Sunday, July 15, 2012

ነፃ ሐሳብ የማያውቁት ኤፍኤሞቻችን


ኤፍሬም ማሞ

1984 ዓ.ም በአገራችን የመገናኛ ብዙሃን ጨዋታ የተለወጠበት ነው፡፡ የደርግ መውደቀትን ተከትሎ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በፕሬስ ህጉ እውን ሆነ፡፡ የግል ጋዜጦችም እንደ አሸን ፈሉ፡፡ የፕሬስ ህጉ በታወጀበት የመጀመሪያ አምስት አመታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የህትመት ውጤቶች ዕውን እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ሰዐት ያሉትን መሰል የህትመት ውጤቶች መቁጠር እጅግ ቀላል ስራ መሆን አለበት፡፡

የ 1987ቱ ህገ መንግሰት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን ቢደነግግም የማሰራጫ መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ግን በፈቃጁ አካል እሽታን ለማግኘት እሰከ 1991 ዓ.ም መጠበቅ ነበረብን-የብሮድካስት ህጉ እስከሚወጣ ድረስ፡፡ ይህም ሆኖ የግል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ነገር የውሃ ሽታ እንደሆነ ስምንት አመታት አለፉ፡፡ በ 1999 ዓ.ም ከአመታት ጥበቃ በኋላ 15 አመልካቾች ለነበሩበት ዘርፍ ለሁለቱ የግል ባለቤቶች የአየሩ ሞገድ ተፈቀደላቸው-ቁጥራቸው አፍሮ ኤፍ ኤምን ጨምሮ ከሶስት ከፍ ለማለት ግን አልቻለም፡፡ የቴሌቪዥኑ ነገር አሁንም እየታሰበበት ነው፡፡ 

የአፍሪካን መገናኛ ብዙሃን በጥልቀት በማጥናት ታዋቂ የነበሩት ዛምቢያዊው ፍራንሲስ ካሶማ የሬዲዮ እጅግ አስፈላጊነት ጎልቶ የሚወጣው በቀውስ ወቀት እንደሆነ  ይገልጻሉ፡፡ በርካታ የመፈንቀለ መንግስት ሙከራን ባሰተናገደችው አፍሪካ የሬዲዮ ጣቢያዎች የጦር አውድማ እንደሚሆኑና ጣቢያውን ያልተቆጣጠረ ቡድን ጥረቱ ሁለ ከንቱ እንደቀረ ጽፈዋል፡፡

የግል የህትመት ውጤቶች ገና ከመጀመሪያው በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ማጥላላት ስራዬ ብለው ያዙ የሚለው ሐሌሉያ ሉሌ በ1999 የጻፉት የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጽኁፍ ነው፡፡ ጸሃፊው ከነጻ ፕሬስ አዋጅ መውጣት በኋላ የወጡ በርካታ የህትመት ውጤቶች በከፍተኛ ደረጃ የብቃት ማነስና የጋዜጠኝነት ሙያ ስነምግባር እጥረት የነበረባቸው፤ እንዲሁም የተፈቀደውን ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ካለልክ መጠቀም ያበዙ ነበሩ ይላሉ፡፡ አክለውም እነዚህ አሳታሚዎች ገለልተኛ ሆነው አለመገኘታቸውና አለማቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸውን የጋዜጠኝነት መርሆች ለመከተል አለመፈለጋቸውን እንደ ዋና ችግር ይጠቅሳሉ፡፡

መንግስት ሬዲዮና ቴሌቪዥንን ለግል ባለቤቶች ለመፍቀድ ማመንታቱ እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን ያላቸውን ጠቀሜታ ጠንቅቆ በመረዳቱ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ በግሉ የህትመት ዘርፍ ከታየው ልምድ በመነሳት በሬዲዮ/ቴሌቪዥን ፈቃድ ዙሪያ ቆጠብ ማለቱ ተመርጦም ይሆናል፡፡ ማንበብና መጻፍ የሚችለው የሃገራችን ህዝብ ብዛት ከግማሽ በታች ይገመታል፡፡ ይህ እውነታ ሬዲዮ በብዙሃን ተደራሽነቱ ልቆ እንደሚገኝ ያሳየናል፡፡

በመርህ ደረጃ የህዝብ የሆኑት በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃን በገዠው ፓርቲ ላይ ያተኮሩ ትችት አዘል ዝግጅቶችን አቀረቡ የሚባልበት ወቅት አለ ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም፡፡ ቢኖር እንኳን በአንዳንድ መንግሰታዊ መስሪያ ቤቶችና ሃላፊዎቻቸው ድክመት ላይ አተኩሮ አለፍ ሲልም የአፈጻጸም ችግር በሚል ማሰሪያ ተድበስብሰው የሚያልፉ መሆናቸውን አስተውለናል፡፡ በአጠቃላይ ትችትን እንደመርዶ የመቁጠር አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡

መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ምክንያት ይሁን ወይም በስንት ጥበቃ የተገኘውን የሬዲዮ ባለቤትነት መብት ላለማጣት በሚደረግ ጥረት በመንግስት/ገዥው ፓርቲ አንጻር የሚሰሙ ትችት አዘል ድምጾች በግል ሬዲዮ ጣቢያዎች መስማት የመስቀል ወፍ ዝማሬን ያህል የሚናፍቅ ነው፡፡  የኤፍ ኤም ሬዲዮ ዝግጅቶች በመዝናኛና ስፖርታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተጨናንቀው የምናስተውለው ሊነኩ የማይፈለጉ እውነታዎች በመኖራቸው ይመስላል፡፡ የመንግስት ጠንካራ እጆች በጀርመኑ ዶቼ ቬለ እና የአሜሪካ ደምጽ የአማርኛ አገልግሎት ላይ የወሰዱት የሽበባ እርምጃ እንደ ማንቂያ ደወል ሳይወሰድ ይቀራል?

ኤፍ ኤም ጣቢያዎቻችን ጎመን በጤና፣ፖለቲካን በሩቁ ብለዋል፡፡ በመዳሰስ ላይ ያሉ ወቅታዊ ማህበራዊ ጉዳዮችም በስጋት የታጀቡና የሆነ አካልን ላለማስቀየም ትጋት የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ታዲያ የግል የህትመት ውጤቶች ይዘውት የሚወጡትን ያህል የገዥውን ፓርቲ አሰራር የሚተቹ ድምጾች ሬዲዮኖቹ ይዘው ባይወጡ እንኳን መንግስትንም ሆነ ተቃዋሚውን የሚመለከቱ ዝግጅቶችን በነጻነት ማንሸራሸር ነበር ከነሱ የሚጠበቀው፡፡

ይህን ልበል አንጅ ትችት በሬዲዮ ሞገድ ላይ ጭራሽ እየተስተዋለ አይደለም ማለት ግን አይደለም፡፡ ትችቱ ያነጣጠረው መንግስት ላይ አለመሆኑን ግን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በዛሚ ፐብሊክ ኮኔክሽን ባለቤትነት የተመዘገበው ዛሚ 90.7 በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ይገዳደራሉ ባላቸው ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ላይ አተኩሮ የሚያቀርበው ዝግጅት አለው፡፡ አፍቃሪ-መንግስት ነው ተብሎ የሚታማው ይኸው ጣቢያ የሚያስተላለፈው የጋዜጠኞች ክብ ጠረቤዛ እሁድ ረፋዱ ላይ በዋናነት በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በጎ ጎን በማጉላት ስራ ላይ የተጠመደ ነው የሚመስለው፡፡ የዚህ አይነቱ ዝግጅት በዓየር ላይ መዋል መንግስትን ግድ የሚለው አይመስለኝም የግል ህትመት ውጤቶቹ እንደሚያትሙት አይነት ይዘት የለውምና፡፡ 

የጋዜጠኞች ክብ ጠረቤዛ አዘጋጆች መድረኩ ለሁሉም ክፍት እንደሆነ ቢገልጹም በአንድ ወቅት አሁን በስደት ላይ የሚገኘውን የቀድሞው አውራምባ ታይምስ ጋዜጠኛ ዳዊት በአለም አቀፍ መድረክ መሸለምን በኮነነ ዝግጅት ላይ ሸላሚዎቹን ብሎም ጋዜጠኛውን ከፍ ዝቅ አድገው ያቀረቡበትን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛው አዘጋጆች ጋዜጠኛው ወይም ሌሎች የተለየ አቋም ያላቸው መድረኩን ተጠቅመው ተፎካካሪ አስተያየት ማቅረብ እንደሚችሉ መጋበዛቸው “እንዳያማህ ጥራው…” የሚለወን አገርኛ አባባል የሚያስታውስ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አሰራር ከጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር የወጣ ድርጊት በሬዲዮ ላይ ለመታየቱ ማሳያ ነውና አዘጋጆቹ ራሳቸውን እንዲመለከቱ የሚጋብዝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

በዝግጅቱ የቀረቡ መሰል ውይይቶችን እንደማስረጃ ማቅረብ ቢቻልም ከቅርብ ጊዜዎቹ አንዱ ጋዜጠኛ አበበ ገላው በቡድን ስምንት ስብሰባ ላይ ጠ/ሚንስትር መለስን የተጋፈጠበትን ሁኔታ የተኮነነበት ዝግጅት ሌላው ነው፡፡ መድረኩ አንዳንዴ ሃሳብ በነጻ የሚንሸራሸርበት ይምሰል እንጅ፤ በዋናነት የአንድ ወገን ደምጽ የሚሰማበት መስሎ ይሰማኛል፡፡ ያ ወገን ደግሞ የማንንም እርዳታ የማይሻና በህትመትና ማሰራጫ ዘዴዎች ተደራሽነቱ የሰፋ በመሆኑ እንደ የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ ያሉ ዝግጅቶች ቢቻል ድምጻቸው እንብዛም ለማይሰማው ወገኖች መሆን ይገባው ነበር፡፡   

መንግስት ተቃወሙኝ በሚላቸው የህትመት ውጤቶች ላይ ጊዜ ጠብቆ እጁን ጠበቅ እንደሚያደርግ ከገበያ የወጡ በርካታ ጋዜጦች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ በሬዲዮ ተዋናዮች ላይ የሚፈጥረው የስነ ልቦና ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡ ቢልልንና በርካታ ሃሳብ በነጻ የሚንሸራሸርባቸው የሬዲዮ ጣቢያወች ቢኖሩን መልካም ነበር፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ገዥው ፓርቲ ትዕግስቱን ቢሰጠውና አሁን በስራ ላይ ያሉት የግል ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ይኸው መብት ያለገደብ የሚንጸባረቅባቸው እንዲሆኑ ቢፈቅድ የነቃ ትውልድን በመፍጠር ለሃገር እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይቆጠራል፡፡

No comments:

Post a Comment