ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በመፈንቅለ መንግሥት ወረዱ፣ ደርግ በትጥቅ ትግል ወረደ፣ ኢሕአዴግ እስካሁን አልወረደም፤ እንደአያያዙም
ሆነ እንደአነጋገሩ በቅርቡ የሚወርድ አይመስልም፡፡ ኢሕአዴግም ቢሆን ግን መውረዱ አይቀርም ጥያቄው ‹‹አልወርድም›› የሚያስብለው
ምከንያት አለው ወይ እና ታዲያ እንዴት ይወርዳል የሚለው ነው፡፡ እዚህጋ ‹‹መውረዱ ለምን አስፈለገ?›› የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡
ነገር ግን በርካታ ሕዝባዊ ብሶቶች፣ እያሽቆለቆለ የመጣ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት አያያዝ እና ሌሎችም በተገኘው
አጋጣሚ ሁሉ ሲዘረዘሩ በመክረማቸው እና ማንም ለነዚህ እንግዳ ስለማይሆን ለጊዜው እሱን መዝለል ይኖርብኛል፡፡ አንድ ነገር አለ፤
ኢትዮጵያ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር (በተለይ የምርጫ) ማየት አለባት - ነገር ግን እስካሁን አላየችም፣ ስለዚህ ከአሁን በኋላስ
ታያለች ወይ ብለን መጠየቃችን የግድ ይሆናል፡፡
ኢሕአዴግ በ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ስርዓት እየተመራ፣ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እያካሄደ እንዴት ከሥልጣን አልወረደም ለሚለው
ጥያቄ ቅንጥብጣቢ የመልስ መዋጮ በማድረጉ ረገድ የተቃዋሚዎች ድክመት እና የሕዝቡ በፕሮፓጋንዳ መታጠብ ሊጠቀሱ ይችላሉ፤ ነገር ግን
በዋነኝነት የኢሕአዴግ ከሥልጣን ለመልቀቅ አለመፈለግ ቢጠቀስ ስህተት አይሆንም፤ ኢሕአዴግ ወይም አባላቱ ሥልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ
በቅርቡ ለማስረከብ ፈቃደኛ የሚሆን አይመስለኝም የምልባቸውን ማስረጃዎች ወደታች እዘረዝራቸዋለሁ፡፡
ኢሕአዴግ ብዙ ከሕገመንግሥቱ ጋር የሚፃረሩ በሚል የተወቀሱም፣ ባይፃረሩም ከስርዓት ማስከበር ይልቅ ቁጥጥርን ግብ
ያደረጉ አዋጆችን አፅድቋል፡፡ ባለሥልጣናቱ እስከ 40 ዓመት ኢሕአዴግ ሊቆይ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ምልክቶች ኢሕአዴግ
አገሪቱን በሥርዓት ለመምራት፣ ወይም መስመር አስይዞ ሥልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት ስላለው የሚያደርጋቸው እንደሆኑ ደጋፊዎቹ በእርግጠኝነት
ይናገራሉ፡፡ ኢሕአዴግ ጠንክረው የሚቃወሙትን ሁሉ አገር ለማፍረስ ዕቅድ እንዳላቸው በጥርጣሬ ይናገራል፤ እነዚህን ምክንያቶችም ሥልጣኑን
ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆንባቸው ቁም ነገሮች አድርጎ ሲያቀርብም አጋጥሞናል፡፡ ነገሩ ግን በነዚህ ምክንያቶች ብቻ የማይወሰን ነው፡፡
ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ለመልቀቅ ቢፈልግ እንኳን የሚከተሉት ጉዳዮች ይፈታተኑታል፡፡
- የኢኮኖሚ ኢምፓየሩን ጉዳይ ለማን
ይተው?
ይህንን ጉዳይ ኢሕአዴግ ራሱ እንደሚያምንበት በማተት ነው የምንጀምረው፡፡ ፓርቲው አምና የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመከረበት ዶሴው ላይ ‹‹የፖለቲካ ኢኮኖሚ ኪራይ ሰብሳቢነት›› በሚል የሰየመው የፖለቲካ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ በከፍተኛ ሙስና በተርመጠመጠ አሠራር የትላልቅ ንብረት እና ንግድ አስተዳዳሪ የሆኑ አባሎቹን ድርጊት ነው፡፡
የኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምንጩ ያልታወቀ ከፍተኛ ሀብት ባለቤቶች ናቸው፡፡ ሀብታቸውን አፍርተው ከጨረሱ በኋላ እንኳን የመጣው የሀብት ማስመዝገብ አዋጅ ተግባር ስኬታማ ሆኖ እንደተነገረን በሁለት ወራት ውስጥ የባለሥልጣናቱ ሀብት ለሕዝብ ይፋ ያልሆነው ይህንኑ ምስጢር ለመደበቅ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ስለዚህ ይህንን የአባላቱን የኢኮኖሚ ኢምፓየር ወይም በውስጥ ቋንቋቸው ‹‹የፖለቲካ ኢኮኖሚ ኪራይ ሰብሳቢነት›› ጣጣ ላለመጋፈጥ ሲባል ተፅዕኖ ፈጣሪ አባላቱ ፓርቲው ሥልጣን ሲለቅ ዝም ብለው አያዩትም (በቀላሉ እንዲለቅ ላይፈቅዱለት ይችላሉ)፡፡ - ቦታውን የማይመጥኑ ሹመኞች ዕጣ
ፈንታ
ኢሕአዴግ ሹመት ለመስጠት የፖለቲካ ታማኝነትን እንጂ አካዳሚያዊ ብቃትን እንደማያስቀድም ደጋግሞ መናገሩ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እነዚህ ከወረዳ ሊቀመንበርነት እስከ ሚኒስትርነት ማዕረግ የተሰጣቸው ቦታውን የማይመጥኑ የፖለቲካ ታማኞች፣ የማይመጥናቸውን ማዕረግና ክብር ለማስቀጠል ኢሕአዴግን በሥልጣን ማስቀጠሉ የማይደራደሩለት ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የማዕረጋቸውና ጥቅማ ጥቅሞቻቸው ቀጣይነት ዋስትና የሚኖረው በፓርቲው የገዢነት ቀጣይነት ላይ ነው፡፡ ይህም የኢሕአዴግ ፖሊሲ ፓርቲው በምርጫ ከተሸነፈ እንዲወርድ በወረቀት ላይ ቢፈቅድም እንኳን እያንዳንዱ ሹመኛ አቅሙ በሚፈቅደውና መቆጣጠር ወይም መምራት በሚችለው ልክ ኢሕአዴግ በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፡፡ - በሥልጣን ሽፋን የተሠሩ ወንጀሎች
ዕዳ
ይሄንኛው ከሁለቱ ምክንያቶች ጋር በተዘዋዋሪም ቢሆን ይገናኛል፤ ወንጀሎቹ ለሹመት እና ለኤኮኖሚ ሳይሆን እንዲሁ በትምክህተኝነት የተሠሩ እና ምናልባትም ደግሞ ሹመቱን እና ኢኮኖሚውን ለማምጣት የተሠሩም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኢሕአዴግ ለዴሞክራሲ ዋጋ ሰጥቶ፣ ፍትሐዊ ምርጫ አካሔዶ እና ተሸንፎ ከአመራሩ ቢወርድ በሥልጣን ሽፋን የተፈፀሙ በርካታ ወንጀሎች ይወጡና አመራሮቹ እና አስፈፃሚዎቹ እንደአስፈላጊነቱ ለፍርድ መቅረባቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የፓርቲ ኃይላቸውን ተጠቅመው የመንግሥት ንብረት ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ፣ ጉዳዮች አግባብ ባልሆነ አካሔድ እንዲቀላጠፉላቸው ያደረጉ ሁሉ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ይህ ኢሕአዴግን ገና ከሩቁ የሚያስፈራው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ከሥልጣን ከመውረዱ በፊት አስቦበት ተንጠልጥሎ አይቀርም አይባልም፡፡
እንግዲህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሦስቱም ምክንያቶች ኢሕአዴግ የሰዎች ስብስብ እንደመሆኑ ሰዎቹ የሠሯቸው ሀጢያቶች ሰለባ
መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሀጢያታቸው ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ስለሚፈሩ ወይም ስለማይፈቅዱ ፓርቲው በወረቀት ላይ ካሰፈረው
ዴሞክራሲያዊነት በተፃራሪ በማንኛውም መንገድ ከሥልጣን እንዳይወርድ ይሠራሉ፤ በዚህም መግባባት አያቅታቸውም፡፡ እንዲያውም በእኔ
አመለካከት የኢሕአዴግ ውስጣዊ ጥንካሬ ይህንን ገመና ለመጠበቅ ሲባል የመጣ የግል ጥቅምን በፓርቲ ከለላ የማዳን ጥንካሬ ነው ብዬ
እላለሁ፡፡ ኢሕአዴግ አባላቱ በነዚህ ሦስት ፈተናዎች አጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ ትክክኛ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ያካሂዳል ብሎ ማለት
እንደማይቻል ከተስማማን ችግሩን እንዴት ሊቀርፈው ይችላል በሚለው ላይ እንነጋገር፡፡
- ኢሕአዴግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ /በተለይም ‹‹አዲሱ አመራር››/ ሙስና ላይ ቁርጠኛ ዘመቻ በመጀመር ባያስመሰክርም ለመሆን እየማለ ነው፡፡ ይህ እርምጃው ምናልባትም የላይኛዎቹን ወንበሮች ሁሉ ባዶ ሊያደርግበት ስለሚችል ቆርጦ የሚቆርጥ ግን አይመስልም፣ በዚህ ካልቆረጠ ታዲያ ማድረግ የሚችለው ትልቁ ነገር አዲስ የሚመጡት ላይ ቁጥጥሩን ማጥበቅ ነው፤ ነባሮቹም አዲስ ሙስና ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ - ዞሮ ዞሮ የእስካሁኑም ቢሆን ከተጠያቂነት ስለማያድነው የማረሳሻ ጊዜ ይፈልጋል፡፡
- ኢሕአዴግ በቢፒአር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶቹን አሠራር ለማሻሻል ሲሞክር የሥራ ቦታዎችም በሚመጥኗቸው ሰዎች እንዲሞሉ የሚል እንቅስቃሴ አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም አሠራሩ ራሱ ለሙስና የተጋለጠና የፓርቲ ሰዎች አላግባብ የተሾሙበት እንደነበርና ችግሩን በሌላ ችግር እንደተካው ፓርቲው ራሱ የኋላ ኋላ በገደምዳሜም ቢሆን አምኗል፡፡ ስለዚህ የከሸፈውን እንደከሸፈ በመተው ፓርቲው የቀረፀውን ፖሊሲ ማስፈፀም የሚችሉ፣ ነገር ግን የግዴታ የፓርቲው አባል ያልሆኑና የተማሩ /ወይም ባጭሩ ቦታዎቹን የሚመጥኑ/ ሰዎች እየቀጠረ ቀስ በቀስ ክፍት ቦታዎችን በባለሙያ መሙላት እና ለሥራ አጥ የፓርቲ አባሎቹ የራሱን ሌላ ተጠያቂነት ውስጥ የማያስገባው የሥራ ፈጠራ ዕድል ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡
- የኢሕአዴግ አባላት በተለያዩ የሥልጣን ሽፋኖች በገቡባቸው ወንጀሎች እጃቸው ተርመጥምጦ እስከዘላለም መዝለቅ እንደማይችሉ የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ስለዚህ ለፓርቲያቸው ቀጣይ ሕልውና የሚያስቡ ከሆነ አመራሮቹ ከአሁኑ ስህተት የሠሩ አባላቶቻቸውን በለመዱት ግምገማ ከመማር ይልቅ ወደፍትሕ በማቅረብ ሌሎቹንም ማስተማር ፓርቲውንም ማንፃትም ከፓርቲው የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ያለእነዚህ እርምጃዎች በድብብቆሽ እስከመጨረሻው መዝለቅ ከባድ ስለሚሆን ፓርቲው ቁርጠኝነት ላይ መድረስ አለበት፡፡
እንግዴህ እነዚህን ምክሮች /መፍትሔ ቢጤዎች/ ፓርቲው ልተግብራቸው ብሎ ቢነሳ እንኳን /በነገራችን ላይ ይነሳል የሚል
ፍንጭ እስካሁን አላሳየም/፣ በተግባር እርምጃ እራሱን ለማንፃት ከፍተኛ ጊዜ እንደሚፈጅበት መገመት ቀላል ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን
ከፍተኛ ጊዜ ለማግኘት ሲባል ደግሞ ሌሎች ወደስልጣን ኃላፊነት እንዳይመጡ
የሚተገብራቸውን መንገድ የማደናቀፍ እና የማሳት ተግባራት ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የቀድሞ ችግሮቹን መልሶ እየደገመ
ወደማይወጣው ‹‹የስህተት እና የማረሚያ ጊዜ ፍለጋ ዑደት››
ውስጥ ሊያስገባው ይችላል፡፡ ማለትም ‹‹ለችግሮቹ ማስተካከያ ጊዜ ይፈልጋል፤ ያንን ጊዜ ለማግኘት ሚዲያ ያፍናል፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን
ያጠብባል፣ የምርጫ ድራማ ይሠራል፤ በዚህም ተጠያቂ ስለሚሆን ይህንን የሚያካክስ ጊዜ ይፈልጋል - ጊዜ ለማግኘት ደግሞ ቀድሞ የሚያደርገውን
ማድረግ አለበት… ይሳሳታል፣ የማረሚያ ጊዜ ይፈልጋል፣ የማረሚያ ጊዜ ለማግኘት ይሳሳታል፣ የማረሚያ ጊዜ ይፈልጋል፣…›› እያለ ይቀጥላል፡፡
ታዲያ ይህ ዑደት ኢሕአዴግ እንዴት በሠላም ሥልጣን ይለቃል የሚል ጥያቄን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡
ይህንን ዑደት ኢሕአዴግ እንዲሰብር ከተፈለገ ከራሱም ከሌሎችም ኢሕአዴግን ከሚተቹ ቡድኖች አንድ እርምጃ አንዱ ወደሌላኛው
መራመድ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢሕአዴግ ለአገሪቷ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሲባል በፍትሐዊ ምርጫ የሥልጣን ሽግግር እንዲካሔድ በበላይ አመራሮቹ
በኩል ቢወስንና በአስፈፃሚዎቹ ላይ ስለአተገባበሩ ጫና ቢያደርግ፤ ተቃዋሚዎችም ኢሕአዴግ ከረፈደም ቢሆን ይህንን እርምጃ በመውሰዱ
ብቻ ያገራችንን ‹‹የድሮውን የመቅጣት ዑደት›› አባዜ ላለመድገም
ሲባል በይቅርታ ቢያልፉትና ለመጪው መንግሥት ጠንካራ ሥርዓት መገንባቱ ላይ ቢያተኩሩ - ለዚህም ቅድሚያ ቃል የሚገቡበትን መንገድ
ቢያመቻቹ ችግሩ በቀላሉ ሊፈታ ይችል ይሆናል፡፡ ኢሕአዴግም በምርጫ ወርዶ ተቃዋሚ የመሆን ታሪክ ሲሠራ እናየው ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያም
ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር በታሪኳ ማየት ትችል ይሆናል፡፡
(ይቀጥላል)
----
ማስታወሻ፡-
- ይህ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል ዐቢይ ርዕስ በተከታታይ የሚቀርቡ ጽሑፎች አካል ነው፡፡
No comments:
Post a Comment