በክፍል አንድ ጽሑፌ ከአንደኛ
ደረጃ ትምህርት ጋር በተያያዘ ለትምህርት ጥራት ችግር መንስኤ ይሆናሉ ያልኳቸውን መዳሰሴ ይታወሳል፡፡ ያኔ ቃል በገባሁት መሠረት
ሁለተኛው ክፍል በሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ጥራቱን የሚገዳደሩትን ችግሮች በወፍ በረር አስቃኛችኋለሁ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለትምህርት
መስክ እየሰጠ ያለውን ትኩረት ማሳያ የሚሆነው ሌላው መረጃ መስኩ በየዓመቱ ከአጠቃላይ የመንግስት በጀት የሚወስደው ድርሻ እያደገ
መምጣት ነው፡፡ እ.አ.አ በ2003 ዓ.ም 14.5 በመቶ የነበረው ድርሻ በ2010 ዓ.ም 18.8 በመቶ መድረስ ችሏል፡፡ ከመንግስት
በጀት ላይ የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ ከትምህርት ጋር እየተገዳደረ የሚገኘው የጤና ዘርፍ ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለትምህርት ዘርፍ
ከሚውለው በጀት 23.1 በመቶ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚውል ነው፡፡
የዘመናችን ትምህርት ትልቁ ችግር
ዓይኑን አፍጥጦ መታየት የሚጀምረው በሁለተኛ ደረጃና እና በተለይም ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ነው፡፡ በነዚህ የትምህርት
ደረጃዎች ችግሮች በቀጥታ ከትምህርት ጋር የተያያዙ መሆናቸው እየቀረ ፖለቲካዊ ይዘት እየተጎናፀፉ ይመጣሉ፡፡ የኢሕአዴግ የካድሬ
እንቁላል መጣል እና የረጅም ጊዜ አሕዳዊ አገዛዝ ፍላጎት የራስ መከላከል ሥራዎች በይፋ ይጀመራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ባሉት 32 የመንግስት
ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ተማሪዎች በነጻነት እንዲያስቡ አይፈለግም፤ አይፈቀድም፡፡ እንኳን ተማሪዎቹ ይቅርና መምህራኑ ጭምር በነጻነት
የሚያስተምሩትን ለመምረጥ አይደፍሩም፡፡ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ለተማሪዎቻቸው የሚያስተላልፉትን ዕውቀት ሀገሪቷ ላይ ካለ ነባራዊ ሁኔታ
አንጻር ተንትኖ ለማስረዳት የሚደፍሩት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ክፍል ውስጥ የተናገሩት ነገር ገዥው ፓርቲን የሚነቅፍ (የማይደግፍ)
ከሆነ የእንጀራ ገመዳቸው ላይ እየተራመዱ ያሉ የሚመስላቸው መምህራን አሉ፡፡ ከክፍል ውጪም በተቋማቱ አመራሮች ለሚፈፀሙ የአሰራር
ስህተቶች እና በደሎች (ለምሳሌ በዘር እየተመራረጡ መሿሿምን የመሰለ) ለመተቸት እምብዛም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ በዚህም ድርጊታቸው
ለተማሪዎቻቸው ‹‹ቀጥ ለጥ ብሎ›› የመገዛት ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ፡፡
ተማሪዎች ‹‹የውጤታማነት››
መንገድ አቅጣጫ ይሰመርላቸዋል፡፡ ለትምህርታቸው የሚሰጡት ትኩረት እና ውጤታቸው እምብዛም ቢሆንም የወጣቶች ሊግ እና ማንኛውንም
የመሪው ፓርቲ ተደራሽነት የሚያሳድጉ/የሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን መሞገስን፣ በጓደኞቻቸው ላይ የበላይነትን እንዲያገኙ
የሚያደርግ ተሰሚነት (በትምህርት ቤት ኃላፊዎች) እና ከበድ ሲልም የንግድ እና የፖለቲካ ሥራ እንዲያገኙ ይመቻችላቸዋል፡፡ ይህ
ስርዓት ለተማሪዎች የሚያስተላልፈው መልዕክት ግልፅ ነው፡፡ በትምህርት ተግቶ ዕውቀት ሸምቶ ሀገሪቷን ለመጥቀም ከመታተር ይልቅ ርካሽ
የፖለቲካ ተወዳጅነት ማግኘት የስኬት መንገድ አቋራጭ ሆኖ ይቀርብላቸዋል፡፡ የመጀመርያውን ምርጫ ለመምረጥ በቂ ማነቃቂያ ስለሌለ
ለትምህርት ትኩረት መስጠት ያለውን ጥቅም ተረድተው ይሻለኛል ብለው የሕይወት መስመራቸውን የሚያስተካክሉት ተማሪዎች ቁጥር ጥቂት
ነው፡፡
ትንሽ ለየት ያለ እክል የሚስተዋለው
(ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ) የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ላይ ነው፡፡ ቅርብ ሊባሉ በሚችሉ የጌዜ ልዩነቶች ተደጋጋሚ የሥልጠና
ካሪኩለም እና ምዘና ዘዴ ለውጦች ተደርጎበታል - የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት መስክ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ይህ የትምህርት
መስክ የትኩረት እጥረት ይስተዋልበት ነበር፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት
ተመርቀው ለሚወጡት ወጣቶች ሥራ አግኝቶ እራስን መቻል ቀላል ፈተና አይደለም፡፡ በከተሞች አካባቢ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ሥራ መሥራት
ከሚችሉት ሰዎች 19 በመቶዎቹ የሥራ-አጥ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ደግሞ እ.አ.አ በ2010ዓ.ም 71,872 ተመራቂዎችን ከግቢዎቻቸው
ሸኝተዋል፡፡
ያሉትን ሁሉ ችግሮች አልፈው
በቂ ዕውቀት ይዘው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጡትን ተማሪዎች ፍሬ ለመቅመስም ተጨማሪ ፈተና አለባት - ሀገራችን፡፡ ደረሱልኝ፣
ውለታዬን መለሱ ብላ ጓግታ ስትጠብቃቸው፤ ሥራ በጀመሩ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወይንም እንደተመረቁ ወዲያውኑ ልጆቿን በስደት ትቀማለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ኢትዮጵያ አሰልጥናቸው ችካጎ ውስጥ የሚኖሩ ሐኪም ኢትዮጵያውያን ቁጥር በመላው ሀገሪቷ ካሉ
ሐኪሞች ቁጥር ይበልጥ ነበር፡፡
መፍትሄውስ?
ዩኒቨርስቲዎቻችን በሁሉም መስኮች
የመጠቀ ዕውቀት ይዘው የሚወጡ ተማሪዎች እንዲያመርቱ መጠበቅ ቀና አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ተመርቀው በተማሩበት የሥራ መስክ
እንዲሰማሩ ዕድሉን የሚያገኙት ወጣቶች ጥቂት መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዩኒቨርስቲዎቻችን የሚወጡት ወጣቶች በየተማሩበት
መስክ መሠረታዊ የሆነ ዕውቀት የያዙ ነገር ግን በማንኛውም ዓይነት ሥራ ለመሰማራት ዝግጁ ሆነው እንዲወጡ ነው መጠበቅ ያለብን
- ከገሀዱ አንፃር፡፡ ሀገራችን አሁን ያለችበት የልማት ደረጃ የሚፈልገውም ይህንኑ ነው፡፡ ከዩኒቨርስቲዎቻችን የሚወጡት ወጣቶችን
ምጡቅ ዕውቀት እንዲይዙ አስበን ለትምህርት የሚወጣውን መዋዕለ ነዋይ በሙሉ ጥራት ላይ ያተኩር የምንልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም
- ግን በእርግጠኛነት እንደርሳለን፡፡ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የትምህርት ሚኒስትር የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን የሀገሪቱን
ትምህርት ፖሊሲ በመጥቀስ ይህንን ሐሳብ ያስረዳሉ - ‹‹… ወጣቶች
በብቃት ሠልጥነው እና በቅተው በግልም ይሁን በመንግስት በየትኛውም ዘርፍ ተወዳዳሪ እና ስኬታማ የሚሆኑበትን ዕድል መፍጠር ነው
- የትምህርትና ሥልጠናው ዓላማ፡፡ ስለዚህ ለተፈለገው ሥራ ብቁ መሆንንና ማድረግን (Fit for the purpose) ማዕከል ያደርጋል
ማለት ነው፡፡››
የአዲስ አበባን ዩኒቨርሲቲ በፕሬዚዳንትነት
ለ7 ዓመታት የመሩት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎችን
በመገንባት እና የተመራቂዎችን ቁጥር በማብዛት ላይ ብቻ ተጠምዶ የጥራትን ጉዳይ ችላ ብሏል›› ብለው መንግሥትን ለሚተቹ እንዲህ
ሲሉ ይሞግታሉ፤ ‹‹የትምህርት መስፋፋት እና የትምህርት ጥራት ተሻሚ
ነገሮች እንደሆኑ ማንም ያውቃል ይህን፡፡ አንዱ ሲሳካ ሌላው ሊጓተት እንደሚችል፣ ሊዳከም እንደሚችል ሁሉም ያውቃል፡፡ ያም ሆኖ
ግን … አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንግዲህ ከ50 ዓመት በላይ ነበር፡፡ … የትምህርት ጥራቱ እንዲህ የሚደነቅ እና የሚሞገስ ነው
ለማለት አይቻልም፡፡ … ስለዚህ ጥራት እና መስፋፋት ኩታ ገጠም ሆኖ ይሂዱ ከተባለ ስንት ዓመት ሊፈጅብን ነው ማለት ነው የትምህርት
ተቋማትን ለማስፋፋት?›› በ1997 የትምህርት ዘመን ስምንት የነበረው የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር አሁን ላይ ወደ ሠላሳ
ሁለት ከፍ ብሏል (በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት የግል
እና የመንግስት ተቋማት ቁጥር 148 ይደርሳል)፡፡ እነዚህ 32 ዩኒቨርሲቲዎች በየዓመቱ 420,387 የመጀመሪያ ዲግሪ እና
14,272 የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም አላቸው፡፡ እ.አ.አ በ2010 የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የመከታተያ ዕድሜ ላይ
(20-24) የደረሱት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከ8.7 ሚሊዮን በላይ ነበር፡፡ የታዳጊዎች ቁጥር መብዛት በራሱ እና የሕዝብ ብዛት ላይ
በሚያሳድረው ግፊት (Demographic Inertia) የተነሳ ዩኒቨርስቲዎችን ማስፋፋት እና በአጠቃላይም ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች
ማዳረስ የማያቋርጥ ጥረት ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን የነበረው ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው
ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት እና ቁጥራቸውን ማብዛት የተሰጠውን ትኩረት
ተቋማቱን ለማጠናከር እና ተማሪዎች ማግኘት የሚገባቸውን ዕውቀት መስጠት ማስቻል ላይ ለሚሰራው ሥራ ማካፈል መጀመር አለበት፡፡
በትምህርት መስክ የግሉ ክፍለ
ኢኮኖሚ ተሳትፎን ማበረታታት እንደ አማራጭ መፍትሄ መታየት ይኖርበታል፡፡ መንግስት ያለበትን የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን
ኩታ ገጠም አድርጎ ለመሄድ ያለበትን የአቅም ችግር ከግሉ ዘርፍ በሚመጣ የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰት መሙላት ይቻላል፡፡ ለዚህም መንግሥት
ወጥ በሆኑና የግሉ ዘርፍ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችለው ሁኔታ የሚያመቻቹ ደንቦችን ማበጀት እና ከዘርፉ ጋርም የጎሪጥ መተያየቱን
ትቶ ተቀራርቦ መሥራት አለበት፡፡ ይህንንም በማድረጉ መንግስት ሦስቱንም የትምህርት ደረጃዎች ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚያውለውን
ወጪ ቀስ በቀስ ወደ ተቋማትን በደንብ ማደራጀት (በመጻሕፍት፣ በቤተ-ሙከራ እና በመሳሰሉት) እና የመምህራንን ቁጥር (በተለይ በመጀመሪያ
ደረጃ) እና ብቃት ወደማሳደግ እንዲሁም የግል ተቋማትን ወደማገዝ እና ውጤታማ ቁጥጥር ወደማድረግ ለማዞር ዕድል ይሰጠዋል፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት
ተመርቀው የሚወጡት ወጣቶች ሥራ አጥ መሆናቸው ስለ ትምህርት ስርዓቱ ከሚናገረው ይልቅ ስለ አጠቃላይ የሀገሪቷ ምጣኔ-ሀብት የሚናገረው
ይልቃል፡፡ ሀገሪቷ ውስጥ ያሉት ባለትኩስ ኃይል ወጣቶች ከየትኛውም የዕድሜ ክልል በእጅጉ በሚበልጥበት ሀገር 85 በመቶ የሚሆነውን
የሥራ ኃይል መቅጠር የሚችለው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚው ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው ከሰለጠኑት
ልጆችዋ ማግኘት የሚገባትን ታገኝ ዘንድ የምጣኔ-ሀብት መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋታል፡፡
ለብዙ የዕድገታችን ማነቆ ለሆኑት
ችግሮቻችን እንደመፍትሄ የሚነሳው የባሕል አብዮት በትምህርትም መስክ ያስፈልገናል፡፡ ማኅበረሰባችን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጡት
ወጣቶች በተለምዶ ዝቅ ተደርገው የሚታሰቡ ነገር ግን ገቢ የሚያስገኙ እና ሀብት እንዲፈጠር አስተዋፅዎ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሲሠሩ
ሲያይ ከማንቋሸሽ ይልቅ ማድነቅ እና ማበረታታት ሊቀለው ይገባል፡፡ ትንንሽ ልጆችንም ሐሳባቸውን እና ጥያቄዎቻቸውን በጨዋነት እንዲያቀርቡ
ማስተማርና ማበረታታት ይገባል፡፡
ፖለቲካዊ መልክ ላላቸው የሀገራችን
ትምህርት ችግሮች ለመሪዎቻችን ቅን ልቦናን ከመመኘት ውጭ ምንም ማለት አልችልም፡፡
No comments:
Post a Comment