በበፍቃዱ ኃይሉ እና በእንዳልካቸው ኃ/ሚካኤል
በወጣትነት ወንድ ዕድሜ ክልል ከሆንክ
አሁን የምናወራው ነገር ቢያንስ አንድ ቀን እንደገጠመህ አንጠራጠርም፡፡ መንገድ ላይ እየሄድክ ነው እንበል፣ ሰፈሩን አታውቀውም፡፡
ወደየሆነ ቦታ አቅጣጫ የሚያመለክትህ ሰው እየፈለግክ ነው፤ አንዲት በአንተ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለች ሴት ከወዲያ ማዶ ስትመጣ
አይተህ በመደሰት ‹‹ይቅርታ የኔ እህት፤›› ትላታለህ - አቅጣጫ ለመጠየቅ፡፡ ሴቲቱ ገልመጥ ብላ ታይህና (ወይም ቀድማ ካየችህ)
እንዳልሰማ ሰው ፊት ነስታህ ታልፍሃለች፡፡ አቅጣጫውም አልተገኘ፣ ክብርህም አልተጠበቀ ይሉሀል ይህን ጊዜ ነው - በለካፊ ወንድነት
የመፈረጅ ጣጣ፣ ወጣት ወንድ የመሆን ጣጣ! ነገር ግን ይሄ ‹‹እዳው ገብስ›› የሆነ ጣጣ ነው፡፡
የዞን ዘጠኝ ብቸኛ የሴት ጦማርያን የሆኑት
ማሕሌት እና ሶልያና ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ ያስነበቡን ‹‹ወጣት ሴት የመሆን
ጣጣ›› ለዚህ ጽሑፍ መወለድ መንስኤ ሆኗል፡፡ እነርሱ የወጣት ሴትነትን ጣጣ በዘረዘሩ ቁጥር ወንድ ሆኖ እያነበበ ያለ ወንድ
የመሆን ጣጣን ማሰብ የሚቸግረው ይኖራል ብሎ ማለት ዘበት ነው፡፡ ነገርዬው ‹‹የሴቶች ጉዳይ›› ብቻ የሚጮህበት ዘመን መሆኑ፣ ወንዶች
ወንድ በመሆናቸው ብቻ የሚጋረጡባቸውን ፈተናዎች (ወይም በዚህ ጽሑፍ ቋንቋ ‹ጣጣዎች›) የሚያወራ መገናኛ ብዙኃን የለም፡፡ የዚህ
ጽሑፍ ዓላማ የሴቶቹን ጣጣ ማጣጣል፣ ወይም ዕውቅና ማሳጣት ሳይሆን ወጣት ወንድ በተለይ እና ወንድ በጥቅሉ መሆንም በራሱ የራሱ
ጣጣዎች እንዳሉት ማመላከት እና ለጣጣዎቹ ዘላቂ መፍትሄ ወደሚያመጡ የውይይት አጀንዳዎች የዞን ዘጠኝን ነዋሪዎች በዚህ መድረክ እና
ከዚህም ውጪ እንዲያበረክቱ ማነሳሳት ነው፡፡
በልጦ የመገኘት ጣጣ
በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን በተገነቡ
ባሕሎች እና እሴቶች መሠረት ወንድ ልጅ የአውራነት፣ ወይም በልጦ የመገኘት ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ለምሳሌ የፍቅር ወይም የትዳር አጋር
ለማግኘት በትምህርት ደረጃ፣ በደመወዝ ሌላው ቀርቶ ተፈጥሮ በሚያስገድዳቸው ቁመት እና ዕድሜ ሳይቀር በልጦ መገኘት አለበት፡፡ ይህንን
ባሕል አመጣሽ በልጦ የመገኘት ኃላፊነት በዘመነኝነት ለመስበር ቢሞከርም የተሳካ አይመስልም፡፡ ሴቲቱን ከፍሎ የሚያስተምር፣ ሸምቶ
የሚያስውብ፣ አግብቶ ቤቱ የሚያመጣ እንጂ በተቃራኒው የሚንቀሳቀስ ወንድ የለም፤ ሴቶቹም (ብዙኃኑ) አይፈልጉትም፡፡
ወንድ ልጅ ለሴት ልጅ ከለላ እንዲሆን
በወንዶቹም በሴቶቹም ይጠበቅበታል፡፡ ሚስቱን ከለካፊ ጎረምሳ ማስጣል (መጠበቅ)፣ መሠረታዊ ፍላጎቷን ማሟላት፣ በየካፌው መጋበዝ፣
የዕድሜ፣ የትምህርት እና የደሞዝ (አቻው የሆነችውን ሳይቀር) ሙሉ የኢኮኖሚ ጥብቅና ማድረግ ያልተጻፈ ግዴታው ነው፣ ወዘተ… ወዘተ… ከዚህም በላይ ደግሞ በዚህ ክፉ ዘመን ኑሮን ታግሎ አሸንፎ፣
ጎጆ መሥርቶ፣ የቤት ዕቃ ሞልቶ፣ ሠርጎ ማግባት አለበት፡፡ ይህንን ሁሉ ማድረግ ስለሚከብደው ቆሞ የቀረ አለሌ የመሆን ጣጣ ፊቱ
ላይ ተደቅኖበታል፡፡
ይህንን ዓይነቱን ጣጣ የወጣት ወንዶች
ጣጣ ብቻ ብለን የጠራነው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን እና ባሕል ውስጥ ሴቶች የቤተሰብ ራስ የመሆን ኃላፊነት የለባቸውም
ማለት ይቻላል፡፡ እርግጥ ነው፣ ጎጆ ከወጡ በኋላ የቤቱን ምሰሶ መሸከሙ የሁለቱም ድርሻ የሚሆን ቢሆንም በተለይ የጎጆው መሠረት
የሚጣልበት ንዋይ በወንዱ ጋጋሪነት እንዲሟላ መሆኑ ከባድ ጣጣ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሴቶች እንዲያውም ቤቱን ሞልቶ እና አደራጅቶ
የተገኘው ወንድ ቤት ዘው የማለት የተሰናዳ ዕጣ ፈንታ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ምስኪኑ ወጣት ወንድ ግን የ‹ገርልፍሬንዱ›ን ወቅታዊ ፍላጎት
በሟሟላት እና ስለወደፊቱ በማቀድ መሐል ብኩን ‹ችስታ› የመሆን ዕጣ ሲገጥመው ‹ገርልፍሬንዱ› ይህ ሰው ለቁም ነገር አይሆንም በሚል
ንቃው፣ ራሱን በሀብት ሲያደራጅ ያረጀ ወንድ ጠቅልሏት - ወጣቱ ከሁለት ያጣ ሆኖ የመቅረት ዕድሉ የዘወትር ድራማ ሆኗል፡፡
የአደገኛ ቦዘኔነት ጣጣ
ወጣት ወንድ፣ በተለይም እኩዮቹን ለመምሰል
ፀጉሩን ካፍተለተለ፣ ሱሪውን ዝቅ አርጎ ከታጠቀ - ምንም እንኳን አለባበስ ከማንነት ጋር
ቀጥተኛ/የማይነጠል ግንኙነት ባይኖረውም በቃ አለቀ - አደገኛ ቦዘኔ ነው፡፡ በአደገኛ ቦዘኔነት የሚፈረጀው በመንግስት
(ብቻ) ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፤ በሕዝቡ ነው፡፡ ታክሲ ውስጥ ለመግባት ከሌላው ሰው ጋር ሲጋፋ ገልመጥ፣ ገልመጥ እያለ ኪሱን የሚያሸሽበት፣
እጁን በጥርጣሬ የሚመለከትበት ብዙ ሰው ነው፡፡
ሥራ አጥነት የአገሪቱ ቁጥር አንድ ችግር
መሆኑ ቢታወቅም፣ ከተሞች በቂ (ያውም ካለ) የወጣቶች መዝናኛ እንደሌላቸው ቢታወቅም፣ ወጣት ወንዶች መንገድ ዳር ሰብሰብ ብለው
ቆመው ከእኩዮቻቸው ጋር ሲጨዋወቱ ሲታዩ፣ ሴት ሊለክፉ፣ ማጅራት ሊመቱ፣ ወይም ደግሞ ሌላ የውንብድና ተግባር ሊፈፅሙ ፈልገው እንጂ
አገራዊ-ማኅበራዊ ቀውስ አባክኗቸው ነው ብሎ የሚያዝንላቸው የለም፡፡
በርካታ ወጣት ወንዶች ከሚታሙበት የሱስ
አዘውታሪነት ችግር ጀርባ ይህ ‹በአደገኛ ቦዘኔነት› (ዱርዬነት) የመፈረጅ ጣጣ አለ፡፡ ብዙዎች መንገድ ዳር ላለመቆም የሚያገኙት
አማራጭ ካፍቴርያ ወይም ጫት መቃሚያ ቤቶችን ነው፡፡ ለትንሽ አገልግሎት ብዙ ዋጋ የሚጠይቁት ካፍቴሪያዎች ወጣት ደንበኞቻቸው ‹ብዙ
ሳይገለገሉ፣ ብዙ መቀመጣቸው›ን ስለማይፈልጉት እንዲወጡላቸው ብዙ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ ይህ የግል ኩራታቸውን የሚፈታተናቸው ወጣት
ወንዶች፣ ከዚህ ይልቅ ከግማሽ ቀን በላይ ቁጭ የሚባልበትን ጫት መቃሚያ እንደተሻለ ጊዜ ማሳለፊያነት በመቁጠር ላይ ናቸው፡፡
በሴት ጠላትነት የመፈረጅ ጣጣ
አንዲት ሴት ልጅ ጾታዊ ጥቃት በደረሰባት
ወይም ተመሳሳይ ነገር በተከሰተ ቁጥር ሴቶቹ ሁሉ፣ ወንዶችን ሁሉ በጥርጣሬ እና በመኮነን ዓይን ይመለከታሉ፡፡ ወንጀሎች የሚፈጸሙት
ሰብኣዊነት በሚጎላቸው ሰዎች መሆኑ ቢታወቅም፣ ልጃቸውን የገደሉ እናቶች ያሉ መሆኑ ቢታወቅም… ሴት ልጅ በወንድ ጓደኛዋ አንድ ጥቃት
በደረሰባት ቁጥር ሁሉም ወንዶች ላይ ጣት ይቀሰርባቸዋል፡፡ በጥርጣሬ ዓይነት ይታያሉ… ‹‹ውይ ወንዶች!›› ይባልላቸዋል፡፡
በአዲስ አበባ፣ ወረዳ ምንትስ፣ ቀበሌ
ምንትስ ውስጥ ‹‹አንድ ባል ሚስቱን በጭካኔ ገደለ›› የሚል ዜና በተነበበ ቁጥር፣ ‹‹አንድ ሰው፣ ሌላ ሰውን መግደሉ›› ወንዱንም
ሴቷንም እኩል የሚያሳዝን ዜና መሆን ሲገባው፣ ሴቶቻችን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወንዳቸውን በጥርጣሬና በፍራቻ ዓይን (በማያውቀው
ጉዳይ) ሲመለከቱት እና የአጥቂነት ውርስ ሲያከናንቡት ማየት የተለመደ እና የዘመናችን ወንድ በቀላሉ ሊወጣው የማይችለው ጣጣ እየሆነ
መጥቷል፡፡ ወንዱም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ዜና በሌላኛው የከተማዋ ጫፍ በተከሰተች ቁጥር ‹የጥፋተኝነት ስሜት› እያዳበረ እንዲመጣ
ተገዷል፡፡
የቅድሚያ መነፈግ ጣጣ
በጥቅሉ ሴቶች ዕድል ተነፍገዋል የሚባል
ሚት (myth) አለ፡፡ ይህ ሚት ምንም እንኳን በከተማው ውስጥ፣ ዛሬ ዛሬ እውነት ይሁን አይሁን ባይረጋገጥም፤ በከተማ ውስጥ ወንዱም
ሴቷም ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ፈተና የሚገጥማቸው መሆኑ ቢታመንም ሴት ዕድል የተነፈጋት ወንዱ ግን እንደነጻ እየተቆጠሩ ዕድሉን ከወንዱ
የማስነጠቅ ጣጣውም ቀላል የሚባል አልሆነም፡፡ ‹‹ቅድሚያ ለሴቶች›› የሚለው አባባል የት እና ለምን እንደሆነ የተዘነጋ ይመስላል፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ በተሰናዳ
የስርዓተ ጾታ ፕሮግራም ሰለባነት፥ ቁስሉን ያልነካ ይልቁንም ወንዶችን ከሴቶች በሚያለያዩ/በሚያራርቁ አጀንዳዎች በተጠመዱ ‹ፌሚኒስቶች›
ሳቢያ የሚመጣ ሌላም ጣጣ አለ፡፡በአውሮጳ የኮርፖሬት አመራር ላይ የደረሱ ሴቶች ቁጥር ሦስት በመቶ አይሞላም፡፡ እውን ሴቶች ዕድሉን ተነፍገው ነው፣ እውን ቅድሚያ
ተነፍገው ነው እዚያ መድረስ ያልቻሉት ለሚለው ጥያቄ ጥልቅ ምርምር እንደሚያስፈልገው የአውሮጳውያኑ እውነታ ሞጋች ነው፡፡ ቢሆንም ግን በአገራችን፣
አንዴ መዘመር በተጀመረው የዕድል መነፈግ ሰበብ ብዙ ወጣት ወንዶች እኩል ዕድል ይዘው ቀርበው ‹‹በቅድሚያ ለሴት›› በዝረራ የመሸነፍ
ጣጣን የመሸከም ዕጣ ፈንታ ተጋርጦባቸዋል፡፡
የወጣት ወንዶች ጣጣ እነኚህ ብቻ አይደሉም፤
የአቻ ግፊት ጣጣ፣ ሴቶቹ እንደጠቀሱት ዓይነት የመምሰል ጣጣ፣ ሌሎቹም ሌሎቹም እየተገዳደሩት ይገኛል፡፡ ጥያቄው ታዲያ ለመሆኑ ይሄ
ሁሉ ጣጣ መፍትሄ አለው፣ ሊኖረውስ ይችል ይሆን የሚለው ነው፡፡
መነጋገር እንደመፍትሔ
መነጋገር የነገር ሁሉ መፍትሔ ነው፡፡
በተለይ ሴቶች በወንዶች ላይ፣ ወንዶች በሴቶች ላይ የሚያመጧቸው እያልን የዘረዘርናቸው ጉዳዮች ሁሉ ባብዛኛው ባለመነጋገራችን፣ እንደነውር
በጣፍናቸው ችግሮች ሳቢያ የተከሰቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ወንዱ ገንዘብ ሳይኖረው ‹‹የለኝም›› ላለማለት ተበድሮ ‹ገርልፍሬንዱን› ከጋበዘ፣
ሴቲቱም ‹‹የወንድ ልጅ ደሞዝ… የሴት ልጅ ዕድሜ አይጠየቅም›› እንደሚባለው ስላለው ነው የሚጋብዘኝ በማለት ሊፕስቲክ፣ ቻፕስቲኳን
ብቻ እየገዛች በሱ ላይ ጥገኝነቷን ካዳበረች… ወዳጅነት ሳይሆን ባይተዋርነት ብቻ በሁለቱ ውስጥ እንደነገሠ ይከርማል፡፡ ብዙዎቹ
በግልጽነት ላይ ያልተመሠረቱ የፍቅር ግንኙነቶችም በመሰላቸት የሚፈርሱት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
ስለዚህ በሁሉም ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገር፣
መነጋገር፣ መነጋገር!
Anjetey Kebe teta!! Ufffff ... Endewe mene ladergachehu!!! <3
ReplyDelete