Thursday, July 26, 2012

ባልቻን ፍለጋ

የመድፍ አረር አካባቢውን አጥኖታል፣ ጎራዴ ይብለጨለጫል፣ የደም ወንዝ ይጎርፋል፡፡ አዎ ይህ ጥቁር ጦር ቀላል  እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ ያ የበጋ ሰማይ ደምን አየ መሰለኝ ክፉኛ ቀልቷል፡፡ በቀላ ሰማይ ስር ጦርን እንደ ብዕር ደምን እንደ ቀለም አድርገው ጀግኖች ታሪክ ይፅፋሉ፡፡ ታሪክን በመክተቡ መሀል ለጥቁሮቹ ጀግኖች አንድ አስደንጋጭ ነገር አጋጠማቸው፡፡ ከመሪዎቻቸው ንዱ የሆኑት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ገደማ  ፊትአውራሪ ገበየሁ ተሰው፡፡ ወላድ በድባብ ትሂድ ገበየሁን ያጣ ጦር አልተበተነም ባልቻን የሚያክል መሪ አግኝቷልና፡፡ ደጃዝማች ባልቻም መድፉን እንደ ቀላል ያገላብጠው ጀመር፡፡ ይሄን የታዘበ አዝማሪም፡

 <<ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፣
መድፍ አገላባጭ፣ ብቻ ለብቻ፡፡>>
ብሎ ተቀ፡፡ ምስጋና ለባልቻ፣ ምስጋና ለገበየሁ ያ ጥቁር ጦር ጠላቱን ድል ነሳ፣ አዲስ ታሪክም ፃፈ፡፡ የካቲት 23/1888 ዓ.ም አድዋ ኢትዮጵያ፡፡

ዛሬ ገበየሁ
አዎ እነ ገበየሁ እነ ባልቻ ታሪክ ከጻፉ ድፍን አንድ ምእተ ዓመት ሊሞላቸው 5 ዓመታት ብቻ ነው የቀረው ወቅቱም 1983 ዓ.ም ውልደቱ በታሪካዊዋ አድዋ የሆነ፣ ራሰ በሀ፣ ቀጭን-አጭር መሪ ነገሰ ኢትዮጵያን ሊያስተዳድር፡፡ የቀድሞው ፕሬዘደንት ያሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፡፡ መለስ እንደ ገበየሁ ከፊት ሆነው ህዝቡን ወደ ድል  ወይስ ወደ ገደል መሩት? ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ መልሶች ናቸው የሚሰጡት፡፡
ባንድ ወገን ‹‹ነፃነትን ያለገደብ ሰጠ፣  ድንቅ እና ውብ ህገ-መንግስት ለህዝቡ አስረከበ፣ ሀገሪቱን በልማት ጎዳና ትጓዝ ዘንድ አረር በማይሸትበት፣ጎራዴ በማይብለጨለችበት የልማት መንገድ መርተዋታል፣ ማን እንደ እርሳቸው? ማን እንደ መለስ?›› በማለት ‹‹ወዲ ወሊደሙ መለስ በልዩ›› (ልጅ ወልደሽ ስሙን መለስ በይው)  እያለ መለስ ለህዝቡ ከመሪም በላይ ናቸውን ሲሰበክ፣ ‹‹ይቀጥል ሊቁ ሰው ጥበብ የተካነው›› እያለ ንጉስ ሆይ ሽህ ዓመት ይንገሱ፣ ዙፋንዎት ይፅና፣ አመራርዎት ይቅና  ይዘምራል፡፡

በሌላ ወገን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በማይወዳት መሪ እየተመራች ነው፣ ‘ባንዲራን ጨርቅ’ ያለ የቅርስን ዋጋ ያሳነሰ፣ ‘ኮሮጆ የሚያስገለብጥ’፣ ህግ ደንታ የማይሰጠው ህግ ሰሪ ህግ አፈራሽ በአጠቃላይ ምሉዕ በኩሉሄ የሆነ መሪ ከቶ ለምኔ? እርሱ ወረደ እለት ስለቴን አስገባለሁ፣ እሱ የሞተ እለት ፈጣሪ የህዝቡን እንባ አይቷል ማለት ነው እያለ ይተቻል፡፡

አዎ ! ዛሬ ‘ገበየሁ’ ፈተናቸው ብዙ ነው፡፡ አዎ ! ዛሬ ‘ገበየሁ’ ‘ጠላትን’ ለመዋጋት ጦር ሜዳ መሄድ አላስፈለጋቸውም ያሉበት ቦታ ድረስ ይሰማቸዋል የመድፍ ጩኸት፣አይናቸው ላይ ያብረቀርቃል የጎራዴው ስለት፣ በዓይነ ህሊናቸው ይታያቸዋል ደም የቀደደው ቦይ ፡፡ በርግጥ ‘ገበየሁ’ ዛሬ ግለሰብ ብቻ ሳይሆኑ ስርዓትም ናቸው ቢባል አያሰገርምም፡፡ በርግጥም መድፉን ብቻቸውን አገላብጠውታል፡፡ 

የሆነ ሆኖ በአሁኑ ወቅትም ‘ገበየሁ’ የት እንዳሉ በትክክል ማወቅ አልተቻለም፡፡ ጓዶቻቸው ‹‹ሥራ ጫና ነበረባቸው አሁን እያረፉ ነው›› ሲሉ ህዝቡ ‹‹ድሮስ ብቻቸውን ህዝብን የሚያክል ነገር እያገላበጡ ምነው አይደክሙ?›› ይላል፡፡ እንዲሁም የ አለፉ ዘመናትን ሲያስታውስ፡
ደከመኝ ሰለቸኝ፣ እረፍት የማያውቀው፣
አብዮታዊ መሪ፣ ጓድ መንግስቱ ነው፡፡
ተብሎ  ለመንግስቱ-ኮመኒስቱ የተዘመረውን መዝሙር ይታወሰዋል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ‹‹አይ ‘ገበየሁ’ ለዘላለሙ አሸልበዋል የስልጣን ሽኩቻውም በበታቾቻቸው መካከል ጡፏል›› የሚል መረጃ ይሰማል፡፡

የትኛው መረጃ እንደሚጨበት ማወቅ አልተቻለም፡፡ ለማንኛውም ጨዋታችን እንዲሞቅ እንዲህ እናስብ፡፡ ከእንግዲህ ‘ገበየሁ’ በህወይት ኖሩም አልኖሩም ወደስልጣን አይመለሱም ስለዚህም የገበየሁን ተኪ ‘ባልቻን’ እንፈልግ፡፡

‘ባልቻን’ ፍለጋ  
‘ገበየሁን’ ይተካ ዘንድ ‘ባልቻን’ እንፈልጋለን፡፡ መጀመሪያ ‘ባልቻ’ ሊኖርባቸው የሚችሉትን ቦታዎች እናስስ እስኪ፡፡

1.      - 'በመስዋዕትነት ከተገኘው ህገ መንግስት'

ከሌሎች ሀገሮች ህገ መንግስቶች በተለየ የኢፌድሪ ህገ-መንግስት ገበየሁ ቢሞት የባልቻ መገኛ የት እንደሆነ በግልፅ አይጠቁምም፡፡ ይልቅስ ህገ መንግስቱ ገበየሁ ‹በማይኖር ጊዜ› በሚል ጥቅል አጠራር ምክትሉ ‘የባልቻን’ ድርሻ ይወርሳል ይላል፡፡ ይህ ህገመንግስታዊ አንቀፅ ለትርጉም ክፍት ነው፡፡ ‘ገበየሁ’ ከስራ ለአጭር ጊዜ ሲርቅ ነው ብቻ ነው ተብሎ ሊተረጎምም ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አይ ‘ገበየሁ’ በሞተም ጊዜ ተክቶ ሊሰራ ይችላል ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ እንግዲህ ‘ባልቻን’ ከህጋዊ መስመር አገኘን የሚሉም ከሁለተኛው ትርጉም የተነሳ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ካለው ድባብ በመነሳት ይህ  የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ይመስላል፡፡ ቢሆን እንኳን እንደ ‘ገበየሁ’ ህዝቡን ብቻውን ማገላበጡ ያጠራጥራል፡፡  

2.     - ‘ጀኔራል ባልቻ’

እነሆ ‘ባልቻን’ ፍለጋ የጦር ካምፕ ውስጥ ነን ‘ባልቻን’ በግልፅ ለማየት ግን አልተቻለም፡፡ በርግጥም ‘ባልቻን’ ከጦር ካምፕ የምናገኝው ከሆነ ግን ጉዳዩ ያስፈራል፡፡ ቢያስፈራም ግን ‘ባልቻ’ በጦር ካምፕ ውስጥ መሽጎ ሊሆን ይችላል፡፡ የተገኝ እለት ‘ጀኔራል ባልቻ’ ሀገሪቱን በአንድ እግሯ አቆሟት መባሉ የማይቀር ነው፡፡

3.     - ‘ባልቻን’ ከቤተ መንግስት
 
ሌላው ጥርጣሬያችን ‘ባልቻን’ እዛው ‘የገበየሁ’ ቤተ-መንግስት ውስጥ ልናገኛቸው እንችላለን የሚለው ነው፡፡ አይሆንም አይባልም፡፡ ሴቱ-ወንዱ የቤተ መንግስት ባለሟል ድንገት ‹‹ባልቻ ነኝ እኮ ስለምን ርቃችሁ ትፈልጉኛላችሁ እዚሁ ቤተመንግስት ነበርኩ እኮ›› ሊል ይችላል፡፡ ‹‹ሹመት በተርታ፣ ስጋ በገበታ››ን እየተረተ ‹‹የሞትንም እኛ ያለንም እኛን›› እያለ ሊያሳውጅ ይችላል ‘ባልቻ’ ከቤተ መንግስት፡፡

4.     - ባልቻን’ ከምድረበዳ

በርግጥም ‘ባልቻን’ ከምድረበዳ ያልነው ‘ከተቃዋሚው’ ጎራ ይመጣ ይሆን የሚለውን ግምታችን ነው፡፡ ዲያስፖራ ተቃዋሚው መግለጫ፣ ኮምኒኬ ወ.ዘ.ተ በማውጣት ዱብ ዱብ እያለ እራሱን እያሟሟቀ ይገኛል፡፡ መቸም ‘ባልቻ’ ‘አትላንቲክን’ ወይም ‘ሚድትራኒያንን’ አለዚያም ‘መረብ’ ወንዝን አቋርጦ ሊመጣ ይችላል ማለት ከባድ ነው! ኧረ በጣም ከባድ ነው፡፡ በሌላ ጎኑ ሀገር ውስጥ ያለውን ተቃዋሚ ስናይ አሁን ባለበት ሁኔታ ጀኔራሎቹ፣ ይሆኑ ወይስ ከቤተ መንግስት እያለ ከመገመት ውጭ ያው በምድረበዳ እየተንከራተተ ነው፡፡ እናም አንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን እንችላለን አዎ ‘ባልቻን’ በድረ በዳ መፈለግ ከንቱ ልፋት ነው፡፡

የሆነ ሆኖ ‘የገበየሁ’ ዘመን እያለቀ ይመስላል፡፡ ‘የባልቻን’ መምጫ ግን ማወቅ አልተቻለም፡፡ ቢመጣስ እንደ ‘ገበየሁ’ ብቻውን ህዝቡን ያገላብጠዋል የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡

1 comment:

  1. ምነው ምነው? "ምሳሌ ዘይበዝኅ" አደረግኸው'ኮ። ምሳሌ ሲያፅፅ እንጂ ሲበዛ አይመችም። እነ ገበየሁ እና ባልቻ አባ ነፍሶ በራሳቸው ወርቅ ኾነው ሰም ይፈለግላቸዋል እንጂ፤ እነርሱ ሰም/ምሳሌ ሊኾኑ ባልተገባ ነበር። ያውም (አርበኞቹ) የባንዶች ምሳሌ? የለም የለም፤ እንዴት ኾኖ!
    (አድናቂህ ባልኾን ባልተቸኹኽ)

    ReplyDelete