ልጆች የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች
ናቸው፡፡ የነገይትዋ ኢትዮጵያ ተተኪ ብላቴናዎች ከአበባነት ወደ ፍሬነት
እንዴት ይቀየራሉ? ምን ዓይነት ፍሬዎች እንድናገኝ እየተሰራ ነው? የሚለውን ጥያቄ በዚህ ጽሑፍ ወፍ በረር ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
እንዴት ይቀየራሉ? ምን ዓይነት ፍሬዎች እንድናገኝ እየተሰራ ነው? የሚለውን ጥያቄ በዚህ ጽሑፍ ወፍ በረር ለመዳሰስ እሞክራለሁ።
ልጆችን ከአስተዳደጋቸው መሠረት አስይዞ አርሞ ማሳደግ ጥቅሙ ለቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ትሩፋቱ ለአገርና ለወገን የሚጠቅሙ የነገይትዋን ኢትዮጵያ የሚረከቡ ብቁ ትውልድ እንዲኖረን ያስችላል። ይህ ግን ዝም ብሎ አይመጣም ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰቡ እንዲሁም ልጆች ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ትምህርት ቤት ትልቁን ኃላፊነት ይወስዳሉ። ሰንሰለታማው የኃላፊነት ድርሻ አንድ ቦታ ላይ ከተስተጓጎለ ወይም ሰንሰለቱ ከተበጠሰ “አሜከላ ዜጋ” የማፍራታችን ዕድል ይጨምራል።
ሕፃናት ወረቀቶች ናቸው ንፁህ ሕሊናቸውን በመልካም ነገሮች እየተገነቡ እንዲያድጉ ከላይ የተጠቀሱት አካላት ምን ምን መደረግ አለባቸውብሎ መወያየት ለነገ የምንፈልገው አይነት ትውልድ ምን አይነት ይሁን የሚለውን ለማወቅ ይረዳናል፡፡
፩፡ቤተሰብ
በቤተሰብ ውስጥ ስለልጆች ያለው አመለካከት
ላይ ለውጥ ቢኖርም አሁንም በቤተሰብ ደረጃ ብዙ ችግሮች አሉብን። ለአብነት ያህል
ብናነሳ ልጆችን የማበረታታት ባህላችንንም ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ እሰየው፣ ጎበዝ፣ በርታ፣ በጣም ተለውጠሃል ወዘተ... የሚሉ ሞራል
የሚገነቡ ማበረታቻዎችን ቢኖሩንም እነዚህን ማበረታቻዎች በተከታታይ ለሕፃናት ማሰማት በራሳቸው የሚተማመኑ ልጆችን ለመፍጠር አዎንታዊ አስተዋፆ አለው።
በአንፃሩ
·
ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም
·
ልጅና ጫማ አልጋ ስር
·
ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ ወዘተ...
ከላይ የተጠቀሱ ሞራል ገዳይ አባባሎችን በማዝነብ ብላቴናዎችን ማሸማቀቅ ልንተወው የሚገባን ማኅበራዊ እንከኖቻችን ናቸው። ወላጆች ልጆቻቸው ፊት ለፊት መጨቃጨቅ፣ መደባደብና መዘላለፍ የልጆችን ሕሊና ክፉኛ
ከመጉዳቱም በላይ ቤት ውስጥ ሰላም ከሌለ ሕፃናት በጭንቀት ውስጣቸው ክፉኛ ስለሚጎዳ ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል ይሳናቸዋል።
ወላጆች አቅማቸው በፈቀደ መጠን የልጆቻቸውን ስሜት ማጥናት አለባቸው፡፡ወደ ቀለም ትምህርታቸውም ሆነ በልዩ ተስእጦአቸው አሊያም በሙያ ምርጫቸው በየትኛው መስክ ዝንባሌ እንዳላቸው በፅሞና መከታተል ያሻል ፡፡ ስሜታቸውን በመጫን ወላጆች የሚመኙትን ወይም ሞክረው ያቃታቸውን ነገር በልጆቻቸው ላይ ለማየት መሞከርና ካለፍላጎታቸውና ዝንባሌዎቻቸው ማሳተፍ ደስተኛ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋልና ወላጆች ጥንቃቄ ሊወስዱ ይገባቸዋል።
በተጨማሪም ከትምህርት ውጪ ያሉትን ሰዓታት ልጆችን ቤት ውስጥ ብቻ እንዲታጎሩ በማድረግ፣ በፊልምና የግዴታ ሥራ ማጥመድ ልጆች ልጅነታቸውን በአግባቡ ተጫውተው እንዳያልፉ ያደርጋቸዋል። በዕቅድ ይመሩ ዘንድ ወላጆች የጫወታና የጥናት ጊዜያቸውን በመመደብ የጊዜ ክቡርነትን በልጅነታቸው በማስተማር የጊዜ አጠቃቀምና ኢትዮጵያዊነት(ቀጠሮ ላይ ያለንን
አገራዊ ደካማነት) የሚታረቁበትን መሠረት መጀመር አለብን።
ወላጆች በአቅማቸው መጠን በምጣኔ መውለዳቸው አስፈላጊውን አሟልተው የሚያስድጓቸው ልጆች እንዲኖሩዋቸው ያደርጋል።ልጆችን በባዶ ሆዳቸው ትምህርት ቤት መላክ ወንጀል ነው። ባዶ ሆድ ጆሮ የለውምና! አዋዋላቸውን መከታተልና ባልጀሮቻቸውን ማወቅም ለተሻለ አስተዳግ ግድ ይላል ፤ ይህም ልጆች በጓደኞቻቸው ተፅዕኖ የሚበላሹበትን አጋጣሚዎች ይቀንሰዋል። በተጨማሪም ልጆች በሰውነት ማጎልመሻ በሚወዱት ዝንባሌያቸው ይሳተፉ ዘንድ ማበረታታት
ጤናማ ብላቴናዎችን ለማግኘት ያግዛል።
ልጆችን አጉል ቅጣት በመቅጣት አካላዊና ሞራላዊ ተፅዕኖ መፍጠር፣ አባትን ወይም እናትን በተናጠል እንዲፈሩ ማድረግ ተሸማቃቂ ስለሚያደርጋቸው ጥፋትን መደበቅን፣ መሰሪነትንና ፍርሃትን ይማራሉና ሊሰመሩባቸው ይገባል።
፪፡ማኅበረሰቡ
ከወላጆች በመቀጠል ቤተዘመድ፣ ጎረቤት፣ የወላጆች የሥራ ባልደረባዎች ልጆችን በመልካም ዓርያነት የመምራት ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል። ልጆችን የሚያሳድገው ማኅበረሰቡ ነው፤ ልጆች ከትምህርት ቤት ጥፋት ፈፅመው ሲመጡ ወላጆች እንዳያውቁባቸው በመፍራት ለጎረቤት ወይም ለወላጆቻቸው ጓደኞች፣ ቤተዘመድ አሊያም ለማያውቁት አልፎ
ሂያጅ ወላጅ ሆኖ ትምህርት ቤት እንዲሄድላቸው በመማፀንና ጥፋታቸውን ይሸሽጉላቸው ዘንድ ሲማፀኑ ልጆቹን መተባበር ከጥፋታቸው እንዳይማሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በአንፃሩም ሐሰትን ይማራሉና ማኅበረሰባችን ይህን የወንጀል ተባባሪነት ምንጭ
ማድረቅ አለብን። ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱትን እንስት ታዳጊዎችን ፆታዊ ትንኮሳ ማድረግና፣ ሲፈፀምባቸው እያዩ በምን አገባኝ በዝምታ ማለፍ ለትውልድ መምከን አሉታዊ ጎን አለውና ሁላችንም በሕግ የበላይነት የሚያምኑ ታዳጊዎችን ለማፍራት የሕፃናትን ጥቃቶች መከላከል አለብን።
፫፡ትምህርት ቤት
ትምህርት ቤት ትውልድ ለማነፅ ዋናውንና ወሳኙን ሚና ይጫወታሉ።
መምህራን ልጆችን በትምህርት ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ህይወታቸው
የተሻሉ ዜጋ ይሆኑ ዘንድ ክትትልና ማበረታቻ በመስጠት የታረሙ ይሆኑ ዘንድ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው። የልጆችን ሞራል የሚሰብሩ ንግ ግሮችን፣
አካላዊና ሞራላዊ ቅጣቶችን መቅጣት፣
በሕፃናት ፊት ፀያፍ ምግባራትን መፈፀም ለልጆች በዕኩይ ምግባር ማደግ ድርሻ አላቸው።
መምህራን የተማሪዎቻቸውን ወቅታዊ አቋም አካላዊና ሞራላዊ ብቃታቸውን መከታተል አለባቸው፣ልጆችን በመቅረብ ያለባቸውን ቤተሰባዊ ችግሮች መረዳትና መፍትሔ መስጠት አለባቸው። (በአገራችን በተጨናነቁ ክፍሎች ውስጥ የሚማሩትን ሁሉንም ልጆች መከታተል ለመምህራን አዳጋች መሆኑ ይሰመርበት)
፬፡መንግስት
መንግስት በታዳጊ ሕፃናት ላይ የሚደርሱትን አስፈላጊ ያልሆኑ የመብት
ጥሰቶች ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት ሕግ አስፈፃሚው አካላትን ልዩ ስልጠናና የአቅም ግንባታ በማድረግ ልጆች የተሻለ ዜጋ ይሆኑ ዘንድ
ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ፣ ከትምህርት ቤት የሚያስቀሩ ወላጆች፣ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርሱ ወንጀለኞች ላይ ሕጉን በማስፈፀም ላይ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት። በተጨማሪም የልጆች መዝናኛ ማዕከላትን፣መናፈሻዎች፣የሰውነት ማጎልመሻ አገልግሎት መስጫ ተቋማትንና የልጆች የጽሕፈት መሳሪያዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ከቀረጥ ነፃ ቢቻል
ካልሆነም ተመጣጣኝ ዋጋ ይኖራቸው ዘንድ ድጋፍ ማድረግ አለበት።
ካልሆነም ተመጣጣኝ ዋጋ ይኖራቸው ዘንድ ድጋፍ ማድረግ አለበት።
ሕፃናት በትምህርት ቤት ውስጥ የሕግ ከለላ ትምህርቶችን ማስተማርያ ስልቶችን ማሳወቅ መብትና ግዴታቸውን በለጋ ዕድሜያቸው ይረዱ ዘንድ ያስችላቸዋል። መንግስት ልጆች የመብት ጥሰት ሲገጥማቸው ከሕግ አካላት ጋር የሚገናኙበትን የቀጥታ መስመር የስልክ ቁጥር ያውቁ ዘንድ የማስተማርያ መጻሕፍቶችን ማሳተምና ማስተማር ግድ ይላል።
የመዋዕለ ህፃናት ደረጃዎችን መዳቢ የልጆች ጉዳይን የሚከታተል አካል ሊኖረን ይገባል። የታዳጊ አጥፊዎችን ማረሚያ ማዕከላት በመሥራት በወጉ ታርመው የተሻለ ዜጋ የሚሆኑበት ያሉትንም ብቃት ባላቸው ባለሙያና ቁሳቁስ ማጠናከር፣ ያልተሰራባቸው ክልሎች ላይ መስራት ያስፈልጋል።
ሁላችንም የምንመኛት የተሻለች ኢትዮጵያ የምትገነባው ኃላፊነት የሚሰማቸው በግብረገብ፣ በትምህርት የታነፁ ተተኪዎች ሲኖሩን
ነውና ሁላችንም ያሉብንን ግዴታዎች መወጣት ይጠበቅብናል። ያኔ ሕልማችን እውን ይሆናልና!
ቸር ያቆየን!
No comments:
Post a Comment