታጋይ አዜብ መስቀል አደባባይ ላይ ተሰቅለው እንደተሳለቁብን "አባት የሌላቸው ልጆች ላሳድግ ስለሆነ የባለቤቴን ራዕይ የማውቀው እኔ ነኝና 'ሳይበረዝና ሳይከለስ' ከቐጠለ አብሬ እሰራላሁ አለበለዚያ ዋ!አሉ።

    ሰሞኑን በወዳጃቸው በአቤ ቶክቻው ብሎግ በላኩት የቪዲዮ መልዕክት እንዲህ አፍንጫቸው የሱዳን, ጉንጫቸው የወልቃይት, እጃቸው የምሁር፣አይናቸው የቻይና እስኪመስል ድረስ ያለቀሱት... ለጠቅላዩ መጠቅለል?፣ጠ/ሚር ባለመሆናቸው?፣ከቤተ መንግስት በመውጣታቸው?፣ወይንስ አቶ መልስ ላለፉት አምስት ዓመት ዕቅድ እና ራዕያቸው ትግራይ በእንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እንድትበለፅግ ያቀዱት በመሞታቸው ምክንያት "ኢፈርት" ትንሽ የመዋዠቅ እክል ገጥሞት ስለነበር ይሆን ? ? ያ ደረት የተደቃበት! እንባ በቪዲዮ የተቀዳበት!የልመና የስንዴ ንፍሮ በድንኳን የተነፋበት የአምስት ዓመቱ "የኮንፊውሽን እና የቡጠራ ቀደዳ" እዚሁ ላይ አማረበት ቁርጣችሁን እወቁ!! ሸዋ ተበላህ በለው!ሶልያና ሽመልስን እናመሰግናለን!! ከሀገረ ካናዳ በቸር ይግጠመን>>>>>>>>>>>

    ReplyDelete