Showing posts with label Media. Show all posts
Showing posts with label Media. Show all posts

Monday, September 19, 2016

ማኅበራዊ ሚዲያው እና የመንግሥት ስጋት



በተስፋዬ ዓለማየሁ

የማኅበራዊ ሚዲያውን አጠቃቀም በተመለከተ ተከታታይ ዘመቻዎች እና ማጥላላቶች በተለያዩ ግዜያት በሕትመት ሚዲያው ሳነብ፣ በብሮድከስት ሚዲያውም ሳደምጥ ቆያቻለሁ፡፡ እነዚህን የአጠቃቀም ጉድለቶች ላይ ያተኮሩ ዘመቻዎች ታዲያ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስመለከታተቸው ነው የሰነበትኩት፡፡ ምክንያቱም መሰል ፈራጅ ዘጋቢ ፊልሞች በሕትመት ሚዲው ላይ ይሠሩ እና ጠንከር ያለው እርምጃ ይከተል ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በመጀመሪ የኮረኮረኝ ጽሑፍ "ከማኅበራዊ ሚዲያው በስተጀርባ" በሚል ርዕስ በሪፖርተር ገዜጣ ላይ ከወጣ በጣም ቆየት ብሏል፡፡  የጽሑፉ ዋና ዓላማ የነበረው ከማኅበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታ ‹በስተጀርባ ያለውን አደጋ ነው ማመመልከት› ነበር፡፡ የጽሑፉ አዘጋጅም በሚገባ አስረጅ ምሳሌዎችን አስቀምጠው ጠቀሜታውንም ለመዳሰስ ሞክረው ጽሑፋቸውን ቢያበቁም፣ ከዚያ በኋላ በተከታታይ እንዲሁ በተለያዩ ግዜያት ቅኝታቸው ማኅበራዊ ሚዲያው ከጥቅሙ ባሻገር ጉዳቶቹ ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን አንብቤያለሁ፡፡ እርግጥ ነው በተነሱት ሐሳቦች ዙሪያ የማኅበራዊ ሚዲያው፣ በዋነኛነትም ፌስቡክ ከጥቅሙ በዘለለ ባሉት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ላይ መሠረታዊ ልዩነት ከጸሐፊዎቹ ጋር የለኝም፡፡ "የጥላቻ ንግግሮችን ማስተላለፊያ ነው""አሉባልታ ማሰራጫ ነው""የሠራ ግዜን ይሻማል"፣ "በቅርባችን ካሉ ወዳጅ ጓደኞቻቸችን ጋር ይለያየናል"፡፡ ሌሎችም የፌስቡክ እንከኖችን እያስታወስን መዘርዘር አንችላለለን፡፡
  
ማኅበራዊ ሚዲያው ግን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ልንዘነጋው አይገባም፡፡ የማኅበራዊ ሚዲውን ችግሮች ማሳየቱ ለተጠቃሚው አጠቃቀሙን እንዲፈትሽ ስለሚያደርጉ መልካም ሊባል ቢሆንም፡፡ ችግሮቹን ማጉላቱ ላይ ግን አልስማማም፡፡ ከሚጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ለራሳችን በጣም ተስማሚ የሆኑ ችግሮች አይጠፉምና በአግራሞት ወይም በድንጋጤ "ይህማ የእኔም ችግር ነው" የምንለው እና ለችግሩም ተጋላጭ እንደሆንን፣ በደንብ እንዲሰማን የሚያደርጉን ማሳያዎች ስለሚዘረዘሩ ሊያሸማቅቁን ይችላለሉ፡፡ ይህንን ስሜት ከመፍጠር ተሻግረው ግን በሕትመት ሆነ በብሮድካስት ሚዲያ የሚተላለፉት መልዕክቶች ውጤታቸው  (ኢፌክታቸው) ምን ያህል እንደሆነ ትዝብቱን ለየግላች ልተወውና፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ንበማስተዋል መጠቀም የሚለው ምክር ላይም እንስማማና፣ ፌስቡክ በአሁኑ ሰዐት ሁነኛ አማራጭ ሚዲያ እንደሆነ ለማሳየት የሚከተለውን እጽፋለሁ፡፡

መነሻ፤ በአገራችን የሕትመት እና የብሮድካስት ሚዲያ ሁኔታ ወፍ በረር ቅኝት

በአገራችን ውስጥ ያለት የብሮድካስት እና ሕትመት ሚዲያዎች ከሚጠበቅባቸው አንፃር ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ በአግባበቡ እያገለገሉን አይደለም፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን ልንደረድር እንችላለለን፤ የጋዜጠኞች ብቃት ማነስ፣ የጋዜጠኞች የሥነ ምግባር ጉድለት፣ የጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለቤቶች የፖለቲካ ፍላጎት እና አመለካከከት፣ የገበያው ትርፋማነት እያልን በርካታ ምክንያቶችን ብንደረድርም "የእናቴ መቀነት…" ከመሆን አይዘልም፡፡  ምክንያቱም በእነዚህ ሰበቦች ወይም ችግሮች ውስጥ እንኳን የጋዜጠኝነት መርሖዎችን ለማክበር ከመሞከር ይልቅ ሲጥሷቸው በግልጽ ይስተዋላሉ እና ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ጠንከር ባሉ ሁሉን ዐቀፍ ተሳትፎ እና ውይይት በሚፈልጉ አገራዊ፣  ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም በዕኩል ደረጃ አያሳትፉም አያገልግሉም፡፡ አብዛኛዎቹ የአገራች ሚዲያዎች በጣም የተካኑባቸው እና የሚሽቀዳደሙባቸው ዘገባዎች በጣም ለስለስ ያሉ ማኅበራዊ፣ የመዝናኛ እና የስፖርት፣ የኪነ ጥበብ፣ የፊልም እና የፋሽን ጉዳዮች ናቸው፡፡

Monday, March 7, 2016

የስድስት ሰዓት ሴት ተጠያቂዎች



በማሕሌት ፋንታሁን

ጥቂት ስለ ቃሊቲ የሴቶች መቆያ እና ማረሚያ ቤት

የማይቻል ነገር እንደሌለ በተግባር ለማየት ከሚያስችሉ ሁኔታዎች አንዱ የእስር ቤት ሕይወት ነው። እስር ቤት እንገባለን የሚል እሳቤ በአይምሯችን ውስጥ ስለማይኖር በአብዛኛው ከተለመደው የኑሮ ዑደት (መወለድ፣ ማደግ፣ መማር፣ መሥራት፣ ማግባት፣ መውለድ፣ ማደርጀት እና መሞት) እና ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተን ነው የግል አቋማችንን የምንቀርፀው። "ከሰው ጋር መተኛት አልወድም/አልችልም፤ እንቅልፍ አይወስደኝም"፣ "ስፕሪስ ሳልጠጣ መዋል አልችልም"፣ "የቀዘቀዘ ምግብ አልወድም"፣ "ሲጃራ ሳላጨስ መኖር አልችልም"፣ "በቀን ቢያንስ ሁለት ፊልሞችን ካላየሁ አልደሰትም"፣ "እከሊትን/እከሌን ሳላይ መዋል አልችልም"፣ "ጨለምለም ካላለ ወደ ቤት መግባት አልወድም"፣ "መብራት ካልጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም" እና የመሳሰሉ የማይለወጡ የሚመስሉን አቋሞቻችን ፈተና ውስጥ የሚወድቁት የእስር ሕይወትን ‹ሀ› ብለን ስንጀምር ነው። ብዙ አልችልም ብዬ የማስባቸውን ነገሮችን ችዬ ስለወጣሁበት ስለ ቃሊቲ የሴት እስረኞች ግቢ ጥቂት ልበላችሁ።

በቃሊቲ እስር ቤት ግቢ ውስጥ ከሚገኙት 8 ዞኖች ሁለቱ የሴት እስረኞች የሚኖሩበት ነው። በአንደኛው ዞን በቀጠሮ ላይ የሚገኙ ሴቶች  በሌላኛው ደግሞ የተፈረደባቸው ሴቶች ይኖሩበታል። ልዩ ጥበቃ ወይም  የቅጣት ቤት የሚባሉ ቤቶች አሉ። ወይም በተፈለገበት ሰዓት ይሠራሉ። ለምሳሌ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ከማንም እስረኛ ጋር እንዳትገናኝ 5ት ሰው ብቻ የሚኖርበት የቅጣት ቤት ውስጥ ነበር የምትኖረው። ISISን በመቃወም ከተጠራው ሰልፍ ጋር በተያያዘ ሚያዚያ ወር 2007 የታሰሩ ሴቶች ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ ለብቻቸው በተሠራላቸው ቤት ይኖሩ ነበር።

በቀጠሮ ዞን ደግሞ 5 ቤቶች ያሉ ሲሆን በፍርደኛ ግቢ 6 ቤቶች አሉ።አንድ ቤት ውስጥ ከ 40 እስከ 120 እስረኞች ይኖራሉ። ቀጠሮ ግቢ ከአንዲት አነስተኛ ሱቅ በስተቀር ሌላ ምንም ስለሌለ የተለያዩ ነገሮችን ለመገበያየት  እና ፀጉር ቤት ለመጠቀም  ፍርደኛ ግቢ መሄድ ግድ ይላል። ቤተሰብ መጠየቂያ ቦታው የፍርደኛ ግቢን አቋርጦ የሚገኝ ቦታ በመሆኑ፤ በቤተሰብ መጠየቂያ ሰዓቶች (ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋቱ 2:30 እስከ 6:00 ከሰዓት ከ7:30 እስከ 10:00 እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ጠዋት ከ2:30 እስከ 6:00)፤ ቀጠሮ ክልል የሚገኙ እስረኞች ከፍርደኛ ክልል ማግኘት የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት ይችላሉ።  በቀጠሮ እና ፍርደኛ ክልል መሐል 200 ሜትር ገደማ ርቀት ያለው ሲሆን በየግቢዎቹ በር እና ማማዎች ላይ ጠባቂ ፓሊሶች አሉ። ዞኖቹ (ቤቶቹ)  ከአስተዳደር ጀምሮ በእስረኞች በተመረጡ የእስረኛ ኮሚቴዎች ይመራል። በየቤቱ ለሊት የሚደረግ ጥበቃ አለ። ሮንድ ይባላል። እያንዳንዷ እስረኛ ተራዋ በደረሰ ቀን ለሁለት ሰዓት ከሌላ አንድ እስረኛው ጋር ይጠብቃል። ከለሊቱ 5:00 ሰዓት እስከ 7:00 እና ከ7:00 ሰዓት እስከ 9:00 ሮንድ ተረኞች የሚጠብቁበት ሰዓት ነው።  የእስረኞች ቆጠራ በቀን ሁለቴ ይካሄዳል። የጠዋት ገቢ ፓሊሶች ከጠዋቱ 12:00 ላይ፤ 11:30 ላይ ደግሞ የማታ ገቢ ፓሊሶች ቆጥረው ይረከባሉ።

የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች

ከላይ የጠቀስኳቸው የእስረኛ "መብቶች" እኛ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ጋር ሲደርስ ቅንጦት ይሆናሉ። እንኳን በውናችን በሕልማችንም አናስበውም። "ይቺም ቂጥ ሆና ለሁለት ተከፈለች" ዓይነት ነገር ነው። ያም መብት ተብሎ  ተሸራርፎ  ሲሰጠን እና ስንከለከል "All animals are equal but some are more equal" የሚለው አባባል ትዝ ይለኛል። የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ማለት በሽብር ወይም በአመፅ ማነሳሳት የሚል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን በቀጠሮ ክልል ሆነው የሚከታተሉ ወይም ተፈርዶባቸው ፍርደኛ ክልል ያሉ ሴቶች ማለት ናቸው። ስያሜው የመጣው ከቤተሰብ ጋር ከምንገናኝበት ሰዓት የተወሰደ ነው። የምንጠየቀው 6 ሰዓት ላይ ብቻ ሲሆን እኔ በቆየሁባቸው ጊዜያት ከ10 ደቂቃ እስከ 30 ደቂቃ ለሚሆን ቅፅበት ነበር። የመጀመሪያዎቹ የስድስት ሰዓት ተጠያቂዎች ለ5 ደቂቃ ብቻ ይገናኙ እነደነበር ሰምቻለሁ። ከዚህ በተጨማሪም የምንጠየቀው  በቅርብ ቤተሰቦች ብቻ ነው። ያለንበት ዞንም ሆነ ቤት በኮሚቴነት መመረጥም መምረጥም አንችልም። ሮንድ ጥበቃ እኛን አያካትትም። ፍርደኛ ግቢ ሄዶ መገበያየት ይናፍቀናል። ቢበዛ የ6 ሰዓት ተጠያቂ ያልሆነ (ኖርማል) እስረኛ እንድንልክ ቢፈቀድልን ነው። ሆኖም ግን አስጠጪ እስረኞች ሰበብ ፈልገው የሚላኩትን ኖርማል እስረኞች ለአሸባሪ ይላላካሉ የሚል ክስ ስለሚያቀርቡባቸው፤ የሚላክልን ማግኘት እስቸጋሪ ነው።


ክሊኒክ እና ፀጉር ቤት ለመሄድ ስንፈልግ ለብቻችን አጃቢ ተመድቦልን ነው። የምትመደብልን አጃቢ ፀጉር ቤት ውስጥ ገብታ ተሰርተን እስክንጨርስ ጠብቃ ይዛን ትመለሳለች። ይሄ ሲገርመን የሆነ ጊዜ ላይ ፓሊሶች የሚሰሩበት ፀጉር ቤት እንድንጠቀም መመሪያ ተላለፈ። ይህ መመሪያ ከተላለፈ በኋላ የሆነ ቀን ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ፀጉር ቤት ለመሄድ ጠይቃ፤ አጃቢዋ እየወሰደቻት የተላለፈውን መመሪያ ስትነግራት  "እኔ እስረኛ ነኝ። ለምንድነው የፓሊስ ፀጉር ቤት የምሰራው? ይቀራል እንጂ!" ብላ ፀጉሯን መሠራቱን ትታ ተመለሰች። እስክትወጣ ድረስም በአቋሟ እንደፀናች ነበር። ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬም የሚደርስብንን መገለል በመቃወም ፀጉሯን በመላጨት መልዕክት አስተላልፋአለች።

Friday, February 12, 2016

ነገረ ‹ቀለም አብዮት›


በዘላላም ክብረት

ሁለቱም ሃገራት በይፋ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጀመሩ መቶ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሁለቱም በተመሳሳይ ወቅት  ከኮሚኒስታዊ አስተዳደርና ስርዓት መፋታታቸውን ባወጁ ማግስት ዴሞክራሲን ተግባራዊ የማድረግ ፈተና አጋጥሟቸዋል፡፡ ሁለቱም ሃገራት በተመሳሳይ ወቅት ባፀደቁት ሕገ መንግስታቸው የምርጫ ዴሞክራሲን (electoral democracy) አውጀዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ሃገራት ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስታቸውን ካፀደቁ ወዲህ ተቃዋሚዎቻቸው ስልጣን ሊይዙ አልቻሉም፤ የመያዝ እድላቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መጥቷል፡፡ ሁለቱም ሃገራት በአሁኑ ወቅት የአንድ ፓርቲ የበላይነት በእጅጉ የጎላባቸው ሃገራት ናቸው፡፡ ሁለቱም ከምዕራቡ ዓለም ጋር (በተለይም በአለፉት 10 ዓመታት ውስጥ) በዴሞክራሲ ጉዳይ እየተጨቃጨቁ እና ምዕራቡን ዓለምም እያንጓጠጡ ቀጥለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ሃገራት እየመሩ ያሉት መንግስታት ትልቁ ፍርሃታቸው አድርገው የሚያቀርቡትም በምዕራባዊያን የሚደገፍ በእነሱ ቋንቋ ‹የቀለም አብዮትን› ነው፡፡ የሁለቱም ሃገራት የጊዜው ገዥዎች ምዕራቡ ዓለም በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ከስልጣን እነሱን ለማውረድ ቀን ከሌሊት እንደሚሰራና ይሄንም እስከ መጨረሻው እንደሚፋለሙት ይገልፃሉ፡፡ የምዕራቡን ዓለም ጣልቃ ግብነት ለመከላከልም ሕጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመራቸውን ገልፀው፤ ጠበቅ ያሉ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያድ) እና የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጎችን በስራ ላይ ማዋላቸውንም በኩራት ይገልፃሉ፡፡ በተለይም የመያድ ሕጋቸው ‹የውጭ ሐይሎችን› ከፖለቲካዉ ምህዳር ለማራቅ ያደረጉት እንደሆነ ሁለቱም በኩራት ይገልፃሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሩሲያ፡፡

ያለፉትን አስር ዓመታት ምስራቅ አውሮፓንና የካውካስስ አካባቢን የሚገልፀው የፖለቲካ መገለጫ ‹አብዮት› ነው፡፡ ከአብዮትም ‹የቀለም አብዮት›፡፡ የኢትዮጵያም የፖለቲካ ምህዳር በተመሳሳይ ጊዜ ባጋጠመው ትኩሳት ምክንያት ከዚህ የአብዮት ተረክ (narrative) ጋር በእጅጉ የሚጋራው ነገር አለ፡፡ አብዮተኞቹ በኬየቭ አደባባይ ሲቆሙና ሲቀመጡ፣ አብዮተኞቹ ቲብሊሲን ሲያጥለቀልቋት ኢሕአዴግ እዚህ ያነጥሳል፤ የአደባባዮቹን ጥበቃ ያጠናክራል፣ አይናቸው በአብዮት ቀልሟል የሚላቸውን ግለሰቦች ያስራል፣ እጅግ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ስለ ቀለም አብዮት አስከፊነት በመንግስቱ ሚዲያዎች ይለቀቃሉ፡፡



በሜይ 23፣ 2014 የቀለም አብዮትን ዋና አጀንዳው አድርጎ ከተካሔደው ሶስተኛው የሞስኮ የዓለማቀፍ ደህንነት ስብሰባ ላይ የሩሲያ ተቀዳሚ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ጀኔራል ቫለሪ ጋሪስሚዮቭ ካቀረቡት መወያያ ላይ የተወሰደ 

(የዩክሬን ሁለተኛው አብዮት በ2014 ሲከሰት በሚያዚያ ወር ውስጥ ብቻ ከታተሙት ሐያ ስድስት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እትሞች ውስጥ ‹ዩክሬንን ያ በእሳት አይጫወትም›፣ ‹ዩክሬን ወደአደገኛ ሁኔታ በመሸጋገር ላይ ናት›፣ ‹ሩሲያ ዩክሬንን አስጠነቀቀች›፣ ‹አይሲሲ በዩክሬን ጉዳይ ምርመራ ሊጀምር ነው› የሚሉ ፅሁፎችን ጨምሮ በአስራ ሁለቱ እትሞች ለውጡን አጣጥሎ፤ ፑቲንን አጀግኗቸው እናገኛለን)

Sunday, February 7, 2016

እከላከላለሁ!


በበፍቃዱ ኃይሉ

ከ18 ወራት እስር በኋላ ስንፈታ ዐ/ሕግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ በሁለት “ምክንያቶች” በወንጀል ሕጉ (አንቀጽ 257/ሀ) ግዙፍ ያልሆነ “በጽሑፍ ለአመፅ የማነሳሳት” ጥፋት ተከላክዬ ነጻ መሆኔን የማረጋገጥ ሸክሙን ወደ እኔ አዙሮታል፡፡ ምክንያቶቹ እነዚህ ናቸው፤

፩) “የግብጽ ዓይነት አብዮት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲነሳ የሚቀሰቅስ ጽሑፍ መጻፉን ለፖሊስ በሰጠው ቃል …‹የእውነት ቃል መስጠቱን› አምኗል” የሚልና፣

፪) ዐ/ሕግ ባቀረባቸው ሰነዶች “በፌዴራሉ ሕገ-መንግሥት የተቋቋመውን ስርዓት ለማፍረስ በጽሑፍ አማካኝነት የቀሰቀሰ ለመሆኑ የተጠቀሱት ማስረጃዎች የሚያስረዱ በመሆኑ” የሚል ናቸው፡፡

የእምነት ወይስ የእውነት ቃል?

ሳይቤሪያ (የማዕከላዊ ጨለማ እስር ቤት) ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ለምርመራ ወጥቶ ሲመለስ ክፍሉ ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች በሙሉ የሚጠይቁት የመጀመሪያው ጥያቄ “አመንክ?” የሚል ነው፡፡ ታሳሪዎቹ ስለምርመራው የሚያውቁት ነገር ስላለ አይደለም ይህንን ጥያቄ የሚጠይቁት፡፡ ነገር ግን የማዕከላዊ ምርመራ በተፈጥሮው፣ በተለይ በሽብር ለተጠረጠረ ሰው “አንዳች ወንጀል እመን” በሚል ስለሆነ ነው፡፡ ሒደቱም፣ በዱላ ነው፡፡ ማዕከላዊ ቆይተው ክስ የተመሰረተባቸው ብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች ፍርድቤት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ “ተከላከሉ” የሚባሉት ለፖሊስ የሰጡት የእምነት ቃል ነው፡፡ ፖሊስ በሥነ ስርዓት ሕጉ ቁጥር 27 መሠረት የተጠርጣሪ ቃል የሚቀበልበትን ሰነድ ሲያስፈርም “… ይህንን በነጻ የሰጠሁትን የእምነት ቃሌን አንብቤ ወይም ተነቦልኝ ፈረምኩ” የሚል ዓ/ነገር ከግርጌው ይጨምርበታል፡፡

ማዕከላዊ ውስጥ የተከሳሽን ቃል በነጻ አእምሮው በፈቃደኝነቱ እንዲሰጥ ማድረግ ነውር ነው፡፡ አንድ ሰው ማዕከላዊ ውስጥ ሲመረመር፣ ክብሩ በስድብ ተዋርዶ፣ እየተደበደበ ነው፡፡ የሥነ ስርዓት ሕጉ አንቀጽ 27/2 ‹ማንኛውም ተጠርጣሪ ለፖሊስ ቃሉን ሲሰጥ በነጻ ፈቃዱ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት፤ ቃል ያለመስጠት መብቱም የተጠበቀ እንደሆነ› ይደነግጋል፡፡ ይህን ግን የማዕከላዊ ፖሊሶች የሚያውቁት አይመስልም፡፡



እኔ ላይ የደረሰው ብቻ ሕግ ለይስሙላ የሚወጣባት እንጂ በሕግ አስከባሪው አካል እንኳን የማይከበርባት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምንኖር ያሳያል፡፡ ማዕከላዊ ውስጥ ቃሌን ለፖሊስ ስሰጥ እንኳን እንደዕቅድ ይዤ ልንቀሳቀስባቸው፣ በመርሕ ደረጃ እንኳን የምቃወማቸውን ነገሮች “አዎ፣ ላደርግ አስቤ ነበር (ማለትም ‹አመፅ ላነሳሳ ጽፌያለሁ›)” ብዬ መርማሪ ፖሊሶች ሲያሻቸው እኔ የተናገርኩትን ወንጀል ሊሆን በሚችልበት መንገድ እየጠመዘዙ፣ ሲያሻቸው ደግሞ ጭራሹኑ እኔ ያላልኩትን ፈጥረው እየጻፉ ያመጡትን የእምነት ቃል አስፈረምውኛል፡፡ ሲደበድቡኝ የከረሙት ሕሊናቸውን በወር ደሞዝ የሸጡ መርማሪዎቼ ያለምንም የሕሊና ወቀሳ የእኔ ቃል ከተባለው ከራሳቸው ቃል ግርጌ “የእውነት ቃሌ ነው” ብለው ጽፈውበታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምንም እንኳን በማዕከላዊ የተጠርጣሪ ቃል በነጻ እንደማይገኝ ከበቂ በላይ በብዙ ተከሳሾችን ጉዳይ በመመልከቱ የሚረዳ ቢሆንም፣ መረዳት ስላልፈለገ “አምኗል” ብሎኛል፡፡ እርግጥ ነው አምኛለሁ፤ በኃይል ፊት ጀግና መሆን ስላልቻልኩ ያላሰብኩ፣ ያላደረግኩትን አምኛለሁ፡፡ እምነቴ ግን እውነቴ አልነበረም፡፡ ወትሮም እኔ የኃይል ትግል ውስጥ አይደለሁምና ኋላም ሆነ ወደፊት በኃይል ፊት የመጀገን ጀብደኛ ሕልም የለኝም፡፡ እስከአቅሜ ጠብታ ድረስ ለፍትሐዊነት የምታገለው ስመታ እየወደቅኩ ነው፤ እረፍት ሳገኝ እየተነሳሁ!

ፍ/ቤቱም ይሁን ከሳሼ መንግሥት ግን መከላከል ሳያስፈልገኝ ቃሉ የኔ አለመሆኑን ሊረዱ የሚችሉባቸው በርካታ ዕድሎች ነበሯቸው፡፡ ጥቂቶቹን ቀጥሎ እንመለከታለን፣

Saturday, January 16, 2016

#Ethiopia: የትዊተር አራማጅነት መሬት ይረግጣል?

በፍቃዱ ኃይሉ

ግርማ ጉተማ የተባለ ሰው ታኅሣሥ 29/2008 የፌስቡክ ገጹ ላይ የጻፈውን ቀንጭቤ በማስነበብ ልጀምር፤ እንዲህ ይላል፣

“ባለፈው ክረምት ‹ለሆነ የፖሊሲ ትምህርት› ኔዘርላንድ በነበርኩ ጊዜ አንድ በመስኩ የአውሮጳ ኅብረት ሰዎችን የማማከር ሥራ የሚሠራ አንጋፋ ፕሮፌሰሬን የማናገር ዕድል አግኝቼ ነበር። ያ መልካም ሽማግሌ ፕሮፌሰር በአውሮጳ ኅብረት የፓርላማ አባላት ሁኔታ ተደናግጧል። እንደአባባሉ፣ ‹እዚያ ያሉ ፖለቲከኞች ደደቦች ናቸው፤… በፖሊሲ ጉዳይ እንድናማክራቸው ባዘጋጁልን ስብሰባ ላይ የምንናገረውን በጥሞና አያዳምጡንም። በየስብሰባው ሁሉ እነርሱ ትዊት በማድረግ አባዜ ተጠምደዋል።” ይልና ጥቂት ወረድ ብሎ ደግሞ “…እኛ ግን ይህንን መልካም ሽማግሌ ፕሮፌሰር ተስፋ ያስቆረጠውን የአውሮጳ ኅብረት ፖለቲከኞች ‹ክፉ አመል› ለራሳችን ጉዳይ መጠቀሚያ ማድረግ እንችላለን። በመጪው ሰኞ [ጥር 2/2008] እነሱ ለስብሰባ ሲቀመጡ እኛ ደግሞ በኢትዮጵያ/ኦሮምያ አካባቢ ያለውን ቀውስ በማጋለጥ በትዊቶች እናጨናንቃቸዋለን።”

፩ - ሀሽታግ

ሀሽታግ ከትዊተር ዕድሜ ያላነሰ ጊዜ ትዊተር ላይ አገልግሎት ሰጥቷል፤ ነገር ግን አሁን-አሁን ፌስቡክን ጨምሮ በሌሎችም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለአገልግሎት በቅቷል፡፡ ሀሽታግ የሁለት ቃላት ጥምር ነው። ሀሽ (#) የተባለው ትዕምርት ሥያሜ ‹ታግ› ከሚለው እና ‹ባጅ› (ወይም ‹ልጥፍ›) ብለን ልንጠራው ከምንችለው ቃል ጋር ተጣምሮ ነው የተፈጠረው። ሀሽታግ አንድ ቃል ወይም ሐረግ በሀሽ ጀምሮ ሲጻፍ (ለምሳሌ #ኢትዮጵያ) የሚፈጠር እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በአንድ ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን ሐሳብ ሲጽፉ ለመናበብ የሚጠቀሙበት መለያ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ለሀሽታጎች የየራሳቸውን ማያያዥያ (ሊንክ) ይሰጡትና ተመሳሳይ ሀሽታግ ተጠቅመው የተጻፉ ጽሑፎችን በአንድነት እንዲታይ ዕድል ይፈጥራሉ። ትዊተር በተመሳሳይ ሰዐት፣ ብዙ ሰዎች የተጠቀሙትን ሀሽታግ ከአንድ እስከ ዐሥር በደረጃ በማስቀመጥ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም ትኩረት እንዲሰጡት ያመቻቻል። በኢትዮጵያ በጣም የመታወቅ ዕድል ካገኙ ሀሽታጎች መካከል #FreeZone9Bloggers (የዞን 9 ጦማሪያን በታሰሩ ወቅት ወዳጆቻቸው እና ሌሎችም እንዲፈቱ የጠየቁበት ሀሽታግ) እና #OromoProtests (በቅርብ ጊዜ በድጋሚ በኦሮሚያ አካባቢዎች የአዲስ አበባ ማስፋፊያ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተቀሰቀሰው የአደባባይ ተቃውሞን የተመለከቱ መረጃዎች የሚነገሩበት ሀሽታግ) ይገኙበታል።

፪ - ሀሽቲቪዝም

‹አክቲቪዝም› የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ብዙ ጊዜ በአማርኛ ‹አራማጅነት› ብለን ለመፍታት እንሞክራለን፤ አንድን ሐሳብ ሰዎች እንዲቀበሉት ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንስቶ ያሉትን የተግባር ሥራዎች ሁሉ ያካትታል። በአጥኚዎች፣ የሆነ ዘዴ ተከትሎ የሚፈፀም የአራማጅነት ሥራን ቃላት በማጣመር የተለያዩ ሥሞችን የመስጠት ባሕሉ አሁን-አሁን እየተለመደ መጥቷል። ለምሳሌ ሀክ የሚለውን የቴክኖሎጂ ሰርጎ መግባት ሥራ (በባሕሪው ሕገወጥ ቢሆንም)፣ አንዳንዶች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በደል ይፈፅማሉ በሚባሉ አካላት ላይ ሲፈፅሙት ‹ሀክቲቪዝም› ይሉታል፤ ሀክ በማድረግ የሚደረግ አራማጅነት እንደማለት ነው። ለምሳሌ ራሳቸውን የኦሮሞ ሀክቲቪስት እንደሆኑ የገለጹ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች በቅርቡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን፣ የመከላከያ ሚኒስትር እና የድሬድዋ ዩንቨርስቲ ድረገጾችን ሰርገው ገብተው በማጥፋት የራሳቸውን መልዕክት አስተላለፈዋል። በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ድረገጽ ላይ ሀከሮቹ ያስተላለፉት መልዕክት ተቃውሞውን ተከትሎ የታሰሩ ሰዎችን ሥም በመዘርዘር ‹እነእከሌ ይፈቱ› የሚል መልዕክት ነው። ይህ ‹ሀክቲቪዥም› ይባላል።

በቅርቡ በጣም ዕውቅና እየተጎናፀፈ የመጣ የአራማጅነት ዓይነትም አለ። ‹ሀሽቲቪዥም› ይባላል። ሀሽቲቪዥም የሆነ ሀሽታግ ተጠቅሞ በአንድ ጉዳይ ላይ 1ኛ). አጋርነትን በማሳየት፣ 2ኛ). ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ እና 3ኛ). መረጃን በፍጥነት ለመላው ዓለም በማሰራጨት በጉዳዩ ላይ የሚፈለገው የተግባር ለውጥ እንዲመጣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በብዛት ከመቀመጫቸው ሳይነሱ የሚፈፅሙት የአራማጅነት ዓይነት ነው።

፫ - ሀሽቲቪዝም የት ያደርሳል?

ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ቶሎ ተስፋ ይቆርጣሉ። የሚታያቸው ስድድቦችና ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ውኃ የማይቋጥሩ ሙግቶች ብቻ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ የሰነፎች እና ከመተቸት በቀር ምንም መሥራት የማይችሉ ሰዎች መደበሪያ እንደሆነ ይናገራሉ። ሸምሱ ቢረዳ በሚል የብዕር ሥሙ የሚጦምረው እና በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች ዘንድ በስፋት የሚታወቀው ሽሙጥ ዐዋቂ፣ መጋቢት 2006 በጻፈው ጦማሩ ላይ ‹ኢትዮጵያዊ የትዊተር አራማጅ መሆን ምንም ሳያደርጉ ዕውቅና ለማፍራት መሞከሪያ መንገድ› እንደሆነ ተከራክሯል። ሸምሱ በጦማሩ፣ ‹ውሱን በሆነው የበይነመረብ (internet) ግንኙነት እና ተዳራሽነት የትዊተር አድራሻ ፈጥረው ከዕውቅ ተጠቃሚዎች ጋር ውይይት በመግጠም፣ የታሰሩ ሰዎችን ፎቶ በመለጠፍና ይፈቱ እያሉ በማለት ብቻ ራሳቸውን ለመጠነኛ ዕውቅና ከማብቃት በላይ› በአገራችን ፋይዳም ሥራም እንደማይጠይቅ ተናግሯል።

እንዲህ ዓይነት አስተያየቶች በእኛ አገር ብቻ የተወሰነ አይመስልም። ባለፈው ዓመት ጆን ዋሊቦንጎ የተባለ የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጠኛ ሀሽቲቪዝም መሬት የማይወርድ እንደሆነ በተከራከረበት ጽሑፉ አንድ ምሳሌ አንስቷል። ፒተር ኬኔት በባለፈው የኬንያ የፕሬዚደንት ምርጫ ላይ ተወዳድሮ የተሸነፈ ፖለቲከኛ ነው። ነገር ግን እንደፌስቡክ እና ትዊተር ቢሆን ኖሮ ከሁሉም ተወዳዳሪዎች የበለጠ ወዳጅ እና ተከታይ የነበረው እሱ ነበር። 

አዳዲስ ጥናቶች ግን በተቃራኒው ሀሽቲቪዝም ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ያመላክታሉ። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታዩት ተስፋ አስቆራጭ ግለሰቦች ላይ ያተኮረ መሰዳደብ የሚበዛውም ይሁን አራማጆች የዚያ ልምድ ሰለባ የሚሆኑት ማኅበራዊ ሚዲያን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ባለማወቃቸው እንደሆነ ነው ጥናቶቹ የሚጠቁሙት። #ThisIsACoup (ይሄማ መፈንቅለ መንግሥት ነው) በሚል፣ የግሪክን ከአውሮጳ ኅብረት የመባረር አጀንዳ የተቃወሙት ሀሽቲቪስቶች፣ እንደዋዛ ባርሴሎና ላይ የጀመሯት አንድ ትዊት ተቀጣጥላ ዓለምን ማዳረሷን ተከትሎ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ሀሽታጉ በአንድ ሐምሌ ወር ብቻ 600 ሺሕ ትዊት (መልዕክቶች) ያስተናገደ ሲሆን፣ 140 ሺሕ ሰዎችም ሀሽታጉን ተጠቅመው መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል። ሀሽታጉ በዚህ መንገድ የበርካታ ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች እና ሚዲያዎችን መሳብ በመቻሉ ጉዳዩ በቀላሉ የሚታለፍ እንዳይሆን በማድረግ ዲፕሎማሲውን ቀይሮታል።

በሚያዝያ ወር 2006 ሰሜን ናይጄሪያ ውስጥ በቦኮሀራም 276 ያህል ልጃገረዶች ተጠልፈው መወሰዳቸውን ተከትሎ #BringBackOurGirls (ሴቶቻችንን መልሳችሁ አምጡ) ሀሽቲቪዝም እየተካሄደ ነው። ሀሽቲቪዝሙ ይህንን ጽሑፍ እየያዙ ፎቶ ተነስቶ ከያሉበት ትዊተር ወይም ፌስቡክ ላይ መለጠፍን ይጨምር ስለነበር የአሜሪካ ቀዳማይ እመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ የዓለማችን በርካታ ዕውቅ ሰዎች ተሳትፈውበታል። በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ሀሽታጉን የተጠቀሙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ትዊቶች በዓለም ዙሪያ ተላልፈዋል። ቦኮሀራም፣ እጅግ ብዙ ሰዎችን በናይጄሪያ እየገደለ እና ብዙ ጥፋት እያደረሰ የነበረ ቢሆንም የናይጄሪያ የብቻዋ የቤት ሥራ የሆነ ያህል በመላው ዓለም ችላ ተብሎ ነበር። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከ2 ሺሕ በላይ ልጃገረዶች በቦኮሀራም እንደተጠለፉ ሪፖርት ያወጣው ከዚያ በኋላ ነው። አሁን የዚህ ሀሽቲቪዝም ውጤት መላው ዓለም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ማድረጉ ነው። ምንም እንኳን ልጃገረዶቹ እስካሁን ባይለቀቁም መላው ዓለም ለናይጄሪያውያኑ እና ለተጠላፊዎቹ ወዳጅ ቤተሰቦች ዘላቂ አጋርነታቸውን ማሳየታቸው በራሱ ተስፋ ቀጣይ መሆኑን ዘጋርዲያን ዘግቧል

#OromoProtests የነጻ ሚዲያ እጥረት ባለባት ኢትዮጵያ ከኅዳር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን የአደባባይ ተቃውሞ ጠቅላላ ሁኔታ እና የደረሰውን የጉዳት መጠን ማወቅ ያስቻለ ሀሽታግ ነው። ብዙ ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ሁኔታውን ሲዘግቡ ማኅበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ የነጻ ሚዲያ እጥረት የወለደውን ክፍተት እየሞላ እንደሆነ አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ተቃውሞውን አለባብሶ ሊያልፈው እንዳይችል ያደረገው፤ በመንግሥት የተገደሉትን ተቃዋሚዎች ማንነት እና ቁጥር እንዲሁም ተቃውሞ የተካሄደባቸውን አካባቢዎች ዝርዝር በሙሉ በርካታ የውጭ ሚዲያዎች እና የአገር ውስጥ ጦማሪያን መዘገብ የቻሉት ይህንን ሀሽታግ በመከተል ነው። ተቃውሞው መሪ እንደሌለው በተደጋጋሚ ተነግሯል፤ መሪ አለው ከተባለ ይህ ሀሽታግ ይሆናል። ሁሉንም ዓይነት ተቃውሞውን የሚመለከቱ መረጃዎች በሙሉ በዚሁ ሀሽታግ አማካይነት ተላልፈዋል። ነጻ ሚዲያ በሚታፈንበት አገር የሀሽቲቪዝም ጥቅም ወደር የለሽ መሆኑ በዚሁ አጋጣሚ ታይቷል።

#FreeZone9Bloggers: Global Digital Activism and the Local Politics in Ethiopia በሚል ርዕስ በሦስት ትልልቅ የአካዳሚ ተቋማት የተሠራ ጥናት #FreeZone9Bloggers በሚለው ሀሽታግ የተካሄደው የትዊተር ዘመቻ (ሀሽቲቪዝም) ‹የተለያዩ የዓለም ክፍል ማኅበረሰቦችን በአንድ አሰባስቧቸዋል› ይላል። ይህም ኢትዮጵያን የሚደግፉ መንግሥታት ተጽዕኖ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ጥናቱ ያትታል። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች ነገሩን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለማስተባበል መገደዳቸው የሀሽቲቪዝሙ ውጤት እንደሆነ ጥናቱ ያመላክታል፤ የወቅቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ሚኒስትር “የዓለም ዐቀፍ ተቋማቱ ጩኸት ጦማሪዎቹን አያስፈታቸውም” ብለው ማለታቸው የተፅዕኖው ማሳያ እንደነበር ነው ጥናቱ የሚጠቁመው።

እንዳለመታደል ሆኖ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የመንግሥት ኃላፊዎች የማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ አይደሉም። አልፎ ተርፎም የበይነመረብ ተዳራሽነቱ 100 ሚሊዮን ዜጎች ባሏት አገር ውስጥ 3 ሚሊዮን አይሞላም። ነገር ግን የኢትዮጵያን መንግሥት የሚደግፉት አገሮች እና መግቢያችን ላይ የጠቀስናቸው የአውሮጳ ኅብረት ፖለቲከኞች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በአግባቡ ይጠቀማሉ። በኢትዮጵያ የሚደረገው ሀሽቲቪዝምም አጋርነትን ከማሳያነት፣ ግንዛቤ ከማስጨበጫነት እና መረጃ በፍጥነት ማሰራጫነት በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊ የሆኑ አገራት ፖለቲከኞችን በቀጥታ በማግኘት በውስጣዊው ፖለቲካ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ተፅዕኖ ማድረግ ይችላል።

***
ይህ ጽሑፍ ዛሬ ጥር 7/2008 በተሰራጨው የአዲስ ገጽ መጽሔት ላይ የታተመ ነው።