በዚህ በምህንድስናው የትምህርት ዘርፍ ልብን የሚሰቅዝ ህሊናን የሚቆጣጠር ርዕስ ብዙውን ጊዜ አይኖርም፡፡በተለይ እንደኔ መሐል አዲስ አበባ በሚገኙ የድሆች መንደር ተወልዶ ያደገ ሰው ለራሱም ሆነ ለማኀበረሰቡ ችግሮች ከግል ጥረት እና ላቂያ በላይ መወቅራዊ መስተካከል እንደሚያሰፈልግ ሰለሚያምን ካልገባው ወይም ካልተሸወደ በስተቀር በሁለንተናው አይተጋም፡፡ምህንድስና ደግሞ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም “ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ስር እናውላለን፡፡” ካሉት በተቃርኖ ተፈጥሮን ባለበት አኳኃን ከሳይንሳዊ ጥናቶች በመረዳት ለሰው ልጆች ጥቅም የሚውልበትን መንገድ ማፈላለግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ በስሎ የሚበላ ፣ ለብዙዎች ችጋር የወዲያው መፍትሔ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የሚያጠግብ ቢኖር እንኳ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የሚፈታ ሰው ሰው የሚሸት መፍትሔ አይሰጥም፡፡ብዙዎች ስሙን ከሩቅ ቢያከብሩትም ቆዳቸው ሳሳ ያለ ሰዎችን አይመስጥም፡፡አንዳንዴ ግን አልፎ አልፎ ልብን ላፍታ የሚያሸፍት ነገር አይጠፋም፡፡ዛሬ በምኞት መልክ እንድንጫወትበት ያሰብኩት ርዕስም ከነዚህ የአንድ ሰሞን የዐሳብ ግልቢያዎች በረከት የተገኘ ነው፡፡
የአንድን ማሽነሪ ንደፍ የሚሰራ ሰው ከሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ውስጥ አንዱ IDIOT PROOF ይሰኛል፡፡ይህም ማሽኑን የሚያመርተውን ፣ የሚገጥመውን፣ የሚያንቀሳቅሰው እና የሚጠግነውን ሰው ክህሎት እና ንቃት በመጠርጠር የሚጀምር ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰውየው አስፈላጊው ዕውቀት ቢኖረው ፣ ተገቢውን ስልጠና ቢያገኝ እንኳ ይሳሳታል ተብሎ ይታመናል፡፡ይህም ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም እንደሚለው ሀገርኛ ቢሒል ያለ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት እንዲህ ያለ ስህተት ይከሰታል ፤ እንዲህ አድርጎ ገልብጦ ይገጥመዋል ፤ የቀኙን ወደግራ የግራውን ወደቀኝ ይቀያይረዋል ብሎ በመገመት ስህተት ፣ ሰህተቱን በመመንጠር የስራውን ክንውን ህጸጽ አልባ ማደረግ ነው ፡፡በኢቪየሽን እና ወታደራዊ ማሽኖች ላይ ስህተት ቢፈጠር ጉዳቱም የከፋ ስለሚሆን ይህ ደናቁርትን የማጥለል ጥበብ በብዛት ይስተዋላል፡፡ ማረፊያ ጎማው (landing gear) ተገልብጦ በተገጠመለት አውሮፕላን ቢሳፈሩ ምን እንደሚፈጠር አስቡት? አያድርስ! ነው ብለው ፈጣሪዎን ይጠሩታል ወይስ ለአእዋፍ እንኳ ያልተፈቀደውን ዘላለማዊ በረራን ይመኙለታል? ጉድና ጅራት ከወደኋላ መሆኑን የተረዱት ፈረንጆቹ ግን በአጋጣሚ ይህን ማረፊያ ጎማ የሚገጥም ሰው ከደናቁርት ወገን ሊሆን ስለሚችል ተስሳቶ እንኳን ገልብጦ እንዳይገጠመው አድርገው ከወዲሁ ያበጁታል፡፡ ጃፓኖች ይህንን ጥበብ ፖካ ዮኬ ይሉታል፡፡ትርጓሜውም መወድቂያህን አሳምር ወይም በጥንቃቄ ውደቅ (fail-safing) እንደማለት ነው፡፡ለነገሩ የምህንድስናውን አነሳው እንጅ በሌሎች የትምህርት ዘርፎችም ይህ ስልት እንደሚተገበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡እስኪ ቅጥ አምባሩ ለጠፋው ቦለቲካችን ለምን አንሞክረውም?
የኢትዮጵያን ያለፉ 40 ዓመታት የቦለቲካ ጨዋታ ላስተዋለ ሰው ብዙ የዕውር ድንብር ታሪኮች ያጋጥሙታል፡፡በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ አለማችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንደገባች ታሪክ ያስረዳናል፡፡በመሆኑም የገበሬዎች አመጽ ወይም የተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ እንደመነሻ ምክንያት ያገልግሉ እንጂ አብዮት የማይቀር ነበር፡፡ ነገር ግን አብዮቱ ሲጀመር በመሀል መኀይማን እንደሚያኮላሹት የተረዳ እና በሩን ለመዝጋት ሙከራ ያደረገ አልነበረም፡፡ካረጀው እና ካፈጀው ዘውዳዊ ስርዓት መላቀቅ ነበረባት፡፡ ነገር ግን ከዘውዳዊው ስርዓት መኳንንት እና መሳፍንት የባሱ ደናቁርት በወንበሩ ሊቀመጡ እንደሚችሉ መገንዘብ የተገባ ነበር፡፡በኃላም ማርክሲዝም አለምን ሲያጥለቀልቅ የኢትዮጵያን በር እንደሚያንኳኳ መረዳት ነብይ መሆንን አይጠየቅም፡፡ነገር ግን በወቅቱ ከነበረው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከነበሩብን ችግሮች እና መልካም ሁኔታዎች አንጻር ሳይቃኝ እንደወረደ በመተግበሩ የአንድ ትውልድ ወጣት እንዳይሆን እንዳይሆን ሆኖ አልፏል፡፡ ነፍጥ ያነገቡ ሰዎች ከወደ ደደቢት ተነስታው በቃህ እስኪሉትም የቻለውን ያህል ጥፋት እንዳደረሰ በመንገር እንደ ኢተቪ አላደክማችኹም፡፡
በ1983 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እናቶች ጸዓዳ ቀሚሳቸውን ገጭ አድርገው ፣ፈንድሻቸውን አፍክተው አስፋልት ላይ እየበተኑ የኢትየጵያ ትንሳኤ እበራፍ ላይ የቆመ መሆኑን ሲያበስሩ ነበር፡፡ብዙም ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣው ማለት የጀመሩት ግን ልማዳዊው (sentimental) የሀገር ፍቅር የሌላቸው በብሔር ቦለቲካ የተለከፉ ደናቁርት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ኢትዮጵያን ሲያራክሱ ነበር፡፡አንዳንዶች አሁን ሀገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ ከቀድሞ ጋር በማነጻጸር የተሻለ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ይናራሉ፡፡ከድንቁርና እና ደናቁርትን ማጥሊያ(Idiot proofing institutions ) ተቋማት አንጻር ስንገመግመው አላዋቂነት ለብቻው ተቀምጦ እናያለን፡፡ለአብነት ያህል የሀገሪቱን ፓርላማ ፣ምርጫ ቦርድ ፣ የፍትሕ አካላት ፣ የሀይማኖት ተቋማት ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፣ የሚዲያ ተቋማት መዘርዘር ይቻላል፡፡በቅርቡ በአንድ የህግ ባለሙያ ወዳጄ ጉትጎታ የእነ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ ወደሚታይበት ወደ ልደታ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጎራ ብዬ ነበር፡፡በኔ ባልተማረ ሰው ምልከታ ‘በህግ አምላክ ሲሉት ውሃ እንኳን ይቆማል’ የሚባልበት ሀገር ውስጥ ያለ ፍትሕ ተቋም አይመስልም፡፡ድኀረ መለስ ኢትዮጵያ ከሚጠብቃት ትልልቅ የቤት ስራዎች ውስጥ አንዱ በህግ ፍትሕ ርትዕን አገኛለው የሚልን መተማመን በማኀበረሰቡ ወስጥ ዳግም ማስረጽ ነው፡፡
የዛሬ ስልሳ አመት ገደማ በሀገረ አሜሪካ ‘ጥቁር ሰው ነው’ ፣ ‘ሴት ከወንድ እኩል ነች’ ብለው ለመቀበል የሚቸገሩ ሰዎች ቁጥራቸው የትየለሌ ነበር፡፡ ችግራቸውን እያስወገዱ ድንቁርናን እየከሉ ስለመጡ ዛሬ ሰማየ ሰማያት ደርሰው በጥቁር ፕሬዚዳንት ለመመራት በቁ፡፡እኛ ግን ምንአልባት በአጸደ ስጋ ቢገኙ እንኳን ከሌላው ኡትዮጵያዊ የከፋ ጉዳት ደርሰብን የማይሉ ወገኖቻችንን እየጠቀስን የልዩነትን ግንብ እንገነባለን ፤ የጥላቻን ጉድጓድ እንቆፍራለን ፤ ልዩነትን እንሰብካለን፡፡
ከዘመኑ የቅኝት ስልት ጋር ራስን እያስታከኩ መንጎድ ቀላል ነው ፡፡ተገደን የምንገባበትም ነው፡፡ማርከሲስት መጣ ተቀበልነው ፡፡ማርክሲስት ወደቀ ተውነው፡፡ምዕራባውንን ስንከተል ነበር አሁን ደግሞ ወደቻይና አዘንብለን ያለምንም ማስተዋል እየከነፍን ነው፡፡ዋሽንግተንም ቤጅንግም መሄድ እጅግ ቀላል ነው፡፡ መለስ ዜናዊም ጥሩ ነገር በዚያ አልገጠማቸወም እንጂ በቅርቡ ዲሲ አይተናቸው ነበር፡፡በወንበሩ ተደላድለው መቀመጣቸው ያልየው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝም በታላቋ ቻይና ቴሌቪዥን ቀርበው የወዳጅ ሀገርን ለጋስነነት ሲያወድሱም ታዘበናል፡፡እንዲህ ቀላል ነው፡፡እኛን የቸገረን አዲስ ማዕበል በመጣ ቁጥር የጠነከረውን ጥፊ መቀበላችን ነው፡፡ እንደ የውሃ ላይ ኩበት እየተገላበጥን መሄዳችን ካለፈ ታሪካችን ተምረን መጻዒው ጊዜ ስህተት የለሽ ማድረግ አለመቻላችን ነው፡፡
ግብጾች እና ታህሪር እንዲህ ያለ ትስስር ያላቸው ይመስለኛል፡፡መኀይምነትና ደናቁርት ስጋ ለብሰው እንዳየሰለጥኑባቸው የሚያደርጉበት መድረክ፡፡አባቶቻቸው ፒራሚድ ሲገነቡ እነርሱ ደግሞ የሰህተትና ድንቁርና ማጥለያ አደባባይ ታህሪርን አበጅተዋል፡፡ በአንዋር ሳዳት እግር ስር የተተካውን ሙባረክን ከነድንቁርናው ያጠለሉት ታህሪርን ይዘው ነው፡፡ወታደራዊውን ፍርድ ቤትንም እንከባበር ያሉት እዚያው ነው፡፡ከሰው መሐል መርጠው ወደ መድረክ ያመጡት ሞሐመድ ሙርሲስ ቢሆን ከተሰመረለት መስመር ውልፍት ቢል ይለቁታል? እድሜ ከሰጠን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ እንዲህ ስላችኹ በቃ መስቀል አደባባይ እንገናኝ እንዳትሉኝ፡፡ ቀስ! … ቀስ! …ገና ብዙ የቤት ስራ አለብን ግብጻውያን እኮ ታንክ ተደግፈው ነው እምቢኝ ድንቁርና! ያሉት ፡፡ ይልቅስ እንደአሁኑ ወቅት ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ እንደማያጣፍጥ በተረዳን ጊዜ ነው ፖካ ዮኬ የሚሰፈልገን የኛ የነገዋ ኢትዮጵያ ወደኃላ የምትራመድ መሆን አይገባትም፡፡ ካለፈ ስህተቷ ተምራ ማንም ደንቆሮ የማይጠመዝዛት ወደፊት የምትጓዝ… "Anything that can go wrong, will go wrong" ህልም እና ምኞታችንን ማን ይከለክለናል፡፡
ደንቆሮ የማይጠመዝዛት...you are the ignorant who think you know a lot. shame on you!
ReplyDeleteaye anonymous, the fact that you pick on the last word tells me that you didn't read the whole article or you don't get the metaphor. kmtechet manbeb yidkem!
DeleteThank you Abel!! you make me to think the issue for over a week and now I come back to say thank you
ReplyDeleteNice post.
ReplyDeletedevops training
nice post.
ReplyDeleteibm message broker training